Monday, May 21, 2012

በእውነት ክርስቶስ የዓለሙ መድኃኒት እንደ ሆነ ዓወቅን፤ አምነንበታልም - የዮሐንስ ወንጌል የ21ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.4፡27-42)


ሰላመ እግዚአብሔር ይብዛላችሁ፡፡
 ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማ ሄደው ነበር ብለናል /ዮሐ.4፡8/፡፡ አሁን ግን “መጡና ከአንዲት ደሀ ብቻ ሳይሆን ከሳምራይት ሴት ጋር ዝቅ ብሎ በመነጋገሩ ተደነቁ፤ ነገር ግን በግሩም ትሕትናው ስለተደነቁ ምን ትፈልጊያለሽ? ወይም ስለ ምን ትናገራታለህ? ያለ ማንም አልነበረም” /ቁ.27፣ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ Homily On John,Hom.33:3/።
  ወንጌላዊው እንደነገረን ሴቲቱ ውኃ ልትቀዳ ወደ ያዕቆብ ጕድጓድ መጥታ ነበር፡፡ ነገር ግን የክብር ንጉሥ ወደ ልቧ ሰተት ብሎ ሲገባ “ማድጋዋን ትታ ወደ ከተማ ሄደች” /ቁ.28/፡፡  በሐሴት ሠረገላ ተጭናም ወንጌሉን ለማፋጠን ተሯሯጠች፡፡ “ለሰዎችም ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ፤ እንጃ እርሱ ክርስቶስ ይሆንን?” እያለች መላ ከተማውን ጠራርጋ ታመጣቸው ነበር። የሚገርመው ሴቲቱ የምታመጣቸው ሰዎች እንደ እንድርያስ ወይም ደግሞ እንደ ፊሊጶስ አንድ ወይም ሁለት ሰዎች ብቻ አይደሉም፡፡ መላ ከተማውን እንጂ፡፡ ትጋቷም ከኒቆዲሞስ በላይ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ በወልደ እግዚአብሔር ቢያምንም እንደ እርሷ ግን በግልጥ ለመመስከር አልወጣም፡፡ በእውነት ይህች ሴት ከሐዋርያት ጋር ብትተካከል እንጂ አታንሥም፡፡ ሐሳብዋን ብቻ ይግለጥላት እንጂ እንዴት እንደምትነግራቸው እንኳን የቃላት ምርጫ አታደርግም፡፡ እናም “ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ፤ እንጃ እርሱ ክርስቶስ ይሆንን?”  ትላቸዋለች፡፡ ተጠራጥራ አይደለም፤ መጥተው ራሳቸው ለራሳቸው እንዲወስኑ እንጂ፡፡ ስለዚህም “ኑና እዩ፤ አይታችሁም እመኑ” እያለች ከነፍሳቸው እረኛ ጋር እንዲገናኙ ትፈልጋቸው ነበር፡፡ ሰዎቹም የምትነግራቸውን ነገር ለማየትከከተማ ወጥተው ወደ ጌታችን ይመጡ ነበር” /ቁ.29-30/። የሚገርመው ደግሞ ይህች ሴት አዋልደ ሰማርያን ላለማየት ብላ በጠራራ ፀሐይ ውኃን ለመቅዳት የመረጠች ሴት ነበረች፡፡ አሁን ግን እውነተኛው ፀሐይ ሲነካት ሐፍረቷ እንደ በረዶ ተኖ ጠፋ፡፡ ስለዚህም ቀድሞ ወደምታፍራቸው ሰዎች በመሄድ “አንድ ነብይን ትመለከቱ ዘንድ” ሳይሆን “ያደረግሁትን ሁሉ፣ ምሥጢሬን ሁሉ የነገረኝን ሰው ትመለከቱ ዘንድ ኑ” እያለች ሕዝቡን ጠራቻቸው /St.John Chrysostom, Hom.34:1/፡፡
 ይህም ሲሆን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ “ጌታችን ብዙ መንገድ በመሄድ ደክሟልና፤ ደግሞም ጠራራ ፀሐይ ነውና
የሚበላ ነገር እንስጠው” ብለው ቀረቡ፤ “መምህር ሆይ! ብላ” ብለውም ለመኑት። እርሱ ግንእናንተ የማታውቁት የምበላው መብል ለእኔ አለኝ” አላቸው /ቁ.31-32/። በእርግጥም የሳምራይቱን እምነት በልቷል፤ ጠግቧልም፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ግን እስራኤልን በበረሐ መናን እያዘነበ የመገበ ጌታ፣ በገዳመ ቆሮንቶስ 40 መዐልትና 40 ሌሊት ምንም ሳይቀምስ የጾመ አምላክ መሆኑን ልብ አላሉም ነበር፡፡ ስለዚህም ግራ በመጋባት የሚበላው አንዳች ሰው አምጥቶለት ይሆንን?” ይባባሉ ነበር። ጌታችን ግንየእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” እያለ የሰው ልጆችን መዳን በመብል መስሎ ይነግራቸው ጀመር /ቁ.33-34,Origen, commentary on John, Book13:309/። ንግግሩም ይቀጥልና እንዲህ ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ያብራራላቸዋል፡-“እናንተ ገና አራት ወር ቀርቶአል መከርም ይመጣል ትሉ የለምን? እነሆ እላችኋለሁ፥ ዓይናችሁን አንሡ አዝመራውም አሁን እንደ ነጣ እርሻውን ተመልከቱ” እያለ በሳምራይቱ ሴት የዘራውን ቃል ዕለቱ ተዘርቶ በሰዓታት ውስጥ ፍሬ አፍርቶ ወደምታመጣቸው ሕዝብ ያመለክታቸው ነበር /ቁ.35/።  እነርሱ ስለ ምድራዊውና እህል የሚሰበሰብበት ወራት ሲነግሩት እርሱ ግን ስለ አማናዊው እህል (የሰው ልጆች መዳን) ይነግራቸው ነበር፡፡ ጌታችን ይቀጥልና፡- “ልጆቼ ይህን ብቻ አይደለም፡፡ ዐይነ ልቡናችሁን አራምዳችሁ አንሡና ሰዎች የእኔን የወልደ እግዚአብሔር ሰው የመሆን ወንጌል የሚሰሙበት ሰዓት እንደደረሠ ዕወቁ፡፡ በሕግና በነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ተብሎ የተለሳለሰና የተዘራ የወንጌል እርሻ አሁን ፍሬ የሚያፈራበት ሰዓት ደርሷል፡፡ ወረደ ተወለደ ብላችሁ የምታጭዱ እናንተም ይወርዳል ይወለዳል ብለው ከዘሩት ከነብያት ጋር በአንድነት ደስ የምትሰኙበት ሰዓት እንደደረሰ ዕወቁ፡፡  የዘሩትም የምታጭዱም ሁላችሁም ለዘላለም የሚሆን የሕይወት ፍሬን የምትሰበስቡበት ወቅት አሁን ደርሷል አንዱ ይወርዳል ይወለዳል ብሎ ይዘራል አንዱም ወረደ ተወለደ ብሎ ያጭዳል የሚለው ቃል በዚህ እውነት ሆኖአልና። ስለዚህም እናንተ ይወርዳል ይወለዳል ብላችሁ ያልደከማችሁበትን ነገር ግን ነብያት ይወርዳል ይወለዳል ብለው ትንቢት የተናገሩለትን ወረደ ተወለደ ብላችሁ ታጭዱ ታስተምሩ ዘንድ ላክኋችሁ፤ ነብያት በመደመዱ ሐዋርያት ገደገዱ እንዲሉ ሌሎች ደከሙ እናንተ በድካማቸው ገባችሁ” ይላቸው ነበር /ቁ.36-38፣ ወንጌል ቅዱስ አንድምታ፣ ገጽ 475/።
 በዚሁ ሰዓት ሴቲቱያደረግሁትን ሁሉ ነገረኝ” ብላ ስለ መሰከረችው ቃል ከዚያች ከተማ የሰማርያ ሰዎች ብዙ አመኑበት፤ በሐሰት ትምህርት ተጠምደው ነበርና እውነት በሆነው በክርስቶስ ጥማቸውን አረኩ፤ በአንዲት ደሀ ሴት ምክንያት መጥተው ከያዕቆብ ውኃ ይልቅ ከሰማያዊው ምንጭ ጠጥተው ረኩ፡፡ ይገርማል! የሰማርያ ሰዎች ወደ ጌታ በመጡ ጊዜ ጌታችን ከእነርሱ ዘንድ እንዲኖር ለመኑት፤ እርሱም ስለ ፍቅራቸው በዚያ ሁለት ቀን ያህል ኖረ። ቃለ እግዚአብሔርንም አስተማራቸው፡፡ ስለ ቃሉም ከፊተኞች ይልቅ ብዙ ሰዎች አመኑ፤ እንደ አይሁድም ለማመን አንዳችም ምልክት አልፈለጉም /ቁ.39-41,Origen Ibid/፡፡  እንዲህ ሲያደርጉም ከተማቸውን ጥለው በመውጣት አባታቸው አብረሃምን መሰሉ /ዘፍ.12፡1/፡፡ እዚህ ጋር ሌላ በጣም የሚደንቅ ነገር አለ፡፡ እርሱም አይሁድ ነብያትን ጠንቅቀው ያውቅዋቸዋል፤ ሳምራውያኑ ግን አንድ ነብይ እንኳን አያውቁም፡፡ አይሁድ እንኳንስ ነብያትን መቀበል ይቅርና በመጋዝ እየተረተሩ በድንጋይ እየወገሩ ይገድሏቸው ነበር፤ ሳምራውያኑ ግን የነብይን ሳይሆን የአንዲት ምስኪን ሴት ምስክርነት ሰምተው ተመለሱ፡፡ አይሁድ ጌታችን ቃሉን አልቀበል ሲሉት በተአምራት ሊያቀርባቸው ሲፈልግ ከሀገራቸው እንዲሄድላቸው ይለምኑት ነበር /ማቴ.8፡34/፤ ሳምራውያኑ ግን ከእነርሱ ዘንድ እንዲኖር ይለምኑት ነበር ለማመንም ተአምራትን አልጠየቁትም ፡፡ ስለዚህም የሰማርያ ሰዎች በፍርድ ቀን በአይሁዳውያኑ ላይ ይፈርዱባቸዋል፤ መፍረዳቸውም በእምነታቸው ነው፡፡
 ከዚህ በኋላ ማለትም ሳምራውያኑ ከጌታ ዘንድ ለሁለት ቀናት ቤታቸውን ትተው ቃለ እግዚአብሔር ሲማሩ ከቆዩ በኋላ ባለ ውለታ ለሆነቻቸው ሴት እንዲህ አሏት፡-አሁን የምናምን አንቺ ስለነገርሽን ብቻ አይደለም፥ እኛ ራሳችን ከቃሉ ሰምተነዋልና፤ እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለሙ መድኃኒት እንደ ሆነ ዓወቅን፤ አምነንበታልም እንጂ” /ቁ.42,St.John Chrysostom Ibid/፡፡
ወዮ! በትሕትናህ ከፍ ያደረግከን ሳንወድህም የወደድከን አምላክ ሆይ ስለ ግሩም ፍቅርህ ምን እንላለን? ተመስገን ከማለት ውጭስ ምን መሥዋዕት አለን? ጌታ ሆይ! ፍቅርህን በኃጢአት በረዶ ስናቀዘቅዛት ጫጩቶችዋን እንደምትሰበስብ ደሮ ልታቅፈን መጣህ፡፡ ቅዱስ አባት ሆይ! እንደሳምራይቱ ሴት ሁል ጊዜ አንተን የሚያስተናግድ ልብ ስጠን፡፡ ዘርን ከሚሰበስቡት ወገን እንጂ ከተዘራው ጋር እንክርዳድን ከሚጨምሩ ወገኖች አታድርገን፡፡ አምላክ ሆይ! ሳምራይቱን ሴት እንድትሰብክ አልላክሃትም፤ እርሷም እንዲህ ዓይነት ምስክርነት ሰጥታ አታውቅም፡፡ ነገር ግን የፍቅርህ ሙቀት ሲነካት ያደረገችውን ሁሉ ከሐዋርያት በላይ አደረገችው፡፡ ከአንተ በተቀበለችውም ከተማውን ሁሉ ጠራርጋ ወደ አንተ አመጣቻቸው፡፡ ዛሬም የዚህችን ሴት ዓይነት ፍቅርና ቅናት እንዲሁም ትጋት አድለን፡፡ ፍቅርህ ገብቶን በፍቅርህ የጠፉትን በጎች ወደ በረታቸው የምንሰበስብ አድርገን፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን እንደዚህች ሴት ያደረግነውን ኃጢአት በአንድ ንስሐ አባት ፊት ለመናገርና ላለማፈር ሁል ጊዜ ብርታቱን ስጠን፡፡ በእውነት አንተ የዓለም ሁሉ መድኃኒት ነህና የዛለውን መንፈሳችን አንተን ይመለከት ዘንድ ቅዱስ መንፈስህን አትውሰድብን፡፡ አሜን!

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount