(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፲፭ ቀን፣
፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ
አሐዱ አምላክ አሜን!
“አብድዩ”
ማለት “ገብረ እግዚአብሔር - የእግዚአብሔር አገልጋይ” ማለት ነው፡፡ ይኽ ስም በዘመኑ የታወቀ ስም ነበር፡፡ ነቢዩ አብድዩ ነገዱ
ከነገደ ኤፍሬም ሲኾን አባቱ አኪላ እናቱም ሳፍጣ እንደሚባሉ የቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ያስረዳል፡፡
ነቢዩ አብድዩ
የአክአብ ቢትወደድ ነበር፡፡ ኤልዛቤል ነቢያት ካህናትን ስታስፈጃቸው ኃምሳውን በአንድ ዋሻ ኃምሳውን በአንድ ዋሻ አድርጐ ልብስ
ቀለብ እየሰጠ ይረዳቸው የነበረውም ይኸው ነቢይ ነው /፩ኛ ነገ.፲፰፡፫-፲፫/፡፡ አክዓብ ሞቶ አካዝያስ ከነገሠ በኋላም አብድዩ
ቢትወደድ ኾኖ ኖሯል፡፡
የመጽሐፉ
የአንድምታ ትርጓሜ መቅድም እንደሚነግረን ነቢዩ አብድዩ ከጨዋነት ወደ ነቢይነት የተመለሰው በነቢዩ ኤልያስ አማካኝነት ነው፡፡ በመጽሐፈ
ነገሥት ካልዕ ምዕራፍ ፩ ከቊጥር ፲፫ ላይ የተጠቀሰውና ንጉሥ አካዝያስ የላከው ሦስተኛው አለቃም ይኸው አብድዩ ነው፡፡
ትንቢተ አብድዩ
ትንቢተ
አብድዩ ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በጣም ትንሿና ፳፩ ቊጥሮችን ብቻ የያዘች ባለ ፩ ምዕራፍ መጽሐፍ ነች፡፡ ነገር ግን ትንሽ ስለኾነች
እግዚአብሔር ወደ እኛ እንዳትደርስ አላደረጋትም፡፡
የመጽሐፏ
ዋና ዓላማም በኤዶምያስ ላይ ስለሚመጣው ፍርድ መናገር ነው፡፡ ኤዶምያስ ማለት ደግሞ በጽርዕ አጠራር የኤዶም አገር ናት /ማር.፫፡፰/፡፡ ኤዶም
ማለትም የያዕቆብ ወንድም የዔሳው ሌላ ስሙ ነው /ዘፍ.፳፭፡፴/፡፡ ከእርሱ የተገኙ ሕዝቦችም ኤዶማውያን ይባላሉ፡፡ አገራቸውም “የኤዶም
አገር፣ የሴይር ምድር” እየተባለች ትጠራለች /ዘፍ.፴፪፡፫/፡፡
ኤዶም ከጥንት
አንሥቶ የወንድሙ የያዕቆብ ጠላት ነው፡፡ የያዕቆብ ልጆች (እስራኤላውያን) ከግብጽ የ፬፻፴ ዓመታት ባርነት በኋላ ወደ አገራቸው
ሲመለሱ “በምድሬ አታልፍም” ብሎ የከለከላቸውም ስለዚኹ ነው /ዘኅ.፳፡፲፰/፡፡ ንጉሥ ዳዊት ኤዶማውያንን ድል አድርጓቸው ነበር፤
በአገራቸው ላይ ጭፍሮችን አስቀምጦም ግብር ያስገብራቸው ነበር /፪ኛ ሳሙ.፰፡፲፫-፲፬/፡፡ በኋላ ላይ ግን ለይሁዳ እንዳይገብር
ሸፍተዋል፤ በዳዊት ልጆች ላይም በየጊዜው አደጋ ይጥሉ ነበር /፪ኛ ነገ.፰፡፳/፡፡
ኤዶማውያን
በይሁዳ ላይ በሚደርሰው ማንኛውም ዓይነት ችግር ደስ ይሰኙ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ አይሁዳውያን በባቢሎናውያን በተማረኩ ጊዜ የልብ
ልብ ይሰማቸው ነበር፡፡ አይሁዳውያን በባቢሎናውያን እንዲማረኩም የራሳቸው የኾነ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ ከመጽሐፉ ማንበብ እንደምንችለው ይሁዳ በባቢሎን ጭፍሮች ስትወረር፡- ኤዶም
ከወራሪዎቹ አንዱ ነበር፤ በወንድሞቹ ይኸውም በይሁዳ ልጆች ጥፋት ደስ ይለው ነበር፤ በአይሁድ ጭንቅ ቀን በትዕቢት ይናገር ነበር፤
ሀብታቸውን ይወስድ ዘንድ እጁ ዘርግቷል፤ ከጠላት አምልጠው የሸሹትን ለመግደል በመንታ መንገድ ላይ ቆሞ ይጠብቅ ነበር፤ ከምርኮ
የቀሩትን ደግሞ ከተደበቁበት እየፈለገ ለጠላት አሳልፎ ይሰጥ ነበር /ቊ.፲፩-፲፬/፡፡ እግዚአብሔር ግን በነቢያቱ በእነ ነቢዩ
ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤል፣ አብድዩ፣ ሶፎንያስ እና በሌሎችም አድሮ ከዚኽ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ አስጠነቀቃቸው፤ በእነርሱ ላይ የሚመጣውንም
ፍርድ ተናገረባቸው፡፡
እግዚአብሔር
ግን ለልጆቹ እጅግ ቀናተኛ አምላክ ነውና ኤዶም ይሁዳን በፈረደበት ፍርድ እንደሚፈርድበት ተናግሯል /ቊ.፲፭/፡፡ እንክርዳድ ዘርቶ
ስንዴ ማጨድ አይቻልምና፥ ኤዶም ክፋትን እንደዘራ ፍዳው በራሱ ላይ እንደሚመለስ ተናግሯል፡፡ ይኸውም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡-
“ሰው ራሱን ካልጐዳ በስተቀር ማንም ሊጐዳው አይችልም” እንዳለው ነው፡፡ ቀጥሎም እግዚአብሔር የጽዮን ተራራ ክፉ በሚያደርጉ ኹሉ
ላይ የሚያቃጥል እሳትን እንደምታወጣ ተናገረ፡፡ ይኸውም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው /ቊ.፲፯-፲፰/፡፡
በአጠቃላይ
መጽሐፉ አንድ ሰው በገዛ ወንድሙ ጉዳት ደስ ሊለው እንደማይገባና ይልቁንም ሊያዝንለትና ከተቻለውም ሊረዳው እንደሚገባ የሚያስረዳ
ነው፡፡ መጽሐፉ የሚያልቀው፡- “… መንግሥቱም ለእግዚአብሔር ይኾናል” ብሎ በማወጅ ነው፡፡ ይኸውም “በያዕቆብ ቤትም ለዘለዓለም
ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም” እንደተባለ ስለ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገር ነው /ሉቃ.፩፡፴፫/፡፡
ከዚኽ ምን እንማራለን?
v ኤዶም “የወንድሜ ችግር የእኔ ችግር አይደለም፤ የወንድሜ
ውርደት የእኔ ውርደት አይደለም” ብለው ለሚያስቡ ኹሉ አርአያ ነው፡፡ ዛሬ የወንድማችንን ችግር እንደ ራሳችን ችግር የማንወስድ
ሰዎች ካለን እኛ አዲሶቹ ኤዶሞች ኾነናል ማለት ነው፡፡
v ኤዶም እንኳንስ ወንድሙን ያዕቆብን ሊረዳው ቀርቶ አልፎ
ተርፎም ጉዳት ሲያደርስበት የነበረ “ወንድም” ነው፡፡ ዛሬም መርዳት እንኳን “ባንችል”፥ አልፈን ተርፈንም ወንድሞቻችንን የምንጐዳ
ከኾነ ቃሉ እንደሚናገር ፍዳን በራሳችን ላይ የምንጨምር ኤዶማውያን ኾነናል ማለት ነው /ቊ.፲፭/፡፡
v ኤዶም ጥልንና መለያየትን የሚሰብክ ወንድም ነው፡፡ ዛሬም
ከቤተ ክርስቲያን ባሕርይ ጋር የማይስማማ መለያየትን የምንሰብክ ከኾነ ስማችን “ክርስቲያን” ሳይኾን “ኤዶማውያን” ነው፡፡
v ኤዶም ስለ ምስር ወጥ ብሎ ብኵርናውን የሸጠ ሰው ነው፡፡
ዛሬም ሰማያዊውን መና ረስተን ስለ ምድራዊ ምስር ብቻ የምንባክን ከኾነ ዜግነታችን ክርስቶሳዊ መኾኑ ቀርቶ ኤዶማዊ ኾኗል ማለት
ነው፡፡ ታላቅ መኾናችን ቀርቶ ታናሽ ኾነናል ማለት ነው፡፡
v ኤዶም ማለት መሬት ማለት ነው፡፡ ስለዚኽ ሐሳባችን ኹሉ
ኤዶማዊ ከኾነ ሰማያውያን መኾናችን ቀርቶ ምድራዊያን ነን ማለት ነው፡፡ የፊተኛው ሰው የአዳም መልክ ይዘናል እንጂ የኋለኛ ሰው
የክርስቶስን መልክ አልያዝንም /፩ኛ ቆሮ.፲፭፡፵፯/፡፡ የሚበሰብሰው ደግሞ የማይበሰብሰውን አይወርስም፡፡
ኹሉን የሚገዛ ጌታ አምላካችን በኹለንተናችን ላይ ነግሦ ኤዶማዊ ማንነታችንን
ይሻርልን፡፡ አሜን!!!
No comments:
Post a Comment