Pages

Monday, June 11, 2018

ምሥጢራትን የመሳተፍ ሕይወት

በ ገብረ እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሰኔ 04 ቀን 2010 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! 
 
የኦርቶዶክሳዊ ሕይወት ዋና ዓላማውና ግቡ ምእመናን እግዚአብሔርን እንዲመስሉ፣ በቅድስና ላይ ቅድስና፥ በክብር ላይ ክብር፥ በጸጋ ላይ ጸጋ እየጨመሩ እየተመነደጉም እንዲኼዱ ነው፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ፡- “ለክብርህ ከፍተኛነት ፍጻሜ የለውም” እንዲል፥ ቅድስናው፣ ቸርነቱ፣ መልካምነቱ፣ ክብሩ ወሰን ድንበር ስለሌለው እርሱን መምሰልም ወሰን፣ ድንበር፣ ልክ የለውም፡፡ በዚህ ዓለም ብቻ ሳይኾን በወዲያኛውም ዓለም የማይቋረጥ ምንድግና ነው፡፡ ስለዚህ የኦርቶዶክሳዊ ሕይወት ዋና ዓላማና ግብ እግዚአብሔርን መምሰሉ ብቻ ሳይኾን ይህ ራሱ የማይቋረጥ እድገትም ነው፡፡ ከአንዱ ክብር ዓይን ወዳላየችው፣ ጆሮ ወዳልሰማችው፣ የሰውም ልብ ወዳላሰበው ወደ ሌላ ክብር መወለጥ ነው፡፡ 

 
ይህ ጥንቱንም ለሰው ልጆች የተሰጠ ሕይወት ይህ ነው፡፡ አበው ሲናገሩ፡- “አትብላ ያለውን ዕፅ ሳይበላ ትእዛዙን ጠብቆ ቢኾን ኖሮ ከዕፀ ሕይወት በልቶ ታድሶ ኢየሩሳሌም [ሰማያዊት] በገባ ነበር” የሚሉትም ለዚህ ነው (ሊቀ መዘምራን ሞገስ ዕቁባ ጊዮርጊስ፣ አምስቱ አዕማደ ምሥጢር ወምስለ ሥነ ፍጥረት አንድምታ ትርጉም፣ ገጽ 230)፡፡
 
ሊቀ ነቢያት ሙሴ እንደሚነግረን እግዚአብሔር ሰውን፡- “በአርአያውና በአምሳሉ” ፈጥሮታል (ዘፍ.1፡26)፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ እንዲሁ መንፈሳዊ ስጦታ የተሰጠው፣ ፍጥረታትን የሚገዛ የሚነዳ ብቻ ሳይኾን አምላክ ዘበጸጋ እንዲኾንም የተፈጠረ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን “የክብሩ ወራሾች የስሙ ቀዳሾች ለመኾን ያብቃን” የሚለው አነጋገርም ይህን የሚያስረዳና እጅግ ጥልቅ የኾነ መልእክትን በውስጡ የቋጠረ ኃይለ ቃል ነው፡፡ የሰው አፈጣጠር ከቅድስናው ክብር፣ ከቸርነቱ ክብር፣ ከደግነቱ ክብር፣ ከጥበቡ ክብር፣ ከገዢነቱ ክብር፣ ከነጻ ፈቃዱ ክብር በጸጋ ወራሽ ወይም ተካፋይ እየኾኑ ማደግ መኾኑን የሚያስረዳ ነው፡፡ 
 
የሰው ልጅ ቀድሞውኑም እንዲህ እንዲኾን የተፈጠረ ቢኾንም ቅሉ እንዴት ማደግ እንዳለበት ግን መንገዱን ስቶታል፡፡ ምንም እንኳን አትብላ ከተባለው ዕፅ ባይበላ ወደ ቀጣዩ ማዕርግ ለማደጉ ምልክት ትኾነው ከነበረችው ዕፀ ሕይወት በልቶ ይታደስ የነበረ ቢኾንም፥ ይህን ያለ ረድኤተ እግዚአብሔር፣ ያለ እግዚአብሔር ጸጋ አጋዥነት በራሱ ኃይልና ብርታት ሊፈጽመው በማሰቡ ግን ወድቋል (ቅዱስ ሄሬኔዎስ፣ በእንተ መናፍቃን፣ መጽ. 3፣ ምዕ. 23፣ ቁ. 1)፡፡ ትእዛዙን በመጠብቅ በእግዚአብሔር ረድኤት ሳይኾን በምክረ ከይሲ ዕፀ በለስን በመብላት “እንደ እግዚአብሔር” ለመኾን በመመኘቱ ስቷል (ዘፍ.3፡5)፡፡
 
ይህን ጊዜ ለብሶት የነበረው ብርሃን ተለየው፡፡ ዛሬ ጉም ከአንድ ተራራ ወደ ሌላ ተራራ ተነሥቶ ሲኼድ እንደምናየው ተለየው፡፡ አፈረ፡፡ እግዚአብሔርን ወደ መምሰል ማደግስ ይቅርና ጭራሽ ወደ ታች የሚኼድ፣ በበደል ላይ በደል የሚጨምር ኾነ፡፡ ፈጣሪን ትቶ ፍጡርን እስከ ማምለክ ደረሰ፡፡ በጨለማ፣ በድንቁርና ውስጥ ወደቀ፡፡ የሰማዩን፣ መንፈሳዊውን ሕይወት ማየት ተሳነው፡፡ 
 
በልብ መታሰቡ፣ በቃል መነገሩ፣ በመጻሕፍም መዘከሩ ከፍ ከፍ ይበልና፥ አካላዊ ቃል የባሕርያችን መመኪያ ከምትኾን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋም ነፍስ ነሥቶ ሰው ሲኾን ግን አስቀድሞ በበደል ምክንያት አይቻል የነበረው እግዚአብሔርን መስሎ ማደግ ወይም ቅድስና የሚቻል አደረገው፡፡ የሰው ልጅ ከዕፀ ሕይወት በልቶ ታድሶ ማደግ የሚችል አደረገው፡፡ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ” ብሎ መጥቶ ማደግ መመንደግ የሚችል አደረገው (ዮ.6፡48)፡፡ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምም፡- “ከዕፀ ሕይወት እንበላ ዘንድ አደለን፡፡ ይኸውም እኛን ስለ መውደድ መጥቶ ያዳነን የክርስቶስ ክቡር ሥጋው ቅዱስ ደሙ ነው” በማለት ይህን ግልጽ አደረገልን (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ፣ ቁ. 2)፡፡  
 
ስለዚህ የሕይወት ግቡ ይኼ ነው፡፡ የሕይወት ግቡ በዚህ መንገድ ከእግዚአብሔር ጋር መንፈሳዊና ምሥጢራዊ አንድነት መፍጠር ነው፡፡ የሕይወት ግቡ እንዲሁ ከእግዚአብሔር ጋር አንድነት ሳይፈጥሩ በሥነ ምግባር የተሻለ ሰው መኾን ብቻ ሳይኾን በእውነትና በውስጣዊ፣ ፍጥረታዊ ሰውም በማይመረምረው መንገድ ከእግዚአብሔር ጋር በጸጋ ተዋሕዶ መፍጠር ነው፡፡  
   
ይህን የሕይወት ዋናው ግብ የምንጀምረውም በዚህ ዓለም ነው፤ የምንፈጽመውም በወዲያኛው ዓለም ነው፡፡ ይህ ግብ በዚህ ዓለም ፍጽምና አያገኝም፤ በወዲያኛውም ዓለም ገና “ሀ” ተብሎ አይወጥንም (Nicholas Cabasilas (1974); The Life in Christ, p. 43)፡፡ ይህን ሕይወት ማየት የሚችል ዓይን፣ መስማት የሚችል ጆሮ፣ ማሽተት የሚችል አፍንጫ፣ መቅመስ የሚችል አፍ፣ በአጠቃላይ በመንፈሳዊው ዓለም መኖር የሚችል መንፈሳዊ ማንነት ይሻል፡፡ 
 
ይህን ማድረግ የምንችልበት ዓቅም ተሳታፊዎች የምንኾነውም ቅዱሳን አበው እንደሚነግሩን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰጠው ጸጋ ተሳታፊዎች ስንኾን ነው፡፡ ከእነዚህ ጸጋዎች ስንሳተፍ ፍጥረታዊ ሰው ከመኾን መንፈሳዊ ሰው ወደ መኾን (1ኛ ቆሮ.2፡14)፣ ከሚበሰብሰው ወደማይበሰብሰው (1ኛ ቆሮ.15፡50)፣ “አፈር ነህና” ከሚለው “ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው” ወደ መባል እናድጋለን፥ እንለወጥማለን፡፡ ከሥጋና ከደም ማንነት ወጥተን እግዚአብሔር በገለጠውና በሰጠው “በአዲስ ሕይወት” በመንፈሳዊው ዓለም መኖርና መመላለስ የምንችልበት መንፈሳዊ ማንነትን ገንዘብ እናደርጋለን (ሮሜ.6፡4)፡፡ 
 
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰጠው ጸጋ፣ ከሰጠው ሕይወት የምንሳተፈው ደግሞ አካሉ በምትኾን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አማካኝነት ነው (ኤፌ.5፡30)፡፡ አካሉ በምትኾን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አማካኝነት ሕዋስ ስንኾን ሕይወቱን ጸጋዉን እንቀበላለን፡፡
 
ስለዚህ ከላይ ስንጠቅሰው ወደ ነበረው የሕይወት ግብ፣ እግዚአብሔርን ወደ መምሰል፣ የስሙ ቀዳሽ የክብሩም ወራሽ መኾን የምንችለው በቤተ ክርስቲያን አማካኝነት ነው፡፡ መዳን የምንችለው፣ ወደዚህ የሕይወት ግብ መድረስ የምንችለው፣ በዚህ የሕይወት ጎዳና መጓዝ የምንችለው በቤተ ክርስቲያን አማካኝነት ነው፡፡ ፍጥረታዊ ሰው ከመኾን ወጥተን የክርስቶስና መንፈሳዊ ሰው ወደ መኾን የምንለወጠው፣ የምናድገውም በቤተ ክርስቲያን አማካኝነት ነው፡፡  
 
“በቤተ ክርስቲያን አማካኝነት ነው” ስንልም በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አማካኝነት ማለታችን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን፥ ቤተ ክርስቲያን የሚያሰኛት የምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን መኖር ነውና፡፡     
 
ወደዚህ ሕይወት ዘልቀን የምንገባበት የመጀመሪያው በር ምሥጢርም ጥምቀት ነው (1ኛ ቆሮ.12፡13)፡፡ ስንጠመቅ በክርስቶስ ሕያዋን እንኾናለን፤ እንንቀሳቀሳለን፤ እንኖርማለን (ሐዋ.17፡28)፡፡ በሌላ አገላለጽ ዲያብሎስን ክደን፣ እግዚአብሔርን አምነን፣ አዲስ ስም ወጥቶልን ክርስቶሳዊ፣ መንፈሳዊ፣ ምሥጢራዊም ወደ ኾነ ሕይወት እንወለዳለን፡፡ ወደ አዲስ ዓለም፣ ወደ አዲስ ሕይወት፣ ከፍጥረታዊ ሰው መንፈሳዊና ምሥጢራዊ ሰው ወደ መኾን እንገባለን፡፡
 
በጥምቀት በርነት ወደዚህ መንፈሳዊና ምሥጢራዊ ሕይወት ከገባን በላ ለዚህ ልደታችን የተገባ ይልን - የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን - እንቀበላለን፡፡ ጌታችን ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል እንደ ወረደ እኛም ተጠምቀን በምሥጢረ ሜሮን ስንከብር ይህን ይል እንቀበላለን፡፡ በዚህ ከምንቀበላቸው ስጦታዎች መካከልም፡- ምግባርን ትሩፋትን የመሥራት፣ የመጸለይ፣ የማፍቀር፣ ራስን የመግዛት፣ ተአምራትን የማድረግ ይል ወይም ዓቅም (ለምሳሌ በዘፈን የደነቆረ ጆሮአችንን ስብሐተ እግዚአብሔርን እንዲሰማ አስተምሮና በንስሐ መፈወስ) ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ 
 
ብዙዎቻችን እነዚህን እንደ ተቀበልን አናውቅም፡፡ አበው እንደሚነግሩን ግን ይህ ኹሉ ተጠምቀን በምሥጢረ ሜሮን በከበርን ጊዜ በኹላችንም ዘንድ አለ፡፡ ይኸውም እንደ ክብሪት ማለት ነው፡፡ ክብሪት ውስጥ እሳት መኖሩ የሚታወቀው ሲጫር እንደ ኾነ ኹሉ፥ በእኛ ዘንድ ይህ እንዳለ የሚታወቀውም ሥራ ስንሠራበትና መንፈስ ቅዱስም በማይነገር ምሥጢር ሲረዳን ስናገኘው ነው፡፡
 
ስንጠመቅ ከጢአት ነጽተን የክርስቶስን መልክ እንይዛለን፡፡ በሜሮን ስንከብር የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችን እንቀበላለን፡፡
 
ወደ ቅዱስ ሥጋውና ወደ ክቡር ደሙ ስንቀርብ ግን ሙሉ ለሙሉ ተለውጠን የክርስቶስ ግዛት - ማደሪያ - እንኾናለን፡፡ “አፈር ነህና” ስንባል የነበርነው የክርስቶስ አካሉ ወደ መኾን እናድጋለን፡፡ ከዚህ በላይ እድገት የለም፡፡ “ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ” ይላልና (ዮሐ.6፡56)፡፡ ከወላጆቻችን ጋር ካለን አንድነት ወደ ጠነከረ አንድነት እንገባለን፡፡ ከዚህ በላይ ሌላ ምኞት የለንም፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡- “ክርስቶስ የእኛ ኾኗል፤ ክርስቶስ የሕይወታችን ሕይወት ኾኗል፤ ደሙ ደማችን ኾኗል፡፡ በምሥጢረ ቁርባን ከኾነው በላይ እግዚአብሔር ለሰው ሊሰጠው የሚገባ ነገር የለም፡፡ ሰውም ከክርስቶስ ከተቀበለው በላይ ሊጠይቀው የሚችል ሌላ የሚበልጥ ነገር የለም” ያለውም ለዚህ ነው (Archimandrite George (2006); Theosis the True Purpose of life, p. 36)፡፡
እርሱ በእኛ አድሮ ሲኖር መንፈሳዊ ተጋድሎው ቀላል ይኾናል፡፡ ይልን የሚሰጠን እርሱ በእኛ ዘንድ ስለሚኖር ማንም አይችለንምና (ፊልጵ.4፡13)፡፡ በኹሉም ረገድ ጽኑዓን እንኾናለን፡፡ ቅዱሳን፥ ቅዱሳን የተባሉትና የሚባሉት በኹለንተናቸው እርሱ ስለሚያድርባቸው ነው፡፡ እርሱ ሲያድርባቸው ጠቢባን ይኾናሉ፡፡ ሙት ሥራን ከራሳቸው ያርቃሉ፡፡ ክፋትን ይጸየፋሉ፡፡ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ውለው ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ቢያድሩ የማይሰለቹ ወደ መኾን ያድጋሉ፡፡ እንዲህም ስለ ኾነና እርሱ ረድቸው እንደ ኾነ ስለሚገነዘቡ ትሑታን ወደ መኾን ያድጋሉ፡፡ ልዕልና ነፍስን ገንዘብ ያደርጋሉ፡፡
ከስንፍናችን የተነሣ በየጊዜው ከዚህ ለክርስቶስ ሕያዋን እንድንኾን ከተወለድንበት ሕይወት ልንወጣ እንችላለን፡፡ የክርስቶስ የአካሉ ሕዋሳት ብንኾንም ሙታን ልንኾን እንችላለን፡፡ እግዚአብሔር ግን ከቸርነቱ የተነሣ ንስሐ በተባለ ሌላ ምሥጢር እንደ ገና ሕይወት እንድንዘራ፣ ከቅዱስ ሥጋውና ከክቡር ደሙ እየበላንና እየጠጣንም ሕያዋን እንድንኾን፣ እንድንንቀሳቀስ እንድንኖርም ያደርገናል፡፡ 
 
ስለዚህ አንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን መገንዘብ ያለበት ስንፍናንና በልቡ ውስጥ ሊኖር የሚችለውን ክፉ መዝገብ ከራሱ ማራቅ ሲፈልግ በእግዚአብሔር ጸጋና ሀብት እንጂ እንዲሁ በራሱ ዓቅምና ብርታት አለመኾኑን ነው፡፡ እነዚህ ድካሞች፣ ወይም ክፉ መዝገቦች ከእኛ ርቀው የሚኼዱት ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ስንሳተፍና በዚሁ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ስንቀበል ነው፡፡ 
 
ስለዚህ ወደ ዋናው የኦርቶዶክሳዊ ሕይወት ግብ ለመድረስ ዋና ምሥጢሩ ያለው እዚህ ላይ መኾኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ መንፈሳዊ ማንነትን ጠብቆ ለመቆየት፥ ራስን ከክፉው ዓለም አውጥቶ ወደ ክርስቶስ ዕቅፍ ውስጥ ማስገባት ያሻል፡፡ ሳናስታጉልና አባቶች እንደሚነግሩን መደበኛ በኾነ ጊዜ ወደ ምሥጢር መቅረብ ያስፈልጋል፡፡ ኃይልን ኹሉ ገንዘብ ማድረግ የሚቻለን በዚህ መንገድ ነው፡፡ የሰላምን ኃይል፣ የደስታን ኃይል፣ የትሕትናን ኃይል፣ የፍቅርን ኃይል፣ የጸሎትን ኃይል፣ የሌላውንም ኃይል ኹሉ ገንዘብ ማድረግ የሚቻለን በዚህ መንገድ ነው፡፡ በአጠቃላይ በቅድስና ሕይወት የማደግ ኃይልን ገንዘብ ማድረግ የምንችልበት ቀላሉ መንገድ ይህ ነው፡፡ 
 
ከክርስቶስ ውጭ ኾነን ራሳችንን መለወጥ አይቻለንም፡፡ ከፍትወታችን፣ ከስሜታችን፣ ከሚማርከን ነገር መላቀቅ አይቻለንም፡፡ እኛ ራሳችን በራሳችን ዓቅም እውነተኛ ክርስቲያን፣ እውነተኛ ኦርቶዶክሳዊ መኾን አይቻለንም፡፡ እርሱ ራሱ ሲናገር፡- “ያለ እኔ ምንም ማድረግ አትችሉም” ብሎናልና (ዮሐ.15፡5)፡፡ የቱንም ያህል ራሳችንን ለመለወጥ ብንጥርም እንኳን የትም መድረስ አንችልም፡፡ ማድረግ የምንችለው አንድ ነገር ነው፤ እርሱም ራሳችንን ወደ እግዚአብሔር መመለስ፤ በየጊዜው ከምሥጢር በመሳተፍ መጓዝ፤ ኃይልን ታጥቀን መንፈሳዊ ሕይወታችንን መምራት! የእግዚአብሔር ኃይል እንዲመራን አድርገን እርሱን መከተል! እግዚአብሔር በውስጣችን ያስቀመጠውን ዓቅም በየጊዜው ማጠጣትና መኮትኮት! ይህ ነው የእኛ ሥልጣንና ኃይል! 
 
ይህን በምሳሌ መግለጽ እንችላለን፡፡ ዳግም ስንወለድና በምሥጢረ ሜሮንም ስንታተም የተቀበልነውን መንፈሳዊ ዓቅም የፍራፍሬ አትክልት፣ አበባ፣ ሌሎችም ዕፅዋት እንዳሉት መስኖ አድርገን ማሰብ እንችላለን፡፡ በውስጣችን ሊኖር የሚችለውን ክፉና መንፈሳዊ ያልኾነው ነገር ደግሞ እሾኽ፣ አሜኬላና አረም እንደ ተሞላ መስኖ አድርገን መውሰድ እንችላለን፡፡ ውኃ ማጠጣት ግን የእኛ ሥልጣን ነው፡፡ ፍራፍሬው፣ አትክልቱ፣ አበባበውንና ሌላውም ዕፅ ያለበትን መስኖ ብቻ የምናጠጣ ከኾነ ሌላው በራሱ ጊዜ ውኃ አጥቶ ይደርቃል፡፡ የእሾኹን መስኖ የምናጠጣ ከኾነም እንደዚሁ በጎው መስኖ ይደርቃል (Wounded By Love; The Life & Wisdom of St. Porphyrios (2015); p. 135)፡፡
ስለዚህ እሾኽና አሜኬላ አረምም ስለ ተሞላው መስኖ ማሰብና መጨናነቅ አያስፈልግም፡፡ አረሙን ስለ መንቀል መብሰልሰል አያሻም፡፡ እንድናስብ የሚገባው በእኛ ዘንድ ያሉትን አረሞችን ስለ መንቀል መጨነቅ ሳይኾን መንፈሳዊውን መስኖ እንዴት ማጠጣት እንዳለብን ነው፡፡ እንዲለመልም የምንፈልገው መስኖ በየስንት ጊዜ ማጠጣት እንዳለብን ነው - ከምሥጢራት በመሳተፍ! ያን ጊዜ መስኖው ሕይወታችን በጎ ፍሬ ያፈራል፡፡ ጣፋጭ ፍሬ ያፈራል፡፡ በጎ መዓዛ ያለው ፍሬ ያፈራል - የጸሎት ፍሬ፤ የፍቅር ፍሬ፤ የሰላም ፍሬ፤ የየውኀት ፍሬ፤ የትዕግሥት ፍሬ፤ የበጎነትና የእምነት ፍሬ፤ ይህንንም የመሳሰለ በጎ ፍሬ ኹሉ!  
ቅዱሳን አበው እንደሚነግሩን ልጅነታችን ጠብቀን በመንፈሳዊ ሕይወታችን ለማደግ ኹለት መንገዶች አሉ - ቀላልና ከባድ! ከባዱ መንገድ ክፉ ነገሮችን ከእኛ ለማራቅ የሚደረግ ተጋድሎ ነው! ለምሳሌ ድካም ለማራቅ ብሎ ብዙ መጸለይ፣ ብዙ መስገድ፣ ብዙ መንፈሳዊ ተግባራት ላይ ጽሙድ መኾን፣ ዕለተ ሞትን ማሰብ፣ ምረረ ገሃነምን ማስታወስና የመሳሰሉ ናቸው፡፡ ይህም ከላይ በምሳሌው እንደ ተመለከትነው በእኛ ውስጥ ያለውን እሾኽ፣ አሜኬላና አረም ለመንቀል እንደ መጣር ነው፡፡ ይህ ከባድ ጥረትን የሚሻ ቢኾንም የሚችሉት አሉ፡፡ 
 
ቀላሉ መንገድ ደግሞ እግዚአብሔርን መውደድ ነው፡፡ ይህ የራስን ድካም ሳያስቡ የሚከናወን ነው፡፡ ለእኛ ለደካሞች የሚያዋጣው ኹለተኛውና ቀላሉ መንገድ ነው፡፡ ኃይልን የሚሰጠን እግዚአብሔርን ወድዶ ንስሐ መግባት ቀላሉ መንገድ ነውና፡፡ እግዚአብሔርን ወድዶ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን መቀበል ቀላሉ መንገድ ነውና፡፡
ዛሬ የጀመርነው ትንሹ መንፈሳዊ ሕይወት ነገ ሌላ ትንሽ ሊጨመርበት የሚችለው መጨመሪያውን መንገድ በአግባቡ በመጠቀም ነው፡፡ ለምሳሌ ዛሬ የጀመርነው አጭር ጸሎት ነገ እያደገ እንዲኼድ ደማችንን ማፍሰስ አይጠበቅብንም፡፡ ይህም መከናወን የሚችለው ቀላሉን መንገድ በመከተል ነው፡፡ የቅዱሳንን ሕይወት ስንመለከት በዚህ መንገድ እንደ ኼዱ ነው፡፡ ከእነ ድካማቸው ወደ እርሱ መጡ፡፡ ደጋግመው ቀረቡ፡፡ ከእርሱ እንዳይለዩ የሚያስችላቸውን የቆራጥነት ኃይልን ታጠቁ፡፡ እርሱም ድካማቸውን የሚመኩበት አደረገላቸው፡፡ ኀዘናቸው የሚመኩበት አደረገላቸው፡፡ ራሳቸውን ዝቅ ሲያደርጉ የምንመለከታቸው የሚያበረታቸው እርሱ እንደ ኾነ ስለሚያውቁ ነው፡፡ ስለዚህ እኛም ይህን የቅዱሳንን መንገድ ልንመለከት ልንከተለው ያስፈልጋል፡፡ በጎ ምግባራትን መሥራት፣ ኃይለ አጋንንትንም ማራቅ የምንችልበት፥ ቢኖርም እንኳን ጸጋን የምናገኝበት እንጂ የማንወድቅበት እንዲኾን ሳናስታጉል፣ በየጊዜው ወደ ምሥጢራት መቅረብ ያሻል! 
 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!  

2 comments: