Friday, December 20, 2013

ነቢዩ ሚክያስ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፲፪ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
“ሚክያስ” ማለት “መኑ ከመ እግዚአብሔር - እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው?” ማለት ነው፡፡ ይኸውም ተልእኮውን የሚያስረዳ ነው፡፡ ምክንያቱም መጽሐፉን ስናነብ የሚከተሉትን እንገነዘባለንና፡-

©     እንደ ኃጢአት ያለ አስከፊና አውዳዊ ነገር የለም፤ ነገር ግን የእዚአብሔር ጸጋ ከዚኽ ይልቃል፡፡
©     በኃጢአት እንደተገዛች አገር ያለ ባርያ የለም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጃት ሰማያዊት ከተማ ትጠብቀናለች፡፡
©     ራሱንና አገሩን ያፈርሳልና ክፉ ንጉሥን የሚመስለው የለም፤ ነገር ግን አማናዊው ንጉሣችን እግዚአብሔር ነው፡፡
©     ወደ ሰማያዊው ስፍራ መርቶ የሚያደርስ እንደ ሐዲስ ኪዳኗ ቤተ ክርስቲያን ያለ ማንም የለም፡፡
©     እንደ እግዚአብሔር ያለ በደልን ይቅር የሚል፣ ቸርነቱና ምሕረቱ የተትረፈረፈ ማንም የለም፡፡
የነቢዩ ሚክያስ ትውልዱ ከነገደ ቢንያም ነው፡፡ አገሩ “ሞርሼት ጌት” እንደምትባልም ከመጽሐፉ መረዳት እንችላለን /ሚክ.፩፡፩፣፲፬/፡፡ ሞርሼት ጌትም ከኢየሩሳሌም ደቡባዊ አቅጣጫ ወደ ፳ ማይል ያኽል ርቀት ላይ የነበረች ቦታ ናት፡፡
 ነቢዩ ሚክያስ በሚያገለግልበት ወራት ነቢዩ ኢሳይያስ፣ ነቢዩ ሆሴዕና ነቢዩ አሞጽም ያገለግሉ ነበር፡፡
በነቢዩ ሚክያስ ዙርያ የነበረው ነባራዊ ኹኔታ
 ነቢዩ ሚክያስ በሚያገለግልበት ወራት (ከ፯፴፭-፮፹፰ ቅ.ል.ክ.) የነበሩት የይሁዳ ነገሥታት ኢዮአታም፣ አካዝና ሕዝቅያስ ናቸው /ሚክ.፩፡፩/፡፡ ከእናንተ መካከል፡- “ለመኾኑ ነቢያቱ በዘመኑ የነበሩትን የነገሥታቱን ስም የሚጠቅሱት ለምንድነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲኽ ብለን እንመልስለታለን፡- “እነዚኽን ነገሥታት ብንመክራቸው፣ ብናስተምራቸው አንሰማም ብለው ጠፉ (በጠላት ተማረኩ)” ለማለት ነው፡፡
  ነቢዩ ሚክያስ የነበረበት ዘመን እንግዲኽ በጣም ከባድ ጊዜ ነበር፡፡ እግዚአብሔር የይሁዳንና የያዕቆብን በደል ለማየት ዓይኑን ያነሣበት ጊዜ ነበር /ሚክ.፫፡፰/፡፡ በትንቢት መነጽር እየተመራ ነቢዩ ሚክያስ የይሁዳና የያዕቆብ መንግሥታት ውድቀት ተመልክቷል፡፡ በእነዚኽ መንግሥታት ውስጥ በደል ነግሧል፡፡ የውጭ ጠላቶችም ከደጅ ላይ ናቸው፡፡
 ነቢዩ ሚክያስ የኹለቱም ነገሥታት፡ የይሁዳና የያዕቆብ በደላቸው እንደምን ጣርያ እንደ ነካ ይመለከት ነበር፡፡ ባለጸጐቹ ድኻውን ይበድሉታል፤ የድኻው ጩኸትም መንበረ ጸባዖትን ያንኳኳል፡፡ ቤተ መንግሥቱ፣ ቤተ ክህነቱና ተራው ሕዝብ ነቢዩ ኢሳይያስ እንደተናገረው “በበደል የተሞላ” ነበር /ኢሳ.፩፡፬-፮/፡፡ አለቆቹ ከተራው ሕዝብ ጋር ወደ ቤተ እግዚአብሔር ቢመጡም የአምልኮ መልክ ነበራቸው እንጂ ከልባቸው ተጸጽተው አልነበረም /ሚክ.፮፡፯-፰/፡፡
 ነቢዩ ሚክያስ በጊዜው የነበሩትን ኃጢአቶች ሲዘረዝራቸው እንዲኽ ይገልጣቸዋል፡- አምልኮተ ጣዖት፣ በደልን ለመፈጸም ገና በመኝታ ሳሉ ዕቅድ ማውጣት፣ የድኻውን እርሻ መመኘት፣ የድኻውን ቤት መቀማት፣ ስስት፣ ግፍ፣ ንጹሐንን ከገዛ ቤታቸው ማሳደድ፣ የሐሰት ነቢያትን ማበረታታት፣ መልካም ነገርን መጥላትና ክፉውን መውደድ፣ ፍትሕንና እውነትን ማጣመም፣ ካህናቱ በዋጋ ማስተማራቸው (ከእኛ ዘመን ሰባክያን ጋር ያነጻጽሩ)፣ ጉቦ (ከእኛ ዘመን አለቆች ጋር ያነጻጽሩ)፣ ውሸተኛ መስፈሪያ (ከእኛ ዘመን ነጋዴዎች ጋር ያነጻጽሩ)፣ …፡፡
 በነቢዩ ዘመን የነበረውን ፖለቲካዊ ኹኔታ ስንመለከትም ከነቢዩ ኢሳይያስ ኹኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ በነቢዩ ሚክያስ ዘመን የነበሩት የአሦር ነገሥታት ቴልጌልቴልፌሶር ሦስተኛ፣ ስልምናሶር እና ሰናክሬም ይባላሉ፡፡ ሰናክሬም ወታደሮቹን ወደ ደቡባዊና ምዕራባዊ የይሁዳ መንደሮች ልኮ ነበር፡፡ ለብዙ ጊዜም ሳይማርካቸው ሲገዛቸው ቆይቷል፡፡
 ከግብጽና ከኢየሩሳሌም ውጪ መካከለኛውን ምሥራቅ በአሦር መንግሥት ስር ነበር፡፡ ነገር ግን ይኸ ኹሉ ግዛት የአሦር ሠራዊት አልነበረበትም፤ ሕዝቡ ዝም ብሎ ለአሦራውያን ነገሥታት ግብር ይከፍል ነበር እንጂ፡፡ በአሦር አዲስ ንጉሥ በተሾመ ቁጥር ግብርን ከሚከፍሉ ከእነዚኽ ግዛቶች በርካታ ግጭቶች ይገጥማቸው የነበረውን ከዚኹ የተነሣ ነው፡፡ አዲስ የሚሾመው ንጉሥም “ግብርን አንከፍልም” ከሚሉት ከእነዚኽ ግዛቶች ጋር ጦርነትን ማድረግ ያዘወትሩ የነበረው ለዚኹ ነው፡፡ ከእነዚኽ ኹሉ ጦርነቶች የከፋውም ከግብጽ ጋር የተደረገው ጦርነት ነበር፡፡
ይኽ ኹኔታም ከግብጽ ውጪ ለነበሩ አገሮች ታላቅ አለመረጋጋትን ያስከተለ ነበር፡፡ ምክንያቱም አንደኛ አገራቸው በአሦራውያን እንዲወረር ይኾናል፤ ኹለተኛ ሕዝባቸው በምርኮ እንዲፈልስ ይኾናል፡፡ ነገሥታቱ፣ የሃይማኖት መሪዎቹና ባለጸጐቹ ግን ገንዘባቸውን ተገን በማድረግ ከዚኽ ባርነት ያመልጡ ነበር (ግብርን መክፈል ስለሚችሉ ማለት ነው)፡፡
 የይሁዳ መንግሥት በኃያልነቱ ጣርያ ደርሶ የነበረው በንጉሡ በዖዝያን ጊዜ ነበር /፪ኛ ዜና ፳፮/፡፡ ዖዝያን በትዕቢቱ ባደረገው ኃጢአት በለምጽ ከተመታ በኋላ ወደ ንግሥና የመጣውም ልጁ ኢዮአታም ነበር፡፡ የኢዮአታም ዘመነ ንግሥናም በድል አድራጊነቱ፣ ሕንፃዎችን በመሥራትና የመከላከያ ሠራዊቱን በማደራጀት ይታወቃል /፪ኛ ዜና ፳፯/፡፡ ኢዮአታምን የተካው ደግሞ አካዝ ነበር፡፡ አካዝ ወደ ንግሥና ሲመጣም የአሦር መንግሥት በዓለም ላይ በጣም ገንኖ የወጣበት ሰዓት ላይ ነበር፡፡ ቴልጌልቴልፌሶር በ፯፻፴፪ ቅ.ል.ክ. ላይ ሶርያን ድል አድርጓታል፡፡ ከ፲ ዓመት በኋላ ሰማርያን ወርሮ የእርሱ ምርኮኛ ስላደረጋትም የይሁዳ መንግሥት (የሚረዳኝ የለም በማለት) በራስ መተማመንን አጣ፡፡ ይኽ የበለጠ ጐልቶ የወጣው ደግሞ በንጉሥ አካዝ ጊዜ ነበር፡፡ ከአካዝ በኋላ ወደ ንግሥና የመጣው ንጉሥ ሕዝቅያስ ነበር፡፡ ሕዝቅያስ ብዙ ነገሮችን በማደስ ይታወቃል /፪ኛ ዜና ፳፰/፡፡ ሕዝቅያስ ከአሦር ጋር የነበረውን ግንኝነት አቋርጧል፡፡ ይሁዳን ከአምልኮተ ጣዖት ለማላቀቅ ልቡ ተነሣስቷል፡፡ ቤተ መቅደሱን ለማንጻትና ለማደስም ሽቷል፡፡ ይኽ የተሐድሶ መነሣሣት የተፈጠረው ደግሞ ነቢዩ ሚክያስ ባስተማረው ትምህርት ነበር /ኤር. ፳፮፡፲፰/፡፡
ትንቢተ ሚክያስ
የነቢዩ ሚክያስ የትንቢት መጽሐፍ በአራቱም ወንጌላውያን መጠቀሱ በጥንታውያን የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ዘንድ ልዩ ስፍራ እንዲኖረው የራሱን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ እንደ ሊቃውንቱ አባባል፥ ትንቢተ ሚክያስ፡-
Ø በብዙ ኅበረ አምሳል የተሞላ ነው፡፡ ለምሳሌ ስለ ጽዮን ተራራ መናገሩ የቤተ ክርስቲያን /ዕብ.፲፪፡፳፪/፤ አንድም የአዲሲቱ አየሩሳሌም መምጣትን /ራዕ.፳፩፡፩/ የሚያስረዳ ስለኾነ ለእስራኤላውያን ተስፋን የሚያሰንቅ ነበር፡፡
Ø የጥምቀትን ምሳሌ በዚኽ መጽሐፍ ስለሚገኝ ግርዘት እንደሚያልፍ ያሳያል /ሚክ.፯፡፲፱/፡፡
Ø ምንም እንኳን መጽሐፉ በስፋት የእስራኤልንና የይሁዳን መፍረስ የሚናገር ቢኾንም ከዚያ በኋላ ሊመጣ ያለውን የክብር ጊዜም ተንብዮአል፡፡ ይኸውም በመሲሑ የሚከናወን ነው /ሚክ.፬፡፩-፯/፡፡
Ø በዚኹ መጽሐፍ የምናገኘውና በአበው ልዩ ስፍራ እንዲሰጠው ካደረገው ሌላ፥ አገር ኹሉ በኃጢአት ቢበላሽም እግዚአብሔር ለአንድ ሰው ስንኳ ቢኾን ቸርነቱን እንደሚያደርግ መግለጡ ነው፡፡ ይኸውም ነቢዩ “ቅሬታ” ብሎ ገልጦታል /ሚክ.፪፡፲፪/፡፡ እግዚአብሔር በየትኛውም ጊዜ (በጣም አስከፊ ጊዜ ነው በምንለውም ጭምር) ለቅሬታዎቹ ያዝናል፤ ይራራልም፡፡ ኖኅንና ሎጥን ማስታወሱ ይበቃል፡፡
Ø ከዘለዓለም አንሥቶ የነበረውና ለድኅነተ ሰብእ ሥጋ ለብሶ የሚመጣው መሲሕ የት እንደሚወለድ በግልጽ የተናገረው ብቸኛው ነቢይ ቢኖር ነቢዩ ሚክያስ ነው /ሚክ.፭፡፪/፤ ረበናተ አይሁድም ይኽን መስክረዋል /ማቴ.፪፡፩-፮/፡፡ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምም በሐሙስ ውዳሴ ማርያም ላይ ይኽን ሲያደንቅ፡- “ወዮ! ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ከአብ ከባሕርይ አባቱ ከመንፈስ ቅዱስ ከባሕርይ ሕይወቱ ጋራ ክብር ይግባውና በአንድ በመንፈስ ቅዱስ ተገልጾላቸው የክርስቶስን ነገር የተናገሩ ሚክያስና ዳዊት የተናገሩት ነገር ምን ይረቅ? ምን ይጠልቅ? አንድም ሚክያስና ዳዊት ለተናገሩት ነገር አንክሮ ይገባል” ብሏል፡፡
Ø ይኽ መጽሐፍ እግዚአብሔር ኃጢአትን እንዴት እንደሚጠላ፥ በአንጻሩ ደግሞ ኃጢአተኞችን እንዴት እንደሚወዳቸው በግልጽ የሚያሳይ መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር ቅዱስ እንደመኾኑ ኃጢአትን ይጸየፋል፤ አባት እንደመኾኑ ደግሞ ልጆቹን ይወዳል፡፡ ብርሃን ከጨለማ ጋር ኅብረት እንደሌለው ኹሉ እግዚአብሔርም ከኃጢአት ጋር ኅብረት የለውም፡፡
Ø ነቢዩ ሚክያስ ምንም ሳይፈራና ሳያፍር የይሁዳንና የእስራኤልን ኃጢአት ግልጽ አድርጐ ነግሯቸዋል፡፡ ከፍቅሩ የተነሣም ለዚኽ ኹሉ ኃጢአታቸው ፈውሱ ንስሐና ንስሐ ብቻ መኾኑን ነግሯቸዋል፡፡ በምሕረትና በትሕትና ኾነው ወደ እግዚአብሔር እንደሚለሱም ጋብዟቸዋል /፮፡፰/፡፡
Ø ይኽ መጽሐፍ ከገለጣቸው ዋና ዋና ቁምነገሮች አንዱ መናፍቃን የድኾችን መበደል፣ የፍትሕ መጓደል ምንም ባይገዳቸውም እግዚአብሔር ግን ሕዝቡን መቼም መች እንደማይተዋቸው ነው፡፡
የትንቢተ ሚክያስ መጽሐፍ ዋና ዋና ዓላማዎች እንደሚከተለው ማስቀመጥ እንችላለን፡-
©     በኃጢአት ምክንያት ከሚመጣው ሞት ማምለጫ መንገዱ ንስሐ ብቻ መኾኑን መግለጥ፤
©     እግዚአብሔር፥ ሕዝቡን በሚያሰጨንቁ ሰዎች ላይ እንደምን ያለ ፍርድ እንደሚፈርድ ማሳየት፤
©     ድኾችን የሚበድሉ ባለጸጐችን መገሰጽ፤
©     ለሚሰሙት በልቡናቸው ከሚያስጨንቋቸው ሰዎች እንዲኹም ከሚማርኳቸው ጠላቶች ተሻግረው ልትመጣ ያለችውን የመሲሑን ጊዜ እንዲያዩ ማድረግ፤
©     ነቢዩ ሚክያስ ምንም እንኳን ከአንድ ምዕተ ዓመት ከግማሽ በኋላ ኢየሩሳሌም እንደምትማረክ ቢናገርም፣ ዳግመኛም ቅጥሮቿ እንደሚሠሩ ተናግሯል /፯፡፲፩/፡፡
 አስቀድመን ለመግለጽ እንደሞከርነው ነቢዩ ሚክያስና ነቢዩ ኢሳይያስ የዘመን ጓደኛሞች ናቸው፡፡ ኢሳይያስ በኢየሩሳሌም ሲያስተምር ሚክያስ ደግሞ በምዕራባዊው ይሁዳ ያስተምርና ትንቢት ይናገር ነበር፡፡ ስለ መሲሑ የተናገሩት ትንቢት ያስተማሩት ትምህርት ብዙውን ጊዜ ይመሳሰላል፡፡ በትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ ፪ ከቁጥር ፩ እስከ ፬ ያለውን ኃይለ ቃልና በትንቢተ ሚክያስ ምዕራፍ ፬ ከቁጥር ፩ እስከ ፭ ያለውን ስናስተያየው አንድ ነው፡፡ በሌላ በኵል ነቢዩ ኢሳይያስ “ድንግል ትፀንሳለች …” ብሎ ደረቅ ትንቢትን ሲናገር /ኢሳ.፯፡፲፬/ ነቢዩ ሚክያስም “አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ! አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትኾኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ዠምሮ ከዘለዓለም የኾነ በእስራኤልም ገዥ የሚኾን ይወጣልኛል” በማለት ደረቅ ትንቢት ተናግሯል /ሚክ.፭፡፩-፭/፡፡
 መጽሐፉን እንደሚከተለው መክፈል እንችላለን፡-
1.     የሰማርያና የኢየሩሳሌም መፍረስ /ምዕ.፩-፫/፤
2.    የእግዚአብሔር መንግሥት መመሥረት ፤ ይኸውም ክብር ይግባውና በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚኾን መተንበይ /ምዕ.፬-፭/፡፡
3.    እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ስላለው ክርክር /ምዕ.፮/፤
4.    እግዚአብሔር ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ ከሰው የሚፈልገው ለተርእዮ ሳይኾን ከልብ የኾነ አምልኮ እንደሚሻ፣ ጠላት ቢጥላቸውም እግዚአብሔር እንደሚያነሣቸው ተስፋ መስጠት /ምዕ.፯/፡፡
 መጽሐፉ የሚያልቀው እጅግ ግሩም በኾነ ጸሎት ነው፡፡ ጸሎቱም እንዲኽ ይላል፡- “ላድን ልራዳ ባልኽ ጊዜ የዓለሙን ኃጢአት የሚያስተሠርይ እንዳንተ ያለ ፈጣሪ ማን ነው? ከሞት የቀሩት በኃጢአት የተዳደፉ የወገኖቹንም ኃጢአት ይቅር የሚል እንዳንተ ያለ ማን ነው? ለአምላክነቱ ቀንቶ የሚመጣውን መዓቱን አያጸናም፤ ፈቃዴ ምሕረት ይቅር ባይ ነውና፡፡ ከመዓት ወደ ምሕረት ይመልሰናል፡፡ ይቅርም ይለናል” /ሚክ.፯፡፲፰-፲፱/፡፡  
…ተመስጦ…
 ቅዱስ እግዚአብሔር ሆይ! ነቢዩ ሚክያስ የኃጢአትን አስከፊነትና መራራነት በተናገረ ጊዜ ነፍሳችን ራደች፤ ተንቀጠቀጠችም፡፡ ውስጣችን በሐፍረት ተዋጠ፤ ተዋረድንም፡፡ ኃጢአት የጸጋ ልብሳችንን ገፍፎ ዕራቆታችንን አስቀረን፡፡ የሕይወትን ጣዕም አሳጣን፤ ባዶነትም ተሰማን፡፡ ውስጣችን ባርያ ኾነ፤ ምርኮም ተማረክን፡፡ ብርታታችን ከእኛ ተወሰደ፤ እጅግም ደካማ ኾንን፡፡
 ቸርነትኽና ምሕረትኽ ግን ረዳን፤ ከጠፋንበት ፈለገን፡፡ ይቅርታኽ የኃጢአታችንን ጭጋግ አስወገደው፤ ብሩሃን እንድንኾንም አደረገን፡፡ አጥተነው የነበረውን ብርታት ተመለሰልን፤ ብርቱዎች ኾንን፡፡ ከኃጢአት ቀንበር ተላቅቀን ከእጅኽ እንድናርፍ ኾንን፡፡ የተገፈፍነውን ጸጋ መለስክልን፤ አለበስከንም፡፡ ይኽን የክብር ሸማ ተጐናጽፈንም ከሰማይ ሠራዊት ጋር እንድናመሰግንኽ አደረግከን፡፡
 ኃጢአታችን ልቡናችንን ባሳወረው ጊዜ፣ ፈቃዳችንን ድል ባደረገው ጊዜ መሪ እንደሌለው ሠረገላ ኾንን፡፡ አንተ ግን መሪያችን ትኾን ዘንድ ወደ ቤተ ልሔም መጣኽ፡፡ አርያማዊው መሪያችን ሆይ! ፍቅርኽ እንደምን ይረቃል? እንደምን ይመጥቃል?
 ቅዱስ አባት ሆይ! ነቢዩ ሚክያስ የሰማርያንና የኢየሩሳሌምን ኃጢአት እየተመለከተ ያለቅስ ነበር፡፡ ከሐዘኑ የተነሣም ዕራቆቱና በባዶ እግሩ በአገሩ ዞረ፡፡ አንተ ግን ታጽናናው ዘንድ ሰማያዊቱን ኢየሩሳሌም አሳየኸው፡፡ አዲሱቱ ሰማይንና አዲሲቱን ምድር ገለጥኽለት፡፡ መለኮታዊው ፍቅርኽ ግን ማን ሊናገረው ይችላል?
 ቅዱስ እግዚአብሔር ሆይ! ዛሬም ቢኾን የሰማርያና የኢየሩሳሌም ዕጣ በእኛ ደርሶአልና በዚኽ ፍቅርኽ ተመልከተን! ከአምልኮተ ጣዖት፣ በደልን ለመፈጸም ገና በመኝታ ሳለን ዕቅድ ከማውጣት፣ የድኻውን እርሻ ከመመኘት፣ የድኻውን ቤት ከመቀማት፣ ከስስት፣ ግፍን ከመሥራት፣ ንጹሐንን ከገዛ ቤታቸው ከማሳደድ፣ የሐሰት ነቢያትን ከማበረታታት፣ መልካም ነገርን ከመጥላትና ክፉውን ከመውደድ፣ ፍትሕንና እውነትን ከማጣመም፣ “በከንቱ ከተቀበላችሁ በከንቱ ስጡ” የሚለውን ቃልኽን ረስተን በዋጋ ከማስተማር፣ ጉቦ ከመቀበል፣ በውሸተኛ መስፈሪያ ከመነገድ ጠብቀን፡፡ አምላክ ሆይ! ይቅር በለን! ራራልን! ከምርኮ መልሰን! “የዓለሙን ኃጢአት የሚያስተሠርይ እንዳንተ ያለ ፈጣሪ ማን ነው? ከሞት የቀሩት በኃጢአት የተዳደፉ የወገኖቹንም ኃጢአት ይቅር የሚል እንዳንተ ያለ ማን ነው?” ብለን የድል ዝማሬ እንድንዘምርም አድርገን፡፡ አሜን!!!
ዋቢ ድርሳናት፡- የትንቢተ ሚክያስ አንድምታ፣

                   A Patristic Commentary on The Book Micah By Fr. Tadros Malaty

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount