(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐሙስ መጋቢት 17 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ
አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ውድ መቅረዛውያን
እንዴት አላችኁ? በዛሬው ጽሑፌ ከአንባብያን ከተላኩልኝ ጥያቄዎች ለኹለተኛው ጥያቄ የተሰጠውን ምላሽ አቀርብላችኋለኁ፡፡ መልሱን
የሚሰጡን በምሥራቀ ፀሐይ ቀበና መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ሰባኬ ወንጌል እንዲኹም በታዕካ ነገሥት ባዕታ ለማርያም ገዳም የመጻሕፍተ
ሐዲሳት የ5ኛ ዓመት ደቀ መዝሙር የኾኑት ቀሲስ ፋሲል ታደሰ ናቸው፡፡ የልድያን ልቡና የከፈተ አምላክ የእኛንም እዝነ ልቡናችን
ይክፈትልን፡፡ አሜን!
ጥያቄ፡- ሰላም ለእናንተ ይኹን መቅረዞች!!!
አንድ ውስጤን የሚያስጨንቀኝና እንቅልፍ ያሳጣኝ ጥያቄ አለኝ፡፡ ለብዙ ዓመታት እምነቴ ፕሮቴስታንት ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. 2010
ላይ ግን ወደ ኦርቶዶክስ ተመልሻለኁ፡፡ ከንስሐ አባቴ ጋርም ተገናኝቻለኁ፡፡ ነገር ግን ኃጢአቴን ስናዘዝ በደፈናው “ከመግደል ውጪ
ኹሉንም ሠርቻለኁ” ነው ያልኳቸው፡፡ አኹን ግን “ለምን ኹሉንም በዝርዝር አልነገርኳቸውም? በግልጽ ባለ መናገሬ እግዚአብሔር ይቅር
ባይለኝስ? እንዴትስ በድጋሜ ልንገርዎት ልበላቸው?” እያልኩ ቀን በቀን እጨነቃለኁ፡፡ ምን እንዳደርግ ትመክሩኛላችኁ?
ሳምራዊት
ነኝ ከሆላንድ