Thursday, March 12, 2015

አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 03 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
     በየዓመቱ መጋቢት 5 የምናከብረው በዓል አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ያረፉበት በዓል ነው፡፡ በዚኽ ዕለት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በቅዳሴዋም በትምህርቷም ኹሉ እኒኽን ታላቅና ቅዱስ አባት ታነሣለች፤ ታወድሳለች፤ ተጋድሎአቸውንም ለልጆቿ ታስተምራለች፡፡
ሀገራቸው ንሒሳ (ግብጽ) ሲኾን አባታቸው ስምዖን እናታቸውም አቅሌስያ ይባላሉ፡፡ ልጅ አጥተው 30 ዓመታት ሲያዝኑ ኖረዋል፡፡ እኛ አንድ ነገርን ለምነን በእኛ አቈጣጠር ካልተመለሰልን ስንት ቀን እንታገሥ ይኾን? ዛሬ በልጅ ምክንያት የፈረሱ ትዳሮች ስንት ናቸው? ለመኾኑ እግዚአብሔርን ስንለምነው እንደምን ባለ ልቡና ነው? ጥያቄአችን ፈጥኖ ላይመለስ ይችላል፡፡ ያልተመለሰው ለምንድነው ብለን ግን መጠየቅ ይገባናል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡- “የምንለምነውን የማናገኘው በእምነት ስለማንለምን ነው፤ በእምነት ብንለምንም ፈጥነን ተስፋ ስለምንቆርጥ ነው” ይላል፡፡ ሰውን ብንለምነው እንደዘበዘብነው፣ እንደ ጨቀጨቅነው አድርጎ ሊቈጥረው ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ግን እንዲኽ አይደለም፡፡ “ለምኑ ታገኙማላችሁ፤ አንኳኩ ይከፈትላችሁማል” ያለን ርሱ እግዚአብሔር እንጂ ሰው አይደለምና፡፡ የሚያስፈልገን ከኾነ ያለ ጥርጥር ይሰጠናል፡፡ መቼ? ዛሬ ሊኾን ይችላል፤ ነገ ሊኾን ይችላል፤ ወይም እንደ ስምዖንና እንደ አቅሌስያ የዛሬ 30 ዓመት ሊኾን ይችላል፡፡  ጭራሽኑ ላይሰጠንም ይችላል፡፡ አልሰጠንም ማለት ግን ጸሎታችን ምላሽ አላገኘም ማለት አይደለም፡፡ የለመንነው እኛን የሚጎዳን ስለኾነ እንጂ፡፡ እግዚአብሔር ሲሰጥ ስለ ፍቅሩ፤ ሲነሳም ስለ ፍቅሩ ነውና፡፡

ስምዖንና አቅሌስያ ጥያቄአቸው የተመለሰው ከ30 ዓመት በኋላ ነበር፤ ከሥዕለ ሥላሴ ወድቀው እግዚአብሔን ሲለምኑ፡፡ በዚኽም መሠረት አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ መጋቢት 29 ተጸንሰው ታኅሳስ 29 ቀን ተወለዱ፡፡ እንደተወለዱም፡- “ስብሐት ለአብ፣ ስብሐት ለወልድ፣ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ ለዘአውጻእካኒ እምጽልመት ውስተ ብርሃን” ብለው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ አባታችን በዚኹ ዕለት ተወልደው እንዲኽ ማመስገናቸው ሊደንቀን ይችላል፡፡ ይኸውም ብዙዎቻችን ሕፃናት እግዚአብሔርን ዐያውቁትም ብለን ስለምናስብ ነው፡፡ ይኽ ግን ስሕተት ነው፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ገና በእናቱ ማኅፀን ሳለ ያመሰገነው እግዚአብሔርን ስላወቀው ነበር፡፡ የሆሣዕና ሕፃናት እግዚአብሔርን በዕልልታ ያመሰገኑት መላእክትንም የመሰሉት አምላካቸውን ስላወቁት ነው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በተወለዱ በሦስተኛው ቀናቸው “አሐዱ አብ ቅዱስ፣ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ” ብለው ያመሰገኑት አምላካቸውን ስላወቁት ነው፡፡ የሆሣዕና ድንጋዮች እግዚአብሔርን ዐውቀዉት ካመሰገኑ በአርአያ ሥላሴ የተፈጠሩት ሕፃናት ቢያመሰግኑማ ምን ይደንቃል?
አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም የሔዱት በሦስት ዓመታቸው ነበር፤ በቅዱስ ገብርኤል አማካኝነት፡፡ አበምኔቱ አባ ዘመደ ብርሃንም ሕፃኑን ተቀብለው መዝሙረ ዳዊትንና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን እያስተማሩ አሳደጓቸው፡፡ በኋላም ማዕርገ ምንኩስና ተቀብለዋል፡፡ ተወዳጆች ሆይ! ዛሬ ሕፃናትን የምንወስዳቸው ወዴት ነው? ዓለማዊ ትምህርት ብቻ ነውን? መንፈሳዊ ትምህርትም እናስተምራቸው፡፡ ልጆቻችን ጥበበኞች፣ ባለጸጎች፣ ዐዋቂዎች እንዲኾኑ የምንሻ ከኾነ ቅዱሳት መጻሕፍትንም እናስተምራቸው፡፡ ሕፃናት ልጆቻችን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሔደው ቅድሚያ የሚማሩት “አባትህንና እናትህን አክብር” የሚል ነው፡፡ ስለዚኽ ቀድመን የምንጠቀመው እኛው ነን፡፡ ልጆቻችን ወደ ገበያ ቦታ፣ ለነፍሳቸው ምንም ወደማይጠቅማቸው ስፍራ ለመውሰድ የማናቅማማ ከኾነ ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመውሰድማ እንዴት? አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እንዲኽ ስማቸው በሰማያት ብቻ ሳይኾን በምድርም ላይ ገንኖ የምንሰማው ከልጅነታቸው አንሥተው ቅዱሳት መጻሕፍትን ስለተማሩ ነው፡፡ በሦስተኛው ዓመታቸው እንደ ነቢዩ ሳሙኤል ወደ ቤተ እግዚአብሔር ስለሔዱ ነው፡፡ ለመኾኑ ለልጆቻችን በቤት የምንከፍትላቸው ፊልም ምንን የተመለከተ ነው? የቶምና ጄሪ የተንኮል ሥራ ወይስ የነ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ የነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ የነ ቅዱስ ቂርቆስ፣ የነ ሠለስቱ ደቂቅ የቅድስና መንገድ?

አባታችን ማዕርገ ምንኩስናን ከተቀበሉ በኋላ እግዚአብሔር ሀብተ ፈውስን ሰጥቷቸዋል፡፡ ብዙ ዕውራንን፣ ብዙ ሐንካሳንንም ፈውሰዋል፡፡ እኛም ከተጠቀምንበት እግዚአብሔር ሀብተ ፈውስን ለእያንዳንዳችን ሰጥቶናል፡፡ ኃጢአት ለማድረግ የሚፋጠኑትን አንካሳ እግሮች እንድናቀና፣ በዘፈንና በማይጠቅም ወሬ የደነቆሩትን ዦሮዎች እንድንከፍት፣ በስድብ በርግማን ዲዳ የኾኑትን አንደበቶች እንድንፈታ እግዚአብሔር ሀብተ ፈውስን ሰጥቶናል፡፡ ከምንም የሚበልጠው ሀብተ ፈውስም ይኸው ነውና የአባታችንን አሰረ ፍኖት ተከትለን ብዙ ድውያነ ነፍስን ማዳን ይቻለናል፡፡
አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በትእዛዘ እግዚአብሔር በበረኻ ሲኖሩ 60 አናምርትና 60 አናብስት አብረዋቸው ይኖሩ ነበር፡፡ ሊደንቀን ይችላል፡፡ ነገር ግን እነዚኽ እንስሳት ከዥምሩም የእኛ ጠላቶች አልነበሩም፡፡ በበደላችን ምክንያት ከእኛ ስለተለዩ እንጂ፡፡ ሔዋን ከእባብ ጋር የተነጋገረችው እባብ የሰው ባርያ ስለ ነበር ነው፡፡ እንስሳት ኹሉ የሰው አገልጋዮች ናቸው፡፡ የእኛ የቅድስና ማዕርግ እንጂ እነዚኽ እንስሳት ከሰው ጋር ጠብ የላቸውም፡፡ እነ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ እነ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ፣ እነ አቡነ አረጋዊ፣ እነ ነቢዩ ዳንኤል እነዚኽን እንስሳት ያዘዝዋቸው ድሮውንም የእኛ ችግር እንጂ እነዚኽ እንስሳት ለእኛ ክፉዎች ስላልኾኑ ነው፡፡ “ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር ይቀመጣል፤ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፤ ጥጃና አንበሳ ደቦል ፍሪዳም በአንድነት ያርፋሉ፤ ታናሽም ልጅ ይመራቸዋል፡፡ ላምና ድብ አብረው ይሰማራሉ፤ ግልገሎቻቸውም በአንድነት ያርፋሉ፤ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል” እንዲል /ኢሳ.11፡6-7/፡፡  እኛ ግን ከበረኻ አውሬዎችስ ይቅርና ከሰውም ጋር ተስማምተን መኖር አቅቶናል፡፡
አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ዕድሜአቸው 300 ዓመት ሲኾን ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ከተቀበሉ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡ እንደመጡ የሔዱት ወደ ሮሐ ነበር፡፡ በዚያም ከቅዱስ ላሊበላ ጋር ተገናኝተው ሥራዉን ባርከዉለታል፡፡ በመላዋ ኢትዮጵያ ተዘዋውረው ከማስተማራቸው በላይም የዝቋላንና የምድረ ከብድን ገዳማት መሥርተዋል፡፡
አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንድ ቀን ከምድረ ከብድ ተነሥተው ወደ ዝቋላ ሲሔዱ ሥላሴን በሽማግሌዎች አምሳል በጥላ ስር ዐርፈው ያገኟቸዋል፡፡ “በእግዚአብሔር ዙፋን ተማጽነናል፡፡ አዝለህ አንዳንድ ምዕራፍ ሸኘን” አሏቸው፡፡ አባታችንም ሥላሴን አዝለው “ሸኟቸው”፡፡ በኋላ ግን በአንድነት በሦስትነት ተገለጡላቸው፡፡ አባታችን ደንግጠው ወደቁ፡፡ ወዮ! እግዚአብሔር ስንት ጊዜ ተሸከሙኝ ብሎ ለምኖን ይኾን? ስንት ጊዜ አልፈነው ሔደን ይኾን? እግዚአብሔር የሚሸከም እንጂ የሚሸከሙት አይደለም፡፡ ግን አባት ነውና ከልጆቹ ጋር መጨዋወት፣ ልጆቹን መባረክ፣ ልጆቹ ርስቱን መንግሥቱን የሚወርሱበት መንገድ ያዘጋጃል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡- “ወዳጄ ሆይ! እግዚአብሔር ነዳያንን የሚልክልህ መስጠትን እንድትለማመድ ነው፡፡ ዛሬ በነዳያኑ አድሮ የሚለምንህ ለኋለኛይቱ ቀን ስንቅ እንዲያስቀምጥልህ ወድዶ ነው፡፡ ታድያ ንጉሥ ወደ ቤቱ መጥቶ የሚያባርር ሰው እንደምን ያለ ጎስቋላ ሰው ነው? እንግዲያውስ ነዳያንን ስታይ ወደ አንተ የመጣው ንጉሠ ሰማይ ወምድር ክርስቶስ እንጂ ሰው አይደለምና አትግፋው፡፡ በረከትህንም ከቤትህ አውጥተህ አትሸኘው” ብሎ ያስተማረው ምንኛ ግሩም ነው?
በሌላ ጊዜ ወደ ዐረብ ሀገር ሔደው ነበር፡፡ በጣዖታቱ ያደሩ አጋንንትም ፈርተው ሸሹ፡፡ ጣዖታቱ ተሰባበሩ፡፡ የዐረቡ ንጉሥም ይኽን ዐይቶ “አንተ ፀጉር ልብሱ ምንድነህ? ሰው ነህን?” አላቸው፡፡ ርሳቸውም፡- “አዎ! ሰማይንና ምድርን በፈጠረ በኢየሱስ ክርስቶስ የማምን ሰው ነኝ” አሉት፡፡ ንጉሡም “አይሁድ ሰቅለው በገደሉት ሰው ታምናለህን?” አላቸው፡፡ “አፍርበት መስሎሃልን? አንተም ብታምንበት የዘለዓለም ሕይወት ባገኘህበት ነበር” ብለዉታል፡፡ “በወንጌል አላፍርም” እንዲል /ሮሜ.1፡16/፡፡ እንዲኽ ማለታቸው ነበር፡- “ርግጥ ነው በአፍአ ስታየው ጌታዬ በአይሁድ ተሰቅሏል፡፡ መሰቀል ብቻ ሳይኾን ሞቷል፡፡ መሞት ብቻ ሳይኾን ወደ ምድር ልብ ወርዷል፡፡ ነገር ግን የሞተው ስለበደሉ አይደለም፤ ስለ እኔና ስላንተ በደል እንጂ፡፡ የሞተው የእኔንና የአንተን ሞት ለመግደል ነበር፡፡ የተሰቀለው የኔንና የአንተን ኃጢአት በመሸከም ነበር፡፡ ወደ መቃብር የወረደው ርደተ ገሃነምን ያስቀርልን ዘንድ ነው፡፡ ሞት አገኘሁ ብሎ የሚታየውን ሥጋዉን ዋጠ፡፡ በማይታየውም ድል ተደረገ፡፡ ሞት አኹን ድል ተደርጓል፡፡ መቃብር ድል መንሣቱ ቀርቷል፡፡ አንተም ይኽን ብታምን ደግሞም ብትጠመቅ የዘለዓለምን ሕይወት ታገኛለህ፡፡” በእውነት የአባታችን በረከታቸው፣ ቃል ኪዳናቸው ከእኛ ጋር ትኹን፡፡

አባታችን እንዲኽ ለመስማት ዕፁብ ድንቅ በኾነ ግብር ቆይተው 262 ዓመት በኢትዮጵያ ኖረው፣ ስለ ኢትዮጵያ ጸልየው፣ በቃል ኪዳናቸው ያመነውን የተማፀነውን ጌታ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ሊምርላቸው ተስፋቸውን ተቀብለው መጋቢት 5 ቀን ለእሑድ አጥቢያ ቅዳሜ ማታ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ሲኾን በ562 ዓመታቸው ዐረፉ፡፡ መላእክትም በአክናፈ እሳት ኢየሩሳሌም ወስደው በየማነ ምሥዋዕ ቀብሯቸዋል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተም እኔን ምሰሉ” እንዳለን በምግባር በሃይማኖት አባቶቻችንን መስለን እንድንጸና የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን አማላጅነት የጻድቁ የአባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቃል ኪዳን ይርዳን አሜን!!!

10 comments:

  1. እባካችሁ ወንጌል ስበኩ

    ReplyDelete
    Replies
    1. አንተ የማትረባ ጌታ የተናገረውን አላነበብክም?ማቴ26-13 “እውነት እላችኋለሁ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበት እርሷ ያደረገችው ደግሞ ለርሷ መታሰቢያ እንዲኾን ይነገራል” ታድያ ባለቤቱ ጌታ ይህን እያለ አንተ ምን ይሁን ነው የምትለው? ለዚህች እናት ወንጌል በዓለም ሁሉ በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበት እርሷ ያደረገችው ደግሞ ለርሷ መታሰቢያ እንዲኾን ከተነገረ 562 ዓመት ሙሉ ክርስቶስን በሕይወቱ ሰብኮ በጾም በጸሎት በቀዊም በስግደት በገድል በትሩፈት ተወስኖ ሰይጣንና ሰራዊቱን ድል ነስቶ ዘለዓለማዊ ቃልኪዳን ከፈጣሪው ተቀብሎ በምልጃው በጸሎቱ የሚጠብቀንን የሚረዳንን በቃልኪዳኑ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ለመግባት የሚያግዘንን ንዑድ ክቡር የሚሆን የባሕታውያን አለቃ ወርእሰ ኩሎሙ ቅዱሳን የተባለ ቅዱስ አባታችን ገብረ መንፈስን ላንሰብክ ስለእርሱም ላናስተምር ነው? 1000000000 ጊዜ አንተም ሆንክ የግብር አባትክ ዲያብሎስ ትበግናላችሁ ትቃጠላላችሁ እንጂ እኛስ ነገረ ቅዱሳንን ከመማር ከማስተማር ለሰከንድም አናቆምም እሺ!!!ምክንያቱም እነሱን መስበክ ክርስቶስን መስበክ፤እነርሱን ማክበር አክባሪያቸውን ማክበር መሆኑን እናውቃለንና “እግዚአብሔር በጻድቁ እንደከበረ እንደተመሰገነ እወቁ” እንዳለ ክቡር ዳዊት

      Delete
  2. wedaje hoy kewengel wuchi yetesebeke min hitsets agegneh yihon joro yalew mesimatun yisma

    ReplyDelete
    Replies
    1. ወንድም/እህት ከወንጌል ውጭ ምን የሆነ ነገር አለ???? እብ 13፣7 አንብብ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርት ለተግሳጽ ሕይወትን ለማቅናት ይረዳል፣ 2ኛ ጢሞ 3፣16 በወንጌል መሰራት ያቃተው ገድል መስራት የማይችል መንፈስ ስለተሸከምክ ነው ወንጌሉ የማይታይህ እንጂ ወንጌሉ እኮ ማኑዋል ነው፣ የሐዋርያት ስራ ምንድን ነው??? ከዘፍ 3 ጀምሮ እስከ የሐንስ ራእይ 9ዐ ፐርስንት በላይ በሙሉ የሚተርከው ስለቅዱሳን ሰዎች ነው፣ ካዲያ ለምን ታነባለህ???? እነ አብርሃም እነ ኖህ የእነ ዳዊት ሌሎችም የነብያት ታሪክ የሚተርከው መጽሐፍ ቅዱስ የሚተርካቸው እነዚህ ምንድን ናቸው ሰዎች አይደሉ??? መጽሐፍ ቅዱሱ እራሱ ስሙ በቅዱሳን ስም አይደል የተሰጠው??? የማቴየስ ወንጌል ወንጌሉ የጌታ ቢሆንም ስሙ የተሰጠው በሐዋርያት ስም ነው ስለዚህ ወንድሜ፣ ቃል ስጋ ሆነ የሚለው ትርጉም በጣም አስተውለው፣ ትርጉምንም እንዲገልጽልህ ጸልይ፣ ማስተዋሉን በተዋህዶ የከበረው እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ይስጥህ፡፡ ቃሉን ያብራልህ፤ ምሳሌዎችህን የሰማይ ቅዱሳንን እንዳታይ የጋረደው አውሬውን ራእ 13፣6 በሐዋርያው ቅዱስ ሃናን ምልጃ የሳውልን የአይን ቅርፊቱን እንዳነሳለት የአንተንም የአይነ ልቦናህን ቅርፊት አንስቶ ያብራልህ፣ ሐዋ 9፣18

      Delete
    2. lante wengel minginew wodaje sinde new yeluter buchila!!!!!!!!!!!!!

      Delete
  3. amen kale hiwotn yasemaln !!!!!!!

    ReplyDelete
    Replies
    1. ቃለ ሕይወት ያሰማልን እግዚአብሔር ጸጋውን ያብዛላችሁ የአባታችን በረከት አይለየን፣ አይለያችሁ

      Delete
  4. ቃለ ሕይወት ያሰማልን

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount