(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፥ ታኅሳስ ፪ ቀን፥
፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
“ሕዝቅኤል” ማለት “እግዚአብሔር ብርታትን ይሰጣል” ማለት ነው፡፡ ይኸውም
በነቢይነት የተላከው በዘመኑ ወደ ነበሩ ዓመፀኞች ሰዎች፣ ፊታቸው የተጨማተረ ልባቸውም የደነደነ ልጆች ወደ እስራኤል ልጆች ስለ ነበረ እግዚአብሔር ብርታትን እንደሚሰጠው ሲያስረዳ ነው /ሕዝ.፪፡፫-፬/፡፡ ነቢዩ
ሕዝቅኤል የካህኑ የቡዝ ልጅ ነው፡፡ እናቱም “ህሬ” እንደምትባል የቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ያስረዳል፡፡ የእስራኤል ካህን እንደ
ነበር፤ ዳግመኛም ባለ ትዳር እንደ ነበር /ሕዝ.፰፡፩/ ተገልጧል፡፡
ነቢዩ
ሕዝቅኤል በ፮፻፳፫ ከክ.ል.በ. የተወለደ ሲኾን ከሕፃንነቱ አንሥቶ የነቢዩ ኤርምያስ ደቀ መዝሙር ነበር፡፡ በመኾኑም በነቢዩ ኤርምያስ
ዘመን የነበረው ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ኹናቴ በነቢዩ ሕዝቅኤል ላይ ቀላል የማይባል ተጽዕኖ አሳድሮበታል፡፡
በነቢዩ ሕዝቅኤል
ዙርያ የነበረው ነባራዊ ኹኔታ
የሕዝቅኤል የአገልግሎት ዘመን በኹለት ልንከፍለው እንችላለን፡-
1.
ኢየሩሳሌም በ፭፻፹፯ ከክ.ል.በ. በጠላት እጅ በመውደቋ አስቀድሞ በባቢሎን ምርኮኞች መካከል የፈጸመው
የስብከት አገልግሎትና /ምዕ.፬-፳፬/፤
2.
ኢሩሳሌም በጠላት እጅ ከወደቀች በኋላ በባቢሎን የፈጸመው የስብከት አገልግሎት /ምዕ.፴፫-፵፰/ በማለት፡፡
ሀ) ሕዝቅኤል
ከምርኮ በፊት
አስቀድመን
ለመግለጽ እንደሞከርነው ነቢዩ ሕዝቅኤል የተወለደው በ፮፻፳፫ ከክ.ል.በ. ነው፡፡ ይኽ ጊዜ ደግሞ በኹለት መልኩ ነቢዩን ተጽዕኖ
አሳድሮበታል፡፡ በአንድ መልኩ ንጉሥ ኢዮስያስ ባዕድ አምልኮን ለማስወገድ፣ የእግዚአብሔርን ቤትና አምልኮ ለማሳደስ ይጣደፍበት የነበረበት
ሰዓት ነው፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ይኽ ወቅት በአመዛኙ ነቢያት ያንሰራሩበት ወራት ነበር፡፡ ስለዚኽ ንጉሥ ኢዮስያስ ባዕድ አምልኮን
ለማስወገድ፥ የእግዚአብሔርንም ቤትና አምልኮ ለማሳደስ ሲያደርገው የነበረው ጥረት፣ የሕጉ መጽሐፍ ዳግም የመገኘቱና በንጉሡ የመነበቡ
ዜና በነቢዩ ሕዝቅኤል የጨቅላነት አእምሮ ላይ የታተሙ ድርጊቶች ናቸው፡፡ ከዚኽም በላይ አባቱ ካህን እንደመኾኑ መጠን ቤተ መቅደሱ
ሲታደስ ነቢዩ ሕዝቅኤል በምን ዓይነት ኹናቴ ሊኖር እንደሚችል (ወደ ቤተ መቅዱስ ሔዶ ዕድሳቱን ሊያግዝ እንደሚችል) ማወቅ አያዳግትም፡፡
ነቢዩ ሕዝቅኤል የነቢዩ ኤርምያስ ደቀ መዝሙር እንደመኾኑ መጠንም ኤርምያስ ምን ያኽል በሕዝቅኤል ልቡና ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡
ነቢዩ ሕዝቅኤል
በማንነቱ ላይ ተፅዕኖ ያደረገው ግን ይኸው ብቻ አይደለም፤ በጊዜው የነበረው ፖለቲካዊ ትኩሳትም ጭምር እንጂ፡፡ ገና ዐሥር ዓመቱ
ሳለ የአሦር ዋና ከተማ የነበረችው ነነዌ ከመንግሥቷ ጋር ወድቃለች፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላ የግብጹ ፎርዖን ኒካዑ ፍልስጥኤምን
ወርሮ ንጉሥ ኢዮስያስን በመጊዶ ገድሎታል /፪ኛ ነገ.፳፫፡፳፱/፡፡ ከዚኽም በላይ ነቢዩ ኤርምያስ ሕዝቡ የግብዝነት ምልልሳቸውን እንዲያስተካክሉ፤
መፃተኛውን፣ ድኻ አደጉን፣ መበለቲቱን እየበደሉ እልፍ ጊዜ መሥዋዕት ማቅረባቸው ቤተ መቅደሱን የወንበዴዎች ዋሻ ማድረግ እንደኾነ
ሲያሳሰባቸው /ኤር.፯፡፰-፲/፤ ካልተመለሱ ግን እነርሱ በባዕድ ንጉሥ እንደሚማረኩ፥ ቤተ መቅደሱም እንደሚፈርስ በቤተ መቅደሱ በር
ኾኖ በመጮኽ በግልጽ ሲነግራቸው /ኤር.፯፡፬/ ነቢዩ ሕዝቅኤል ይሰማ ነበር፡፡ የኢዮስያስ ልጅ ኢዮአክስ (ሰሎም) በነገሠ ገና በ፫ኛው ወሩ የግብጽ ንጉሥ አስሮ እንደወሰደው /፪ኛ ዜና ፴፮፡፩-፬፣ ኤር.፳፪፡፲-፲፪/፣ የግብጹ
ንጉሥ ኢየሩሳሌምን ሊያፈርሳት አለመውደዱ፤ ይኸውም ከእርሷ የሚያገኘው የወርቅና የብር ግብር እንዳይቀርበት መኾኑን ሕዝቅኤል አይቷል፡፡
ነቢዩ ሕዝቅኤል
በዚኽ የወጣትነት ዕድሜው በገዛ ወገኖቹ ይከሰቱ የነበሩትን ለውጦችም ያይ ነበር፡፡ ያለ ምንም ሐፍረት ጣዖታት በኢየሩሳሌም ጐዳናዎች
እንዴት ይታዩ እንደ ነበር፣ የካህናቱና የመምህራኑ ሕይወት እንዴት በክፋት የተለወሰ እንደነበር፣ የቤተ መቅደሱ አገልግሎትም እንዴት
እንደታጐለ አሳምሮ ያውቃል፡፡ ነቢዩ ኤርምያስ ስለዚኹ ድርጊታቸው ሕዝቡን ሲገስፃቸው፣ ባሮክ በቤተ መቅደስ ኼዶ የነቢዩ ኤርምያስን
መጽሐፍ ሲያነብላቸው ሰምቷል፡፡ ይኽ ብቻ ሳይኾን ንጉሡም ጥቂት ሐረጐችን ከሰማ በኋላ የእግዚአብሔርን ቃል አቃልሎ ጥቅሉን ሲያቃጥለው
ሰምቷል /ኤር.፴፮፡፩-፳፮/፡፡
በዚኹ ዓመት
የባቢሎኑ ንጉሥ ናቡከደነፆር የግብጹን ፎርዖን ኒካዑን ድል አድርጐታል፡፡ ናቡከደነፆር ቀጥሎ የመጣው ወደ ቅድስቲቱ ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም
ነበር፤ በ፭፻፺፯ ከክ.ል.በ. ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ከተማይቱን፣ ቤተ መቅደሱን፣ ሕዝባዊ ሕንፃዎቿን፣ ጠላትን ለመከላከል የምትጠቀምባቸው
ግንቦቿን እንኳ አልነካም፡፡ ይልቁንም በዚያ ሰዓት በይሁዳ ገና ፫ ወር ብቻ የነገሠው ንጉሥ ዮአኮንና እናቱ፥ ባርያዎቹም፥ አለቆቹም፥ ጃንደረቦቹም፣ የእግዚአብሔርም ቤት መዛግብትን ኹሉ፣ የንጉሡም ቤት መዛግብትን ወደ ባቢሎን ወሰደው /፪ኛ ነገ.፳፬፡፰-፲፮/፡፡ ይኽም ማለት ከ፫፻ ዓመታት በፊት
የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን በእግዚአብሔር መቅደስ ያኖራቸውን ንዋያተ ቅዱሳት ኹሉ ተማርከዋል ማለት ነው፡፡ የባቢሎኑ ንጉሥ ናቡከደነፆር በዚኹ ዓመት ኢየሩሳሌምን ኹሉ፥ አለቆቹንም ኹሉ፥ ጽኑዓን ኃያላኑንም ኹሉ፥ ጠራቢዎቹንም ኹሉ፥ ብረት ሠራተኞቹን ኹሉ አሥር ሺህ ምርኮኞች አፍልሷቸዋል፡፡ ከድኾችና ከአገሩ ሕዝብ በቀር ማንም አልቀረም፡፡ ነቢዩ ሕዝቅኤልም አብሮ ተማርኳል /፪ኛ ነገ.፳፬፡፲፬/፡፡ ይኽም በ፳፭ ዓመቱ መኾኑ ነው፡፡ ወጣቱ ነቢይ ሕዝቅኤል ይኽን ኹሉ እያየ ልቡ ይቈስል ነበር፡፡
ለ) ነቢዩ
ሕዝቅኤል በኮቦር ወንዝ
ወጣቱ ነቢይና ካህን ሕዝቅኤል በ፳፭ ዓመቱ ላይመለስ ኢየሩሳሌምን ትቷት ወደ
ባዕድ አገር ኼዷል፡፡ ከተማረኩት ወገኖቹ ጋር በኮቦር ወንዝ አጠገብ ይኖር ነበር፡፡ በመዠመሪያዎቹ የምርኮ ዓመታት ነቢዩ የወገኖቹን
ኹኔታ እያየ በአርምሞ ያለቅስ ነበር፤ በአንጻሩ ደግሞ የባቢሎን ኃያልነት ወደ ላይ እየበረታ ሲኼድ ያያል፡፡ አይሁድ በገነት ከሚመስልዋት
አገራቸው ተሰድደው፥ የባቢሎንን ከቀን ወደ ቀን የኃያልነት ዘውድ ጭና ወደ ላይ መውጣት ያየሉ፤ በዚኽም በስነ ልቡና እጅግ ይጐዱ
ነበር፡፡ መጐዳታቸው ግን ምርኮኞች በመኾናቸው ብቻ አይደለም፡፡ ይኖሩባት ዘንድ የተሰጠቻቸው ቦታ (ቴል አቢብ - የአኹኗ ግን አይደለችም)
ከዋና ከተማው የራቀች ስላልነበረችና የባቢሎናውያን “የድሎት” ኑሮን በአቅራብያ ያዩ ስለ ነበርም ጭምር እንጂ፡፡
አይሁድ
በዚኽ የምርኮ ምድር የግል እንቅስቃሴአቸውና ሃይማኖታዊ ግብራቸው የተገደበ አልነበረም፡፡ ባሻቸው ሰዓት መሰባሰብ ይችላሉ፡፡ ሽማግሌዎቻቸው
ማስተማርና በሕዝባቸው ላይ መፍረድ ይችላሉ፡፡ የግል ሥራ መሥራት ይችላሉ፡፡ ኢየሩሳሌም ካሉ ወገኖቻቸው እንኳ በመልዕክት ሰላምታ
ለመለዋወጥ አይከለከሉም ነበር፡፡
በተማረኩ
በ፭ኛው ዓመት ማለትም በ፭፻፺፪ ከክ.ል.በ. አከባቢ ግን ሰማያት ተከፈቱ፡፡ ሕዝቅኤል ለመዠመሪያ ጊዜ ራዕይ አየ፡፡ በዚኹ የትንቢት
መንፈስ እየተመራም ለ፳፪ ዓመታት ማለትም እስከ ፭፻፸ ከክ.ል.በ. ድረስ እያገለገለ ቆይቷል፡፡
ከተማረኩ
በ፮ኛው ዓመት ላይ ነቢዩ ሕዝቅኤል፥ ሴዴቅያስ በግብጽ ተማምኖ በናቡከደነፆር ማመፁን ሰማ /ሕዝ.፲፯፡፲፭/፡፡ ነቢዩም፥ ሴዴቅያስ
ከዚኹ ድርጊቱ እንዲቈጠብ፥ እንዲኽ ካልኾነ ግን በክፉ አወዳደቅ እንደሚወድቅ አስጠነቀቀው፡፡ ንጉሡ ይኽን ምክር የማይቀበል ከኾነ
የግብፅ ንጉሥ አስሮ እንደወሰደው የኢኮንያን ዕጣ ፈንታ እንደሚደርስበት፣ ኢየሩሳሌምም ከእኅቷ ከሰማርያ ባለመማሯ እንደምትወድቅ
ነገረው፡፡ እንደተናገረውም ከተማረኩ በ፲ኛው ዓመት ላይ ኢየሩሳሌም ወደቀች /ሕዝ.፳፬፡፪/፡፡ በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ሴዴቅያስ በሌሊት
ተደብቆ ለማምለጥ ሲሞክር በኢያሪኮ ተያዘ፡፡ ልጆቹ በፊቱ ተረሸኑ፡፡ ዓይኖቹ በጠላት እጅ ተጐልጉለው ወጡ፡፡ ዓይነ ስዉር ኾኖም
ተማርኮ ወደ ባቢሎን ኼደ፡፡ ሌሎች ጥቂት ሰዎችም ሸሽተው ወደ ግብጽ ኼዱ፡፡ ከእነዚኽ ጥቂት ሰዎች ጋርም ነቢዩ ኤርምያስና ባሮክ
አብረው ነበሩ፡፡
ነቢዩ ሕዝቅኤል
ከኢየሩሳሌም ውድቀት በፊት ያደረገው ስብከት የንስሐ ስብከት ነበር፡፡ ምክንያቱም ተማርከው የነበሩ አይሁድ፡- “በቶሎ ወደ አገራችን
እንመለሳለን፤ ባቢሎን ተሸንፎ አኹኑኑ ከአገራችን ይወጣልናል” የማለት ሐሳብ ስላደረባቸው ነበር፡፡ በዚኽም ኹሉ ወደ እግዚአብሔር
የመመለስ ምልክት አላሳዩም፡፡ “ኢየሩሳሌም ልትወድቅ አትችልም” የሚል አጕል እምነት ነበራቸው፡፡ ይኽም እግዚአብሔር ቅዱስ መኾኑንና
ኃጢአታቸውም ፍርድን እንደሚያስከትል ስላልተረዱ ነው፤ ከተማይቱ ከወደቀች በኋላ ግን የሕዝቡ መንፈስ ተለወጠና በኾነው ነገር እያዘኑ
ተስፋ ቈረጡ፡፡ ነቢዩ ሕዝቅኤል ግን ይኽን ኹሉ ቢያይም ተስፋ አልቈረጠም /ሕዝ.፴፬፡፲፫/፡፡ ከዚኽም የተነሣ ስብከቱ ተለውጦ የሚያጽናና
ቃል ኾነ፡፡ እግዚአብሔር በምሕረቱ ሕዝቡን እንደሚያድን፣ ለሕዝቡ ደንታ በሌላቸው እረኞች ላይም ፍርዱን እንደሚያመጣና በእነርሱ
ፈንታም እርሱ ራሱ እረኛ እንደሚኾንላቸው /ሕዝ.፴፬/፣ አዲስ ልብ እንደሚሰጣቸው /ሕዝ.፴፮፡፳፮-፳፰/፣ ወደ ምርኮ የኼዱት ኹለቱም
ወገኖች ማለትም እስራኤልና ይሁዳ ተመልሰው አንድ እንደሚኾኑና ዳዊት ንጉሥ እንደሚኾንላቸው /ሕዝ.፴፬፡፳፬/፣ የክብር ባለቤት ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ከከበረች ድንግል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንደሚወለድና ከወለድችውም በኋላ በድንግልና ፀንታ እንደምትኖር
/ሕዝ.፵፬/ ነገራቸው፡፡ ይኽን አዲስ ኹኔታ በአዲስ ቤተ መቅደስ ምሳሌነት ገለጠላቸው /ሕዝ.፵-፵፰/፡፡ የዚኹ ኹሉ ፍጻሜ በሐዲስ
ኪዳን መፈጸሙ እሙን ነው፡፡
ቃሉ ለሰዎች
እንዲሰማቸው ሕዝቅኤል ለረዥም ጊዜ በጐኑ በመተኛት፣ የሚያረክሰውን በመብላት፣ ጠጕሩን ቈርጦ በመበተን፣ ዲዳ በመኾን፣ ሚስቱ ስትሞት
ባለማልቀስ፣ በሌላም በአዲስ ኹኔታ ያስተምር ዘንድ ታዘዘ /ሕዝ.፬፣ ፭፣ ፲፪፣ ፳፬/፡፡ ሽማግሌዎች የነበሩ ምርኮኞች ይሰሙት ነበር፡፡
በመዠመሪያ ግን በቃሉ አልተደሰቱም፡፡ ከኢየሩሳሌም መፍረስ በኋላ በቃሉ ቢደሰቱም ብዙዎች በቃሉ መሠረት አልተለወጡም /ሕዝ.፪፡፬፣
፴፫፡፴-፴፫/፡፡ ኾኖም በነቢዩ አገልግሎት ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ፈቃደኛ የኾኑትን አዘጋጀ፡፡
የነቢዩ ሕዝቅኤል
ልዩ መገለጫዎች
1.
ካህን እንደ መኾኑ እግዚአብሔርን በንጹሕ
ልቡናው አገልግሏል፡፡ ሕገ እግዚአብሔር ኹለንተናውን ገንዘብ አድርጐታል፡፡
2.
ነቢይ እንደ መኾኑ የእስራኤልንና የይሁዳን
እንዲኹም የአሕዛብን ኃጢአት ተናግሯል፡፡ የእግዚአብሔር ፍርድ እስከምን ድረስ እንደኾነም ግልጽ አድርጓል፡፡ የዚኹ ኹሉ መፍትሔም
መሲሑን (ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን) መመልከትና ንስሐ መግባት ብቻ እንደኾነ አስተምሯል፡፡
3.
እረኛ እንደ መኾኑ የበጐቹን መከራ ተካፍሏል፡፡
ከአውሬ ድምፅ እንዲጠነቀቁ አስጠንቅቋቸዋል፡፡ የሚያጽናናቸው የእግዚአብሔር ቃል ብቻ መኾኑን አስረድቷቸዋል፡፡
4.
ባለ ራዕይ እንደመኾኑ ብዙ ራዕዮችን አይቷል፡፡
5.
የስነ መለኮት ምሁር እንደ መኾኑ ከውድቀት ዠርባ
ያለውን ምስጢር ገልጦላቸዋል፡፡
6.
የንስሐ አባት እንደ መኾኑ ከምርኮ በኋላ ሕይወታቸውን
እንዴት መምራት እንዳለባቸው መክሯቸዋል፡፡
7.
ፀሓፊ እንደ መኾኑ ያየውን ራዕይ ግሩም በኾነ አጻጻፍ ከትቦልናል፡፡
ትንቢተ ሕዝቅኤል
ሕዝቅኤል በባቢሎን ሳለ ከ፭፻፺፪-፭፻፸ ከክ.ል.በ. ለእስራኤል ምርኮኞች የተናገረው
ትንቢት ነው /ሕዝ.፩፡፩፣ ፳፱፡፲፯/፡፡ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በምርኮ የነበሩት አይሁድ “ኢየሩሳሌም ልትወድቅ አትችልም፤
በቶሎ ወደ አገራችን እንመለሳለን፤ ባቢሎን ተሸንፎ አኹኑኑ ከአገራችን ይወጣልናል” የሚል አጕል እምነት ነበራቸው፡፡ ሕዝቅኤል ግን
ወደ አገራቸው ቶሎ እንደማይመለሱ ለማስገንዘብ ቤት ገዝቶ ይኖር ነበር፡፡ የነቢዩ ኤርምያስን ቃል ያስታውሳቸው ነበር፡፡ የእግዚአብሔር
ክብር ከቤተ መቅደሱ እንደሚለይ /ሕዝ.፲፡፲፮-፲፰/፣ ኢየሩሳሌምም እንደምትወድቅ /ሕዝ.፳፫፡፳፩/ ይነግራቸው ነበር፡፡ በመኾኑም
የእግዚአብሔርን ምሕረት ቸርነት ለማግኘት ብቸኛውና አማራጭ የሌለው መንገድ ንስሐ እንደኾነ አስረግጦ ይነግራቸው ነበር /ሕዝ.፲፰፡፳፯/፡፡
በጣም የሚገርመው
ደግሞ በነቢዩ ዘመን የነበሩት አይሁድ የደረሰባቸው ኹሉ በአባቶቻቸው በደል ምክንያት እንደኾነና እነርሱ ግን ንጹሐን እንደኾኑ ያስቡ
ነበር፡፡ ሕዝቅኤል ግን ይኽ ትክክል እንዳልኾነ ነገራቸው /ሕዝ.፲፰፡፪/፡፡ እያንዳንዱ ሰው በራሱ ኃጢአት እንደሚቀጣና የሌላ ሰው
ጽድቅም ለእርሱ ጽድቅ እንደማይኾንለት ይነግራቸው ነበር /ሕዝ.፲፬፡፳/፡፡
ከላይ ለመግለጽ
እንደሞከርነውም ከተማይቱ ከወደቀች በኋላ ተስፋ ቈርጠው የነበሩት ሕዝብ በመጽሐፉ በስፋት ተስፋ ስጥቷቸዋል፡፡ ስለ ንጉሡ ስለ ኢየሱስ
ክርስቶስ መምጣት ነግሯቸዋል፡፡
መጽሐፉን
እንደሚከተለው መክፈል እንችላለን፡-
1.
ከኢየሩሳሌም ውድቀት በፊት ስለ እግዚአብሔር ፍርድ የተናገረው ትንቢት /ምዕ.፩-፳፬/፤
2.
በአሕዛብ መንግሥታት ላይ የተናገረው ትንቢት /ምዕ.፳፭-፴፪/፤
3.
ከኢየሩሳሌም ውድቀት በኋላ ስለ እስራኤል መመለስ የተናገረው ትንቢት /ምዕ.፴፫-፵፰/፡፡
የነቢዩ የመጨረሻው ዕረፍት
ሚያዝያ ፭ የሚነበበው ስንክሳር እንደሚነግረን ነቢዩ ሕዝቅኤል ያረፈው በሰማዕትነት
ነው፡፡ “የእስራኤል ልጆች በባቢሎን ሳሉ ጣዖት ባመለኩ ጊዜ ገሠፃቸው፤ ስለዚኽም አለቆቻቸው በላዩ አስነሥተው ገደሉት” በማለትም
ያስታውሰናል፡፡ በስንክሳሩ ያለው ሐሳብ በቀጥታ የቅዱስ ኤጲፋንዮስ ይመስላል፡፡
ለሕይወት የሚቀርልን
ተወዳጆች
ሆይ! ነቢዩ ሕዝቅኤል ራዕዩን ማየት የዠመረው በ፴ ዓመቱ ላይ ነው፡፡ በዚኹ የዕድሜ ክልል የምንኖር ወጣቶች ከዚኹ ነቢይ ምን እንማር
ይኾን? ነቢዩ ሕዝቅኤል ያደገው በመንፈስ አባቱ በነቢዩ ኤርምያስ እግር ስር ነው፡፡ እኛስ የመንፈስ አባቶቻችንን ምን ያኽል እናውቃቸዋለን?
ነቢዩ ሕዝቅኤል ያስተምር የነበረው፡- “ድኻውንና ችግረኛውንም ቢያስጨንቅ ቢቀማም መያዣውንም ባይመልስ ዓይኖቹንም ወደ ጣዖታት ቢያነሣ ርኩስን ነገር ቢያደርግ፥ በአራጣ ቢያበድር፥ ትርፎቻም ቢወስድ፥ በውኑ እርሱ በሕይወት ይኖራልን? በሕይወት አይኖርም፤ ይኽን ርኵሰት ኹሉ አድርጎአልና ፈጽሞ ይሞታል፤ ደሙ በላዩ ላይ ይሆናል። እነሆም፥ ልጅ ቢወልድ፥ እርሱም አባቱ የሠራውን ኃጢአት አይቶ ቢፈራ እንዲኽም ባይሠራ፥ በተራራ ላይ ባይበላ ዓይኖቹንም ወደ እስራኤል ቤት ጣዖታት ባያነሣ የባልንጀራውንም ሚስት ባያረክስ፥ ሰውንም ባያስጨንቅ መያዣውን ባይወስድ ባይቀማም ከእንጀራውም ለተራበ ቢሰጥ ለተራቈተውም ልብስን ቢያለብስ፥ እጁንም ድኻን ከመበደል ቢመልስ አራጣን ትርፎቻንም ባይወስድ ፍርዴንም ቢያደርግ በትእዛዜም ቢኼድ፥ እርሱ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ … አይሞትም። … ኃጢአተኛውም ካደረጋት ኃጢአት ኹሉ ቢመለስ ትእዛዜንም ኹሉ ቢጠብቅ ፍርድንና ቅን ነገርንም ቢያደርግ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም። የበደለው በደል ኹሉ አይታሰብበትም፤ በሠራው ጽድቅ በሕይወት ይኖራል። በውኑ ኃጢአተኛ ይሞት ዘንድ እፈቅዳለኹን? ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ከመንገዱስ ይመለስና በሕይወት ይኖር ዘንድ አይደለምን? ጻድቁ ግን ከጽድቁ ቢመለስ ኃጢአትንም ቢሠራ ኃጢአተኛውም እንደሚያደርገው ርኵሰት ኹሉ ቢያደርግ፥ በሕይወት ይኖራልን? የሠራት ጽድቅ ኹሉ አትታሰብለትም፤ ባደረገው ዓመፅና በሠራት ኃጢአት በዚያች ይሞታል። … የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እንግዲህ ስሙ፤ በውኑ መንገዴ የቀናች አይደለችምን? ይልቅስ የእናንተ መንገድ ያልቀናች አይደለችምን? ጻድቁ ከጽድቁ ቢመለስ፥ ኃጢአትንም በሠራ ጊዜ፥ በዚያም ቢሞት፥ እርሱ ባደረገው በደል ይሞታል። ኃጢአተኛውም ከሠራው ኃጢአት ቢመለስ ፍርድንና ቅን ነገርንም ቢያደርግ ነፍሱን ይጠብቃል” ባለው ቃል ምን ያኽል ተጠቅመናል?
ዋቢ ድርሳናት፡- የትንቢተ ሕዝቅኤል
መቅድም፣ ስንክሳር፣ A Patristic Commentary on Ezekiel by Fr. Tadros Malaty
No comments:
Post a Comment