Thursday, March 26, 2015

ኃጢአቴን በዝርዝር አለመናዘዜ አስጨነቀኝ፡፡ ምን ላድርግ?



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐሙስ መጋቢት 17 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ውድ መቅረዛውያን እንዴት አላችኁ? በዛሬው ጽሑፌ ከአንባብያን ከተላኩልኝ ጥያቄዎች ለኹለተኛው ጥያቄ የተሰጠውን ምላሽ አቀርብላችኋለኁ፡፡ መልሱን የሚሰጡን በምሥራቀ ፀሐይ ቀበና መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ሰባኬ ወንጌል እንዲኹም በታዕካ ነገሥት ባዕታ ለማርያም ገዳም የመጻሕፍተ ሐዲሳት የ5ኛ ዓመት ደቀ መዝሙር የኾኑት ቀሲስ ፋሲል ታደሰ ናቸው፡፡ የልድያን ልቡና የከፈተ አምላክ የእኛንም እዝነ ልቡናችን ይክፈትልን፡፡ አሜን!

ጥያቄ፡- ሰላም ለእናንተ ይኹን መቅረዞች!!! አንድ ውስጤን የሚያስጨንቀኝና እንቅልፍ ያሳጣኝ ጥያቄ አለኝ፡፡ ለብዙ ዓመታት እምነቴ ፕሮቴስታንት ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. 2010 ላይ ግን ወደ ኦርቶዶክስ ተመልሻለኁ፡፡ ከንስሐ አባቴ ጋርም ተገናኝቻለኁ፡፡ ነገር ግን ኃጢአቴን ስናዘዝ በደፈናው “ከመግደል ውጪ ኹሉንም ሠርቻለኁ” ነው ያልኳቸው፡፡ አኹን ግን “ለምን ኹሉንም በዝርዝር አልነገርኳቸውም? በግልጽ ባለ መናገሬ እግዚአብሔር ይቅር ባይለኝስ? እንዴትስ በድጋሜ ልንገርዎት ልበላቸው?” እያልኩ ቀን በቀን እጨነቃለኁ፡፡ ምን እንዳደርግ ትመክሩኛላችኁ? 
ሳምራዊት ነኝ ከሆላንድ

ቀሲስ ፋሲል ታደሰ፡- ከምንም በፊት የንስሐንና የንስሐ አባትን ምንነት መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ ጠያቂዋ ስለ ንስሐ ደጋግማ መማር፣ ማንበብ ይጠበቅባታል፡፡
የንስሐ ትልቁ ጉዳይ ኃጢአትን ለንስሐ አባት መናዘዝ ነው፡፡ የነፍስ ቅጣቷም በኑዛዜ ውስጥ የሚገለጥ ነው፡፡ ይኽም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው፡፡ ሲቀጥልም ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ ነው፡፡ ከዚኽ አንጻር     “ለምንድነው በዝርዝር ያልነገርኳቸው? በዝርዝር ለመንገር ምን ያኽል ብርታት ያስፈልገኛል?” ብሎ ራስን መጠየቅ ግድ ነው፡፡ ኃይል፣ ብርታት አግኝተን ለመናዘዝ ደግሞ ቃለ እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚኽ በቃለ እግዚአብሔር የንስሐ አባት ምንነት ላይ ማተኮር ያስፈልጋል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ ሌሎችም ነቢያት፣ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፣ ሌሎችም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲኾኑ ሰጠ” እንዳለ /ኤፌ.4፡11-12/፤ በሌላ ስፍራም “እንዲኹ ሰው እኛን እንደ ክርስቶስ ሎሌዎችና እንደ እግዚአብሔር ምሥጢር መጋቢዎች ይቁጠረን፡፡ እንደዚኽም ሲኾን በመጋቢዎች ዘንድ የታመነ ኾኖ መገኘት ያስፈልጋል” እንዳለ /1ኛ ቆሮ.4፡1-2/ ንስሐ አባት መጋቢ ነው፤ ቃለ እግዚአብሔርን ይመግባልና፡፡ የንስሐ አባት ምሥጢረኛ ነው፡፡ አደራ ጠባቂነት፣ መጋቢነት የሚለው ሐሳብ ምሥጢርን የሚጠብቁ፣ በእግዚአብሔር ፊት ንስሐ ሲነገራቸው ያንን ጠብቀው ከእግዚአብሔር ጋር ብቻ የሚያስታርቁ፣ የተሰጣቸውን አደራ የሚጠብቁ መኾኑን በመረዳት መጋቢና ምሥጢር ጠባቂ መኾናቸውን ማመን ያስፈልጋል፡፡ ዳግመኛም የእግዚአብሔር ቃል፡- “ካህኑ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ነውና ከንፈሮቹ ዕውቀትን ይጠብቁ ዘንድ ይገባቸዋል፤ ሰዎችም ሕግን ከአፉ ይፈልጉ ዘንድ ይገባቸዋል” እንዲል ካህናት መልእክተኞች መኾናቸውንም ማመን ያስፈልጋል /ሚልክ.2፡7/፡፡
ካህኑ እንደ ሰውነታችን ድካም የተለያየ ችግር ሊኖርበት ይችላል፤ ሥልጣኑ ግን የመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ የሚያስተላልፈውም መልእክት የግሉን ፍልስፍና ወይም አመለካከቱን ሳይኾን የእግዚአብሔርን ሐሳብ ነው፡፡ ለዚኽም ነው “መጋቢ ናቸው፤ መልእክተኛ ናቸው” እየተባለ የተጻፈላቸው፡፡ ከዚኽም አንጻር ንስሐ የሚገባ ሰው “ካህኑ መጋቢ ነው፤ ጠባቂ ነው፤ ምሥጢረኛ ነው፤ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ነው” የሚለውን በሕሊናው ከተረዳ ፍርሐት ይወገድለታል፤ ዓላማውን ይረዳል፤ በዝርዝር ለመናገርም ብርታትን ያገኛል፡፡  
ዳግመኛም ጌታችን ራሱ ምሳሌ አድርጎ እንደተናገረ ካህናት ቸር ጠባቂ ናቸው /ዮሐ.10፡11/፡፡ የሚጠብቁንም መፍትሔውን እንዲሰጡን ውስጣችንን ስንነግራቸው ነው፡፡ ሐኪሞች ጤናችን እንዲጠበቅ “እንዲኽ አታድርግ፤ ይኽንን ተገልገል፤ ይኽንን አድርግ” እንደሚሉት ኹሉ ንስሐ አባትም የነፍስ ጠባቂ ነውና ይኽን የመሰለ መድኃኒተ ነፍስ ያዝዛል፡፡ የሚጠብቁን ውስጣችንን ሲያውቁ ነው፡፡ መድኃኒቱን የሚያዙልን ድክመታችንን ሲያውቁ ነው፡፡ መፍትሔውን የሚጠቁሙን ችግራችንን ሲያውቁ ነው፡፡ አንድ ሐኪም “ይኽ ጤናህን ይጠብቅልኻል” የሚለኝ በሽታዬን በዝርዝር ስነግረው ነው፡፡ አኹንም ተነሳሒ ለመምህረ ንስሐዉ ድክመቱን ሲነግረው “ለዚኽ ችግርኽና ድካምኽ እንዲኽ እንዲኽ ማድረግ ይገባኻል፤ በዚኽ መልኩ መጠንከር ትችላለኽ” ብሎ ጠባቂነቱን ይገለጣል፡፡ በግ የተባሉ ምእመናንም ተጠባቂነታቸው የሚመሰከረው እንዲኽ ባለ መንገድ ነው /ዮሐ.21፡15/፡፡
ከዚኽም በተጨማሪ የንስሐ ምሥጢር ኑዛዜ ላይ መኾኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በንስሐ ሥርዓት ውስጥ ዋናው ነገር አንድ ሰው በሕሊናው፣ በአንደበቱ፣ በተግባር የሠራውን ኃጢአት መዠመሪያ ለራሱ ይናዘዛል፡፡ ብቻውን ሲኾን ለራሱ ያስታውሳል፡፡ ምክንያቱም ለራሱ ያላመነበትና ያልጸጸተው ኃጢአት በእግዚአብሔርና በካህኑ ፊት አይናዘዘውም፡፡ ለኅሊናው ከተናገረና ካመነበት ግን በእግዚአብሔር ፊት “ኃጢአትን ሠርቻለኁ” ብሎ ለማልቀስ አይቸገርም፡፡ ወደ ካህኑ ሔዶ የሚናገረውም ይኽ ለራሱና ለእግዚአብሔር የተናገረውን ኃጢአት ነው፡፡ ለካህኑ መናገሩም የእግዚአብሔር እንደራሴና አገልጋይ ስለኾነ ነው፡፡ በካህኑ ፊት የሚናዘዝ በእግዚአብሔር ፊት ይናዘዛል፡፡ ይኸውም ነቢየ እግዚአብሔር ኢያሱ አካንን፡- “ልጄ ሆይ! ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ክብር ስጥ፡፡ ለርሱም ተናዘዝ፡፡ ያደረግኸውንም ንገረኝ፤ አትሸሽገኝ” እንዳለው ነው /ኢያሱ.7፡19/፡፡ ለዚኽም ነው ኑዛዜ ማለት ኃጢአትን ሳይደብቁ መናገር ማለት ነው የምንለው፡፡
የንስሐ ዋና ምሥጢርና የነፍስ ቅጣቷም እዚኽ ጋር ነው፡፡ ቅጣት የሚባለው ጾሙ፣ ስግደቱ፣ ቀኖናው አይደለም፡፡ ቀኖና መቀጣጫ አይደለም፤ በረከት ማግኛ ነው፤ ደጅ መጥኛ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ባሳዘነው አንደበትና ሰውነት አንድ ሰው ለእግዚአብሔር የሚገዛበት መንፈሳዊ ሥርዓት ነው፡፡ ቀኖና ማካካሻ ወይም መቀጣጫ ሳይኾን “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችኁ ጸልዩ” እንዳለው ዳግም እንዳንበድል የእግዚአብሔርን ኃይል የምናገኝበት ነው፡፡ እንደ በደላችን መጠን ቀኖና እየተሰጠን አይደለም፡፡ ለምን? የምንሠራው ኃጢአት ተካክሶ የማያልቅ ነውና፡፡ እንደ ሰው ሰውኛው ካየነው ኃጢአታችን በመቀጣጫ የማይስተሰረይ ይኾናል፡፡ ስለዚኽ የሚያነጻን የእግዚአብሔር ምሕረቱ ነው፡፡ የነፍሳችን ታላቁ ቅጣት ግን ከላይ እንደተናገርኩት በካህኑ ፊት በዝርዝር መናገራችን ነው፡፡ ጸጸት የሚያሰኘውም ይኸው ነው፡፡ ከዚኽ አንጻር ኑዛዜ በድፍረት የሠራሁትን ኃጢአት እየፈራኁና እየተንቀጠቀጥኩ (የአክብሮት) የማደርገው የይቅርታ ፍለጋ ሥርዓት ነው፡፡ እንዲኽ ስንናዘዝ ነው ውጤቱ የምናገኘው፡፡
የእግዚአብሔር ቃል የሚያስረዳንም ይኸንን ነው፡፡ “ኃጢአቱን የሚናዘዛት ሥርየትን ያገኛል፤ የሚሰውራት ግን አይለማም፤ አይጸድቅም” እንዲል /ምሳ.28፡13/፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ለማንም አንዳች እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ሔደህ ራስህን ለካህን አሳይ” ብሏል /ማር.1፡44/፡፡ ለማንም እንዳትናገር ብሎ ቢያዘውም ለካህኑ ብቻ እንዲነግረው ግን አዝዞታል፡፡ አሳይ ማለቱ ይኽን የሚያስረዳ ነውና፡፡ ስለዚኽ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትን የምናገኘው ለካህኑ በመናገር የንስሐ ሥርዓትን ስንፈጽም ነው፡፡
ካህኑ ያንን ኃጢአት ይዞ መዝግቦ የሚያስቀምጥበት ኹኔታ የለውም፡፡ እግዚአብሔር የተወለትን ያ ካህን ሲያሰላስል የሚከርምበት ሥርዓት የለውም፡፡ ለምንድነው ለካህን የምናገረው? ከላይ ከተናገርኩት በተጨማሪ፡-
·        ዳግም ላለመበደል፤
·        ካህኑ ምስክር እንዲኾን፤
·        ኑዛዜ ትክክለኛ የጸጸት መገለጫ ስለኾነ፤
·        ከዚኽ ከዚኽ አንጻር እንናገራለን፡፡ ለካህኑ መናገራችን በካህኑ ደረጃ የሚጠቅመው ቀኖና ለመስጠት እንዲያመች ብቻ ነው፡፡
ከዚኽ በኋላ ሥርዓተ ጸሎት አድርጎ “እግዚአብሔር ይፍታሕ፤ እግዚአብሔር ይፍታሽ” እንዲል ብቻ ነው፡፡
ደግሞም ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም፡፡ ለሐኪም እንግዳ ነገር እንደሌለ ኹሉ ለካህንም ከሚያስተናግዳቸው የንስሐ ልጆቹ አንጻር እንግዳ ነገር የለም፡፡ ምክርና ተግሣፅ መስጠት ይችል እንደኾነ እንጁ ልጁን የሚወቅስበት፣ የሚያስደነግጥበት፣ የሚያስደነብርበት፣ የሚያባርርበት ኹኔታ የለውም፡፡ ኹላችንም ሥጋ ለባሾች ስለኾንን የሰውን ድካም እናውቃለን፡፡ ስለዚኽ ከእኛ ከካህናት የሚጠበቀው እግዚአብሔር ይቅር ሊላት የተዘጋጀችውን ነፍስ “እግዚአብሔር ይፍታሽ” ብለን ብቻ መሸኘት ነው፤ ከዚያ በኋላ ዳግም እንዳይበድል መምከር ነው፡፡ ከዚኽ ባለፈ የተለየ ትዝብት፣ የተለየ ምልከታ፣ “እንዲኽ ዓይነት ሰው ነው” ፤ “እንዲኽ እንዲኽ ያደረገ ሰው ነው” አንልም፤ አይባልምም፡፡ ምክንያቱም እኛም ሰዎች ነን፡፡ እግዚአብሔርም ያዘዘን ቸር ጠባቂ መልካም እረኛ እንድንኾን ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ራሳችንን ዝቅ በማድረግ የሰዎችን ችግር በመረዳት ከባቴ አበሳ (በደልን የምንሰውር) በመኾን ቀኖና እንድንሰጥ ነው፡፡ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም እንደተናገረው ቤተ ክርስቲያን ሐኪም ቤት እንጂ ፍርድ ቤት አይደለችም፡፡  
ስለዚኽ ተነሳሕያን ንስሐቸውን ሳይፈሩ በዝርዝር መናገር አለባቸው፡፡ ሳይፈሩ ሲባልም ከመናገር ደብቀው ሳይፈሩ ማለቴ ነው፡፡ ባይኾን ፍርሐቱ ቅድም እንደጠቀስኩት የመጸጸት፣ የአክብሮት ፍርሐት ብቻ መኾን አለበት፡፡
 “በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ኹሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው” እንዲል /1ኛ ዮሐ.1፡9/ ኃጢአትን ገልጾ መናገር ተገቢ ነው፡፡ “የሚሰውር አይለማም” ስላለ ባልተናዘዝነው ኃጢአት ስርየት አናገኝም፡፡ ሐኪሙ ላልተናገርነው ሕመም መድኃኒት እንደማይሰጠን ኹሉ ካህኑም ኃጢአታችንን የምንተውበትና በመንፈሳዊ ሕይወታችን የምንጠነክርበትን ቀኖና የሚሰጠን የተናገርነውን ኃጢአት መሠረት አድርጎ ነው፡፡ በዋናነት ደግሞ እግዚአብሔር “ንስሐ ግቡ” ብሎ ያዘዘንን የምንፈጽመው ኃጢአታችንን ሳንደብቅ ስንናገር ነው፡፡
ስለዚኽ ይኽን ኹኔታ በመገንዘብ “ለንስሐ አባቴ በዝርዝር ያልነገርኳቸው ኃጢአቴ አስጨነቀኝ” ያሉት ጠያቂ በርትተው ለመናገር ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ የሚበረታታ ባይኾንም ድንገት አንዳንድ ተነሳሕያን በሰው ሰውኛው “ካህኑ ላይ ጥርጣሬ አለኝ፡፡ ከባልንጀሮቼ ወይም ከቤተሰቦቼ ጋር ቅርበት ስላለው ምሥጢሬ ሊወጣ ይችላል” የሚል ስጋት ካለባቸው መዠመሪያ ለመናገር መወሰን፣ ካልኾነ ግን ስጋት የያዛቸውን ካህን ተሰናብተው ለሌላ ካህን መናገር ግዴታ ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!      

3 comments:

  1. it is best advise continuie with in this

    ReplyDelete
  2. We need like this of advise from our fathers.

    ReplyDelete
  3. it is best advise continuie with in this፣ጥያቄ ግን አለኝ ፣ 10 ትእዛዝ አልተከተሉኩም ከመግደል ባሻገር፣ ሁሉን ጥፋት ሰርቼ አለሁ ከተባለ ሀጢያቱ ተነገረ ማለት አይደለም ወይ ? መተንተን አለበት ሴባል ምኑ ስል ከራሴ ጋር ስነጋገር መልስ አጥቸ ነው ። ለምሳሌ ፣ ሰረኩ ፣ ካለ ከዜህ በላይ መተንተን እንዴት ነው ? እባክዎን ያብራሩት ።

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount