በዲ/ን ኄኖክ ኃይሌ
(ከመጽሐፈ ገጹ የተወሰደ)
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ነሐሴ 14 ቀን 2011 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ስለ እመቤታችን ቅድስት
ድንግል ማርያም በልጅዋ
ፈቃድ ከሞት መነሣት
ኦርቶዶክውያን አባቶች
ሲያስተምሩ ከመጽሐፍ ቅዱስ
የሚጠቅሱት ማስረጃ በመዝ.
131፡8 ላይ ያለውን
‹‹አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ ፤
አንተና የመቅደስህ ታቦት››
የሚለውን ቃል ነው፡፡
ይህንን ጥቅስ ከድንግል ማርያም ትንሣኤ
ጋር አያይዞ መጥቀስ
አሁን የተጀመረ ነገር
ሳይሆን ብዙ ክፍለ
ዘመናትን ያስቆጠረ ነገር
ነው፡፡ ሠላሳ ሦስተኛው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ቅዱስ ቴዎዶስዮስ ከእርሱ ቀድመው
የተነሡ አበው ያስተላለፉለትን የእመቤታችንን ዕረፍትና ትንሣኤ ታሪክ
የዛሬ ከአንድ ሺህ
አምስት መቶ ዓመታት
በፊት በጻፈው ድርሳን
ላይ ፣ በነገረ
ማርያም ሊቃውንት ዘንድ
Doctor of Dormition በመባል የሚታወቀው ሊቁ ዮሐንስ
ዘደማስቆ ፣ ሐዋርያውያን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በድርሳኖቻቸው ላይ ስለ
ድንግል ማርያም ትንሣኤ
ባነሡና በዓለ ዕርገትዋን ባከበሩ ቁጥር
የሚያነቡት የመጽሐፍ ቅዱስ
ክፍል ‹‹አቤቱ ወደ
ዕረፍትህ ተነሥ ፤
አንተና የመቅደስህ ታቦት››
የሚለውን የዳዊት መዝሙር
ነው፡፡ በእርግጥ ይህንን
ቃል ከድንግል ማርያም
ጋር ምን ያገናኘዋል? ‹ማርያም ተነሣች›
የሚል ነገር አለውን?
የሚለውን ጥያቄ በዚህች
አጭር ጽሑፍ እንመለከታለን፡፡ ወደዚህ ጉዳይ
ከመግባታችን በፊት ግን
አንድ ቁምነገርን እናስቀድም፡፡
በሐዲስ ኪዳን ለምናምን ፣ በወንጌል ለምንመራ ክርስቲያኖች የብሉይ ኪዳን
መጻሕፍት ምን ያደርጉልናል? የሙሴ ሕግጋት
፣ የነቢያት መጻሕፍት ፣ የዳዊት
መዝሙራት ለክርስቲያኖች ምን
ይጠቅሙናል? ብለን ከመጠየቅ እንጀምር፡፡ የዚህ
ጥያቄ መልሱ ጌታችን
‹‹በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ
እኔ የተጻፈው ሁሉ
ሊፈጸም ይገባል›› እንዳለው የብሉይ ኪዳን
መጻሕፍት ሁሉ በምሥጢር የሚናገሩት ስለ
ክርስቶስ ስለሆነ ነው፡፡
(ሉቃ. 24፡44) ‹ከሙሴና ከነቢያት ጀምሮ
ስለ እርሱ የተጻፈውን ተረጎመላቸው› ተብሎ
የተነገረላቸው የኤማሁስ መንገደኞች ‹በመንገድ ሲናገረን መጻሕፍትን ሲከፍትልን ልባችን
ይቃጠልብን አልነበረምን?› ብለው
እንደተናገሩ ብሉይ ኪዳን
በእርግጥ ስለ ክርስቶስ እንደሚናገር በሚገባ
ትርጉሙን ከተረዳን ልባችን
በጥልቅ ተመሥጦ ይቃጠላል፡፡ ይህንን የአባቶችን ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜ
መነፅር በዓይናችን ካጠለቅን ብሉይ ኪዳንን
እያነበብን በሐዲስ ኪዳን
ባሕር ውስጥ መዋኘት
እንችላለን፡፡ በኅብረ
አምሳል (Typology) አስቀድሞ
የተነገረበትን ምክንያት (Primary application) እና
ፍጻሜውን (Ultimate fulfillment) ስንረዳ
በታሪክና ትንቢት ሁሉ
ውስጥ መድኃኔ ዓለም
ክርስቶስን እያገኘነው ስንደነቅ እንኖራለን፡፡
በገነት መካከል ተኝቶ
ከጎኑ የሁላችንን እናት
ሔዋንን ያስገኘውን አዳም
ታሪክ ስናነብ በዕለተ
ዓርብ በቀራንዮ በመስቀል ላይ አንቀላፍቶ ከጎኑ በፈሰሰው የጥምቀት ውኃ
የሁላችን እናት ቤተ
ክርስቲያንን ያስገኘውን ክርስቶስን እናየዋለን፡፡ ወይን
ጠጥቶ ሰክሮ ዕርቃኑን የወደቀውንና ካም
ሲዘብትበት ፣ ሴምና
ያፌት ዕርቃኑን የሸፈኑለትን የኖኅን ታሪክ
ስናነብ የሞትን ጽዋ
ጠጥቶ በሰው ልጅ
ፍቅር ሰክሮ ዕርቃኑን የተሰቀለውንና አይሁድ
ሲዘብቱበት ፀሐይና ጨረቃ
ዕርቃኑን የሸፈኑለትን ክርስቶስን እናየዋለን፡፡ አብርሃም የሚወደውን ልጁን
ይስሐቅን ሊሠዋ መፍቀዱንና በግ የመሠዋቱን ታሪክ ስናነብ
አንድያ ልጁን እስኪሠጥ ድረስ ዓለሙን
የወደደውን እግዚአብሔር አብንና
እስከ ሞት ድረስ
የታዘዘ ልጁን ንጹሑን
በግ ክርስቶስን እናየዋለን፡፡ ዳዊት ጎልያድን ድል አድርጎ
እስራኤልን ነጻ ሲያወጣ
ስናይ ክርስቶስ ዲያቢሎስን ድል አድርጎ
የሰው ልጅን ነጻ
ሲያወጣ ይታየናል፡፡ እስራኤል በበረሃ ተጉዘው
በበትር ከተመታው ከዓለት
ውኃ ፈልቆላቸው ሲጠጡ
ስናይ በዕለተ ዓርብ
ጎኑን በጦር ተወግቶ
በደሙ ጥማችንን ያረካልን መድኃኔ ዓለም
ይታየንና ከቅዱስ ጳውሎስ
ጋር ‹ያም ዓለት
ክርስቶስ ነበረ› እንላለን፡፡
ወደ መገናኛው ድንኳን
ገብተን ደብተራ ኦሪትን
ብንጎበኝ እንኳን ክርስትናችን አይለቀንም፡፡ በመሠዊያ ላይ የሚሠዋውን በግ ስናይ
የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግደው የእግዚአብሔር በግ
ኢየሱስ ክርስቶስ በሕሊናችን ይመጣብናል፡፡ ወደ
ድንኳኑ ዘልቀን በመቅረዙ ላይ መብራት
ሲበራ ስናይ እውነተኛው ብርሃን ክርስቶስ ፣ ዕጣን
ስናይ የኃጢአት ሽታችንን ያራቀልን ክርስቶስ ፣ በወርቅ
የተለበጠ ታቦት ስናይ
በመለኮቱ መለወጥ የሌለበትን ክርስቶስ ፣
መናውን ስናይ የሕይወት እንጀራ ክርስቶስ እየታየን እንደ
ኤማሁስ መንገደኞች ‹‹ልባችን
እየተቃጠለ ለካስ ኦሪትና
ነቢያት ሁሉ የሚናገሩት ስለ ክርስቶስ ነበረ?›› እንላለን፡፡
ኦርቶዶክሳውያን ከሆንን
ደግሞ ጌታን ባገኘንበት ሥፍራ ሁሉ
እመቤታችንን ፍለጋ ማማተራችን አይቀርም፡፡ አዳምን
የክርስቶስ ምሳሌ ሆኖ
ስናየው አዳምን ያለ
አባት ያስገኘችዋ መሬት
ያለ ወንድ ዘር
የወለደችውን ድንግል ሆና
ትታየናለች፡፡ አብርሃም የሠዋውን ከዱር
ቀንዱ እንደታሰረ የወጣ
በግ ስናይ የድንግልናዋ ማኅተም ሳይፈታ
የወለደችው የበጉ እናት
ትታየናለች፡፡ ወደ
መገናኛው ድንኳን ገብተንም አናርፍም ፣
እርሱ መብራት ሆኖ
ሲታየን እርስዋ መቅረዝ
ትሆንልናለች፡፡ እርሱ
ዕጣን ሲሆን እርስዋ
ማዕጠንት ትሆናለች ፣
እርሱ ታቦት ሲሆን
እርስዋ ታቦቱ ያለበት
ቅድስተ ቅዱሳን ትሆናለች ፣ እርሱ
ጽላት ሲሆን እርስዋ
የጽላቱ ማደሪያ ታቦት
ትሆናለች ፣ እርሱ
በጽላት ላይ የተጻፈው ቃል ሲሆን
እርስዋ ጽላት ትሆናለች ፣ እርሱ
የተሰወረ መና ሲሆን
እርስዋ የመናው መሶበ
ወርቅ ትሆናለች፡፡ ለሰብአ
ሰገል ‹ሕጻኑን ከእናቱ
ከማርያም ጋር አዩት›
እንደተባለላቸው እኛም
በሔድንበት የብሉይ ኪዳን
መጻሕፍት ሁሉ የጌታችንን ምሳሌ ባነበብንበት ሥፍራ ሁሉ
እናቱንም እናያታለን፡፡
እውነቱን ለመናገር ለመመርመር ትዕግሥት ላለው
ሰው ስለ ክርስቶስ በሚናገሩት የብሉይ
ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ
እንኳን ድንግል ማርያምን ቀርቶ ከሐዲው
ይሁዳንም ማግኘት ይቻላል፡፡ ዮሴፍ የክርስቶስ ምሳሌ ሲሆን
ዮሴፍ በሃያ ብር
እንዲሸጥ ሃሳብ ያቀረበው ወንድሙ ይሁዳ
የአስቆሮቱ ይሁዳ ምሳሌ
አይደለምን? ፍልስጤማውያንን ድል
ያደረገው ናዝራዊው ሶምሶን
የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ሲሆን
ሶምሶንን እየሳመች አሳልፋ
የሠጠችው ደሊላ ስሞ
የሸጠው የይሁዳ ምሳሌ
አይደለችምን? አባቱን ለመግደል ሲያሴር ኖሮ
መጨረሻ በዛፍ ላይ
ተሰቅሎ የሞተው አቤሴሎምስ ጌታውን አሳልፎ
ሠጥቶ ተሰቅሎ የሞተው
የይሁዳ ምሳሌ አይደለምን? ‹የታመንሁበት የሰላሜ
ሰው እንጀራዬን የበላ
ተረከዙን በእኔ ላይ
አነሣ› ተብሎ የተነገረው ስለ ይሁዳ
አይደለምን? ብሉይ ኪዳን
እንኳን አምላክን ስለወለደችው ቅድስት ድንግል
ቀርቶ አምላኩን ስለሸጠው ይሁዳም ትንቢት
ተናግሯል፡፡
አሁን ወደ ቀደመ
ነገራችን እንመለስ! ‹አቤቱ
ወደ ዕረፍትህ ተነሥ
፤ አንተና የመቅደስህ ታቦት› ብሎ
ዳዊት ስለ ቤተ
መቅደስ መሠራትና ታቦቱም
ወደ ቤተ መቅደሱ
ስለመግባቱ የዘመረው መዝሙር
፣ ልጁ ሰሎሞንም መቅደሱ ተሠርቶ
ሲያልቅ ደግሞ የዘመረው ይህ መዝሙር
ከድንግል ማርያም ጋር
ምን ያገናኘዋል? (2ዜና 6፡41) ኦርቶዶክሳውያን አባቶች
ከጥንት ጀምሮ ይህንን
ጥቅስ ከድንግል ማርያም
ጋር የሚጠቅሱት ዳዊት
ስለ መቅደሱ መሠራትና ስለ ታቦቱ
መግባት የተናገረ መሆኑ
ጠፍቷቸው ነው? ‹አቤቱ
ወደ ዕረፍትህ ተነሥ
፤ አንተና የመቅደስህ ታቦት› የሚለውን የዳዊት መዝሙር
ከድንግል ማርያም ጋር
አገናኝተን እንድናስብ ያነሣሣን ምንድር ነው?
ወደሚለው እንምጣ፡፡
ዳዊት ስለ ታቦቱ
የተናገረውን እኛ ስለ
ድንግል ማርያም ሆኖ
እንዲሰማን ያደረገው ራሱ
ዳዊት ነው፡፡ ዳዊትን
የእግዚአብሔር ታቦት
ወደ እርሱ ስትመጣ
‹‹የእግዚአብሔር ታቦት
እንዴት ወደ እኔ
ይመጣል?›› ሲል አልሰማነውምን? (2ሳሙ. 6፡9)
ይህን ንግግርስ ኤልሳቤጥ ‹‹የጌታዬ እናት
ወደ እኔ ትመጪ
ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?›› ብላ ለድንግል ማርያም አልደገመችውምን? (ሉቃ. 1፡43)
ዳዊት የፈራው ታቦት
ወደ እርሱ ሲቀርብ
ከዙፋኑ ተነሥቶ በታቦቱ
ፊት እየዘመረ ሚስቱ
ሜልኮል እስክትንቀው አልዘለለምን? (2ሳሙ. 6፡16)
በኤልሳቤጥ ማኅፀን የነበረው ዮሐንስስ የድንግልን ‹‹የሰላምታዋን ድምፅ
በሰማ ጊዜ› እናቱ
እስክታደንቀው ‹ፅንሱ
በደስታ ዘለለ›› አልተባለምን? (ሉቃ. 1፡44)
ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ
የድንግል ማርያምና የልጅዋ
ክብር ላልገባቸው ሰዎች
‹‹እንደ ዮሐንስ በማኅፀን ውስጥ መዝለል
ቢያቅታችሁ ምነው ነፍስ
ካወቃችሁ በኋላ እንኳን
ለእግዚአብሔር ማደሪያ
እንደ ዳዊት በምስጋና ብትዘሉ?›› ያለው ለዚህ ነው፡፡
እኛ ምን እናድርግ የእግዚአብሔር ታቦት
በጌት ሰው በአቢዳራ ቤት ሦስት
ወር ያህል ቆየች
እንደተባለ ‹‹ማርያምም በዘካርያስ ቤት ሦስት
ወር ያህል ቆየች››
ተብሎ ተጽፎ አነበብን፡፡ (2ሳሙ. 6፡11
፤ ሉቃ. 1፡56)
ታዲያ የድንግል ማርያም
ታሪክ ከእግዚአብሔር ማደሪያ
ከታቦቱ ታሪክ ጋር
አንድ ሆኖ ስናገኘው ዳዊት ስለ
ታቦት የተናገረውን ስለ
ድንግል ማርያም እንደምን አንጠቅስ? የነገረ
ማርያምን ታሪክ እንጥቀስ ካልንማ ታቦቱ
በወርቅ እንደተለበጠ በንጽሕና ያጌጠችውን ፣
ታቦቱ በመቅደስ እንደኖረ በመቅደስ ያደገችውን ፣ ታቦቱን
በትሩ አብባ የተገኘች አሮን እንደ
ጠበቃት በትሩ ያበበች
ዮሴፍ የጠበቃትን፣ ታቦቱን
የነካ ዖዛ እንደተቀሠፈ (2ሳሙ. 6፡7)
የድንግልን ሥጋ ነክቶ
የተቀሠፈውን ታውፋንያ ታሪክ
እንጠቅስ ነበር፡፡
‹የመቅደስህ ታቦት› ማለት
መቅደስ የተባለው የሰውነትህ ማደሪያ እናት
ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ ሰውነቱን ‹ይህን
መቅደስ አፍርሱት› አላለምን? ‹በጉ መቅደስዋ ነው› ተብሎ
አልተጻፈምን? ስለዚህ ‹አቤቱ
ወደ ዕረፍትህ ተነሥ
አንተና የመቅደስህ ታቦት›
ማለት ጳውሎስ ወደ
ዕረፍቱ ለመግባት እንትጋ
እንዳለው ‹‹ጌታ ሆይ
‹ዕረፍትህ› ወደተባለ ወደ
ሰማያት አንተ ብቻ
ተነሥተህ አትቅር የመቅደስ ሰውነትህ ማደሪያ
እናትህንም ይዘህ ተነሥ››
ማለት ነው፡፡
የእመቤታችን ትንሣኤ ብዙዎችን ማከራከሩ እንዴት
ያሳዝናል? ክርስቶስ ‹ትንሣኤና ሕይወት እኔ
ነኝ› ብሏል፡፡ እውነት
ትንሣኤን ለወለደች እናት
መነሣትዋ ትልቅ ነገር
ነው? የሕይወት እናት
ሕያው ሆነች ቢባል
ያስቆጣልን? ሞትን የሞተው
በልጅዋ አይደለምን? የሕይወትን እናት ሞት
ይዞ አስቀራት ማለት
ደስታ የሚሠጠው ለሞት
አበጋዞች ነው፡፡ ‹‹አምላክ
ያደረባት የምትናገር ታቦት
ፈርሳ ቀርታለች ማለት
፣ ታቦተ ጽዮን
ድንግል በሞት ፍልስጤም ተማርካ ቀርታለች›› ማለት የሚያስደስተው በማኅፀንዋ ፍሬ
የተፈረካከሰው ዲያቢሎስ ነው፡፡ ለእኛ
ለኦርቶዶክሳውያን የሚደንቀን መሞትዋ እንጂ
መነሣትዋ አይደለም፡፡
ቅዱስ ያሬድ ‹‹የማርያም ሞት ግን
ሁሉን ያስደንቃል›› እንዳለው ሕይወትን ያስገኘች ድንግል ፣
አምላክን የታቀፉ ክንዶች
፣ የእግዚአብሔር ዙፋን
የሆኑ ጉልበቶች በሞት
መሸነፋቸው ያስደንቀናል፡፡ መነሣትዋ ግን የምንጠብቀው ነው፡፡ አልዓዛርን ‹አልዓዛር አልዓዛር› ብሎ ያስነሣ
ጌታ ፣ በዕለተ
ዓርብ በሞቱ ብዙ
ሙታንን ያስነሣ ጌታ
እናቱን አስነሣ ሲባል
የሚቆጡ እንዴት ያሉ
ናቸው?
ሁለቱ ምስክሮች የተባሉ
ሄኖክና ኤልያስ ወደ
ምድር መጥተው አስተምረው ከተገደሉ ‹‹ከሦስት
ቀን ተኩል በኋላ
ከእግዚአብሔር የወጣ
የሕይወት መንፈስ ገባባቸው በእግሮቻቸውም ቆሙ…
በሰማይም ፡- ወደዚህ
ውጡ የሚላቸውን ታላቅ
ድምፅ ሰሙ ፤
ጠላቶቻቸውም እየተመለከቱአቸው ወደ
ሰማይ ወጡ›› ይላል፡፡ (ራእ. 11፡4-12) ሄኖክና ኤልያስን ከምጽአቱ በፊት
ዳግም ላይሞቱ ከሞት
አስነሥቷቸው በጠላቶቻቸው ፊት
ወደ ሰማይ የሚያሳርጋቸው አምላክ እናቱን
በወዳጆችዋ ፊት አስነሥቶ አሳርጓታል ሲባል
በቁጣ መቃወም ምን
ይባላል?
እንደልጅዋ በራስዋ ዐረገች
(Ascension) በማለትና ልጅዋ
ወደ ራሱ ነጥቆ
ወሰዳት (Assumption) በማለት
መካከል ያለውን ልዩነት
መረዳት ከቻልን የእመቤታችን ማረግ ምኑ
ያከራክራል? ዝናምን ከከለከለው ኤልያስ ንጹሑን
ዝናም ያስገኘችው ድንግል
አትበልጥምን ፣ አካሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር
ካደረገው ሄኖክስ ይልቅ
ለእግዚአብሔር ማደሪያ
የሆነችው እመ አምላክ
አትበልጥምን?
እኛ ግን ቅዱስ
ኤጲፋንዮስ ‹‹በሞትዋ ምድር
መራራ ኀዘን ስታዝን
በሰማይ ደስታ ሆነ
እንዳለ›› እመቤታችን ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዓለም ስትሸጋገርም ሆነ ፣
በልጅዋ ሥልጣን ተነሥታ
ስታርግ በሰማይ የሚኖረውን ደስታ በእምነት እናስተውላለን፡፡ ያ
ደሃ አልዓዛር እንኳን
ሲሞት መላእክት ነፍሱን
ወደ አብርሃም አጅበው
ወስደውት ነበር ፣
ኤልያስም ሲያርግ መላእክት በእሳት ሰረገላና በእሳት ፈረሶች
ነጥቀውት ነበር፡፡ የአምላክን እናት ዕርገት
ስናስብ ከዚህ በላይ
ዝማሬ ይታየናል ፤
ቅዱስ ቴዎዶስዮስ እንደጻፈው ቅዱስ ያሬድም
‹በመሰንቆሁ እንዘ የሐሊ›
እንዳለው አባትዋ ዳዊት
‹አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና
የመቅደስህ ታቦት› እያለ
እየዘመረ ወላዲተ አምላክ
ወደዚያኛው ዓለም ተሸጋግራለች፡፡ ኤልያስ ወደ
ሰማይ ሲነጠቅ መጎናጸፊያውን ለበረከት እንዲሆነው ለደቀ መዝሙሩ
ኤልሳዕ እንደሠጠው እመቤታችንም በልጅዋ ሥልጣን
ወደ ሰማይ ስታርግ
መግነዝዋን (መታጠቂያዋን) ለቶማስ
በመሥጠትዋ ኦርቶዶክሳዊያን አብያተ
ክርስቲያናት አሁንም ድረስ
ተከፋፍለው በታላቅ ፍቅር
በረከትዋን ይቀበሉበታል፡፡
እኛ ኦርቶዶክሳዊያን ስለ
እመቤታችን መነሣት ስናስብ
የምንጠይቀው ‹ተነሣች ወይስ
አልተነሣችም ፤ ወደ
ሰማይ ዐረገች ወይንስ
ዐላረገችም› ሳይሆን ‹በሰማይ
የተደረገላት አቀባበል ምን
ይመስል ይሆን?› ብለን
ነው፡፡ ደሃው አልዓዛር በሞተ ጊዜ
መላእክት ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት
ከተባለ የአምላክን እናት
ምን ያህል አጅበዋት ይሆን? ወደ
ሰማይ ማረግ ለእርስዋ ቁምነገር አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሰማይን
በእጆቹ የሚይዘውን አምላክ
በእጆችዋ የያዘች ሁለተኛ
ሰማይ ናት፡፡ እርስዋ
ወደ ሰማይ በማረግዋም ዕድለኛዋ እርስዋ
ሳትሆን ሰማዩ ነው፡፡
ሰማይ ዙፋኑ ነው
፣ ምድርም የእግሩ
መረገጫ ናት ድንግል
ማርያም ግን እናቱ
ናት፡፡ ከእናትና ከዙፋን
እናት ትበልጣለች፡፡ ቅዱስ
ያዕቆብ ዘሥሩግ እንዳለው ሰማይ አልወለደውም ፣ አላሳደገውም ፣ አላጠባውም ድንግል ግን
ይህንን ሁሉ አድርጋለች፡፡ ስለዚህ ወደ
ሰማይ ማረግዋ ክብሩ
ለሰማዩ እንጂ ለእርስዋ አይደለም፡፡
እመቤታችን ወደ ሰማይ
ስታርግ በእርግጥ አቀባበሉ እንዴት ይሆን?
እኛ የሰው ልጆች
እናታችንን ማክበርም መጦርም
የምንችለው በምድር እስካለችና እኛም እስካለን ድረስ ነው፡፡
‹እናትና አባትህን አክብር›
ያለን ፈጣሪ ግን
እናቱን ማክበር የሚችለው በምድር ብቻ
ሳይሆን በሰማይም ጭምር
ነው፡፡ እናቱ ወደ
እርሱ ስትመጣ መድኃኔዓለም ክርስቶስ እንዴት
ተቀብሏት ይሆን?
ንጉሥ ሰሎሞን እናቱ
ቤርሳቤህ ወደ ቤተ
መንግሥቱ በመጣች ጊዜ
ያደረገውን እናስታውስ፡፡ ‹‹ንጉሡም
ሊቀበላት ተነሣ ሳማትም
፤ በዙፋኑም ተቀመጠ
፤ ለእናቱም ወንበር
አስመጣላት በቀኙም ተቀመጠች፡፡ እርስዋም ፡-
አንዲት ታናሽ ልመና
እለምንሃለሁ አታሳፍረኝ አለች፡፡ ንጉሡም ፡-
እናቴ ሆይ አላሳፍርሽምና ለምኚ አላት››
ተብሎ ተጽፎአል፡፡ (1ነገሥ.
2፡19-20) ከዳዊት ሆድ
ፍሬ በዙፋኑ ላይ
ከተቀመጠው ንጉሥ ሰሎሞን
ይልቅ በዳዊትን ዙፋን
ለዘለዓለሙ ይነግሣል የተባለለት ክርስቶስ ይበልጣል፡፡ ስለ ክርስቶስ ‹‹ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ››
ተብሎ ተጽፎአል፡፡ (ማቴ.
12፡42) ክርስቶስ ከሰሎሞን የሚበልጥ ከሆነ
የክርስቶስ እናትም ከሰሎሞን እናት ትበልጣለች፡፡ ሰሎሞን ለእናቱ
ከሠጣት ክብርም በላይ
ክርስቶስ ለእናቱ የሚሠጣት ክብር ይበልጣል፡፡ የሰሎሞን ቤተ
መንግሥት በምድር ነው
፤ የክርስቶስ ቤተ
መንግሥት ግን በሰማይ
ነው፡፡ መድኃኔ ዓለም
ወደ ሰማያዊው መንግሥቱ እናቱን በጠራት
ጊዜ እንደምን ተቀብሏት ይሆን? እንደ
ሰሎሞን እናት ወንበር
አስመጣላት እንዳንል በሰማይ
መቆም መቀመጥ የለም፡፡ ነገር ግን
‹‹የወርቅ ልብስ ተጎናጽፋ ንግሥቲቱ በቀኝህ
ትቆማለች›› ተብሎ ድንግሊቱ ስለተሠጣት ክብር
ተጽፎአል፡፡ ወርቅ መልበስዋ አነሳት የሚል
ካለ ደግሞ ‹‹አሕዛብን በብረት በር
የሚገዛቸውን ወንድ ልጅ
የወለደችው›› ድንግል ‹‹ፀሐይን
ተጎናጽፋ ፤ ጨረቃም
ከእግሮችዋ በታች የሆነላት ፣ ዐሥራ
ሁለትም ከዋክብት አክሊል
የሆኑላት አንዲት ሴት
ነበረች›› ተብሎ ተጽፎላታል፡፡ (መዝ. 44፡9 ፣ ራእ.
12፡1)
ለእኛ ለኦርቶዶክሳዊያን ድንግል
ወደማያልፈው ዓለም ስትሸጋገር የነበራትን የክብር
አቀባበል በሕሊናችን ከማሰብ
በቀር ምን የሚያውከን ነገር የለም፡፡ ቅዱስ ገብርኤል ድንግልን ምን
ብሎ ተቀብሏት ይሆን?
እዚህ ‹ጸጋን የተሞላሽ ሆይ ደስ
ይበልሽ› ብሎ ሰላምታ
ያቀረበላት ይህ መልአክ
ጸጋን የተሞላችው ወደ
እርሱ ስትመጣ ምን
ብሎ ተቀብሏት ይሆን?
ቅድስት ኤልሳቤጥስ አሁንም
‹ወደ እኔ ትመጪ
ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?› ብላት ይሆን?
መጥምቁስ ዳግም በሰማይ
በደስታ ዘልሎ ይሆን?
ነቢያቱ ድንግልን እንዴት
ተቀበሏት? ኢሳይያስ ‹ትፀንሳለች› ያላትን ድንግል
ሲያያት ምን ይል
ይሆን? ሕዝቅኤልስ ‹የተዘጋችዋ ደጅ› ወደ
እርሱ ስትመጣ ምን
አለ? ጌዴዎን ጸምሩን
፣ ኤልሳዕ ማሰሮውን ፣ አሮን
በትሩን ፣ ኖኅ
መርከቡን ባየ ጊዜ
ምን ብሎ ይሆን?
ሙሴስ ያልተቃጠለችው ዛፍ
ወደ እርሱ ስትመጣ
ዳግም እንደ ሲና
ተራራው ጊዜ ጫማውን
አውልቆ ይሆን? አዳም
የልጅ ልጁን ሲያይ
ሔዋንስ ዳግሚት ሔዋንን
ስታይ ምን ብላ
ይሆን? ሁሉንም በሰማይ
ለመረዳት ያብቃን!
No comments:
Post a Comment