Monday, May 7, 2012

አባታችን ተክለሃይማኖት ማለት እኒህ ናቸው=+=በታምራት ፍስሃ=+=

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን፡፡


            አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት የክርስቶስ ፍቅር ብልጫ ሆኖባቸዋልና ፡ ክርስትናቸውም የጣኦትን አምልኮ ተፀይፋለችና እኔ ክርስቲያን ነኝ በማለት የወንጌሉን የቃል ትምህርት በህይወት እየኖሩ አልጫ ለሆነው አለም ጨው ፡ በጨለማ ላለው ህዝብ ብርሃን ሆነው በኢትዮጵያ ከሰሜን እስከደቡብ ከምእራብ እስከ ምስራቅ ወንጌልን በቃልና በተግባር እያስተማሩ ዞሩ ፤ አለምን ንቀዋታልና ሃብትንና ስልጣንን ገፍተው ስለክርስቶስ በዱር በገደል በገዳም በዋሻ ይኖሩ ዘንድ ራሳቸውን ግድ አሉ፡፡ በነገስታት ቤት በቅምጥል ከመኖር ይልቅ ስለክርስትናው የነፃነትና የህይወት ምስክርነት በጣኦት አምላኪወች ፊት በሃዋርያት ድፍረት በሰወች ፡ በእንስሳትና በእፅዋት ላይ አድሮ ክርስቶስን ያስካደውን ፡ እግዚአብሄርን ያስረሳውን የዲያቢሎስ ሰራዊት በፅድቅ ታገሉት ፡ በወንጌሉ ሃይል ድል ነሱት ፡ በክርስቶስ ቃል አሳፈሩት ፡ በጨለማ ይንከላወስ ለነበረው ህዝብም ክርስቶስን ሰበኩላቸው ፡ በስላሴ ስም አጠመቋቸው ፡ የክርስቶስን ቅዱስ ስጋ ክቡር ደም አቀበሏቸው ፡ ዳግመኛም ቤተክርስቲያንን አሳንፀው ፡ ምእመናን መልሰው ወደጣኦት አምልኮ ወደሃጢአትም እንዳይመለሱ ፡ ካህናት አባቶችን እንዲጠብቋቸው  እያዘጋጁላቸው ለህዝቡ ሁሉ ሃዋርያ ሆነው ኖሩ፡፡


            ለሰውነታቸው እረፍትን ለስጋቸው ምቾትን ያሳዩአት ዘንድ አልወደዱም ፡ መከሩ ብዙ ሰራተኛው ግን ጥቂት እንደሆነ ተገንዝበዋልና ፡ ለሁሉ ክርስቶስን ሰብከው ፡ ሁሉን ክርስቲያን አድርገው እስኪጨርሱ ድረስ ተጋድሏቸውን አስረዘሙ ፡ የክርስቶስ ቅናት ግድ ብሏቸዋልና ፡ የዲያቢሎስ በህዝቡ ላይ መሰልጠን ልቦናቸውን አስቆጥቶት ነበርና ስጋቸው ያርፍ ዘንድ አልወደዱም፡፡ “የሁሉ ፈጣሪ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው ፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው ፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው” እያሉ ባላመኑት ፊት ፡ በሚያስፈሩት ፊት ፡ ዲያቢሎስ በሚመለክበት ፡ አስማት ጥንቆላ በገነነበት ፡ ሰው መግደል ቀላል በሆነበት ፡ ክፋት በነገሰበት ፊት ለስጋቸው ሳይሳሱ መሰከሩ ፤ መገረፍን እየታገሱ ወንጌልን መሰከሩ ፡ ወንጌልን በቃል በግብር መሰከሩ ፡ ወርቅ ሃብትን እየናቁ ክርስቶስን ሰበኩ ፡ ክርስትናን ሰበኩ፡፡

            ዲያቢሎስ ግን ታገላቸው ፡ የሰውን ልብ አራዊት እያደረገ ፡ በምትሃትና በማስመሰል የሰውን ህሊና እየተቆጣጠረ ፡ በግልፅና በስውር ታገላቸው ፡ ክርስቶስን መስበክ ያቆሙ ዘንድ በሃብት በጥጋብ በምቾት ያታልላቸው ዘንድ በአለማዊ ቅምጥልና ታገላቸው ፡ የውሽት ወሬን እያስወራ ፡ የሃሰት ምስክሮችን እያቆመ ፡ መልካሙን ስራቸውን እያክፋፋ ታገላቸው ፡ ዲያቢሎስ በሰው አድሮ ታገላቸው ፡ የዲያቢሎስ ትግል ግን አባታችንን ብቻ አልነበረም ፡ ክርስትናውም እንዳይሰበክ ታገለ እንጂ ፡ ክርስቶስ እንዳይመለክ ታገለ እንጂ ፡ መልካምነት እንዳይሰለጥን ታገለ እንጂ ፡ ዲያቢሎስ አባታችንን ታገላቸው ፡ አስገረፋቸው ፡ አሰደዳቸው ፡ ወደ ጥልቁ አስወረወራቸው ፡ በእጅጉ ታገላቸው ፡ አባታችን ተክለሃይማኖት ግን በክርስቶስ ሃይለኛ ነበሩ ፡ የሃዋርያትን መንፈስ የያዙ ነበሩና ፡ ስለሚያስተምሩለት ፡ ስለሚደክሙለት የምስራች ፅኑ እምነት ነበራቸውና ፡ የቆሙበት መሰረት ክርስቶስ ነበርና ፡ ዲያቢሎስን ድል ነሱት ፡ የመንፈስን ጦር ታጥቀው ነበርና ፡ በወንጌል ቃል ስለትነት ዲያቢሎስን ድል ነሱት ፡ ከሰለጠነበት ሻሩት ፡ የማረከውን አስመለሱት ፡ ለእርሱ ይገብሩ የነበሩትን ሁሉ ለክርስቶስ አስገበሩ፡፡
በዘመናቸው ክርስትና ደመቀች ፡ ክርስቶስ ከበረ ፡ ወንጌል ተሰበከች ፡ የዲያቢሎስ ሃይል ደከመ ተሻረ ፡ አብያተ ጣኦታት ተዘጉ ፡ አብያተ ክርስቲያናት ተከፈቱ ፡ ካህናተ ጣኦታት ተሻሩ ካህናተ ክርስቶስ ተሾሙ ፡ በአባታችን ፅኑ የምትመስል የወንጌል ቃል  በህይወት ታየች ፡ በተግባር ተዳሰሰች ፡ ክርስቶስ ከበረባት ፡ ዲያቢሎስ ወደቀባት ፤ እኔን ብቻ ይድላኝ ይሙቀኝ ብለው በአለማዊ ቅንጦት ይኖሩ ዘንድ አልወደዱምና ፡ ለብዙወች ተረፉ ፤ መስቀሉን ተሽክመው ክርስቶስን ተከተሉት ፡ በዚህም ብዙወችን አስከተሉ ፡ በፆም በፀሎት በትህርምት ፡ በበጎነት ፡ በሃይል በስልጣን ፡ በእምነት በፀጋ ፡ ወንጌልን ለብሰው ብርሃን ሆነው ታዩ ፡ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትደበቅ እንደማትችል ፡ ፀሃይም ብርሃኗን ስትሰጥ ለመደበቅ እንዳይቻላት የአባታችን የተክለሃይማኖትም ፅድቅ ሊደበቅ አይቻለውም ፡ ብርሃን ነውና ለሁሉ አበራ ፡ ጨው ነውና ሁሉን አጣፈጠ ፡ መርከብ ነውና በማእበል የተገፉትን አሻገረ፡፡

               ክርስቶስን ፈለጉት ፡ እናት ልጇ ቢጠፋባት ፈልጋ እስክታገኘው ድረስ መፈለጓን እንዳታቋርጥ አባታችንም ክርስቶስን እስኪያገኙት ድረስ ፈለጉት ፡ ወርቅ የጠፋበት ወርቁን ያገኝ እንደሆነ ዳሩን መሃሉን ፡ ሜዳውን ገደሉን መፈለግ እንዳይሰለች ክርስቶስን ሳይሰለቹ ፈለጉት ፡ ካገኙትም በኅላ ሊለቁት ከቶ አልፈለጉም ፡ ክርስቶስን ያዙት ፡ የሙጥኝ አሉት ፡ ክብርን ባለጠጋነትን ትተው ንቀው ባለጠጋ ክርስቶስን ተጠጉት ፡ ከእርሱም ፈቀቅ ይሉ ዘንድ ከቶ አልወደዱም ፡ ይልቁንስ ክርስቶስን ወደዱት ፡ የክርስቶስ የፍቅሩ ጥልቀት መጨረሻ የለውምና ፡ ሰውንም የመውደዱ ልኬት መጠን የለውምና ክርስቶስን ወደዱት ፡ ክርስቶስን ለበሱት ፡ ክርስቶስም ተዋሃዳቸው ፡ ክርስቶስ አስቀድሞ ስለሰው ሁሉ ራሱን መስዋእት እንዳደረገ ፡ ሃዋርያትም ስለክርስቶስ ወንጌልን ለሰው ሁሉ ስለመስበካቸው ራሳቸውን ክደው ለመስዋእት ዝግጁ እንዳደረጉ ፡ እስጢፋኖስ በሚወግሩት ፊት ስለክርስቶስ መስበኩን እንዳላቋረጠ ፡ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖትም ስለሰው ሁሉ መዳን ግድ ብሏቸዋልና ራሳቸውን ክደው መስቀሉን ተሽከሙ ፡ ቃላቸውንም አስረዝመው ክርስቶስ የሁሉ ጌታ እንደሆነ አስተማሩ ፡

               ለእግዚአብሄርም ምርኮ አገቡ ፡ ለአለማዊ ንጉስ ምርኮን ማርኮ ያስገባ ሹመት ሽልማት ሙገሳ ይደርሰዋል ፡ ለእግዚአብሄርስ ምርኮን ያስገባ ምን ይደርሰዋል? አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት ቁሳዊ ገንዘብ አለማዊ ሽልማትን ንቀዋታልና ይሄንን ከአለማዊ ንጉስ ያገኙ ዘንድ አልወደዱም ፡ ነገር ግን ቅዱሳን ለእግዚአብሄር ፀጋ እንዲሽቀዳደሙ ክርስቶስ ስለሚሰጣቸው ክብር ይሽቀዳደሙ ዘንድ ተጉ ፡ ክርስቶስ በሰጣቸው መክሊት እጅግ አትርፈው በክርስቶስ ፊት ይቀርቡ ዘንድ ተጉ ፡ ራሳቸውንም ከከንቱ ውዳሴ ይጠብቁ ዘንድ ፡ እንዲህ ሲሉ ስለራሳቸው ተናገሩ፦ “ ወዮልኝ ወዮታ አለብኝ እውነተኛ ዳኛ በመጣ ጊዜ በዚያች ቀን ምን እመልሳለሁ? “የሰማዩ አባቴን ፈቃድ ከሚሰራ በቀር ወደመንግስተ ሰማያት የሚገባ የለም” ፡ ያለውን ቃሉን አላሰብኩማና ፡ ወይኔ ያን ጊዜ ወዴት እሽሻለሁ? ከሕያው እግዚአብሄር ከቁጣው  ፊትስ ወደት ሄጄ  እማፀናለሁ ፡ ወዮልኝ ፡ ጨው ምግብን ሁሉ እንዲያጣፍጥ እሱን ግን የሚያጣፍጠው እንደሌለ ፡ አልጫም ከሆነ በኅላ ከአፍአ ጥለው ሰወች እንደሚረግጡት ሆኛለሁና ፡ መብራት ቢጠፋ የሚያበራለት የለም ፡ ጨለማ ከሚወርሰው በቀር ፡ ባለመድሃኒትንስ ማን ይፈውሰዋል? ራሱ የሚድንበትን ካላወቀ ፡ ነፍሴም በኔ ላይ እንዲሁ ሆነች ፡ ሌሎችን አጣፈጥኩ ፡ ለራሴ ግን አልጫ ሆንኩ ፡ ሕሙማንን ፈወስኩ ለራሴ ግን ድውይ ሆንኩ ፡ ለአለም አበራሁ ለራሴ ግን ጨለምኩ ፡ ከእንግዲህስ ለአይኖቼ እንቅልፍን ለቅንድቦቼም ማንጎላጀትን አልሰጣቸውም፡፡”( ገድ ተክ ም53)
             ዳግመኛም ከነብያት ከሃዋርያትና ከሰማእታትም በረከት ይካፈሉ ዘንድ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት “ድካም በማብዛት እንደነቢያት ወንጌልን በማስተማር እንደሃዋርያት በመገረፍ እንደሰማእታት አጥንቱ ከሥጋው ጋር እስኪጣበቅ ከሰውነቱም ማለቅ ብዛትና የሚያቃጥለውን ላብ እንደደም ዥረርታ በማፍሰስ ከስግደቱ የተነሳ የሰውነቱ መለያ እስኪቆጠር ድረስ ተባህትዋን በመያዝ እንደመነኮሳት ሆኖ መንፈሳዊ መገዛቱን ለመጨረስ ቆርጦ ተነሳ፡፡” (ገድ ተክ ም54) የአባታችም ፀሎትም እንደማይደርቅ ውሃ ምንጭ ወይም እንደትንፋሽ ሌሊትና ቀን የዕንባውም አወራረዱ ያለልክ ነበር ፤ ከሁሉ ግን የሚበልጠው ሥራው የስጋ ፈቃድን መተውና መንፈስ ቅዱስን የተመሉ አባቶች የከለከሉትን ወዳሴ ከንቱ መናቅ ነበር፡፡

              እንግዲህ ምን እንላለን? ለሃዋርያት ከአገር አገር የዞሩበት ፡ ሃብታም ሲሆኑ በድህነት የተመላለሱበት ፡ ስለክርስቶስ ሲሉ የተነቀፉበት ፡ የተገፉበት ፡ የተራቡበት ፡ በመስቀል ተሰቅለው ፡ በሰይፍ ተቆርጠው ፡ በድንጋይ ተወግረው ፡ በእሳት ተቃጥለው ፡ በአራዊት ተበልተው ፡ እንደወንበዴ እንደወንጀለኛ ስለመሞታቸው ሽልማታቸው ምንድን ነው??  ሰውን ሁሉ ወደአማናዊው እውነት ይመልሱ ዘንድ ራሳቸውን ስለመካዳቸው ፡ ክርስቶስን ይሰብኩ ዘንድ በሁሉ ዘንድ የተናቁበት ፡ ወገን እንደሌላቸው ፡ መጠለያ ማረፊያ እንደሌላቸው በዱር በገደል ስለመቅበዝበዛቸው ደመወዛቸው ምንድን ነው?? ይህስ ደመወዛቸውን እኛ ምድራውያን እንደምን ልንለካው ይቻለናል? የክርስቶስ የፀጋው ስጦታ ከዚህ አለም ሃሳብ እጅጉን የተለየ የበለጠም ነውና ፡ ስጋዊ አእምሮን የሚያልፍ ነው ፡ ስጋዊ ህሊናም ሊረዳው አይቻለውም ፡ እኒህ ቅዱሳን ግን በእግዚአብሄር የተዘጋጀላቸውን አክሊል ከሩቅ እየናፈቁ መልካሙን ተጋድሏቸውን በትእግስት ተጋደሉ፡፡

              አባታችን ተክለሃይማኖትም ይህን ሁሉ ተጋድሎ ይፈፅሙ ዘንድ አስቀድመው ራሳቸውን ዝግጁ አደረጉ ፡ ክርስቶስን ለብሰው ክርስቶስን መስለው ለሚኖሩ የተዘጋጀውን የፅድቅ አክሊል ያውቁ ነበርና ፡ ስለዚህም ህይወታቸውን ሙሉ መልካሙን ግብር ፈፀሙ ፡ ሩጫቸውን ሮጡ ፡ ክርስቶስም ምድራዊ ድካማቸውን በቃ ይላቸው ዘንድ ጊዜው እንደደረሰ ባወቁ ጊዜ ይህ የሰማእታት በረከት ያልፋቸው ዘንድ አልወደዱምና ጌታችን ክርስቶስን እንዲህ ሲሉ ለመኑት ፦ “ጌታየ ወደ ሰማእትነት አደባባይ ሄጄ በስምህ እንድሞት እዘዘኝ”( ገድ ተክ  ም53፡22) ጌታችንም እንደሃዋርያት በትምህርት እንደሰማእታት ደምን በማፍሰስ ስለወንጌል እንደተጋደለ መሰከረለት እንዲህም አለው ፦ “መጋደልንስ ፈፀምክ ከሞት በቀር ምንም ምን  አልቀረህም” በማለት፡፡ ነገር ግን ጌታችን ክርስቶስ ምንም እንኳን ከሃድያን መናፍቃን ፡ አላውያንም ነገስታት አባታችን ተክለሃይማኖትን የሚገድሉት ደሙንም የሚያፈሱት እንዳልሆኑ ያውቃልና ስለእሱ ብሎ ዳግመኛም በስሩ ስላሉ ደቀመዛሙርቱ አርአያ ይሆን ዘንድ በፀሎት ፅሙድ በመሆን ፡ በፆም እጅጉን በመበርታት ፡ ከአለማዊም ምቾት በመራቅ ስጋውን ስለነፍሱ ንቋታልና ጌታችን ክርስቶስ የአባታችንን ሞቱን ከሰማእታት ሞት ጋር አንድ ያደርጋት ዘንድ ወደደ፡፡ የአቡነ ተክለሃይማኖትን ክብር ከሰማእታት ክብር ጋር አንድ ያደርግ ዘንድ ፤ ክርስቶስ አስቀድሞ ተሰዋ ፡ ሃዋርያትም እንደክርስቶስ ክርስቶስን ለብሰዋልና ተሰው ፡ ሰማእታትም ስለክርስቶስ ተሰው ፡ አባታችንም ስለክርስቶስ ስላደረገው ተጋድሎ ሞቱ እንዲሁ ተቆጠረለት፡፡

                  ዲያቢሎስ ክርስቶስን በአይሁድ ልብ ክፋትን አስርፆ ፡ በጲላጦስ አስወስኖ አሰቀለው ፡ መስዋእትም ሆነ ፤ ሰማእታትን ዲያቢሎስ በሰዋች አድሮ እንዲሰው አደረጋቸው ፤ አባታችንም ዲያቢሎስ የበሽታ ምንጭ እርሱ ነውና በበሽታ እንዲሞት አደረገው ፤ ነገር ግን ክርስቶስ በራሱ ፍቃድ የሞተ እንደሆነ ፡ ሰማእታትም ክርስቶስ በወሰነላቸው ቀን በክርስቶስ ፈቃድ የሞቱ እንደሆኑ ፡ አባታችንም ዲያቢሎስ አሽንፎት የሞተ አይደለም ፡ ነገር ግን በክርስቶስ ፈቃድ በበሽታ ይሞት ዘንድ መስዋእትም ይሆን ዘንድ ይህ ሆነ እንጂ፡፡ እንግዲህ እኔ ብርሃን ነኝ ያለ ጌታ እናንተ የአለም ብርሃን ናችሁ ብሎ ሃዋርያትን በሾመ ጊዜ የክርስቶስ ብርሃንነት እንዳልሻረ ፡ ሞቱንም ከሰማእታት ሞት ጋር አንድ አደረገ ፡ ስለክርስቶስ ሲሉ መከራን ታግሰዋልና ፡ አባታችንም ሰማእት ዘእንበለደም ተብለዋልና ሞታቸውን እንደራሱ ሞት እንደሰማእታትም ሁሉ ሞት ቆጠረለት፡፡

                 “ከዚህ በኅላ አባታችን ተክለሃይማኖት ተነስቶ የሀዋርያትን ስራ ይከታተል ጀመር ፤ ይሄውም ወንጌልን ለማስተማር ፡ እንደጌታ ለመቸንከር ፡  ወደ መስቀል ለመውጣት በክርስቶስ ስም ሁልጊዜ  በሰማእትነት ለመሞት ነው፡፡ የወዳጅና የዘመድ ፍቅር ፡ የገንዘብ ፍቅር አላሳዘነውም ፡ አቤቱ ጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ የመንግስተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ በቴን እንደተከፈተ ተውኩልህ እያለ ቤቱ እንደተከፈተ ትቶ ወንጌልን ለማስተማር ፈጥኖ ወጣ፡፡ ጌታየ ሆይ እንግዲህስ ለችግረኛው ለእኔ ያለአንተ ረዳት የለኝም ፤ ለደካማው ለእኔ ያለአንተ ደጋፊ የለኝም  ፤ ለወደቅኩ ለእኔ ያለአንተ የሚያስነሳኝ የለኝም ፤ ላዘንኩ ለእኔ ያለአንተ የሚያረጋጋኝ የለም ፤ ለደሃው ለእኔ ያለ አንተ መጠጊያ የለኝም ፤ ይህንም የመሰለ ሁሉ እያለ አባታችን ተክለሃይማኖት ከቤቱ ወጥቶ ሄደ”(ገድ ተክ ም29) ወንጌልን በቃል በተግባር ያስተምሩ ዘንድ አባታችን ከትውልድ መንደራቸው ተለዩ  ፤ ከክርስቶስ ተለይተው ጠፍተው የነበሩትን ይመልሱ ዘንድ አባታችን ከቤታቸው ወጡ ተለዩ ፤ የክርስቶስን መስቀል ይሽከሙ ዘንድ የስጋቸውን ፈቃድ ለነፍሳቸው አስገዙ ፤ ክርስቶስን ያስከብሩ ዘንድ ሰውነታቸው ካዱ ፡ ጎዱ፡፡

                  እንግዲህ አባታችን ተክለሃይማኖት ማለት እኒህ ናቸው ፦ ለሰውነታቸው እረፍትን ለስጋቸው ምቾትን ያሳዩአት ዘንድ ያልወደዱት አባታችን እኒህ ናቸው ፡ መከሩ ብዙ ሰራተኛው ግን ጥቂት እንደሆነ ተገንዝበዋልና ፡ ለሁሉ ክርስቶስን ሰብከው ፡ ሁሉን ክርስቲያን አድርገው እስኪጨርሱ ድረስ ተጋድሏቸውን ያስረዘሙ አባታችን እኒህ ናቸው ፡ የክርስቶስ ቅናት ግድ ብሏቸዋልና ፡ የዲያቢሎስ በህዝቡ ላይ መሰልጠን ልቦናቸውን አስቆጥቶት ነበርና ስጋቸው ያርፍ ዘንድ ያልወደዱ አባታችን እኒህ ናቸው ፤  “የሁሉ ፈጣሪ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው ፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው ፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው” እያሉ ባላመኑት ፊት ፡ በሚያስፈሩት ፊት ፡ ዲያቢሎስ በሚመለክበት ፡ አስማት ጥንቆላ በገነነበት ፡ ሰው መግደል ቀላል በሆነበት ፡ ክፋት በነገሰበት ፊት ለስጋቸው ሳይሳሱ የመሰከሩ አባታችን እኒህ ናቸው ፤ መገረፍን እየታገሱ ወንጌልን የመሰከሩ ፡ ወንጌልን በቃል በግብር የመሰከሩ ፡ ወርቅ ሃብትን እየናቁ ክርስቶስን የሰበኩ ፡ ክርስትናን የሰበኩ አባታችን ተክለሃይማኖት ማለት እኒህ ናቸው፡፡ የወንጌሉ ቃል ፅኑ ሆኖብን ለምንከላወስ ለእኛ የወንጌሉን የህይወት ኑሮ ያሳዩን አባታችን እኒህ ናቸው፡፡

የአብ ፍቅር ፡ የወልድ ቸርነት ፡የመንፈስ ቅዱስ አንድነት ፡ የእመቤታችን አምላጅነት  ፡ የአባታችን የአቡነ ተክለሃይማኖት ረድኤት በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን፡፡

ታምራት ፍስሃ
ሚያዚያ 28/2004

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount