Tuesday, December 24, 2013

ነቢዩ ዮናስ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፲፮ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
 “ዮናስ” ማለት “ርግብ” ማለት ነው፡፡ ዳግመኛም እንደ ቅዱስ ጀሮም ትርጓሜ “ስቃይ” ተብሎም ይተረጐማል፡፡ ይኸውም ተልእኮውን የሚገልጥ ነው፡፡ ነቢዩ ዮናስ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በዓሣ አንበሪ ሆድ ውስጥ አድሮ እንደ ወጣ ኹሉ፥ የደቂቀ አዳምን ሕማም ለመሸከም መጥቶ የተሰቃየው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷል፡፡ ስለዚኽ የነቢዩ ዮናስ እንዲኽ በዓሣ አንበሪ ሆድ ውስጥ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት መቆየት የጌታችንን ሞትና ትንሣኤ በጥምቀት ተካፋዮች ለሚኾኑ ኹሉ በርግብ የተመሰለውን መንፈስ ቅዱስ እንደሚቀበሉና ለዚያ የተዘጋጁ እንዲኾኑ ማዘጋጀት ማለትም ማወጅ ነበር ማለት ነው /ማቴ.፲፪፡፴፱-፵/፡፡
 ነቢዩ ዮናስ ነገዱ ከነገደ ይሳኮር ወገን ሲኾን አባቱ አማቴ እናቱም ሶና ይባላሉ፡፡ በአይሁድ ትውፊት እንደሚነገረው ደግሞ ዮናስ ነቢዩ ኤልያስ ከሞት ያስነሣው የሠራፕታዋ መበለት ልጅ ነው /፩ኛ ነገ.፲፰፡፲-፳፬/፡፡ 
 
 ነቢዩ ዮናስ በአገልግሎት የነበረበት ዘመን በዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት ሲኾን መኖርያውም በገሊላ በጋትሔፈር ከተማ ነበረ /፪ኛ ነገ.፲፬፡፳፭/፡፡
ነቢዩ ዮናስ የሰሜናዊው ክፍል ማለትም የእስራኤል ነቢይ ነበር፡፡ ሲያገለግል የነበረውም ከ፰፻፳፭ እስከ ፯፻፹፬ ቅ.ል.ክ. ገደማ  ነው፡፡ ከአሞጽም ጋር በዘመን ይገናኛሉ፡፡
 ከእስራኤል ውጪ ወደ አሦራውያን ዋና ከተማ ወደ ነነዌ ኼዶ እንዲያስተምር በዚያ ዘመን ከነበሩት ነቢያት ብቸኛው ነው፡፡ ከዚኽም የተነሣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ዮናስን “ነቢየ አሕዛብ” በማለት ይጠሩታል፡፡ 
ነነዌ
 ይኽች ጥንታዊት ከተማ በጤግሮስ ወንዝ ዳር ከዛሬዋ የሞሱል ከተማ በተቃራኒ ከባግዳድ ሰሜን ምዕራብ ፫፻፶ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ነበረች፡፡ የመሠረታትም ናምሩድ ይባላል /ዘፍ.፲፡፲፩/፡፡ በኋላም ሰናክሬም የአሦር መንግሥት ዋና ከተማ አደረጋት /፪ኛ ነገ.፲፱፡፴፮/፡፡
 የነነዌ ሕዝቦች መዠመሪያ ባቢሎናውያን ሲኾኑ /ዘፍ.፲፡፲፩/ አስታሮት (“የባሕር አምላክ”)የሚባል ጣዖትን ያመልኩ ነበር፡፡ ከተማይቱ በሃብቷና በውበቷ ትታወቅ ነበር፡፡ የአሦር ነገሥታትም በጦርነት የማረኳቸውን ሰዎች ያጉሩባት ስለ ነበረች “ባርያ” ተብለው የሚታሰቡ ሰዎች የሚበዙባት ነበረች፡፡ ነገሥታቱ በጨካኝነታቸው፣ የብዙ ንጹሐን ዜጐችን ደም በከንቱ በማፍሰስ፣ በምርኮኞች ሞትና ስቃይ ደስ በመሰኘት እንደ መዝናኛም በመቊጠር ይታወቃሉ፡፡ ነቢዩ ናሆም “የደም ከተማ” ብሎ የጠራትም ከዚኹ የተነሣ ነው /ናሆ.፫፡፩/፡፡ ነቢዩ ዮናስ ይኽችን ከተማ ነበር ወደ ንስሐ እንዲጠራ በልዑል እግዚአብሔር የተላከው፡፡
 ነቢዩ ሶፎንያስ እንደምትጠፋ በተናገረው ትንቢት መሠረት /ሶፎ.፪፡፲፫/ በ፮፻፲፪ ቅ.ል.ክ. ላይ በባቢሎናውያን ፈርሳለች፡፡
ትንቢተ ዮናስ
  ከብሉይ ኪዳን ኹለት መጻሕፍት ስለ አሕዛብ የሚናገሩ ናቸው፡፡ እነርሱም ትንቢተ አብድዩና ትንቢተ ዮናስ ናቸው፡፡ ትንቢተ አብድዩ ስለ ኤዶማውያን የሚናገር መጽሐፍ ሲኾን ትንቢተ ዮናስ ደግሞ ስለ ነነዌ ሰዎች ይናገራል፡፡ በትንቢተ አብድዩ አሮጌውና ደም አፍሳሹ ሰውነት (ኤዶማዊነት) ቀርቶ አዲሱና ጽዮናዊ (መንፈሳዊ) ሰው እንደሚመጣ በምሳሌ ይናገራል፡፡ በትንቢተ ዮናስ ደግሞ አሕዛብ አምነው በንስሐ እንደሚመለሱና እግዚአብሔርም በአሕዛብ መካከል ቤተ ክርስቲያን እንደሚያቋቁም በኅብረ አምሳል ያስረዳል፡፡
 አይሁዳውያን ብዙውን ጊዜ ነቢያትን ሲያሳድዱና ሲገድሉ እንደነበረ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚኽ ምድር በተመላለሰበት ወራት ተናግሯል /ማቴ.፭፡፲፪፣ ፳፫፡፴፩/፡፡ ከዚኹ በተቃራኒ የነነዌ ሰዎች ማለትም አሕዛብ ግን የነቢዩ ዮናስን የአንድ ቀን ትምህርት ተቀብለው እውነተኛ ንስሐ ገብተዋል፡፡ ይኽ ደግሞ አሕዛብ ክርስቶስን እንደሚቀበሉት፥ የገዛ ወገኖቹ የተባሉት አይሁድ ግን እንደሚክዱት የሚያስረዳ ነው፡፡ ነቢዩ ዮናስ ወደ ነነዌ ላለመኼድ የኮበለለበት ምክንያትም ይኼው ነበር፡፡ ጀሮም የተባለ የጥንታዊቷ የላቲን ቤተ ክርስቲያን ሊቅ ትንቢተ ዮናስን በተረጐመበት መጽሐፉ ይኽን ሲያብራራ፡- “ነቢዩ ዮናስ የአሕዛብ በንስሐ መመለስ የአይሁድ ጥፋትን እንደሚያመለክት በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ነበር፡፡ ስለዚኽ ወደ ነነዌ ላመኼድ የፈለገው አሕዛብን ጠልቶ አይደለም፤ የገዛ ወገኖቹ ጥፋት በትንቢት መነጽር አይቶ አልኼድም አለ እንጂ፡፡ ይኸውም ሊቀ ነቢያት ሙሴ በአንድ ስፍራ ላይ “ወዮ! እኒኽ ሕዝብ ታላቅ ኃጢአት ሠርተዋል፤ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፡፡ አኹን ይኽን ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍኽ እባክህ ደምስሰኝ” እንዳለው ነው /ዘጸ.፴፪፡፴፪/፡፡ ሙሴ እንዲኽ ስለጸለየ እስራኤላውያን ከጥፋት ድነዋል፤ ሙሴም ከሕይወት መጽሐፍ አልተደመሰሰም፡፡ … ዳግመኛም ንዋየ ኅሩይ ቅዱስ ጳውሎስ “ብዙ ኀዘን የማያቋርጥም ጭንቀት በልቤ አለብኝ ስል በክርስቶስ ኾኜ እውነትን እናገራለኹ፤ አልዋሽምም፤ ሕሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል፡፡ በሥጋ ዘመዶቼ ስለ ኾኑ ስለ ወንድሞቼ ከክርስቶስ ተለይቼ እኔ ራሴ የተረገምሁ እንድኾን እጸልይ ነበር” እንዳለው ነው /ሮሜ.፱፡፩-፪/፡፡… ነቢዩ ዮናስ እንግዲኽ ብቻውን ከነቢያት ተመርጦ ወደ እስራኤል ጠላቶች (ወደ አሦራውያን)፣ ጣዖትን ወደምታመልክና እግዚአብሔር ወደማታውቅ አገር ኼዶ እንዲሰብክ መመረጡ በእጅጉ አሳዝኖታል” ይላል፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም፡-  “የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚኽ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና” ብሏል /ማቴ.፲፪፡፵፩/፡፡
 አሕዛብ አሚነ ክርስቶስን እንደሚቀበሉና አይሁድ ከአሚነ ክርስቶስ እንደሚወጡ የተረጋገጠው በነነዌ ሰዎች መመለስ ብቻ አይደለም፡፡ የመርከበኞቹና የመርከቢቱ አለቃ ባሳዩት እምነት፣ ፈሪሐ እግዚአብሔርንና ለእግዚአብሔር ባቀረቡት መሥዋዕትም ጭምር እንጂ፡፡ ቅዱስ ጀሮም ቅድም በጠቀስነው መጽሐፉ ላይ እንዲኽ ሲል ያክላል፡- “አይሁድ ፍርድን በራሳቸው ላይ ጨመሩ፤ አሕዛብ ግን እምነትን ገንዘብ አደረጉ፡፡ የነነዌ ሰዎች በንስሐ ወደ አምላካቸው ተመለሱ፤ የእስራኤል ሰዎች ግን ንስሐ ባለ መግባታቸውና በጠማማ መንገዳቸው ስለጸኑ ጠፉ፡፡ እስራኤል መጻሕፍትን ተሸክመው ቀሩ፤ የነነዌ ሰዎች (አሕዛብ) ግን የመጻሕፍቱን ጌታ ተቀበሉት፡፡ እስራኤላውያን ነቢያት ነበሯቸው፤ የነነዌ ሰዎች (አሕዛብ) ግን የነቢያቱን ሐሳብና መልእክት ገንዘብ አደረጉ፡፡ የእስራኤል ሰዎች ፊደሉ ገደላቸው፤ መንፈስ ግን የነነዌን ሰዎች (አሕዛብን) አዳናቸው፡፡”
 በአጠቃላይ መጽሐፉን በአራት ክፍል ከፍለን ማየት እንችላለን፡-
1.     ምዕራፍ አንድን ስናነብ ነቢዩ ዮናስ ወደ ነነዌ ኼዶ እንዲያስተምር እንደታዘዘና ነቢዩም ወደ ኢዮጴ እንደ ኰበለለ፣ ከመከበኞች ጋር ተወዳጅቶ ከመርከብ ወጥቶ ሲቀመጥ ኃይለኛ ማዕበልና ሞገድ እንደተነሣ፣ ነቢዩ ዮናስ ወደ ማዕበሉ እስኪጣል ድረስም ማዕበሉ ጸጥ እንዳላለ እናነባለን፡፡ የባሕሩ ማዕበልና ሞገድ ጸጥ ያለው ነቢዩ ወደ ባሕሩ ሲጣል ነው፡፡ በኃጢአት ማዕበል የሚነዋወፀው የሕይወታችን ባሕርም ፀጥ ያለው ክብር ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእኛን ባሕርይ ባሕርይ አድርጐ ሲመጣ ነው፡፡
2.    ምዕራፍ ኹለትን ስናነብ ነቢዩ ዮናስ ወደ ባሕሩ ሲጣል ዓሣ አንበሪ እንደተቀበለውና በከርሡም ሦስት ሌሊትና ሦስት መዓልት እንደተሸከመው፤ ዮናስም በዚያ ኾኖ ያመሰግን እንደነበር እናነባለን፡፡ በዚኽም የዋኁ ዮናስ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእኛን ሞት ተሸክሞ ወደ መስቀል እንደወጣና ከዚያም ሞታችንን ይገድል ዘንድ ወደ መቃብር እንደወረደ የሚያስረዳ ነው፡፡ የዮናስ ምስጋናም የቤተ ክርስቲያን ምስጋና ነው፡፡
3.    ምዕራፍ ሦስትን ስናነብ ዓሣ አንበሪው ነቢዩ ዮናስን እንደተፋውና ወደ ነነዌ እንደኼደ የነነዌ ሰዎችም በዮናስ የንስሐ ጥሪ ከሊቅ እስከ ደቂቅ እንተመለሱ እናነባለን፡፡ እውነተኛው ዮናስ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጐ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ አሕዛብን ወደ መንግሥቱ እንደሚጠራና ብዙዎች እንደሚያምኑበት ያመለክታል፡፡
4.    ምዕራፍ አራትን ስናነብ ደግሞ ነነዌ እንደዳነችና እግዚአብሔርም ዮናስን በአስደናቂ ጥበቡ የውስጥ ሰላሙን እንደመለሰለት እናነባለን፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ደስ የተሰኘው ከልጆቹ ከሕዝብም (ከዮናስም) ከአሕዛብም (ከነነዌም) ዕርቅን ሲፈጽም ይቅርም ሲላቸው ነው፡፡    
ከትንቢተ ዮናስ ምን እንማራለን?
©     ትንቢተ ዮናስ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን ጥልቅና የማይለካ ፍቅር የተገለጠበት መጽሐፍ ነው፡፡ በመጽሐፉ እግዚአብሔር የእስራኤል ብቻ ሳይኾን የኹሉም አምላክ እንደኾነ ተገልጧል፡፡ የሕዝብም የአሕዛብም ሠራዒና መጋቢ እንደኾነና የኹሉም ድኅነትን እንደሚሻ ተመልክቷል፡፡
©     በመጽሐፉ የነቢዩን ድካም ተገልጧል፤ ይኸውም ነቢያት እንደኛ ሰዎች እንደነበሩና ድካም እንደነበረባቸው ግን ደግሞ እግዚአብሔር በመለኮታዊ ጥበቡ ድካማቸውን ለታላቅ ተልእኮ እንደተጠቀመበት ተጽፏል፡፡
©     እግዚአብሔር ከአእምሮ በላይ ጠቢብ እንደኾነ፣ ፈጣሪን አያውቁም ተብለው ለሚታሰቡ እንደ መርከበኞቹ ላሉ ሰዎች እንኳን የዕውቀት ብርሃንን እንደሚሰጣቸው ተገልጧል፡፡
©     እግዚአብሔር ከጥበቡና ከጥልቅ ፍቅሩ የተነሣ ልጆቹን ለመገሠፅና ከእርሱ ጋር እንዲታረቁ ለማድረግ ግዑዛን ፍጥረታት እንኳን እንደሚጠቀም ተገልጧል፡፡ ለምሳሌ፡- መርከቢቱ ያናውፅ ዘንድ የተላከው ጽኑ ንፋስ፣ ዮናስን የዋጠው ዓሣ አንበሪ፣ ዮናስ ዋዕየ ፀሐይ እንዳይመታው የበቀለችው ቅል፣ ቅሊቱን እንዲበላ በማግሥቱ የታዘዘው ትል እግዚአብሔር ከዮናስ ጋር ለመታረቅ የተጠቀመባቸው ፍጥረታት ናቸው፡፡ ዛሬስ እግዚአብሔር በምን ዓይነት መንገድ እየጠራን ይኾን?

  አነቃቅቶ ላስዠመረን አተጋግቶ ላስፈጸመን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባው አሜን!!!

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount