(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፮ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
“ሆሴዕ” ማለት ከ፲፪ቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ ሲኾን የስሙም ትርጓሜ “መድኃኒት”
ማለት ነው፡፡ መድኃኒት መባሉም እንደ ኢያሱ ወልደ ነዌ ባጭር ታጥቆ፥ ጋሻ ነጥቆ፥ ዘገር ነቅንቆ አማሌቃውያንን አጥፍቶ እስራኤልን
አድኖ፥ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋዉን ቆርሶ፥ ደሙን አፍስሶ፥ ፲፫ቱን ሕማማተ መስቀል ታግሦ፥ አጋንንትን ድል ነስቶ ነፍሳትን
አድኖ አይደለም፤ አባት እናቱ በትንቢቱ በትምህርቱ እንዲያድን አውቀው “ሆሴዕ - መድኃኒት” ብለዉታል እንጂ፡፡ ስለዚኽ የስሙ ትርጓሜ
ተልእኮውን የሚያስረዳ ነው ማለት ነው፡፡
ነቢዩ ሆሴዕ
እስራኤላውያን (ሰማርያ - ሰሜናዊው ክፍል) በ፯፻፳፪ ቅ.ል.ክ. በአሦራውያን ወደ ምርኮ ከመኼዳቸው በፊት፥ ዳግማዊ ኢዮርብዓም በሰማርያ ነግሦ በነበረበት ዘመን በእስራኤል (በሰሜናዊው)
መንግሥት ተነሥቶ የነበረ ነቢይ ነው፡፡ ከመጽሐፉ መረዳት እንደምንችለውም ነቢዩ ሆሴዕ በሚያገለግልበት ወራት ነቢዩ ኢሳይያስ፣ ነቢዩ
ሚክያስና ነቢዩ አሞጽም ያገለግሉ ነበር /ሆሴ.፩፡፩/፡፡
ነቢዩ ሆሴዕ
ባለትዳር ነው፡፡ ሚስቱም “ጎሜር” እንደምትባል ተጠቅሷል /ሆሴ.፩፡፫/፡፡ ከመጽሐፉ ማንበብ እንደምንችል “ጎሜር” ጋለሞታ ነበረች፡፡
መተርጕማን እንደሚያስተምሩት
ግን፡- “የጎሜር
ጋለሞታ ተብላ መጠራት በኹላችንም ልቡና እንደሚመጣ የወንድና የሴት ዓይነት ግልሙትና አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ያላዘዘውን ሥራ መሥራትም
ዝሙት ነውና ጎሜር ጣዖትን ታመልክ ስለነበረ ነው” ይላሉ፡፡ እግዚአብሔር ነቢዩን ይኽቺ ሴት እንዲያገባ ያደረገውም ሕዝቡ ምን ያኽል
ከእግዚአብሔር ርቆ እንደነበርና ከጣዖታት ጋር እንደምን ያለ አንድነት ፈጥረው እንደነበሩ በምሳሌ ሲናገራቸው ነው፡፡
በደንብ
ካስተዋልነው ሆሴዕ ማለት መድኃኒት ነው፡፡ ጎሜር ደግሞ ጋለሞታ ናት፡፡ ይኽ መድኃኒት የተባለ ሆሴዕ ይኽቺን ሴት አግብቷታል፡፡
በጣም ይወዳት እንደነበረም ተገልጧል፡፡ በዚኽም እውነተኛው መድኅን (ኢየሱስ) የገዛ መንገዳችንን ተከትለን በጠፋንበት ወራት እኛን
ከመውደዱ የተነሣ እንደፈለገንና ከእኛ ጋርም እንደተዋሐደ ምስጢርን የሚያስረዳ ነው /ሆሴ.፫፡፩/፡፡ በአጭሩ ይኽቺ ሴት (ጎሜር)
የምእመናን ምሳሌ ናት፡፡
ነቢዩ ሆሴዕ
ከባለቤቱ ከጎሜር ሦስት ልጆችን ወልዷል፡፡ የመዠመሪያው ልጅ ወንድ ሲኾን “አይዝራኤል” ይባላል፤ ይኸውም “የናቡቴን ደም ተበቅዬ
ኢይስራኤል በተባሉበት ቦታ አጠፋቸዋለኹ” ለማለት ነው፡፡ ኹለተኛይቱ
ሴት ስትኾን “ሎሩሃማ - ምሕረት ዘአልባ - ምሕረት የሌላት” ትባላለች፤ ይኸውም “የእስራኤልን ወገኖች ዳግመኛ ይቅር አልላቸውምና”
ለማለት ነው፡፡ ሦስተኛው ልጅ ወንድ ሲኾን “ሎዓሚ - ኢሕዝብ - ሕዝቤ ያልኾነ” ይባላል፤ ይኸውም “እናንተ ወገኖቼ አይደላችሁምና
እኔም አምላካችሁ አይደለኹም” ለማለት ነው፡፡ ይኼ ኹሉ መባሉ ምንም እንኳን አባታቸው “ሆሴዕ - መድኃኒት” ቢኾንም ሕዝቡ እስካልተመለሱ
ድረስ እንደሚጠፉ፣ ምሕረት እንደማያገኙ፣ ሕዝቡ እንደማይባሉ እርሱም አምላካቸው እንደማይባል ሲገልጽ ነው፡፡ ነፍሳችን እንዲኽ ወደ
መድኃኒቷ ካልተመለሰች እንዲኽ መባሏ የማይቀር ነው፡፡ እንዲኽ ከመባልስ እግዚአብሔር ይሰውረን፡፡
ነቢዩ ሆሴዕ
በራሱ መጽሐፍ እንደነገረን በዘመኑ የነበሩት ነገሥታት ስድስት ናቸው፡፡ በይሁዳ በኵል የነበሩት ዖዝያን፣ ኢዮአታም፣ አካዝና ሕዝቅያስ
ሲኾኑ፤ በእስራኤል በኵል የነበሩት ደግሞ ዮአስና ኢዮርብዓም ናቸው /ሆሴ.፩፡፩/፡፡ ስለዚኽ የነቢዩ የአገልግሎት ዘመን ከ፯፻፹፯
አንሥቶ እስከ ፮፻፺፯ ቅ.ል.ክ. ድረስ ገደማ ነው ማለት ነው፡፡
በዚኽ ስም
የሚጠሩ ሌሎች ሦስት ሰዎች አሉ፡፡ ከእነርሱ አንዱ ከሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ነገሥታት የመጨረሻውና በእርሱ ዘመነ መንግሥት
ሰማርያ የወደቀችው ንጉሥ ነው፡፡
ነቢዩ ሆሴዕ
የነበረበት ነባራዊ ኹኔታ
ነቢዩ ሆሴዕ በነበረበት ወራት ሕዝቡ በምን ዓይነት ግብረ ገብነታዊና ሃይማኖታዊ
ውድቀት እንደነበሩ ከመጽሐፉ በግልጽ ማንበብ እንችላለን፡፡ ትንቢተ ሆሴዕን ስናነብ በሕዝቡ ዘንድ መገዳደል፣ ዝሙት፣ ጣዖትን ማምለክ፣
ትዕቢት፣ … ተንሰራፍቶ እንደነበር እንገነዘባለን፡፡ በየትኛውም ዓይነት ደረጃ ያለ ሰው እግዚአብሔርን የረሳበት ዘመን ነበር /ሆሴ.፲፫፡፮/፡፡
ለዚኽም ነው ነቢዩ ሆሴዕ፡- “ምድሪቱ ከእግዚአብሔር ርቃ ታላቅ ግልሙትና ታደርጋለች” /ሆሴ.፩፡፪/፤ “እውነትና ምሕረት እግዚአብሔርንም
ማወቅ በምድሪቱ የለም” /ሆሴ.፬፡፩/፤ “ስለዚኽ ምድሪቱ ታለቅሳለች” /ሆሴ.፬፡፫/ እያለ የተናገረው፡፡ ሕዝቡ እውቀትን ከማጣት
የተነሣ ጠፍቷል /ሆሴ.፬፡፩፣፮/፡፡
ከላይ
ለመግለጽ እንደተሞከረው ነቢዩ ሆሴዕ በሚያገለግልበት ዘመን የነበሩት ነገሥታት ፮ ናቸው፡፡ ከዚኽም በተጨማሪ፡- “ንጉሥ የለንም”
ብሎ እንደተናገረው ዙፋኑ ለ፲፩ ዓመታት ያኽል ባዶ ነበር /ሆሴ.፲፡፫/፡፡ በዙርያም የአሦር መንግሥት ተደጋጋሚ ጥቃትን ሲያደርስ
ነበር፡፡ ነቢዩ ተግሳጹን ጠንከር ያደረገውም ከዚኽ ነባራዊ ኹኔታ የተነሣ ነው፡፡
ትንቢተ ሆሴዕ
ትንቢተ
ሆሴዕ ፲፬ ምዕራፍን የያዘ መጽሐፍ ሲኾን እጅግ ግሩምና አኹን ካለንበት ነባራዊ ኹኔታ ጋር በጣም የሚመሳሰል ነው፡፡ ይኸውም እንደሚከተለው
በአጭር በአጭሩ ማየት እንችላለን፡-
©
የዚኽ መጽሐፍ የመዠመሪያው ዓላማ እግዚአብሔር
ከሕዝቡ ጋር ያለውን አንድነት የሚገልጥ ነው፡፡ ምንም እንኳን እስራኤል (የሰው ልጅ) ጋለሞታ ብትኾንም እግዚአብሔር ይወዳታል፡፡
እጮኛው እንትኾን፣ ለዘለዓለም በሰማያዊው ጫጉላ ከእርሱ ጋር ተዋሕዳ እንድትኖር፣ ጽድቅና እውነት የሚባሉ ልጆችም እንድትወልድለት
ይፈልጋል /ሆሴ.፪፡፳፩/፡፡ ለብቻው እንደሚቀመጥ የምድረ በዳ አህያ ወደ አሦር መውጣቷን እንድትተው፣ ለአሕዛብ የምትሰጠውን እጅ
መንሻ ትታ እንድትመለስ ይሻል /ሆሴ.፰፡፱/፡፡ ወዳጄ ሆይ! እኔና አንተም ወደዚኽ አንድነት እየተጠራን ነውና ከጋለሞታነታችን ተመልሰን
እጮኛችንን ለመቀበል የሰርግ ልብሳችንን እናዘጋጅ /ማቴ.፳፭/፡፡
©
የዚኽ መጽሐፍ ሌላው ዓላማ እስራኤል
ምን ያኽል በደዌ እንደተያዘች መግለጥና /ሆሴ.፭፡፲፫/ ብቸኛው መድኃኒቷ እግዚአብሔር መኾኑን መግለጥ ነው /ሆሴ.፲፬፡፬/፡፡
በሌላ አገላለጽ የያዛት ደዌ ምን ያኽል አደገኛ እንደኾነ አውቃ ዘይትን አፍስሶ ወደሚያድናት ሐኪሟ እንድትመለስ ማድረግ ነው፡፡
በመጽሐፉ እንደተገለጸ ለያዛት ደዌ ምንጩ ብዙ ነው፡፡ ጥቂቶቹን ለመግለጽ ያኽልም፡- ከእግዚአብሔር ርቃ ምድራዊ ነገር ላይ ብቻ
መባከኗ /ሆሴ.፩፡፪/፤ እውቀትን ከማጣቷ የተነሣ /ሆሴ.፬፡፮/፤ ትዕቢቷ /ሆሴ.፭፡፭/፤ በእግዚአብሔርና በዲያብሎስ፣ በአምልኮተ
እግዚአብሔርና በአምልኮተ ጣዖት፣ በመልካምና በክፉ ነገር መካከል ያለውን ድምበር ማፍረሷ /ሆሴ.፭፡፲/፤ እግዚአብሔር ክፋቷን እንደሚያስበው
እርሷ አለማሰቧ /ሆሴ.፯፡፪/፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትን እየፈለገች ግን ደግሞ ከእርሱ ጋር አንድነትን መፍጠር መጥላቷ /ሆሴ.፯፡፲፬/፤
ከምድር ፍሬ ብቻ ደስታን አገኛለኹ ስትል እውነተኛውን ደስታ ማጣቷ /ሆሴ.፱፡፲፮/፤ ወእለ ዘተርፈ መግለጽ እንችላለን፡፡ ተወዳጆች
ሆይ! እኛስ በዚኽ ቃል ስንመዘን ምን ያኽል በደዌ ተይዘን ይኾን? ታድያ መቼ ነው የምንታከመው?
©
እስራኤል ለእግዚአብሔር የተለየች ነበረች፡፡ የተቀደሰች ነበረች፡፡ እርሷ ግን አምላኳን ትታ ፊቷን
ወደ በአል አዙራለች፡፡ ለጣዖት የተሠዋውን መሥዋዕት መመገብ ዠምራለች፡፡ ደግነትን ጥላለች፡፡ ከእግዚአብሔር ውጪ ለራሷ ነገሥታትን
ሾማለች፡፡ ነፋስን ዘርታ ዐውሎ ነፋስን አጭዳለች፡፡ በአሕዛብ መካከል እንደ ረከሰ ዕቃ ኾናለች፡፡ ፈጣሪዋን ረስታለች፡፡ የእግዚአብሔር
ጉባዔ መኾኗ ቀርቶ የዲያብሎስ መፈንጫ ኾናለች፡፡ በእግዚአብሔር ክንድ መደገፍን ትታ በአሦርና በግብጽ ትተማመን ዠምራለች /ሆሴ.፰/፡፡
ከዚኽ ኹሉ እንድትወጣና ወደ ፈጣሪዋ እንድትመለስም እግዚአብሔር ይጠራታል፡፡ የትንቢተ ሆሴዕ ሌላውና ዋናው ዓላማም እስራኤል ከዚኽ ድርጊቷ ተመልሳ በንጽሕናና በቅድስና ከሙሽራዋ ከእግዚአብሔር
ጋር በፍቅር እንድትኖር መጋበዝ ነው /ሆሴ.፲፬/፡፡ ነቢዩ ሆሴዕ ሕዝቡ ምን ያኽል ኃጢአታቸው በዝቶ ከሞት አፋፍ ላይ እንዳደረሳቸው
ይናገርና፥ ቢመለሱ ግን ይኽ ሞት እንደሚዋጥ ተስፋን ይሰጣቿል /ሆሴ.፲፫፡፲፬/፡፡ ተወዳጆች ሆይ! እንዲኽ ኃጢአተኞች ለምንኾን
ለእኛም የተከፈተልንን የድኅነት ተስፋ ልንጠቀምበት ያስፈልጋል፡፡ ምንም ያኽል አመንዝሮች ብንኾንም እግዚአብሔር እግዚአብሔር ነው፡፡
እስከተመለስን ድረስ እንደ ደናግላን አድርጐ ይቀበለን ዘንድ የታመነ ወዳጅ ነው፡፡ የፍቅሩ ልኬት እንዲኽ ነው ተብሎ የሚመጠን አይደለምና
በእግዚአብሔር ፊት የሚዘጋ የንስሐ በር የለም፡፡ አኹን ያለንበት ዘመን እግዚአብሔር መጥቶ ጽድቅን እስኪያዘንብልን ድረስ እርሱን
የምንሻበት ዘመን ነው፡፡ እንኪያስ በጽድቅ እንዝራ፤ እንደ ምሕረቱ መጥንም እንጨድ፤ ጥጋታችንም እንረስ፡፡ ክፋትን አርሰን ኃጢአትን
ማጨድ ይብቃን፡፡ የሐሰትንም ፍሬ መብላት ይብቃን /ሆሴ.፲፡፲፪-፲፫/፡፡
በአጠቃላይ
ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስተምሩት የትንቢተ ሆሴዕ ዋና መልእክት ፍቅረ እግዚአብሔርን መግለጥ ስለኾነ “የብሉይ ኪዳን ዮሐንስ” ይሉታል /ሆሴ.፪፡፳፩-ፍጻሜ/፡፡ መጽሐፈ ሆሴዕ
ክብር ይግባውና ስለ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚኽ ዓለም መምጣት /ሆሴ.፮፡፩-፫/፣ ወደ ግብጽ መሰደድና መመለሱ
/ሆሴ.፲፩፡፩/፣ ስለ ሞቱና ትንሣኤው በኅብረ አምሳል ያስተምራል /ሆሴ.፲፫፡፲፬/፡፡ በሐዲስ ኪዳንም በብዛት ተጠቅሶ ይገኛል
/ሮሜ.፱፡፳፭-፳፮/፡፡
የትንቢተ
ሆሴዕን መጽሐፍ እንደሚከተለው መክፈል እንችላለን፡፡
1.
የእስራኤል ነባራዊ ኹኔታ ምን እንደሚመስል /ምዕ.፩-፫/፤
2.
እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለው ተግሳጽ /ምዕ.፬-፲/፤
3.
የድኅነት ተስፋ /ምዕ.፲፩-፲፫/፤
4.
የንስሐ ፍሬ ምን እንደኾነ /ምዕ.፲፬/፡፡
የነቢዩ ሆሴዕ
የመጨረሻ ዕረፍት
ነቢዩ ሆሴዕ
እንዲኽ እስራኤልን እያገለገለ ከኖረ በኋላ በመልካም ሽምግልና በሰላም በፍቅር ዐረፈ፡፡ መታሰቢያውም የካቲት ፳፮ ላይ ነው፡፡
ምስጋና ለእግዚአብሔር ይኹን፤ የነቢዩ ሆሴዕ በረከትና ረድኤትም ከኹላችን
ጋር ትደር ለዘለዓለሙ አሜን!!!
Ø የትንቢተ ሆሴዕ አንድምታ መቅድም፤
Ø የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፤
Ø ስንክሳር፤
Ø A Patristic Commentary on The
Book of Hosea By Fr. Tadros Malaty፡፡
No comments:
Post a Comment