በዳዊት አብርሃም
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ማግሰኞ ኅዳር 30
ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
አሜን!!!
የጽሑፉ ምንጭ፡-
ሐመር መጽሔት፥ የግንቦት 2005 ዓ.ም. እትም ነው፡፡
የንስሐ አባቶችን ሚና የሚያወሱና አገልግሎታቸውን የሚዘረዝሩ የሥርዓተ ቤተ
ክርስቲያን መጻሕፍት በተለይ ካህናት ምእመናንን የመጠበቅ የእረኝነት ተግባራቸው ላይ ያተኩራሉ፡፡ ካህናት ምእመናንን ቃለ እግዚአብሔር
መመገብ አለባቸው፤ ይኸውም በአደባባይ መስበክን የሚመለከት ሲኾን ከዚኹም ጋር በግል ለእያንዳንዱ የንስሐ ልጃቸው ምክር አዘል የኾነ
ቃለ እግዚአብሔርን ማካፈልን ይጨምራል፡፡
የንስሐ አባቶች ለልጆቻቸው በግል የሚሰጡት አገልግሎት ጌታችን በወንጌል፡-
“መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋበት ዘጠና ዘጠኙን በበረኻ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሔድ ማን ነው?”
/ሉቃ.15፡5/ ያለው ቃሉን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ካህናት ከእግዚአብሔር በአደራ እንዲጠብቁ የተሰጣቸውን ኹሉንም ሳይዘነጉ እያንዳንዱን
በነፍስ ወከፍ ሊጠብቁና ሊያገለግሉ ይገባቸዋል፡፡
“ሕዝብ በበዛበት በአደባባይ መስበክ ለካህኑ ዋና ተግባሩ ነው ብለን ነበር፤
ነገር ግን ይኽ ብቻ በቂ አይኾንም፤ እንዲኹ ለእያንዳንዱ የተለየ ርዳታ የተለየ ጥበቃ ሊደረግና በግል ሊሰበክ ይገባል፡፡ ሊቀ ካህናት
ክርስቶስ እንዲኹ በአደባባይ ብቻ አያስተምርም ነበር፡፡ ነገር ግን እንደ ዕድሜያቸው እንደየፍላጐታቸው ለእያንዳንዱ የተለየ ርዳታ
ያደርግ ነበር፡፡ ከሱም በኋላ የተነሡ መምህራን እንዲኹ ሥራቸውን በማኅበር በአደባባይ በግልም ለእያንዳንዱ ያደርጉ እንደነበር የታወቀ
ነው፡፡” /ትምህርተ አበ ነፍስ፣ ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ገጽ 110-111/፡፡
ይኽ የንስሐ አባትነት ተግባር በዘመናችንም ያልተቋረጠ መኾኑ
እሙን ነው፡፡ ችግሩ የሚነሣው የንስሐ አባቶች ከንስሐ ልጆቻቸው ጋር የሚፈጥሩት ግላዊ ግንኙነት ከቤተሰባዊነት ያልተሻገረ ኾኖ ሲቀነጭር
ነው፡፡ ብዙ ካህናት ወደ ምእመናን ቤት መጥተው ሲያበቁ መስቀል ከማሳለምና ጠበል ከመርጨት ያለፈ አገልግሎት አይሰጡም፡፡ ካህናት
ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንዳስቀመጠላቸው ከሥራቸው ኹሉ ቅድሚያውን ሰጥተው ማስተማር፣ መምከር፣ ኑዛዜን መቀበል፣ ማጽናናትና መገሰጽ
ይገባቸዋል፡፡ እያንዳንዱ የንስሐ ልጃቸውን በጥንቃቄ ይዘው ለሥጋ ወደሙ ማብቃት ግባቸው ስለኾነ ትኩረታቸው ኹሉ ወደዚኽ ዋነኛ የክህነት
ዓላማቸው መሰብሰብ ይኖርበታል፡፡
በዚኽ ጽሑፋችን ካህናት ኾነው ሳለ ወደ ልዩ ልዩ ሥራዎችና አገልግሎቶች አዘንብለው
የአበነፍስነት ተግባራቸውን ችላ ያሉ ካህናትን ለማንቃት ያስችለን ዘንድ የመልካም ልምድ ባለቤት የኾኑ አባቶችን አብነት ነሥተን
እናያለን፡፡ ከዚያ ቀድመን ግን ችግሩን በመጠኑ እንዳስሳለን፡፡
የንስሐ አባት
ማግኘት
በርካታ ታላላቅ አድባራትና ገዳማት በሚገኙባት አዲስ አበባ ከተማ የሚገኙት
ካህናት በቁጥር ምን ያኽል የበዙ መኾናቸውን የሚያውቅ ሰው በዚኽች ከተማ ውስጥ የንስሐ አባት ማግኘት የቸገራቸው ሰዎች ይኖራሉቢባል
ትልቅ ተቃርኖ ይመስለው ይኾናል፡፡
መጋቢት 7 ቀን 2005 ዓ.ም. የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን
ሰንበት ትምህርት ቤት ወደ አቡነ መልከ ጼዴቅ ገዳም አዘጋጅቶት በነበረው መንፈሳዊ ጉዞ ላይ አባላቱ ስለ ንስሐ አባትና ልጅ ግንኙነት
ውይይት አድርገው ከውይይቱ የተገኘው ውጤት ፍጹም ባልተጠበቀ ኹኔታ ይኽን ችግር የሚያሳይ ነበር፡፡ በተለይ የሰንበት ትምህርት ቤቱ
የመዠመሪያ ዓመት ተማሪዎች መካከል ብዙዎቹ የንስሐ አባት ማግኘት ግራ የሚያጋባ ሒደት እንደኾነባቸው ገልጸዋል፡፡
አባት ማግኘት የቻሉት እንኳን በአጋጣሚ በጓደኛ በኵል እንዳገኙ የገለጹ ሲኾን
መፍትሔውንም በተመለከተ ለቀረበው ጥያቄ ከተሰጡት ሐሳቦች መካከል የችግሩ ሰለባ የኾነች አንዲት ወጣት ማንኛውም ክርስቲያን የንስሐ
አባት ማግኘት ሲፈልግ አገልግሎቱን የሚያገኝበት ቢሮ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ሊከፈት ይገባዋል ያለችውን አወያዮቹ ያስታውሳሉ፡፡
አንድ ለስንት?
የንስሐ አባት ማግኘት
ይኽን ያኽል ሲቸግር በሌላ በኵል ደግሞ አንዳንድ አባቶች የንስሐ ልጆቻቸው ቁጥር ከመጠን በላይ ብዙ ከመኾኑ የተነሣ የንስሐ አባትና
ልጅ የመኾኑ ምክንያት ምን ይኾን? የሚል ጥያቄን የሚያጭር ይኾናል፡፡ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከኾነ ከ1,000 በላይ
የንስሐ ልጆች ያሉዋቸው ካህናት አሉ፡፡ ይኽ ኹኔታ ምን ችግር አስከትሏል? በሚል ሐሳብ ተነሣስተው ቀሲስ ፋሲል ታደሰ በግላቸው
ባካሔዱት ጥናት መጠይቅ ከቀረበላቸው ካህናት መካከል አንደኛው የሰጡት ምላሽ የሚያሳየው ካህኑ 500 የንስሐ ልጆች ያሉዋቸው ሲኾን
ከነዚኽም መካከል ለንስሐ ያበቁዋቸው 105 ያኽሉን ብቻ ነው፡፡
ቁጥሮች ይናገራሉ
ይኽ መጠይቅ በ2001 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በተለያዩ አጥብያዎች ለሚገኙ ንስሐ
አባት ላላቸው ለአንድ መቶ ምእመናን ለቀረቡ መጠይቆች የተሰጡ ምላሾች ቁጥሩ የመላሾች ብዛት ያመለክታል፡-
1. ንስሐ አባትዎ የቤተ ሰብዎን አባላት ያውቃሉ?
·
በመጠኑ ያውቃሉ= 40
·
በአግባቡ ያውቃሉ= 12
·
አያውቁም= 48
2. ከንስሐ አባትዎ ትምህርት ያገኛሉ?
·
አላገኝም= 76
·
በመጠኑ አገኛለኹ= 14
·
በሚገባ አገኛለኹ= 10
3. ከንስሐ አባትዎ ጋር በይበልጥ ምን ይነጋገራሉ?
·
ስለ መንፈሳዊ ሕይወት= 23
·
ስለ ማኅበራዊ ኑሮ= 66
·
ስለ ሌሎች ጉዳዮች= 11
4. ንስሐ አባትዎ እርስዎንና ቤተሰብዎን ይከታተላሉ?
·
በአግባቡ ይከታተላሉ= 9
·
በመጠኑ ይከታተላሉ= 13
·
አይከታተሉም= 78
5. ርስዎ ንስሐ አባትዎ ጋር በቅርቡ (ቶሎ ቶሎ) ንስሐ እየገቡ ነው?
·
አዎ በየቅርቡ ንስሐ እገባለኹ= 15
·
ገብቼ አላውቅም= 68
·
አልፎ አልፎ እገባለኹ= 17
በአጠቃላይ በ100 ምእመናን ላይ የተሠራው መጠነኛ ዳሰሳ ሙሉ ለሙሉ ችግሮችን
ባይወክልም ማሳያ ግን ሊኾን ይችላል፡፡ ይኽ የሚያመለክተው የበርካታ ካህናት አደራ አለመወጣት እና የምእመናንንም የዕውቀት ማነስ
እና ቸልተኝነት ነው (ቀሲስ ፋሲል ታደሰ፣ 2001 ዓ.ም.፣ የቀበና ምሥራቀ ፀሐይ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌል
ሓላፊ)፡፡
ይቀጥላል…
No comments:
Post a Comment