Thursday, December 25, 2014

ወደ እግዚአብሔር ለመድረስ (ደረጃ ሦስት)



በዲ/ን ሳምሶን ወርቁ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐሙስ ታኅሳስ 16 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!


“እንደ እንግዳ መኖር”
 የተከበራችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች የመንግሥተ እግዚአብሔር ተጓዦች እንዴት ሰነበታችሁ? እነሆ ሦስተኛውን የመንፈሳዊ ሕይወት ደረጃ በምናባችን ዛሬ እንመለከታለን፡፡ አስቀድመን የመጀመሪያውን የመንፈሳዊ ሕይወት ደረጃ ጀርባችንን ለዓለም በመስጠት ጀምረናል፡፡ በመንገዱ ያሰበበት ለመድስ የሚጓዝ አሽከርካሪ በመንገድ እንዳይቀር በየደረሰበት ከተማ ነዳጅ እንደሚሞላ እኛም ተስፋ ወደምናደርጋት መንግሥተ እግዚአብሔር እስክንደርስ ድረስ በየደረጃዎቹ ላይ የምናገኛቸውን የቃለ እግዚአብሔር ስንቅ እየቋጠርን እንጓዛለን፡፡ በባለፈው ጽሑፍ “ከዓለማዊ መሻት መለየት” ሁለተኛውን የመንፈሳዊ ሕይወት ደረጃ ተመልክተናል፡፡ ከዓለማዊ መሻት መለየት በዓለም ካለው አላፊ ጠፊ ከሆነው ከገንዘብ ከሥልጣን ከዕውቀት ፍቅር ተለይተን፤ በምድር ላይ ስንኖር አለን የምንለው ነገር ሁሉ ከእኛ እንዳልሆነ አውቀን፤ ከራስ ወዳድነት ርቀንና ከውዳሴ ከንቱ ተለይተን መኖር ማለት መሆኑን ተመልክተናል፡፡

ሦስተኛው የመንፈሳዊ ሕይወት ደረጃ ስለ መንፈሳዊ ስደት፤ መጻተኛነትን ያስመለክተናል፡፡ ስለዚህም ሦስተኛው የመንፈሳዊ ሕይወት ደረጃ “እንደ እንግዳ መኖር”  ሲል ቅዱስ ዮሐንስ ይገልጸዋል፡፡ እንደ እንግዳ መኖር ማለት ምን ማለት ነው? ለልማዱ እንግዳ በእንግድነት በሄደበት ቤት ሊውል ሊያድር ሊሰነብት ይችላል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን በእንግድነት በሄደበት ቤት እስከ እድሜ ዘመኑ ፍፃሜ አይኖርም፡፡ ሰው በዚህ ዓለም ሲኖር ከፊሉ በህፃንነት፣ ከፊሉ በወጣትነት፣ ከፊሉ በጉልምስና፣ ከፊሉ በእርጅና ዘመኑ በዚህ ዓለም የነበረውን የእንግድነት ዘመኑን ፈጽሞ በሞት ይወሰዳል፡፡ ማንም ቢሆን በዓለም ብዙ ዘመን በመቆየቱ በሞት የተረሳ የለም፡፡ ስለዚህ እንደ እንግዳ መኖር ማለት የምንኖርበት ዓለም ዘላለማዊ አለመሆኑን ተረድተን እንደሚገባ መኖር ማለት ነው፡፡ “ወዳጆች ሆይ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች እንደመሆናችሁ እለምናችኋለሁ” /1ጴጥ. 2፤11/፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት መጻተኛ ስደተኛ በሄደበት አገር ቤት ልስራ፣ ዘር ልዝራ አይልም እንደ ማንም ተጠግቶ ይኖራል፤ እናንተም ሥጋችሁን በነፍሳችሁ አስጠግታችሁ ኑሩ ሲሉ እግድነትን ይተረጉሙታል፡፡
 እንግዳ በእንግድነት በሄዱበት ቤት የቱንም ያህል በተመቸ ሁኔታ ለጊዜው ቢስተናገድ ኋላ ላይ በነፃነት የፈቀደውን ሁሉ የሚያደርግበት ቤቱን መናፈቁ አይቀሬ ነው፡፡ እኛም በምንኖርበት ዓለም የቱንም ያህል በተመቸ ሁኔታ እንኳ ብንኖር የኛ የምንለው ፍጹም ዕረፍት ሰላም የምናገኝበትን ለዘለዓለም የምንኖርበትን የእግዚአብሔርን መንግስት ነፍሳችን ትናፍቃለች፡፡ ስለዚህ እንደ እንግዳ መኖር ማለት ዘለዓለማዊውን፤ እግዚአብሔር ለኛ ያዘጋጀልንን፤ እኛ እንደሚገባ ከተመላለስን በኃላ ላይ የኛ የሚሆነውን መንግሥተ እግዚብሔርን እየናፈቁ መኖር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እኛ አገራችን በሰማይ ነውና ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንጠባበቃለን” /ፊሊ. 3፡20/ የሚለን፡፡
ዛሬ ላይ ሆነን ዕለት ዕለት ሰው በሰው ላይ የሚፈጽመው ግፍና ጭካኔ መንስኤው ልዩ ልዩ ቢሆንም በዋነኝነት እንግድነቱን ሞቱን መዘንጋቱ ወይም አለማወቁ ነው፡፡ እንግዳ መጻተኛ በሄደበት በተሰደደበት ሀገር ገንዘቡን ቋጥሮ ወደ ቤቱ ወደ ሀገሩ መመለስን ያስባል እንጂ በተሰደደበት ሀገር ሀብት ጥሪቱን አያፈስም፡፡ ነገር ግን መጻተኛነታቸውን  የዘነጉ፤ ያላወቁ ብዙዎች ሀብት ዕውቀት ጊዜያቸውን ወደ ዘለዓለማዊ ቤታቸው እስኪመለሱ በሰማያዊ መዝገብ ከማኖር ይልቅ የዚህ ዓለም ሥልጣን ገንዘብ ዝናን… አስበልጠው በስደት በመጡባት ዓለም ጥሪታቸውን ይጨርሳሉ፡፡ “ያላችሁን ሽጡ ምጽዋትም ስጡ ሌባ በማይቀርብበት ብልም በማያጠፋበት በሰማያት የማያልቅ መዝገብ የሚሆኑትን የማያረጁትንም ኮረጆዎች ለራሳችሁ አድርጉ” /ሉቃ. 12፡33/፡፡
ዛሬ ላይ ሰዎች እንደ እንግዳ እንዳይኖሩና እንግድነታቸውን እያስረሳቸው ያለ ምንድን ነው?
፩. ከፍቅረ እግዚአብሔር የቀደመ የቤተሰብ ፍቅር  
የቤተሰብ መሠረቱ ጋብቻ ነው፡፡ ጋብቻ ደግሞ ባልና ሚስት ሰማያዊ ቤታቸውን የሚያንጹበት የቅድስና ሕይወት ነው፡፡ ክርስቲያን ደግሞ ቤተሰቡን ይወዳል ይንከባከባል፡፡ በጋብቻ ውስጥ ልጆች ይወለዳሉ፡፡ ወላጆቻቸው በልዩ ፍቅርና እንክብካቤ ያሳድጓቸዋል፡፡ ከዚህም የተነሳ ልጆችም በአንጻሩ ለወላጆቻቸው ልዩ ቤተሰባዊ ፍቅር ያዳብራሉ፡፡ በልጆችና በወላጆች መካከል ፍቅር ሲኖር ቤተሰቡ በፍቅር ይሞላል፡፡ ከዚህ በተለየ ግን በቤተሰብ ውስጥ ያለ ፍቅር ልጆችንም ሆነ ወላጆችን እንግድነታቸውን ካስረሳቸው እግዚአብሔርን ከመከተል ካዘገያቸው ትልቅ የመንፈሳዊ ሕይወት ተግዳሮት ይሆናል፡፡ “አባት እናቱን ከእኔ አብልጦ የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም” /ማቴ. 10፡37/፡፡
 ብዙ ጊዜ ደግሞ ከእግዚአብሔር በፊት ቤተሰባችንን ስናስቀድም ለማወቃቸን ችግሩን የከፋ ያደርገዋል፡፡ በእርግጥ ሰው ቤተሰብ ሲመሠርት እንደቀድሞ ዕለት ዕለት በአገልግሎት በጸሎታት መሳተፍ ለጊዜውም ቢሆን በመጠኑ መቀነሱ ጤናማ ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ በተለየ በሰንበት እንኳን ወደ ቤተክስቲያን መምጣት ከተሳነው የጥዋት የማታ ጸሎቱን ካስታጎለ በእውነት ተዘክሮተ እግዚአብሔርን አቁሟልና ለቤተሰቡ ያለው ፍቅር  እንግድነቱን አስረስቶታል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከእግዚአብሔር በፊት ያስቀደምናቸው ለቤተሰባችን የምንሰጠው ፍቅር እንግድነታችንን አስረስቶ ሰማያዊ ቤታችንን ሊያስረሳን ስለሚችል ልንጠናቀቅ ይገባል፡፡
፪. ከፍቅረ እግዚአብሔር የቀደመ የባልንጀራ ፍቅር
ባልንጀራን እንደራስ መውደድ የሚገባ  ነው፡፡  ነገር ግን በጓደኝነታችን ውስጥ እግዚአብሔር ካልከበረ፣ እርሱ ካልቀደመ የእንግድነት ሕይወታችንን ሊያዘናጋን ይችላል፡፡ “አትሳቱ ክፉ ባልጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋዋል” /1ቆሮ 15፡33/፡፡ ከቤተሰቦቻችንም ሆነ ከባልንጀሮቻችን መካከል ያለው ግንኙነት እንደሚገባ ሊሆን ይገባል፡፡ አንዳንዶች ለምን እንደሚገባ በክርስቲያናዊ ሕይወት አትመላለሱም ተብለው ሲጠየቁ ምን ላድግ እሱን ለማን ትቼ? እርሷን ለማን ትቼ? “ስለፍቅር ሁሉ ይቅር”  በማለት “ፍቅር” በሚመስል ባልተገባ መስዋዕትነት ለእግዚአብሔር ካአላቸው ፍቅር ይልቅ ለባልንጀራቸው ያላቸው  ፍቅር ይቀድምባቸዋል፡፡ ለብዙዎች ቀላል መስሎ ይታያቸዋል፡፡ ነገር ግን ለኛ ለጊዜው መልካም መስሎ የሚታየን ነገር ግን በሕይወታችን እግዚአብሔርን ሁለተኛ እያደረገ ለእርሱ ልንሰጥ የሚገባውን ቦታ እየወሰደብን ያለው ነገር ኋላ ላይ እንግድነታችንን አስረስቶ በመንግስተ እግዚአብሔር መኖሪያ እንዳያሳጣን ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡
ታዲያ እንደእንግዳ ለመኖር ምን እናድርግ?
ከእግዚአብሔር ከሚለየን የቱንም ዓይነት ግንኙነት በብቸኝነት መኖር በእጅጉ የተሻለ ነው፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቦታ ፈቅደንም ሆነ ሳንፈቅድ የወሰዱብን ሰዎች ላይ መፍረድ አይገባም፡፡ ምክንያቱም እነርሱ የኛን የእምነት ደረጃ በልቡናችን ውስጥ የሚቀጣጠለውን ለእግዚአብሔር ያለንን መሻት ሊረዱት አይችሉምና፡፡ ስለዚህ አንዳንዴ ከምንወዳቸው ወዳጆቻችን ሳይቀር እግዚአብሔርን በማስቀደማችን የሚመጣብንን ነቀፋ ባስ ሲል ስድብ በጸጋ ልንቀበል ይገባል፡፡ ከዚህ በተለየ በዋነኝነት እንደ እንግዳ ለመኖር እንደ ሊቀ ነቢያት ሙሴ መጻተኛነትን በእምነት ልንመርጥ ያስፈልጋል ፡፡ “ሙሴ ከተወለደ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ” /ዕብ.11፡24/፡፡ ሙሴ የፈርዖን ልጅ መባልን እምቢ ብሎ ስደተኛ፤ መጻተኛ፤ እንግዳ መባለን መረጠ፡፡ ሀገሩ ርስቱ ግብጽ አይደለችምና በእምነት ከፀና እግዚአብሔር ያዘጋጀለትን ምድረ ርስትን እንደሚወርስ አምኗልና እንግድነትን መረጠ፡፡ እኛስ እግዚአብሔር መንግስቱን እንደሚያወርሰን አምነነዋልን? ዳግም ወደ ቤታችን ስንመለስ በደስታ እንደሚቀበለን እናምናለን? /ሉቃ.15፤22/፡፡ ካመንን መጻተኝነትን እንምረጥ፤ በእንግድነትም እንኑር፡፡ ምክንያቱም እኛ ከዓለም አይደለንምና “ከመረጥኋችሁ እንጂ ለዓለም ስለ አይደላችሁ” /ዮሐ.15፡19/፡፡ ስለዚህ እኛን ለጊዜው ደስ የሚያሰኙን ከቤተሰብ ከባልንጀራ ጋር ያለንን ግንኙነት የቱን ያህል ወደ እግዚአብሔር እየመሩን እንደሆነ ቆም ብለን ልንመረምር ይገባል፡፡ ይህ ደረጃ ሦስት ነው፡፡ የልቦናችንን እግር እናበርታ፤ መንገደኞች ነንና፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

1 comment:

FeedBurner FeedCount