Tuesday, December 23, 2014

ትምህርተ ሃይማኖት (ክፍል ስድስት)



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ማግሰኞ ታኅሳስ 14 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!


መ) ዶግማ እና ቀኖና
 ውድ የመቅረዝ ተከታታዮች! እንዴት አላችኁ? ትምህርተ ሃይማኖት በሚል ርእስ መማማር ከዠመርን የዛሬ ስድስተኛው ክፍል ነው፡፡ ባለፉት አምስት ተከታታይ ትምህርቶች የሃይማኖት ትርጕም፣ ሃይማኖት ያላቸው ፍጥረታት፣ የሃይማኖት አስፈላጊነት፣ ኦርቶዶክስና ተዋሕዶ ስለሚሉ አገላለጾች፣ ስለ ነገረ ቤተ ክርስቲያን፣ ስለ ቅዱስ ትውፊት እንዲኹም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ኦርቶዶክሳዊ አረዳድ ተመልክተናል፡፡ ለዛሬ ደግሞ ከመግቢያው የመጨረሻ ስለኾነው ስለ ዶግማና ቀኖና እንማማራለን፡፡ ቢቻላችኁ ለማንበብ በቂ ጊዜ ሰጥታችኁና ተረጋግታችኁ ብታነቡት መልካም ነው፡፡ እግዚአብሔር ዓይነ ልቡናችንን ያብራልን፡፡ አሜን!!!
 
በቤተ ክርስቲያን የሚሰጠው ትምህርት በኹለት ትምህርቶች የሚጠቃለል ነው፡፡ ዶግማ እና ቀኖና ተብሎ፡፡
1. ዶግማ
 ዶከይን ከሚለው የግሪክ ቃል የተገኘ ሲኾን በጥሬው አመለካከት፣ አስተሳሰብ፣ አዋጅ ማለት ቢኾንም በምሥጢራዊ ማለትም በቤተ ክርስቲያናዊ ትርጓሜው ግን ሃይማኖት (የእምነት መሠረት) ማለት ነው፡፡ በመኾኑም ዶግማ የተደነገገ ሳይኾን የተገለጠ ነው፡፡ መገኛውም እግዚአብሔር ነው፡፡ ከሰው ሊፈጠር አይችልም፡፡ ከእግዚአብሔር የተሰጠ እውነት ነው፡፡ በማኝኛውም አካል (በሲኖዶስም ጭምር)፣ በየትኛውም ዘመን፣ በየትኛውም ኹኔታ (በሞትም በሕይወትም) የማይለወጥ ማንነት አለው፡፡
 ዶግማ የቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ ትምህርተ ሃይማኖት ነው ብለናል፡፡ ስለ ቅድስት ሥላሴ፣ ስለ ምሥጢረ ሥጋዌ (ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው መኾኑን፣ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልና ተጸንሶ በድንግልና እንደተወለደ፣ እንደ ተሰቀለ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ እንደተነሣ፣ ዳግመኛ በክበበ ትስብእት እንደሚመጣ)፣ ስለ መንፈስ ቅዱስ፣ ስለ ምሥጢረ ጥምቀት፣ ስለ ምሥጢረ ቁርባን፣ ስለ ቤተ ክርስቲያንና ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን፣ ስለ ክብረ ድንግል ማርያምና ክብረ ቅዱሳን የምንማው እንጂ ማናችንም ልናሻሽለው አንችልም፡፡ እንኳንስ አንድ ግለሰብ ይቅርና ሲኖዶስም ቢኾን አለመለወጡን፣ አለመፋለሱን ይመረምራል እንጂ መጨመር ወይም መቀነስ አይችልም፡፡ ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “ነገር ግን (ሐሳባችንን ቀይረን) እኛ ብንኾን ወይም ከሰማይ መልአክ ከሰበክንላችኁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን የሚሰብክላችኁ የተረገመ ይኹን” ያለውም ስለዚኹ ነው /ገላ.1፡8/፡፡
2. ቀኖና
 ቀኖና ማለት ሕግ፣ ሥርዓት፣ ደንብ፣ ፍርድ፣ ቅጣት፣ መጠን፣ ልክ ማለት ነው /ኪዳነ ወልድ ክፍሌ (አለቃ)፣ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፣ ገጽ 799/፡፡ በግሪኩ ካኖን ሲኾን በዕብራይስጡ ቃኒህ ይሉታል፡፡ ይኸውም አንድን ነገር ለመለካት፣ ለመመዘን፣ ትክክል መኾኑንና አለመኾኑን ለመለየት፣ መጠኑን ለማወቅ የሚያገለግል መለኪያ ወይም መስፈርት ነው፡፡
 ማኅበረ ሰብእ እስካለ ድረስ ሕግ አለ፡፡ ሕግ እንዲኖር የኹለት ሰዎች በአንድ ላይ መኖር በቂ ነውና፡፡ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ “አሐቲ ጕባኤ” እንዲል የምእመናን ስብስብ ስለኾነች የራሷ ሕግ አላት፡፡ አባቶች “ያልተገራ ፈረስ የባለቤቱን ጥርስ ይሰብራል” እንደሚሉት ይኽ የምእመናን ስብስብ ሰላማዊ እንዲኾን የሚያደርገው የቤተ ክርስቲያን ሕግ ወይም ሥርዓትም ቀኖና ይባላል፡፡
  ጠቅለል ባለ መልኩ ስንመለከተው ሕግ ኹለት ዓይነት ነው፤ ተፈጥሮአዊ ሕግና የስምምነት ሕግ፡፡ የተፈጥሮ ሕግ የምንለው የእግዚአብሔርን ሕግ ነው፡፡ ሰዎች ይኽን የእግዚአብሔር ሕግ ሊለውጡት አይችሉም፡፡ ለምሳሌ ወንድ ከሴት ጋር መጋባት አምላካዊ ሕግ ነው፡፡ ግብረ ሰዶማዊነትም ይኽን የተፈጥሮ ሕግ የሚቃረን ነው፡፡ ፈረስና አህያ ተዳቅለው በቅሎን ይወልዳሉ፡፡ ነገር ግን በቅሎ ራሷን መተካት አለመቻሏ ከሕገ ተፈጥሮ ውጪ የተወለደች መኾኗን ነው የሚነግረን፡፡ ጦጣና ዝንጀሮ ተዳቅለው የሚወልዷቸው እንስሳትም አሉ፡፡ ነገር ግን ልክ እንደ በቅሎ ራሳቸውን መተካት አይችሉም፡፡ ለምን? ስንልም ከሕገ ተፈጥሮ ማለትም ከእግዚአብሔር ሕግ ውጪ የተወለዱ ናቸውና፡፡ ስለዚኽ ተፈጥሮአዊ ሕግጋትን ተቃርነን የምናደርጋቸው ነገሮች ትርፉ ድካምና በራስ ላይ ጉዳትን መጨመር ብቻ ነው የሚኾነው፡፡
 የስምምነት ሕግ የምንለው ደግሞ በፓርላማ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በቤተ ክርስቲያን ደግሞ በቅዱስ ሲኖዶስ የሚወጣውን ሕግ ማለታችን ነው፡፡ ምንም እንኳን የስምምነት ሕግ ብለን ብንጠራውም ቅዱስ ሲኖዶስን የሚመራው መንፈስ ቅዱስ ስለኾነ እንዲኹ የሰዎች ስምምነት ነው ብለን የምንወስደው ወይም ዝቅ አድርገን የምንመለከተው አይደለም፡፡ እነዚኽ ሕጎች ኹለት መሠረታዊ ጠባያት አሏቸው፡፡ ጥቅል ወይም ዝርዝር ሕጎች ሊኾኑ ይችላሉ፡፡
  የስምምነቱ ሕግ ጊዜያዊም ለረዥም ጊዜ የሚቈይም ሊኾን ይችላል፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሔር በምሕረት ዓይን እንዲያየንና በቤተ ክርስቲያን እንዲኹም በዓለም ላይ የተጋረጡትን ችግሮች እንዲያርቅ ቅዱስ ሲኖዶስ ለኹለት ሳምንት ጾምና ጸሎት ቢያውጅ ጊዜአዊ ሕግ (ቀኖና) ይባላል፡፡ በዓመት ሰባት የአዋጅ አጽዋማት መኖራቸው ግን በሕይወት እስካለን ድረስ የሚገዛን ቀኖና ነው፡፡
 የስምምነት ሕግ የተጻፈም ያልተጻፈም ሊኾን ይችላል፡፡ ያልተጻፈ መኾኑ ግን ሕግ ከመኾን አይከለክለውም፡፡ ካልተጻፈ ተብሎ አይጣስም፡፡ እያንዳንዳችን የአንዳችንን ፍላጐት ለመጠበቅ ተፈጥረናልና /ዘፍ.4/፡፡
ቀኖና ቤተ ክርስቲያን
 ቀኖና የሚለው ቃል እንደ አኹኑ ለቤተ ክርስቲያን ከማገልገሉ በፊት ሕዝቡ በማንኛውም የዕለት ተዕለት ሕይወቱ የሚዳኝበት ሕግን ያካተተ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያናዊ (ክርስቶሳዊ ሕግ) እና ሕዝባዊ (ቄሳራዊ) ሕግ ተብሎ የተለየው በኋላ ነው /The Oxford Dictionary of the Christian Church, pp 277/፡፡ ቤተ ክርስቲያንም መዠመሪያ አከባቢ ላይ ቀኖና የሚለውን ቃል ስትጠቀም የመጻሕፍቶቿን ዝርዝር፣ የሥርዓተ አምልኮቷን አፈጻጸም፣ የምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን አፈጻጸም፣ የአንድ ክርስቲያን ሥነ ምግባር ምን መምሰል እንዳለበት ለመግለጥ ነበር፡፡ ይኽ ቀኖና እንዲኖራት ምክንያት የኾናትም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይከሰቱ የነበሩት አለመግባባቶች ናቸው፡፡ በተለይ አንዳንድ ከእምነትም ከምግባርም የሚወጡ ሰዎች ሲገኙ ምእመናን ግራ እንዳይጋቡ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ይወጣ ነበር፡፡ እንደ ችግሩ መጠንም የሚወጣው ሕግ (ቀኖናው) ዳርቻው አጥቢያዊ፣ ወይም ሀገረ ስብከታዊ፣ ወይም ሀገራዊ፣ ወይም ዓለማቀፋዊ ይዘት ሊኖረው ይችላል፡፡ ለምሳሌ ትንሽ ቆየት ብለን እንደምንመለስበት በጉባኤ ኒቅያ የተደነገጉት ቀኖናት ዓለማቀፋዊ ይዘት ያላቸው ቀኖናት ናቸው /Ibid/፡፡
 ቤተ ክርስቲያን ቀኖናዊት ካልኾነች እውነተኛ አይደለችም፡፡ የእግዚአብሔርን ልጅ ማወቅ ብቻውን ትርጕም የለውም፤ አጋንንትም ያውቁታልና፡፡ ትርጕም የሚኖረው ስናምንና ስንጠመቅ ነው፡፡ ይቅርታ ሰላምን እንደሚሰጥ ይታወቃል፤ ይቅር ካላልን ግን ትርጕም የለውም፡፡ በሌላ አገላለጽ እምነታችንን የምናከናውንበት ዝርዝር ቀኖና ከሌለ እምነታችን ትርጕም አልባ ነው፤ ምክንያቱም ቀኖና “እምነታችንን እንዴት እንፈጽም?” ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ዝርዝር አፈጻጸም ነውና፡፡
 የቤተ ክርስቲያን ቀኖናት የተሰጡት በሐዋርያት ነው፡፡ ለሕዝቡ ያስተማሩትም እነርሱ ናቸው፡፡ በእነርሱ ወንበር የተቀመጡት ሊቃነ ጳጳሳትም በቅዱስ ሲኖዶስ አማካኝነት ጊዜውን የዋጀ ቀኖና ይሠራሉ፡፡
 ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ከሌለ የሚሠለጥነው ዲያብሎሳዊ ሕግ ነው፡፡ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ዋና ዓላማም ሰዎችን ሥርዓት አስይዞ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖራቸው ማድርግ ነው፡፡ እንደ ምሳሌ ብንጠቅስ አርዮስን ለመገሰፅ ቤተ ክርስቲያን 25 ዓመት ፈጅቶባታል፡፡ የኢትዮጵያ እስር ቤቶች እንኳን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ደብረ ሐይቅ (የግራኝ መሐመድ ወንድም የታሰረበት)፣ ደብረ ዳሞ፣ ሐይቅ እስጢፋኖስ፣ ክብራን ገብርኤል፣ ግሸን ደብረ ከርቤ እና ሌሎች ታላላቅ ገዳማት ነበሩ፡፡ ይኽ የኾነበት ዋና ምክንያትም የቀኖና ዓላማ ሰዎች እንዲታረሙ ማድረግ እንጂ ሰውን መቅጣት ስላልኾነ ነው፡፡ አጼ ቴዎድሮስ አንድን ሌባ ያገኛሉ፡፡ ይዘዉም እጁን ይቈርጡታል፡፡ በዚያን ጊዜ የነበሩ ታላቁ ሊቅ አለቃ አካለ ወልድም በቅኔ አድርገው አጼ ቴዎድሮስን ወረፏቸው፡፡ አለቃ አካለ ወልድ ይኽን ያደረጉበት ዋና ምክንያትም “ሰውዬው እጁ ስለተቈረጠ ከዚያ በኋላ መሥራት አይችልም፤ የሰው ጥገኛ ነው የሚኾነው፡፡ ቀኖና ሊሰጠው ይገባ ነበር” ሲሉ ነው፤ እንደተናገርን የቀኖና ዓላማ ሰውን ማዳን እንጂ ሰውን መጉዳት ወይም ጫና መፍጠር አይደለምና፡፡
  “ሕግ ከጽዮን ይወጣል” /ኢሳ.2፡3/ እንደተባለ የሕግ ምንጭ ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡ ሕግ አውጪ ብቻ ሳትኾን ሕግ ተርጓሚዋና ሕግ አስፈጻሚዋም ርሷ ራሷ ናት፡፡ ሕጓም ዓለምአቀፋዊ ዳርቻ አለው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ባለችበት ኹሉ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንም አለ፡፡ አትስረቅ፣ አትግደል፣… የሚሉት የቤተ ክርስቲያን ሕጎች ናቸው፡፡ በመኾኑም እነዚኽ ሕጎች በማንኛውም ቄሣራዊ ሥርዓት፣ በማንኛውም ዓይነት ቋንቋ፣ በማንኛውም ዓይነት ማኅበረ ሰብእ ውስጥ አሉ፡፡ የሥላሴ አጥር ዳር ድንበር የለውምና የቤተ ክርስቲያን ሕግም ዳር ድንበር የለውም፡፡ ጾም የቤተ ክርስቲያን ሕግ ነው፡፡ አፈጻጸሙ ግን እንደየቦታውና እንደየሰዉ ኹናቴ ሊለያይ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በዓፋር የሚኖር ክርስቲያን እስከ ዘጠኝ ሰዓት ካልጾምክ ካልነው በውኃ ጥም እንገድሏለን፡፡ አዲስ አበባ ላይ የሚኖረው ክርስቲያን ዓፋር ላይ እንደሚኖረው ክርስቲያን 4፡00 ሰዓት ላይ ውኃ ልጠጣ ቢል ግን የተለየ ምክንያት ከሌለው በቀር ተቀባይነት የለውም፡፡ እንዲኽ ሲባል ግን እያንዳንዱ ሰው በራሱ ሕሊና ያለበትን ኹናቴ እያመዛዘነ በራሱ ውሳኔ የሚያደርገው ነው ማለታችን አይደለም፡፡ እንዲኽ ዓይነት ለየት ያለ ቀኖና (Exceptional Canon) የሚያወጣው የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ አካል ብቻ ነውና “ይኼ እኮ ቀኖና ነው፤ ባናደርገውም ምንም ችግር የለውም” ከሚለው ግላዊ አስተሳሰብ ልንጠነቀቅ ያስፈልጋል፡፡ 
 ቀኖና ቤተ ክርስቲያን የራሱ የኾነ ልዩ ባሕርያት አሉት፡፡
·        ሥልጣን ባለው አካል የሚደነገግ፣ የሚተገበር፣ የሚሻሻል ነው፡፡ ሲደነገግም ሲሻሻልም በግለሰቦች የግል ፍላጐት ወይም ፈቃድ የሚደነገግ ወይም የሚሻሻል አይደለም፡፡
·        ሃይማኖታዊ ይዘት አለው፡፡ ምክንያቱም ዓላማው ሰውን ኹሉ ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር ማፍለስ ስለኾነ ቄሣራዊ ይዘት የለውም፡፡ ቢኖርም እንኳን አንድ ክርስቲያን በዚኽ ምድር የሚኖረው ቆይታ ከሰማያዊ ሕይወቱ ጋር ሳይጣረስበት እንዴት መኖር እንዳለበት የሚያስረዳ ነው፡፡
·        የሰው ልጅ ከሚችለው በላይ ሸክምን አይጭንም፤ “ሸክሜ ቀሊል ነው” እንዲል /ማቴ.11፡29/፡፡
·        የሸላሚነትና የቀጪነት ሥልጣን አለው፡፡ ቄሣራዊ ሕግ የሸላሚነት ይዘት የለውም፡፡ በቤተ ክርስቲያን ቀኖና ግን ለምሳሌ ተጋድሎአቸውን በድል ያጠናቀቁት ክርስቲያኖች ቀን ተለይቶላቸው፣ ታቦት ተቀርጾላቸው በምእመናን ዘንድ ክብርን እስከ ማግኘት ይደርሳሉ፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ደግሞ የዘለዓለም አክሊል ዘውድ አለው፡፡
·        የአምልኮ ይዘት አለው፡፡ በውስጡ ጾም፣ ጸሎት፣ ምጽዋት እና የመሳሰሉትን ኹሉ ያካትታል፡፡
·        የመመዘን ጠባይ አለው፡፡ ለምሳሌ የቃየን መሥዋዕት ያልሰመረችው መሥዋዕት ስላላቀረበ ሳይኾን በሕጉ መሠረት አሰስ ገሰስ ኾኖ ስለተገኘ ነው /ዘፍ.4/፡፡
·        በአንድ ጊዜ በአንድ ቦታ የተደነገገ አይደለም፡፡
·        ሰዎችን ደስ ለማሰኘት አይወጣም፤ የሚወጣው እግዚአብሔር ደስ ለማሰኘት ብቻ ነው፡፡ “ለዓለም ከሚመች ከንቱ ልፍለፋ ራቅ” እንዲል ለዓለም የሚመች ቀኖና አይወጣም፡፡ ቀኖና የሚወጣው የምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት እንዲያድግና ምእመናን በሚኖሩበት ማኅበረ ሰብእ ውስጥ አርአያ እንዲኾኑ ነው፡፡
·        አንጻራዊ ጽድቅ ስለሌለ አንጻራዊ ቀኖናም የለም፡፡ ጥቁሩን ጥቁር ነጩንም ነጭ የሚል እንጂ የተድበሰበሰ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን አታወጣም፤ እንዲኽ ካልኾነ የውጫሌ ሕግ ነው፡፡ በዓለማዊ ሕግ የወንጀሉ መጠን ይታያል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ሕግ ግን ወንጀል ወንጀል ነው፡፡
የቀኖና ምንጮች
 ዛሬ ላለው የቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና ምንጮቹ ልዩ ልዩ ቢኾኑም ጠቅለል ባለ መልኩ ግን እንደሚከተለው ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡
ሀ) የሐዋርያት ሲኖዶስ
 እነዚኽ መጻሕፍት በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ. 81 ተብለው ከሚታወቁት መጻሕፍት የሚካተቱ ሲኾኑ ሐዋርያት በየጊዜው በመንፈስ ቅዱስ መሪነት እየተሰበሰቡ የደነገጓቸው እጅግ ጠቃሚ የሥርዓት መጻሕፍት ናቸው፡፡ እነርሱም መጽሐፈ ዲድስቅልያና መጻሕፍተ ሲኖዶሳት (ትእዛዝ፣ ግፅው፣ አብጥሊስ፣ ሥርዓተ ጽዮን) ናቸው፡፡ ሲኖዶስ የተባለውና አራት ክፍል ያለው መጽሐፍ በውስጡ ስለ ሥርዓተ ቅዳሴ፣ ስለ አገልጋዮች ማዕረጋት ቀኖና ይናገራል፡፡ መጽሐፈ ዲድስቅልያ ደግሞ ስለ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር እና ሥርዓተ አምልኮን በዝርዝር ይናገራል፡፡
 እናስተውል! የጌታ ትእዛዛት በሙሉ ዶግማ ነው፡፡ ጾም፣ ጸሎት፣ ጥምቀት፣ ቁርባን፣ ንስሐ፣ ከወንድም ጋር መታረቅ…ወዘተ ዶግማ ነው፡፡ ቀኖና የሚኾነው ዝርዝር አፈጻጸሙ ላይ ሲኾን ነው፡፡ ቀኖና ከሐዋርያት የሚዠምረውም ለዚኹ ነው፡፡ በመኾኑም አንድ ሰው ተነሥቶ ጾም አያስፈልግም ቢል የቀኖና ሳይኾን የዶግማ ጥሰት ነው፡፡
ለ) ዓለም አቀፍ ጉባኤያት
  ጉባኤያት ዓለማቀፋውያን ጉባኤያት የሚባሉት ከኹሉም አብያተ ክርስቲያናት የመጡ ተወካዮች ሲኖሩበት ነው፡፡ የጉባኤው መነጋገሪያ አጀንዳም ዓለማቀፋዊ መኾን አለበት፡፡ የተወሰነው (የሚወሰነው) ውሳኔም በኹሉም አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተፈጻሚ መኾን አለበት፡፡ የነገሩ ጉዳይ ለአንዲት ሀገር ብቻ የሚተው መኾን የለበትም፡፡ ለምሳሌ በ325 ዓ.ም. የተካሔደው የኒቅያ ጉባኤ ዓለማቀፋዊ አጀንዳን የያዘ (ዓለም ስለመዳኑና ስላለመዳኑ)፣ ከኹሉም አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች የነበሩበት፣ ውሳኔውም በኹሉም አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተፈጻሚነት የነበረው ነው፡፡
 በኦሬንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ዓለም አቀፍ ጉባኤያት ሦስት ሲኾኑ፤ ምሥራቃውያን 7፥ ካቶሊኮች ደግሞ 20 ይቀበላሉ፡፡
 ኦሬንታል አርቶዶክሶች የምንቀበላቸው ሦስቱም ጉባኤያት ጉባኤ ኒቅያ (በ325 ዓ.ም. የተካሔደ)፣ ጉባኤ ቁስጥንጥንያ (በ381 ዓ.ም. የተካሔደ) እና ጉባኤ ኤፌሶን (በ431 ዓ.ም. የተካሔደ) ናቸው፡፡ በእነዚኽ ዓለም አቀፍ ጉባኤያት ብዙ ቀኖናዎች ተደንግገዋል፡፡ ለምሳሌ በጉባኤ ኒቅያ ከተወሰኑት ቀኖናት የትንሣኤ በዓል እሑድ መከበር እንዳለበት፣ ስለ አርዮስ ጉዳይ፣ ስለ መጻሕፍት ጉዳይ፣ ስለ አራቱ መንበረ ፓትሪያሪኮች ይገኙባቸዋል፡፡
ሐ) ብሔራውያን ጉባኤያት
 ከዓለማቀፋውያን ጉባኤያት በተጨማሪ በየአካባቢው ጉባኤያት ሊደረጉ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በቅዱስ ያሬድ ዜማ ላይ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ጕዳይዋ አይደለም፡፡ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ አይደለም ብለን ግን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስር ኾነን ያሬዳዊ መዝሙር አያስፈልገንም ወይም በኦርጋንና በፒያኖ እንዘምር ማለት አንችልም፡፡ እነርሱ በያሬዳዊ መዝሙር ስላልዘመሩ ብለንም ሃይማኖታዊ (የዶግማ) ወይም የቀኖና ችግር አለባቸው አንልም፤ ውሳኔው በብሔራዊ ጕባኤ የተወሰነ ነውና፡፡
 ከብሔራውያን ጉባኤያት በተጨማሪ ሀገረ ስብከታዊ ጉባኤም ሊደረግ ይችላል፡፡ አጥቢያዊ ጉባኤም ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን በአንድ ሀገረ ስብከት የተወሰነው ውሳኔ በሌላ ሀገረ ስብከት ተፈጻሚ ላይኾን ይችላል፡፡ በአንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚሠራ ቀኖናም በሌላ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ላይሠራ ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በአንዳንድ ገዳማት ላይ ሴቶች አይገቡም የሚባለው የዚያ ገዳም ብቻ ቀኖና ስለሚኾን ነው፡፡
መ) የቅዱሳን አበው ቀኖናት
 እነዚኽ ቀኖናት ምንም እንኳን በግለሰብ ደረጃ የተወሰኑ ቢኾኑም ቤተ ክርስቲያን የእኔ ብላ የተቀበለቻቸው ቀኖናት ናቸው፡፡ ለምሳሌ ሥርዓተ ምንኩስና የነ አባ እንጦንስ ወይም የእነ አባ ጳኩሚስ ሃይማኖት አይደለም፤ የእነዚኽ ቅዱሳን አባቶች የትሩፋት ሥራ እንጂ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ስለ ቅዱስ ቁርባን የተናገረው ሥርዓት የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ. ሥርዓት ኾኖ የቀረውም ከዚኽ አንጻር ነው፡፡ የቅዱሳን ገድላትና ድርሳናትም እንደምንጭነት ይጠቀሳሉ፡፡
የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ይዘት
 ቤተ ክርስቲያናዊ ቀኖና በውስጡ በጣም ብዙ ነገሮችን ያካተተ ነው፡፡ የቅዱሳት መጻሕፍት ቀኖና፣ የሥርዓተ አምልኮ ቀኖና፣ የአጽዋማት ቀኖና፣ የበዓላት ቀኖና፣ የቅዱሳን ቀኖና፣ የቅዱሳት ሥዕላት ቀኖና፣ የአለባበስ ቀኖና ተጠቃሾች ናቸው፡፡ እስኪ ጥቂቶቹን ብቻ እንደማሳያ በአጭር በአጭሩ ለማየት እንሞክር፡-
1. ቅዱሳት መጻሕፍት ቀኖና
  የቅዱሳት መጻሕፍት ቀኖና ስንል የመጻሕፍቱ እውነተኛነትን፣ ቅዱስነትንና አምላካዊነትን የተመለከተ ማለታችን ነው፡፡ እነዚኽን ቅዱሳት መጻሕፍት ሰፍረውና ቈጥረው የሰጡንም ሉተራውያን ወይም ካቶሊካውያን ሳይኾኑ ኦርቶዶክሳውያን አባቶቻችን ናቸው፡፡ በተለይም እነ ቅዱስ ሄሬኔዎስ፣ ቅዱስ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ፣ ቅዱስ አትናቴዎስ በዚኽ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
 እነዚኽ ቅዱሳን አባቶች የብሉይ ኪዳንን መጻሕፍት ለመቀበል ያስቀመጧቸው መስፈርቶች ነበሩ፡፡ ከእነዚኽም መካከል፡-
ü ወደ ግሪክኛ የተተረጐመ፡፡ አባቶች ይኽን ያሉበት ዋናው ምክንያት አይሁዳውያኑ የጌታችንን የባሕርይ አምላክነት ካለመቀበላቸው የተነሣ ብሉይ ኪዳንን ቈነጻጽለዉት ስለነበር ነው፡፡ ስለዚኽ ከዚኽ ከተቈነጻጸለው መጽሐፍ ሊመጣ ከሚችለው ግድፈት ለመዳን አይሁዳውያኑ ይኽን እንደሚያደርጉ አስቀድሞ የሚያውቅ እግዚአብሔር በ285 ቅ.ል.ክ. ላይ ወደ ግሪክኛ የተተረጐመው የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ መቀበል ግድ ኾኖባቸዋል፡፡
ü የዕብራውያን ባሕል ያለበት፡፡ አባቶች መጽሐፉ የዕብራውያን ባሕል ያለበት መኾን አለበት ያሉበት ምክንያት እግዚአብሔር አስቀድሞ ለዕብራውያኑ በባሕላቸው ስለነገራቸው ነው፡፡ መጽሐፉ ዕብራዊ ባሕል ከሌለበት ተቀባይነት አያገኝም፡፡
ü የአብርሃም እምነት ያለበት፡፡ የአብርሃም እምነት መኾን አለበት ሲሉም ከአንድ አምላክ በቀር ወደ ባዕድ አምልኮ የሚመሩትን መጻሕፍት ለመለየት ነው፡፡
 የሰባ ሊቃናት ትርጕም የምንለውም ይኽን ቀኖና ተከትሎ የተሠራ ትርጕም ነው፡፡ በ2000 ዓ.ም. የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ. ያሳተመችው መጽሐፍ ቅዱስ ትርጕሙ አብዛኛው ከዚኹ ትርጕም የተወሰደ ነው፡፡
እናስተውል!   በአንዳንድ የአማርኛ ትርጕሞች ላይ (ለምሳሌ በ1980 ዓ.ም. እትም ላይ) በስሕተት ተጽፎ የምናገኘው ቢኾንም በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ዴትሮካኖኒካል የሚባሉ መጻሕፍት የሉም፡፡ ዴትሮካኖኒካል የሚሉት ካቶሊኮች ናቸው፡፡ ይኸውም ተጨማሪ መጻሕፍት ለማለት ነው፡፡ ነገር ግን እነዚኽ መጻሕፍት ከመዠመሪያውኑ የነበሩ እንጂ በኋላ የተጨመሩ አይደሉም፡፡ ለዚኽ ማረጋገጫውም በ1948 ዓ.ም. ላይ በሙት ባሕር ላይ በተገኙት ጥቅሎች እነዚኽ ተጨማሪ ናቸው ተብለው የታሰቡት መጻሕፍት በዕብራይስጥ ተጽፈው መገኘታቸው ነው፡፡ ስለዚኽ አይሁዳውያኑ በ280 ዓ.ም. ላይ ታናክ የሚሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ቀኖና ሲሠሩ የሰባ ሊቃናቱን ትርጕም የክርስቲያኖች መጽሐፍ ነው ብለው ስለቈነጻጸሉትና ስለቀነሷቸው እንደተጨማሪ መጻሕፍት ማየት (ዴትሮካኖኒካል ናቸው ማለት) በጥንታዊቱ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ያልነበረ ነው፡፡
 አኹንም እናስተውል! እነዚኽን መጻሕፍት እንደ ፕሮቴስታንቱ ዓለምም አፖክሪፋ አንላቸውም፡፡ አፖክሪፋ ማለት በግሪክኛ የተሰወረ፣ ያልተገለጠ፣ ከእግዚአብሔር ያልተሰጠ ለማለት ነው፡፡ ፕሮቴስታንቱ ዓለም ይኽን እንዲል ያደረገው ዋናው ምክንያት ከላይ እንደገለጽነው አንደኛ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍቱን ተጨማሪ ናቸው ስላለችና እነርሱም ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሲወጡ ተጨማሪ የሚለውን ቃል ብቻ ይዘው ተጨማሪ አያስፈልገንም በማለት፤ ኹለተኛ አይሁዳውያኑ የጌታችንን የባሕርይ አምላክነት ላለመቀበልና ለክርስቲያኖች በነበራቸው የመረረ ጥላቻ በተንኰል የቈነጻጸሉትን መጽሐፍ ያለምንም ጥያቄ ስለተቀበሉት ነው፡፡ ስለዚኽ ራሳችንንና ወንድማችንን ከእንደዚኽ ዓይነት ኦርቶዶክሳዊ ያልኾነ ትምህርት ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ አብዛኞቹ የእንግሊዘኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጕሞች የተተረጐሙት ከዚኹ አይሁድ ከቈነጻጸሉት ቀኖና የተወሰደ መኾኑንም ማስታወሱ ተገቢ ነው፡፡ ደኅና ነው ተብሎ የሚታሰበው “Revised Standard Version” የሚባለው ነው፡፡  
  ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የሐዲስ ኪዳንን መጻሕፍት ለመለየት የተጠቀሙበት መስፈርትም አለ፡፡ እርሱም፡-
ü ሐዋርያት ወይም የሐዋርያት ደቀ መዛሙርት የጻፉት መኾን አለበት፤
ü ከ99 ዓ.ም. በፊት መጻፍ አለበት፡፡ ይኽን ያሉበት ዋና ምክንያትም ከ105 ዓ.ም. በኋላ የግኖስቲኮች የክሕደት መጻሕፍት በስርጭት ላይ ስለነበሩ ነው፡፡
ü የክርስቶስና የሐዋርያት ትምህርት የሚገልጽ መኾን አለበት፡፡
 አንድ ኦርቶዶክሳዊ ምእመን ቅዱሳት መጻሕፍትን (አሥራውም ይኹኑ አዋልድ) ሲለይ ከምንም በላይ ማየት ያለበት ቁጥሩን (81፣ 66፣ 73፣ 76 የሚለውን) ሳይኾን ኦርቶዶክሳዊ ይዘታቸውን ነው፡፡ አንድ መጽሐፍ ኦርቶዶክሳዊ ይዘት እንዳለው የሚታወቀውም፡-
·        ነገረ እግዚአብሔርን የሚያስክድ ካልኾነ፡፡ ለምሳሌ የጀሆቫ ዊትነስ፣ የሞርሞን አማኞች ያዘጋጁት “መጽሐፍ ቅዱስ” ፍጹም ክሕደት ነው፡፡
·        የሟርት ይዘት ከሌለው፡፡ ምንም እንኳን ተጨማሪ ሥራ የሚጠይቅ ቢኾንም የዚኽ ጽሑፍ አዘጋጅ እስከ አኹን ድረስ ባለው መረጃ መሠረት በሐዲስ ኪዳን ኅቡእ ስም የለም፡፡ ምንም እንኳን በአንዳንድ የቤተ ክርስቲያናችን ድርሳናት ላይ እንዲኽ ዓይነት ጽሑፍ ብናገኝም ወደ ኋላ ስንሔድና የዚያ ድርሳን ጥንታዊውን የብራና ጽሑፍ ስንመለከት ግን ጸ፣ጸ፣ጸ፣ጸ፣ጸ፣ጸ፣ ጨ፣ ጨ፣ ጨ፣ ጨ፣ ገ፣ ገ፣ ገ፣ ገ፣ ገ… የሚል ኅቡእ ስም የለውም፡፡ እነዚኽ ኅቡእ ስሞች በኋላ ላይ በስርዋፅ የገቡ ናቸው፡፡ አኹን አኹን የሚታተመውን ድርሳነ ሚካኤልን እንደ አንድ ማሳያ ብንወስደው ከ15ኛ መቶ ክፍለ ዘመን በፊት በነበረው የድርሳነ ሚካኤል የብራና ጽሑፍ ላይ እንዲኽ ዓይነት ኅቡእ ስም የለውም፡፡ ዘወትር ለጸሎት በምንጠቀምበት በወንጌል፣ በመዝሙረ ዳዊት፣ ወይም በውዳሴ ማርያም ኅቡእ ስም የለም፡፡ ኅቡእ ስም ተብሎ በብዛት የምናገኘው በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲኽ በግለሰቦች በሚታተሙት መጻሕፍት ላይ ነው /የቃል መረጃ ከመምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል፣ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን መምህር/፡፡ በመኾኑም በቤተ ክርስቲያናችን በአዋልድ መጻሕፍት ቀኖና ዙርያ ብዙ የሚቀር ሥራ እንዳለ ያመለክታል፡፡ የሚመለከታቸው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም የድርሻቸውን እንደሚወጡ እምነታችን ነው፡፡     
·        እምነታችንን ከእግዚአብሔር አውጥቶ ለሌላ አካል አሳልፎ የሚሰጠን ካልኾነ፡፡ ለምሳሌ ይኽን ቃል ደጋግመኽ በለው ካለ፤ የፈጣሪን ሥራ በሌላ የሚቀይር ከኾነ፤ ከዚኽ ከዚኽ የሚያድኑ ጸሎቶች የሚል ከኾነ፤ በትራስኽ ላይ ብትንተራሰው ካለ፤ ይኽን ክታብ በአንገትኽ ላይ ብታንጠለጥለው የሚል ዓይነት ከኾነ ያለ ምንም ቅድመ ኹኔታ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት እንዳልኾኑ ዐውቀን ልንጥላቸው ይገባል፡፡
2. የቅዱሳን ቀኖና
  በቀኖና ወይም በሥርዓት ደረጃ ቅዱሳንን ማክበር የተዠመረው ከኹለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንሥቶ ነው፡፡ ነገር ግን ይኽን ያደረገው ቅዱስ ሲኖዶስ ሳይኾን ሕዝቡ ወይም ምእመኑ ራሱ ነው፡፡ በዚኽም ቀድመው ይታሰቡና ይከበሩ የነበሩት ቅዱሳን ሰማዕታት ናቸው፡፡ ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዠምሮ ግን አንዳንድ ሰዎች በራሳቸው እይታ ቅዱስ እንደኾነ የሚያስቡትን ኹሉ ቅዱስ ለማስባል ስለተነሣሡ ቤተ ክርስቲያን በጉባኤ ደረጃ ቀኖና ቅዱሳን ማውጣት ዠመረች፡፡ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና ቅዱሳን ማውጣት ዠመረች ማለት ግን ለሰዎቹ ቅድስናን ሰጠች ማለት ሳይኾን ለቅድስናቸው ዕውቅናን ሰጠች ለማለት ነው፡፡ ይኸውም ከትሩፋታቸው ብዙ እንድንማር፣ በቃል ኪዳናቸው እንድንጠቀም፣ አሰረ ፍኖታቸውን እንድንከተል፣ አማላጅነታቸውን እንድንጠይቅ ነው፡፡
 አንድን ቅዱስ ቅዱስ ለማለት መስፈርቶች አሉት፡፡ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያኽል፡-
·        ከምንም በፊት ክርስቲያን መኾን አለበት፡፡ አምኖ የተጠመቀ፣ ቅዱሳት ምሥጢራትን ሲፈጽም የኖረና ከእኩያት ጋር የተጋደለ መኾን አለበት፡፡ አለበለዚያ ክርስቲያን ሳይኾኑ (ካቶሊክም ፕሮቴስታንትም ጭምር) የፈለገ ያኽል በጐ ምግባር ቢኖራቸውም ቅዱሳን አይባሉም፡፡
·        በክርስቲያናዊ ምግባራቸው የታወቁ፡፡ ሃይማኖት ያለ ምግባር የሞተ ነውና፡፡ እንዲኽ ሲባልም ፈጽመው ኃጢአት ያልሠሩ ለማለት አይደለም፤ እንዲኽ ያለ ዕሩቅ ብእሲ ከእመቤታችን በቀር ማንም አይገኝምና፡፡
·        ገቢረ ተአምራትን የፈጸሙ፡፡ እንዲኽ ሲባልም ተአምራትን ማድረግ ብቻውን መስፈርት ሊኾን እንደማይገባ ሊታወቅ ይገባል /ማቴ.7፡21/፡፡
·        ቅዱሳኑ ካረፉ በኋላ ዓጽማቸው ሕሙማንን ከፈወሰ፤ ባረፉበት ቦታ ጠበል ከፈለቀ፡፡
·        ለየት ያለ አገልግሎት ለቤተ ክርስቲያን ካበረከቱ፡፡ ለምሳሌ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ. እነ ቅዱስ ላሊበላ፣ እነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ እነ አቡነ ጴጥሮስ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያደረጉትን አስተዋጽኦ ማስታወሱ በቂ ሊኾን ይችላል፡፡
እንዲኽ በቀኖናው መሠረት ቅዱስ የተባለው ታላቅ ሰው ቅድስና ሲሰጠው የሚከተሉት ነገሮች ይፈጸሙለታል፡-
v በስሙ ቤተ ክርስቲያን ይታነጽለታል፤
v ገድል ይጻፍለታል፤
v በዓል ይደረግለታል፤
v ቅድስናውን አጕልቶ የሚያሳይ ሥዕል ይሣልለታል፤
v ዐፅሙ በክብር እንዲያርፍና ምእመናን እንዲያከብሩት ይደረጋል፤
v ምእመናን በስሙ ሊሰየሙና ውሉደ እግዚአብሔር ሊባሉ ይችላሉ /በዓላት ምን? ለምን? እንዴት?፣ በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ፣ 2005 ዓ.ም.፣ ገጽ 144-145/፡፡
3. የሥርዓተ አምልኮ ቀኖና
 በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የምንፈጽመው ማንኛውም ዓይነት መንፈሳዊ ድርጊት የአምልኮ ባሕርይ አለው፡፡ ስናምን፣ ስንሰጥ፣ ስንቀበል ኹሉ አምልኮ ነው፡፡ ማንኛውንም ዓይነት ምሥጢር ስንፈጽም የእግዚአብሔር መኾናችንን ነው የምንገልጠው፡፡
 ያለ ሃይማኖት ሀብተ መንፈስ ቅዱስን መቀበል አይቻልም፡፡ የእግዚአብሔር ሀብት ከእግዚአብሔር ጋር በመኾን እንጂ እንደ ሲሞን መሠሪ የምንገዛው አይደለምና፡፡
 ሃይማኖት መታዘዝንም ይጨምራልና እንደ ቀኖና ዲያቆኑን፣ ቄሱን ወይም ጳጳሱን ማክበር ይጠበቅብናል፡፡ በጉድለት፣ በትዕቢት፣ በጭቅጭቅ የምንቀበል ከኾነ አለመታዘዝ ነው፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች ደናግላን ሳይኾኑ ተክሊል ካልተደረገልን ብለው ይጨቃጨቃሉ፡፡ በዚኽም ምሥጢረ ተክሊልን ሲፈጽሙ አምልኮተ እግዚአብሔር እየፈጸሙ እንደኾኑ ይረሳሉ፡፡ ከሥርዓተ አምልኮው ይልቅ በቤታቸው ስለሚሰቅሉት ፎቶ ይጨነቃሉ፡፡ ስለዚኽ ቀኖናና አምልኮ በእጅጉ የተቈራኙ መኾናቸውን ዐውቀን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በምንፈጽማቸው መንፈሳዊ ድርጊቶች ላይ ልንጠነቀቅ ይገባናል፡፡
4. ሥርዓተ ሲመትን የሚመለከት ቀኖና
በጥምቀት የተወለደ ኹሉ አገልጋይ ነው፤ “ያገለግሉኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ” እንዲል /ዘጸ.8፡1/፡፡ ይኸውም አሥራቱን ቀዳምያቱን የሚያወጣ፣ የሚታዘዝ ሕዝብ ይኾነኝ ዘንድ ማለት ነው፡፡ ከእነዚኽ ከተጠመቁት ተመርጠው የሚያገለግሉት ደግሞ ስዩማነ ካህናት (የአገልጋዮች መሪዎች) ይባላሉ፡፡ እነዚኽን ስዩማነ ካህናት ለመሾምም የራሱ የኾነ መስፈርት አለው፡፡ ይኽን መስፈርት ሳያሟላ ማንም ራሱን ሊሾም አይችልም፡፡ ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ ይሁዳ ሲጐድል ሐዋርያት በይሁዳ ፈንታ ሌላ አንድን ሐዋርያ ለመሾም ሲጾሙ፣ ሲጸልዩ፣ ዕጣ ሲጥሉ፣ እጅግ ተጨንቀው ይኽን ኹሉ ሲያደርጉ ማየታችን ኹሉም ሰው ሐዋርያ እንዳልኾነ የሚያስረዳ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ አንድን ክርስቲያን ስዩመ ካህን ለማድረግ የራሱ መስፈርት እንዳለው የሚያስገነዝብ ነው፡፡
  በአጠቃላይ ቀኖና እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም፡-
1.  የፍላጐት ልዩነት በሰዎች መካከል አይቀሬ ነው፡፡ እነዚኽን ሰዎች ወደ ስምምነት ለማምጣት ደግሞ የግድ ሕግ ያስፈልጋል፡፡ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊኖሩ የሚችሉ አለመስማማቶችን የሚፈታ ነው፡፡
2.  በሰውነታችን ውስጥ ያሉት ብልቶች የየራሳቸው ድርሻ አላቸው፡፡ ብዙዎች ቢኹኑም አንድ ሰውነት ናቸው፡፡ ብዙዎች ኾነው ሳለ የአንድ ሰውነት አባል ኾነው መቀጠል የሚችሉት ግን እጅ የእግርን፣ ዓይን የዦሮን ሥራ ልሥራ እስካላለች ድረስ ብቻ ነው፡፡ እንዲኽ ሕገ ተፈጥሮን ጥሶ መዘበራረቅ ካለ ሰውነት እንደ ሰውነት መቀጠል አይችልም፡፡ ልክ እንደዚኹ እኛ ክርስቲያኖችም ብዙዎች ብንኾንም የአንድ ክርስቶስ ብልቶች ነን፡፡ የአንድ ክርስቶስ ብልቶች ኾነን የምንቀጥለው ግን ካህኑ የክህነቱን ምእመናንም የምእመናንን ሥራ የሠራን እንደኾነ ብቻ ነው፡፡ አንዱ ምእመን ተነሥቶ የካህኑን ሥራ ልሥራ ቢል የቤተ ክርስቲያን አንድነት ሊጠበቅ አይችልም፡፡ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ይኽ አንድነት እንዲኖር ይረዳል፡፡
3.  ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን መብታችንና ግዴታችንን ለይቶ የሚነግረን ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ምእመን ዐሥራት በኵራት የማውጣት ግዴታ አለበት፡፡ ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መገዛት አለበት፡፡ ይኽን ሳያደርግ ቀርቶ ከቤተ ክርስቲያን መጥቶ ምሥጢራትን ልፈጽም ቢል ተቀባይነት የለውም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሕግስ ይቅርና የትራፊክ ሕግም ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!

2 comments:

  1. ረጅም እድሜ ከጤና ጋር ይስጥልን! በጣም ጥሩ አስተማሪ ጽሑፍ ነው:: እግዚአብሔር ይስጥልን::

    ReplyDelete
  2. በጣም ጥሩ አገላለፅ ነው ግን አስተያየት ከተባለ አይቀር የተሰማኝን ልናገር አቀራረቡ ትንሽ አሰልቺ ነገር ነው በጣም ረጅም ሰለሆነ ለማንበብ ትንሽ ያሰለቻል ግን ታግሶ ላነበበው በጣም አስተማሪ ነው እግዚአብሔር ያክብርልን ቃለ ሂዎት ያሰማለን amen🙏🙏

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount