Saturday, December 27, 2014

ነገረ መላእክት (Angelology)



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ቅዳሜ ታኅሳስ 18 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ትርጕም
 ጥሬ ቃሉን ስንመለከተው መልአክ የሚለው የግእዝ ቃል ኹለት ትርጉሞች አሉት፡፡ አንደኛው አለቃ፣ ሹም ማለት ነው፡፡ በዮሐንስ ራዕይ ላይ የምናገኛው ሰባቱ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች መላእክት ተብለው መጠራታቸውም ከዚኽ አንጻር ነው /ራዕ. 2 እና 3/፡፡ ኹለተኛውና ከተነሣንበት ርእስ አንጻር ስናየው ደግሞ መልክእተኛ፣ የተሰደደ፣ የተላከ የሚል ትርጕም አለው /ዕብ.1፡14/፡፡ ይኸውም የመላእክት ተግባር ምን እንደኾነ የሚያስረዳ ቃል ነው፡፡ መላእክት ከእግዚአብሔር ወደ ሰው፥ ከሰውም ወደ እግዚአብሔር የሚላላኩ መናፍስት ናቸውና፡፡ መላእክት በሌላ ስማቸው የሰማይ ሠራዊት ተብለው ይጠራሉ፡፡

መላእክት ስንት ወገን ናቸው?

መላእክት ኹለት ወገን ናቸው፡፡ ብርሃናውያን መላእክትና የጨለማ አበጋዝ የኾነው የዲያብሎስ ሠራዊት የኾኑት እኩያን መላእክት፡፡ ስለዚኽ የእግዚአብሔርን መላእክት ከሌሎቹ መላእክት በአጠራር የምንለያቸው ቅዱስ በሚል ቅጽል ነው፡፡

መላእክት መቼ ተፈጠሩ?

መላእክት የተፈጠሩት በመዠመሪያው ቀን ነው /ኩፋ.2፡7-8/፡፡ መዝሙረኛው ክቡር ዳዊትም ይኽን በማስመልከት፡- “በእግዚአብሔር ቃል ሰማያት ተፈጠሩ፤ የሰማይ ሠራዊትም ኹሉ በአፉ እስትንፋስ” ይላል /መዝ.32፡6/፡፡
 ምንም እንኳን በመዠመሪያው ቀን የተፈጠሩ ቢኾኑም ግን ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋና ከሰባቱ ሰማያት በኋላ በ9ኛው ሰዓተ ሌሊት ነው የተፈጠሩት፡፡ ይኽ ለምን እንደኾነ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ አክሲማሮስ በተባለ መጽሐፉ ላይ፡- “በፊት ፈጥሯቸው ቢኾን እኛም አብረነው ፈጠርን፤ ያዝንለት፤ ተራዳነው ባሉ ነበር፡፡ አንድም ርሱ ቢመሠርት እኛ ገነባን፤ ርሱ ቢገነባ እኛ መሠረትን ባሉ ነበር፡፡ ይኽም ሳጥናኤል በኋላ እኔ ፈጠርኳችኁ እንዳለው ማለት ነው” በማለት ያብራሯል /አክሲማሮስ ዘእሑድ፣ ገጽ 24/፡፡
 አንዳንድ ሊቃውንት መላእክት ከሰው በፊት ስለተፈጠሩ የሰው ታላላቅ ወንድሞች ናቸው ይሏቸዋል፡፡
 ተፈጥሮአቸውም ካለ መኖር ወደ መኖር ነው፡፡ መላዕክት እንደ እሳት የሚሞቁ፣ እንደ ነፋስ የሚረቁ ስለ ኾነ /ዝኒ ከማኁ/ አንድም እንደ እሳት እንደ ነፋስ ፈጣኖችና የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽሙ ኃያላን ስለኾነ ባሕርያቸውን ለመግለጥ ከነፋስና ከእሳት ተፈጠሩ ይባላሉ /መዝ.103፡4፣ መዝሙረ ዳዊት ንባቡ ከነትርጓሜው፣ ገጽ 489 /፡፡  


የመላእክት አሰፋፈራቸው እንዴት ነው?

  የመላእክት ቁጥራቸው ከእግዚአብሔር በቀር ማንም አያውቀውም /ዳን.7፡10/፡፡ በነገድ በነገድ ስናያቸው ግን ቅዱስ ኤጲፋንዮስ እንደሚነግረን 100 ነገዶች ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ዐሥር ዐሥር ነገድ የሚይዙ ሲኾኑ ቅደም ተከተላቸውም ይኸው ነው፡- አጋዕዝት /አለቃቸው ሳጥናኤል (ሰማልያል) የአኹኑ ዲያብሎስ ነው/፣ ኪሩቤል /አለቃቸው ኪሩብ ነው፤ አራት ራስ አራት ገጽ አላቸው፡፡ ገጻቸውም ገጸ ሰብእ ገጸ አንበሳ ይመስላል፡፡ ሰውነታቸው ኹሉ በዓይን የተሸለመ ሲኾን ዓይናቸውም እንደ ነብር ቆዳ ዥንጕርጕር ነው /ሕዝ.1፡6-7፣ 18-19/፡፡ አገልግሎታቸው በቀሳውስት አምሳል የሥላሴን ዙፋን መሸከም ነው/፣ ሱራፌል /አለቃቸው ሱራፊ ነው፤ በዲያቆናት አምሳል ለጸሎት የሚተጉና የሚያተጉ የምስጋና መላዕክት ናቸው፡፡ ገጻቸው ገጽ ንስር ገጸ እንስሳ ይመስላል፡፡ ስድስት ስድስት ክንፍ አላቸው ኢሳ.6፡2-3/፣ ኃይላት /አለቃቸው ቅዱስ ሚካኤል ነው /ኄኖክ.10፡2-10/፡፡ የሥላሴ ሰይፍ ጃግሬዎች ናቸው/፣ አርባብ /አለቃቸው ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ በሥላሴ ፊት በአጋፋሪ በአስተናጋጅ አምሳል የሚቆሙ ናቸው ኄኖክ 10፡7-8፣ ሉቃ.1፡19/፣ መናብርት /አለቃቸው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ በጋሻ ጃግሬ አምሳል ያገለግላሉ፡፡ የመብረቅ ጋሻ የእሳት ጦር ይዘው ዘለዓለም እንደ ነፋስ ሲበሩ ይኖራሉ/፣ ሥልጣናት /አለቃቸው ቅዱስ ሱርያል ነው፡፡ የሥላሴ አዋጅ ነጋሪዎችና መላዕክትን በየጊዜው ለጸሎትና ለምስጋና የሚያተጉ ናቸው/፣ መኳንንት /አለቃቸው ሰዳካኤል ይባላል፡፡ የሥላሴ ቀስተኞች ናቸው፡፡ ተራራ የሚንድ፣ ድንጋይ የሚሰነጥቅ፣ የእሳት ፍላፃ የእሳት ቀስት ይዘው ሰውን ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ሲጠብቁ ይኖራሉ፡፡ በትንሣኤ ዘጕባኤ ጊዜ የሰውን ኹሉ አጥንት ሰብስበው ለትንሣኤ የሚያበቁ እንዚኽ ናቸው ማቴ.24፡31-42/፣ ሊቃናት /አለቃቸው ሰላታኤል ይባላል፡፡ የሥላሴ ፈረስ ባልደራስ ናቸው፡፡ የእንስሳት ጠባቂ መላዕክት ናቸው/፣ መላዕክት /አለቃቸው አናንኤል ይባላል፡፡ እንደ ብረት የጸና የእሳት ነጐድጓድን ወደ ምድር የሚወነጭፉ፣ ፀሐይን ጨረቃን ከዋክብትን አዝርዕትን አትክልትን ዕፅዋትን ከምድር በላይ ከሰማይ በታች የተፈጠሩትን የሚጠብቁ ናቸው ኩፋሌ 2፡6-8/፡፡
እነዚኽ ቅዱሳን መላእክት የሚኖሩባቸው ቦታዎች ሦስት ሲኾኑ ኢዮር ራማ እና ኤረር ይባላሉ፡፡ የመዠመሪያዎቹ 40 ነገድ በኢዮር፣ ቀጣዮቹ 30 በራማ፣ የመጨረሻዎቹ 30ም በኤረር የሰፈሩ ናቸው፡፡ 
ዲያብሎስ በትዕቢቱ ከተዋረደ በኋላ ግን የነገደ መላእክቱ ቁጥር ከ100 ወደ 99 የአለቆች ቁጥርም ከ10 ወደ 9 ተቀንሷል፡፡  
እነዚኽ መላዕክት ለተልዕኮ ፈጣሪ ካላዘዛቸው በቀር ከስፍራቸው አይለቁም፡፡ ሲያዛቸው ግን ወደ ላይ እስከ ጽርሐ አርያም ወደ ታች እስከ በርባሮስ ድረስ ከብርሃን ፍጥነት በላይ በኾነ ቅጽበት ይወጣሉ፤ ይወርዳሉ፡፡



  የመላእክት ባሕርይ እንዴት ነው?

የመላእክት ባሕርይ ከሰው ጋር የሚያመሳስለውም የሚያለያየውም ነጥብ አለው፡፡ ከሰው በምን ይለያሉ ቢሉ መላእክት፡-
·        ረቂቃን ናቸው፡፡ ከነፋስ ነፍስ ትረቃለች፤ ከነፍስ መላእክት ይረቃሉ፤ ከመላእክት ደግሞ ሥላሴ ይረቃሉ፡፡
·        እንደ ሰው አይራቡም፤ አይጠሙም፡፡ ልብስ፣ መጠለያ አይፈልጉም፡፡ “እኔም ተገለጥኩላችኁ፤ ነገር ግን እይታን አያችኁ እንጂ ከእናንተ ጋር አልበላኹም፤ አልጠጣኹምም” /ጦቢት 12፡19/፡፡
·        የመላዕክት ምግባቸው የእግዚአብሔር ምስጋና መጠጣቸውም የመለኮት ፍቅር ነው፡፡
·        መላዕክት ፆታ የላቸውም /ማቴ.22፡30-31/፡፡ በመኾኑም አይጋቡም፤ አይዋለዱም፡፡
·        ስለ ነገ አይጨነቁም፡፡
·        መላዕክት ከዝንጋዔ የራቁ፣ ባለ አዕምሮ የኾኑ፣ ዕውቀት ያላቸው፣ ይዋኄንና ትዕግሥትን ገንዘብ ያደረጉ፣ ለዘለዓለም የማይነጥፍና የማያቋርጥ ይልቁንም ዘወትር እንደ ዥረት ውኃ የሚወርድ ምስጋና ያላቸው ናቸው /ሥነ ፍጥረት፣ በቀሲስ ስንታየኁና በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ የተዘጋጀ፣ ገጽ 34/፡፡  
·        ምንም እንኳን ከሰው በፊት ቢፈጠሩም አያረጁም፡፡ ዘወትር ውቦች፣ ብርቱዎችና ውርዙዋን ናቸው፡፡
·        ኢ-መዋትያን ናቸው (አይሞቱም) /ሉቃ.20፡36/፡፡ ይኸውም ልክ እንደ እኛ ነፍስ በእግዚአብሔር ፈቃድ የተደረገ ነው፡፡  
·        እንደ ሰው አንድ ጊዜ ደግ ሌላ ጊዜ ክፉ በመሥራት አይዋልሉም፡፡
ከሰው ምን ያመሳስላቸዋል ስንል ደግሞ፡-
ü ምንም ረቂቃን ቢኾኑም ሕልውና ከአካል ጋር አላቸው፡፡ ዮሐንስ ዘደማስቆ የተባለ አባት ይኽን ሲያብራራው፡- “መላእክት ረቂቃን ናቸው የምንላቸው ከእኛ አንጻር ነው፡፡ ከማንም ጋር ከማይነጻተረው ከእግዚአብሔር አንጻር ሲታዩ ግን ግዙፋን ናቸው፡፡ ፍጹም ረቂቅ እግዚአብሔር ብቻ ነውና” ብሏል፡፡
ü ምንም ረቂቃን ቢኾኑም ውሱናን ናቸው፡፡ እንደ ሰው በቦታ የሚገቱ ባይኾኑም መጠን አላቸው፡፡ መጠናቸውና አርዐያቸውም የተለያየ ነው፡፡ ቁመታቸው ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ መላዕክት አሉ፡፡ በክንፋቸው ብቻ አንድ አገር የሚያለብሱ መላዕክት አሉ፡፡ ራሳቸው ብቻ ተራራ የሚያክሉ መላዕክት አሉ፡፡ በዓይን የተቀረፁ የተሸለሙ ኹለንተናቸው ዓይን የኾነ መላዕክት አሉ፡፡ ስድስት ክንፍ ያላቸው መላዕክት አሉ፡፡ መብረቅ ለብሰው መብረቅ ተጐናጽፈው የሚኖሩ መላዕክት አሉ፡፡ ነፋስ ለብሰው ነፋስ ተጐናጽፈው የሚኖሩ መላዕክት አሉ፡፡ ብሩህ ደመና ጠምጥመው የሚኖሩ መላዕክት አሉ፡፡ እግራቸው ዓምደ እሳት የሚመስል መላዕክት አሉ፡፡ የእነዚኽን መላዕክት አርዓያቸውን መጠናቸውን ከእግዚአብሔር በቀር የሚያውቀው የለም /ኩፋ.2፡7-8/፡፡
ü ዐዋቂዎች ናቸው፡፡ ዕውቀታቸው ግን ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደተናገረው ከሰው እጅግ ከፍ ያለ ነው /2ኛ ጴጥ.2፡11/፡፡ ምንም ከሰው እጅግ ከፍ ያለ ቢኾንም ግን ዕውቀታቸው መጠን አለው፡፡ ከእግዚአብሔርን በቀር ፍጹም ዕውቀት ያለው የለምና፡፡ እኛ ዕውቀታችን እንደ መላእክት የሚኾነ ከትንሣኤ ዘጕባኤ በኋላ ነው /1ኛ ቆሮ.13፡12/፡፡
ü ነጻ ፈቃድ አላቸው፡፡
ü እንደ ሰው ባሕርያቸውን የሚገልጽ ስም አላቸው፡፡
 ሰው ከመበደሉ በፊት ልክ እንደ መላእክት ንጹሕ፣ ውብና ብርቱ ነበር፡፡ በፍጥረታት ላይ ሥልጣን ነበረው፡፡ ርሱ ሲበድል ግን ከሥልጣን የወረደ ሰው እንደ ድሮ የሚያከብረው እንደሌለ ኹሉ ፍጥረታቱ አዳምን አልታዘዝ አሉት፡፡ እንደዉም ተበረታቱበት፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣውም ወደ ቀድሞ ክብራችን ወደ ልጅነት ወደ ቀድሞ ቦታችን ወደ ገነት ከዚያም በላይ ወደ መንግሥተ ሰማያት ሊመልሰን ነው፡፡ በመኾኑም ሰው ምንም እንኳን በዚኽ ዓለም ሳለ ብዙ ውጣ ውረዶችን ቢያሳልፍም በመጨረሻ መላእክትን ይመስላል፡፡ ለዚኽም ነው ቅዱሳን መላእክት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በዕብ.1፡14 ላይ እንደገለጸው ታናሽ ወንድማቸውን ሰውን በማገልገል ላይ ያሉት፡፡

የመላእክት ትክክለኛ ስም ይታወቃልን?

ምንም እንኳን በስም በስም ብንጠራቸውም ስማቸው ነገረ እግዚአብሔርን የሚያስረዳ እንደኾነ እንጂ በቅጥነተ ኅሊና ስናስተውለው ማን ማን እንደሚባሉ አይታወቁም፤ ስም የሌላቸው ኾኖ ሳይኾን የሰው አዕምሮ ሊረዳው አይችልም፡፡ ለምሳሌ ገብርኤል ማለት አምላክ ወሰብእ ማለት ነው፡፡ ይኽም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ማንነትን የሚገልጽ እንጂ የመልአኩ ትክክለኛ ስም አይደለም፡፡ ሚካኤል ማለት መኑ ከመ እግዚአብሔር ማለት እንጂ የመልአኩ ስም አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ የእግዚአብሔር ትክክለኛ ስሙም አይታወቅም፤ የለውም ማለት ሳይኾን ኹለንተናውን የሚገልጽ ስም በሰው ቋንቋ መግለጽ አይቻልም፡፡ 

መላእክት መልክ አላቸውን?

 በመጽሐፍ ቅዱስ ቅዱሳን መላእክት በተለያየ መልክ እንደተገለጹ እናነባለን፡፡ ለምሳሌ፡-
v በእሳት አምሳል /ዘጸ.3፡2-4/፤ ለሙሴ፤
v በዓምደ ብርሃንና ደመና አምሳል /ዘጸ.13፡21፣ 23፡20-21፣ ዘኅ.20፡16/፤ ለሕዝበ እስራኤል፤
v በተራ ሰው አምሳል /መሳ.6፡12-23/፤ ለጌድዮንና ለጦቢት፤
v በነቢይ አምሳል /መሳ.13፡6/፤ ለማኑሄ ሚስት፤
v በእሳት ፈረስና ሰረገላ አምሳል /2ኛ ነገ.6፡16-17/፤ ለኤልሳዕ ሎሌ፤
v በእሳት አምሳል /ሕዝ.8፡2/፤ ለነቢዩ ሕዝቅኤል፤
v በፍታ እንደ ለበሰ፣ ወገቡም በወርቅ እንደታጠቀ ሰው /ዳን.10፡5/፤ ለነቢዩ ዳንኤል፤
v ልክ እንደ ትሑት ሰው /ሉቃ.1፡12-13/፤ ለዘካርያስና ለእመቤታችን፤
v የጌታ ክብር በዙርያቸው ኾኖ /ሉቃ.29-30/፤ ለእረኞች፤
 ይኽም ማለት መላእክቱ ሰው እንዲገባው በሰው አእምሮ መጠን ተገለጡ ማለት እንጂ መልካቸው ተለዋዋጭ ነው፤ የራሳቸው የኾነ ቋሚ መልክም የላቸውም ማለት አይደለም፡፡


የመላእክት ተግባር ምንድነው?

 የመላእክት ተግባር እንደሚከተለው ማየት ይቻላል፡-
Ø ያለማቋረጥ እግዚአብሔርን “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ” እያሉ ያመሰግናሉ /ኢሳ.6/፤
Ø የእግዚአብሔርን መልካም ዜና ወደ ሰው ያመጣሉ፡፡ ይኸውም ለአጋር፣ ለአብርሃም፣ ለሐና እመ ሳሙኤል፣ ለካህኑ ዘካርያስ ለእመቤታችን እንዳመጡላቸው ማለት ነው፡፡
Ø ማስተዋልንና ጥበብን ለሰው ልጆች ያድላሉ፡፡ ይኸውም ቅዱስ ገብርኤል ለነቢዩ ዳንኤል፣ ቅዱስ ዑራኤልም ለዕዝራ እንዳደረጉት ማለት ነው፡፡ 
Ø ሰውን ከጥፋት ያድናሉ፡፡ ይኸውም ሎጥን ከሰዶምና ጐመራ ሰዎች ጋር እንዳይጠፋ /ዘፍ.19/፣ ሠለስቱ ደቂቅን ከሚነድ እሳት እንዳዳኗቸው ማለት ነው /ዳን.3፡12-30/፡፡ መዝሙረኛው ክቡር ዳዊት፡- “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙርያ ይሰፍራል፤ ያድናቸውማል” /መዝ.34፡7/፤ በሌላ ቦታም “ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም መቅሰፍትም ወደ ቤትህ አይገባም፡፡ በመንገድህ ኹሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፡፡ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሱኻል” ያለውም ስለዚኹ ነው /መዝ.91፡10-12/፡፡
Ø ሰውንም መልእክት ወደ እግዚአብሔር ያደርሳሉ፡፡ የሰውን መልእክት ወደ እግዚአብሔር ያደርሳሉ ሲባል ምን ማለት እንደኾነ የቆጵረሱ ሊቀ ጳጳስ ሊቁ ኤጲፋንዮስ በአክሲማሮስ መጽሐፉ ላይ፡-“ (የካህናተ ሰማይ ማዕጠንት) የጻድቃን ጸሎት፤ የሰማዕታት ገድል፤ የደጋግ ሰዎች ምግባር ነው” ብሎ ያብራሯል /መጽሐፈ አክሲማሮስ፣ ገጽ 51/፡፡
Ø የእግዚአብሔርን ቁጣ ወደ ሰዎች ያመጣሉ፡፡ እነርሱም የመዓት መላእክት የሚባሉ ሲኾኑ በትዕቢቱና በክፋቱ ከሥልጣኑ የወረደው የዲያብሎስ ሠራዊት የነበሩና በኋላ ግን አለቃቸው ሲክድ ያልካዱ በእምነታቸው የፀኑ ከሣጥናኤል ሠራዊትነት ተለይተው ከነቅዱስ ሚካኤልና ከነቅዱስ ገብርኤል ጋር የተደመሩት ናቸው፡፡ እነዚኽ የመዓት መላእክት እጅግ ቁጡዎችና ቀናተኞች ናቸው፡፡


ጠባቂ መልአክ

 ክቡር ዳዊት “ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም መቅሰፍትም ወደ ቤትህ አይገባም፡፡ በመንገድህ ኹሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፡፡ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሱኻል” እንዳለው /መዝ.91፡10-12/ እያንዳንዱ ሰው ጠባቂ መላእክት እንዳሉት ያስረዳል፡፡ እስራኤል ዘሥጋን የጠበቃቸው መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡ ይኽንንም ለኢያሱ በኢያሪኮ አጠገብ ነግሮታል /ኢያ.5፡14-15/፡፡ ይሁዳም የመልአኩ ስም ማን እንደኾነ በግልጽ ነግሮናል /ይሁዳ ቁ.9/፡፡
 አስቀድመን እንደተመለከትነው ለእያንዳንዱ ሰው ብቻ ሳይኾን ለእንስሳት፣ ለዕፅዋት፣ ለምድር፣ ለፀሐይ፣ ለጨረቃ፣ ለከዋክብት፣ ከምድርም በታች ለተፈጠሩ ፍጥረታት በሙሉ ጠባቂ መላእክት አሏቸው፡፡ ለምሳሌ እንስሳትን የሚጠብቀው መልአክ ሰላታኤል ይባላል፡፡ አናንኤል የሚባለው ነገደ መላእክት ደግሞ እንደ ብረት የጸና የእሳት ነጐድጓድን ወደ ምድር የሚወነጭፉ፣ ፀሐይን ጨረቃን ከዋክብትን አዝርዕትን አትክልትን ዕፅዋትን ከምድር በላይ ከሰማይ በታች የተፈጠሩትን የሚጠብቁ ናቸው /ኩፋሌ 2፡6-8/፡፡
 ቅዱስ ባሲልዮስ ዘቂሳርያ ሰውን ስለሚጠብቁ መላእክት ሲናገር፡- “ክፉ ሥራ ካልሠራን በቀር ጠባቂ መልአካችን ከእኛ አይለይም፡፡ ጭስ ንብን ከቀፎው እንዲወጣ እንደሚያደርገው ኹሉ የእኛ ኃጢአትም ጠባቂ መልአካችን ከእኛ እንዲለይ ያደርጓል” ብሏል፡፡ 

መላእክት - የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ናቸው!!!

 ቅዱሳን መላእክት የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ብልት ናትና መላእክትም ቤተ ክርስቲያንን ያገለግላሉ፡፡ የጌታችንን ሰው መኾን ያበሰሩን መላእክት ናቸው፡፡ በቤተ ልሔም ግርግም ሲወለድ እጅግ ደስ ብሏቸው ያመሰገኑት መላእክት ናቸው፡፡ ስለ ልደቱ ለእረኞች የነገሯቸው መላእክት ናቸው፡፡ ወደ ግብጽ ሲሰደድ አብረዉት የሔዱ መላእክት ናቸው፡፡ በፈለገ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ተጠምቆ ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ በሔደ ጊዜ ያገለገሉት መላእክት ናቸው፡፡ ጌታችን በጌተሴማኒ የአታክልት ስፍራ ሲጸልይ ሲያበረቱት የነበሩት መላእክት ናቸው፡፡ አይሁድ ሊሰቅሉት ሲሉ ቸርነቱ ከልክሏቸው እንጂ አይሁድን ለማጥፋት የተዘጋጁት መላእክት ናቸው፡፡ ደሙን ወደ ዓለም ኹሉ የረጩት መላእክት ናቸው፡፡ ትንሣኤውን ያበሠሩን መላእክት ናቸው፡፡ ሲያርግ ደግሞም ዳግም እንደሚመጣ የነገሩን እነዚኽ መላእክት ናቸው፡፡ ዳግም ሲመጣ አብረዉት የሚመጡትና ሙታንን የሚቀሰቅሱትም እነዚኽ ቅዱሳን መላእክት ናቸው፡፡

 ይኽ አገልግሎታቸው በሐዋርያትም የተመለከትነው ነው፡፡ ሊቀ ካህኑ ሐዋርያቱን ሲያስራቸው ሰንሰለታቸውን የፈቱላቸው መላእክት ናቸው /ሐዋ.5፡17-20፣ 12፡7-10/፡፡ የገሊላው ንጉሥ ይሁዳ ሐዋርያው ያዕቆብን ከገደለው በኋላ ጴጥሮስንም ሊገድለው ሲል በትል ተበልቶ እንዲሞት ያደረጉት መላእክት ናቸው /ሐዋ.12፡23/፡፡ ፊሊጶስ በሰማርያ እያስተማረ ሳለ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባን አስተምሮ እንዲያጠምቀው የነገሩት ቅዱሳን መላእክት ናቸው /ሐዋ.8፡26/፡፡ ሐዋርያትን እየመሩ፣ አሕዛብንም እያዘጋጁ ወንጌል በአሕዛብ አገር እንዲስፋፋ ያደረጉት ቅዱሳን መላእክት ናቸው /ሐዋ.10/፡፡ እነ ቅዱስ ጳውሎስ መርከብ በአውሎ ነፋስ ቀንና ሌሊት ስትናወጥ አንዲት ነፍስ እንኳን እንደማትጠፋ ያጽናኗቸው ቅዱሳን መላእክት ናቸው /ሐዋ.27፡20-25/፡፡ በአጠቃላይ ቅዱሳን መላእክት ከክርስቶስ ደግሞም ብልቱ ከምትኾን ከቤተ ክርስቲያን (ይኸውም ከእኛ ከምእመናን) አይለዩም፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን እጅግ አድርጐ ይወዳል፡፡ እነዚኽ ቅዱሳን መላእክትንም ጠባቂ አድርጐ ይልክላቸዋል፤ ይልክልናል፡፡   

 በሥራችን ኹሉ ለሚጠብቁን፣ ዘወትር በኃጢአት ስንወድቅ ደግፈው ለሚያነሡን፣ በኃጢአት ስንጨማለቅ “ለዛሬ ተዋት” እያሉ ስለ እኛ መዳን ፈጣሪን ለሚማልዱልን /ሉቃ.13፡7-9/፣ በእኛ ንስሐ መግባት ስለ እኛ በሰማያት ድል ያለ ምስጋና ለሚያቀርቡ /ሉቃ.15፡7/፣ እንቅፋት እንዳይመታን ለሚጠብቁን፣ በርኵሳን መናፍስት አንድም በፈቃደ ሥጋችን ላይ እንድንሠለጥን ለሚራዱን ለእነዚኽ ቅዱሳን መላእክት ውለታ ታድያ እንዴት መክፈል ይቻለናል? እነዚኽን ጠበቃዊቻችን ለሰጠን እግዚአብሔርስ ተመስገን ከማለት በቀር ምን ማለት እንችላለን?  
በረከትና ክብር ጥበብም ምስጋናም ውዳሴም ኃይልም ብርታትም ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ለአምላካችን ይኹን አሜን /ራዕ.7፡12/፡፡

12 comments:

  1. ቃለሕይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  2. ቃለ ህይወት ያሰማልን። ሁሌ ስለ መላዕክት ዜና ብሰማ የማልጠግበው ነው

    ReplyDelete
  3. ቃሌ ሕይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  4. betam teru new bemetam betam betam

    ReplyDelete
  5. ቃለ ሕይወት ያሰማልነን

    ReplyDelete
  6. ቤተክርስቲያን የራሷ የህኑ በጣም ሰፊና ጥልቅ የሆኑ ሚስጥራትን ይዛለች ድንቅ ነው 🥰 ቅል ህይወትን ያሰማልን

    ReplyDelete
  7. ቃለ ሒወት ያሰማልን ብዙ ብዥታ ነው ያጠራልኝ ይሄ ቅዱስ ፅሁፍ እግዚያብሔር ፀጋውን ያብዛልህ

    ReplyDelete
  8. ቃለሕይወት ያሰማለሰን መንግስተ ሰማያትን ያውርስልን የአገልግሎት ዘመን ይርዘም 🙏🙏🙏

    ReplyDelete
  9. ቃለ ሕይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  10. አሜን እግዚአብሔር ይስጥልን ቃለ ሕይወትን ያሰማልን

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount