Thursday, December 26, 2013

ነቢዩ ናሆም

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፲፯ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
“ናሆም” ማለት “መጽናናት” ማለት ነው፡፡ ብዙዎቹ ነቢያት የተላኩት መንፈሳዊነት በቀዘቀዘበት ወራት ነው፡፡ የሕዝቡ ኃጢአት ጽዋው ሞልቶ ነበር፡፡ የነቢያቱ መምጣት ዋና ዓላማም ሕዝቡ ከዚኽ ኃጢአት ለመመለስና ካልተመለሰ ግን እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ሊያመጣ ያለውን ፍርድ ለማስታወቅ ነው፡፡ ጨምረዉም ግን “አጽናኑ ሕዝቤን አጽናኑ” ተብሎ እንደተጻፈ /ኢሳ.፵፡፩/ ለሕዝቡ ተስፋ ድኅነትን ይሰጡ ነበር፡፡ ናሆምም ይኽን የነቢያት ተልእኮ የሚያሳይ ስም ነው፡፡ ምክንያቱም በመጽሐፉ ምንም እንኳን ሕዝቡ ለመጥፋት ሳይኾን ለቁንጥጫ ወደ ምርኮ እንደሚኼዱ ፈቃደ እግዚአብሔር ቢኾንም እግዚአብሔር ራሱ ጠላቶቻቸውን አጥፍቶ እንደሚያድናቸውም ጨምሮ ተናግሯል፡፡ “ለደም ከተማ ወዮላት!” /፫፡፩/፤ “እነሆ የምስራችን የሚያመጣ ሰላምንም የሚያወራ ሰው እግር በተራሮች ላይ ነው” በማለት የገለጻቸው ቃላት ይኽን የሚያስረዱ ናቸው፡፡

Tuesday, December 24, 2013

ነቢዩ ዮናስ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፲፮ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
 “ዮናስ” ማለት “ርግብ” ማለት ነው፡፡ ዳግመኛም እንደ ቅዱስ ጀሮም ትርጓሜ “ስቃይ” ተብሎም ይተረጐማል፡፡ ይኸውም ተልእኮውን የሚገልጥ ነው፡፡ ነቢዩ ዮናስ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በዓሣ አንበሪ ሆድ ውስጥ አድሮ እንደ ወጣ ኹሉ፥ የደቂቀ አዳምን ሕማም ለመሸከም መጥቶ የተሰቃየው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷል፡፡ ስለዚኽ የነቢዩ ዮናስ እንዲኽ በዓሣ አንበሪ ሆድ ውስጥ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት መቆየት የጌታችንን ሞትና ትንሣኤ በጥምቀት ተካፋዮች ለሚኾኑ ኹሉ በርግብ የተመሰለውን መንፈስ ቅዱስ እንደሚቀበሉና ለዚያ የተዘጋጁ እንዲኾኑ ማዘጋጀት ማለትም ማወጅ ነበር ማለት ነው /ማቴ.፲፪፡፴፱-፵/፡፡
 ነቢዩ ዮናስ ነገዱ ከነገደ ይሳኮር ወገን ሲኾን አባቱ አማቴ እናቱም ሶና ይባላሉ፡፡ በአይሁድ ትውፊት እንደሚነገረው ደግሞ ዮናስ ነቢዩ ኤልያስ ከሞት ያስነሣው የሠራፕታዋ መበለት ልጅ ነው /፩ኛ ነገ.፲፰፡፲-፳፬/፡፡ 

ነቢዩ አብድዩ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፲፭ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
 “አብድዩ” ማለት “ገብረ እግዚአብሔር - የእግዚአብሔር አገልጋይ” ማለት ነው፡፡ ይኽ ስም በዘመኑ የታወቀ ስም ነበር፡፡ ነቢዩ አብድዩ ነገዱ ከነገደ ኤፍሬም ሲኾን አባቱ አኪላ እናቱም ሳፍጣ እንደሚባሉ የቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ያስረዳል፡፡
 ነቢዩ አብድዩ የአክአብ ቢትወደድ ነበር፡፡ ኤልዛቤል ነቢያት ካህናትን ስታስፈጃቸው ኃምሳውን በአንድ ዋሻ ኃምሳውን በአንድ ዋሻ አድርጐ ልብስ ቀለብ እየሰጠ ይረዳቸው የነበረውም ይኸው ነቢይ ነው /፩ኛ ነገ.፲፰፡፫-፲፫/፡፡ አክዓብ ሞቶ አካዝያስ ከነገሠ በኋላም አብድዩ ቢትወደድ ኾኖ ኖሯል፡፡
 የመጽሐፉ የአንድምታ ትርጓሜ መቅድም እንደሚነግረን ነቢዩ አብድዩ ከጨዋነት ወደ ነቢይነት የተመለሰው በነቢዩ ኤልያስ አማካኝነት ነው፡፡ በመጽሐፈ ነገሥት ካልዕ ምዕራፍ ፩ ከቊጥር ፲፫ ላይ የተጠቀሰውና ንጉሥ አካዝያስ የላከው ሦስተኛው አለቃም ይኸው አብድዩ ነው፡፡

Monday, December 23, 2013

“ብርሃንካን ሐቅኻን ልአኽ ይምርሑኒ ካዓ ናብ ቅዱስ እምባኻን መሕደሪኻን ድማ ይውሰዱኒ።” መዝ.43:3ብዲ/ን ፅጋቡ ወልዱ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታሕሳስ 14፣ 2006 ዓ.ም. ግእዝ)፡- በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ አሜን!!!
መእተዊ
 በቋንቋ ቤተክርስቲያን ወይም ብናይ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ቅድሚ በዓል ልደት ዘለዋ ሠለስተ ሰናብቲ፡- ስብከት፣ ብርሃንን ኖላዊን ብምባል ይፍለጣ፡፡ ቅድስቲ ቤተክርስቲያ ነገር ኩሉ ብግዚኡ አዝዩ ግሩም ገይሩ ንዝፈጠረ ኣምላክ ምስጋናአ ብዘመናት ከፋፊላ ምቕራብ ባህሪአ እዩ /መክ 3፣11/፡፡ ሕድሕድ ሰንበት ነናይ ባዕሉ ትምህርቲ ዝሐዘ እዩ፡፡ ካብተን ሠለስተ ሰናብቲ እተን ናይ መጨረሽታ ክልተ ማለት እውን ብርሃንን ኖላዊን እግዚአብሔር ብዝፈቐዶ መጠን ክንመሃሃር ኢና፡፡

Sunday, December 22, 2013

ነቢዩ ኢዩኤል

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፲፬ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
“ኢዩኤል” ማለት “እግዚአብሔር አምላክ ነው” ማለት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱሳችን እንደምንመለከተውም “ኢዩኤል” የሚለው ስም በዕብራውያን የተለመደ መኾኑ ነው /፩ኛ ሳሙ.፰፡፪፣ ፩ኛ ዜና ፬፡፴፭፣ ፪ኛ ዜና ፳፱፡፲፪፣ ዕዝራ ፲፡፵፫/፡፡
 አባቱ ባቱአል እናቱም መርሱላ ይባላሉ፡፡ የመጽሐፉ የአንድምታ ትርጓሜ መቅድም እንደሚናገረው ነገዱ ከነገደ ሮቤል ወገን ነው፡፡ ሌሎች ሊቃውንት ግን ኢዩኤል ከነገደ ይሁዳ ወገን እንደኾነ ይናገራሉ፡፡ ለዚኽ አባባላቸው እንደ ማስረጃ የሚያስቀምጡትም አንደኛ ኢዩኤል ይኖር የነበረው በኢየሩሳሌም መኾኑ፤ ኹለተኛ በመጽሐፉ ስለ ካህናት ማንሣቱ /፩፡፲፫/፤ ሦስተኛ ስለ ቤተ መቅደስ መናገሩ /፩፡፱/፣ እና ሌላም ሌላም በማለት ነው፡፡

Friday, December 20, 2013

ነቢዩ ሚክያስ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፲፪ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
“ሚክያስ” ማለት “መኑ ከመ እግዚአብሔር - እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው?” ማለት ነው፡፡ ይኸውም ተልእኮውን የሚያስረዳ ነው፡፡ ምክንያቱም መጽሐፉን ስናነብ የሚከተሉትን እንገነዘባለንና፡-

Tuesday, December 17, 2013

ነቢዩ አሞጽ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፱ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
“አሞጽ” ማለት “ሽክም፣ ጭነት” ማለት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ በዚኽ ስም የሚጠሩ ሦስት ሰዎች ያሉ ሲኾን እነርሱም የነቢዩ ኢሳይያስ አባት /ኢሳ.፩፡፩/፣ የምናሴ ልጅ ንጉሥ አሞጽ /፪ኛ ነገ.፳፩፡፲፰/ እንዲኹም ለዛሬ የምናየውና ከደቂቀ ነቢያት አንዱ የኾነው ነቢዩ አሞጽ ናቸው፡፡
 የቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት እንደሚያስረዳው የነቢዩ አሞጽ አባት ቴና ሲባል እናቱ ደግሞ ሜስታ ትባላለች፡፡ ነገዱም ከነገደ ስምዖን ወገን ነው፡፡

Sunday, December 15, 2013

ነቢዩ ሆሴዕ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፮ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
“ሆሴዕ” ማለት ከ፲፪ቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ ሲኾን የስሙም ትርጓሜ “መድኃኒት” ማለት ነው፡፡ መድኃኒት መባሉም እንደ ኢያሱ ወልደ ነዌ ባጭር ታጥቆ፥ ጋሻ ነጥቆ፥ ዘገር ነቅንቆ አማሌቃውያንን አጥፍቶ እስራኤልን አድኖ፥ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋዉን ቆርሶ፥ ደሙን አፍስሶ፥ ፲፫ቱን ሕማማተ መስቀል ታግሦ፥ አጋንንትን ድል ነስቶ ነፍሳትን አድኖ አይደለም፤ አባት እናቱ በትንቢቱ በትምህርቱ እንዲያድን አውቀው “ሆሴዕ - መድኃኒት” ብለዉታል እንጂ፡፡ ስለዚኽ የስሙ ትርጓሜ ተልእኮውን የሚያስረዳ ነው ማለት ነው፡፡

Friday, December 13, 2013

ነቢዩ ዳንኤል

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፬ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
 “ዳንኤል” ከአራቱ ዐበይት ነቢያት አንዱ ሲኾን የስሙም ትርጓሜ “እግዚአብሔር ፈራጅ ነው” ማለት ነው፡፡ ይኸውም ተልእኮውን የሚገልጥ ነው፡፡ አፍአዊ በኾነ ትርጓሜ (Literally) ስንመለከተው እግዚአብሔር በነቢዩ ዳንኤል አድሮ በአሕዛብ ላይ እንደሚፈርድ፤ በአሕዛብ ላይ ብቻ ሳይኾን የዋሐንን በሚከስሱ ሰዎች ላይ እንደሚፈርድ፤  አንድም እግዚአብሔር ጨቋኙን ንጉሥ አጥፍቶ ወደ ምርኮ የኼዱት ኹለቱም ወገኖች ማለትም እስራኤልንና ይሁዳን ነፃ እንደሚያወጣቸው የሚያስረዳ ሲኾን፤ በምስጢራዊው መልኩ ግን የክብር ባለቤት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዲያብሎስ ምርኮ የኼዱት ኹለቱም ወገኖች ማለትም ሕዝብም አሕዛብም ከኃጢአት ባርነት ነፃ አውጥቶ የክብርን ሸማ እንደሚያለብሳቸው/ሰን የሚያመለከት ነው፡፡ 

Wednesday, December 11, 2013

ነገረ ማርያም - ክፍል ፫ (የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ መግባት)በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲሳት መምህር

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፫ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
 ቅድስት ድንግል ማርያምም እስከ ሦስት ዓመት ድረስ በእናት በአባቷ ቤት ውስጥ ኖራለች፤ ይኽነን በእናት በአባቷ ቤት የነበራትን አስተዳደግ “Protoevangelium of James” (ፕሮቶቫንጊሊዩም ኦፍ ጀምስ) በሚለው ጥንታዊዉ መጽሐፍ ሲገልጽ (ሕፃኗም ከቀን ወደ ቀን በኀይልና በብርታት እያደገች ኼደች፤ የስድስት ወር ልጅ በኾነች ጊዜ እናቷ መቆም ትችል እንደኾነ ለማየት መሬት ላይ አቆመቻት፤ ርሷም ሰባት ርምጃ ተራምዳ ወደእናቷ ዕቅፍ ውስጥ ገባች፤ እናቷም እንዲኽ አለቻትወደ ጌታ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አስክወስድሽ ድረስ በራስች እንዳትራመጂ አለቻትና በመኝታ ቤቷ ውስጥ ውስጥ የቅድስና ስፍራ አበጀችላትአንድ ዓመት በኾናት ጊዜም ኢያቄም ታላቅ ግብዣ አድርጎ ካህናቱን፣ ጸሐፈትን፣ ታላቆችንና ሕዝብን ጠራ፤ ከዚያም ኢያቄም ልጁን ወደ ካህናቱ አቀረባት እነርሱምአባታችን እግዚአብሔር ሆይ ይኽቺን ልጅ ባርካት በትውልድ ኹሉ የሚጠራ ማብቂያ የሌለው ስምን ስጣት እያሉ ባረኳት፤ ሕዝቡም ኹሉይደረግ ይኹን ይጽና አሜንአሉ፤ ከዚያም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዳት ርሱምልዑል እግዚአብሔር ሆይ ይኽቺን ልጅ ተመልከት ለዘላለም በሚኖር በፍጹም በረከትም ባርካትበማለት ባረካት፤ ሐናም ይዛት ወደ ተቀደሰው የማደሪያዋ ክፍል በመውሰድ ጡትን ሰጠቻት…) ይላል፡፡

ነገረ ማርያም - ክፍል ፪ (የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የትውልድ ሀረጓ የተቀደሰ ታሪክ)መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲሳት መምህር

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፪ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

 የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት እንዳስተማሩትና እንደጻፉት በእናቷ በሐና በኩል ያሉ የእመቤታችን ቅድመ አያቶቿ ጴጥሪቃ ቴክታ ሲባሉወኮኑ ክልኤሆሙ ጻድቃን ወፈራህያነ እግዚአብሔር ወይትአመንዎ ለአምላኮሙ በጥቡዕ ልብ እንበለ ኑፋቄይላል (ኹለቱም ሰዎች ደጋጐችና እግዚአብሔርን የሚፈሩ ያለምንም መጠራጠር በፍጹም ልቡናቸው በአምላካቸው የሚተማመኑ ነበሩ) እነሱም በጊዜው ይኽ ቀራችኊ የማይባሉ ባለጠጎች ነበሩ፤ ከሀብታቸው ብዛት የተነሣ ወርቁን ብሩን ንደ ዋንጫ እያሠሩ ከላሙ ከበሬው ቀንድ ይሰኩት ነበር፤ ይኽን ያኽል አቅርንተ ወርቅ፣ አቅርንተ ብሩር እየተባለ ይቈጠር ነበር የዕንቁ ጽዋ እንኳ ፸፣ ያኽል ነበራቸው፡፡

Tuesday, December 10, 2013

ነቢዩ ሕዝቅኤል

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፥ ታኅሳስ ፪ ቀን፥ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
“ሕዝቅኤል” ማለት “እግዚአብሔር ብርታትን ይሰጣል” ማለት ነው፡፡ ይኸውም በነቢይነት የተላከው በዘመኑ ወደ ነበሩ ዓመፀኞች ሰዎች፣ ፊታቸው የተጨማተረ ልባቸውም የደነደነ ልጆች ወደ እስራኤል ልጆች ስለ ነበረ እግዚአብሔር ብርታትን እንደሚሰጠው ሲያስረዳ ነው /ሕዝ.፪፡፫-፬/፡፡ ነቢዩ ሕዝቅኤል የካህኑ የቡዝ ልጅ ነው፡፡ እናቱም “ህሬ” እንደምትባል የቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ያስረዳል፡፡ የእስራኤል ካህን እንደ ነበር፤ ዳግመኛም ባለ ትዳር እንደ ነበር /ሕዝ.፰፡፩/ ተገልጧል፡፡

Sunday, December 8, 2013

ነቢዩ ኤርምያስ

ገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ኅዳር ፳፱፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
“ኤርምያስ” ማለት “እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ያደርጋል” ማለት ነው፡፡ ከአራቱ ዓበይት ነቢያት አንዱ ሲኾን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን አባቱ “ኬልቅያስ” ይባላል፡፡ እናቱ ደግሞ “ማርታ” እንደምትባል የቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ትውፊት ያስረዳል፡፡ አገሩ በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ካለው ከተማ ከ“ዓናቶት” ነው፤ ትውልዱም ከካህናት ወገን እንደነበረ ተጽፏል /ኤር.፩፡፩/፡፡

Friday, December 6, 2013

“መምህር ሆይ! አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነኽ” /ዮሐ.፩፡፶/

በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፥ ኅዳር ፳፯ ቀን፥ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የምታውቅ ነፍስ ሐሴት ታደርጋለች፡፡ ክርስቶስን፡- “አንተ መምህረ እስራኤል ነኽ፤ አንተ ንጉሠ ሰማይ ወምድር ነኽ” ትሏለች፡፡ ይኸውም እንደ ፊሊጶስ ማለት ነው /ዮሐ.፩፡፶/፡፡ ይኽቺ ነፍስ ሐሴትን የምታደርገው ግን በነቢብ ብቻ አይደለም፤ በገቢርም ጭምር እንጂ፡፡ ተወዳጆች ሆይ! ክርስቶስን ታውቁታላችሁን? እንኪያስ ትእዛዛቱን ጠብቁ፡፡ ክርስቶስን የሚያሳዝን ገቢር እየፈጸምን እንደምን ደስ የሚያሰኘውን ነገር ማድረግ ይቻለናል?

Wednesday, December 4, 2013

ነቢዩ ኢሳይያስ

ገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ኅዳር ፳፮ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- ኢሳይያስ የሚለው ስም በአይሁድ ማኅበረ ሰብ ውስጥ እጅግ የተለመደ ስም ነው፤ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ እንኳ ብያንስ ወደ ፯ የሚኾኑ ሰዎች በዚኽ ስም ተጠርተዋል፡፡
 “ኢሳይያስ፣ የሻያ” ከአራቱ ዐበይት ነቢያት አንዱ ሲኾን የስሙም ትርጓሜ “መድኃኒት” ማለት ነው፡፡ ሆሴዕ፣ ኢያሱ፣ ኢየሱስ ማለት መድኃኒት ማለት እንደኾነ መድኃኒት መባሉ ግን እንደ ኢያሱ ወልደ ነዌ ባጭር ታጥቆ፥ ጋሻ ነጥቆ፥ ዘገር ነቅንቆ አማሌቃውያንን አጥፍቶ እስራኤልን አድኖ፥ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋዉን ቆርሶ፥ ደሙን አፍስሶ፥ ፲፫ቱን ሕማማተ መስቀል ታግሦ፥ አጋንንትን ድል ነስቶ ነፍሳትን አድኖ አይደለም፤ ተልእኮውን የሚገልጥ ነው እንጂ፡፡ በሌላ አገላለጽ ሊመጣ ያለው መሲሕ ማለትም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድንግልና ተፀንሶ፣ በድንግልና ተወልዶ፣ ቀስ በቀስ አድጎ፣ የደቂቀ አዳምን ሕማም ተሸክሞ አጠቃላይ የሰው ልጆችን በአስደናቂ መጐብኘትን ጐብኝቶ እንደሚያድናቸው ስለሚናገር “ኢሳይያስ - መድኃኒት” የሚል ስም ተሰጥቶታል፡፡

Monday, December 2, 2013

ነገረ ነቢያት

ገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፥ ኅዳር ፳፬ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- ነቢይ ማለት አፈ እግዚአብሔር፣ መምህር፣ ሰባኪ፣ … ማለት ነው፡፡ ስያሜውም መንፈሰ ትንቢት ላደረባቸው፣ ራዕይን የማየት ጸጋ ለተሰጣቸው እውነተኛ ነቢያት ብቻ የሚሰጥ ነው፡፡
  በብዙዎቻችን አእምሮ እንደሚታሰበው “ነቢይ ማለት ስለ መፃእያት ብቻ የሚናገር ነው”፡፡ ኾኖም ነቢይ መፃእያትን ከመናገር በተጨማሪ እግዚአብሔር በየትኛውም ዘመን ለሰው ልጆች ያለውን ሐሳብና ፈቃድ በተለይ ደግሞ ከዘለዓለማዊ ድኅነት ጋር አያይዞ የሚገልጥ ነው፡፡ ለዚኽም ነው የነቢያትን መጻሕፍት ስንመለከት በውስጡ ብዙ የሕግ፣ የታሪክ፣ የጥበብና የቅኔ ይዘት እንዳለው የምናስተውለው፡፡

FeedBurner FeedCount