(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ግንቦት 14 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ተዋዳጆች
ሆይ! ክፍል አምስትን ሳላቀርብላችሁ ዘገየሁ፡፡ ይቅርታ ይደረግልኝ፡፡ ከዓቅሜ በላይ የኾነ ጉዳይ ገጥሞኝ ነው፡፡
† ቁስጥንጥንያ ከተማ †
እስኪ
ስለ ቁስጥንጥንያ ጥቂት እንበል! ከአንጾኪያ ይልቅ ቁስጥንጥንያ ከቤተ ክርስቲያናዊም ኾነ ከፖለቲካዊ ፋይዳዋ ከፍ ያለ ነው፡፡ መሥራቿ ታላቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ነው፤ በ330 ዓ.ም.፡፡ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ዘመን ከአራት መቶ እስከ አምስት መቶ ሺሕ ኗሪ ነበራት፡፡ መንበረ ፓትሪያሪኩ ለቤተ መንግሥቱ በጣም ቅርብ ነው፤ ሃጊያ ሶፍያ (ቅድስት ጥበብ - መድኃኔ ዓለም በሉት፡፡ ጥበብ ክርስቶስ ነውና)፡፡ በከተማይቱ ሦስት አብያተ ክርስቲያናት ነበሩ፡- በ381 ዓ.ም. ጉባኤ ቁስጥንጥንያ የተካሔደበትና ከሃጊያ ሶፍያ 150 ሜትር ገደማ የሚርቀው ሃጊያ ኢረነ (ቅድስት ሰላም)፣ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ የሚገኝ የቅዱሳን ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በዮሐንስ መጥምቅ ምትረተ ርእስ የተሰየመ ቤተ ክርስቲያን ናቸው፡፡ በቅዱሳን ስም ቤተ ክርስቲያንን መሰየም የቅርብ ዘመን ታሪክ እንዳልኾነ እያስተዋላችሁ ነውን?