Friday, December 19, 2014

የንስሐ ልጆቼን እንዴት ላገልግል? (የመጨረሻው ክፍል)

በዳዊት አብርሃም
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ቅዳሜ ታኅሳስ 11 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የጽሑፉ ምንጭ፡- ሐመር መጽሔት፥ የግንቦት 2005 ዓ.ም. እትም ነው፡፡
ኃጢአትን በመናዘዝ ውስጥ የሚገኝ ፈውስ
ከኃጢአት እስራት በንስሐ ለመፈታት ፈልጐ ወደ ካህኑ የሚቀርብ ተነሳሒ የሚታይበትና ከዚያም በሒደት አልፎበት በመጨረሻ የሚደርስበት የመንፈስና የሥነ ልቡና ኹኔታ አለ፡፡ ይኽንን ኹኔታ ቀሲስ ፋሲል ታደሰ እንደሚከተለው ይገልፁታል፡፡
ደረጃ አንድ
ተነሳሒው ለመዠመሪያ ጊዜ ሲመጣ የተረበሸ ኹኔታ ፊቱ ላይ ይነበባል፡፡ ቁጣ ቁጣ የሚለው የዘለፋና ወቀሳ የሚያበዛ ለራሱ የሰጠውን ዝቅተኛ ግምትና ውስጡ ያደረውን ታላቅ ተስፋ መቁረጥ ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ኹኔታዎች ከገጽታው ይነበባል፤ ካንደበቱ ይደመጣል፡፡

ደረጃ ኹለት
ቀስ በቀስ በካህኑ ርዳታ እውነተኛ ማንነቱን መናዘዝ ይዠምራል፡፡ በዚኽ ጊዜ ፊቱ ላይ ያጠላው ጥልቅ የመታወክ ስሜት ሲገፈፍ ያስታውቃል፡፡ አብዛኛው ተነሳሒ በዚኽ ሰዓት እንባውን መግታት አይችልም፡፡ ያገኘው የተለየ መድኃኒት ኖሮ አይደለም፤ ኾኖም የሚያደምጠው ሰው ማግኘቱ በራሱ ትልቅ እፎይታን ይፈጥርለታል፡፡ 38 ዓመት ሙሉ የአልጋ ቁራኛ የነበረው መጻጉዕ ጌታ ቀርቦ ባነጋገረው ጊዜ አንዳች ነገር እንደሚያገኝ ስለተሰማው “ሰው የለኝም” ብሎ ዠምሮ ችግሩን እንደዘረዘረው ዓይነት በኑዛዜ ላይ ያለውም ሰው በተመሳሳይ መልኩ ተስፋ ማጣቱን በተስፈኝነት እየተካ የደበቀውን ኹሉ እያወጣ የልቡን ይናገራል፡፡
ደረጃ ሦስት - ምሕረት በማግኘት የሚገለጥ ደስታ
 ብዙዎች ተነሳሕያን “አኹን እኔ ይቅርታን አገኛለኹ” የሚል ሐሳብ አላቸው፡፡ ብዙዎች የነርሱ ኃጢአት ከሌላው ሰው ኹሉ የከበደ ስለኾነ “አንተማ/ አንቺማ በቀላሉ አትማርም/ አትማሪም፤ ስለዚኽ ዓመታትን የሚፈጅ ልዩ ቀኖና ገዳም ሔደህ/ ሔደሽ መፈጸም አለብህ/ አለብሽ” የሚል ቃል ወይም ከዚኽ የከበደ ነገር ይጠብቃሉ፡፡ ኾኖም የነርሱ ኃጢአት የቱንም ያኽል ቢበዛ የእግዚአብሔርን ቸርነት እንደማያልፍና፤ የእግዚአብሔር ቸርነትም የትኛውንም ኃጢአት ማጥፋት እንደሚችል ሲሰሙ ከላያቸው የነበረ ሸክም እንደወደቀላቸው ያኽል ነፃ ሲኾኑና ፊታቸው ሲያበራ ይታያል፡፡
ደረጃ አራት
ቀጥሎ ካህኑ የእግዚአብሔርን ቃል ሲነግራቸው የሚያገኙት ታላቅ መጽናናት ነው፡፡ በርግጥም የእግዚአብሔር ቃል ኃጢአተኞችን በሚያስደንቅ ኹኔታ አጽናንቶ ፍጹም ይፈውሳቸዋል፡፡ “መጽሐፍ ቅዱስ አያውቀውም” ብለው ያሰቡት ኃጢአት ከመጽሐፍ ቅዱስ ይነበብላቸዋል፡፡ የነርሱ ዓይነት ሕይወት የነበራቸው ሰዎች ታሪክ ከመጽሐፍ ቅዱስ ይተረክላቸዋል፡፡ ይኽም የተቆረጠ ተስፋቸው እንዲያነሰራራ ያደርገዋል፡፡
ደረጃ አምስት - ለበለጠ መንፈሳዊ እድገት ሲታጩ
“ከኃጢአቴ አልነጻም” ብሎ ያስብ የነበረውን ሰው “ሥጋ ወደሙን መቀበል ትችላለህ” ሲባል ስለራሱ እየተነገረ መኾኑን እንኳን ማመን አቅቶት ግር ይለዋል፡፡ በዝሙት አዳሪነት ሕይወት ውስጥ የነበረች ሴት “ቤተ ክርስቲያን መግባት አልችልም” ብላ ልታስብ ትችላለች፡፡ “መቁረብ ትችያለሽ” ስትባል የሚሰማትን ደስታ መግለጽ ይቸግራል፡፡

 ሰውነታቸውን ረስተው ራሳቸውን ክፉኛ የጠሉና የናቁ ወገኖች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተለያየ አገልግሎት እንዲሳተፉ ስናደርጋቸው ለራሳቸው የሚሰጡት ግምት ይስተካከላል፡፡ ሰብአዊ ክብራቸውን መልሰው ያገኙታል፡፡ ደስታቸው ዘላቂና ፍጹማዊ (የማይዋዥቅ) ይኾናል፡፡ ለውጡ ግልጽ ነው፤ ከገጽታው ዠምሮ ልዩነቱ የሚታይ ነው፡፡ ጠውልጐ የነበረው ገጽታ የሚያበራ ይኾናል፡፡ ተስፋ ቢስ የነበረው ሰው በተስፋ ይሞላል፡፡ በሱስ፣ በዝሙትና በበካናነት የነበረው ራሱን የሚጠብቅ ጤነኛና ጠንካራ ሰው ይኾናል፡፡ በኢኮኖሚ ደቆ የነበረው በገንዘቡ ላይ ሥልጣን ያለው፣ በመጠን የሚኖር፣ ቆጥቦ ሌሎችን እስከ መርዳት የሚደርስ ኾኖ ይገኛል፡፡ ከንስሐ በፊትና በኋላ ያለው የሕይወት ለውጥ በግልጽ የሚታይ ነው፡፡††† 

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount