Sunday, October 11, 2015

ዕለት ዕለት ቃለ እግዚአብሔርን ለማያነቡ ሰዎች የተሰጠ ተግሣፅ



በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መስከረም 30 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ቃለ እግዚአብሔር መንፈሳዊ መሣሪያ ነው፡፡ ይህን መንፈሳዊ መሣሪያ እንዴት እንደምንጠቀምበትና እንደምንታጠቀው ካላወቅንበት ግን በእጃችን ስላለ ብቻ ምንም ሊጠቅመን አይችልም፡፡ ጠንካራ ጥሩርና ራስ ቍር፣ ጋሻና ሰይፍ አለ እንበል፡፡ አንድ ሰው መጥቶም እነዚህን ታጠቃቸው፡፡ ነገር ግን ጥሩሩን በእግሩ፣ ራስ ቍሩን በራሱ ላይ ሳይኾን በዓይኑ ላይ፣ ጋሻውን በደረቱ ላይ ሳይኾን በእግሩ ላይ አሰረው እንበል፡፡ እንግዲህ ይህ ሰው እነዚህን መሣሪያዎች ስለ ታጠቀ ብቻ ጥቅም ያገኛልን? ይባስኑ የሚጎዳ አይደለምን? ይህ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ይህ ሰው ተጠቃሚ ያልኾነው ግን ከመሣሪያው ድክመት አይደለም፤ እንዴት መጠቀም እንዳለበት ሰውዬው ስለማያውቅ እንጂ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘንድም እንደዚህ ነው፡፡ ትእዛዙን በአግባቡ የማንጠቀምበት ከኾነ የቃሉ ኃይል ምንም ባይቀንስም እኛ ግን ምንም የምንጠቀመው ነገር አይኖርም፡፡

ምንም እንኳን ይህን ነገር በግልም ኾነ በጉባኤ ደጋግሜ ብነግራችሁም ምንም ያመጣችሁት ለውጥ የለም፡፡ በዚህ ዓለም ሐሳብ ተጠፍራችሁ ነው የማያችሁ፡፡ ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ስታስቡ አላያችሁም፡፡ ሕይወታችን በግድ የለሽነት የተመላ ስለ ኾነና ይህንን ኃይል ስለማንጠቀምበት የአሕዛብ፣ የአይሁድና የመናፍቃን መሳቂያ መሳለቂያ ኾነናል፡፡ በሌላ ነገር ላይ ግድየለሾች ብትኾኑና በዚህም (በመንፈሳዊውም) እንደዚያ ግድየለሾች ብትኾኑ ኖሮ ይኼን ያህል የሚወቅሳችሁ ሰው ባልተገኘ ነበር፡፡ ነገር ግን በዚህ ዓለም ሥራ ላይ እያንዳንዳችሁ - በምድራዊ ሙያችሁና በፖለቲካ ሥራችሁ ላይ ከሰይፍ በላይ ስሎች ናችሁ፡፡ በሚያስፈልገውና በመንፈሳዊው ነገሮች ላይ ግን ከማንም - ለምሳሌ የንግድ ሥራ ከሚሠሩ ሰዎች - በላይ ደነዞች ነን፤ የቀን ሥራ ከሚሠራ ሰው እኩል እንኳን አንደክምም፡፡
እስኪ ንገሩኝ! መጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመሪያው ሰው (ለአዳም) ሳይኾን ለእኛ እንደ ተጻፈ አታውቁምን? ብጹዕ የሚኾን ጳውሎስ፡- “በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይኾንልን ዘንድ የመጨረሻ ዘመን የደረሰብንን እኛን ሊገሥፀን ተጻፈ” /1ኛ ቆሮ.10፥11፣ ሮሜ.15፥4/ ብሎ የተናገረውን ኃይለ ቃል አልሰማችሁምን?
በከንቱ እየተናገርኩ እንደ ኾነ ዐውቃለሁ፡፡ ንግግሬ ከንቱ ኾነ ብዬ ግን እንዲህ መናገሬን አላቋርጥም፡፡ ማንም የሚሰማኝ ባይኖርም በእግዚአብሔር ፊት የራሴን ድርሻ እወጣለሁ፡፡ በማስተዋል ለሚያደምጡት ሰዎች የሚናገር ሰው ቢያንስ ቢያንስ የሚላቸው ነገር ስለሚገባቸው ስለ ንግግሩ ደስ ይሰኛል፡፡ ዘወትር የሚናገር፣ ግን ደግሞ ማንምም የማያደምጠው ኾኖ ሳለ ንግግሩን የማያቋርጥ ሰው ከሰሚዎቹ ይልቅ ክብሩ ታላቅ ይኾናል፡፡ ምክንያቱም ማንም የሰማው ሰው ባይኖርም የቻለውን ያህል ፈቃደ እግዚአብሔርን ፈጽሟል፡፡ እኛም፥ ምንም እንኳን ቅዱሳት መጻሕፍትን ዕለት ዕለት እንድታነቡ ነግረናችሁ ባትታዘዙንም፣ የእኛም ሹመት ሽልማት ታላቅ ቢኾንም፥ የእኛ ሹመት ሽልማት ቀንሶ የእናንተ መዳን ይበዛ ዘንድ እንወዳለን፡፡ ይህንን ስንነግራችሁ እንኳን እናንተን ለማሳዘንና ሸክም እንድናከብድባችሁ ብለን አይደለም፡፡ በስንፍናችሁ ምክንያት ምን ያህል እንደምናዝንባችሁ እንድታውቁ ብለን እንጂ፡፡
መንፈሳዊ ቅንዓት ያድርብን ዘንድ፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ቸርነት ተስፋ የምናደርጋት መንግሥትም እንወርስ ዘንድ እግዚአብሔር ከእንደዚህ ዓይነት ስንፍና ያውጣን፡፡ ከእርሱም ጋር ለባሕርይ አባቱ ለአብ፣ ለባሕርይ ሕይወቱ ለመንፈስ ቅዱስ ክብር ይኹን፤ ዛሬም ዘወትርም እስከ ዘለዓለሙ ድረስ አሜን፡፡ 

2 comments:

FeedBurner FeedCount