Monday, August 12, 2013

የማክሰኞ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ

ገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፯ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም)፡- ለምስጋና ኹለተኛ፣ ለፍጥረት ሦስተኛ ቀን በሚኾን በዚህ ቀንም እመቤታችን ትመጣለች፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፤ የብርሃን ምንጻፍ ይነጸፋል፡፡ ከዚያ ላይ ኾናም፡- “ሰላም ለከ ኦ ፍቁርየ ኤፍሬም” ትለዋለች፡፡ እርሱም ታጥቆ እጅ ነሥቶ ይቆማል፡፡ ክርክር በዕለተ ሰኑይ አልቋልና “ባርክኒ” ብሎ ተባርኮ “አክሊለ ምክሕነ” ብሎ ምስጋናውን ይጀምራል፡፡

 ፩. ዳዊት ምንም ንጉሠ ነገሥት ቢባል የመመኪያችንን ዘውድ ማምጣት አልተቻለውም /፩ኛ ሳሙ.፲፮፡፲፫/፡፡ ኢያሱ ምንም የስሙ ትርጓሜ መድኃኒት ቢኾንም የደኅንነታችን መጀመሪያ መኾን አልተቻለውም፡፡ ኤልያስም ምንም ንጹሕ፣ ድንግል ቢኾን የንጽሕናችን መሠረት መኾን አልተቻለውም፡፡ የመመኪያችን ዘውድ፣ የደኅንነታችን መጀመሪያ፣ የንጽሕናችን መሠረት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ የመመኪያችን ዘውድ “አክሊለ ሰማዕት” የሚባል ጌታችን ነው፡፡ የደኅንነታችን መጀመርያ “ጥንተ ሕይወት” የሚባል ጌታችን ነው፡፡ የንጽሕናችን መጀመርያም ኹሉ በእጁ የተጨበጠ፣ ዓለምንም በመዳፉ የያዘ፤ በጠፈር ላይ የሚቀመጥ ፣ ዳግመኛም መሠረቱን ከታች የሚሸከምመሠረተ ዓለም” የሚባል ጌታችን ነው /ቅዳ.ማር. ቁ.፶፩/፡፡ እርሱም አካላዊ ቃልን በወለደችልን በድንግል ማርያም ተገኘልን፡፡ እኛን ስለማዳን ሰውነ፤ ሰውም ከኾነ በኋላ ግን ፍጹም አምላክ ነው፡፡ ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ እንደ ወለደችው ኹሉ እርሱም አምላክነቱ ሳይለወጥ ሰው ኾነ፡፡ እርሷ “ድንግል ወእም (ድንግልም እናትም)” ስትባል እንደምትኖር ኹሉ እርሱም “አምላክ ወሰብእ (ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው)” ሲባል ይኖራል /ሃይ.አበ.፷፯፡፯/፡፡ ተፈትሖ ሳያገኛት (ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ) እንደምን እንደወለደችው ግን የማይመረመር አንድም ሊነገር የማይችል፣ ከኅሊናት ኹሉ የሚያልፍ ድንቅ ነው፡፡ በማይመረመር ግብር ከወለድሽው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፪. “ቃል ሥጋ ኾነ” እንዲል በእርሱ ፈቃድ /ዮሐ.፩፡፲፬/፣ “ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና” እንዲል በአባቱ ፈቃድ /ዮሐ.፫፡፲፮/፣ “በመንፈስ ቅዱስ በኀይልም እንደ ቀባው” እንዲልም /ሐዋ.፲፡፴፰/ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ሰው ኾኖ አዳነን፡፡ ሊቁ እንዲህ ማለቱ “ወልድ ያለ ፈቃዱ ሰው ኾነ” የሚሉ መናፍቃን ስላሉ ነው፡፡ ሌሎች ሊቃውንትም፡- “የእግዚአብሔር ልጅ ያለ ፈቃዱ ሰው እንደ ኾነ የሚያምን፤ የሚያስተምር፤ ወይም የአብ ፈቃድ ሌላ ነው፤ የወልድ ፈቃድ ሌላ ነው፤ የመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ ሌላ ነው የሚል ቢኖር፤ ፈቃዳቸው አንድ፤ መንግሥታቸውም አንድ እንደኾነ የማያምን ሰው ቢኖር ውጉዝ ይኹን” ብለው አስተምረዋል /ሃይ.አበ.፻፳፫፡፪/፡፡

 በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ ፍጽምት የምትኾኚ እመቤታችን ሆይ! በድንግልና ጸንተሽ ብትገኚ ላንቺ የተሰጠሸ ጸጋ ፍጹም ነው፡፡ እግዚአብሔር ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቶ ካንቺ ጋራ አንድ ባሕርይ ቢኾን አንድም በጸጋ ቢያድርብሽ ባለሟልነትን አግኝተሸልና ለአንቺ የተሰጠ ክብር ፍጹም ነው፡፡ ይህ ከቃላት በላይ የሚያልፈው ባለሟልነቷ ቅዱስ ባስልዮስ ከሌሎች ቅዱሳን ጋር እያነጻጻረ ሲያብራራው፡- “የዚህ ዓለም ነገር ኹሉ አይመጥናትምና የሚመጥናትን ምን ዓይነት ምስጋና እናቅርብላት? ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ቅዱሳን ሲናገር ዓለም አልተገባቸውም /ዕብ.፲፩፡፴፰/ ካላቸው ከከዋክብት በላይ ኾና እንደምታበራው ፀሐይ ለኾነችው ለአምላክ እናትማ ምን ልንል እንችል ይኾን?... ምን ምሥጢር እንደተከናወነ ተመልከት፤ ኅሊናን አእምሮን የሚያልፍ ነገር እንደኾነም አስተውል፡፡ ታድያ የአምላክ እናት ታላቅነት እንደምን ኹሉም ሰው አይናገር? ማንስ ነው ከቅዱሳን ኹሉ በላይ እንደኾነች ያላስተዋለ? እግዚአብሔር ለአገልጋዮቹ የሚልቅ ጸጋን ከሰጠና የሚነኩት ኹሉ ሰው ከበሽታው ከተፈወሰ፣ ጥላቸው ያረፈበት ተአምር ከተፈጸመለት፣ ጴጥሮስ በጥላው ካዳነ /ሐዋ.፭፡፲፭/፣ የጳውሎስ የልብሱ ዕራፊ መናፍስትን ካወጣ /ሐዋ.፲፱፡፲፩/ ለእናቱማ ምን ዐይነት ሥልጣንና ኀይል ተሰጥቷት ይኾን? በምን ዓይነትስ ሥጦታ አስጊጧት ይኾን? ጴጥሮስ፡- ክርስቶስ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ስላለው ብፁዕ ነህ ከተባለና የመንግሥተ ሰማያት ቁልፍ ከተሰጠው /ማቴ.፲፮፡፲፮-፲፱/ እርሷማ ከኹሉም ይልቅ እንዴት ብፅዕት አትኾን? /ሉቃ.፩፡፵፭/ ጳውሎስ ታላቅ ክብር ያለውን የክርስቶስን ስም በመሸከሙ ምርጥ ዕቃ ከተባለ /ሐዋ.፱፡፲፭/ የአምላክ እናትማ የምእመናን ምግብ የኾነ መናውን ሳይኾን የሕይወት ሰማያዊ እንጀራን ያስገኘች እርሷ ምን ዓይነት ልዩ ዕቃ ትኾን? … ነገር ግን ስለ እርሷ ብዙ እናገራለሁ ብዬ ስለ ክብሯ ጥቂት በመናገር ራሴን በኀፍረት ውስጥ እንዳልጨምር እፈራለኁ፡፡ ስለዚህ ከአሁን ወዲህ የንግግሬን መልሕቅ ስቤ በዝምታ ወደቤ ላይ ማረፍን መርጫለሁ”  ይላል /መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ፣ ነገረ ማርያም በሐዲስ ኪዳን፣ ገጽ ፺-፺፩ ይመልከቱ/፡፡


 ከምድር እስከ ሰማይ ደርሳ፣ በላይዋ ዙፋን ተነጽፎባት በዚያ ላይ ንጉሥ ተቀምጦባት፣ መላእክት ሲወጡባት ሲወርዱባት ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ያያት የወርቅ መሰላል አንቺ ነሽ /ዘፍ.፳፰፡፲፰-፲፱/፡፡ መተርጕማኑ ይህ ምን ማለት እንደኾነ ሲያብራሩ፡- “ከምድር እስከ ሰማይ መድረሷ የልዕልናዋ፣ በላይዋ ላይ ዙፋን ተነጽፎባት ንጉሥም ተቀምጦባት ማየቱ ፱ ወር ከ፭ ቀን በማኅፀኗ ለመሸከሟ፣ መላእክት ሲወጡባት ሲወርዱባት ማየቱ ደግሞ ጌታችን ከእመቤታችን ሰው ከመኾኑ አስቀድሞ ሰው የጸለየውን ጸሎት ያቀረበውን መሥዋዕት ለማሳረግ አይወጡም አይወርዱም ነበር፤ ጌታችን ከእመቤታችን ሰው ከኾነ በኋላ ግን ለተልእኮ የሚወጡ የሚወርዱ ኾነዋልና ሲል ነው”  ይላሉ /ሉቃ.፪፡፲፬፣ ሐዋ.፲፡፫-፬፣ የኦሪት ዘልደትን ትርጓሜ ይመልከቱ/፡፡ ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ በአምሳለ ንጉሥ ካየው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፫. ነደ እሳት ሰፍሮባት፤ በነደ እሳት ተከባ (ጫፎቿ) ሳትቃጠል ሙሴ በደብረ ሲና ያያት ዕፅ አንቺ ነሽ /ዘጸ.፫፡፩-፫/፡፡ ነደ እሳትም ያልኹት ሰው ኾኖ በማኅፀንሽ ፱ ወር ከ፭ ቀን ያደረው ወልደ እግዚአብሔር ነው፡፡ ምንም እንኳን አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ ቢኾንም እሳተ መለኮቱ አላቃጠለሽም፡፡ አባ ሕርያቆስ ይህ ከኅሊናት የሚያልፈውን ነገር ሲያደንቅ ፡- “ቅድስት ድንግልን ለኹሉ ድንቅ የሚኾን የፅንሷን ነገር እንዲህ እያልን እንመርምራት፡፡ ድንግል ሆይ! እሳተ መለኮት በማኅፀንሽ ባደረ ጊዜ አካሉ እሳት ነው፤ መጐናጸፍያው እሳት ነው፤ ቀሚሱ መቋረፍያው እሳት ነው፡፡ እንደምን አላቃጠለሽ? ብለን እንመርምር፡፡ ሰባት የእሳት ነበልባል መጋረጃ በማኅፀንሽ ወዴት ተዘጋጀ? ወዴት ተጋረደ? በቀኝ ጐንሽ ነውን? ወይስ በግራ ጐንሽ ነውን? ሦስት ክንድ ከስንዝር ቁመት የተወሰንሽ ስትኾኚ እንደምን ቻልሽው? የአሥራ አምስት ዓመት ቆንጆ ስትኾኚ አጎበሩ ሻኩራው ነደ እሳት የሚኾን፤ ዐይን የሚበዘብዝ ኪሩቤል የተሸከሙት መንበር ወዴት ተዘረጋ? ወዴት ቆመ?” ይልና /ቅዳ.ማር.ቁ.፸፯-፸፰/ “ኅሊናዬ ይህን አልመረምርም ብሎት ወደ ቀደመ አኗኗሩ ይመለሳል” ብሎ ይቋጨዋል /ቁ.፹፬/፡፡
  ሙሴ ያየው ሐመልማል ነበልባሉን እንዳላጠፋው ኹሉ ጌታም ምንም እንኳን ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽም ነፍስ ነሥቶ ቢዋሐድም ባሕርየ መለኮቱ አልተለወጠምና ሙሴ በደብረ ሲና ያያት ዕፅ አንቺ ነሽ ፡፡ ሙሴ በአምሳለ ሐመልማል ወነበልባል ካየው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፬. አንቲ ውእቱ ገራኅተ ዘኢተዘርዐ ውስቴታ ዘርዕ - ዘር ያልወደቀባት፣ ገበሬ ያልጣረባት ያልጋረባት፣ ለታብቁል (ታብቅል) ባለው ቃል ብቻ ከልምላሜ፣ ከጽጌ (ከአበባ)፣ ከፍሬ የተገኘች ገራኅተ ሠሉስ (የማክሰኞ እርሻ) አንቺ ነሽ፡፡ የወንድ ዘር ሳይወድቅብሽ ፍሬ ሕይወት (የሕይወት መገኛ) ጌታ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ካንቺ ተወልዷልና፡፡ አረጋዊው ዮሴፍ በትሩፋተ ደሙ የዋጀሽ /ቅዳ.ማር. ቁ. ፻፳፰/፣ ዕንቁ የተባለው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም ያገኘብሽ /ሃይ.አበ.፺፮፡፶፭/ የተቈለፈች ሣጥን አንቺ ነሽ፡፡ በዚህ አለ፣ በዚያ የለም የማይሉት ሙሉዕ በኵለሄ የኾነ አካላዊ ቃል በማኅፀንሽ አደረ /መዝ.፻፴፱፡፰/፤ በዚህ ዓለምም ማኅተመ ድንግልናሽ እንደተቈለፈ ወለድሽው /ሕዝ.፵፬፡፩-፪/፡፡ በዕንቁ ከተመሰለው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡  

 ፭. ሥጋዌውን ተልከው ለነቢያት ሲነግሩ የነበሩ፣ አሁን ደግሞ
በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ አይተውትስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር” ብለው በደስታ ያመሰገኑትን ጌታን የወለድሽው ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡

የነቢያት ዜና ትንቢታቸው ንጽሕት ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴው፡- “ኦ ድንግል አምሳል ወትነቢት ዘነቢያት- ነቢያት ትንቢት የተናገሩልሽ ምሳሌ የመሰሉልሽ…” ይላታል /ቅ.ማር.ቁ.፴፯/፡፡ እግዚአብሔር ከነፍስሽ ነፍስ ከሥጋሽ ነሥቶ ካንቺ ጋራ አንድ ባሕርይኗልና ደስ ይበልሽ፡፡ አንድም እግዚአብሔር በጸጋ ቢያድርብሽ ባለሟልነትን  አግኝተሻልና ደስ ይበልሽ፡፡ የሰው ኹሉ ደስታ የሚኾን የመልአኩን ቃል እንደ ኒቆዲሞስ ሳትከራከሪ /ዮሐ.፫፡፬-፱/ እንደ ዘካርያስም ሳትጠራጠሪ /ሉቃ.፩፡፳/ አምነሻልና ደስ ይበልሽ /ሉቃ.፩፡፵፭/፡፡ ሃያውን ዓለም የፈጠረ ጌታ የወለድሽው ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ሃያውን ዓለም ከፈጠረ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኝልን፡፡

፮.
በእውነት ወላዲተ አምላክ ተብለሻልና ደስ ይበልሽ፡፡ አንድም በሚገባ ወላዲተ አምላክ ተብለሻልና ደስ ይበልሽ፡፡ አንድም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡- “ብልህ ሸክላ ሠሪ የሚሠራውን የለዘበ ጭቃ በአገኘ ጊዜ ከእርሱ መልካም ዕቃ እንዲሠራ፤ እንደዚህም ጌታችን የዚህችን ድንግል ንጹሕ ሥጋዋን ንጽሕት ነፍሷን ባገኘ ጊዜ ነፍስ ያለችውን ሥጋ ሊዋሐደው ፈጠረ” /ሃይ.አበ.፷፮፡፲፬/ እንዲል በቅተሸ ብትገኚ ወላዲተ አምላክ ተብለሻልና ደስ ይበልሽ፡፡
 የሔዋን ደኅንነቷ ሆይ! ደስ ይበለሽ፡፡ ሊቁ ያዕቆብ ዘሥሩግም እንዲህ ይላል፡- “የሕዝቦች ሴቶች ልጆች ሆይ! ከአባቶቻችሁ ስሕተት ነጻ ያወጣችሁን ቅረቡት፤ እርሱንም ማመስገን ተማሩ፡፡ ያ ሔዋን የዘጋችውን የማይናገር አፍ አሁን በእመቤታችን ማርያም ተከፍቷልና ለእኅታችሁ ምስጋናን ለመዘመር ቅረቡ፡፡ አሮጊቷ ሴት (ሔዋን) በምላሶቻችሁ ዙርያ የዝምታን ገመድ ቋጠረች፤ የድንግል ልጅ ግን ጮኻችሁ ታመሰግኑ ዘንድ እሥራታችሁን ፈታ…” /A Metrical Homily on Holy Ephrem, pp 47/፡፡ ከአባቶች አንዱም፡- “እንግዲህስ ሴቶች ኹሉ ሐሴት ያድርጉ፤ አሁን ሴቲቱ ዕፀ በለስን ሳይኾን ዕፀ ሕይወትን አስገኝታለችና፡፡ ዳግመኛም ደናግላን እናቶች ኹሉ በፌሽታ ይዝለሉ፤ ያለመታዘዝን ዕፅ በሴት ተፈውሷልና፡፡ እነሆ ክብሩ ከመላእክት ይልቅ የከበረ ኾኗልና ከእንግዲህ ወዲህ የሴትነት ጾታ የሞትና የውድቀት ምልክት መኾኑ ቀርቷል፡፡ ሔዋን ተፈወሰች፤ ድንግል ግን ከበረች፡፡ እነሆ ድንግሊቱ እናትም አገልጋይም፣ ደመናም ድንኳንም፣ ደግሞም የጌታ ታቦት ኾናለችና፡፡ እንግዲያውስ ኑ! አንቺ ከሴቶች መካከል ተለይተሸ የተባረክሽ ነሽ፤ የሔዋን መድኃኒቷ አንቺ ብቻ ነሽ፤ ዓለምን በደሙ የሚገዛትን ጌታ ያስገኘሽ አንቺ ብቻ ነሽ እያልን እናወድሳት” ብሏል፡፡

ፍጥረትን ኹሉ በፀሐይ አብስሎ በዝናብም አብቅሎ የሚመግበውን እርሱ ጡትሽን ይዘሽ አጥተሸዋልና ደስ ይበልሽ፡፡ አንድም ለመንፈሳውያን ኹሉ ሥጋውን ደሙን ሰጥቶ የሚመግበውን እርሱን ጡትሽን ይዘሽ አጥብተሸዋልና ደስ ይበልሽ፡፡

 ተጠምቀው ሕያዋን ኾነው የሚኖሩበት ማየ ገቦ ከአንቺ ከተገኘ ከጌታ የተገኘ ነውና የሕያዋን የጻድቃን እናታቸው ንእድ ክብርት ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ መቅድመ ተአምርም፡- “ሕይወትየ ይቤላ አዳም ለብእሲቱ አእሚሮ ከመ ትወጽእ እግዝእትነ ማርያም እምሐቌሁ ወእምከርሠ ብእሲቱ - አዳምም እመቤታችን ማርያም ከሱ አብራክ እንድትከፈል ከሔዋንም ማኅፀን እንድትወለድ ዐውቆ ሔዋንን ሕይወቴ ነሽ ይላት ነበር” ይላል /መቅድመ ተአምር ቁ. ፲/፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግም፡- “አዳም ያለ ሩካቤ ድንግል የኾነች ሔዋንን አስገኘ፤ የሕይወት እናት ብሎም ጠራት፡፡ በዚህም ነቢይ ኾነ፤ በኹለተኛ ልደት ከእርሷ የሚያበራ ሕይወት ይገለጣልና፤ በድንግልናዋም የእግዚአብሔር ልጅን ታስገኛለችና፡፡ በአዳም ትንቢት የእውነት ሕይወት የኾነው የጌታችንን መምጣት በምሳሌ ተናገረ፡፡ እናቱም ድንግል ማርያም ኾነች፡፡ ሔዋንን የሕያዋን ኹሉ እናት ብሎ ጠራት፤ ሕይወትን አስገኝታለችና፡፡ እርሱም ኢየሱስ የተባለው ጌታችን ነው” ይላል /Jacob of Serug, On the Virgin, pp 36/፡፡ አንድም “ነዋ ወልድኪ- እነሆ ልጅሽ” /ዮሐ.፲፱፡፳፮/ ባለ ጊዜ በዮሐንስ እኛን ለእርሷ መስጠቱ ነውና የሕያዋን ኹሉ እናታቸው ንዕድ ክብርት ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ ለምኚልንና ትልምኝልን ዘንድ ዓይነ ሕሊናችንን ወደ አንቺ እንሰቅላለን፡፡

፯. ድንግል ሆይ! ንዕድ ክብርት ሆይ! ጌታን የወለድሽው ሆይ! እኛን ለማዳን ድንቅ የሚያሰኝ ተዋሕዶ በአንቺ ቢደረግ ንጉሥን ወለድሽልን፤ መንክር በአርያሙ የሚባል ጌታ በማኅፀንሽ አደረ፡፡ ነገር ግን በብዙ ኅብረ መልክእ፣ በብዙ ፆታ መልክእ ኹለቱን ሥነ ፍጥረት የፈጠረ፣ ሀብተ መንፈስ ቅዱስን በብዙ ፆታ በብዙ ዕድል እንደየ ሰዉ የአእምሮ ስፋት የሃይማኖት ጽናት የሚያድል፣ ልዕልናውን ገናንነቱን በብዙ መንክር ራዕይ በብዙ ወገን (ለምሳሌ በፀሐይ፣ በቀላይ፣ …) የተመሰለ እርሱን የጌትነቱን ነገር ጠንቅቀን (ፈጽመን) መናገር አይቻለንምና ዝም እንበል፡፡ ዳግመኛም በብዙ ኅብረ ትንቢት (ለምሳሌ ናሁ ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ ተብሎ) የተነገረ፣ በብዙ ኅብረ አምሳል (ለምሳሌ በአምሳለ ነበልባል ወሐመልማል፣ በአምሳለ ጠል ወፀምር፣ በአምሳለ አንበሳ፣ በአምሳለ እብን ቅውም) የተመሰለ የርሱን የሥጋዌውን ነገር ጠንቅቀን (ፈጽመን) መናገር አይቻለንምና ናርምም (ዝም እንበል)፡፡
ሥጋዌው በአምሳለ ነበልባል ወሐመልማል፣ በአምሳለ ጠል ወፀምር ከተመሰለ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፯. ወደ ደብረ ሲና የወረደው፣ ለሙሴ ሕገ ኦሪትን የሠራ፣ የተራራውን ራስ በጨለማ በእሳት በጽጋግ በነፋስ (በዕበየ ግርማው)ሸፈነ፣ ፈርተው የቆሙትን ፈጥኖ ፈጥኖ በሚሰማ በረቂቅ ነጋሪት ድምጽ የገሠፀ እርሱ የሰው ልጆችን ለማዳን ፭ ሺሕ ፭፻ ዘመን ሲፈጸም ሰው ኾኖ የመጣው የአብ አካላዊ ቃል ነው፡፡ በሌላ አንቀጽም ይኸው ሊቅ፡- “እም ደብረ ሲና ወፅአ እሳት ወጽልመት ወእምኔኪ ወፅአ ለነ አምላክ ወሰብእ፡፡ እም ደብረ ሲና ወፅአ ድንጋፄ ወሀውከ ላዕለ አይሁድ ወእምኔኪ ወፅአ ሁከት ወድንጋፄ ዐቢይ ላዕለ አይሁድ ወሄሮድስ ወዲያብሎስ ምስለ አጋንንቲሁ - ከደብረ ሲና እሳት ጨለማ ወጣ፤ ከአንቺ ግን ሰው የኾነ አምላክ ተገኘልን፡፡ በደብረ ሲና በአይሁድ ላይ ድንጋፄ ሀውክ ተደረገ፤ በአንቺም በአይሁድ በሄሮድስ በዲያብሎስና በሠራዊቱ ላይ ጽኑ ድንጋፄ ተደረገ” ብሏል /ዘጸ.፳፡፲፰፣ ዕብ.፲፪፡፲፱፣ ሃይ.አበ.፵፯፡፱-፲/፡፡ እንዲህ ከተባለ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፰. “ናሁ ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ” ከሚለው የኢሳይያስ አንቀጽ /ኢሳ.፯፡፲፬/ ስትደርሺ “እኔ በኾንኩኝ” ሳትዪ፤ ይልቁንም “ምነው ከዘመኗ ደርሼ፣ ወጥቼ ወርጄ በድንግልና የምትወልደውን ድንግል ባገለገልኳት” ብለሽ በትሕትና የተናገርሽ ደብር ነባቢት ሆይ! ሰውን የሚወድ፣ ሰውም የሚወደው ጌታ ባሕርዩ ሳይለወጥ ካንቺ ከሥጋሸ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቶ ሰው ኾነ፡፡ እንደኛ የሚናገር ሥጋን ነሥቶም ሰው ኾነ፡፡ ጥበብን በሚገልጽ፣ ሥጋዌን በሚያስፈጽም በግብረ መንፈስ ቅዱስ አምላክ በማኅፀንዋ አደረና ፍጹም ሰውነ፡፡ በቸርነቱና በይቅርታው ብዛት አዳምንድነው ዘንድ፣ ኃጢአቱንም ያስተሠርይለት ዘንድ፣ በሰማያዊ ቦታ በሰማያዊ መዓርግ ያኖረው ዘንድ /ኤፌ.፪፡፮/፣ ወደ ቀደመው ቦታው ወደ ቀደመው ክብሩ ይመልሰው ዘንድ ፍጹም ሰውነ፡፡ በቸርነቱ በይቅርታው ብዛት አዳምን ወደ ቀደመው ቦታ ከመለሰው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፱. የድንግል ክብሯ ሊናገሩት አይቻልም፡፡ ከእናንተ መካከል፡- “ይኸው እየተናርን አይደለምን?” የሚል ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡- “ለርሷ እንደሚገባ አድርጎ መናገር የሚቻለው የለም” ሲል ነው፡፡ “ለምን?” ጌታ መርጧታልና፡፡ አሁንም ከእናንተ መካከል፡- “ታድያ እርሱ ከመረጣትማ ምን ይደንቃል?” የሚል ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡- አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ላይ፡ “በአማን ነጸረ እግዚአብሔር አብ እምሰማይ ምሥራቀ ወምዕራበ ሰሜነ ወደቡበ ወውስተ ኵሉ አጽናፍ አስተንፈሰ ወአጼነወ ወኢረከበ ከማኪ ወሠምረ መዐዛ ዚአኪ ወአፍቀረ ሥነኪ ወፈነወ ኀቤኪ ወልዶ ዘያፈቅር - እግዚአብሔር አብ በሰማይ ኾኖ ምሥራቅንና ምዕራብን ሰሜንንና ደቡብን ዳርቻዎችን ኹሉ በእውነት ተመለከተ፤ ተነፈሰ፤ አሻተተም፤ እንዳንቺ ያለ አላገኘም፡፡ የአንቺ መዐዛ ወደደ፤ የሚወደውን ልጁንም ወደ አንቺ ላከ” ብሎ እንደተናገረው እንድትመረጥ ኾና ተገኝታለችና ነው /ቅዳ.ማር.ቁ.፳፬/፡፡

ሐዋርያው “ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል” እንዲል /፩ኛ ጢሞ.፮፡፲፮/ በመመርመር ገንዘብ በማድረግ የሚቀርበው በሌለው ብርሃን ባሕርዩ አድሮ የሚኖረ እርሱ /ሃይ.አበ.፴፫፡፫/ ሰው ኾኖ በማኅፀንዋ አደረ /ዮሐ.፩፡፲፬/፡፡ ዘጠኝ ወር ከአምስተ ቀን በማኅጸንዋ ኖረ፡፡ ሰውም ከመኾኑ አስቀድሞ ሰውም ከኾነ በኋላ የማይመረመር እርሱን ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ ወለደችው፡፡ ሰውም ከመኾኑ አስቀድሞ ሰውም ከኾነ በኋላማይመረመረው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፲. ነቢዩ ዳንኤል ያየውና እጅ ሳይፈነቅለው ከረጅም ተራራ የወረደው ደንጊያ /ዳን.፬፡፩-፴፭/ ከአብ ዘንድ የወጣው አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ያ ድንጋይ የሰው እጅ ሳይነካው ከረዥሙ ተራራ እንደተፈነቀለ ኹሉ አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስም ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ዘር ምክንያት ሳይኾነው ከድንግል ተወለደ፡፡ ዳንኤል በአምሳለ እብን (ደንጊያ) ካየው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፲፩.
ሐሩረ ፀሓይ ያልወደቀባት፣ ነፋስ ያልወዘወዛት፣ ለታብቁል (ታብቅል) ባለው ቃል ከልምላሜ፣ ከጽጌ፣ ከፍሬ የተገኘች ዐፅቀ ሠሉስ (የማግሰኞ ቅርንጫፍ) አንች ነሸ /ኩፋ.፪፡፲፪/፡፡ እንዲህ ማለቱ ነው፡- “በዕለተ ሠሉስ የተገኙ ቅጠሎች፣ ቅርንጫፎች ፀሐይ እንዳላጠወለጋቸው፣ ነፋስ እንዳልወዘወዛቸው ኹሉ አንቺም የኃጢአት ፀሐይ አልለወጠሽም፡፡ በሥጋሽ፣ በነፍስሽ፣ በኅሊናሽም ድንግል ነሽ እንጂ” /መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ፣ ነገረ ማርያም በብሉይ ኪዳን፣ ክፍል ፩፣ ገጽ ፲/፡፡ አባ ጊዮርጊሥም፡- “በበደል ምሣር የማትቈረጪ፣ ከኀጢአት ዐውሎ ነፋስ የተነሣ የማትነዋወጪ፣ ዘወትር ፍጹም የምትለመልሚ፣ በዘመኑ ኹሉ የምታፈሪ፣ በወሮች ኹሉ የምትለቀሚ፣ ከዕፅዋት ኹሉ ይልቅ የምታምሪ እመቤቴ ማርያም ሆይ! የተባረክሽ ዕፅ ነሽ” ይላታል /እንዚራ ስብሐት፣ ገጽ ፲፬/፡፡ አምላክን የወለድሽ ንጽሕት፣ በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ ኅትምት የምትኾኝ ሆይ! ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ስለ ማዳን ሰው ኹኗልና (አካላዊ ቃልን ወልደሽልናልና) የሃይማኖትም (የክርስቶስም) ሙዳይ (መገኛ) ነሽ፡፡ (በልጅሽ ላመኑ) የአባቶቻችን የቀናች ሃይማኖታቸው ነሽ፡፡ እኛን ስለማዳን ሰው ከኾነ ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፲፪. የከበርሽ አምላክን የወለድሽ ሆይ! የማይመረመር ቃልን የወሰንሺው የብርሃን እናቱ አንች ነሽ፡፡ እርሱንም ከወለድሽው በኋላ ማኅተመ ድንግልናሽ ሳይለወጥ ኖረሻልና በአፍኣ በውስጥ በሥጋ በነፍስ ያከብሩሻል፤ ያገኑሻል፡፡ እንዲህ ካለ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፲፫. ወዮ! ስለ አንቺ ድንቅ የሚነገረውን ነገር መናገር የሚቻለው ምን አንደበት ነው? ቅድመ ዓለም ያለ እናት ተወልዶ፣ ድኅረ ዓለም ያለ አባት እንደምን እንደወለደሽው መናገር የሚቻለው ምን አንደበት ነው? የአካላዊ ቃል እናቱ ንጽሕት ደንግል ሆይ! ኪሩቤል ለሚሸከሙት ለንጉሥ ማደሪያ ኾንሽ፡፡ ንዕድ ክብርት ሆይ! እኛምብርሽን ገናንነትሽን ዕፁብ ዕፁብ እያልን እናመሰግንሻለን /ሉቃ.፩፡፵፰/፡፡ የአካላዊ ቃል እናቱ መልካሟ ርግብ (ርግበ ኖኅ) ማርያም ሆይ! ስምሽን በትውልደ ሴም፣ በትውልደ ካም፣ በትውልደ ያፌት እንጠራለን፡፡ ሊቁ እመ አምላክን “መልካሟ ርግብ” አላት፡፡ ይኸውም የኖኅ ርግብ “የጥፋት ውሃ ጐደለ፤ የጥፋት ውሃ ተገታ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሰላም ነው” ስትል የምሥራቹን የዘይት ቅጠል ይዛ እንደታየች ኹሉ /ዘፍ.፰፡፲፩/ እመቤታችንም “የኀጢአት ውሃ ጐደለ፤ የመርገም ውሃ ተገታ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ዘመነ ሰላም ነው” ስትል ዓመተ ፍዳ ዓመተ ኩነኔን ኣሳልፎ ዓመተ ምሕረትን የተካ፣ ለዓለሙ ኹሉ ታላቅ የምሥራች የኾነ፣ የዓለም መድኃኒት ክርስቶስን ወልዳልናለችና፡፡ እንዲህ ካለ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፲፬.ናትነትን ከአገልጋይነት ጋር /ሉቃ.፩፡፴፰/ ያለሽ እመቤታችን ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ በክንድሽ የያዝሺውን (የታቀፍሽውን) መላእክትመሰግኑታልና፡፡ እሳታውያን የኾኑ ሱራፌልም ሳያቋርጡ ክንፋቸወን ዘርግተው፡- “የክብር ባለቤት ይህ ነው” ይላሉ፡፡ “በቸርነቱ በይቅርታው ብዛት የሰውን ኹሉ ኃጢአት ለማስተሥረይ ሰው የኾነ የክብር ባለቤት ይህ ነው” እያሉ በፍርሐት በረዐድ ኾነው ያመሰግኑታል፡፡ የሰውን ኃጢአት በቸርነቱ ብዛት ከሚያሰተሠርይ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
ይህን ሲጨርስ በያዘችው መስቀለ ብርሃን ባርካው ታርጋለች፡፡ እርሱም ተባርኮ እጅ ነሥቶ ይቀራል፡፡

አነሣሥቶ ላስጀመረን ፤ አስጀምሮም ላስፈጸመን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባው አሜን፡፡

2 comments:

 1. https://www.youtube.com/watch?v=rsJSv-rJUjM
  ዘሠሉስ የውዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ

  አዘጋጅ፦ሊቀ ጉባኤ ጌታሁን ደምፀ
  በታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ስብከተ ወንጌል ኃላፊ
  ንባብ፦ ደቀ መዝሙር ሳሙኤል ታደሰ
  +++

  ReplyDelete
 2. yemamelak weladete amelak bereketena feqer yelejewa cherenet yebezalot

  ReplyDelete

FeedBurner FeedCount