Wednesday, May 2, 2012

ምክረ አበው ቁጥር አንድ



v ከጐደለን ይልቅ ያለን ይበልጣል፡፡
v  ተቀብሎ የማያመሰግን ከቀማኛ ይቆጠራል፡፡
v  ለንስሐ የመደብነው ጊዜ ዓለም የማትፈልገውን የዕድሜያችንን ማለቅያ መሆኑ ያሳዝናል፡፡
v  ነገሥታት በክርስቲያኖች ጸሎት ካልታገዙ ሰይጣን ሲያውካቸው ሕዝቡን ያውካሉ፡፡
v  በጠብ ውስጥ ያለ ረሀብ፣ በድሪቶ ውስጥ ያለ ጥጋብ፣ በጐፈሬ ውስጥ ያለ ጽድቅ አይታወቅም፡፡
v  እንደ ዳዊት ስንዘምር እንደ ሜልኮል የሚያሽሟጥጡ አይጠፉም፡፡
v  ሰይጣን ላያስተኛን ተኙ ይለናል፡፡
v  ማርያም የተመሰገነችው በማርታ ምክንያት ነውና ለማርታም ምስጋና ይገባታል፡፡
v  ዝናው ከሥራው በላይ የገነነበት ሰው ያልታደለ ነው፡፡
v  ኃጢአቱን ተረድቶ ንስሐ የሚገባ ኃጢአተኛ ምንም በደል ከሌለበት ነገር ግን ራሱን እንደ ጻድቅ ከሚቆጥር ሰው የበለጠ ይሻላል፡፡
v  በሽታን እንጂ በሽተኛን አትጥላ፡፡
v  ወጣትና ጤናማ ከሆንክ በድካም ለምትሸነፍበት ለእርጅናህ ዘመንም ጭምር ጹም፡፡
v  በቻልከው መጠን መንፈሳዊ ሀብትን አከማች፤ በማትችለው ጊዜ ትመነዝረው ዘንድ፡፡
v  በብዙ ሰዎች መካከል ተቀምጦ ኅሊናን ባሕታዊ ማድረግ እንዲሁም በብሕትውና ተቀምጦ በሐሳብ በከተማ ውስጥ መኖር ይቻላል፡፡
v  ከመጠን በላይ የሚመሰገንና የሚከበር ሰው ብዙ ኩነኔ ያገኟል፤ በሰው ዘንድ ከቁም ነገር ሳይቆጠር መልካም ነገርን ሠርቶ ያለፈ ሰው ግን በሰማይ ታላቅ ክብር ይጠብቋል፡፡
v  አንድ መነኰሴ ነበረ፡፡ አስቀድሞ ፍጹም የነበረ ሲሆን በኋላ ግን የትርፋቱን ነገር ቸል አለ፡፡ አንድ ቀንም አባ ኢዮብ ከተባለ ሌላ መነኰሴ ማደርያ ጐጆ ጋር ገባ፡፡ አባ ኢዮብ ያስቀመጠው ምግብንም እስከ መስረቅ ደረሰ፡፡ አባ ኢዮብም ይህንን የስርቆት ተግባር አወቀበት፡፡ ደስ ብሎትም አየው፡፡ አባ ኢዮብ በጊዜ ሞቱ ያን ሰው ጠርቶ እጆቹን ሳማቸው፤ ወደዳቸው፤ እንዲህም አለ፡- “ወንድሜ እኔስ እኒህን እጆችህን እስማቸዋለሁ፤ መንግሥተ ሰማያት የምገባበትን ምክንያት ስላመጡልኝ አመሰግናቸዋለሁአለ፡፡ ያም ሌባ መነኰሴእንዲህ የሰው መጽደቂያ ሁኛለሁንብሎ ንስሐ ገባ፡፡ እግዚአብሔር ይርዳን!!!!!!

ልትድን ትወዳለህን?- የዮሐንስ ወንጌል የ23ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.5፡1-9)!!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!! ሰላመ እግዚአብሔር ይብዛላችሁ ወንድም እኅቶቼ!

  የ23ኛ ሳምንት ጥናታችን እነሆ! “ከዚህ በኋላ፣ በቅፍርናሆም የነበረው የገብረ ንጉሡን ልጅ በገሊላ ሆኖ ከፈወሰ በኋላ፣ በቃና ሁለተኛ የሆነውን ምልክት ካሳየ በኋላ አሁን ደግሞ የአይሁድ በዓል ነበረና ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ” /ቁ.1/። ብዙ ሊቃውንት ይህ በዓል የአይሁድ ፋሲካ ነበረ ይላሉ፡፡ በዓለ ኃምሳ ነው የሚሉም አሉ፡፡ ጌታችን በተደጋጋሚ ወደ በዓላቶቻቸው የሚሄደው ብዙ ሰዎች ለገቢረ በዓል ስለሚወጡና በዚያም ብዙዎችን በወንጌል መረብ ለማጥመድ ነው፡፡ እናም ጌታ ወደ በዓላቸው ሲወጣ “በኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ወደ ምትባል፤ አምስት መመላለሻም” ወደ ነበረባት አንዲት መጠመቂያ ገባ /ቁ.2/። ቤተ ሳይዳ ማለት ቤተ ሳህል- የምሕረት ቤት ማለት ነው፡፡ እግዚእበሔር አምላክ በክርስቶስ ኢየሱስ ለሚሰጠው መዳን፣ በአማናዊው ጥምቀት ለሚገኘው ሥርየተ ኃጢአት ምሳሌና ጥላ ይሆን ዘንድ በዚህች መጠመቂያ ድውያነ ሥጋ ይፈወሱባት ወደ ነበረችው መጠመቅያ ገባ/St.John Chrysostom Homily On the Gospel of John,Hom .36፡1/፡፡ ወንጌላዊው “መጠመቅያዋ አምስት መመላለሻ ነበሩባት” ብሎ እንደነገረን አስቀድመን እንዳልነው እስራኤል ዘሥጋ በአምስቱ መጻሕፍተ ኦሪት ኃጢአታቸውን በዝርዝር አዩ፤ ተመለከቱ እንጂ ፍጹም የሆነ ምሕረትን አላገኙም ነበር፡፡ ስለዚህም “ኃይልህን ከአርያም ላክልን፤ ከደዌአችንም ፈውሰን” ብለው እንዲለማመጡ የተሰጠች ነበረች /Augustine, Sermon on NT Lessons 75:2/፡፡

 “በዚህች ውስጥ የውኃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ በሽተኞችና ዕውሮች አንካሶችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውኃውን ሲያናውጠውም በመጀመሪያ የገባ ከማናቸው ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር”/ቁ.3-4/፡፡ መልአኩ ውኃውን ሲያናውጠው ካለባቸው ማንኛውም ዓይነት ደዌ ሥጋ ይፈወሱ ከነበረ የመላእክት ጌታ የሆነው ወልድ ሲገለጥ ደግሞ ከደዌ ዘሥጋ ብቻ ሳይሆን ከነፍሳቸው ደዌም ሥርየተ ኃጢአትን እንደሚያገኙ የሚያሳይ ነበር፡፡ እነዚህ አይሁድ ግን ይህን መዳን ቸል በማለት ጌታ ሊያድናቸው ስላልቻለ ሳይሆን መዳን ስላልፈለጉ ብቻ ኃጢአታቸውን በዝርዝር እያዩ በዚያው ቀሩ፡፡ ይባስ ብለውም ደሙ በእኛና በልጆቻችን ይሁን ብለው ማሉ /ቅ.ዮሐንስ አፈ.ዝኒከማሁ/፡፡ ጌታችን በዚህች መጠመቅያ የነበሩትን ሁሉም ሰዎች ከማዳን ይልቅ ሁሉም የሚያውቁት፣“ከታመመ ሠላሳ ስምንት ዓመት የሆነው አንድ ሰው ” ሊያድንላቸው ወደደ/ቁ.5/፡፡ ይህን የሚያደርገውም ሁሉም አድነን እንዲሉትና ወደው ፈቅደው ከሚማቅቁበት በሽታ ይፈወሱ ዘንድ ነው /አውግስጢኖስ ዝኒ ከማሁ/፡፡ እናም ሰው ወዳጁ ጌታ ይህ ሰው በደዌ ዳኛ ባልጋ ቁራኛ እንደተያዘ ለብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ ወደ አልጋው ቀረበ፡፡ አቤት ፍቀር! በዘባነ ኪሩብ የሚቀመጠው እርሱ “አንድ ቀን እድን ይሆናል” ብሎ ተስፋ ወደሚያደርገው ታማሚ ጠጋ አለና ፈውስ በሆነው ቃሉ፡- “ልጄ! ልትድን ትወዳለህን? አለው። እንዴት ያለ ትሕትና ነው? እንዴት ያለ ፍቅር ነው? በሽተኛ ምን እንደሚፈልግ ግልጽ ቢሆንም አስፈቅዶ ይፈውሰው ዘንድ “ልትድን ትወዳለህን? ተስፋህ ፍጻሜ እንዲያገኝ ትፈልጋለህን? ብፈውስህ ትፈቅዳለህን?” ይሏል /ቁ.6/፡፡ ወንድሞቼ አንድን ነገር ፈልገን ለአንዲት ሳምንት እንኳን ሳንጸልይና ሳንታገሥ እግዚአብሔርን የምናማርር ስንቶች እንሆን? ይህ መጻጉዕ ግን እንዲህ አላለም፡፡ ጌታ ሲጠይቀው እንኳን፡- “የታመመ ሰው ምን እንደሚፈልግ አጥተኸው ነው እንዲህ የምትጠይቀኝ?” ብሎ አይቆጣም፡፡ ከዚያ ይልቅ በፍጹም ትዕግሥት፡-“ጌታ ሆይ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም፤ ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል” /ቁ.7/፡፡ ድውዩ ይህንን የሚለው ጌታችን የሠላሳ ዓመት ጐልማሳ ቢያየው ነጥቆ ይጥለኛል ባይሆን እንኳን ከሚከተሉት አንዱ ያዝልኛል ብሎ ነው፡፡ በሌላ አገላለጥ አምላክ መሆኑን ስላልተረዳ ነው /ወንጌል ቅዱስ አንድምታ ገጽ478/። ከዚህ በኋላ ውኃውን መልአክም አልመጣም፤ ውኃውም አልተንቀሳቀሰም፡፡ ይልቁንም የመላእክት ጌታ፡- “ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” አለው /ቁ.8/። “ሰውዬውም ወዲያው ዳነ፤ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ” /ቁ.9/። እንዴት ግሩም ነው! እንኳንስ ለ38 ዓመት ለ38 ሰዓት ታሞ የተኛ ሰው ፊዚዮቴራፒ ሳያሠራለት እንደልቡ አይንቀሳቀስም፡፡ ይህ መጻጉዕ የነበረ ሰውዬ ግን ለ38 ዓመት የተሸከመችውን አልጋ ተሸክሞ ወደ ቤተዎቹ ሄደ፡፡ ወዮ! አባታችን ሆይ!እኛም እንደ ቤተሳይዳዎቹ ታማሚዎች በደዌ ነፍስ ተይዘን የምሰቃይ ነበርን፡፡ ሰው አጥተን ለ5500 ዘመናት በደዌ ዳኛ በሲዖል ቁራኝነት ተይዘን ነበር፡፡ ነገር ግን የዓለም ሁሉ መድኅን የሆነው አንድያ ልጅህን ልከህ ከዚሁ እስራት ፈታኸን፡፡ ታድያ ለዚሁ ፍቅርህ ተመስገን ከማለት ውጪ ምን እንላለን? ቅዱስ አባት ሆይ! ዛሬም ይህን መድኃኒት የሆነው ድምጽህን ከመስማት ልባችን እንዳይጠነክር እርዳው፡፡ “አሜን ይሁልንልን” ብለንም ከተኛንበት የስንፍናና ያለማመን አልጋ እንድንነሣ ወደ አማናዊው ሰንበት (ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያት) በጽናት እንድንጓዝ እርዳን፡፡ መዳናችን እንድንፈጽም አበርታን፡፡ አሜን!! ሰላም ወሰናይ!!

Tuesday, May 1, 2012

ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሚነሡ ጥያቄዎች- በዲያቆን ዳንኤል ክብረት


አቡነ ተክለ ሃይማኖት እና የመንግሥት ለውጥ አንዳንዶች «ከዛግዌ ሥርወ መንግሥት ወደ ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት የተደረገውን ሽግግር ያከናወኑት አቡነ ተክለሃይማኖት ናቸው፡፡ ይህንንም ያደረጉት ይኩኖ አምላክ የሸዋ ሰው ስለሆነ ለዘራቸው አድልተው ነው» ይላሉ፡፡ በሸዋው ይኩኖ አምላክ እና በዛግዌ ሥርወ መንግሥት ወራሹ በነአኩቶ ለአብ መካከል መቀናቀን የተጀመረው አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሐይቅበትምህርት ላይ በነበሩበት ጊዜ ነበር፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሕፃን በነበሩበት ጊዜ ከዳሞት የሚመጣው የሞተለሚያውያን ኃይል ሸዋንደጋግሞ በመውረር አብያተ ክርስቲያናትን ዘርፏል ሕዝቡንም ማርኳል፡፡ ይህ ጉዳይ የሸዋን ሕዝብ ማስቆጨቱ እና ማነሣሣቱ የማይቀርነው፡፡ በተለይም ከአኩስም የተሰደደው የሰሎሞናዊው ሥርወ መንግሥት ዘር ሸዋ መንዝ ነው የገባው ተብሎ በሚታመንበት ሁኔታ ሸዋዎችራሳቸውን ለመከላከል መደራጀት ጀምረዋል፡፡ ደቡቡ ኢትዮጵያ ከማዕከላዊው መንግሥት መቀመጫ ከሮሐ እየራቀ ሄዶ ስለነበርለይኩኖ አምላክ ጥሩ መደላድል ሆኖታል፡፡ ገድለ ኢየሱስ ሞዓ እንደሚተርከው የመንግሥትን ነገር ከይኩኖ አምላክ ጋር የተነጋገሩት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሳይሆኑ አቡነ ኢየሱስሞዓ ናቸው፡፡ ያን ጊዜ ደግሞ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በተማሪነት ሐይቅ ገዳም ውስጥ ነበሩ፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ እና ይኩኖ አምላክ በመንግሥት ጉዳይ ላይ ለመነጋገር የበቁት ይኩኖ አምላክ በሸዋ ላይ ይደርስ ከነበረው የሞተለሚጥቃት ሸሽቶ በሐይቅ እስጢፋኖስ ትምህርት ቤት ወጣትነቱን ያሳለፈ በመሆኑ ነበር፡፡ ሁለቱ ባደረጉት ስምምነት የዐቃቤ ሰዓትነትን መዓርግ ለሐይቅ ገዳም መምህር እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህም ማለት የንጉሡ ገሐዳዊ ግንኙነቶች በዐቃቤ ሰዓቱ በኩልእንዲፈጸሙ ማለት ነው፡፡ • የንጉሡ ደብዳቤ ወደ ሐይቅ ገዳም ሲላክ መነኮሳቱ ተቀምጠው እንዲሰሙ • ለገዳሙ የተሰጠውን መሬት የመኳንንቱም ሆነ የነገሥታት ልጆች እንዳይነኩ • ነፍስ የገደለ፣ ንብረት የሰረቀ፣ እግረ ሙቁን ሰብሮ እዚህ ገዳም ገብቶ ቢደውል ከሞት ፍርድ እንዲድን • ለገዳሙ የተሰጠው ርስት ለአገልጋዮች ብቻ ስለሆነ ዘር ቆጥሮ ማንም ተወላጅ እንዳይወርስ • የገዳሙ ርስት መነኩሴ ላልሆነ ጥቁር ርስት እንዳይሰጥ የሚሉት ታወጁ፡፡ ይህ ሁሉ ሲከናወን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሐይቅ ትምህርት ላይ ነበሩ፡፡ በኋላ ዘመን ይኩኖ አምላክ ኃይሉ እየበረታ ነአኩቶ ለአብም ግዛቱ እየጠበበ እና ኃይሉ እየደከመ ሲሄድ ከወሎ በታች ያለውን ሀገርየያዘው ይኩኖ አምላክ እና ላስታን እና ሰሜኑን የያዘው ይኩኖ አምላክ ለጦር ይፈላለጉ ጀመር፡፡ በዚህ ዘመን ነበር አቡነ ተክለ ሃይማኖትከኢየሩሳሌም የተመለሱት፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ያደረጉት ነገር ቢኖር ኃይሉ እየገነነ የመጣውን ይኩኖ አምላክን እና የወቅቱን ንጉሥ ነአኩቶ ለአብን ማደራደርነበር፡፡ ይኩኖ አምላክ ለመንገሥ ከቅብዐት በቀር የቀረው ኃይል አልነበረም፡፡ የነአኩቶ ለአብ ኃይል ደግሞ ቢዳከምም አልሞተም፡፡ሁኔታው ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንዳይሄድ ያሰጋቸው አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሁለቱን በማደራደር ከአንድ ስምምነት ላይአደረሷቸው፡፡ • ይኩኖ አምላክ ምንም ኃይል ቢኖረው ነአኩቶ ለአብ እስኪያርፍ ድረስ ንግሥናውን እንዳያውጅ • ከነአኩቶ ለአብም በኋላ የዛግዌ ዘር የላስታን አውራጃ እንዲገዛ • የላስታው ገዥ በፕሮቶኮል ከንጉሡ ቀጥሎ እንዲሆን ይህ ስምምነት ባይኖር ኖሮ ጦር በሰበሰበው በይኩኖ አምላክ እና ሥልጣን ላይ በነበረው በነአኩቶ ለአብ መካከል በሚፈጠረው ጦርነትየሀገሪቱ ልጆች ባለቁ ነበር፡፡ ዛሬ ቢሆን ይሄ ተግባር የኖቬል ሽልማት የሚያሸልም ነበር፡፡ ይህ ስምምነት በኋላ በዐፄ ይትባረክ ዘመንበመፍረስ የተከሰተውን ጦርነት ያየ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ያደንቃል እንጂ አይተችም፡፡ ሲሦ መንግሥት አንዳንዶች «አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት በዋሉት ውለታ ለቤተ ክርስቲያን ሲሦ መንግሥት ተሰጠ» ይላሉ ይኩኖ አምላክሲነግሥ በኢትዮጵያ ውስጥ ጳጳስ አልነበረም፡፡ ከአቡነ ጌርሎስ ሞት በኋላ ከግብፅ የመጣ ጳጳስ አልነበረም፡፡ ይህ ሁኔታ በመንፈሳዊትንሣኤ ላይ ለነበረችው ኢትዮጵያ የአገልጋዮች እጥረት አስከተለ፡፡ በዚህ ጊዜ የተሰባሰቡት የኢትዮጵያ ሊቃውንት በትምህርትምበአገልግሎትም የበረቱትን አቡነ ተክለ ሃይማኖትን መረጡ፡፡ የሚሾም ሲኖዶስ አልነበረምና እግዚአብሔር «ሐዋርያትን በሾምኩበትሥልጣን ሾምኩህ» አላቸው፡፡ ይኩኖ አምላክ ምንም እንኳን በንግሥናው ቢገዛ እንደ ወጉ ሥርዓተ መንግሥት አልተፈጸመለትም ነበር፡፡ በመሆኑም በዘመኑ የነበሩትአቡነ ተክለ ሃይማኖት ሥርዓተ መንግሥቱን ፈጸሙለት፡፡ እርሱም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ርስት ሰጠ፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ርስት መስጠት በይኩኖ አምላክ የተጀመረ አይደለም፡፡ እንዲያውም ቅዱስ ላሊበላ ለአኩስም፣ ለላሊበላ፣ለመርጡለ ማርያም እና ለተድባበ ማርያም የሰጠው ርስት ይበልጣል፡፡ በወቅቱ ለሐዋርያዊ አገልግሎት እና ለተማሪዎች ድርጎ ለቤተክርስቲያን ጥሪት ያስፈልጋት ስለነበር ይኩኖ አምላክ ርስት ሰጥቷል፡፡ ይህ ግን ከመንግሥት ዝውውር ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ዛሬም ቢሆን እኮ አንዳንድ የአውሮፓ ሀገሮች ለቤተ ክርስቲያን የተለየ በጀት ይሰጣሉ፡፡ እጨጌ የሚለውን ስም ከርስት አስተዳዳሪነት ጋር የሚያገናኙት ሰዎች አሉ፡፡ እጨጌ የሚለውን ስም ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት የሰጣቸውመንግሥት ሳይሆን የወላይታ ሕዝብ ነው፡፡ በወላይተኛ «ጨጌ» ማለት «ሽማግሌ፣ ታላቅ፣ አባት» ማለት ነው፡፡ ወደ አማርኛ ሲመጣ«እጨጌ» ተባለ፡፡ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን አገልግሎት አይቶ ይህንን የሰጣቸው ሕዝቡ ነው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሥልጣን ወዳድአለመሆናቸውን በግልጽ አሳይተዋል፡፡ ከብዙ ዘመናት በኋላ አቡነ ዮሐንስ 5ኛ ከግብጽ መጥተው አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በግማሽኢትዮጵያ በመንበረ ጵጵስና እንዲያገለግሉ ለምነዋቸው ነበር፡፡ እርሳቸው ግን ለሥልጣን ፍላጎት እንደሌላቸው ገልጸው እንዲያ ሕዝብሲወዳቸው እና ሲፈልጋቸው ወደ በኣታቸው ነው የተመለሱት፡፡ «ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሌላ ናቸው » አንዳንዶች «በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከ8 እስከ 13ኛው መክዘ ባለው ጊዜ የኖሩ ሌላ ተክለ ሃይማኖት የሚባሉ ጻድቅ ነበሩ፡፡ የርሳቸውታሪክ ከሌላ ተክለ ሃይማኖት ታሪክ ጋር ተዳብሎ አሁን ያለWን ገድለ ተክለ ሃይማኖት አስገኘ፡፡ እናም ጻድቁ ተክለ ሃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስአይደሉም » ይላሉ እስካሁን ድረስ ይህንን አባባል የሚጠቅሱ ሰዎች ያቀረቡት ማስረጃ የላቸውም፡፡ እገሌ አይቶት ነበር፡፡ እዚህ ገዳም ነበር ከማለትውጭ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ለሌለ ማስረጃ ሲባል ያለ ማስረጃ አይሰረዝም፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስን በተመለከተ ያሉት ማስረጃዎች አራት ዓይነት ናቸው፡፡ 1. ገድላቸው 2. የሌሎች ቅዱሳን ገድሎች 3. ዜና መዋዕሎች እና 4. የግብፅ ቤተ ክርስቲያን መረጃዎች ገድለ ተክለ ሃይማኖት እኔ ለማየት የቻልኩት የደብረ ሊባኖስ፣ የሐይቅ እስጢፋኖስ፣ የዋልድባ፣ የጉንዳንዳጉንዲ እንዲሁም ዐፄ ምኒሊክ ወላይታን ሲወጉያገኙት የወላይታ ገድለ ተክለ ሃይማኖት ቅጂዎች አልፎ አልፎ ከሚያሳዩት መለያየት በስተቀር የሚተርኩት በ13ኛው መክዘ ስለነበሩትተክለ ሃይማኖት ነው፡፡ እኒህ ተክለ ሃይማኖት ጽላልሽ ተወልደው፣ በኢትዮጵያ ገዳማት ተምረው፣ በመላ ሀገሪቱ ሰብከው፣ ግብጽእና ኢየሩሳሌም ተሻግረው፣ ደብረ ሊባኖስን መሥርተው ያገለገሉትን ተክለ ሃይማኖት ነው የሚናገሩት፡፡ ሌላው ቀርቶ ወሎ ጉባ ላፍቶ፣ ጎንደር አዞዞ ተክለ ሃይማኖት የተገኙት ገድላትም ተመሳሳይ ታሪክ ነው የሚተርኩት፡፡ እስካሁንከኒህኛው ተክለ ሃይማኖት ውጭ ስላሉ ሌላ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሚተርክ ገድል አልተገኘም፡፡ አለ ከመባል በቀር፡፡ የኢትዮጵያ የብራና መጻሕፍትም ሆኑ በአካል ያልተገኙት ማይክሮ ፊልሞቻቸው በተከማቹባቸው በብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትወመዛግብት፣ በመንበረ ፓትርያርክ ሙዝየም እና ቤተ መጻሕፍት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ቤተ መጻሕፍት፣በብሪቲሽ ሙዝየም እና ቤተ መጻሕፍት፣ በቫቲካን ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት፣ አሜሪካ ኮሌጅቪል በሚገኘው ቅዱስ ዮሐንስኮሌጅ ያሉትን ማይክሮ ፊልሞች እና የብራና መጻሕፍት ዝርዝሮችን ብናይ ስለ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስ እንጂ ስለሌላ ተክለ ሃይማኖት የተጻፈ ገድል የለም፡፡ (የዚህን ዝርዝር የጥናት ውጤት በቅርብ ለኅትመት አበቃዋለሁ፡፡) ሌሎች ገድሎች ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሚያነሡ አያሌ ገድሎች አሉ፡፡ ገድለ አኖሬዎስ ዘሞረት፣ ገድለ አቡነ አኖሬዎስ ዘወረብ፣ ገድለ አቡነፊልጶስ፣ ገድለ አቡነ ኤልሳዕ፣ ገድለ አቡነ ሕዝቅኤል፣ ገድለ አቡነ ዜና ማርቆስ፣ ገድለ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ፣ ገድለ አቡነቀውስጦስ፣ ገድለ አቡነ ማትያስ፣ ገድለ አቡነ ታዴዎስ ዘጽላልሽ፣ ገድለ አቡነ ገብረ ክርስቶስ ዘግድም፣ ገድለ አቡነ መርቆሬዎስዘመርሐ ቤቴ፣ ገድለ አቡነ አድኃኒ ዘዳሞት፣ ገድለ አቡነ ኢዮስያስ ዘወጅ፣ ገድለ አቡነ ዮሴፍ ዘእናርያ፣ ገድለ አባ ጊዮርጊስዘጋሥጫ እና ሌሎች ወደ አሥራ ሦስት የሚጠጉ ገድላት ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ተጨማሪ መረጃዎች ይሰጣሉ፡፡ እነዚህ ሁሉገድላት የሚያነሷቸው ተክለ ሃይማኖት ግን ተክለ ሃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስን ነው፡፡ ዜና መዋዕሎች የይኩኖ አምላክ፣ የዓምደ ጽዮን፣ የዘርዐ ያዕቆብ፣ የሱስንዮስ፣ እና የሌሎቹም ዜና መዋዕሎች ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘደብረሊባኖስ ይተርካሉ፡፡ ግብፃውያን መዛግብት የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው ቅዱሳን መካከል አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንዱ ናቸው፡፡ እንዲያውምቤተ ክርስቲያንዋ የአራት ቅዱሳንን ብቻ የልደት በዓል ታከብራለች፡፡ የጌታን፣ የእመቤታችንን፣ የዮሐንስመጥምቅን እና የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን፡፡ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ጥንታውያንም ይሁኑ ዘመናውያንመዛግብት የሚገልጹት በ12ኛው መክዘ ጽላልሽ ተወልደው ስላደጉት ስለ ደብረ ሊባኖሱ አቡነ ተክለ ሃይማኖትነው፡፡ እናም ወደፊት አዲስ ነገር ተገኘ ስንባል ያን ጊዜ እንከራከር ካልሆነ በቀር እስካሁን ድረስ ግን ከአቡነ ተክለሃይማኖት ጋር የታሪክ ዝምድና ያላቸው ሌላ ተክለ ሃይማኖት መኖራቸውን የሚገልጥ ማስረጃ የለም፡፡
 ተመሳሳይ ገጾች

አባታችን ተክለሃይማኖት ማለት እኒህ ናቸው

በአቡነ ተክለሃይማኖት ገድል ላይ የሚነሱ አንዳንድ ጥያቄዎች

እግር ያለው ባለ ክንፍ

ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ

ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ በጥር 20 ቀን በ277 ዓ.ም ተወለደ። ሀገሩ ፍልስጤም ሲሆን ልዩ ስሟ ልዳ ይባላል። ጊዮርጊስ ማለት ኮከብ፣ ብሩህ፣ ሐረገወይን፣ ፀሐይ ማለት ነው። አባቱ ዞሮንቶስ (አንስጣስዮስ) ይባላል ከልዳ መኳንንት ተሹሞ ይኖር ነበር፤ እናቱ ቴዎብስታ (አቅሌስያ) ትባላለች። ማርታና እስያ የሚባሉ እህቶች ነበሩት። 10 ዓመት ሲሞላው አባቱ ስለሞተ ሌላ ደግ ክርስቲያናዊ መስፍን ከቤቱ ወስዶ አሳደገው። በጦር ኃይልም አሠለጠነው። አድጎ ሃያ(20) አመት ሲሞላው መስፍኑ የ15 ዓመት ቆንጆ ልጅ ነበረችውና እርሷን አግብቶ ሀብቴን ወርሶ ይኑር ብሎ ድግስ ሲያስደግስ ጌታ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለዚህ አላጨውምና የመስፍኑን ነፍስ ወሰደ። እርሱም ኀዘኑን ጨርሶ ወደ ቤሩት ሄደ።

በቤሩት ደራጎንን ያመልኩና ሴት ልጃቸውን ይገብሩለት ነበርና በኃይለ መስቀል ድል ነስቶት ህዝቡን ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር አስገብቷቸዋል። ወደፋርስ ቢመለስ ዱድያኖስ ሰባ ነገሥታት ሰብስቦ ሰባ ጣዖታት አቁሞ ሲሰግድ ሲያሰግድ ቢያገኛቸው ለሃይማኖቱ ቀናዒ ነውና ከቤተመንግስቱ ገብቶ “እኔ ክርስቲያን ነኝ በኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ” አለው። እርሱም ማንነቱን ከተረዳ በኋላ “አንተማ የኛ ነህ በ10 አህጉር ላይ እሾምሃለሁ የኔን አምላክ አጵሎንን አምልክ” አለው። ቅዱስ ጊዮርጊስም “ሹመት ሽልማትህ ለአንተ ይሁን እኔ አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስን አልክድም” አለ። በዚህ ጊዜ እጅግ ተናዶ መከራን አጸናበት እርሱ ግን “ይህን ከሀዲ እስካሳፍረው ድረስ ነፍሴን አትውሰድ” በማለት እግዚአብሔርን የለመነና እንደጸሎቱ የተደረገለት። በእምነቱም ጽናት የሰው ልጅ ሊሸከም የማይችለውን መከራ የተቀበለ ቅዱስ አባት ነው። ከእነዚህም መከራዎች ውስጥ፡- 1. በእንጨት አስቀቅሎ ሥጋውን በመቃን አስፈተተው፣ ረጃጅም ችንካሮች ያሉበት የብረት ጫማ አጫምቶት ሂድ አለው። ቅዱስ ሚካኤልን ልኮለት ፈውሶታል። በሰባ (70) ችንካር አስቸንክሮ በእሳት አስተኩሶ አናቱን በመዶሻ አስቀጥቅጦ በሆዱ ላይ የደንጊያ ምሰሶ አሳስሮ እንዲያንከባልሉት አደረገ። ሥጋውን በመጋዝ አስተልትሎ ጨው ነስንሶበት ሥጋው ተቆራርጦ ወደቀ። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈቀ ሌሊት በእጁ ዳስሶ “ገና 6 ዓመት ለስሜ ትጋደላለህ፣ 3 ጊዜ ትሞታለህ፣ በ4ኛው ታርፋለህ።” አለው። 2. ዱድያኖስ ደንግጦ “የሚያሸንፍልኝ ቢኖር ወርቅ እሰጠዋለሁ” ቢል አትናስዮስ የተባለ መሰርይ ከንጉሱ ላምን በጆሮዋ ሲያንሾካሹክባት ለሁለት ተሰንጥቃ ገድሏት ፈቃድን ተቀበለ። ሆድ በጥብጦ አንጀት ቆራርጦ የሚገድል መርዝ ቀምሞ አስማተ ሰይጣን ደግሞ ሰጠው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ስመ እግዚአብሔርን ጠርቶ ቢጠጣው እንደ ጨረቃ ደምቆ እንደ አበባ አሸብርቆ ተገኝቷል። ጠንቋዩም ማረኝ ብሎት ከእግሩ ወደቀ። መመለሱን አይቶ የቆመባትን መሬት በእግሩ ረግጦ ውሃን አፍልቆ ወደ ጌታችን ቢያመለክት ሐዋርያው ቶማስ በመንፈስ መጥቶ አጥምቆት ጥር 23 ቀን አንገቱን ለሰይፍ ሰጥቶ በሰማዕትነት አርፏል። እሱን ግን በመንኮራኩር አስፈጭቶ ከትልቅ ጉድጓድ ጥሎት ደንጊያ ዘግቶበት አትሞበት ሄዷል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተፈጨውን ሥጋ በእጁ ዳስሶ መንፈሱን መልሶ አንስቶታል፤ ተመልሶም “አምላኬ ከሞት አዳነኝ” ብሏቸዋል። 3. በብረት አልጋ አስቸንክሮ ከበታቹ እሳት አንድዶበታል። እሳቱም ደሙ ሲንጠባጠብ ጠፍቷል። ዱድያኖስ “ኢየሱስ አምላክ መሆኑን አሳየኝ” ቢለው የለመለሙትን ዕፅ አድርቆ፣ የደረቁትን አለምልሞ፣ ከሞቱ 430 ዓመት የሆናቸውን ሙታንን አስነስሰቶ አሳይቶታል። ነገር ግን ልቡ ክፉ ነውና በረሀብና በጽም ይሙት ብሎ ምንም ከሌላት መበለት ቤት አሳስሮታል። እርሷም የሚቀመስ ስትፈልግ ቤቷን በእህል አትረፍርፎ የታሰረበት ግንድ አፍርቶ ልጇ ጆሮው የማይሰማ ነበርና ፈውሶላት መበለቲቷን ከነልጆቿ አጥምቆ ቅዱስ ሚካኤል ከእስራቱ ፈትቶት ተመልሷል። ዳግም በመንኩራኩር ፈጭታችሁ ደብረ ይድራስ ወስዳችሁ ዝሩት ብሎ አስፈጭቶ ሥጋውን ቢዘሩት ሥጋው ያረፈበት ሳር፣ ቅጠሉ፣ ደንጊያው፣ እንጨቱ ሁሉ “ጊዮርጊስ ቅዱሱ ለእግዚአብሔር፣ ጊዮርጊስ ሰማዕቱ ለእግዚአብሔር፣” እያሉ አመስግነዋል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለሦስተኛ ጊዜ ከሞት አስነስቶታል። ሔዶም “አምላኬ ከሞት አዳነኝ” አላቸው። ጭፍሮቹ ደንግጸው ከእግሩ ስር ወደቁ። ከመሬት ውሃ አመንጭቶ ቅዱስ ዮሐንስ አጥምቋቸዋል። 4. “ንጉሡ ልሹምህ ለአጵሎን ስገድ” ብሎ ቢለምነው እሺ ብሎ ገብቶ ሲጸልይ የንጉሱ ሚስት እለእስክንድርያ “ምን እያልክ ነው?” ብትለው አስተምሯት አሳምኗታል። ሲነጋ ንጉሱ በአዋጅ ህዝብን አሰብስቦ “ጊዮርጊስ ለጣዖቴ ሊሰግድ ነው’ ብሎ በተሰበሰበ ህዝብ መካከል አንድን ብላቴና (የመበለቷን ልጅ) “የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ ጊዮርጊስ ይጠራሃል” በል ብሎ ወደጣዖቱ ቢልከው ጣዖቱ ላይ ያደረው ሰይጣን እየጮኸ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለበት ቦታ መጣ፤ አምላክ አለመሆኑን አናዞት መሬት ተከፍታ እንድትውጠው አደረገ። ብዙ ሰዎች ይህንን ተዓምር አይተው አመኑ። ንጉሱን ሚስቱ እንዲመለስ ብትነግረው በአደባባይ አሰቅሎ አሰይፏት ሞታለች ደሟን ጥምቀት አድርጎላት ሰማዕት ሆናለች። በመጨረሻም በሰይፍ እንዲመተር አስደረገ። ቅዱስ ጊዮርጊስም ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃልኪዳን ተገብቶለት በ27 ዓመቱ በሚያዝያ 23 ቀን በ9፡00 ሰዓት ሰማዕት ሆኗል። አንገቱ ሲቆረጥ ውሃ፣ ደም እና ወተት ወጥቷል። ==>> ከሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ረድኤት በረከት ይክፈለን!!! Source: http://www.melakuezezew.info/

FeedBurner FeedCount