በዲያቆን ሄኖክ
ኃይሌ
(ከመጽሐፈ ገጹ የተወሰደ)
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 13 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ማርያምና ማርታ
እኅትማማቾች ናቸው፡፡ ‹ኢየሱስም
ማርታንና እኅትዋን ፣
አልዓዛርንም ይወድ ነበር›
(ዮሐ. 11፡5) ስለዚህም
በቢታንያ በሚገኘው ቤታቸው
እንግዳ ሆኖ ተገኘ፡፡
እጅግ ለሚወዱት ጌታ ፍቅራቸውን
ለመግለጽ እኅትማማቾቹ ይሻላል
ብለው ያሰቡትን ሁለት የተለያየ
ዓይነት አቀባበል አድርገውለት
ነበር፡፡ ማርታ ለምትወደው
እንግዳዋ ምግብ ለማቅረብ
ብዙ ተጨንቃ በጓዳ ሥራ
ላይ ተወጠረች፡፡ ‹ለታላቁ ጌታ
ምን ላቅርብለት ይሆን?› ብላ
ተጠበበች፡፡ መቼም የምናከብረው
ሰው እንግዳ ሆኖ ሲመጣ
ሙያውም ሊጠፋብን ይችላል፡፡
ማርታም የገጠማት ይኼው
ነው ፣ ምኑን ከምኑ አድርጋ እንደምታቀርብ ግራ
ገባት ፤ ጌታችን እንዳለው ‹በብዙ
ነገር ተጨነቀች ታወከች›፡፡
እኅትዋ ማርያም
ግን ሃሳቧን ጥላ ቃሉን
ልትሰማ ከጌታ እግር
ሥር ቁጭ አለች፡፡ ማርያምን በማርታ
ዓይን ሆነን ስናያት እንግዳ ሲመጣ
ሥራ ላለመሥራት ከእንግዳ ጋር
ከሚቀመጡ ሥራ ጠል
እኅቶች አንድዋን ትመስለናለች፡፡
እኅትዋ ከጭስ ጋር
ስትታገል ፣ ምን
ልሥራ ብላ ስትርበተበት እስዋ በቤትዋ
እንደ እንግዳ መቀመጥዋን ስናይ
‹ምን ዓይነቷ ግፍ የማትፈራ
ናት› ብለን መታዘባችን አይቀርም፡፡ ማርታ
ግን ታዝባ ዝም አላለችም፡፡ ‹‹ጌታ ሆይ፥
እኔ እንድሠራ እኅቴ ብቻዬን
ስትተወኝ አይገድህምን? እንኪያስ
እንድታግዘኝ ንገራት አለችው።
ጌታችንም ኢየሱስም መልሶ፦
ማርታ፥ ማርታ፥ በብዙ
ነገር ትጨነቂአለሽ ትታወኪማለሽ፥ የሚያስፈልገው
ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፤ ማርያምም መልካም ዕድልን
መርጣለች ከእርስዋም አይወሰድባትም
አላት።›› ሉቃ. 10፡38-42
በእኛ ግምገማ ማርታ የበለጠ
ለጌታ ፍቅር ያላት ቢመስለንም ጌታችን ግን
የማርታን በፍቅር ለሥራ
መድከም ሳይነቅፍባት የማርያም
ምርጫ ግን ‹የማይቀማ በጎ ዕድል›
መሆኑን ተናገረ፡፡ እንዴት
ሊሆን ይችላል?
በእኅትማማቾቹ ቤት
የተገኘው ሌላ እንግዳ
ቢሆን ኖሮ ማርያም ያደረገችው የሚያስወቅስ
ይሆን ነበር፡፡ በእነርሱ ቤት
የተገኘው ግን የሰማይና
የምድር ፈጣሪ ነው፡፡
እርሱ ደግሞ የሚቀበሉት እንጂ የሚሠጡት
እንግዳ አይደለም፡፡ ቅዱስ
ኤፍሬም ሶርያዊ እንዳለው
‹‹ማርታ ጌታ ራሱ የፈጠረውን ምግብ በገበታ
ልታቀርብለት›› ተጨነቀች፡፡(Martha gave him to
eat: viands which He had created she placed before Him)
የዋኋ ማርታ
ያላወቀችው ነገር እርሱ
ደስ ብሎት የሚበላው ምግብ እርስዋ
የምትሠራው ዓይነት ምግብ
እንዳልሆነ ነው፡፡ እንደ
ሐዋርያቱ ቀርባ ብትጠይቀው
ኖሮ ፡- ‹‹አንቺ የማታውቂው
የምበላው መብል ለእኔ
አለኝ›› ይላት ነበር፡፡
(ዮሐ. 4፡32) ምን
ትጠጣለህ? ብትለው ለሙሴ
እንደነገረው ‹ኃጢአተኛ ሲጸጸት
ዕንባውን እጠጣለሁ› (ኃጥእ
አመ ይኔስሕ ዕንባሁ እሰቲ)
ብሎ ይመልስላት ነበር፡፡ አልጠየቀችውም
እንጂ መራራ ሐሞት እስኪጠጣ ድረስ በሰው
ልጅ ፍቅር ስለተጠማው ጕሮሮው ይነግራት
ነበር፡፡ (‹ሰላም ለጕርዔከ
በጽምአ ፍቅረ ሰብእ
ሐማሚ፡፡ እስከ ስቴ
ሐሞት ጥዕመ ወዘወይነ ትፍስሕት ከራሚ›
እንዲል) የእርሱ ምግብና
መጠጥ የሰው ልጅ ልቡን ሠጥቶ ወደ እርሱ መመለሱ ነው፡፡
ማርያም ግን የማይቀሟትን በጎ ዕድል መረጠች፡፡ ከራሱ ከጌታችን እግር ሥር ቁጭ ብሎ ከመማር በላይ ምን ዕድል አለ? ፈጣሪ ሲናገር መስማትስ እንዴት መታደል ነው? እርሱ የሚናገረው ቃል እኮ መለኮታዊ ቃል ነው! ከጌታ የሚወጣው ቃል የሚሠራና ሕያው የሆነው የራሱ የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ ‹ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል› (ዕብ. 4፡12) እርሱ የሚናገረው ቃል ሙቱን አፈፍ አድርጎ ያስነሣል ፣ ለምጻሙን ያነጻል፡፡
ማርያም ግን የማይቀሟትን በጎ ዕድል መረጠች፡፡ ከራሱ ከጌታችን እግር ሥር ቁጭ ብሎ ከመማር በላይ ምን ዕድል አለ? ፈጣሪ ሲናገር መስማትስ እንዴት መታደል ነው? እርሱ የሚናገረው ቃል እኮ መለኮታዊ ቃል ነው! ከጌታ የሚወጣው ቃል የሚሠራና ሕያው የሆነው የራሱ የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ ‹ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል› (ዕብ. 4፡12) እርሱ የሚናገረው ቃል ሙቱን አፈፍ አድርጎ ያስነሣል ፣ ለምጻሙን ያነጻል፡፡
አስረው እንዲያመጡት
ከአይሁድ የተላኩት የሮም
ወታደሮች እንኳን ከትምህርቱ
ጣዕም የተነሣ ተደንቀው ‹‹እንደዚህ
ሰው ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም››
ብለው ባዶ እጃቸውን ተመልሰዋል፡፡ (ዮሐ.7፡46)
የኤማሁስ መንገደኞችም ‹በመንገድ
ሲናገረን ልባችን ይቃጠል
አልነበረምን?› ብለዋል፡፡(ሉቃ.
24፡32) ይህ የጌታችን
ድንቅ ትምህርት ማርታ ማድቤት
ሆና አመለጣት፡፡ ‹ብዙ ነቢያት
ሊሰሙት ወድደው ያልሰሙትን›
ቃል የመስማት ዕድል ቤቷ
ድረስ መጥቶላት እርስዋ ግን
ሥራ ላይ ነበረች፡፡ እንደ ሙሴ
ወደ ተራራ ሳትወጣ ፣ በደመና
ሳትከበብ ቤቷ ድረስ
እግዚአብሔር መጥቶ ሊያናግራት
ሲል እስዋ ግን ምግብ እየሠራለች ነው፡፡
‹ማርታ ግን
አገልግሎት ስለበዛባት ባከነች›
ይላል፡፡ ይህ ቃል
በእግዚአብሔር ቤት ለምናገለግል
፣ የማርታ ችግር ላለብን
ሰዎች ምንኛ ከባድ ቃል ነው? ለመቅደሱ ቀርበን ከፈጣሪ
ለራቅን ፣ ጠዋት
ማታ በሥራ ፣ በዕቅድ ፣ በስብሰባ
ተወጥረን እንደ ማርታ
ብዙ ድስት ለጣድን ለእኛ ምንኛ
ከባድ ቃል ይሆን? አቡነ ሺኖዳ ‹‹እስከ ዛሬ
የእግዚአብሔርን ቤት አገለገልሁ
፤ የቤቱን ጌታ የማገለግለው
መቼ ይሆን?›› ብለው ነበር፡፡
ቤቱን እያገለገልን የቤቱን ጌታ
ማገልገል ያቃተን ፣
በአገልግሎት ተወጥረን ከጸሎት
፣ ከንስሓ ፣ ከሥጋ
ወደሙና ቃሉን ለራስ
ብሎ ከመስማት ለተለየን ሰዎች
እጅግ ከባድ ቃል ነው፡፡
እያገለገሉ ከፈጣሪ መራቅ
እጅግ ከባድ ነው፡፡ እንደ ማርታ
ፈጣሪ ባለበት ቤት እየኖሩ
ከፈጣሪ መለየትም እጅግ
የከፋ ነው፡፡ ማርያም የምትማርበትን
ክፍል አጽድተን ፣ በኋላም
ገበታውን አቅራቢ ሆነን
የምንወደውን ፈጣሪ ሳንሰማው
መቅረት እንዴት ያሳዝናል?
ለሰብአ ሰገል ወደ
ቤተልሔም ሔደው እንዲሰግዱ
የጠቆሟቸው አይሁድ ነበሩ
፤ እነርሱ ግን ሔደው
አልሰገዱለትም፡፡ ቅዱስ አምብሮስ
እንዳለው ኖኅ መርከብ
ሲሠራ የረዱት የቀን ሠራተኞች
ነበሩ ፤ እነርሱ ግን ከጥፋት
ውኃ አልዳኑም፡፡ ለፍቶ ደክሞ
አገልግሎ ፣ ሌላውን
አስተምሮ ፣ ቤተ
እግዚአብሔርን ሠርቶ መኮነን
እንዴት ያሳዝናል? እንደ
መርፌ የሌላውን ቀዳዳ እየሠፋን
የራሳችንን መስፋት ያቃተን
፣ እንደ መቋሚያ ለሌላው ድጋፍ
እየሆንን ራሳችንን ማቆም
ያቃተን ‹አገልግሎት ስለበዛብን
የባከንን› ብዙዎች ነን፡፡
ማርታ ከቃሉ
በመራቋ ምክንያት አገልግሎትዋን
እንኳን በጸጥታ ማገልገል
አልቻለችም፡፡ ብቻዋን መሥራትዋም
አስቆጫት፡፡ ‹‹ጌታ ሆይ፥
እኔ እንድሠራ እኅቴ ብቻዬን
ስትተወኝ አይገድህምን? እንኪያስ
እንድታግዘኝ ንገራት አለችው።››
ይህ ንግግርዋ ብዙ ጉድለት
እንዳለባት ያሳያል፡፡ እኅትዋ
እስከሆነች ድረስ ቀስ
ብላ ጠርታ ‹ምን ማድረግሽ ነው? ነይና
አግዢኝ እንጂ› ልትላት
ትችል ነበር፡፡ አልዓዛር በሞተ
ጊዜ በለቅሶ ቤት ‹ማርያምን
በስውር ጠርታ፦ መምህሩ
መጥቶአል ይጠራሽማል› ብላ
እንደተናገረችው አሁንም በስውር
ጠርታ ልትወቅሳት ትችል ነበር፡፡
(ዮሐ. 11፡28) እርስዋ
ግን በቀጥታ ለእኅትዋ ከመናገር
ይልቅ እኅትዋን በጌታ ፊት
አሳጣቻት ፣ ከእኅትዋ
ይልቅ እርስዋ ለጌታ የበለጠ
ፍቅር ያላት እንደሆነች የሚያሳይ ንግግር
ተናረች፡፡ ሰው ቃለ
እግዚአብሔር ሲጎድለው ጠበኛ
ይሆናል፡፡ እርሱ እየሠራ
የሌሎች አለመሥራት ያበሳጨዋል
፣ በቀጥታ ሔዶ ለሰው
ችግሩን ከመናገር ይልቅ
በተዘዋዋሪ መናገር ይቀልለዋል፡፡
የዋኋ ማርታ ለአገልግሎት ስትባክን የገጠማት
ፈተናም ይኼው ነው፡፡
እዚህ ላይ
የሚያስደንቀው የማርያም ዝምታ
ነው፡፡ ማርታ ስትከስሳት
ጌታችን መልስ ሠጠላት
እንጂ ማርያም አንድም ቃል
አልተነፈሰችም፡፡ ‹ቃሉን መስማት
ይበልጣል ብዬ ነው!›
ብላም አልተመጻደቀችም፡፡ ዝም አለች፡፡
በእርግጥ እኅትዋ ስትከስሳት
ምን ተሰምቷት ይሆን? በአፍዋ
ዝም ብላ በልብዋ እየተሳደበች ይሆን
እንዴ? አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው ‹የለም
በውስጥዋም ክፉ ሃሳብ
አልነበረም› ይላል፡፡ ‹እንግዲህ
እንደ ማርያም አርምሞና ትዕግሥትን
ገንዘብ እናድርግ› (ናጥሪ
እንከ አርምሞ ወትዕግሥተ ከመ
ማርያም) በማለት በአፍዋ
አርምሞን (ዝምታን) ብቻ
ሳይሆን በልብዋም ትዕግሥትን
ገንዘብ አድርጋ እንደነበር
ይመሰክራል፡፡
ያስደንቃል! እጅግ
በምታከብረው ጌታ ፊት
የገዛ እኅትዋ ስትከስሳት ማርያም
እንዴት አልተበሳጨችም? ቢያንስ
በልቧ እንኳን እንዴት አላጉረመረመችም?
መልሱ ግልጽ ነው፡፡ ማርያም ሌላ
ዓለም ውስጥ ስለነበረች ነው፡፡ ከጌታችን
አንደበት የሚወጣውን አምላካዊ
ቃል ሰምታ ልቧ ተሰውሯል ፤ አካልዋ
በቤት ውስጥ ቢሆንም ኅሊናዋ ወደ
ሰማያት ከፍ ብሏል፡፡
በጌታችን ቃል ልቡ
የተሰበረ ሰው ደግሞ
እንኳን ቢሰድቡት ቢደበድቡትም
አይሰማውም፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ
በድንጋይ መወገሩ ገለባ
የመሰለው ጌታችንን እያየ
ስለነበር ነው፡፡ ቅዱስ
ያሬድ የአፄ ገብረ መስቀል ጦር እግሩ
ላይ ተሰክቶ ምንም ያልታወቀው
በእግዚአብሔር ቃል ልቡ
ስለተመሠጠ ነው፡፡ ማርያምም
ልቧ በቃሉ ስለተመሰጠ በእኅቷ ንግግር
ምንም አልተሰማትም፡፡
★ ★ ★
ከብዙ ወራት
በኋላ ጌታችን ዳግመኛ ወደነማርታ
ሀገር ወደ ቢታንያ ተመልሶ መጣ፡፡
በዚህ ጊዜ ግን እንግዳ ሆኖ የሔደው
ወደነማርታ ቤት ሳይሆን
ወደ ለምጻሙ ስምዖን ቤት
ነበር፡፡ የቢታንያው ስምዖን
ለጌታችን የራት ግብዣ
አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዚህ
ዕለት ታዲያ የቢታንያ ነዋሪዎች እንደመሆናቸው
ማርታ ፣ ማርያምና አልዓዛርም በስምዖን
ቤት ተገኝተው ነበር፡፡
ማርያም ጌታችን
ባስተማራት ትምህርት ልቧ
ተሰብሮ ፣ የምትኖርበትን
የኃጢአት ኑሮ ተጸይፋ
ነበር፡፡ ስለዚህ ዋጋው
እጅግ ውድ የሆነ የአልባስጥሮስ ሽቱ ገዝታ
ወደ ስምዖን ቤት ገሰገሰች፡፡
ከጌታችን እግር ሥር
ተደፍታም በዕንባዋ አጠበችው
፣ በፍጹም ጸጸት ወደ
ፈጣሪዋ ተመለሰች፡፡ የአስቆሮቱ
ይሁዳ ‹ይህ ጥፋት ምንድር ነው?› ብሎ
ለሽቱው ብክነት ተቆጨ
‹ለድሆች ቢሠጥ ይጠቅም
ነበር› የሚል የውሸት ምክንያትም አቀረበ፡፡
ማርያም ፈተናዋ ብዙ
ነው ፤ ቃሉን ስትማር እኅትዋ ተቸቻት
፤ ንስሓ ስትገባ ደግሞ ይሁዳ
ተነሣባት፡፡ ማርታ ቃሉን
ከመስማት ይልቅ ‹ለምግብ
ሥራ ቅድሚያ እንሥጥ› ብላ
እንደነበር ይሁዳም ‹ለነዳያን
አገልግሎት ቅድሚያ ይሠጥ›
አለ፡፡ (ይሁዳ ጌታችን
ሲያስተምር ‹እናትህና ወንድሞችህ
መጥተዋል እያለ ትምህርት
እንዲቋረጥ የሚታገል ሰው
እንደነበር ልብ ይሏል›
ማቴ.12፡46 ትርጓሜ)
ይሁዳ ሲናገር
ማርያም እንደ ልማዷ
ዝም አለች ፤ ጌታችንም እንደ ልማዱ
መልስ ሠጠላት፡፡ እርስዋንም ‹ኃጢአትሽ
ተሰርዮልሻል› ብሎም አሰናበታት፡፡
ማርያም በተማረችው ቃል
የንስሓ ፍሬ አፈራች
፤ የኃጥኡን መመለስ ለሚወደው
ጌታ ዕንባዋ አቀርባ ከማርታ
በላይ አስተናገደችው፡፡ መስተንግዶዋም ከማርታ
ብቻ ሳይሆን ታላቅ ግብዣ
ካደረገለት ከለምጻሙ ስምዖንም
የበለጠ ሆነ፡፡ ጌታችንም
ለለምጻሙ ስምዖን ከእርሱ
መስተንግዶ የእርስዋ መስተንግዶ
ምን ያህል የበለጠ እንደሆነ አነጻጽሮ
ነግሮታል፡፡ (ሉቃ. 7፡44-46)
ከላይ እንደተገለጸው
ማርያም እንዲህ ስትጸጸትና
ኃጢአትዋ ሲሰረይላት ማርታ
በለምጻሙ ስምዖን ቤት
ውስጥ በእንግድነት ተገኝታ ነበር፡፡
ምን እያደረገች ይሆን? የእኅትዋን
መመለስ በመገረም እያየች
ይሆን? ወይስ በቤትዋ ያመለጣትን ትምህርት
ከጌታችን እግር ሥር
ቁጭ ብላ እየሰማች ይሆን? ቅዱስ
ዮሐንስ ወንጌላዊ መልሱን
እንዲህ ሲል ጽፎልናል፡፡
‹‹በዚያም እራት አደረጉለት፤
ማርታም ታገለግል ነበር››
(ዮሐ. 12፡2)
ለማመን ያስቸግር
ይሆናል፡፡ አዎን ማርታ
በሰው ቤትም እንኳን አላረፈችም፡፡ በቤትዋ
እንዳደረገችው በስምኦን ቤትም
በአገልግሎት ላይ ነበረች፡፡
እኅትዋ ስትማር ጓዳ
የነበረችው የዋኋ ማርታ
ምንም እንኳን ጌታችን አገልግሎቷን
ሳይነቅፍ የሚበልጠው ከእግሩ
ሥር መገኘት እንደሆነ የነገራት
ቢሆንምም አሁንም መልካሙን
ዕድል አልመረጠችም፡፡ እኅትዋ ስትማር
ታገለግል እንደነበረች ፣
የእኅትዋ ኃጢአት ሲሰረይም
እስዋ አገልግሎት ላይ ናት፡፡
ማገልገል መልካም ነው
፤ እኛ በአገልግሎት ስንባክን ፣
ሌሎች ወደ እግዚአብሔር ሲቀርቡ ኖረዋል፡፡
ንስሓ ገብተው
ወደ ሥጋ ወደሙ ሲቀርቡም እኛ አገልግሎት
ላይ ከሆንን እንደ ማርታ
ዕድላችንን ያልተጠቀምን ምስኪኖች
ነን፡፡ የሚያሳዝነው ማርታ
አላወቀችም እንጂ የስምዖን
ቤት ግብዣ ከጌታ እግር ስር ለመቀመጥ የመጨረሻ ዕድሏ
ነበር፡፡ ምክንያቱም ጌታችን
ከዚያች ቀን በኋላ
በጥቂት ቀናት ልዩነት
ተሰቅሎ ሞቶአል፡፡ ከዚያም
ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቶ በአርባኛው
ቀን አርጓል፡፡ ማርያም የመጀመሪያ
ዕድሏን ለመማር ፣
የመጨረሻ ዕድሏን ደግሞ
ለንስሓ ተጠቀመችበት፡፡ ማርታ
ግን ‹ታገለግል ነበር›፡፡
ይቆየን!
(ቅድስት ማርታ የኋላ ታሪኳን ስናነብ ሕይወቷን እንደ ወንጌሉ ታሪክ ‹በአገልግሎት ብቻ› ሳይሆን ራስዋን ለጌታዋ በመሥጠት በቅድስና ያሳለፈች መሆኗንና ከሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት አንድዋ መሆኗን መታሰቢያዋም ጥር 18 እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ይህ ጽሐፍ ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ብቻ ያለውን ታሪኳን መነሻ በማድረግ የተጻፈ መሆኑን ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡)
ቃለ ሕይወት ያስምዕከ ዲያቆን ሄኖክ እኁየ። እግዚአብሔር ያብርህ አዕይንተ አልባቢነ ከመ ማርያም እኅተ አልአዛር።
ReplyDeleteቃለ ሕይወት ያሰማልን
ReplyDeleteቃለ ሕይወት ያሰማልን መንግስተ ሰማይንም ያውርስልን
ReplyDeleteቃለ ሕይወት ያሰማልን መንግስተ ሰማይንም ያውርስልን
ReplyDelete