Thursday, March 31, 2016

መጻጉዕ - ለምን እስከ ሠለሳ ስምንት ዓመት ሳይድን ቆየ?



በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 22 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ተወዳጆች ሆይ! እነሆ እግዚአብሔር ፈቃዱ ኾኖ በዚህ ሳምንትም “ወደ ኦሎምፒያስ የተላኩ መልእክታት እና ሌሎች” በተሰኘ አዲስ የሊቁ መጽሐፍ ተገናኝተናል፡፡ እርሱ እስከ ወደደ ድረስም እስከ አሁን በተተረጎሙት ሳንረካ ብዙ ለመተርጎም ወደ ፊት እንሔዳለን፡፡ የሊቁ ሥራዎች ለዚህ ትውልድ ዓይነተኛ መድኃኒቶች ናቸውና፤ እንዲሁ ለማወቅ ያኽል ብቻ ተነብበው በመጻሕፍት መደርደሪያ ላይ የሚቀመጡ ሳይኾኑ መንፈሳዊ ሕይወታችን እንዲጎለምስ ዕለት ዕለት ልናነባቸው የሚገቡ ናቸውና፤ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ላይ እስከ ምን ድረስ ጠንካራ ክርስቲያኖች ልንኾን እንደሚገባን የሚያሳዩ ናቸውና፡፡
ሊቁ፥ በዚህ መጽሐፍ ላይ ሦስት ዋና ዋና ርእሶችን ይዞልን ቀርቧል፡፡ በመጀመሪያው ርእስ ላይ የእግዚአብሔር ከአእምሮ የሚያልፍ አሠራርና ፍቅር፥ ጓደኞቹ የቤቱን ጣራ ነድለው ባወረዱት ሽባ አንጻር እናያለን፡፡ እንዲሁ የበይ ተመልካቾች ግን አንኾንም፤ የድርሻችንን ዘግነን እንወስዳለን እንጂ፡፡ በኹለተኛው ዐቢይ ርእስ “ሰው ራሱን ካልጎዳ በስተቀር ማንም እርሱን ሊጎዳው እንደማይችል” በማለት የሰው ብቸኛና እውነተኛ ጠላቱ እርሱ ራሱ እንደ ኾነ ያስረዳናል፤ ማስረዳት ብቻም ሳይኾን መፍትሔዉንም ያመላክተናል፡፡ በሦስተኛው ዋናው ርእስ ላይ ወደ አምስት የሚኾኑ ንኡሳን አርእስት አሉ፡፡ እጅግ በጣም አስደናቂ ወደኾነችው ወደ ዲያቆናዊት ኦሎምፒያስ የላካቸው መልእክታት ናቸው፡፡ በእነዚህ መልእክታት ውስጥ እጅግ በጣም ብዙ አሳቦች ተነሥተዋል፡፡ በዚህ ዘመን ያሉ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናትና አገልጋዮች ከእነዚህ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ደብዳቤዎች እጅግ በጣም ብዙ ቁም ነገሮችን ያገኛሉ፡፡ ራሳቸውንና አገልግሎታቸውን ይመዝናሉ፡፡ ምእመናንም በአስደናቂዋ ሴት አንጻር ራሳችንን እንመለከታለን፡፡ አሻቅበን ማየት ከተቻለንም ከዲያቆናዊቷ ከኦሎምፒያስ ምን ያኽል ርቀት ላይ እንዳለን እናያለን፡፡ የዘመኑ ባለጸጎችም ከዚህች ባለጸጋ ሴት የድርሻችሁን ትወስዳላችሁ፡፡
አሁን እዚህ የማቀርብላችሁ ትምህርትም በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት ይህ ሳምንት “መጻጉዕ” እንደ መባሉ ሊቁ በዚህ መጽሐፍ ስለ መጻጉዕ ካስተላለፈልን ትምህርት የተቀነጨበ ነው፡፡ መልካም የምክርና የተግሣጽ ጊዜ ይኹንልዎት!

መጻጉዑ በዚህ ደዌ ከተያዘ ሠላሳ ስምንት ዓመት ኾኖታል፡፡ ያለማቋረጥ ያሟል፤ ነገር ግን አማርሮ አያውቅም፡፡ ሕመሙን በጥብዓትና በታላቅ ትዕግሥት ኾኖ ይቋቋም ነበር እንጂ የእግዚአብሔርን ስም አልሰደበም፤ በፈጣሪው ላይ የወቀሳ ቃልን አልተናገረም፡፡ “ይህስ እንደ ምን ይታወቃል? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቀድሞ ሕይወቱ በግልፅ የሚነግረን ነገር የለውም፡፡ የሚነግረን ሠላሳ ስምንት ዓመት ሙሉ ታምሞ እንደ ነበረ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በላይ እንዳላማረረ፣ እንዳልተቈጣ ወይም እንዳልተነጫነጨ ምንም አይነገረንም” የሚል ሰው ቢኖር እኔም፡- “ኃይለ ቃሉን ቸል ሳይልና በአንቃዕድዎ ኾኖ ለሚያስተውል ሰው ይህን ግልፅ አድርጎ ነግሮናል” ብዬ እመልስለታለሁ፡፡ ምክንያቱም ከዚያ በፊት ስለ ጌታችን ምንም የማያውቀው መጻጉዕ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እርሱ ሲመጣና እንደ “ዕሩቅ ብእሲ” ዐይቶት በታላቅ ቅንነት ኾኖ ሲያናግረው ስትሰሙ ጥንቱም እንደ ምን ያለ ጠቢብ ሰው እንደ ነበረ መገንዘብ ትችላላችሁ (ሊባል የተፈለገው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ስላላወቀው እንደ ዕሩቅ ብእሲ አይቶት ይህን ያኽል ቅንነት ካሳየው ሲያውቀው ደግሞ ይበልጥ በቅንነትና በጥበብ ይቀርቧል ነው፡፡) ጌታችን፡- “ልትድን ትወዳለህን?” ሲለው “ይህን ያኽል ዓመት የደዌ ዳኛ የአልጋ ቁራኛ ኾኜ ተኝቼ እያየኸኝ እንዴት ትጠይቀኛለህ? የመጣኸው በቁስሌ ላይ ጥዝጣዜን ለመጨመር፣ የዘለፋ ቃልን ለመናገር፣ በእኔ ላይ ለመሳለቅ፣ እንዲሁም በሕመሜ ለማላገጥ ነውን?” በማለት የተለመደ ዓይነት መልስን አልመለሰለትም፡፡ እንደዚህ ብሎ አልተናገረም፡፡ ሊናገርስ ይቅርና አላሰበውምም፡፡ ከዚህ ይልቅ በቅንነት ኾኖ እንዲህ አለ እንጂ፡- “አዎን ጌታ ሆይ!” እንግዲህ ተመልከቱ! ከሠላሳ ስምንት ዓመት በኋላ እንኳን ይኼን ያኽል ቅንና ጨዋ ከነበረ፣ ውሳጣዊ ብርታቱ ከተሰበረ በኋላ እንኳን እንዲህ ከኾነ፥ ሕመሙ ሲጀምረው ደግሞ ምን ያኽል መንፈሰ ብርቱ ሊኾን እንደሚችል አስቡት፡፡ ምክንያቱም በሽታዎች መጀመሪያ ላይ ሲጀምሩ ይኼን ያኽል አይከብዱም፡፡ ለረጅም ጊዜያት ሳይድኑ ሲቆዩ ግን እጅግ አስጨናቂዎችና የማይቻሉ እንደሚኾኑ እሙን ነው፡፡ ይህ መጻጉዕ ግን ከብዙ ዓመታት በኋላም ቢኾን ጠቢብና ትዕግሥተኛ ነበር፡፡ በመኾኑም ከዚህች ቀን በፊትም ቢኾን ሕመሙን በአኰቴት ተቀብሎት ይኖር እንደ ነበር ግልፅ ነው፡፡
እንግዲያውስ እኛም እነዚህን ነገሮች በማስተዋል እንደ እኛ የእግዚአብሔር አገልጋይ የኾነውን መጻጉዕ በትዕግሥቱ ልንመስለው ይገባናል፡፡ ምክንያቱም፡- አንደኛ ሽባ መኾኑ በራሱ ነፍሳችንን ለመደገፍ በቂ ነው፤ ኹለተኛ ያን የመሰለ ከባድ በሽታን ከተመለከተ በኋላ ከዓቅም በላይ ናቸው የሚባሉትን እንኳን ሳይቀር በእርሱ ላይ የሚመጡትን ክፉ ክፉ ነገሮችን ከመቋቋም ይልቅ በስንፍና ተይዞ እንዲሁ ተንጋሎ መተኛት የሚችል ሰው የለም፡፡ ጥንካሬውን ብቻ አይደለም፤ ያገኘው በሽታ በራሱ ለእኛ የሚሰጠው እጅግ ታላቅ የኾነ ጠቀሜታ አለው፡፡ ምክንያቱም የመጻጉዕ መዳን እግዚአብሔርን እንድናመሰግን ያነሣሣናል፤ በሽታውና ድካሙም ትዕግሥትን እንድንማርና የእርሱን ዓይነት ጉጉት እንዲኖረን ያደርጋል፤ በሌላ መልኩ ደግሞ የእግዚአብሔር ፍቅሩ እንደ ምን ጥልቅና ምጡቅ እንደ ኾነ ያሳየናል፡፡ መጻጉዑ ከእንደዚህ ዓይነት በሽታ መዳን መቻሉ፣ ከእንደዚህ ዓይነት በሽታ ብቻ ሳይኾን ይህን ያኽል ከረዘመ ጊዜ በኋላ መዳን መቻሉ በራሱ እግዚአብሔር ምን ያኽል ይጠብቀው እንደ ነበር የሚያመለክት ነውና፡፡ ወርቅን የሚያነጥር ሰው አንዲትን የወርቅ ቅንጣት ወደ እሳት ውስጥ ጨምሮ እጅግ ንጹህ እስክትኾን ድረስ ይጠብቃታል፡፡ እግዚአብሔርም ልክ እንደዚሁ ሰዎች እስኪነጹ፣ እስኪለወጡና ባገኛቸው ነገር ጥቅም እስኪያገኙ ድረስ ፈተና ውስጥ እንዲቆዩ ይፈቅዳል፡፡ ይህ ደግሞ ከጥቅምም እጅግ ከፍ ያለ ጥቅም ነው፡፡
ስለዚህ ፈተና ሲገጥመን ውስጣችን ሊረበሽ ወይም ተስፋ ሊቈርጥ አይገባውም፡፡ ያ ወርቅን የሚያነጥር ሰው በእሳት ውስጥ የጨመራትን የወርቅ ቅንጣት እዚያ ውስጥ ምን ያኽል ጊዜ መቆየት እንዳለባት ያውቃል፤ መቼ ከእሳቱ ሊያወጣት እንደሚገባውም ያውቃል፡፡ እንዲሁ እስከ መጨረሻው በእሳቱ ውስጥ ተጥላ እንድትቀርና በዚያ እንድትቃጠል አይፈቅድም፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ይህን ከወርቅ አንጣሪው በላይ ያውቃል፡፡ መቼ ከርኵሰታችን እንደምንነጻ ያውቃል፡፡ በመኾኑም ራሳችንን በመጣልና ተስፋ በመቁረጥ በክፋት ላይ ክፋት እየጨመርን እንዳንሔድ ሽቶ መቼ ከዚያ ፈተና እንደሚያወጣን ያውቃል፡፡ ስለዚህ ድንገት ያላሰብነው ነገር ቢገጥመን በፍጹም የምናማርር፣ ወይም ተስፋ የምንቈርጥ ልንኾን አይገባንም፡፡ ከዚህ ይልቅ የእነዚህ ነገሮች ምንነትን የሚያውቅ እግዚአብሔርን መጠበቅ፣ እርሱ እስከ ፈቀደው ጊዜ ድረስም ልቡናችንን በእሳት እንዲፈተን ማድረግ ይገባናል፡፡ ምክንያቱም ይህ ነገር በእኛ ላይ እንዲኾን የፈቀደው ለእኛ ጥቅምና በዚያ ውስጥ ኾነን በምናሳየው ጥረት ይበልጥ ሊያከብረን ስለሚወድ ነው፡፡
ይህን በማስመልከትም ጠቢቡ ሰው እንደዚህ ሲል መክሮናል፡- “ልጄ ሆይ! ለእግዚአብሔር ትገዛ ዘንድ ብትሔድ ሰውነትህን ለመከራ አዘጋጅ፤ ልብህን አቅና፤ ኹልጊዜ ታገሥ፤ አታወላውልም፤ በመከራ ብትጨነቅም አትጠራጠር” /ሲራ.2፥1-2/፡፡ “ኹሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ስጠው፡፡” ለምን? እግዚአብሔር ከዚያ መከራ መቼ እኛን ማውጣት እንዳለበት ያውቃልና፡፡ ስለዚህ ኹሉንም ለእርሱ ልንሰጥ፣ ዘወትር እርሱን ልናመሰግን፣ ኹሉንም ነገር - ጥቅምም ይኹን ቅጣት - በአኰቴት ልንቀበል ይገባናል፤ ይህም ቢኾን ለእኛ ረብሕ የሚኾን ነውና፡፡ አንድ ሐኪም፥ ሐኪም የሚባለው ታካሚውን ገላዉን ሲያጥበውና ሲመግበው እንዲሁም ደስ ወደሚያሰኝ ስፍራ ሲወስደው ብቻ አይደለም፤ በእርሱ (በታማሚው) ሰውነት ላይ የቀዶ ጥገና ምላጭና ቢላ ሲያሳርፍም ጭምር ሐኪም ነው፡፡ አባትም አባት የሚባለው ልጁን ሲንከባከብ ብቻ አይደለም፤ የገዛ ልጁን ከቤት ሲያስወጣው፣ ሲገሥጸው፣ ሲገርፈውም ያው አባት ነው፡፡ ስለዚህ እኛም እግዚአብሔር ከሐኪሞችም በላይ ሰውን ወዳጅ እንደ ኾነ በማወቅ፥ ምን ዓይነት የሕክምና ዓይነት እንደሚሰጠን በጥልቀት አንጠይቅ፤ ወይም ደግሞ ለደረሰብን መከራ እርሱን ተጠያቂ አናድርግ፡፡ ከዚህ ይልቅ እርሱ የወደደውን ነገር - ቅጣትም ይኹን ቅጣት የሌለው ነገር - ብቻ ምንም ይኹን ምን በአኰቴት ልንቀበል ይገባናል፡፡ በየትኛውም መንገድም ቢኾን የእርሱ ፈቃድ እኛ እንድንድንና ከእርሱ ጋር አንድ እንድንኾን ነውና፡፡ የትኛው መንገድ ለእኛ እንደሚጠቅምም እርሱ ያውቋል፡፡ እያንዳንዱ ሰው የትኛው መንገድ ወደ እርሱ እንደሚመልሰው ያውቃል፡፡ ኹላችንም እንዴትና በምን ዓይነት መንገድ ልንድን እንደምንችል ያውቃል፡፡ በመኾኑም የሚመራን በዚህ እኛ በምንድንበት መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ ወደየትኛውም መንገድ ቢወስደንም - ልክ እንደ መጻጉዑ - እርሱ እንደሚያዘ’ን ተከትለን መሔድ እንጂ ትልቁ ጉዳያችን በለስላሳና በቀላል አልያም ደግሞ በከባድና በሸካራ ጎዳና እንድንሔድ የሚያዘ’ንን ትእዛዝ መኾን የለበትም (ልንሔድበት የሚገባ’ው መንገድ እርሱ ስለሚያውቀው እንዲሁ መታዘዝ እንጂ የመንገዱን ከባድነት ወይም ቀላልነት የእኛ አጀንዳ ሊኾን አይገባውም፡፡) መጻጉዕ ነፍሱ ለዚህን ያኽል ጊዜ - ወደ እቶን እሳት የመጣል ያኽል - በመከራ መቆየቷ ለእርሱ ጥቅም ነበር፡፡ ከዚህ በምንም በማይተናነስ መንገድ ግን እግዚአብሔር በመከራው ኹሉ አብሮት ነበር፤ ታላቅ የኾነ መጽናናትንም ሲሰጠው ኖሯል፡፡ መጻጉዕን እንዲህ ያበረታው፣ የጠበቀው፣ የቸርነት እጁን የዘረጋለት፣ በክፉ አወዳደቅም እንዳይወድቅ ያደረገው እርሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ እንዲህ ያደረገው እግዚአብሔር ነው ሲባል ግን መጻጉዑ አመስጋኝቱንና ጽናቱን መርሳት የለባችሁም፡፡ ምንም ያኽል እኛ ጠቢባን ብንኾን፣ ምንም እንኳን ከሰው ኹሉ ልቀን ብርቱዎች ብንኾንም የእግዚአብሔር ቸርነት ካልረዳን በቀር እጅግ ጥቂቷን ፈተናም ብትኾን መቋቋም አንችልም፡፡ ምንም ስለማንጠቅምና ወራዶች ስለምንኾን ስለ እኛ እንዲህ ብዬ የምናገረውስ ለምንድን ነው? ምክንያቱም ጳውሎስም ቢኾን፣ ጴጥሮስም ቢኾን፣ ያዕቆብም ቢኾን፣ ዮሐንስም ቢኾን እግዚአብሔር ባይረዳቸው ኖሮ ታላቅ የኾነ ውርደት ባገኛቸው፤ ክፉ የኾነ አወዳደቅም በወደቁ ነበር፡፡ ይህንን በማስመልከትም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቃልን አነብላችኋለሁ፤ ለጴጥሮስ እንዲህ ያለውን፡- “እነሆ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥርህ ለመነ፤ እኔ ግን እምነትህ እንዳይደክም ስለ አንተ ጸለይኹ” /ሉቃ.22፥31-32/፡፡ “ሊያበጥርህ” ሲል ምን ማለት ነው? ሊገለብጥህ፣ ሊጠመዝዝህ፣ ሊያነዋውጽህ፣ ሊያሸብርህ፣ ሊያርድህ፣ ሊያስጨንቅህ፣ በአጠቃላይ እኽል ሲበጠር እንደሚኾነው ዓይነት ማለት ነው፡፡ “እኔ ግን” አለ ጌታ፤ “እኔ ግን መከራዉን መቋቋም አትችልምና፥ ይህን እንዳያደርግብህ ከለከልሁት፡፡” “እምነትህ እንዳይደክም” የሚለው አገላለጽ እግዚአብሔር ሰይጣንን ባይከለክለው ኖሮ የጴጥሮስ እምነት ይደክም ብሎም ይወድቅ እንደ ነበር የሚያስረዳ ነው፡፡ እንግዲህ ተመልከቱ! ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይወደው የነበረው፣ እጅግ በጣም ብዙ ጊዜ ሕይወቱን የሰጠለት፣ የሐዋርያነት ማዕርግ ያለው፣ በራሱ በጌታ ብፁዕ ተብሎ የተጠራው፣ በእምነቱ እንደ ዓለት ፅኑዕ በመኾኑ ኰክሕ የተባለው ጴጥሮስ እንኳን፥ ጌታችን ክርስቶስ ዲያብሎስ እንደሚፈልገው መጠን እንዲፈትነው ቢፈቅድለት ኖሮ በእምነት ደክሞ ይወድቅ ከነበረ፥ ሌላው ሰው’ማ ከእግዚአብሔር እርዳታ ውጪ ኾኖ እንደ ምን መቆም ይቻሏል? በመኾኑም ንዑድ ክቡር የሚኾን ጳውሎስ ስለዚሁ ምክንያት እንዲህ አለ፡- “ነገር ግን በማትችሉት መከራ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፤ መታገሥ እንድትችሉም ከፈተናው ጋር መውጫው ደግሞ ያደርግላችኋል” /1ኛ ቆሮ.10፥13/፡፡ ተመልከቱ! ብፁዕ ጳውሎስ እያለ ያለው ከምንችለው በላይ በኾነ መከራ እንደማንፈተን ብቻ ሳይኾን በምንችለው መከራ ውስጥም ቢኾን እግዚአብሔር አብሮን እንዳለ ነው፡፡ አስቀድመን እኛ የዓቅማችንን ያኽል ብንጥር - ለምሳሌ ለእምነታችን ብንቀና፣ እርሱን እግዚአብሔርን ተስፋ ብናደርግ፣ ብናመሰግን፣ ብንጸናና ብንታገሥ - እኛን ለመርዳት አብሮን አለ፡፡ ከዓቅማችን በላይ በኾኑ መከራዎች ብቻ ሳይኾን፥ በምንችላቸው መከራዎችም ቢኾን ጸንተን ለመቆም ረድኤተ እግዚአብሔር ያስፈልገናል፤ እንዲህ እንደ ተባለ፡- “የክርስቶስ መከራ በእኛ ላይ እንደ በዛ እንዲሁ መጽናናታችንም በክርስቶስ በኩል ይበዛልናል፡፡ ይኸውም በእግዚአብሔር በምንጽናናበት መጽናናት በመከራ ኹሉ ያሉትን ማጽናናት እንድንችል ነው” /2ኛ ቆሮ.1፥5/፡፡ ስለዚህ መጻጉዕን ያጽናናው፥ መከራ ይቀበል ዘንድም የፈቀደው እርሱ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጻጉዑን ከፈወሰው በኋላ እንደ ምን ያለ ቸርነት እንዳሳየውም ተመልከቱ! ምክንያቱም ከዚያ በኋላም ቢኾን አልተለየውም፤ አልተወዉም፡፡ በቤተ መቅደስ ውስጥ ሲያገኘውም እንዲህ ብሎታልና፡- “እነሆ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ” /ዮሐ.5፥14/፡፡ እንደዚያ እንዲታመም የፈቀደው ጠልቶት ቢኾን ኖሮ ባላዳነው ነበር፤ ወደ ፊት ይጠነቀቅ ዘንድም ባልነገረው ነበር፡፡ “ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ” የሚለው አገላለጽ መከራዎች ከመምጣታቸው አስቀድሞ ራሱን እንዲጠብቅ የሚያደርግ ነውና፡፡ በሽታዉን አድኖለታል፤ ተጋድሎዉን ግን አልፈጸመለትም፡፡ ደዌዉን አርቆለታል፤ ፍርሐቱን ግን አላስወገደለትም፡፡ ይኸውም (በመፍራት) ያገኘውን ጥቅም እስከ መጨረሻው አጽንቶ እንዲይዝ ነው፡፡ ይህም የአንድ፥ ሰውን የሚወድ ሐኪም ጠባይ ነው፡፡ ሰውን የሚወድ ሐኪም አሁን ካሉ ሕመሞችን መፈወስ ብቻ ሳይኾን ወደፊትም ታካሚው ድጋሜ እንዳይታመም ማድረግ ያለበትን ጥንቃቄ ይነግሯልና፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ያደረገው እንደዚህ ነው፤ (ለመጻጉዑ) የቀድሞ ኹኔታዎች በማስታወስ ወደ ፊት ሊጠነቀቅ እንደሚገባው እየነገረ ነፍሱን እየደገፈለት ነውና፡፡ ምክንያቱም ከአንድ አስቸጋሪ ኹኔታ ስንላቀቅ ከዚያ በኋላ በዚያን ጊዜ የነበሩ ኹኔታዎችንም እንዘነጋቸዋለን፡፡ ጌታችን ግን መጻጉዑ ይህንን እንዳያደርግ በማሰብ፡- “ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ” አለው፡፡
 ከዚህም በተጨማሪ ጌታችን መጻጉዑን አስቀድሞ የተጠነቀቀለትና ያሰበለት በዚህ ብቻ እንዳልኾነ ማየት ይቻላል፤ ተግሣጽ በሚመስለው ንግግሩም ጭምር ነው እንጂ፡፡ ምክንያቱም ኃጢአቱን በአደባባይ አልገለጠበትም፡፡ ከዚያ ይልቅ አግኝቶት የነበረው ደዌ በኃጢአቱ ምክንያት እንደ ነበረ ለብቻው ነገረው፤ ኃጢአቱ ምን እንደ ነበረ ግን አልተናገረም፡፡ “ኃጢአት ሠርተህ ነበር”፤ ወይም “በድለህ ነበር” አላለውም፤ እንዲሁ “ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ” አለው እንጂ፡፡ ስለ ቀድሞ ኃጢአቱ በማስታወስ ለወደ ፊቱ ሊጠነቀቅ እንደሚገባው አነቃው፡፡ ጎን ለጎንም ትዕግሥቱን፣ ጽናቱንና ጠቢብነቱን ኹሉ ለእኛ ግልፅ አደረገልን፡፡ ምንም እንኳን “እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ሰው ቀድሞኝ ይወርዳል” በማለት ስለ በሽታው እንዲያለቅስ፣ ሰው በማጣትም እንደ ተቸገረ በአደባባይ እንዲናገር ቢያደርገውም፥ ኃጢአቱን ግን በአደባባይ አልገለጠበትም /ዮሐ.5፥7/፡፡ እኛው ራሳችን ኃጢአታችንን መደበቅ እንደምንፈልግ ኹሉ እግዚአብሔር ደግሞ ከእኛ በላይ አበሳችንን ይሸፍንልናል፡፡ በመኾኑም በአደባባይ ፈወሰው፤ ምክሩን ግን ለብቻው ሰጠው፡፡ ድንገት ሰዎች ልቡናቸው ደንድኖ ኃጢአታቸውን አላስተውል ካላሉ በቀር እግዚአብሔር ኃጢአታችንን በፍጹም በአደባባይ አይገልጥብንም፡፡ ጌታችን፡- “ተርቤ ስታዩኝ አላበላችሁኝም፤ ተጠምቼ ስታዩኝ አላጠጣችሁኝም” ብሎ አሁን መናገሩ እነዚህን ቃላት ሊመጣ ባለው ጊዜ (በአደባባይ) እንዳንሰማ ነው፡፡ በዚህ ዓለም ሳለን የሚያስፈራን፣ ወይም የሚገልጠን እንኳን በወዲያኛው ዓለም እንዳይገልጠን ወድዶ ነው፡፡ ይኸውም “ነነዌ ትገለበጣለች” ብሎ የሚያስፈራ ቃል ሲናገር ነነዌ እንዳትገለበጥ ወድዶ እንደተናገረው ማለት ነው /ዮና.1፥2/፡፡ ኃጢአታችንን ሊገልጥብን ፈቃዱ ቢኾን ኖሮ፥ እንደሚገልጣቸው አስቀድሞ ባልነገረን ነበር፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ እንደሚገልጣቸው መናገሩ እንዳይገልጥብን በመፍራት፣ እንዳይገልጥብን ባንፈራ እንኳን ሊመጣ ያለውን ምረረ ገሃነም በመፍራት ከኃጢአታችን ኹሉ ንጹሃን እንድንኾን ወድዶ ነው፡፡ በጥምቀት የሚኾነውም ይኸው ነው፡፡ ተጠማቂው ኃጢአቱን በአደባባይ ለማንም ሳይገልጥበት ወደ መጠመቂያው ውኃ እንዲገባ ያደርጓል፡፡ ሰውዬው በመጠመቁ ያገኘውን በረከት በአደባባይ ይነግርለታል፤ ኃጢአቱ ግን ከእግዚአብሔርና ሥርየተ ኃጢአትን ካገኘው ከተጠማቂው ከራሱ በቀር ማንም አያውቀውም፡፡ በመጻጉዑ ዘንድ የኾነውም ይኸው ነው፡- ተግሣጽን በስውር ሰጠው፤ ተግሣጽ ብቻም ሳይኾን ለዚህን ያኽል ረጅም ጊዜ ለምን እንዲህ እንደታመመም ምክንያቱን አሳወቀው፤ ኃጢአቱ የመታመሙ ምክንያት እንደ ነበረ አስታወሰው፡፡ “ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በቤተ መቅደስ አገኘውና፥ እነሆ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ አለው” እንዲል፡፡
     ቀሪዉን ከመጽሐፉ እንድታነብቡት ጋብዣችኋለሁ!!!


3 comments:

  1. 'ዳግማዊ ዮሃንስ' የቅዱሱ አባት በረከት አይለይህ

    ReplyDelete
  2. Fetari ytebkh ayzoh ketl esk tdekm. xdk bedkam newna yemigegnew

    ReplyDelete
  3. ቃለ ሕይወት ያሰማልን ። እግዚአብሔር በረከቱን ፀጋውን ያብዛልህ.

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount