Pages

Thursday, June 14, 2018

ሙስሊሞች በክርስቲያኖች ጉባኤ


በአማን ነጸረ እንደ ጻፈው
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሰኔ 07 ቀን፣ 2010 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ጥሎብኝ፣ ክርስቲያን ወንድሞቼ ስለ ቁራን በተቃርኖ ሲተረጉሙ መስማት ይጨንቀኛል፡፡ በራሴ ደርሶ ስላየሁት ይሆናል፡፡ የቤ/ ገድላትና ድርሳናት በማያምኑባቸው ሰዎች ሲተረጎሙ በአማኝ ዕዝነ ልቡና እያዳመጥኩ ብዙ ጊዜ ቅር ይለኛል፡፡ የባለቤትነትና የማንነት ስሜት በሌለህ እምነት ውስጥ ገብተህ ስትተረጉም እንደ ምዕመን ሳይሆን እንደ ፈላስፋ ሁሉን ነገር በአመክንዮ እየፈታህ ትገጥምና ጭርሱን እምነት የሚለውን ከአመክንዮ (ሎጂክ) በላይ የሆነ አስተሳሰብ ትዘነጋለህ፡፡ ያን ጊዜ መዘንጠል ይመጣል፡፡ ያለ አነባበቡ፣ ተነሺና ወዳቂ ሳይለይ የሚያነብ ሰው በድፍረት ንባቡን ሲሾፍረው ‹‹ኧረረረረረ ዘነጥልከው!›› ይላሉ የቤ/ አስነባቢዎች፡፡ ሰው የማያምነበትን ሲተረጉም ደግሞ ዝንጠላ የማያመልጠው ግድግዳ ይሆንበታል፡፡ ጥሎብኝ፣ ከዚህ ግድግዳ መላተም አልወድም፡፡


ዘመናት ፈትነው ያነጠሩት ትውፊታችንም - በኦርቶዶክሳዊው ክርስትናና እስልምና መካከል - በዚህ ዘመን ያንን የሚያበረታታ አይመስለኝም፡፡ ሥጋዊውም ሆነ መንፈሳዊው ትውፊታችን ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም ይመስጠኛል፡፡ ባህል፣ እምነት፣ የእርስ በርስ ተገናዝቦ (የራስን ማንነት ሳይተዉ የሌላውንም በተዓቅቦ፣ ግን በአክብሮት ሀገራዊ ገንዘብ አድርጎ ማየት) መኖር ታላቅ ጸጋችን ነው፡፡ ብዙ ሰይፍና ሰልፍ ያለፈ፣ ተፈትኖ የነጠረ ትውፊት፡፡ ብቻ ታሪክ ከተፋቅሮ ይልቅ ሰይፍና ሰልፍ ላይ ስለሚያተኩር፣ ተጣልቶ መታረቅ እንጂ ሕይወትን አስታርቆ ያለጥል መኖር ዜና ስለማይሆን፣ አሁን አሁን ደግሞ ልዩነትን በአደባባይና በጉባኤ ተቀምጦ ከማንጠር ይልቅ ማንነትን መድቦና ጠርዝ ይዞ፣ ቀሊል ቲፎዞ አሰባስቦ ከወዲያና ከወዲህ በማያልቅ ሤራ ‹‹ጅቡ መጣልህ!›› መባባል ለጩዋሂ ክብርና ሞገስ የሚያስገኝ ሆነና ስላለፉት የፍቅር ታሪኮች እያወጉ መጻኢውን በዚያ አንጻር መመኘት አንድም በአድር ባይነት አንድም በወገበ ሰባራነት (spineless) ስለሚያስተች መካከለኞች ጠፉ፡፡ ደመ-ፍል ቡድንተኞች ሳይመረጡ እየተቧደኑ፣ እየተጀጎሉ ነገሡብን፡፡ ከሁለቱም አቅጣጫ በሚወረወር ድንጋይ ላለመወገር መካከለኞች ተሸሸጉ፡፡ የተሸሸጉት እንዲወጡ እየጸለይን ከሽሽግ ግሩማን ታሪኮቻችን ጥቂት እናውጋ፡፡

1.ሙስሊሙ በክርስቲያኖች ጉባኤ ተገኝተው የሰጡት ፍርድ

ስለ ነፍስ ተፈጥሮ ባገራችን ተደጋጋሚ ክርክሮች ተነስተዋል፡፡ አሁንም አልፎ አልፎ በየመጻሕፍቱ የልዩነት ነጥቦች አሉ - ለጉባኤ የሚበቁ ባይሆኑም፡፡ በቀደመው ጊዜ ከተካሔዱት ክርክሮች በንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ዘመን የተካሄደው ይጠቀሳል፡፡ ይህ ጉባኤ ለየት የሚለው፣ አብዝተው (የጸጋ ዘውግ የሆነውን) ክርስትና በማስፋፋት የሚታወቁትና በፈላሻነት የሚጠረጠሩ እጀ ሠሪዎችን ለሰቆቃ ዳርገዋል እየተባሉ በሚሽነሪዎች የሚከሰሱት የሸዋው ሣህለ ሥላሴ ስለ ነፍስ ጉባኤ አዘጋጅተው፣ በጉባኤው ሙስሊሞች የመናገር እድል አግኝተው፣ ንግግራቸውም ውሳኔ ሆኖ በንጉሥ ቃል በመጽደቁ ነው - በእርግጥ ውሳኔው ከክርስትናችን የሚጣረስ አልነበረም፡፡ የክርክሩ ጭብጥ ‹‹ነፍስ በማኅፀን ሳለች ታውቃለች? ወይስ አታወቅም?›› የሚል ነበር ይላሉ ዐፅሜ፡፡ እና በዚህ ጉባኤ ላይ ወላስማ ጥጃዬ የተባሉ ሙስሊም ተነሥተው ‹‹አላህ›› አሉ፣ ‹‹አላህ ሁለት በድን አንድ ላይ አይፈጥርም!››፡፡ ቃላቸው ፍርድ ነበር፡፡ በዚህ የክርስቲያኖች ጉባኤ ላይ በአላህ ስም የሚምሉት ሰው የሰጡት ፍርድ ውሳኔ ሆነ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በዚያ ዘመን በነበረው የክርስትና ዘውጎች፣ የጸጋ-ቅብዓት-ተዋሕዶ /ካራ/ ክርክር የየጁ ባለሙስሊም ጀርባ ባላባቶች ተደጋጋሚ ጉባኤያትን አካሂደዋል፤ ጳጳሳትን ለማስመጣትና ዴር ሡልጣንን ለማስከበር ታግለዋል፡፡ ርእሳችን ጉባኤ ነውና ጉባኤው ላይ እናተኩር፡፡

2. ግራዝማች መሐመድ በፈራጅነት የመራው የክርስቲያኖች ጉባኤ

ዘመኑ በዘመነ መሳፍን ነው፡፡ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስ፣ እጨጌው እጨጌ ወልደ ዮና፣ ንጉሡ ዳግማዊ ኢዮአስ የቤገምድሩ ገዥ ራስ ጉግሣ ሳሉ ነው፡፡ ቅብዓትና ጸጋ ‹‹ነኀብር፡ በብሂለ፡ ነሥአ፡ መንፈስ፡ ቅዱስ - መንፈስ ቅዱስን ተቀበለ በማለት እንተባበራለን›› ብለው ዘታየስ ሣህሉ የተባለውን የተዋሕዶ ወገን 1812 . አጋማሽ ይገጥማሉ፡፡ ንጉሡና ጳጳሱ ከተዋሕዶ ወገን ናቸው፤ እጨጌውና ራስ ጉግሣ ደግሞ ለጸጋው ያደላሉ፡፡ እንዲያም ሆኖ ራስ ጉግሣ በቦታው (ጎንደር) አልተገኙም፡፡ ‹‹ግራዝማች መሐመድንና ባሻ ወዳጄ ፈራጅ ይሆኑ ዘንድ ላኩዋቸው - ፈነዎሙ፡ ለግራዝማች፡ መሐመድ፡ ወለባሻ፡ ወዳጄ፡ ይኩሙ፡ ፈታሕተ፡፡›› ክርክሩ እየከረረ መወጋገዝ ተጀመረ፡፡ አቡነ ቄርሎስ ከተዋሕዶ ውጪ ያለውን ሁሉ አወገዙ፡፡ ጭንቅ ሆነ! ያን ጊዜ በጎንደር-ጎጃም-ትግራይ-ሸዋ የጸጋና ቅብዓት አማኞች ቁጥር ቀላል አልነበረማ! ግዝቱ (እንደ ዐፄ ቴዎድሮስና ዮሐንስ የመጣው ይምጣ ያለ ካልሆነ በቀር ሊወጣው የማይችል) ሀገራዊ ሁከት የሚፈጥር ነበር! ስለዚህ፡- ‹‹ወእምዝ፡ ይቤልዎ፡ ለጳጳስ፡ እለ፡ ግራዝማች፡ መሐመድ፡ ፈታሕተ፡ ሃይማኖት፡ ይቤለከ፡ እግዚእነ፡ ራስ፡ ጉግሣ፡ እመ፡ ትፈቅድ፡ ንበር፡ በምኵናንየ፡ ፍታሕ፡ ግዝተከ፡ ከመ፡ ይንበር፡ ኵሉ፡ በሃይማኖቱ፡፡ ወለእመ፡ አበይከ፡ አኮ፡ ሠናይ - ከዚያም እነ ግራዝማች መሐመድ፣ የሃይማኖት ዳኞች ጳጳሱን / አቡነ ቄርሎስን/ እንዲህ አሉት፡- ጌታችን ራስ ጉግሣ እንዲህ ይልሀል፡ በግዛቴ መኖርን ትወድ እንደሆነ ሁሉም ()ሃይማኖቱ ይኖር ዘንድ ግዝትህን ፍታ፡፡ እምቢ ካልክ ግን መልካም አይደለም፡፡›› በዚህ ትእዛዝ መሠረት ጳጳሱ በፍራቻ ግዝቱን ለጊዜው ፈቱ፡፡ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ታሪክ ነገራ ይቀጥላል፡፡ ለኛ ግርምት ያህል ግን እስከዚህ ያለው ይበቃል፡፡ የጉግሣ ‹‹ይንበር ኵሉ በሃይማኖቱ!›› ዛሬ ብዙ ዘመናይ የሚያሸብሽላት መርህ ናት፡፡ ታዲያ "በየሃይማኖቱ" ሲባል በደባልነት አይደለም፡፡ አንዱ ያንዱን ወሰንና ቤተ ጸሎት አክብሮ፣ ለሌላውም ለእሱ ይሄንኑ ጠብቆለት በባንዲራና በአኗኗር ተዋሕዶ፣ በእምነትና በቤተ ጸሎት የራስን ማንነት ሳያጡና ሳይዋጡ (በተዓቅቦ) መኖር ማለት ነው፡፡ መገናዘብ ማለት እንዲያ ይመስለኛል፡፡ አንዱ ያንዱን ከዘለፈማ፣ ያስተርታል፤ ‹‹የሰው አባት የሚሰድብ የራሱን ያስሰድባል፤›› ያስተርታል፡፡
አባት አሰዳቢ ከመሆን ይሰውረን!

ኧህ! አባት ሲባል ካህኑ አባቴና ጓደኛው ትዝ አሉኝ፡፡ ሁለቱም ካህናት ናቸው፡፡ አባቴ ከጎጃም፣ እሳቸው ከወሎ ናቸው - ያባቴ ጓደኛ፡፡ አባቴ ቄሰ ገበዝ ሳለ እሳቸው ያረፍዳሉ፡፡ እንዲህ የአባ (የወሎው) የአባት ስም መሐመድ ነው፡፡ ለኩሸታዊ ነገር ፍለጋ ሲሆን አባቴ በምንኩስና ስማቸው ሳይሆን በአባታቸው ስም ነው የሚጠራቸው - መሐመድ፡፡ አንድ ቀን፣ በክረምቱ ወራት አባ ኪዳን አርፍደው መጡ፡፡
#አባቴ- ምነው መሐመድ አንግተህ መጣህ?
#አባ- የጉም ጅብ ፈርቼ ነዋ! (አባቴን በጎጃሜነቱ ለመንካት)
#አባቴ- ኧረ ተው መሐመድ! እናምንስ ብትፈራ አባትህ ‹‹አላህዋ ክበር›› ካለ በኋላ ለኪዳን ትመጣለህ?
ረጅም ሳቅ ሆነና አባ በቀሪ መመዝገባቸው ቀረ፡፡
ዳግም እንመራረቅ፡- አባት አሰዳቢ ከመሆን ይሰውረን!

No comments:

Post a Comment