Tuesday, October 27, 2015

ቅዱስ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ (1)



በሥርጉተ ሥላሴ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጥቅምት 16 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት፥ ቅዱስ አግናጥዮስ ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን ስለ ትሕትና ለማስተማር በመካከላቸው ያቆመው ሕፃን ነው፡፡ ከዚህም የተወለደበትን ዘመን መገመት ይቻላል (30-35 ዓ.ም.)፡፡ በጌታችን ደቀ መዛሙርት መካከል በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው?” የሚል ክርክር በተነ ጊዜ፥ ጌታ ሕፃኑን ቅዱስ አግናጥዮስን አቅፎ በመሳም፡- ተመልሳችሁ ከየውሀት ጠባይዓዊ ደርሳችሁ እንደዚህ ሕፃን ካልሆናችሁ መንግሥተ ሰማያት አትገቡም አላቸው፥ “ሕፃንንም ጠርቶ በመካከላቸው አቆመው እንዲህም አለ፥ እውነት እላችኋለሁ ካልተመለሳችሁ እንደዚህም ሕፃን ካልሆናችሁ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም . . . ” እንዲል /ማቴ.18፥2-5፣ አንድምታ ወንጌል/፡፡ ሰማይና ምድርን ፈጥረው በተሸከሙ እጆች፣ ሕዝብና አሕዛብን ለማዳን ግራ ቀኝ በተዘረጉ ቅዱሳት ክንዶች መታቀፍ ምንኛ መቀደስ ነው?! ቅዱስ አግናጥዮስ ጌታችን በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ሕፃን ብሎ እንደመሰለለት እንደዚያው እንደ ምሳሌው ሆኖ እስከ መጨረሻ ሕይወቱ በየውሀት ጠባይዓዊ የኖረ፣ ጌታ አቅፎ እንደ ተሸከመው እርሱም ጌታውን በልቡናው የተሸከመ ቅዱስ አባት ነው፡፡ ስለዚህም ቅዱስ አግናጥዮስ ራሱን በተደጋጋሚ ቲኦፎረስ (Theophorus - እግዚአብሔርን በልቡናው የተሸከመ፣ ለባሴ እግዚአብሔር)ስቶፎረስ (Chritophorus - ክርስቶስን በልቡናው የተሸከመ፣ ለባሴ ክርስቶስ) እያለ ይጠራ ነበር፤ በጣም ደስ የሚሰኝበት ሙም ነበር፡፡ ለዚህም ነው በመጨረሻ ለተራቡ አናብስት ተጥሎ ሰማዕትነቱን በፈጸመበት ሰዓት አናብስት ሌላውን አካሉን በመላ ሲበሉ ልቡን መርጠው የተ፡፡

ቅዱስ አግናጥዮስ የዮሐንስ ወንጌላዊ ደቀ መዝሙር ሲሆን፥ በአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ጴጥሮስ 3ኛ ሆኖ በራሱ በቅዱስ ዮሐንስ 70 ዓ.ም. ጵጵስናን ተሾሟል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ነው የሾመው የሚሉም አሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ፥ ሐዋርያትን አህለው ሐዋርያትን መስለው ከተነ፣ ወንጌልን ከሐዋርያት በቀጥታ ተቀብለው በቃልም በተግባርም ለዓለም ከመሰከሩ ሐዋርያውያ አበው አንዱ ነው፡፡ በወቅቱ የሮማ ንጉሥ፥ በንጉሥ ትርያዳን ትእዛዝ ለተራቡ አናብስት ተሰጥቶ ሰማዕት እስከ ሆነ ድረስ በአንጾኪያ ቤተክርስቲያን መንበር ለ40 ዓመታት ያበራ ሐዋርያ ነው፡፡ የከበረ ቅዱስ አግናጥዮስ በአንጾኪያ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ በነበሩ በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ዘንድም እጅግ ተወዳጅ አባት ነበር፡፡
ቅዱስ ያሬድ “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ” የሚለውን የመላእክት ዝማሬ ተመልክቶ ለቤተ ክርስቲያናችን የምስጋና ሥርዓት መሠረት እንደ ሆነ ሁሉ፥ ቅዱስ አግናጥዮስም “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ” የሚለውን የመላእክት ምስጋና በራእይ ያየና የአንጾክያ ቤተ ክርስቲያንም በዚሁ መልክ እንድታመሰግን መሠረት ያበጀ እርሱ ነው፡፡ 


ስለ እርሱ ማንነት በጥልቀት ማወቅ የሚቻለው ለተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ከጻፋቸው መልእክታት ሲሆን፥ ሁሉንም የጻፋቸው እርሱ ራሱ እንደሚለው በተራቡ አናብስት መንጋጋ እንደ ስንዴ ተፈጭቶ ለክርስቶስ የተወደደ መሥዋዕት ለመሆን ከአንጾኪያ ወደ ሮም በሚጓዝበት ወቅት ነበር፡፡ ሲጽፋቸውም እንደ አንድ የሥነ መለኮት ምሁር ሳይሆን እንደ እረኝነቱ የጻፋቸው ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት የእርሱ ናቸው የተባሉ 15 መልእክታት ያሉ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ ሰባቱ ብቻ በትክክል የእርሱ ናቸው፤ ሌሎች የቀሩት ግን በስሙ የተቀሰጡ ናቸው ተብሎ ይታመናል፡፡ ለዚህም ሰባቱ በእነ ቅዱስ ፖሊካርፐስና በአውሳብዮስ ዘቂሳርያ መጠቀሳቸው ነው፡፡ ይሁን እንጂ በሥራዎቹ ዙሪያ ከተጠኑት ጥናቶች አብዛኛዎቹ የውጭ ምንጮች በመሆናቸው ተጨማሪ ጥናቶች፥ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ጥንታውያን መዛግብትን በጥልቀት መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ይህን ያልንበት ምክንያት በሃይማኖተ አበው መጽሐፍ ዘአግናጥዮስ ፍል ላይ፥ “የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳሳት የከበረ ሰማዕት አግናጥዮስ በዐሥራ ሦስተኛው መልእክቱ እንዲህ አለ ” የሚል ፍንጭ ስላለ፥ ቢያንስ በትንሹ ዐሥራ ሦስት መልእክታት እንዳሉት መረዳት ስለሚቻል ነው፡፡ ተጨማሪ ጥናቱ ወደ ፊት በአጥኚዎች እንደሚደረግ ተስፋ በማድረግ ለጊዜው ቅዱስ አግናጥዮስ በመልእክታቱ የጠቀሳቸውን ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ከዚህ ቀጥለን እንመለከታለን፡፡
የቅዱስ አግናጥዮስ አስተምህሮዎች
ቅዱስ አግናጥዮስ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ያስተማረ ሲሆን፥ በተለይ ጠንከር ባሉ መሠረታተ ሃይማኖት ላይ ያለውን ጥርት ያለ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ እንደሚከተለው እንቃኛለን፡፡
1.  ምሥጢረ ሥላሴ
እግዚአብሔር ፈጣሬ ፍጥረታት መሆኑንና በአካል ሦስትነት በመለኮት አንድነት ያለ መሆኑን ሲመሰክር እንዲህ ብሏል፡-
ፍጥረታትን ሁሉ የፈጠረ እግዚአብሔር የፍጥረቱን ሁሉ ሹመትና መዐርግ መስጠት የሚቻለው በመልክ በገጽ ፍጹም በሚሆን በሦስት አካል በጌትነቱ ዙፋንተቀምጦ ሁሉን የሚገዛ ነው፡፡” (ሃይ.አበ. ምዕ.11 ክፍል 1 ቁ. 2)፡፡
ጌታችን በወንጌል “ኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን?” ብሎ እንደተናገረ (ዮሐ. 14:8-14) ቅዱስ አግናጥዮስ በሥላሴ ዘንድ አካላት በመገናዘብ አንዱ አካል በሌላው ህልዋን ሆነው የሚኖሩ መሆናቸውን ባስተማረበት ክፍል፡-
“አብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ህልው እንደሆነ፥ ወልድም በአብ በመንፈስ ቅዱስ ህልው እንደሆነ፥ መንፈስ ቅዱስም በአብ በወልድ ህልው እንደሆነ እናምናለን፤ ይህች ሦስትነት ያለመለየት ያለመለወጥ በሦስት አካላት በአንድ መለኮት የተካከለች ናት፡፡” ብሏል (ሃይ.አበ. ምዕ. 11 ክፍል 1 ቁ. 5)፡፡
ሥላሴ የስም፣ የግብር፣ የአካል ሦስትነት ቢኖራቸውም በአገዛዝ፣ በፈቃድ፣ በክብር፣ በሥልጣን፣…  አንድ እንደሆኑም እንዲህ በማለት አስተምሯል፡-
“አንዲት አገዛዝ፣ አንዲት ፈቃድ፣ አንዲት ኀይል፣ አንዲት መንግሥት፣ አንዲት ስግደት፣ አንዲት ምስጋና፣ አንዲት ክብር፣ አንድ ጽንዕ ለሥላሴ ይገባል፤ አንዲት ምክር፣ አንዲት ሥልጣን፣ አንድ ክብር፣ አንዲት ጽንዕ፣ አንድ አኗኗር፣ አንድ ፈቃድ ለሥሉስ ቅዱስ ነው፡፡”(ሃይ.አበ. ምዕ. 11 ክፍል 1 ቁ. 6)፡፡
በመጨረሻም በሥላሴ አካላት ዘንድ አንዱ ሌላውን ወደ መሆን መለዋወጥ ሳኖርባቸው በአካል ሦስትነት በአንድ መለኮት አንድነት ጸንተው እንደሚኖሩ ሲገልጥ፡-
“አብም አብ ነው እንጂ ወልድን መንፈስ ቅዱስን አይደለም፣ ወልድም ወልድ ነው እንጂ አብን መንፈስ ቅዱስን አይደለም፣ መንፈስ ቅዱስም መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ አብን ወልድን አይደለም፡፡ አብ ወልድን መንፈስ ቅዱስን ወደመሆን አይለወጥም፣ ወልድ አብን መንፈስ ቅዱስን ወደመሆን አይለወጥም፣ መንፈስ ቅዱስም አብን ወልድን ወደ መሆን አይለወጥም፡፡ እሊህ ሦስቱ አካላት በጌትነት በክብር ፍጹማን ናቸው በአንድ መለኮት አንድነትም አንድ ናቸው፡፡” (ሃይ.አበ. ምዕ. 11 ክፍል 1 ቁ. 5)
በማለት ከሐዋርያት በቀጥታ ያገኘውን ትምህርት አስተላልፏል፡፡ ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊት እና ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ዛሬም ድረስ ስለ ምሥጢረ ሥላሴ የምታምነው እና የምታስተምረው ይህንኑ ነው፡፡ በዚህም ቤተ ክርስቲያናችን እስከ ዛሬ ድረስ የሐዋርያትን ትምህርት ሳታዛባ በትክክል ጠብቃ ያለች መሆኑን እንረዳለን፤ ታሪክን ወደ ኋላ መለስ ብሎ ማጥናት እና በየዘመኑ የነበረውን አስተምሮ ማጥናት የሚጠቅመውም ለዚህ ነው፡፡
2.  ምሥጢረ ሥጋዌ
ቅዱስ አግናጥዮስ በብዛት ደጋግሞ ከሚጠቅሳቸው ትምህርተ ሃይማኖት ውስጥ እግዚአብሔር ሰው የሆነበት ምሥጢር ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ይህንንም ከምሥጢረ ሥላሴ አያይዞ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ በተለየ አካሉ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋን እንደተዋሐደ ሲመሰክር እንዲህ ይላል:-
“ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል በእመቤታችን በንጽሕት ድንግል ማርያም ማኅፀን አደረ፤ ስለመለኮት ተዋሕዶ በዚህ የምንናገርም በወልድያለውን ነው፡፡ ስለ አብ ስለ መንፈስ ቅዱስ አይደለም፤ ፈጽሞ አብ መንፈስ ቅዱስ ሰው ለመሆን በድንግል ማኅፀን አደሩ አንልም፡፡ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ ብቻ ከእርሷ ተወለደ እንላለን እንጂ፡፡” (ሃይ. አበው ዘአግናጥዮስ፥  ምዕ. 11 ክፍል 1 ቁ. 3)፡፡
በቅዱስ አግናጥዮስ ዘመን በአጠቃላይም በዘመነ ሐዋርያውያ አበው፥ ብዙ ፈላስፎች ክርስትናን በፍልስፍና ማዕቀፍ አስገብተው ለመረዳት በመፈለጋቸው እና የቀደመ የፍልስፍና ጫማቸውን አውልቀው በእምነትና በንጹሕ ኅሊና ከመቀበል ይልቅ ክርስትናን ለፍልስፍና መላምቶች ካልተገዛህ በማለታቸው ልዩ ልዩ ክህደቶችን አፍልቀዋል፡፡ ቅዱስ አግናጥዮስን የመሰሉ የቤተ ክርስቲያን አዕማድ እነዚህን መናፍቃን  በትምህርታቸው በማሳፈር፤ ምእመናን ከስህተት ትምህርት እንዲጠበቁ በእጅጉ ታግለዋል፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ አግናጥዮስ ምእመናንን፥
“ለራሳቸውና ለሚከተሏቸው ሰዎች ጥፋት የሚሆን ከክርስቶስ ትምህርት ተቃራኒ የሆነ ትምህርት ከያዙ፣ ለእግዚአብሔር ፈቃድ ያልተገቡ ነገሮችን የሚያደርጉ ሲሆኑ የክርስቶስን ስም በሐሰት ከተሸከሙ ከማይረቡ ሰዎች ከዱር አውሬ እንደምትርቁ  ራቁ፤ እነርሱ በማይድን በሽታ እንደተያዙሳይጮሁ ተደብቀው እንደሚነክሱ እብድ ውሾች ናቸው” በማለት ከሐሰተኞች መምህራን እንዲጠበቁ  በተደጋጋሚ ያስጠነቅቃል (Epistle to the Ephesians, Chapter 7)፡፡
 ከፍልስፍና በወረሱት የምንታዌ ትምህርታቸው የተነ ደግ ደጉ ነገር፣ ረቂቁ ዓለም በደጉ አምላክ ተፈጠረ፤ ክፉ ክፉው፣ ግዙፉ ዓለም እና ግዙፍ የሆነው ነገር በሙሉ ርኩስ እና በፉው አምላክ የተፈጠረ ነው ብለው የሚያምኑ መናፍቃን (ዶሴቲስቶች) በዘመኑ ከተነሱት ከዎች ዋነኞቹ ነበሩ:: ሥጋ ግዙፍ እና ርኩስ ነው፤ ስለዚህ አምላክ ሊዋሐደው አይችልም፣የክርስቶስ ሥጋን መዋሐድ ምትሐት ነው እያሉ ያስተምሩ ነበር:: እነዚህ መናፍቃን ሥጋዌን ምትሐት ከማለታቸው የተነ ጌታችን በዚህ ምድር ያደረጋቸው ተግባራት በሙሉ የማስመሰል ናቸው እንጂ በእውነት የተደረጉ አይደሉም ይሉ ነበር:: ቅዱስ አግናጥዮስ ክርስቶስ ሥጋን በምትሐት ሳይሆን በእውነት እንደተዋሐደ ፍጹም ሰው እንደ መሆኑ ከኀጢአት በስተቀር በዚህ ምድር የሠራቸው ሥራዎች በሙሉ በእውነት የተደረጉ እንጂ ምትሐት እንዳይደሉ ሲያስተምር:-
“ከእግዚአብሔር በአፍኣ የሆኑ የማያምኑ ሰዎች እንደተናገሩ እግዚአብሔር ሰው የሆነው በታይታ በምትሐት ከሆነ፣ በእውነት ሥጋን ካልነሳ፣ የሞተው: መከራን የተቀበለው በምትሐት እንጂ በእውነት ካልሆነ፤ እኔ በምን ምክንያት ስለእርሱ እታሰራለሁ፣ ራሴንስ ለተራቡ አናብስት ለመስጠት ስለምን እቸኩላለሁ? እንዲህ ከሆነ ሞቴ ከንቱ ነዋ!ክርስቶስን በመከራው ለመምሰል መከራን የምቀበል እኔ ሐሰተኛ ነኛ! እንዲህም ከሆነ ‘እነርሱም ወደ ወጉት ይመለከታሉ ሰውም ለአንድያ ልጁ እንደሚያለቅስ ያለቅሱለታል፥ ሰውም ለበኵር ልጁ እንደሚያዝን በመራራ ኀዘን ያዝኑለታል’ያለ ነቢዩ ከንቱ ተናገራ! (ዘካ.12:10):: እነዚህ ሰዎች ከሰቃልያን አይሁድ የማይተናነሱ የማያምኑ ናቸው፡፡ እኔስ አለኝታየን በማስመሰል፣ በምትሐት በሞተልኝ ላይ አላደርግም፤ በእውነት ነው እንጂ፡፡ ድንግል ማርያምም በእውነት እግዚአብሔር የተዋሐደውን ሥጋ በማኅፀኗ ተሸከመች፡፡ እግዚአብሔር ቃልም እንደእኛ ሕማም ሞት የሚስማማው ሥጋን ተጋርዶ በእውነት ከድንግል ተወለደ፡፡ ሰውን ሁሉ በማኅፀን የሚስል እርሱ በእውነት በማኅፀን ኖረ፤ ከድንግልም ያለ ሩካቤ ለራሱ ሥጋን አዘጋጀ፡፡ እንደእኛ ዘጠኝ ወር በማኅፀን አደረ፣ እንደእኛ በእውነት ተወለደ፣ እንደእኛ በእውነት ጡትን ጠባ፣ በላ ጠጣ፡፡ 30 ዘመናት ከሰው ጋር ከተመለለሰ በኋላ በዮሐንስ እጅ በምትሐት ሳይሆን በእውነት ተጠመቀ፣ ሦስት ዓመት ወንጌልን አስተማረ፣ ታምራት አደረገ፣ ፈራጅ ሲሆን በአይሁድ በሐሰት ተፈረደበት፣ በገዥው በጲላጦስ ተገረፈ፣ በጥፊ ተመታ፣ በማስመሰል: በማታለል ሳይሆን በእውነት ተሰቀለ:: በእውነት ሞተ፣ ተቀበረ፣ ከሙታንም ተለይቶ ተነሣ ” (Epistle to the Trallians, chapter 10)፡፡
ዳግመኛም እግዚአብሔር ስለ እ ሞተ የሚለውን ይዘው መለኮት በባሕርዩ ታመመ ሞተ ላሉ መናፍቃንም ምላሽ ሲሰጥ፥
“እኛ ግን የባሕርይ አምላክ ክርስቶስ ሰው እንደ መሆኑ በሥጋ እንደ ታመመ፤ በመለኮት እንዳልታመመ እናምናለን፤ በሥጋ ሞተ፤ በመለኮት አልሞተም፡፡… መለኮት ሞተ ካልክ ሦስቱ ሞቱ እንዲያሰኝብህ፤ የጌታችንንም ሥጋ በመቃብር ውስጥ እንደ ሙታን በድን እንዳደረግኸው አታውቅምን?” (ሃይ.አበ. ምዕ.11፣ ክፍል 11፣ ቍ.10-13)፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋሐደው ሥጋ እንደ ተነሣ፣ አሁንም በተዋሐደው ሥጋ በአባቱ ቀኝ በጌትነቱ ተቀምጦ እንዳለ፣ ዳግመኛም በሚመጣበት ጊዜ በክበበ ትስብእት እንደሚመጣ፤ መለኮት እና ሥጋ ከተዋሕዶ በኋላ መቼም መች መለያየት እንደሌለባቸው በስፋት መስክሯል፤ እንዲህ ሲል፡-
“ክርስቶስ ሲወለድ: ሲሰቀል ብቻ ሳይሆን ከትንሣኤም በኋላ በተዋሕዶ ነው፤ አሁንም እንዲሁ ነው፡፡ ወደ ጴጥሮስ እና አብረውት ወደ ነበሩት መጥቶ እንዲህ አላቸው፥ ‘እኔ ራሴ እንደ ሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት፥ መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና እኔን ዳስሳችሁ እዩ አላቸው’ (ሉቃ.24፥39)፡፡ ቶማሰንም እንዲህ አለው ‘ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን’ (ዮሐ.20፥27):: ወዲያውም እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ አመኑ፡፡ ቶማስም ‘ጌታዬ አምላኬም’ አለው ((ዮሐ.20፥28) በተዋሐደው ሥጋ በምስጋና፥ በክብርና በሥልጣን ሊመለስ፤ በተዋሐደው ሥጋ ወደ ላከው ወደ አብ  እያዩት ከፍ ከፍ አለ፡፡ መላእክትም እንዲህ አሏቸው ‘ደግሞም፦ የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል’ (ሐዋ. 1፥11):: መናፍቃን እንደተናገሩት በመጨረሻ ያለ ሥጋ የሚመጣ ከሆነ ዐይንም ሁሉ የወጉትም እንዴት ያዩታል? እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ባወቁትስ ጊዜ እንዴት ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ (ራእ.1፥7):: መናፍስት በተፈጥሯቸው አካልም፣ ምስልም፣ ምልክትም፣ ቅርፅም የላቸውምና ” (Epistle to the Smyrneans, chapter 3)::
በዚህ ይነት ለመናፍቃን ምላሽ እየሰጠ በማሳፈር እና ምእመናንን ከክፉ ትምህርታቸው እንዲጠበቁ በመምከር ከሐዋርያት ለተረከባት እምነት ጠበቃ ነበረ፡፡
3.  ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን
ቅዱስ አግናጥዮስ በላካቸው መልእክታት በሙሉ የሚጠቅሰው ሌላው ጉዳይ ምእመናን በቤተ ክርስቲያን እንዴት በሥርዐት መተዳደር እንዳለባቸው ነው፡፡ ምእመናን ጳጳሳትን፣ ቀሳውስትን እና ዲያቆናትን እጅግ እንዲያከብሩ በተደጋጋሚ ይናገራል:: ምእመንስ ይቅርና፥ ካህናትም እንኳ ቢሆኑ ከጳጳሳት ዕውቅናና ፈቃድ ውጭ ምንም ነገር እንዳያደርጉ ያስጠነቅቃል፡፡ እንዲህ ይነቱን ሥርዐት በሥላሴ ዘንድ ካለች የፈቃድ አንድነትና ስምነት ጋር እያነጻጸረ በቤተ ክርስቲያንም እንደዚህ አይነት ፍጹም የሆነ የልብና የሐሳብ አንድነት እንዲኖር ያስተምራል፡፡
“[አይሁድ ክርስቶስን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ትቃወማለህ ባሉት ጊዜ] ‘እኔ ከራሴ አንዳች አደርግ ዘንድ አልችልም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም እውነት ነው፥ የላከኝን ፈቃድ እንጂ የእኔን ፈቃድ አልሻምና’ [ማለትም እኔ ምንም ምን ከራሴ ብቻ አንቅቼ አላስተምርም: በህልውና እንደሰማሁ አስተምራለሁ እንጂ፤ የእኔ ፈቃድ ከአባቴ ፈቃድ ልዩ፣ እንግዳ ሆኖ የእኔ ፈቃድ ሊደረግ አልወድም፤ የእኔ ፈቃድ ከአባቴ ፈቃድ አንድ ነውና የአባቴ ፈቃድ ሊደረግ እወዳለሁ እንጂ] እንዳለ (ዮሐ. 5፥30፣ ወንጌል አንድምታ) እናንተም ካህናትም ሆናችሁ ዲያቆናት ወይም ምእመናን ያለ ጳጳሱ ፈቃድ ምንም ነገር አታድርጉ:: እንዲህ ያለው ተግባር ኀጢአት እና የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚቃወም ነው” (Epistle to the Magnesians, chapter 7)፡፡
ካህናትን የሚያቃልሉ ለካህናት የማይታዘዙ ሁሉ መጨረሻቸው ጥፋት እንደ ሆነ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፡-
“ሁሉም ነገር መጨረሻ ያለው መሆኑንና ትእዛዙን በመጠበቃችን ሕይወት እንደ ተዘጋጀልን፣ ያለመታዘዝ ፍጻሜው ግን ሞት እንደ ሆነ፣ ሁሉም እያንዳንዱ እንደ ምርጫው ወደየቦታው እንደሚሄድ ተገንዝበን ከሞት ርቀን ሕይወትን እንምረጥ” (Epistle to the Magnesians, chapter 5)፡፡
ይቀጥላል…

10 comments:

  1. እግዚአብሔር ይስጥልን፣ቃለ ሕይወት ያሰማልን።

    ReplyDelete
  2. ቃለ ሕይወት ያሰማልን መንግስተ ሰማያት ያውርስልን ፀጋውን ያብዛሎት

    ReplyDelete
  3. Thank you.God bless you and your family..

    ReplyDelete
  4. ቃለ ሕይወት ያሰማልን እግዚአብሔር ከቅዱስ አግናጥዮስ በረከት ይክፍለን

    ReplyDelete
  5. በጣም እናመሰግናለን ቃለ ሕይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  6. ቃለ ህይወትን ያሰማልን አሜን

    ReplyDelete
  7. ቃለሕይወት ያሰማልም

    ReplyDelete
  8. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  9. ቃለ ሂደት ያሰማልን

    ReplyDelete
  10. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount