በአማን ነጸረ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ 3 ቀን፣
2009 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ባለመወድሱ “ኩሉ ይሤኒ ለእመ አሠንይኮ – (አንተ) ለበጎ ካደረግኸው ሁሉም ለበጎ ይሆናል” እንዲል ማኅበራዊ ሚዲያን (እስከ ተቻለን) ስለ ኦርቶዶክሳዊ ትውፊትም ሆነ ስለ ተቀረው አገራዊ ጉዳይ ለበጎ ዓላማ ለማዋል ሳንታትር የቀረን አይመስለኝም፡፡ ከታተርንባቸው አርእስተ ጉዳዮች ደቂቀ እስጢፋኖስንና ጥንተ አብሶን የተመለከቱ በእመቤታችን ዙሪያ እያጠነጠኑ ታሪክና ዶግማ የሚያጣቅሱ ረዘም ያሉ መጣጥፎ ይጠቀሳሉ፡፡ መረጥናቸው፡፡ አየናቸው፡፡ ከለስናቸው፡፡ በክለሳው የፍቁራን ወንድሞቼ ብርሃኑ አድማስ፣ የኄኖክ ኃይሌና የገብረ እግዚአብሔር ኪደ በቀና ልቡና የታጀበ ጥልቅ አስተያየት ታከለበት፤ ከእነርሱ በመጣ ጥቆማ መነሻነት መጣጥፎቹን በተጨማሪ ማጣቀሻ አዳበርናቸው፡፡ ዳበሩ፡፡ ተገጣጠሙ፡፡ ከግጥምጥሙ “ወልታ ጽድቅ” የምትሰኝ ደንቧላ መጽሐፍ በሽልም ወጣች፤ ተወለደች! መወለዷ ጥሩ! ዜና ልደቷን ተሻግረን እስኪ የጽንሰቷን ነገር እንስማው…