Wednesday, September 30, 2015

በዶክተር ዓለማየሁ ዋሴ መጽሐፍ "እመጓ"ላይ የቀረበ አጭር ሥነ ጽሑፋዊ ዳሰሳ



ከዲ/ን ብርሃኑ አድማስ ምጽሐፈ ገጽ የተወሰደ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መስከረም 19 ቀን 2008 ዓ.ም.)፤- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የመጽሐፉ ርእስ - እመጓ
ደራሲ፡- ዓለማየሁ ዋሴ እሸቴ (/)
የገጽ ብዛት፡- 204
የኅትመት ዘመን፡- ነሐሴ 2007 ..(ሁለተኛ ዕትም)
ዋጋ - 65 ብር
መጽሐፉ ምንድን ነው?
ሲጀመር መጽሐፉ እውነተኛ ታሪክ ነው? ልቦለድ ነው? የጉዞ ማስታወሻ ነው? ወይስ ምን ልንለው እንችላለን? የሚሉትን ጥያቄዎች መልሰን ካልጀመርን መጽሐፉን የምንዳስስበትን መርህ ለመምረጥ ስለማያስችለን በትንሹም ቢሆን ማንሳቱ የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ የታሪኩን መጽሐፍ እንደ ልቦለድ፣ ሌላውንም በሌላ መንገድ ልንመረምረው አንችልምና፡፡
ይህን መጽሐፍ ካነበብነው ውስጥ አብዛኛዎቻችን በመጽሐፉ ውስጥ ያለው ታሪክ ወይም ቅዱሱ ጽዋ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ በሚለው ታሪክ እውነተኝነት መፈተናችን የማይቀር ይመስለኛል፡፡ እውነት አድርገን እንድንወስደው የሚገፉ ነገሮችን የያዘ መሆኑ በራሱ ደግሞ ብዙዎቻችን ለርግጠኝነትም እንዲዳዳን አስገድዷል፡፡ የመጽሐፉ አተራረክ ጉዞንና ፍለጋን መሠረት አድርጎ መዘጋጀቱ፣ በመጽሐፉ የተገለጹት መቼቶች (ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ) እውነተኛና የሚታወቁ መሆናቸው፣ ግርሃም ሃንኩክ ስለታቦተ ጽዮን ምልክትነት የሰጣቸው የሻርተር ሕንጻ ቅርጽና የወልፍራም ፓርዚባል ግጥም ትርክት ለታቦተ ጽዮን ምልክትነት ከማገልገል ይልቅ ለራሱ ለጽዋው ቀጥተኛ ምልክቶች የመሆን እድላቸው የሚያይል ተደርጎ መፈከሩና ጸሐፊውም ሃንኩክን መሞገቱ፤ እና በድርሳነ ዑራኤል ትርክት መሠረት በሥነ ስቅለቱ ቅዱስ ዑራኤል ከጌታ ጎን የፈሰሰውን ደምና ውኃ የረጨበት ጽዋ መንዝ ውስጥ እመጓ ተቀብሯል የሚለው ትውፊት ለመጽሐፉ በሚስማማ ሁኔታ መተረኩ መጽሐፉን እውነተኛ ነው ለማስባል ከሚገፉት ዋና ዋናዎቹ ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች መኖራቸው ግን መጽሐፉን የታሪከም ሆነ ታሪካዊ ልቦለድ አድርገው ሊያስወስዱት ግን አቅም ያንሳቸዋል፡፡
መጽሐፉ የታሪክ፣ የጉዞ ማስታወሸ፣ ግለ ታሪክና የመሳሰሉት ቢሆን ኖሮ ከጸሐፊው ባለሙያነት ጋር ተዳምሮ መሠረታዊ የሆኑ አላባዎችን ልናገኝበት እንችል ነበር፡፡ መጽሐፉ መግቢያ መቅድምና የመሳሰሉት ብቻ ሳይሆን የይዘት ማውጫ፤ ማጣቀሻ መጻሕፍት፣ በየምዕራፉ ሥር ለየምዕራፉ የሚሆኑ አርእስት እንደሌሉት ስናይ ከታሪክና ከመሳሰሉትሥነ ጽሑፎች ሊመደብ የሚችል አለመሆኑን ጸሐፊው አስቀድሞ ነግሮናል ማለት ይቻላል፡፡ ጸሐፊው ተመራማሪና ከዚህ ዓይነት ጽሑፎች ጋር ያለውን የሞያ ትውውቅ ለሚረዳ ሰው እንዚህ ሁሉ ታስቦባቸው የተደረጉ መሆናቸውን ለመረዳት አስቸጋሪ አይሆንምና፡፡ ወደ ውስጥ ዘለቅ ብለን ስናነብም አቀራረቡ የጊዜ ቅደም ተከተለን አለመጠቀሙ፣ እንዲያውም ምልሰትን ደጋግሞ መጠቀሙን ስናይ በፈጠራ ጽሑፍ አቀራረብ ላይ ያለውን ትውውቅም ስለምንረዳ መጽሐፉን እውነተኛ ወይም የታሪክ አድርገን ልንወስድ ይቸግረናል፡፡
አቀራረቡ ልቦላዳዊ የቴክኒክ አጻጻፍን ተከትሎ የቀረበ ታሪካዊ ልቦለድ ሊሆን አይችልም ወይ የሚል ጥያቄም ሊነሣ ይችላል፡፡ ታሪካዊ ልቦለድ በርግጥ በታሪክ ባለሞያዎች ዘንድ ዕውቅና ያለውን በእውኑ ዓለም በአንድ ታሪካዊ ጊዜ (Historical time) ውስጥ የኖሩ ሰዎችን ሕይወት መሠረት አድርጎ በልቦለድ መልክ የሚዘጋጅ ሥነ ጽሑፋዊ ሥራ ነው፡፡ በመሆኑም ምንም እንኳ የእውነት መዛባትና የታሪክ ሸፍጥን ሊያስተናግድ ባይገባውም የታሪክ አዋቂዎች ታሪክን በሚያቀርቡበት መደበኛ መንገድ ተጨባጭ ማስረጃዎችን እያቀረበ ትንታኔ እየሰጠ መሔድ ስለማይጠበቅበት ጥያቄው ሊነሣ ይችላል፡፡ ሆኖም እንደ ተባለው በታሪካዊ ልቦለድ ውስጥ ዐቢዩ ነገር አንድ የታወቀ ዕውናዊ ታሪክ መቅረቡ ስለሆነ ይህ መጽሐፍ ልብን ሰቅዞ በሚይዝ አቀራረብ ያቀረበልን የቅዱሱ ጽዋ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር ታሪካዊ ማስረጃ አለው ወይ የሚለውን ጥያቄ እንድናስቀድም ይገፋፋል፡፡
አንዳንድ ምዕራባውያን በገድለ ጲላጦስ ላይ ዮሴፍ ዘአርማትያስ በዕለተ ስቅለቱ ከጌታ ጎን የፈሰሰውን ደምና ውኃ የተቀበለበትን ገበቴ ነገር ሆሊ ግሬል (Holy Grail) በማለት ወደ አውሮፓ እንደሔደ የሚገልጹ ትርክቶች አሏቸው፡፡ ምንም እንኳ የሆሊ ግሬል እና የሆሊ ቻሊስ (Holy Chalice) ትርክት ራሱ በእነርሱ አንድ ወደ መሆን የሚመጣው 12ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ ቢሆንም በዕለተ ሐሙስ ጌታ ደቀ መዛሙርቱን ስላቆረበበት ጽዋ የሚናገር ምንም ዓይነት ታሪክ ምዕራቡን ጨምሮ እስካሁን በዓለም ላይ አልተገኘም፡፡ በቅዱሱ የቤተ ክርስቲያን ትውፊትም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ እርሱን አስመልክቶ የተተረከ ነገርም እስካሁን አላጋጠመኝም፡፡ ምዕራባውያንም ቢሆኑ 12ኛው ክፍለ ዘመን በፈረንሳይኛ ከቀረበውና በኋላ 13ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በእነ ወልፍራም ፓርዚባልና በሌሎች ተመሳሳይ ሚታዊ ሥነ ጽሑፎች ከተገለጸው የፈጠራ ሥራ በቀር ታሪካዊ በሆነ መንገድ ማስረጃ አቅርበው አስካሁን አለን አላሉም፡፡ ጌታ በዕለተ ሐሙስ ሥርዓተ ቁርባንን የመሠረተበትና ሥጋውን ደሙን ያቀበለበትን ጽዋ ታሪካዊ በሆነ መንገድ ለመፈለግ ቢሞከር ሊያያዝ የሚገባውም ጌታ የመጨረሻውን ራት ካበላበት ከማርቆስ እናት ቤት ጋር መሆን ነበረበት፡፡ እውነቱን ለመናገር ትርክቶቹ ከማርቆስ እናት ቤትና ከራሱ ከማርቆስ ጋር ቢገናኙ ኑሮ ለመጠራጠርም የተሻለ ዕድል ይሰጥ ነበር፤ ነገር ግን አልሆነም፤ እርሱ ቢሆን ደግሞ ታሪኩ ወደ አፍሪካ ያመራ ነበር፡፡ የእስክንድርያው መንበር መሥራች እርሱ ነውና፡፡ በዚሁም መሠረት እስካሁን ድረስ ቅዱሱ ጽዋ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩን የሚናገር የታሪክ አካል የለንም፡፡ ስለዚህ እመጓን በዚህ ሁኔታ ታሪካዊ ልቦለድም ብሎ ለመመደብ የሚያስችል ምንም ታሪካዊ ፍንጭ ቢያንስ ለጊዜው የለንም ማለት ነው፡፡
እንዲህ ከሆነ እመጓ በሥነ ጽሑፍ ዘርፎች ውስጥ የምትመደበው የት ነው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ከሌላ አቅጣጫ ማየት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ለነገሩ መጽሐፉ ውስጥ እንደ ባቡር ፍርጎ በተቀጣጠሉና አንድ አካል በሆኑ ታሪካዊ ሂደቶች የሚጠቃለለው ዋናው ታሪክ እውናዊ ካልሆነ የመጽሐፉን ምንነት ለማወቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ በአጭሩ መጽሐፉ ሐዲስ ሚቶሎጂን (Modern Myth) መሠረት አድረጎ የተዘጋጀ ፈጠራ የጉዞ ልቦለድ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምንም እንኳ ቀደም ተብሎ እንደተገለጸው ገዳማቱ በእውን ያሉና ከገዳማቱ ጋር የተያያዙት ታሪኮችም በአብዛኛው እውነተኝነት የሚታይባቸው ቢሆንም መጽሐፉን ከሚታዊ የጉዞ ልቦለድነት ሊያወጡት አይቻላቸውም፤ ዋናው የመጽሐፉ ትርክት ታሪክ የሚሰኝ አይደለምና፡፡ ስለዚህ ይህን መጽሐፍ መቃኘትና መፈተሽ የሚገባን ከዚሁ ከሐዲስ ሚቶሎጂ ሥነ ጽሑፋዊ የአቀራረብ መርህ በመነሳት ይሆናል እንጂ ከሌሎች መደበኛ ልቦለዳዊ ሥራዎች አንጻር እንኳ ለማየት የሚያስቸግር ይመስለኛል፡፡
እመጓ እንደ ሐዲስ ሚቶሎጂ መጽሐፍ
በአብዛኛዎቹ የሥነ ጽሑፍ ምሁራን ዘንድ እንደሚገለጸው ከሆነ የሚት መጻሕፍት በየትኛውም ማኅበረሰብ በታሪክ ውስጥ ያለፉ የማኅበረሰቡ አካላት ጀግኖቻቸውን፣ ታሪካቸውን፣ እምነታቸውን፣ አስተሳሰባቸውንና ፍልስፋዎቻቸውን የሚያስተላልፉበት፤ የሥነ ምግባር ሕጋቸውን የሚደነግጉበት የአኗኗር ዶግማ የሚቀርጹበት ሥርዓት ያለው ተረክ ነው፡፡ ሥርዓት ያለው የሚባለውም በአጥኝዎች ዘንድ ተደጋግሞ እንደሚገለጸው ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ አወቃቀርና ጠባያትን የያዘ ራሱን የቻለ መንገድ ያለው በመሆኑ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት እመጓን በትንሹም ቢሆን ለመረዳት አስፈላጊ የምላቸውን የአጠቃላይ ሚትና የሐዲስ ሚቶሎጂ ጠባይ በማንሳት ለመቃኘት እሞክራለሁ፡፡
ተጋዳሊ/ አርበኛ
በሚት ውስጥ (ሚት የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል የምጠቀመው ገላጭ በሆነ መንገድ ወደ አማርኛ ተተርጉሟል የሚል እምነት ስለሌለኝ መሆኑ ይታወቅልኝና) ከፍተኛውን ስፍራ ከሚይዙት ነገሮች አንዱ ተጋዳሊ ወይም አርበኛ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት በእመጓ ውስጥ የምናየው ተጋዳሊ ወይም አርበኛ ለጊዜው ሲሳይ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ለጊዜው ያልኩት በኋላ ፍካሬ ላይ ስመጣ በእኔ እምነት ጀግናው ወይም ተጋዳዩ ስለሚለወጥ ነው፡፡ የሥነ ጽሑፍ ባለሞያዎችም ሆኑ የሚት ፈላስፎች አንድ አርበኛ ሊሆን የሚችለውን ነገር በብዛት አትተዋል፡፡ ስለዚህም የእመጓውን ሲሳይ ቢያንስ ከጥቂቶቹ የአርበኛ አላባውያን አንጻር መቃኘቱ በመጽሐፉ ውስጥ ሊተላለፍ የተፈለገውን ለመርዳት ይጠቅማልና በትንሹ ልነካካቸው፡፡
 1) ከነባሩ አቋመ ማኅበረሰብ ያፈነግጣል፤
2) አርበኞች ወይም ተጋዳዮች ማኅበረሰቡ በተጨነቀበት ውስጥ የሚደርሱ አካላት ናቸው፤
3) በማኀበረሰባቸው ወይም በሚታገሉበት ዓለም ውስጥ ትልቅ ተጋድሎ ይጠብቃቸዋል፤
4) እነርሱም አንዳች የተለየ እርዳታ ወይም ሃይል በማግኘት ከመከራው ያመልጣሉ፤ በተጋድሎም አሸናፊ ይሆናሉ፤
5) መመረጥ - ወደ ሆነ ቅጽር መዝለቅን - በረከትን ወይም ድልን ይዞ መመለስን ያሟላል፡፡
መለየት፣ መመረጥ ወይም መጠራት
ከጀግናው ወይም ከተጋዳዩ ጋር ተያይዞ የሚመጣውና የማይቀረው የሚት አላባ ደግሞ መመረጥ ወይም መለየት ነው፡፡ ይኸውም ተጠሪውን አካል ከሚኖርበት እውናዊ ዓለም ወይም ከተለመደው ሕይወት ውስጥ ወደ ተለየ ተጋድሎና ዓላማ ወይም ማኅበረሰቡ አልተገነዘበውም ተብሎ ወደ ታሰበው ረቂቅ ወይም ስውር ነገር የሚጠራ ነው፡፡ ባለሞያዎች እንደሚሉት ጥሪውም የማኅበረሰቡን ወግ ባሕል እምነትና ሥርዓተ ማኅበር ተከትሎ በተለያየ መንገድ ሊከናወን ይችላል፡፡
ከጥሪ ጋር ተያይዞ ቢያንስ ሁለት ነገሮችን መያዝ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ የመጀመሪያው የተጠራው አካል ለተጋድሎ የሚጠራ እንደመሆኑ መጠን በሂደቱ ውስጥ ካለ ማኅበረሰብ ጋር የሚፈጠረው ቅራኔ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ትግሉን የተመለከተው ነው፡፡ ትግሉ የሚጀመረው ተጠሪው ጥሪውን ከሰማ በኋላ ፍርሃቱን አርቆ ጥሪውን ተቀብሎ ለመቀላቀል በሚደረግ የራስ ትግል ሆኖ በኋላ ደግሞ የሚፈልገውን አንዳች ነገር ለማግኘት ወይም የተጠራለትን ዓላማ ለማሳካት የሚፈጽመው ተጋድሎን ከሚፈጽመበት ሁኔታ ጋር የሚተርክ ይሆናል፡፡
በእመጓም ውስጥ በደንብና በጉልህ ከምናያቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ ይሔንኑ መለየት ወይም መመረጥን የሚመለከት ነገር ነው፡፡ በመጽሐፉ ገጽ 36 ላይ በምልሰት ትረካ የቀረበውና የፍለጋው የመጀመሪያ ጉዞ የሚሆነው የሲሳይ በገዳማውያኑ ዘንድ መመረጥና ታመሐል መድኃኒቱ ደግሞ እኛ ጋር አለለና በቶሎ ተብሎ መጠራቱ ነው፡፡ ጥሪው ደግሞ ለምን እንደሆነ መጽሐፉን ያነበብን ሁሉ በቀላሉ ልንረዳው የምንችለውና በመጽሐፉ በተለያዩ ቦታዎች በተለይም በእማሆይ እሴተ ማርያም ለሲሳይ ሲብራራ የምንሰማው በኋላም በፍጻሜው ላይ እንደምናየው የቅዱሱን ጽዋ ታሪክ ማስተዋወቅና ከበረከቱ ማሳተፍ በሚል ታሪክ መሰል ነባር ባህለ ገዳማተ ኢትዮጵያን ተከትሎ የቀረበ የሕይወት ጥሪ ነው፡፡
ትግሉን በተመለከተም እጅግ በጥሩ ሁኔታ ቀርቧል፡፡ ከመጀመሪያው ጥሪ ቀጥሎ ወዲያው የሚከተለው የሲሳይ ፍርሃትና ድንጋጤ ነው፤ ከዚያም የራሱን የውስጥ ትግልና ክርክር ካሳየ በኋላ የጥሪው ድምጽ አሸንፎ ጉዞውን ሲጀምር ቢታይም የራስ ትግሉ የሚፈልገውን ነገር ምንነት እስከሚያውቅበት ጊዜ ይቆያል፡፡ ወደ አሜሪካ ተጉዞ የሚፈልገው ነገር ምን እንደሆነ ካወቀ በኋላ ግን ግራ መጋባቱና ፍርሃቱ ይጠፉና ደስተኛነትና ጉጉት ይተካሉ፡፡ ከዚህ በኋላም እልህ አስጨራሽ ትግሉንና ውጣ ውረዱን በሙሉ በግልጽ የሚታይ ሆኖ ቀርቦልናል፡፡
በእመጓ ውስጥ ያለው የልዕለ ተፈጥሮ ረድኤት የሚታየው ግን በቀጥታ በተጋዳሊው በኩል ሳይሆን በተጋዳሊውና በልዕለ ተፍጥሮው ኃይል መካከል ባሉት በየገዳማቱ በሚገኙት መነኮሳት በኩል ነው፡፡ ከመጀመሪያው ከናዳ ማርያም ገዳም ጉዞው ጀምሮ የመነኮሳቱ አንዳች ትንቢታዊና ምሥጢራዊ ንግግር በተለይም ቆለኛዋ እማሆይ እና የአቡነ አሮኑ ዓይነ ስውር አባት ምሪትና ከአባ አድሪል አጽም ጋር ማገናኘት ይህንኑ ልዕለ ተፈጥሮአዊ ኃይል ወይም በመቼቱ መሠረት የፈጣሪን ርዳታ፣ ፈቃድና የጊዜውን መድረስ ባሕል አመላካች ነው፡፡
ጉዞ
በሚት ውስጥ ጎልተው ከሚታዩት ነገሮች አንዱ አርበኛው ወይም ተጋዳሊው የሚያደርገው ጉዞ ነው፡፡ በዚህ ጉዞ ውስጥ በየትኛውም ትውፊትና ሃይማኖታዊም ሆነ ባሕላዊ ትርክት ውስጥ እንደሚታወቀው ያለ ብዙ ዓይነት ውጣ ውረድን ወይም ድካምንና ውጣ ውረድን የሚያሳይ ጉዞ አለ፡፡ ጉዞው የተጋድሎ አካል ሆኖ አርበኛው ወይም ተጋዳዩ ያደረገውን ሂደት የከፈለውን ዋጋና መሥዋዕትነት እንዲሁም ይዞት የሚመለሰውን ድል ወይም በረከት የሚያሳይ ነው፡፡ በእመጓም ሲሳይ በየገዳማቱ በጎጃም ጀምሮ በወሎ በጎንደርና በሰሜን ሸዋ ያደረገውን አልህ አስጨራሽ ጉዞ፤ የቃላቱን ትርጓሜ ለማወቅ ወደ አሜሪካ የሄደበትን ጉዞና በእያንዳንዱ ጉዞ ይዞት የሚመለሰውን ድል ወይም ውጤትና በተለይም በድምሩ በፍለጋ የተሰማራበን ቅዱሱን ጽዋ በማግኘት የተፈጸመውን አስደማሚ ጉዞ ይተርካል፡፡

ውስጣዊ/ መንፈሳዊ/ ኅሊናዊ ጉዞ
ውስጣዊ ጉዞ አርበኛው ወይም ታጋዩ በራሱ ኅሊና ውስጥ የሚያደርገው ጉዞና የሚደርስበት ሁኔታ ነው፡፡ በእመጓ ውስጥ ዋናው ጉዞ ይህም አልፎ አልፎ ብልጭ ድርግም ሲል ታይቷል፡፡ በተለይ በእመጓ ቆላ አፋፍ ላይ በምናብ ምጥቅ ብሎ ይሄድና ስለ እመጓ ቆላ እና ስለጽዋው ሁኔታ የሚተርክበትን ሂደት እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡
ቅጽር ዘለቃ
ከዚሁም ጋር ቢመት ውስጥ የማይቀረውና በተጋድሎው ውስጥ የሚገለጸው ቴዎድሮስ ገብሬ ቅጽር መዝለቅ ሲል የገለጸው (Crossing of the threshold) በአግባቡ ይታያል፡፡ በእኔ እምነት የሲሳይ ለዚህ ሁኔታ መታጨት በራሱ እንደ መጀመሪያ ሽግግር ሊቆጠር ይችላል፡፡ ካዘገየነው ግን የእነ አባ አክሊሉና የእነ እማሆይ እሴተ ማርያም ቁልፍ ምስጢር ጠባቂነትና ይህን ለማለፍ የገጠመው ፈተናና ምክራቸውን እየሰማ በብዙ ትዕግሥት ካርታውን ለማግኘት የበቃበት ሒደት ይሄን የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡
ከዚህ የሚከተለው ደግሞ የሞት ሽረት ትግልን የሚጠይቀው የመጨረሻ ቅጽር መዝለቅን የሚመለከተው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ቅጽር የሚፈለገው ነገር ቅርስም ይሁን በረከት ወይም አንድ ውድ ተፈላጊ ነገር ያለበትን ቦታ ማግኘትና መግባትን የሚመለከት ነገር ነው፡፡ ተፈላጊው ነገር የሚገኝበት ጥበቃው ጠንካራ የሚሆንበት አደገኛ ጠባቂዎች የሚበዙበትና ልዕለ ተፈጥሮ ሃይልም የሚከሰትበት አደገኛ ቦታ ሊሆን ይችላል፡፡ አርበኛውም በዚህ የሚያደርገው ተጋድሎና ውጤቱ የሚቱ ወሳኝ አካል ነው፡፡ በእመጓም ይህ የመጨረሻ ቅጽርን የማለፍ ሂደት የሚጠናቀቀው ቅዱሱን ጽዋ ወዳለበት ዋሻ በመግባት ነው፡፡ በዚህም ይህ ቅጽርን የማለፍ ሂደት ምን ያህል እየከበደና እየተውሰበሰበ እንደሄደና ተጋዳሊው እንዴት አሸናፊ ሆኖ እንደዘለቀ እመጓ እጅግ ልብ አንጠልጣይ በሆነ መንገድ በትረካ ስለምታቀርብ እንዲህ ዓይነት ዓላባዎችን በማሟላት ሂደት ውስጥ ብርቱ መጽሐፍ ሆና ትሰማኛለች፡፡
የእመጓ አስደናቂነት
የመጽሐፉ አስደናቂነት የሚመጣው ግን ቀደም ብዬ አርበኛውን ባብራራሁበት ወቅት ጠቆም አድርጌው ያለፍኩትን ሁኔታ በማስቀደም የምናየው ይሆናል፡፡ እመጓ ሐዲስ ሚቶሎጂን ተደርጋ ከተጻፈች በርግጥ ተጋዳዩ ከዚሁም ጋር ተጓዡ ማን ነው የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ይመስለኛል፡፡ በእኔ እምነት በእመጓ ውስጥ ላይ ላዩን ስናይ ተጓዡ ወይም ተጋዳዩ ሲሳይ ቢመስልም እውነተኛ ተጋዳዮቹ እና ተጓዦቹ ግን እን አባ ገዳማውያኑ ናቸው፡፡ በሐዲስ ሚት ውስጥ እንደምንረዳው ከሆነ የሲሳይን ጉዞ አስተውለን ካየነው ሲሳይ የሚጓዘው ገዳማውያኑ በጥንቃቄ በአቀነባበሩት መንገድ ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ በመጽሐፉ ገጽ 164 ላይ አባ አክሊሉ "አንተ ደግሞ ፍለጋው የማያልቀው የዚህ ትውልድ ናሙና ነህና" ሲሉ እንደገለጹት ሲሳይ የትውልዱ ናሙና ሆኖ እርሱ ቅርሱን እየፈለገ መስሎት ራሱ የሚፈለግ እንጂ ፈላጊ፣ ተጓዥ፣ ተጋዳይም አይደለም፡፡ ተጋዳይም፣ ተጓዥም እነ አባ ናቸው፡፡ ተፈላጊው ደግሞ ሥጋው ደሙ የተፈተተበት ጽዋ ሳይሆን በሥጋው በደሙ ሊከብር፣ እውነትና ታማኝነትን ይዞ ሁሉን ሊወርስ የሚፈለገው በሲሳይ የተወከለው ዘመናዊው ትውልድ ይመስለኛል፡፡ እንዲህ ከሆነ በእመጓ ውስጥ የምናየው ቅጽር ዘለቃ ሲሳይ ያካሔዳቸው እነ አባ አክሊሉን የማግባባት፣ የካርታውን ትርጉም ማግኘትና ወደ ዋሻው ውስጥ የመግባት ሒደቶች ሳይሆኑ እነ አባ አክሊሉና ገዳማውያኑ የሲሳይን እና የእርሱን ትውልድ ልብ ለማግኘት የሚሞክሩባቸው አስደናቂ መሻገሮች ናቸው፡፡ በርግጥም በምርምር፣ በተጨባጭነት፣ በዘመናዊነትና በፍልስፍና ለሚመካና ሲሳይ ደጋግሞ እንደሚገልጽው ሁሉ ምስጢር ሆኖብናል የሚለውን የዚህን ትውልድ የአስተሳሰብ ቅጽር አልፎ ልቡን አግኝቶና ትውልዱን ማርኮ መመለስ ቀላል ተጋድሎ አይደለም፡፡
ስለዚህ በምናየው ትረካ ውስጥ የቅጽር ዘለቃው የሲሳይ ቅዱሱ ጽዋ ወዳለበት ዋሻ ቢመስልም መጨረሻ ላይ የምንረዳው ግን በገዳማውያኑ ሥርዓት ባለው መንገድ ወደ ሲሳይ ልቡና ውስጥ የሚደረግ የሕይወት ፍልስፍናን ይዞ የመግባት ትግል ይመስላል፡፡ ምንም እንኳ በሥጋ ተጓዡ ሲሳይ ቢሆንምና ተጋዳዩ እርሱ ቢመስልም ቀስ ብለን ስናየው ግን ተጓዦቹና ቅጽር አላፊዎቹ እነርሱ እንደሆኑ ለመረዳት ይቻላል፡፡ ይህም ከአባ አክሊሉ ንግግር በኋላ ሲሳይ ሸረካከተኝ የሚለውን በማስታወስ ልንረዳው እንችላለን፡፡ በዚህም መሠረት በእኔ እምነት ጀግናዎቹ እነ አባ የመጀመሪያ የቅጽር ዘለቃ ሙከራቸው ታመሃልና ሳትውል ሳታድር ወደ እኛ ና፤ መድኃኒቱ ደግሞ እኛ አለ የሚለው መልእክታቸው ነው፡፡ እንደምናስታውሰውም ይህ መልእክት ሲሳይን ረብሾታል፤ ማለትም ወደ ልቡ ገብቷል፤ ስለዚህም እነርሱ ወዳሉበት አስጉዞታል፡፡ የእርሱን ዘመናዊነት፣ ተመራማሪነት፣ አዋቂ ነኝ ባይነት የሚያውቁት እነ አባ ደግሞ ቀስ ብለው በብልሃትና በጸሎታቸውም ኃይል ቀስ በቀስ የእርሱን አላስፈላጊ የአመክንዮ አጥሮች እየደረማመሱ ለመግባት ሲንደረደሩ ይታያል፡፡ ሁለተኛው የእነ አባ ቅጽር ዘለቃ የሲሳይ ቅርሱን የማግኘት ጉጉቱን ተገን አድርጎ ራሳቸው አባ አክሊሉንም ሳይቀር በሰላ ንግግሩ አሳምኖ ፍንጭ አገኛለሁ ብሎ ከሞከረው ተዋስኦ ላይ የሚነሣው የአባ አክሊሉ ንግግር ነው፡፡ በመጽሐፉ ከገጽ 162 እስከ 165 ላይ ባለው የአባ አክሊሉ ንግግር ላይ እንደምንረዳው ጋላቢ ፈረስ ላይ እንደሚንጠለጠል ገብስ ከፊት ለፊት በሚያሳዩት የሚያስጎመጅ ቅርስ ፍለጋ ተስቦ ሲሳይ እነ አባ ወዳዘጋጁት ወጥመድ ውስጥ ሰተት ብሎ ይገባል፡፡ ከዚህ በኋላ በደማሚት እንደሚደረማመስ ትልቅ የዐለት ቋጥኝ የሲሳይ የአመክንዮ ሙግት፣ የእውቀትና የፍልስፍና አጥር እስኪበጣጠስ ድረስ የአባ አክሊሉ የሰላ ትችት ይወርዳል፡፡ ራሱ ሲሳይም ሰውነቱ ሳይቀር በሰላ ጎራዴ ሲሸረካከት ይሰማዋል፡፡ የንግግራቸው አካሔድና ብርታትም የትኛውንም አንባቢ ከሚንቧችበት የትዕቢት ተራራ እንደ ማግኔት ጎትቶ የሚያወርድ እንደገለባ ክምር የተቆለለውንም ለራስ የተሰጠ የተሳሳተ ግምት በሰላ የሕይወት ሂስ የሚበታትን በመሆኑ ሁሉንም አንባቢ ከየተቀመጠበትየክብር ዙፋን አውርዶ ቁጭ የሚያደርግ ይመስለኛል፡፡ ይህ ደግሞ ተደራስያንን ሁሉ የጉዞው አካል አድርጎ ያማለለ ጉዳይ ስለሆነ የመጽሐፉን ሐዲስ ሚትነት ፍንትው አድረጎ የሚያወጣው የጽሑፉ አካል ይመስለኛል፡፡ ሆኖም የሲሳይ ልብ እንደገና ያንሠራራል፤ የተነገረውን የሕይወት ፍልስፍና ይረሳና ወደዚያው ወደሚፈልገው ቁስ የማግኘት ድካም ወጥመድ ውስጥ የበለጠ ይንደረደራል፡፡ በዚህ በደንብ አለመገኘቱን የሚያስታውሉት አባ አክሊሉም ተጨማሪ ፍንጭ ይሰጡና በእርሳቸው ምክርና ትምህርት ከተናደው የሲሳይ የልብ ቋጥኝ ሥር ያለውን መሬት ውስጥ የተደበቀ ዐለት መንቅሎ ለመጣል መለኮታዊ እርዳታን ታሳቢ ያደርጋሉ፤ ስለዚህም እርሱ ፈልጎ ያገኘ እንዲመስለው ለመርዳት እየተጠነቀቁ ቅርሱ ወዳለበት ዋሻ ሊያስገባ የሚችል ደምሳሳ ጥቁምታ ይሰጡታል፤ የሲሳይን ተመራማሪ ፈላጊና አግኝ ነኝ ባይ ሥነ ልቡና አውቀውታልና፡፡ ስለዚህም ሲሳይ ወደ መጨረሻው ቅጽር ገባሁ ሲል እነ አባ ወደ ሲሳይ ልብ ዘልቀው ገብተው ጠጣር ዐለቱን ይፈነቅላሉ፤ በደረሰበት መለኮታዊ የሃይል ግጭት ሲሳይ ባለማመን የጠጠረ ልቡን ነቅሎ ጥሎ ይወጣል፤ እነ አባም የመጨረሻው የልቡ መካከል ገብተው ጠንካራ የእውቀት የፍልስፍናና የአመክንዮ አጥሮቹን ዘልቀው ገብተው ልቡን ማርከው አሸንፈው ይወጣሉ፡፡ ስለዚህም እመጓ ላይ ላዩን ለሚያያት ሲሳይ የተጓዘባት የምትመስል ነገር ግን እነ አባ ወደ ትውልዱ የተጓዙባት ድንቅ ሚታዊ የጉዞ ልቦለድ መጽሐፍ ናት፡፡ ከዚህም እመጓን ዘመናዊ ወይም ሐዲስ ሚቶሎጂ የሚያሰኛትን አንዱንና ዋናዉን ነገር አቅርቤ እቋጫለሁ፡፡
እመጓና ፍልስፍና
የሚት አጥኚዎች እስካሁን ካሏቸው ክርክሮች አንዱ ሚትና ፍልስፍና ያላቸውን ግንኙነት በተመለከተ ነው፡፡ ክርክሩ ሚት የፍልስፍና አካል ነው፤ አይ ራሱ ፍልስፍናም ሚት ነው የሚል እንደሆነ በጉዳዩ ላይ የሚጽፉ አካላት ይጠቅሳሉ፡፡ ሁለቱም ጎራዎች የየራሳቸው ትንታኔ፤ ደጋፊና ተቃዋሚ ያላቸው ናቸው፤ የማነሳው በእኛ ሀገር ከዚህ አንጻር ለሚደረግ ጥናት እመጓ ለማሳያነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚኖራት መሆኑን ለመጠቆምና እኔን ወደሚስበኝ ነገር ለመንደርደር እንጂ ክርክሩ ውስጥ ለመዝለቅ አይደለም፡፡ ክርክሩን የሚያስነሳው መሠረታዊ ጉዳይ ግን ሁለቱም ስለሕይወት በተለይም ስለ ሰው ልጅ ሁለንተና ስለ ማንነት ከመጠየቅ አንሥቶሕ ይወትን፣ አስተሳሰብን፣ አኗኗርን፣ ጥቅምን፣ ጉዳትን፣ የመሳሰሉትን የሚፈክሩ በመሆናቸው ነው፡፡
ቴዎድሮስ ገብሬ "ሚት የሰው ልጅ የሚኖርበትን ዓለም ዝብርቅርቅ ዓለም ለመረዳት፣ እንዲሁም የተረዳውን ይህንኑ ዓለም መልክ ለማስያዝ የሚሞክርበት ልማድ ነው" ( በይነ ዲስፕሊናዊ የሥነ ጸሑፍ ንባብ፤ 2001 ገጽ 67) በማለት የሚገልጽበትን ፍልስፍናዊ ሀሳብ ብወስድ እመጓ አሁን በሀገራችን ያለውን ሁኔታ ዝብርቅርቅ ሁኔታ ለመግለጽ ለማሳየት ለመፈከርና በመጨረሻም መልክ ለማስያዝ የሚደረግ ጥረትን ለመጀመር ወይም የተጀመረውን ለማስፋፋት የተፈጠረች ድንቅ የጉዞ ልቦለድ ናት ማለት ይቻላል፡፡ በእመጓ ውስጥ በእኔ እምነት የአንድ የተማረ በተለይ ከሰሜን ኢትዮጵያ የሆነ የእኛን ዘመን ሰው በቀዳሚነት መሪ አድርጋ በሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ያለ መዳከርን በዜጎች መካከል ያለ ዝብርቅርቅ ሕይወት ገላልጣ ካቀረበች በኋላ ፈር ለማስያዝ የሚደረግ የጥረት ሀሌታ ይዛ ብቅ ያለች የሕይወት ፍልስፍና መጽሐፍ ትመስለኛለች፡፡ ለዚህም ማስረጃዎቼን እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡
1) የመጽሐፉ ዋና ታሪክ ቅዱሱን ጽዋ በመፈለግ በሚመስል ተረክ ላይ ማጠንጠኑ
ቅዱሱ ጽዋ እንደምናውቀው ደመ አምላክን ማቀበል በራሱ በአምላክ የተጀመረበት ቅዱስ ንዋይ ነው፡፡ እንደ ክርስትና አስተምህሮ ደግሞ የሰው ልጅ ከሚመገበው ነገር ብቸኛው ሕይወት ያለውና ሕይወትንም መስጠት የሚችለው ሥጋውና ደሙ ብቻ ነው፡፡ በትረካ ላይ እንደምናየው ደግሞ ይህን ቅዱስ ጽዋ ሚጠብቁ እንኳ ወይም ያዩት ቢሞቱም አስከሬናቸው አይፈርስም፡፡ ስለዚህ ተጓዥ በሚመስለን በሲሳይ ዘንድ መረዳት ያለው ባይሆንም ፍለጋው ከሕይወት ጋር ግንኙነት እንዳለው መረዳት ይቻላል ማለት ነው፡፡ የሚያሳዝነው ግን ሲሳይ ጽዋውን እንጂ ጽዋውን እንዲህ ተፈላጊ ያደረገውን መርሳቱ ነው፡፡ በደራሲው ማሳየት የተፈለገውም ይኸው ይመስላል፡፡
2) ሁለተኛውና ዐቢዩ ነገር ደግሞ ጉዞው የሚጀመረው "ታመሐልና እኛ የገዳም አባቶች ደግሞ መድኃኒቱ አለን" በሚል መልእክት መሆኑ ነው፡፡ በዚህ መልእክት ተደናግጦና ራሱን ክርክር ውስጥ ከትቶ የቆየው ሲሳይ ከሔደና ትንሽ ከተጓዘ በኋላ የሚፈልገው ነገር ሌላ መስሎት ቢጓጓም የሚጠናቀቀው ግን ስለ ሕይወት ያለውን መረዳት፣ አስተሳሰብ አስተካክሎ በመመለስ ነው፡፡ ሆስፒታል እንደተኛ የሆነውን እንዲህ ሲል ይገልጽልናል፡- ... “አሁንም ቅዱሱን የኪዳን ቅርስ ማየት ትፈልጋለህ?” አሉኝ  የብርሃን ጎረፉ ከመብረቃዊው ኃይል ጋር ድንገት በአእምሮዬ ብልጭ ያለ መሰለኝ፡፡  እርሳቸው ሆን ብለዉ ያጋጩኝ ይመስል ደንገጥ ብዬአባታችን አልፈልግም!” አልኳቸውአሁን ከሕመምህ ተፈወስክ፤ ወደ ልብህም ተመለስክአሉና መስቀላቸውን ግንባሬ ላይ ደገፍ አደርገው ሲያበቁእንደዚህ ልቡና ከገዛህና ማስተዋልን ገንዘብ ካደረክ፣ ከጥድፊያና በወረት ከመናጥ ራስክን ካቀብክ ቅዱሱን የኪዳን ቅርስ ማየት ትችል ይሆናልአሉ፡፡ ስለዚህ ጉዞው በሽታን በመፈለግ ተጀምሮ ድኅነትን በማግኘት ይፈጸማል ማለት ነው፡፡
3) የሕይወት ፍልስፍና ዝብርቅርቆች በደንብ ተገልጸውበታል
ገና በመጀመሪያወቹ ቅጠሎች ላይ ከይለፍ ቅጽ ጋር ተያይዞ የሚገጥመው ግራ መጋባትና ያለፈበት መንገድ፤ ሲሳይ ወደ አሜሪካ ሲሔድ ከጎኑ የተቀመጠችው የዲቢ ተሳፋሪ ለውጭ ሀገር ያላት ጉጉትና ተስፋ ከሲሳይ ትዝብትና ብስጭት ጋር፤ በአንጻሩ ሲመለስ የሚገጥመው ደግሞ አንድ የፒስኮር ልዑክ የነበረ አሜሪካዊው ስለኢትዮጵያ ያለው አመለካከት ትረካ ሲደማመሩ ራሱን የቻለ መልእክት ለማስተላለፍ የዋሉ ትርክቶች እንደሆኑ ለመረዳት ይጋብዛል፡፡ በርግጥም ኢትዮጵያ እኛ የምንሸሻት ሌሎቹ ደግሞ የሚጎመጁላት ሳትሆን አትቀርም፡፡
የጎጃም ባላባቶቹ ለፈረንጆቹ ያደረጉት ግብዣ፣ የአያ አሽኔ የሽምብራ አሸት ግብዣ፤ የደብረ ብርሃኗ እናት ለእንግዳ ለቤትና ለሕይወት ያላቸው ትርጉም፤ የመንዝ የሰርግ ባህል፤ የመነኮሳቱ ስጦታዎች ላይ የምናየው ልግስና መስጠትን የደስታ ምንጭ አድርጎ ሲያቀርብ በሌላ በኩል ደግሞ ገና ወደ አሜሪካ ሲሔድ ከሚገጥመው የበረራ የይለፍ ቅጽ ጋር ተያይዞ ያለው ውስብስብነት፤ ቁሳዊነት፣ ቁጥራዊነትና ሰብአዊነት ወይም ማኅበራዊነትን ማጣት አዲሱ ትውልድ ለሕይወት፣ ለምቾት፣ ለደስታ እና ለእርካታ የሚሰጠውን ትርጉም እንዲፈትሽ የቀረቡለት የሕይወት ተሞክሮዎች ይመስላሉ፡፡ በሚሲሲፒ ወንዝ ዙሪያ ተቀምጦ የታዘበው የተመጋቢነት፣ የተጠቃሚነት፣ እንኳን ሕይወትን መርገምንም እስከመፈለግ የሚደርስ ስግብግብነት፣ ሲሳይን እንግዳዬ ነህ የሚለው የፐሮፌሰሩ ጥቁር ቡና ብቻ ግብዣ፤ የነጩ አሜሪካዊ ትውስታና ናፍቆት ( ደስታንና እርካታን ፍለጋም መመለስ) ስናይ ሁሉም ነገሮች ታስቦባቸው የተሰናሰሉ ይመስላል፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ ሲሳይ ከአሜሪካም ከኢትዮጵያም የተመራረጡ ነገሮች እያደነቀ በተወሰኑት ደግሞ እያዘነ፤ እየተቸ፤ እየፈረደም መገለጹ የትውልዱን መምታት መሳከርና መያዣ መጨበጫ ማጣት ለመጠቆም መምሰሉ አሁንም ሲሳይ ላይ የሚካሔደውን ፍለጋ በጉልህ ለማሳየትና ፍለጋውን የተገባ ነው ለማለት የታሰበበት ይመስላል፡፡
4) ከዚህም በላይ ጽዋውን ይፈልገዋል እንጂ ሕይወትን አይፈልገውም
የሲሳይ ቁሱን የማየት፣ የማስተዋወቅ ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው፤ ሔዶ ለፓትርያርኩ መንገር፣ ጋዜጠኛ መጥራት፤ ለዓለም ማወጅ፤ የመሳሰሉትን ይተርክልናል፡፡ ከዚሁም ጋር ኢየሩሳሌም ስትጮህ፤ ቆጵሮስ ስትጣራ፤ ሮም ስትቃትት፤ እንግሊዝ ስትቦተልክ እመጓን ለምን ዝም አልሽ እያለ ይጠይቃል፤ ይህም ሕይወት የያዘችው ዝም ብላ ያልያዙት እንደያዙ ሆነው የሚያደርጉትን ጩኸት ለመሞገት ምን አልባትም ሕይወት፤ ደስታና እርካታ ያለው ብዙ በተወራለት ሳይሆን በተያዘው ተግባራዊ ኢትዮጵያዊ የሕይወት ፍልስፍና ወይም ባህል ውስጥ ነው ለማለትና የሕይወትን ፍልስፍናን ለማጠየቅ ይመስላል፡፡ ከዚህም ጋር ሲሳይ በአበባ ንገድ የገጠመውን ሲተርክ የፈረንጆቹ የአበባ ንግድ ትርጉምና የእኛ ሀገር ትርጉም ይለያያል፡፡ እንደ ነጮቹ ከሆነ ኢትዮጵያ አበባ ከማምረት በፊት የግድ ለዳቦ የሚሆኑትን ሰብሎች ብቻ ማምረት አለባት፤ ፍቅርን ለመግለጽ፣ አበባ ለመስጠትና ለመነገድም ገና ነሽ ዓይነት መልእክትና አበባ በእኛ ሀገር እኛ ባናመርተው እንኳ በተፈጥሮ የተሰጠንና ያለን መሆኑን መዘንጋት ያለበት መሆኑን ጠቁሞ ለንግድ ታስቦበት ባይደረግም ሲጀመር የአበባ አገሩ የት ሆነና ለማሰኘት የቀረበ ይመስለኛል፡፡ በዚያውም ደራሲው የአበባም የፍቅርም የስጦታም የልግስናም ሀገሩ የት ሆነና እያለ የሚሞግት ይመስላል፡፡ ይህን የምዕራቦቹንና የእኛም ትውልድ እየተጋራው ያለውን የሕይወትና የመሳሰሉት ትርጉም ለመረዳ ሁለት ነገሮችን ማንሣት የሚጠቅም ይመስለኛል፡፡ አንደኛው ብዙ ወንድሞቻን በሚዲያችን ሳይቀር ቀርበው “ሀገሬ ኢትዮጵያ ልማላሜሽ ማማሩ” የሚለውንና መሰል ገለጻዎችን የሚተቹበት ነው፡፡ ይህ ነገር ላይ ላዩን ሲያዩት እውነት ቢመስልም አባ አክሊሉ እንደሚገልጹት ግን እውነታው የተገላቢጦሽ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በሕይወታዊ ስብጥር (Genetic Diversity) ከከበሩት ሀገሮች አንዷ በመሆኗ ብቻ ሳይሆን ከአፋር ዝቅተኛ ስፍራ እስከ ሰሜን ተራሮችና የባሌ ተራሮች ያላትን ዕምቅ ሃይል ለመረዳት የእኛ ትውልድ ዐይን የሌለው በመሆኑም ጭምር ነው፡፡ ምዕራቡ ራሱን በልምላሜ ለመጠበቅ የሚያደርገው ጥረት ትልቅ ቢሆንም በተፈጥሮ ከእኛ ጋር ሊወዳደር አይችልም፡፡ ሆኖም የእኛ ትውልድ ይህን ሊረዳ የሚችልበት አቅም የሌለው ባለሞያወቹም የመንገርም ሆነ ይህን የማስተዋወቅ አቅም ያነሳቸው ከመሆኑም በላይ አንዳንድ ነገር ቢኖረንም ሲሳይ እንዳደረገው በምዕራባዊ ላቦራቶሪ ሲረጋገጥ ብቻ የሚለካ መሆኑን በደንብ የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡ በጓሳ መገራ ፓርክ ላይ የተደረጉት ገለጻዎችም ከዚህ በሽታችን እንድናገግም ለመጠቆም ያህል የቀረበ ጠብታ ይመስለኛል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ምዕራቡ ስለእኛ ያለውና እኛም ሳናውቀው የምናስተጋባው መሆኑን ለማየት ከጥቂት ዓመታት በፊት በጤፍና በመሳሰሉት ላይ ከፍተነው የነበረውን ዘመቻ ማስታወስ በቂ ይመስለኛል፡፡ ምዕራቡማ ከሰማነው የማይለው የለም፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ድሪም ላይነር አውሮፕላን በለንደን ሂትሮ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ እያለ ከባትሪው የእሳት አደጋ እንደደረሰበት መዘገቡን ተከትሎ የተሰጠውን የምዕራባውያን ምላሽ ማስታወሱ አብነት ሊሆነን ይችላል፡፡ እንደ ብዙዎቹ እምነት ከሆነ ኢትዮጵይ ሲጀመር ድሪም ላይነር አውሮፕላን ለምን ይኖራታል፡፡ ሲሳይም የተሳለው ይህንኑ ምዕራቡ ለእኛ የመደበለንን የኑሮ ፍልስፍና ተቀብሎ ግራ ሲጋባ በመሆኑ ሕይወትን ይፈልገዋል ለማለት ይቸግራል፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ጽዋውንም የሚፈልገው ለዓለም ለመናኘት እንጂ ጽዋውን ካከበረው ከክርስቶስ ደም ለመጠቀም አይደለም፤ ቢሆን ኖሮ ያን ያክል አይንከራተትም ነበርና፡፡ ስለዚህ ሲሳይ ሕይወት አለበት የሚባለውን ወይም የነካውን ይፈልጋል እንጂ ሕይወትን ራሱን አይፈልግም፤ ሌላው ቀርቶ ሕይወት ምን እንደሆነም ገና የገባው አይመስልም፡፡ ይዞረዋል እንጂ አያየውም፤ ቢፈልገውም ያልፈዋል፤ ቢያገኘውም አያውቀውም፤ ለእርሱ ሕይወት የክሳራ መጫወቻ ጠጠር ሆኖበታል ይመስላል፤ ለምን የዳንጋላዎቹን እረኛዎች አንሥቶ ስለ ባሕላዊው ክሳራ ጫወታ ሲትርክ ይጫወትበት የነበረው የሚያብለጨልጭ ድንጋይ መሰል ስባሪ ኦፓል መሆኑን የሚያወቀው ዘግይቶ ነውና፤ ስለዚህ ቢይዘውም እንደዚያ በሽንት ተቦክቶ የተቆፈረ ገደል ላይ የሚወረውረው መጫወታች እንጅ የከበረ ነገር መሆኑን አታውቁም የሚል ይመስላል፡፡
5) እርሱ የተማረውን ትምህርትና የሚኖርበት ፍልስፍና የሚሞገተው በገዳም አባቶችና እናቶች መሆኑ ከላይ ያልነውን የሚያጠናክርልን ደግሞ እርሱ የሚመገተው በገዳማውያኑ በመሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል በናዳ የነበረው የሥዕሎቹ ትርጓሜ አንዱ ነው፡፡ ይህንንም መንፈሳዊውን ነገርና ዓለም ሁሉ ለእርሱ ስላልገባውና በተማረበት የምርምር ሥርዓትና ሕግ መሠረት ባለመሆኑ ብቻ እንደ ሕልም የሚቆጥርን ምሁርና የኢንተርኔት ቻትን እንደ ምትሐት ሊገምት ከሚችል ገበሬ ጋር ብናነጻጽረው በቂ ሊሆን ይችላል፡፡ ለአንድ ገበሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ወንድሙ አሜሪካ ወይም ሌላ ሀገር ካለው ጋር የሚያደርገው ቻት ምትሐት የመምሰሉን ያህል መንፈሳዊውም ዓለም በተጫባጭነት ላይ ብቻ ለተመሠረተ አንድ ምሁር ቅዠት ይመስለዋል፡፡ ይህንን አባባሉንም በሥዕሉ አሳሳልና ፍልስፍና በአግባቡ ይሞገታል፡፡ አንድ ዓይና ሆኖ መሳል ለገዳማውያኑ ይኸው ማለት ነውና፤ ስላላወቀው ስህተት አድረጎ መውሰድ ለገበሬው ምትሐት ከመሰለው የሚበልጥ ሞኝነት ነውና፡፡ ከዚህም በላይ የአቡነ አሮኑ ዐይነ ሥውር ብርሃነ ኅሊና መሆን፣ ስለአስከሬኖቹ አባ አክሊሉ የሰጡት ሃይማኖታዊ ወይም ፍልስፍና (ሕያዋን ናቸው ማለታቸው) የአባ አክሊሉ የሕይወት፤ የታሪክ፤ እና የአኗኗር መንገድ - “ታዩን ዘንድ አላሸበረቅንም”፣ “ድልድዩ አልተሰበረም”፣ “ለሌሎቹ አልተጣላችሁም” እና የመሳሰሉት አገላለጾች ችግሩ የእነርሱ ሳይሆን የሲሳይና የእርሱ ትውልድ የአስተሳሰብ የአኗኗር ፍልስፍና ችግር መሆኑን ለመግለጽ የቀረቡ ጠንካራ ሙግቶች ይመስሉኛል፡፡ የእረኞቹ፣ የመንዘ ገበሬዎች ሕይዎት፣ የሥራ ባልደረቦቹ፤ የእርሱ አኗኗር፤ የጓደኛው መልስ፤ መጠራቱ፤ ተጋድሎውና ከእነ አባ መርሐ ጥበብ እስከነ አባ አክሊሉ ያለው አንድ የሕይወት መስመር፤ የሥዕሎቹ ፍልስፍና፤ የሚሲሲፒ ጉዞውና ከሀገር ውስጥ ወንዞች አንጻር የሚመጣው መፈክር፤ እነዚህ በሙሉ ትልልቅ የሕይወት ፍልስፍና ትንቅንቆች ይመስሉኛል፡፡ ይህ ከሆነ መጽሐፉን ሚታዊ ፍልስፍና ወይም የፍልስፍና ለማለት የሚያስደፍር ይመስለኛል፡፡
እመጓና ኪን
እመጓን ዘመናዊ ሚት ውስጥ ከሚያስመድባት አንዱ የቀረበበችበት ኪናዊ ብቃት ነው፡፡ እጅግ ልብ አጠንጠልጣይ ታሪክ፤ ሰውነትን ሰቅዞ በሚይዝ፣ መንገድ ለማቋረጥ በሚያስቸግር የትረካ ስልት መቅረቡ የኪናዊነቱን ደረጃ አመላካች ይመስለኛል፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ ኩላዊነትን በማሳየት ደረጃ ከፍተኛ ሚና የምትጫወት ይምስለኛል፡፡ ከጎጃም ተነሥቶ፣ በጎንደር፣ በወሎ፣ በሸዋ በመመላለሱና ትግራይን በማስገባቱ ብቻ ሳይሆን የአባ አክሊሉ ከዝቋላ ከአሮሞው ማኅበረሰብ መፈጠርና ሰሜናዊውን ሲሳይን መገሰጽና መሞገት፤ የእነ አባ አድሪል ሕይወትና ሶርያዊ ሆነው ሳለ የሚሰጣቸው ክብር፣ ምዕራባዊ ባህል የፈጠረውን ግጭት እየሞገተ ለአሜሪካውያን የሚሰጠው ክብር ኩላዊነቱን ከፍ ያደርገዋል፤ ይህ ደግሞ የሐዲስ ሚቶሎጂ ኪናዊነት ዓይነተኛ ጠባይ ነው፡፡ ይህም ሁሉ ሲሆን ደግሞ መቼቱ ከተሠራበት ከኦርቶዶክሳዊ ትውፊት ጋር አለመጋጨቱ የኪናዊነቱን ምጥቀት የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡
ማጠቃለያ
እመጓ የእኛ ዘመን ዘመናዊ ትውልድ የደረሰበትን የባህል ግጭት ማዕከል አድረጎና ቀዳሚው የሕይወት ፍልስፍናችን ከአዲሱ የሰው ልጅ የቴክኖሎጂ እድገትና ውስብስብነት ጋር ከመስማማት አልፎ ሚያመጣውን ችግር የማስወገድና የማከም አቅም ያለው መሆኑን ለማሳየት የተዘጋጀ ሚታዊ ድንቅ የጉዞ ልቦለድ መሆኑን ለመረዳት የሚያዳግት አይመስልም፡፡ በተለይም ጽዋው መንዝ ውስጥ እመጓ ይገኛል ብሎ ሲሳይን በዚሁ አሳምኖ መጨረሱ መጽሐፉ አንደኛ በአንጻረ ጽዋ የሕይወት መገኛዎች (ለምሳሌ እነ አባ አክሊሉ ዓይነት ሰዎች) ያሉት እዚህ ነው፤ ማዕከሉም (መንዝ ለኢትዮጵያ ማዕከል እንደምትሆነው) እዚሁ ነው፤ መንዝህ የሕይወት መርጫዉም፣ ተረጭውም፤ ረጪውም፣ የሚረጨውም እዚሁ ነው፡፡ እመጓ - እመ እጓል - የልጆች እናትም ኢትዮጵያ ናት፤ ሌላው ከእንጀራ እናትነት አያልፍም የምትል ለኢትዮጵያ ከተሜ ትውልድ ፈውስነት የቀረበች የአእምሮ ማረጋጊያ (Mental Therapy) ትመስለኛለች፡፡ ሆኖም መጽሐፉ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ያለውን ቦታና ማኅበረሰባዊ ተጽእኖ ለማየት ገና ገና ሰፊ ጥናትና ምርምርን የሚሻ ድንቅ መጽሐፍ መሆኑን ከመናገር ለማለፍ ለአሁኑ አስቸጋሪ ይመስላል፡፡

1 comment:

  1. waw betam des yemil melkta new endanbebkut zemnawi ena bahlawi esetochn yeyaze yetlyayu adbaratn ena gedamtn behasab eske tesetachw kalkidan yemyaskag ye kedmu abatochn tegadaynt ye kidusan abatoch koratnt yene aba edril felga becha betm des yelall mechrshawem asamnon new yalkew

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount