Wednesday, September 4, 2019

ከገጠመን ችግር ለመውጣት በፍጥነት ልናደርገው የሚገባን ምንድን ነው?

በመምህር ብርሃኑ አድማስ
(ከመጽሐፈ ገጹ የተወሰደ)
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ነሐሴ 29 ቀን 2011 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡

ባለፉት ስምንት ዐመታት (ከቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ እና ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዕረፍት) ወዲህ ኢትዮጵያ ባልተቋረጠ የለውጥ፣ የውዝግብና የነውጥ ሂደት ውስጥ ትገኛለች፡፡ ሁለቱም ታላላቅ መሪዎች ያረፉት በዘመነ ዮሐንስ ማጠቃለያ ወር ላይ ነበር፡፡ የእነርሱን ዕረፍት ተከትሎ እንዳሁኑ ጎልቶ ባይነገርላቸውም ብዙ ለውጦችም ነውጦችም በተከታዮች ዐመታት ውስጥ ነበሩ፡፡ ከዐራት ዐመታት በኋላ ልክ በዘመነ ዮሐንስ ደግሞ አሁን ላለንበት ለውጥም እንበለው ምስቅልቅል የዳረገን አብዮት ተቀሰቀሰ፡፡ አሁን ባለቤቱ እኔ ነኝ እኔ ነኝ የሚባልለት ሕዝባዊ ጫናን መሣሪያ ያደረገ (ከየት እንደሆነ ግን ከግምት በቀር ብዙዎቻችን በትክክል የማናውቀው) ለውጥ ተፈጠረ፡፡ አራቱን ዐመታትም የማንጠበቃቸውና ሊተነበዩ የማይችሉ ተከታታይ ለውጦች ከጥፋቶችና ምስቅልቅሎች ጋር በሀገራችን ተከሰቱ፡፡ ሁኔታዎቹም ለከፊሉ ደስታ ለከፊሉም ሐዘን የሆኑበት ብዙም ሳይቆይ ደግሞ ደስታና ሐዘን በፍጥነት የተፈራረቁበት ሆነ፡፡ እንዲህ ያሉ ክስተቶች ሳያቋርጡ ያለፉበት የዐራት ዐመታት አንድ የለውጥ ወቅት ሊፈጸም ሳምንታት ብቻ ቀርተውታል፡፡

ከርሞ ደግሞ እንደገና ዘመነ ዮሐንስ ይጀምራል፡፡ በእኔ እምነት ይህኛው ዘመነ ዮሐንስ ደግሞ ካለፉት ጠንከር ያሉ ያልተጠበቁ ነገሮች ሊከሰቱበት ይችላሉ የሚል ግምትን ይዣለሁ፡፡ ምን አልባትም ክፉውም ሊጨምር ይችል ይሆናል፡፡ በዚህኛው የዘመነ ዮሐንስ ዙር እንጨርሰው አንጨርሰው ለመናገር እውነተኛ ሀብተ ትንቢት የሚጠይቅ ቢሆንም ወደ አንድ መቋጫ የምንሔድበት ምዕራፍ ላይ መድረሳችንን ለመረዳት ግን ካሳለፍናቸው ሒደቶች ብቻ መረዳት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ምን ይሆን መድረሻችን? አልፎ ያየው የታደለ ይመስለኛል፡፡ ይህ ሁሉ ግን ማለፉ ብቻ ሳይሆን ተከስቶ እንደነበር እንኳ እስኪረሳ ድረስ ለማለፍ መቃረቡን እኔ በግሌ አምናለሁ፡፡

እየሆነ ያለውን ሁሉ ደግሞ ከልቡ በእኛ የፖለቲካ ፕሮግራም ነው፣ ወይም በዚህ ዕቅድ መሠረት ነው ማለት የሚችል አንድም አካል ያለ አይመስለኝም፡፡ ሁኔታውንና አጋጣሚውን ተጠቅሞ የለውጥ መሪና ፊታውራሪ ለመምሰል በፕሮፓጋንዳ መድከምና ለውጡን አቅዶ ማምጣት በእጅጉ የተለያዩ ናቸውና፡፡ እኔ በግሌና እኔን የሚመስሉት ሁሉ ከላይ በአጭሩ ከጠቀስኳቸው ሁነቶች ጋር ሁኔታውን የእግዚአብሔር ፍርድ ወይም ጣልቃ ገብነት ነው የምንለው ከላይ በተደረደሩትና ብዙ ሰው በማያስታውላቸው ግን ማንም በማይለውጣቸው ሒደቶች ውስጥ እያለፍን ነው ብለን ስለምናምን ነው፡፡ የሂደቱ ተሳታፊዎችን እኔ በግሌ እንደ ገጸ ባሕርይ ብቻ ነው የማያቸው፡፡

በርግጥ ይህ ሃሳቤ የማይዋጥላቸው የእግዚአብሔርን ጣልቃ ገብነት አለ የሚለውን የሚሞግቱ ብዙ አካላት መኖራቸውንም አውቃለሁ፡፡ የመጀመሪያዎቹ ስለ እግዚአብሔርን ጣልቃ ገብነት የራሳቸው ምናባዊ ሥዕል ይኖራቸውና ከምናባቸው ጋር አልገጥም ሲላቸው ለመቀበል የሚቸገሩት ናቸው፡፡ እንዲህ ዐይነት ሰዎች ለእነርሱ ክፉ የሚመስሏቸው እየኖሩ ደግ የሚመስሏቸው የሞቱ የተጠቁ ሲመስላቸው እግዚአብሔር አልታያቸው ይላል፡፡ በዚያውም ላይ እግዚአብሔር እንደ መብረቅ ድብልቅልቅ አድርጎ እርሱ መሆኑን ለሁሉም አሳይቶ ጸጥ ለጥ አድርጎ ልክ እንደ ወታደርም እንደ መንግሥትም ሆኖ ኅሊናቸው የሚጠብቀውን አለማድረጉ የአግዚአብሔር ጣልቃገብነት እንደሌለ እንዲቆጥሩ የሚደርጋቸው ናቸው፡፡ ለእኔ እንደሚገባኝ እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔር ያልሠራ የመሰላቸው እነርሱ የመደቡለትን ባለማድረጉ ብቻ ነው፡፡ እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች ሌላው ቀርቶ ክፉ ሰዎች መሾማቸው፤ አንዳንዶች እያታለሉ መቀጠላቸው፣ወዘተ የመሰሉትን እየጠቀሱ እግዚአብሔርማ ቢኖር እንዲህ አይረግም ነበር ይላሉ፡፡

ክፉና አታላይ ሰዎችን እግዚአብሔር በሒደት ውስጥ እንደሚፈቅድላቸው የሚያሳዩ የቅዱስ መጽሐፍ ታሪኮችም ትዝ አይሏቸውም፡፡ ለእኔ እነዚህ ሁኔታዎች እንዲያውም እግዚአብሔር ጣልቃ ለመግባቱ ምልክቶች ሊሆኑም ይችላል፡፡ ለምሳሌ ከእሥራኤል ስደት በፊት የዮሴፍን መሸጥ፣ ከዳዊትም በፊት የሳዖልን መንገሥ መመርመር ለዚህ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ ካስፈለገም የሐማ ተንኮል የፈጠረው ድንጋጤ ለኋላው ነጻነት ያደረገውን አስተዋጽኦ ማሰብ ይቻላል፡፡ ወይም ደግሞ እንደ አኪጦፌል ያለውን ተንኮለኛ እንደኩሲ ባለ ሌላ ተንኮለኛም የሚጥለው መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ አኪጦፌልን የመሰለ ተንኮለኛ ለመጣል የግድ ደግ ሰው ነው የሚያስፈልገው ማለት አይቻልምና፡፡ እነዚህና ሌሎች ታሪኮች የሚነግሩን እግዚአብሔር ጣልቃ ሲገባ ደጎችንና ለእኛ ኅሊና የሚስማሙ ክስተቶችንና ግለሰቦችን በማሳየት ብቻ ሳይሆን ክፉ የሚመስሉን ሁኔታዎችን፣ ሰዎችን፣ መሪዎችን ሁሉ ጭምር ይጠቀማል፡፡

ሌሎች ሰዎች ደግሞ ስለ እግዚአብሔር ጠባቂነት መናገር ዜጎች ድርሻቸውን እንዳይወጡ የሚያዘናጋ ነው ብለው የሚሰጉት ናቸው፡፡ ይልቁንም ከፍተኛ ኃላፊነት ያለባቸው ሰዎች ይህን የሚደግፉ ከሆነ ሥራቸውን እግዚአብሔር አለ ብለው በመተው ሀገርን ለአደጋ ሊያጋልጡ ይችላሉ የሚል ሥጋት ያይልባቸዋል፡፡ የእነዚህን አካላት ሥጋት በአክብሮት የምወስድ ብሆንም እኔ የማምነው ግን የእግዚአብሔር ጣልቃገብነት የፈለጉትን እያደረጉ ወይም ተንኮልና ሤራቸውን ወይም ቸልተኝነታቸውን በእግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት አመካኝተው የሚያላግጡትን ሰዎች ሀሳብ የያዘ አይደለም፡፡ እንደዚያ ዐይነቱን ንግግር እኔ የማየው ልክ እንደ ሐሰተኛ ትንቢት ነው፡፡ ምክንያቱም እንደዚያ ዐይነት ንግግሮች ታሳቢ ያሚያደርጉ ሰዎች በርግጥ በንግግራቸው ከልብ የሚያምኑ ከሆነ ራሳቸውን ከምንም ዐይነት ሸፍጥ፣ ማስመሰልና አድሎ ስለሚያጸዱ ሕዝብም ሊቀበላቸው አይቸግረውም ብዬ አስባለሁ፡፡ ንግግራቸው ከሥራቸው ሳይገጥም የሚናገሩት ከሆነ ግን ለእኔ የሚመስለኝ የንግግሩ ዐላማ የራስን ሥራ (የተንኮልና የሸፍጥ ሥራዎችን ጨምሮ ከፉና ደጎችን ሁሉ) ሕዝብ የእግዚአብሔር አድርጎ እንዲቀበልላቸው በማሰብ የተቀባይነት ማግባቢያዎች አድርጌ ነው፡፡ ይህ ደግሞ መቅሰትን ከማፋጠን ያለፈ ተግባር የሚኖረው አይመስለኝም፡፡

ሦስተኛዎቹ ደግሞ የእግዚአብሔርን ኃይል በመጠራጠር ሳይሆን ኢትዮጵያን ብቸኛ (exceptional) አድርጎ እግዚአብሔር እንዲያስባት የሚያደርግ ምክንያት አይታየንም የሚሉ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ተፈጥሮአዊና የሚጠበቅ የማያስነቅፍ ነገር ከመሆኑም በላይ እውነትነትም አለው፡፡ የእኔና የእኔ ቢጤዎች እምነትም የሚመነጨው ይህን ካለመረዳት ወይም ኢትዮጵያ ብቻ ልዩ (exceptional) ነች ከሚለው ብቻ አይደለም፡፡ ልዩ ሀገር የሚያሰኛት ነገር መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚያ ይልቅ በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች ሀገሮች እግዚአብሔር ጣልቃ እንዲገባ የሚያስገድድ ልዩ ነገር መኖሩን ከመቀበል ላይ ነው፡፡

ይህ እግዚአብሔርን ጣልቃ እንዲገባ የሚያደርገው ሁኔታ በሀገራችን እንዳለ ደግሞ አውቃለሁ፤ መሪዎቻችንና የፖለቲካ ተዋናዮችን ስለመጨመሩ ባላውቅም እግዚአብሔርን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ጣልቃ እንዲገባ የሚስገድደው ነገር እንዳለ ግን እኔ በግሌ በርግጠኝነት አምናለሁ፡፡ ርግጠኝነቴ የሚመነጨውም አንዳንዶች ከሚጠረጥሩት ወይም ከሚሰጉት ሐሰተኛ ራዕይ ወይም በመገለጥ ሰበብ የሚነገር ከሚመስለኝ ቅዠት እንዳልሆነ ማረጋገጥ እፈልጋልሁ፡፡ ልዩ ናት የሚለውንም ለምን እንደማልተው ከማስቀደም ልጀምር፡፡

እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ከሆነ እሥራኤልና ኢትዮጵያ የተለዩ ሀገሮች ናቸው፡፡ እሥራኤል በተለይ በብሉይ ኪዳን፤ ኢትዮጵያ ደግሞ በተለይ በሐዲስ ኪዳን፡፡ ስለ እሥራኤል ያለውን ትቼ ስለኢትዮጵያ ያለውን ግን ትንሽ ላቅርብ፡፡ የሙሴ ሚስት ኢትዮጵያዊት የሆነችው በአጋጣሚ አልነበረም፡፡ ከሌላ ወገን አትጋቡ የሚለውን ትእዛዝ ከእግዚአብሔር ተቀብሎ ለሕዝቡ ያስተላለፈው ሙሴ ይሄን ሲፈጽም አንተ ልዩ (exceptional) ልትሆን አትችልም ብለው የተቃወሙት አሮን ወንድሙና ማርያም እህቱ በአግዚአብሔር የተቀጡት ዝም ብሎ አልነበረም፡፡ ሙሴ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው የክርስቶስ ምሳሌ ስለሆነ ክርስቶስ በሥጋ በተገለጠ ዘመን ከእሥራኤል ይልቅ በሌሎች ይልቁንም ኢትዮጵያ አማናዊ ምሳሌ የምትሆንበት ድንቅ ምልክት ስለሆነ ነበረ እንጂ፡፡ ንግሥተ ሳባ ኢየሩሳሌም ሄዳ አሁንም የክርስቶስ ምሳሌ የሆነውን ሰሎሞንን አግኝታ ከዚያም የተነሣ በታሪካችን ትልልቅ የሆኑ ነገሮች (ታቦተ ጽዮንን ጨምሮ) ወደ እኛ የመጡት ዝም ብሎ አይደለም፡፡ እነዚህን ታሪኮችና ሌሎች ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ታሪኮችንና ምሳሌዎችን አስመልክተው አብራርተው የጻፉት እነ ኦሪገን፣ ዮሐንስ አፈወርቅና ሌሎች ሊቃወንትም ኢትዮጵያን ልዩ መሆኗንና ገልጠው ገና 2ኛው መቶ ዐመት ጀምረው ያሰተማሩት ሁነቶቹ ቀላል ስላልሆኑ ነው፡፡

ይህ ማለት ግን ልዩ ስለሆነች ምንም ችግር ዐይነካትም ማለት ደግሞ አይደለም፡፡ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በስፋት የሚነግሩን እግዚአብሔር እሥራኤልን እንድታሸንፍ መርዳቱን ብቻ ሳይሆን ከፈቃዱ ስትወጣ ደግሞ ለአሰቃቂ መከራዎችም አሳልፎ ይሰጣት እንደነበርና በንስሐ ስትመለስ ደግሞ እንዴት ወደ ክብር እንደሚመልሳትም ጭምር ነውና፡፡ የኢትዮጵያም እንዲሁ ነው፡፡ በታሪካችን ውድቀቶቻችንም ሆኑ ትንሣኤዎችቻን ካልተጠበቁ ሁኔታዎች የሚነሡ መሆኑን የታሪክ አጥኚዎች ሳይቀሩ የመሰከሩለት ጉዳዩ ከአምላክ ጣልቃ ገብነት ጋር በእጅጉ የተያያዘ ስለሆነ ነው፡፡

ከዚህም በላይ ደግሞ እግዚአብሔር በየትኛውም ሀገር ጣልቃ የገባባቸው ታሪኮች ብዙዎች ናቸው፡፡ የአግዚአብሔር ማዳን በግልጽ የሚታየው ደግሞ እርሱ ጣልቃ እንዲገባ የሚያስገድዱ የአማኞች ሁኔታዎች በየሀገሮቹ ሲኖሩ ነው፡፡ ከእነዚያ ምሳሌ ለማምጣት አሁን ቦታውም ጊዜውም አይፈቅድም፡፡ በኢትጵያም ከቅጣት ባለፈ እግዚአብሔርን ጣልቃ ገብቶ ከፍጹም ጥፋት እንዲያድናት የሚያስገድድ ሁኔታ በእኛ ዘመንም መኖሩን ግን እኔ በግሌ የማውቀውም የማምነውም ነገር ነው፡፡ በዚህ እውቀትና እምነት የሚስማሙ ብዙዎች መኖራቸውንም ደግሞ አውቃለሁ፡፡ የዚህን ዕወቀቴን ምንጭ ግን መናገር አያስፈልገኝም፡፡ በርግጠኝነት ግን አውቃለሁ፡፡ አዎን ድፍን ያለ አውቃለሁ ለመቀበል የሚያስቸግር ብቻ ሳይሆን ሊያስገምትና ሊያሰተች ቢችልም ለዛሬ ግን ከዚህ ውጭ አማራጭ የለኝምና እምነቴን በመግለጽ ብቻ እተወዋለሁ፡፡ ይህ እንዳለ የማውቀው ነገር ደግሞ እግዚአብሔርን እንዲረዳን እንዲያስገድድ አምናለሁ፡፡ ስለዚህም በርግጠኝነት ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ መንገድ እንደምትሔድ ከተስፋ በላይ አምናለሁ፡፡ በዚህ ጊዜ ተሻግረው የሚገኙትን ሰዎች የሚያውቀው ግን እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ይህን የማያምኑ ሰዎች መኖራቸውም እንደማያስቀረውም አምናለሁ፤ ይህንንም ኖረው የሚያዩት ደጋግመው የሚመሰክሩት ሀቅ ይሆናል፡፡

ታዲያ ይህ ሁሉ ለምን ይደርስብናል?

አንዳንድ ሰዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች በተገናኘን ቁጥር ከሚያሳስቧቸው ጭንቀቶች አንዱ ይህ ሁሉ ግፍና መከራ፤ ስደት፣ መፈናቀል፣ ግጭት፣ ሞት፣ የአብያተ ክርስቲያን ቃጠሎ፣ የሰዎች መለዋወጥ፣ለምን ይደርስብናል የሚለው ነው፡፡
ለዚህ ሁሉ ጉዳታችን እውነተኛውና የማያወላዳው ምክንያት በአንድ ነገር ሊጠቃለል የሚችል ይመስለኛል፡፡ ከአባቶቻችን ዘመን ጀምሮ እስካሁን እኛን ጨምሮ እግዚአብሔርን በእጅጉ በድለናል፤ አጥፍተናል በሚለው፡፡ አሁን መዘርዘር የማያስፈልገኝ ብዙዎቻችንም በደንብ የምናውቃቸው በደሎቻችን ብቻ ከጽዋ አይደለም ከጋን ሞልተው ፈስሰዋል፡፡ የማናውቀው በደላችን ደግሞ እጅግ ብዙ ሊሆን ይችላል፡፡ እውነቱን እንነጋር ከተባለ ኢትዮጵያ የብዙ ስውራን ቅዱሳን ሀገር በመሆኗ በእነርሱ ጸሎትና እኛ እናውቅልሃለን በምንለው በብዙው ገጠሬ የዋሕ ሕዝብ ቅንነትና ትዕግሥት ትኖራለች እንጂ እንደ እኛማ ቢሆን ከዐሥር በላይ ብነከፋፈልና ብንጠፋፋ እንኳ ይገባን ነበረ፡፡ ሌላው ቀርቶ ዝርክርክ ምግባረ ቢስነታችንን ትተን ሃይማኖትን እንደ ርእዮተ ዐለምና እንደፖለቲካ መሣሪያ ብቻ ለመጠቀም የሚዳዳን ሰዎች የምናደርገው ድርጊት ብቻ ስንት መዐትና ቁጣ ሊያመጣብን የሚገባ ነበር፡፡ ስለዚህ ማንኛችንም ሌላውንና የትኛውንም ነጥለን ተጠያቂ የምናደርግበት ምንም ዐይነት ሃይማኖታዊ ምክንያት ቢያንስ ለእኔ ፈጽሞ አይታየኝም፡፡ ከእኛ የባሱ የሚመስሉን ሰዎችም መባሳቸው የተረጋገጠ እንኳ ቢሆን አብረን ባጠፋነው ጥፋት የጉዳቱ ቀዳሚ ሰለባዎች ከመሆናቸው ያለፈ የተለየ ነገር አይታየኝም፡፡ የአንድን በሽታ ቫይረስም ሆነ ባክቴሪያ ቀድሞ የተሸከመ ስናይ ደግሞ በሽታውንና በሽተኛውን በመለየት እርሱን በማዳን እኛንም ማትረፍ ይገባናል እንጂ ለቫይረሱና ለባክቴሪያው ጉዳት ተጎጂውን ተጠያቂ ማድረግ አይገባንም፡፡

ስለዚህ ለወቅታዊ ችግራችን መፍትሔው አሁን እንደምናደርገው በመካሰስ፣ በመነቃቀፍና በመወነጃጀል ብቻ የሚመጣ አይመስለኝም፡፡ በአክቱቪዝምና በአድቮካሲ ወይም በተቋርቋሪነት መንፈስ ምንም ያህል ብንተጋና ብንጋደል የምንፈልገውን ውጤት ለማምጣት ይቻለናል ብሎ ለማሰብ በግሌ እቸገራለሁና፡፡ ወደ ጠቃሚ መፍትሔ ማምራት የምንፈልግ ከሆነ ልንጀምርበት የሚገባውን ቀዳሚ ነገር መርሳት ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ከችግሮቻችን ወጥተን በተሻለ ሁኔታ ላይ ለመገኘት ያስችላሉ ብዬ እንደ መፍትሔ የማስባቸውን እንደሚከተለው በአጭር በአጭሩ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡

የመፍትሔ ጥቆማዎች

1) ብሔራዊ /ዐለም አቀፋዊ/ ንስሐ

በእኔ እምነት ችግሮቻችን የበደሎቻችን፣ የጥፋቶቻችን፣ የስሕተቶቻን፣ የድንቁርናችን ውጤቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ የሚያስፈልገን በእውነት ጥፋተኝነታችንን ማመንና ከልብ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው፡፡ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ፣ ከሊቃነ ጳጳሳት እስከ ምእመን፣ ከሊቅ እስከ ማይም፣ ሁላችንም መበደላችንን ዐለም ራሱ ያውቃል፡፡ ታሪክም ይመሰክርብናል፡፡ እንኳን ዛሬ ጥንትም አባቶቻችን ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ወዳጅነት አጽንተው የሚዘልቁት በእውነተኛ ተነሣሂነት ነው፡፡ ለመሆኑ እውነተኛ ብሔራዊ ንስሐ የምትለው ምንድን ነው የሚለኝ ቢኖር፡-

) ንስሐን እውነተኛ የሚያደርው የመጀመሪያው እንኳን በሕይወት ስላሉ በታሪክ ስለምናውቃቸው ስለየትኞቹም ሰዎች ከልባችን ምሕረትን ከመለመን በቀር ምንም ዐይነት ነገርን አለመመኘትና እንዳጠፉ ብናስብ እንኳ ይቅር ማለት አለብን፡፡ በቅዳሴያችን ሁልጊዜ በምልጃ ከምናቀርባቸው ጸሎቶች አንዱ "እግዚአብሔር እንዳይቀየማቸው ከመዓትም ተመልሶ ፍጹም ዕረፍትን ይሰጣቸው ዘንድ ስለበደሉ አባቶቻችንና ወንድሞቻችን እንማልዳለን" የሚለው የተካተተው እኛ ባናስታውለውም ክርስቲያን ልቡ ከዚህ መንፈስ መውጣት ስለሌለበት ነው፡፡ እኛ ግን እንኳን ከልባችን ስለበደሉት ልንለምን ይቅርና ስላለፉ ሰዎች ምን እያልን እንደምንጽፍ ለሚያይ ሰው እንኳን እግዚአብሔርን አንዳንዱ ነገራችን ሰይጣንንም የሚያስደንቅ ይመስለኛል፡፡

ለ) ሁለተኛው እውነተኛ የሚያደርገን አሁንም በቅዳሴያችን ላይ "ስለ ዐለም ሁሉ እግዚአብሔር ማሰብን ያስቀድም ዘንድ ለእያንዳንዱም የሚያስፈልገውን ያማረውን የሚሻለውንም ያስብ ዘንድ ስለ ዐለም ሁሉ እንማልዳለን" እያልን ደጋግመን በየዕለቱ እንደምንጸልየው በዚሁ መንፈስ በእውነት መለመን አለብን፡፡ ከጥቅሱ እንደምንረዳው ክርስቲያን ሁሉ ግዴታው ስለ ዐለም ሁሉ ማማለድና ጌታችን በመስቀል ላይ እንዳደረገው ዐለምን ከእግዚአብሔር የማስታረቅ ኃላፊነት መቀበላችንን መርሳት የለብንም፡፡ ጎላ ብሎ የተሠመረበትን ስናየው ደግሞ ምልጃችን የሚፈልጉትን ሳይሆን የሚያስፈልጋቸውን፣ እነርሱ ያማራቸውን ሳይሆን በእግዚአብሔር ፊት ያማረውን (ማንንም የማይጎዳውን) እንዲሁም ዐለምና ሰዎች የሚመኙትን ሳይሆን ለሁላችንም የተሻለውን እንዲያስብልን መሆኑን ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ በዚህ ከልብ አምነንበት የምናስቀድስና የምንጸልይ ከሆነ ጽሑፎቻችንና ንግግሮቻችንም ሌላ መንፈስ ሊጠናወጣቸው አይገባም፡፡ ከቅዳሴያችን ባሻገር ያሉ የመስተብቁዕና የምልጃ ጸሎቶቻችን በሙሉ በዚሁ መንፈስ የተቃኙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል በዐርብ የሊጦን ጸሎታችን ላይ "አድኅን እገዚኦ ዛተኒ ሀገረ፤ ወካልአተኒ አህጉረ ወበሐውርተ እለ በሃይማኖተ ዚአከ የኀድሩ ውስቴቶን - አቤቱ ይህችን (የምንኖርባትን) አገር አንተን በማመን የሚኖሩባቸውን በዐለም ያሉ ሌሎች ሀገሮችን ሁሉ አድን"እያልን የምንጸልየውን ማንሣት ይቻላል፡፡ እነዚህ እንግዲህ ለማሳያ ያህል ብቻ ናቸው፡፡ ስለዚህ እውነተኛ ንስሐ ማለት ቃለ እግዚአብሔራችን፣ ቅዳሴያችን፣ ጸሎታችን እንደሚያዘው ብቻ ሆኖ መጸለይና ሁሉንም ነገራችን ከዚያ አለማራቅን የሚመለከት ነው፡፡

ብሔራዊ ንስሐ ማለት ደግሞ ለምሳሌ መጪውን ዐመት በሙሉ ወደ እግዚአብሔር መመለሳችንን የሚያሳዩ ድርጊቶችን በሁሉም አጥቢያዎቻችንና በየግላችንም ማሳየት፡፡ ይህም ማለት በየትኛውም በዐለ ንግሥ ሳይቀር ከበሮ እየደለቁ በከፍተኛ ደስታ ሆኖ መዘመሩን ትቶ ከንስሐ ጋር የተገናኙ ቀለሞችን በለቅሶና በሐዘን እያመረገዱ (በማስረገጥ ብቻ ሆኖ መተው)፡፡ ለምሳሌ ያህል በአምስቱ ዐመት የጣልያን ጦርነት ዘመን እንኳን በሌላው ክብረ በዐል እንደ ልደት ባሉት ዕለታት እንኳ "ኢየሱስ ክርስቶስ አስተጋብአነ፤ እስመ ዝርዋን አግብርቲከ ንሕነ" የሚሉት ዐይነቶች ብቻ በለቅሶ በማመርገድ ብቻ ይባሉ እንደነበር በዘመኑ የነበሩ ሊቃውንት ነግረውኛል፡፡ ለድልም ያበቁን እነዚያ ሀገራዊ ንስሐዊ ጸሎቶች እንደሆኑ የታመነ ነው፡፡ እኛም መከራው፣ ሐዘኑ፣ ስደቱ፤ መፈናቀሉና ሞቱ ከልብ የሚሰማን ከሆነ ዳንኪራ እስኪመስል ድረስ ከበሮ መደለቁን ትተን ከልብ በቃለ እግዚአብሔሩ ሁሉ እግዚአብሔርን መለመንና መለማመጥ እንጂ እንደ ኖኅ ዘመን ሰዎች ከአስረሺ ምቺው መሰል ሁኔታ ሳንላለቀቅ ለምን ይህ ሁሉ ደረሰብን ማለት ተገቢ መስሎ አይታየኝም፡፡ በግላችንም ቢሆን ጋብቻው ባይቀር ሰርጉን መተው፤ ሰርጉም ካልቀረ ቢያንስ ድለቃውን መተው፡፡ አሁን እኮ በየሚዲያው የምናየው በየሁኔታው ኮምፕሌክስን የሚያመለክቱ ከወትሮው የተለዩ ፈር የለቀቁ ድለቃዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ቀርቶ ሌላውንም ቢሆን ዘፈንና ልክ ያለፈ የደስታና የድግስ ዝግጅት ሁሉ ለአንድ ዐመት ብንተወዉና ወደ ምጽዋትና ለተፈናቀሉት ዕርዳታ ብናደርገው መልካም ይመስለኛል፡፡ ብሔራዊ ወይም ሀገራዊ ንስሐ የሚባለው ሁኔታዎች ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ወደ ይቅረታና ወደ ፍትሕ መመለስ የሚያመለክቱ ሲሆን ነው፡፡ ይህ የምናደርግ ከሆነ በሦስት ቀናት ልባዊ ጸጸት ለነነዌ ሰዎች በይቅርታ የተመለሰ አምላክ ወደ እኛም ይመለሳል፡፡ ቢያንስ ከሚጠፉት ጋር አብረን ከመጥፋት እንድናለን፡፡ ለሀገርም ለሁሉም ሰውም እንጠቅማለን እንጂ አንጎዳም፡፡ ሌሎቹ ድርጊቶች ሁሉ ከዚህ ዐይነት መመለስ ጋር መሆን አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡

2) ነገሮችን በውል መረዳት

ወደ እግዚአብሔር የመመለስ መንገድን ከጀመርን በኋላ እንደ ሰው ድርሻችን ለመወጣት የምናስብ ከሆነ ደግሞ አስቀድሞ ነገሮችን በውል ለመገንዘብ መጣር ያለብን ይመስለኛል፡፡ በሚዲያ ከምናያቸው ነገሮች ቅርንጫፉን ይዞ ከመሮጥ ረጋ ብሎ በማድመጥ ነገሮችን ከሥር መሠረታቸው ማየት በእጅጉ ጠቃሚ ነው፡፡ ይህን ለሁላችንም ቢያንስ እኩል ማድረግ የሚቻል እንዳልሆነ የታወቀ ነው፡፡ ይህን የምናምን ከሆነ በየፊናችን ከመንጫጫትና በየመሰለን ከመተቻቸት ረጋ ብሎ ሀሳብ ማቅረብ የሚችሉ አካላትን ማዳመጥ ተገቢ ነው፡፡ በሰለጠነው ዐለም ሀገሮቹንም ሆነ ሕዝቡን ስልጡን ከሚያሰኙት ነገሮች አንዱ አብዛኛው ሕዝብ በርጋታ ነገሮችን አዳማጭ መሆኑ እንደሆነ ከብዙ አካላት ሰምቻለሁ፡፡ ድጋፍና ተቃውሞውን የሚገልጸው መስማት ካለበት አካል በአግባቡ ካዳመጠ በኋላ በሚይዘው አቋም አንጂ አንድ ነገር በሆነ ቁጥር በመጯጯህ አይደለም፡፡ በፍጹም ሕዝብ ሁሉ አስተያየት ሰጪ ሊሆንም አይችልም፡፡ እኛ ሀገር ግን ሁሉም በሁሉም ጉዳይ ተናጋሪ አስተያየት ሰጭ ከመሆኑ በላይ በትዕግሥት ነገሮችን ለመመርመር ጊዜ የሚወስዱ እንኳ ይሰደባሉ፤ ይወገዛሉ፡፡ ምን ዐይነት በሽታ እንደሆነም በእውነት ሊገባኝ አይችልም፡፡

ከዚህም አልፎ ተቋማት በግለሰቦች መንገድ፣ ከግለሰቦችም በችኩሎችና እንደፈለጋቸው በሚናሩ ግለሰቦች መጠን እንዲናገሩ ሲገፋፉ ስመለከት ሁኔታዎቻን ሁሉ ወደ ጥፋት እንጂ ወደ ድኅነት የሚወስዱ ስለማይመስለኝ በእጅጉ እፈራለሁ፡፡ በዚህ ሁኔታ በማዘን ብዙ ሀሳብ ያላቸውና ከሰው ሁኔታ አንጻር አስተያየት መስጠታቸው ትርጉም የለሽ መሆኑን አስበው ዝም ያሉ ሊቃውንትን ሳስብ ደግሞ መንገዳችን ሁሉ ያለማስተዋል፣ የድንቁርናና የጨለማ ጉዞ ለማድረግ ሳንመካከር የወሰንን ስለሚመስል ብዙዎችን እንደሚያስፈራ ከአንዳንድ ውይይቶቼ ተገንዝቤያለሁ፡፡ ባሉ ተቋማት እምነት ከሌለን እንኳ ተቋማዊ አሠራር ፈጥሮ መሥራት የሚገባውን መሥራት እንጂ በደመነፍስ መሔድ ከጥፋት ውጭ የሚፈይድልን ነገር ስለማይኖር ነገሮችን በርጋታ ከመመርመርና ከማዳመጥ መጀመር በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን መዘንጋት ያለብን አይመስለኝም፡፡

ለምሳሌ ያህል የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን የሚያጠቋት ለምንድን ነው የሚለውን በአግባቡ ሳንመልስ ዘልለነው ብንሔድ አስቦና አቅዶ ለተነሣ ጠላት ከማገዝ በቀር የምንፈይደው ነገር አናሣ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ ከዐፄ ልብነ ድንግል መማር ካልቻልን ከማን ልንማር እንችላለን? ነገር ከሥሩ ውኃ ከጥሩ እንደሚባለው አጥርቶ መነሣት ቢጠቅም እንጂ አይጎዳም፡፡ ከሚታየው ሞኝ መልእክተኛ አለፍ ብሎ የማይታየውን ለማየትና ተገቢውን ክርስቲያናዊም ሆነ ሕጋዊ ጥብቅና ለመስጠትም ያመቻል፡፡ እንደ አባቶቻችን ለፍርድ ከጠነቀቅን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆኑ አይጠረጠርም፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ ከሆነ ደግሞ እርሱን የሚያሸንፈው ማን ሊሆን ይችላል? ስለዚህ የሌሎች አሰላለፎች ሳያስፈራን ይልቁን በርጋታ ሆኖ አሰላለፍን ከእውነትና ከእግዚአብሔር ጋር ማድረግ ይገባናል፡፡

3) አጋጣሚውን በአግባቡ መጠቀም

ብዙ ስሕተቶችና ጥፋቶች እንደነበሩብና እንዳሉብን ከልብ ከተሰማን ምን አልባት አንዳንዱ ጫና ያንንም ለማስተካከል እንድንችል እግዚአብሔር የፈጠረልን ዕድልም ሊሆን ይችላል፡፡ ነገሮችን ሁሉ በውልና በአግባቡ ከመረመርን ከስሜተዊነት ተላቅቀን ጠቃሚ፣ ዘላቂና ሥልታዊ ነገሮችን በተግባር እንድናውል ሊጠቅሙን ይችላሉ፡፡ የዚህ ጽሑፍ አላማ ጥንካሬያችንን ያለንን አሳይቶ መከራከር ያልሆነውም ለዚህ ነው፡፡ ከዚያ ይልቅ ድክመቶቻችን ለመመርመር ብንጠቀምበት የበለጠ እንጠቀማለን፡፡ ካበለዚያ ግን ጥንካሬያችንንም ልናጣው እንችላለን፡፡ ስለዚህ ከቅዱስ ሲኖዶስና ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ የሥልጠናና የሰው ኃይል ማፍሪያ ተቋሞቻችን ፈትሾ ተቋማዊ አስፈላጊና ኦርቶዶክሳዊ ለውጦችን ከማካሔድ አንሥቶ እስከ ምእምናን የአስተሳሰብ ሥሪት ግንባታ ድረስ አስበን ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ እስከሚገባኝ ድረስ የእብዛኛው የእኛ ምእመናን አስተያየት ምንጩ የየግለሰቡ ሕይወትን መሠረት ያደረገ ልምድ ነው፡፡ ይህ ተፈጥአዊ ቢሆንም በተደራጀና ኦርቶዶክሳዊ አስተምሮአችንን በጠበቀ መንገድ እንዲሆን ብንሠራ አብዛኛዎቹ ልዩነቶቻችን በፍጥነት ሊስተካከሉ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም የብዙዎቻችን እስተያየት ምንጩ የፖለቲካ ፍልስፍና ያደረሰብን ተጽእኖ፤ ከዘመኑ የተበድያለሁ ትርክት፣ ከዐለማዊ ተቋማት አሰራር እና ከመሳሰሉት እንደሚነሣ ሚዲያዎቹ ምስክር ናቸው፡፡ ከተጠቀሱትም ሆነ ካጠጠቀሱት የሚጠቅም ነገር ሊገኝ እንኳ ቢችል ሁለተኛ ነገር ድጋፍ እንጂ ቀዳሚ ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚህም በላይ ውስብስብ ስለሆነ ወደ አንድ ለማምጣትም ቢያንስ አድካሚ ያደርገዋል፡፤ ከኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮና ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ዕውቀት ከተነሣን ግን ችግሮቻችን በአግባቡና በፍጥነት ልንፈታ እንችላለን፡፡ ለዚህ ደግሞ ከምእመኑ እስከ ሲኖዶስ ባሉ ተቋሞቻን ላይ ተገቢውን ጫና በተገቢው መንገድ ማድረግና አስፈላጊውንና እውነተኛውን ለውጥ በማምጣት ከችግሮቻችን ለመውጣት አጋጣሚውን መጠቀም ይገባናል፡፡

4) ለሰማዕትነት መዘጋጀት

ከላይ የተጠቀሱትን እያደረግን ምንም ቢመጣ ችግር ያለው አይመስለኝም፡፡ በተገቢው መንገድ በእውነተኛ ንስሐና ለዐለም ሁሉ በጎውን ከመመመኘት አልፈን፤ ጸልየን፣ ፍርድና ፍትሕ ለመጠንቀቅ በምንችለው ሁሉ ካደርግን በኋላ ደግሞ መፍራት፣ መበርገግ፣ መንጫጫት ሳይሆን ለእውነተኛ ሰማዕትነት መዘጋጀት ነው፡፡ የክርስትና ሃይማኖት የሚጠይቀው ይህንን ነው፡፡ እውነተኛ ሰማዕትነት ካለ እግዚአብሔር አንዳንዱን እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ የት ትሸሻለህ የሚል ድምጽ ያሰማዋል፡፡ አንዳንዱን ደግሞ በቃ ሲል እንደ ቆስጠንጢኖስ መስቀል አሳይቶ መንገዱን ይመራዋል፡፡ እንደ ዳዊትም እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ ውጣ የሚለውንም ካገኘ እርሱ ስለሚያውቀው እኛ መርጠን ልንሰጠው አንችልም፡፡ በእውነትና ለእውነት ከሔድን እውነት እኔ ነኝ ያለው አምላክ እውነተኛውን፣ የሚያስፈልገንን እና የሚሻለውን ሁሉ ያደርግልናል፡፡

እንግዲያውስ በሀገራችን ያሉ ክስተቶች በቀስታና ያለማንም ከልካይ የሚጀመሩበት ዘመነ ዮሐንስ እየገባ መሆኑን ተገንዝበን እጆቻችን ንጹሕ አድርገን ወደ እግዚአብሔር እናንሣ፡፡ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ታደርሣለች ተብሏልና እጆቻችን ለጸሎት ተነሥተው በፊቱም ደርሰው ተመልክቷቸው ፍትሕ ከእርሱ ለመቀበል ያብቃን፤ አሜን፡፡


No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount