Monday, May 21, 2012

የገብረ ንጉሡ ልጅ መፈወስ- የዮሐንስ ወንጌል የ22ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.4፡43-ፍጻሜ)!!


  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!


“ከሁለቱ ቀኖችም በኋላ፣ ሳምራውያኑ ከእኛ ጋር ሁን ብለውት ለሁለት ቀናት ቃለ እግዚአብሔርን ሲያስተምራቸው ከቆየ በኋላ፣ እነርሱም የአይሁድ ወይም ደግሞ የሳምራውያን ብቻ ሳይሆን የዓለም ሁሉ መድኃኒት መሆኑን ካመኑና ለሴቲቱ ከነገሯት በኋላ ጌታችን ከዚያ ወጥቶ ወደ ገሊላ ሄደ” /ቁ.43/። ከተመቸን ብላችሁ በአንድ ቦታ አትኑሩ፤ ወጥታችሁ ወርዳችሁ አስተምሩ እንጂ ብሎ አብነት ለመሆን ከሰማርያ ወደ ገሊላ ሄደ /ወንጌል ቅዱስ አንድምታ ገጽ 476/፡፡ 


 ነገር ግን ብዙ ጊዜ ወደ ተመላለሰባት በኋላም አልቀበል ሲሉት “አንቺ ቅፍርናሆም እስከ ሰማይ ከፍ አልሽን? ወደ ሲዖል ትወርጃለሽ“ ብሎ ወደ ተናገረላት ወደ ቅፍርናሆም አልሄደም /ማቴ.11፡23/፤ ምክንያቱም “ነቢይ በገዛ አገሩ እንዳይከበር ኢየሱስ ራሱ መስክሮአልና” /ማቴ.13፡57/ /ቁ.44፣ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ Homily On The Gospel of John Hom.35/።
 “ወደ ገሊላም በመጣ ጊዜ፥ የገሊላ ሰዎች ራሳቸው ደግሞ ለገቢረ በዓል ወጥቶ ሳለ በኢየሩሳሌም ያደረገውን ተአምራት ሁሉ አይተዋልና አመኑበት” /ቁ.45፣ ዮሐ.2፡23/። እነዚህ ገሊላውያን ምንም እንኳን እንደ ሳምራውያን ያለ ምልክት ባያምኑም ቃሉም ሰምተው ገቢረ ተአምራቱንም አይተው ካላመኑት የአይሁድ ሰዎች ግን ይሻላሉ /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡ 


 ከዚህ በኋላ ጌታችንውኃውን የወይን ጠጅ ወዳደረገባት ወደ ቃና ዳግመኛ መጣ” /ቁ.46/። “ስለምን ዳግመኛ መጣ?” ቢሉ፡- “እናንተ የቃና ሰዎች ሆይ! ከዚህ በፊት ውኃውን ወይን ሳደርግ አይታችሁኛል፡፡ አሁን ደግሞ ያንን እምነታችሁ አጸናላችሁ ዘንድ ከልበ ደንዳኖቹ ከቅፍርናሆም ሰዎች ይልቅ ወደ እናንተ መጣሁ” ሲላቸው እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ለዚህም ነው ወንጌላዊው፡- “በቅፍርናሆም ልጁ የታመመበት ከንጉሥ ቤት የሆነ አንድ ሹም ጌታችን ከይሁዳ ወደ ገሊላ እንደ መጣ ሰምቶ ልጁ ሊሞት ስላለው ወደ እርሱ ሄደ ወርዶም እንዲፈውስለት ለመነው” የሚለን /ቁ.47/።
 
 ይህ ገቢረ ንጉሥ በእምነቱ ትንሽ ደከም ያለ ነበር፡፡ ጌታችን በጠባብ ደረት በአጭር ቁመት ሲመላለስ ቢያየው በሽተኞችን ካልዳሰሰ አጋንንትን በአካል ተገኝቶ ካልገሰጸ ማዳን የማይቻለው መስሎት ነበር፡፡ የፍቅር ንጉሥ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን እንኳንስ ዳብሶ እንኳንስ በቃል ተናግሮ በሐልዮም መፈወስ የሚችል መድኃኒት ነው፡፡ ለዚህም ነው ለገቢረ ንጉሡምልክትና ድንቅ ነገር ካላያችሁ ከቶ አታምኑም” የሚለው /ቁ.48/። ሰውዬው ግን አሁንም ምንም ጌታችን በአካል እዚያ ካልተገኘ በቀር ማዳን አይችልም ብሎ ማሰቡ ቀጠለ፤ ድውይ መፈወስ እንጂ ሙት ማስነሣት የማይቻለው ነው ብሎ ማሰላሰሉ ቀጠለ፡፡ ስለዚህም፡-ጌታ ሆይ! ማመኑንም አምናለሁ፤ ይልቁንም ብላቴናዬ ሳይሞት ፈጥነህ ወርደህ አድንልኝ” ይላል፡፡ መምጣቱና እንዲህ ማለቱ በራሱ ግን እምነት ነበር /ቁ.49፣ Gregory the Great, Foury Gospel Homilies, Hom.28/።  

 የእምነተ ጐደለዎችን አለማመን የሚረዳ ጌታም፡-ሂድ ልጅህ በሕይወት አለ” ብሎ የተሰበረ ልቡን ጠገነለት /ቁ.50/። እግዚአብሔር እንኳንስ ትንሽዋ እምነት አንዲት ኩባያ ውኃ እንኳን የማይንቅ ቅዱስ ነው፡፡ ስለዚህም የሰውዬውን ትንሽዋ እምነት ሳይንቅ ፈወሰለት፡፡
 ከዚህ በኋላ ሰውዬው ጌታችን የነገረውን ቃል አምኖ ሄደ”።እመን እንጂ አትፍራ” አይደል ቃሉ? እምነት ተራራን ያፈርሳል፤ እምነት በሰዎች ዘንድ አበቃለት አከተመለት የተባለውን ተስፋ ይቀጥላል፡፡ ለዚህም ነው ሰውዬው ጌታ የነገረውን ቃል አምኖ ወደ ሀገሩ ሲወርድ በመንገድ ባሮቹ አግኝተው፡-ብላቴናህ በሕይወት አለ” ብለው በቀጥታ ጌታ የነገረውን መልሰው የሚነግሩት /ቁ.51/።  ሰውዬው ምልክትን ፈልጎ ቢመጣም የጌቶች ጌታ፣ የነገሥታት ንጉሥ፣ የአማልክትም አምላክ የሆነው ክርስቶስ ግን እዚያ ሳይሄድ ፈወሰለት፡፡ አስቀድመን እንደተናገርነው ይህ ጌታ እንኳንስ ተናግሮ፤ እንኳንስ ዳብሶ፤ እንኳንስ ተዳብሶ አስቦም የሚያድን መድኃኒት ነው፡፡ ሰውዬው አሁን ወደ ሀገሩ ደርሷል፡፡ ባሮቹም የልጁን መዳን አብሥረውታል /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡ 

 እምነተ ደካማ ነበረ ብለን እንደተናገርን አሁንም ሰውዬው “በጎ የሆነበትን ሰዓት ጠየቃቸው”፡፡ እነርሱም ትናንት በሰባት ሰዓት ንዳዱ ለቀቀው” ብለውም ነግረውታል /ቁ.52/  ከዚህ በኋላ አባትዬው ጌታችን፡-ልጅህ በሕይወት አለ” ባለው በዚያ ሰዓት እንደ ሆነ አወቀ፤ ከመላ ቤተ ሰዎቹ ጋርም አመነ /ቁ.53/፡፡
 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መጥቶ ውኃውን ወይን ካደረገ በኋላ ያሳየው ሁለተኛው ተአምር ሁለተኛ ምልክት ይህ ነው”። ይህ ሁሉ ሲሆን፣ ድውዩ በቅፍርናሆም ሳለ ጌታ ግን በቃና ሆኖ በሐልዮ ሲፈውሰው ልቡ የተዘጋ አይሁድ እዚያው ቆሞ ነበር /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡ 

 ወዮ! ጌታ ሆይ! በእውነት አንተ የልብን ሐሴት የምትመልስ፣ የተሰበረውን የምትጠግን፣  የሕይወትም ምንጭ ነህና ከንጉሡ ቤት እንደመጣው ሹም መንፈሳችን የዛለው ልጆችህን ከወደቅንበት ከጥልቁ ወደ አንተ አንሣን፤ አምላክ ሆይ! ዛሬም ለማመን ምልክትን የምንሻ ብዙዎች ነንና አለማመናችንን እርዳው! ለሹሙ ያሳየኸውን ቸርነት ይህን ለማይገባን ለእኛም አድለን፤ አባት ሆይ! በዘላለማዊ ሕይወት መጽሐፍ ስምህ ተጽፎልሃል፣ ስምሽ ተጽፎልሻል፣ ኃጢአትህ ተሠርዮልሃል እንድትለን፣ በምግባር በሃይማኖት እንድታጸናን በቸርነትህም መንግሥትህን እንድታወርሰን፣ በመጣህ ጊዜ “ኑ እናንተ የአባቴ ብሩካን” ከምትላቸው ቅዱሳንህ ጋር እንድትደምረን እንማጸናሃለን አሜን ይሁንልን ይደረግልን!!

ተመሳሳይ ገጾች 

የዮሐንስ ወንጌል የ21ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.4፡27-42)

የዮሐንስ ወንጌል የ20ኛ ሳምንት ጥናት

የዮሐንስ ወንጌል የ17ኛ ሳምንት ጥናት



No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount