Saturday, October 4, 2014

ማኅሌተ ጽጌ፤ ምንጩ ትርጉሙና መልእክቱ (ክፍል አንድ)

በዲ/ ያረጋል አበጋዝ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መስከረም 25 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

 ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ኃይለ ቃልን ከትርጓሜ፣ ትርጓሜን ከምሥጢር እንዲሁም ደግሞ ምሥጢርን ከዜማ ጋር አስተባብረውና አስማምተው የሚደርሱ ሊቃውንት ባለቤት ናት፡፡ 5ኛው ..ዘመን የተነሣው ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ አምስቱን ጸዋትወ ዜማ ሲደርስ 14ኛው ..ዘመን የተነሣው አባ ጊዮርጊስ ደግሞ ሰዓታትን ደርሷል፡፡ በዚሁ ዘመን አባ ጊዮርጊስ ጋር ጥልቅ መንፈሳዊ ፍቅር የነበረው አባ ጽጌ ድንግልማኅሌተ ጽጌየተባለውን ድርሰት ደርሷል፡፡ ማኅሌተ ጽጌ ግጥማዊ አካሔድ ያለው ድንቅ ኢትዮጵያዊ ድርሰት ነው፡፡ ይህ ድርሰት በማንኛውም ጊዜ የሚጸለይ ቢሆንም በተለየ ሁኔታ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውለው ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 5 ቀን ድረስ ባለው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የስደት ዘመን ነው፡፡ በዚህ ወቅት በየሳምንቱ እሑድ ሌሊት በሙሉ የእመቤታችንን ከልጇ ጋር ወደ ግብፅ መሰደድና መንከራተት እያሰቡ የሚደረስ ምሥጋናና ጸሎት ነው፡፡
 
 በሀገራችን የመስከረምና የጥቅምት ወራት የአበባ ወራት /ዘመነ ጽጌ/ ናቸው፡፡ ይህም ወቅት ተራሮች በአበባ የሚያጌጡበትና ለዓይን ማራኪ የሚሆኑበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህም ዘመን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስስለ ልብስስ ስለምን ትጨነቃላችሁ? የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፡፡ አይደክሙም፣ አይፈትሉም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም፡፡ እግዚአብሔርን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጐደላችሁ እናንተንማ ይልቁን እንዴት እንግዲህ ምን እንበላለን ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ ...» /ማቴ.528-33/ በማለት የተናገረውን ቃል በማሰብ መጨነቅ የሚገባን መንግሥተ ሰማያት ለመግባት እንጂ በዚህ ዓለም ስላለው ነገር እንዳልሆነ ተራሮችን በአበባ ያለበሰ አምላክ በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረንን እኛን ለኑሮ የሚያስፈልገንን ምግብና ልብስ እንደማይነሳን እያሰብን የምንዘክርበት ወቅት ነው፡፡ እንዲሁም ክቡር ዳዊት «ተዘከር እግዚኦ ከመ መሬት ንሕነ ሰብእሰ ከመ ሳዕር መዋዕሊሁ ወከመ ጽጌ ገዳም ከማሁ ይፈሪ፤ አቤቱ እኛ አፈር እንደሆን አስብ ሰውስ ዘመኑ እንደሣር ነው እንደ ዱር አበባ እንዲሁ ያብባል ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ያልፋልና» /መዝ.1214-16/ በማለት እንደ ተናገረው የሰው ሕይወት በሣር ይመሰላል፡፡ ሣር አድጐ አብቦ ከዚያ በኋላ ይደርቅና በነፋስ አማካኝነት የረገፈው ሣር እየተነሣ የነበረበት ቦታ ስንኳ እስከማይታወቅ ድረስ ይሆናል፡፡ ሰውም ከአደገ በኋላ በሕማም ፀሐይነት ይደርቅና በሞተ ነፋስነት ይወሰዳል፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ መቃብር ሲወርድ የነበረበት ቦታ ይዘነጋል፡፡ ስለዚህ ዘመነ ጽጌ ሰው ዘመኑ እንደ አበባ በቶሎ የሚረግፍ መሆኑን በማሰብ ይህ ዘመን ሳያልፍ መልካም ሥራ ለመሥራት ትንሣኤ ኅሊና የሚነሣበት ጊዜ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ለዘመነ ጽጌ የሠራው ድጓም ይህንኑ የሰውን ዘመን አጭርነት የሕይወቱን ኢምንትነት በዚህ ሕላዌ የተፈጠረ ሰው በዚህ ዓለም ክፉ ሥራ መሥራት እንደሌለበት ሁልጊዜ በተዘክሮተ ሞት እንዲኖር የሚያስረዳ ነው፡፡

በዘመነ ጽጌ ቅዱስ ያሬድ ከደረሰው ድጓ በተጨማሪ ከላይ እንደተጠቀሰው 14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሣ አባ ጽጌ ድንግል ከዚሁ ዘመን ጋር የተያያዘ ድርሰት ደርሷል፡፡ ይህ ድርሰት በግጥም መልክ የተደረሰ በአብዛኛው አምስት ስንኞች ያሉት ሲሆን ብዛቱም 15 ያክል ነው፡፡ ይህም ድርሰት «ማኅሌተ ጽጌ» በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ ፍሬ ከአበባ አበባም ከፍሬ እንደሚገኘው ሁሉ ማኅሌተ ጽጌም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምንና ልጇን መድኃኒታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን በአበባና በፍሬ እየመሰለ የሚያስረዳ ድርሰት ነው፡፡ እርሷን በአበባ ሲመስል ልጇን በፍሬ እርሷን በፍሬ ሲመስል ደግሞ ልጇን በአበባ እየመሰለ ይናገራል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ «ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ ወየዓርግ ጽጌ እምጉንዱ፤ ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፤ ከሥሩም ቁጥቋጦ ያፈራል»  /ኢሳ.11፡1/ ብሎ ከእሴይ ዘር የምትገኘውን እመቤታችንን በበትር ከርሷ የሚገኘውን ክርስቶስን ደግሞ በጽጌ መስሎ ትንቢቱን ተናግሯል፡፡ አባ ጽጌ ድንግልም ድርሰቱን በዚሁ አንጻር በመቀመር እያንዳንዱን መልክዕ እመቤታችንንና ልጇን አስተባብሮ በጽጌና በፍሬ በመመሰል የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ በምሥጢር በታሪክ፣ በጸሎትና በመሳሰለው መልክ ድንቅ በሆነና በተዋበ ሁኔታ አዋሕዶ ደርሶታል፡፡  
 እመቤታችን ጣዕሟንና ፍቅሯን እንዲሁም ምስጋናዋን ሲናፍቁ የነበሩትን ቅዱስ ኤፍሬምንና አባ ሕርያቆስን ውዳሴዋንና ቅዳሴዋን እንደገለጸችላቸው ለፍቅሯ ሲሳሳ ለነበረው ለአባ ጽጌ ድንግል ደግሞ ይህንን ማኅሌተ ጽጌን እንዲደርስ አድርጋዋለች፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ማኅሌተ ጽጌ በመልክዕ አደራረስ ሥርዓት የተደረሰ ሲሆን ይህንንም ለመመልከት እንዲያመች በሚከተሉት ክፍሎች ከፋፍሎ ማቅረብ ይቻላል፡፡  
1. ጸሎት

በዚህ አገባብ ጸሎት ስንል በተለየ ሁኔታ ጸሎትነቱ የጐላውን ለማየት እንጂ ድርሰቱ በሙሉ ጸሎት ነው፡፡ ሌሎቹንም እንዲሁ ታሪክ፣ ተግሳጽ፣ ምሥጢር ተብለው መከፈላቸው በበዛውና በጐላው ለመግለጽ ነው እንጂ ሁሉም በሁሉ አለ፡፡ በጸሎትነታቸው ጐልተው ከሚታዩት ውስጥ የተወሰኑትን እንመለከታለን፡፡

1.1. አንብርኒ ማርያም ውስተ ልብኪ ከመ ሕልቀት፣
ወከመ ማዕተብ ፁርኒ በመዝራዕትኪ ልዕልት፣
በእንተ ርስሐትየሰ ኢትመንንኒ ንግሥት፣
እስመ ወሀብኩ ንብረትየ ለፍቅርኪ ሞት፣
ዘአሰገርዎሙ ለሰማዕት በጽጌሁ ሕይወት፡፡

ጠቢቡ ሰሎሞን «የምእመናንንና የክርስቶስን ነገር በምሥጢር በተናገረበት በመኃልይ መጽሐፉ «እንደ ማኅተም በልብህ እንደ ማኅተም በክንድህ አኑረኝ» /መኃ.96/ ይላል፡፡ ይኸውም የምእመናንንና የክርስቶስን አንድነት የሚገልጽ ነው፡፡ «አንብርኒ ማርያም ውስተ ልብኪ ከመ ሕልቀት፤ ወከመ ማዕተብ ፁርኒ በመዝራዕትኪ ልዕልት» ማለቱ እመቤታችንን እንደ ማኅተም በልብሽ አኑሪኝ በማለት በእናትነትሽ፣ በአማላጅነትሽ አትርሽኝ ካለ በኋላ «በእንተ ርስሐትየሰ አትመንኒ ንግሥት» ይላል፡፡ ይኸም ማለት አትርሽኝ በልብሽ አኑሪኝ ብዬ የምለምንሽ አንቺ እንዳትረሽኝ የሚያደርግ መልካም ሥራ ኖሮኝ አይደለም፡፡ ስለዚህ በሰውነቴ ክፋት ምክንያት በኃጢአቴና በወራዳነቴ ምክንያት እኔን ከማሰብ ከልቡናሽ አታውጪኝ በማለት እመቤታችን በርኅሩኅ ልቧ «መሐር ወልድየ ወተዘከር ኪዳንየ» እያለች እንድታዘክረን የሚያሳስብ ጸሎት ነው፡፡

ሶበ አተቦ ለማይ በቅዳሴኪ እንዘ ይጼሊ፣
ረሰዮ ኅብስተ ጽጌ ሃይማኖት ሳሙኤል ዘሐቅለ ዋሊ፣
ምሕረተ ወፍትሐ ለተአምርኪ አኀሊ፣
ሥረዪ ኃጢአትየ ወእጸብየ አቅልሊ፣
እስመ ኩሉ ገቢረ ማርያም ትክሊ፡፡ 
አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ቅዳሴ ማርያምን እየደገሙ ውኃው በተአምራት ኅብስት ይሆንላቸው ነበር፡፡ ይህን ተአምር ከአደነቀ በኋላ «ማርያም ሆይ ሁሉን ማድረግ ትችያለሽና ኃጢአቴን አስተስርይልኝ» ይላል፡፡ ጌታችን «እውነት እላችኋለሁ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ ይህን ተራራ ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም» /ማቴ.171/ በማለት ላመነ የሚሣነው ነገር እንደሌለ ተናግሯል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መልአኩ «ትጸንሻለሽ፣ ትወልጃለሽ ...» ብሎ ባበሠራት ጊዜ ይህ እንደምን ይሆንልኛል?  ብላ ስትጠይቅ «ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም» ሲላት በፍጹም እምነት ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ እንደቃልህ ይሁልኝ» በማለት የተቀበለች ናት፡፡ ይህንንም ቅድስት ኤልሳቤጥ መንፈስ ቅዱስን ተመልታ «ከጌታ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና የታመነች ብፅዕት ናት» /ሉቃ.1453 ብላ መስክራለች፡፡ ላመኑ ሁሉ የሚቻል ከሆነ እመቤታችን ግን ቅዱሳን ሁሉ የሚማጸኑትን አምላክ በሥጋ ወልዳ ያስገኘች ስለሆነች ለእርሷ የሚሳናት ነገር የለም፡፡ ስለዚህም ነው ላንቺ የሚሳንሽ ነገር የለምና ኃጢአቴን አስተስርዪልኝ፣ የከበደኝን ሁሉ አቅልይልኝ በማለት የለመነው፡፡

1.2. «ተአምርኪ ማርያም ተሰብከ በኦሪት፣
አመ ተሰነዓውኪ ጳጦስ ምስለ መለኮት፣
ዘርእየኪ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
ጸልልኒ በአዕፁቅኪ ሐመልማላዊት ዕፀት
ሦከ ኃጢአትየ ያውዒ ጽጌኪ እሳት፡፡

«ማርያም ሆይ ነበልባል ከሐመልማል ተዋሕዶ ሙሴ በደብረ ኮሬብ ባየ ጊዜ ተአምርሽ በኦሪት ተሰበከ ተነገረ፡፡ ምሳሌሽ በሐመልማልና በእሳት አምሳል የታየ ማርያም ሆይ ጽጌ ልጅሽ ኃጢአቴን ያጠፋልኝ ዘንድ በጥላሽ ሥር አስጠጊኝ፡፡”

ሙሴ በምድያም በስደት ሆኖ የአማቱን የዮቶርን በጎች እየጠበቀ ሳለ በኮሬብ ተራራ ድንቅ ራእይ ታየው፡፡ ቁጥቋጦው በእሳት ሲነድ፡፡ ቁጥቋጦውም ሳይቃጠል አየ፡፡ ዘጸ.33፡፡ ይህ የምሥጢር ተዋሕዶ ተምሳሌታዊ ራእይ ነበር፡፡ ሐመልማል የእመቤታችን ምሳሌ ሲሆን እሳቱ ደግሞ የመለኮት ምሳሌ ነው፡፡ የሐመልማሉ ርጥበት እሳቱን አለማጥፋቱ አምላክ ሰው ሲሆን ከመለኮቱ ክብር ዝቅ ያለማለቱ ምሳሌ ነው፡፡ እሳቱ ደግሞ ሐመልማሉን አለማቃጠሉ መለኮት ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ በተዋሐደ ጊዜ እንዳጸናትና እንዳደረገችው የሚያስረዳ ነው፡፡

ደራሲው የእመቤታችን ክርስቶስን የማስገኘት ተአምርና የእርሷ የአምላክ እናት መሆን ከጥንት ጀምሮ ሲነገር የኖረ መሆኑን ካስታወሰ በኋላ ጸሎቱን «ጸልልኒ በአዕፁቅኪ ሐመልማላዊት ዕፀትኮ ሦከ ኃጢአትየ ያውኢ ጽጌኪ እሳት» በማለት ያቀርባል፡፡ ይኸም ማለት « ከሐመልማል ጋር ተዋሕዶ የታየው እሳት ጽጌሽ/ ልጅሽ ክርስቶስ/ ኃጢአቴን ይቅር ይለኝ ዘንድ በአንቺ ሐመልማልነት አስጠጊኝ” ማለት ነው፡፡

ዳዊት «በአንቺ የሚኖሩ ሁሉ ደስ ይላቸዋል» /መዝ.867/ ብሎ እንደተናገረ በእመቤታችን እናትነትና አማላጅነት ጥላ ሥር የሚኖሩ ከልጇ ከክርስቶስ ሥርየተ ኃጢአትን አግኝተው፣ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ተጐብኝተው ደስተኞች እንደሚሆኑ የተናገረው ትንቢት መፈጸሙን የሚያስረዳ ነው፡፡

 ይቀጥላል…

1 comment:

FeedBurner FeedCount