Thursday, October 8, 2015

ዘመነ ጽጌ



በዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መስከረም 27 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ክኅሎቱ ከፍጡራን ኅሊና በላይ የሆነ የቅዱሳን አምላክ የመላው ዓለም ፈጣሪ "ይህን" የሚታየውንና "ያን" የማይታየውን ሁሉ መልካም አድርጎ ፈጥሮታል:: በዚህም ሁሉ ውስጥ ፍጥረታቱ ለመገኘታቸው ሦስት መንገዶች እና ሦስት አላማዎች ታይተዋል:: መንገድ ላልነው በኃልዮ(በማሰብ) የተፈጠሩ አሉ እንደመላእክት ያሉት ለዚህ ምሳሌ ሆነው ይቀርባሉ:: ደግሞም በነቢብ(በመናገር) የተፈጠሩ አሉ እንደ ብርሃን ያሉትን ለአብነት መጥቀስ የሚቻል ሲሆን በሦስተኛው መንገድ በገቢር (በሥራ) የሰውን ልጅ ብቻ ፈጥሮታል:: ለሦስት አላማ ያልነውን ስናይ ደግሞ፡-

ለአንክሮ ለተዘክሮ የተፈጠረ አለ:- ይህ ለመጠቀሚያ ነው:: የዚህ ዓይነት ፍጡር መኖሩ ለፈጣሪ ሃለዎት ማስረጃነት እርባና ያለው ነው:: " የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና"~~"ተፈጥሮ እንኳ አያስተምራችሁምን?" (ሮሜ.1:20,1.ቆሮ. 11:15) እንዲል::
ለምግብነት የተፈጠሩም አሉ:- እነዚህ ጉልበትን ያጠነክራሉ የኑሮ መሰረት ይሆናሉ "እክል ያጸንዕ ኃይለ ሰብዕ .... እህልም የሰውን ጕልበት ያጠነክራል።"~~"የኑሮህ መጀመርያ የምትበላው እህል ...ነው" (መዝ.103:15, ሲራ 29:21)ይላልና:: ሦስተኛው ወገን መላእክትንና የሰው ልጆችን የያዘ ሲሆን እነዚህም ጥንቱን ፈጣሪያቸውን አመስግነውት ክብሩን ይወርሱ ዘንድ ተፈጥረዋል::
በዚህ የሥነ ፍጥረት ፍልስፍና ውስጥ ሊቃውንቱ የመጀመርያው ፍጥረት ጊዜ ነው ይላሉ:: ሊቀ ነቢያት ሙሴ የዘልደት መጀመርያ ባደረገው መነሻ እንዲህ ይለናል "በቀዳሚ ገብረ እግዚአብሔር ሰማየ ወምድረ " (ዘፍ 1:1) በመጀመርያ ብሎ ጊዜ ቀዳሚ ግኝት የግኝቶችም ልኬት ቀመር መሆኑን ይጠቁመናል:: የአልዓዛር ልጅ ሲራክ የተባለ ኢያሱ በመጽሐፉ እግዚአብሔር ከምድር በአርአያውና በአምሳሉ ለፈጠራቸው ለሰው ልጆች ከሰጠው ገጸ-በረከት ቀዳሚው ጊዜ ነው ይለናል:: " ዘመንን ቀንን በቁጥር ሰጣቸው"(ሲራ 17:2) በዚህ የጊዜ ምህዋር ውስጥ ደግሞ የአዝማናትን ኡደት የወቅቶችን መፈራረቅ የሚቆጣጠር ምድርን በዳርቻው የሚያጸናው እርሱ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ነው:: "አንተ የምድርን ዳርቻ ሁሉ ሠራህ በጋንም ክረምትንም አንተ አደረግህ።" እንዲል(መዝ. 75:17)::
አንድ ዓመት በአራት ወቅቶች(አዝማናት) የተከፋፈለ ነው:: እነዚህም፡-
ü ዘመነ መጸው
ü ዘመነ ሐጋይ
ü ዘመነ ጸደይና
ü ዘመነ ክረምት ይባላሉ:: (የዘጠኝ ወር በጋ
የአስራ ሶስት ወር ጸጋ የሚል ብኂል በማኅበረሰቡ ዘንድ አለ)
አሁን ያለነው ከመስከረም 26 እስከ ታህሳስ 25 ድረስ 90 ዕለታት በሚታሰበው ዘመነ መጸው ወርኃ ነፋስ ውስጥ ነው:: በሥሩም አምስት ንዑሳን ክፍላት ያካትታል ዘመነ ጽጌ: ዘመነ አስተምሕሮ: ዘመነ ስብከት: ዘመነ ብርሃንና ዘመና ኖላዊ የሚባሉትን:: ለዚህም እንዲህ የሚል አብነት ይገኛል "ወለእመ ፈቀድከ ታእምር ክፍለ ዘመኑ ለመጸው ትዌጥን እምዕስራ ወሰዱሱ ለመስከረም ወትፌጽም እምዕሥራ ወሐሙሱ ለታህሳስ ወኁልቆ ዕለቱ ተስአ ውእቱ ወእምዝ ኢታህፅፅ ወኢትወስክ:: በውስቴቱ ሐለዉ ሐምስቱ ንዑሳት ክፍላት ዘውእቶሙ ዘመነ ጽጌ: ዘመነ አስተምሕሮ: ዘመነ ስብከት: ዘመነ ብርሃን ዘመና ኖላዊ"

በዚሁ ዘመን ሥር የመጀመርያው ንዑስ ክፍል ዘመነ ጽጌ (የአበባ ጊዜ) ከመስከረም 26 እስከ ህዳር 5 ያለውን 40 ዕለታት አካቶ የያዘው ነው:: በጊዜም ለምዕመናን የነፍስ ቀለብ የሰማይ ፍኖት ስንቅ በዜማ ቢሉ በንባብ በብዙ ህብረ አምሳል ስለ አበባ በቤተክርስቲያናችን ወንጌል ይሰበካል በነገረ ሃይማኖትና በክርስቲያናዊ ሕይወት ዙርያ ሰፊ ትምህርት ይሰጣል:: እስኪ በጣም በጥቂቱ አበባን በቤተ ክርስቲያናችን ለነገረ ሃይማኖት አስተምሮ በዘመነ ጽጌ እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውል እንመልከት::
ስለ ነገረ ክርስቶስ
ሊቃውንቱ "ቡሩክ እጽ ዘሰናየ ይፈሪ ወኃጢዓተ ይሰሪ" እያሉ መልካም ፍሬን የሚያፈራ ኃጢዓትን የሚደመስስ ቡሩክ እጽ(የበረከት እንጨት) ክርስቶስ መሆኑን ከሊቁ የማኅሌት ምንጭ ቅዱስ ያሬድ ድጓ ጠቅሰው ይመሰክራሉ :: መልሰውም ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ "ትወጽእ በትር እምስርወ እሴይ ወየአርግ ጽጌ" (ኢሳ.11:1) ያለውን ምስጢራዊ የትንቢት ፍጻሜ ይዘው እንዲህ ይላሉ "ይእቲ በትር አምሳለ ማርያም ቅድስት ወጽጌ ዘወጽአ እምኔሃ አምሳሉ ለወልድ=ይህችውም በትር የቅድስት እናቱ የድንግል ማርያም ምሳሌ ናት ከእርሷ የተገኘው አበባም የወልድ አምሳል ነው":: በዚህም ላይ የድንግል አበባ ክርስቶስ "የእግዚአብሔር ጸጋ ለማንም እንዳይጎድለው፥ ብዙዎቹም የሚረክሱበት አንድ መራራ ሥር ወደ ላይ በቅሎ እንዳያስጨንቅ" በበጎ መአዛው የመላውን ዓለም ክፉ ጠረን ለውጦ በመልካም ጣዕም ከህዝብና ከአህዛብ መራራነትን አጥፍቶ ህዝቡን ሁሉ ስለማዳኑ ይነገራል(ዕብ 12:15):: በጥልቀትም ናዝራዊ የነበረው ብርቱ ሰው ሶምሶን "እምአፈ በላኢ ተረክበ መብልዕ ወእምአፈ ህሱም ተረክበ ጣዕም" ብሎ ለጠየቀው እንቆቅልሽ ፍቺ በፍፃሜው ከበላተኛ የተገኘ ምግብ ከመራራው የሰውልጅ ግንድ የተገኘ ጣፋጭ ፍሬ ክርስቶስ ሁሉን አጽንቶ ለአበባና ለፍሬ እንዳበቃ ምስክርነት ይሰጣል(መሳ. 14:14)::
ስለ ነገረ ማርያም
"መዝገቡ ለቃል ጽጌ እንተ ኢትትነገፍ" ይህችን ለቅዱሳን አበው የህሊናቸው እረፍት..... ለፍሬ ሕይወት ክርስቶስ የማረፊያው ሙዳይ የሆነች አበባ ድንግል ማርያምን "የቃል ማደርያ የሆነች የማትረግፍ አበባ" እያለ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ያወድሳታል ሊቃውንቱም በምስጋናው ይተባበሩታል::
ይልቁንም ዘመኑ ዘመነ ጽጌ የሌሊቱ ምስጋና ማኅሌተ ጽጌ የምስጋናውም ደራሲ አባ ጽጌ ድንግል እየተባለ ድንግል የተወደደ ልጇን ይዛ ወደ ግብጽ በረሃ መሰደድዋን በማሰብ መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞን "በእሾህ መካከል እንዳለ የሱፍ አበባ፥ እንዲሁ ወዳጄ በቈነጃጅት መካከል ናት።" ያለውን ምስጢራዊ ፍቺ እሾህ ከሆኑ አይሁድ መካከል ተገኝታ በሃይማኖት አብባ ፍሬ ትሩፋት ሰርታ የተገኘች የቆላ የሱፍ አበባ ድንግል ማርያም መሆኗን እየገለጡ "ሌቱን" የንጋትዋን ምስራቅ የፀሐይ መውጫዋን ሲያመስግኗት ያድራሉ:: (መኃ 2:2)
ስለ ነገረ መስቀል
ቀድሞ በዘመነ መስቀል (ከመስከረም 17 እስከ መስከረም 25) ለዘጠኝ ቀናት ሲነገር የቆየው ምስጢር መስቀል አበባ ተብሎ እየተዘመረ ከዚህም ይሻገራል:: ልብ በሉ አዳም ወደ ሞት እንጨት (እጸ በለስ) እጆቹን ዘርግቶ ሞቱን ቢያቀብለን ከማዕረጋችን ተዋርደን ወደ ምድርም ወረድን ክርስቶስ ግን ወደ ሕይወት እንጨት (እጸ መስቀል) እጆቹን ዘርግቶ ሕይወቱን ቢያቀብለን ወደ ቀደመ ክብራችን ተሻገርን:: ምንም እንኳ ጢቢቡ በማኅሌቱ "እነሆ፥ ክረምት አለፈ፥ ዝናቡም አልፎ ሄደ።አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፥ የዜማም ጊዜ ደረሰ"(መኃ 2:11) እንዳለው ዘመነ ክረምቱም ቢያልፍ ዘመነ መጸው ቢተርፍ ዜና መስቀሉ ግን ዓመቱን ሁሉ ይሰበካል:: ለዚህም የመንፈሳዊው ዜማ አባት ቅዱስ ያሬድ
"
በከመ ይቤ ሰሎሞን በእንተ ማርያም ንዑ ንትፈጋዕ ወኢይኅልፈነ ጽጌ ደመና መስቀል ዘዮም አብርሃ በስነ ማርያም= ሰሎሞን ስለ ማርያም እንደተናገረው ደስ ይበለን የበረከቱ አበባ አይለፈን ይኸውም ዛሬ በማርያም ውበት (በድንግል ባህሪ በክርስቶስ ሥጋ) መስቀሉ አብርቷልና" (ድጓ ዘዘመነ ጽጌ)
ስለ ነገረ ቤተ ክርስቲያን
ሥሯ በምድር ላይ ቅርንጫፎቿ በሰማይ ያለውን ኆኅተ ሰማይ ቤተ ክርስቲያንን ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ "እነሆ፥ ድንጋዮችሽን ሸላልሜ እገነባለሁ፥ በሰንፔርም እመሠርትሻለሁ።የግንብሽን ጕልላት በቀይ ዕንቍ፥ በሮችሽንም በሚያብረቀርቅ ዕንቍ፥ ዳርቻሽንም ሁሉ በከበሩ ድንጋዮች እሠራለሁ።ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፥ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል።...በአንቺ ላይ የተሠራ መሣሪያ ሁሉ አይከናወንም በፍርድም በሚነሣብሽ ምላስ ሁሉ ትፈርጂበታለሽ። የእግዚአብሔር ባሪያዎች ርስት ይህ ነው፥ " (ኢሳ 54:11) ሊቁ ይህን ሲገልጥ የቤተ ክርስቲያንን ውበት እንዲህ እያለ ያደንቃል "በከመ አሰርገዎሙ ለሰማይ በከዋክብት ወለምድርኒ በሥነ ጽጌያት ከማሁ አሰርገዋ ለቤተ ክርስቲያን በደመ ሰማዕታት = ሰማያትን በከዋክብት ያስጌጠ ምድርንም በአበባ የሸለመ ቤተ ክርስቲያንንም በሰማዕታቱ ደም አስሸበረቃት" መሠረተ ዜማ ቅዱስ ያሬድም ለቤተ ክርስቲያን የመወደድ ጌጧ የሰማዕታት ገድል መሆኑን እንዲህ እያለ አስረድቷል "ሰማዕትኒ ያሰረግዋ ለቤተ ክርስቲያን በገድሎሙ" /ድጓ ዘቴዎቅርጦስ /
ጽጌን (አበባን) በጠንካራ ጎንና መልካም ምሳሌው ከላይ ያየነውን ጥልቅ የነገረ ሃይማኖት ማብራርያ ከዚህ እናቆየውና ወደኛ ከሚሻገረው የክርስቲያናዊ ሕይወት ምክር እንፃርሰው ደካማ ባህሪያት አብነት የሚሆኑ የጽጌን ደካማ ባህሪያት የሚመለከቱ ጥቂት ነጥቦችን እንደማጠቃለያ ለመመልከት እንሞክራለን:: ከአቃፊው ወጥቶ ለዓይን የሚማርከው እምቡጥ አበባ ሲፈነዳም ለአፍንጫ የሚያውደው መልካም መአዛ ዘላቂ ሳይሆን አላቂ ቋሚም ሳይሆን ጊዜአዊ ነው::
ልብ እናድርግ ለአበባ ህጹጽነቱ ፈጥኖ መጠውለጉና በጊዜ መወሰኑ ነው እኛም ሥጋ ለባሾቹ የሰው ልጆች በምድር ላለን ቆይታ ህያው ሆኖ ነዋሪ በምድር ላይ ቀሪ ማንም የለምና እንደዚሁ ነን::
ፈጥኖ እንደመጠውለግ ....... ቅዱስ ዳዊት እንዲህ ይላል "ሰውስ ዘመኑ እንደ ሣር ነው እንደ ዱር አበባ እንዲሁ ያብባል ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ያልፋልና፥ ስፍራውንም ደግሞ አያውቀውምና። "(መዝ. 102:15) ቅዱስ ያሬድም በዘመነ ጽጌ ድጓው እንዲህ ሲል ከነቢዩን ቃል እያጣቀሰ ነገሩን ያጸናዋል "ተዘከር እግዚኦ ከመመሬት ንህነ ዘለሐኮ በእዴከ ኢታማስን ህዝበከ ከመጽጌ ገዳም ዘይፀመሂ ፍጡነ ከማሁ መዋዕሊነ....አቤቱ እኛ እኛ እንደ አፈር መሆናችንን አስብ የምድረ በዳ አበባ ፈጥኖ እንደሚጠወልገው እኛም ዘመን እንደዚያው ነውና በእጅህ ያበጀኸውን ህዝብህን አታጥፋ":: እንግዲህ በአምላኩ ፊት ሰው ምን ያህል ደካማ እንደሆነ እናስተውል:: ታዲያ ስለምነው በሚያልፍ እውቀቱ: በሚጠፋ ጉልበቱ: በሚረግፍ ውበቱ: በሚያልቅ ሀብቱ ሲታመን የሚኖር? ቅዱስ ያሬድ ግን እንዲህ እያለ ይዘልፈናል "ብዕሉሰ ለሰብዕ ከመጽጌ ገዳም ወኃይሉሰ ለሰብዕ ከመ ሳዕር ድኩም...የሰው ንብረቱ እንደምድረ በዳ አበባ ኃይሉም እንደደረቅ ሳር ነው" አዎ የምንመካበት ክብራችን ታይቶ ጠፊ ፈጥኖ ጠፊ ነው:: ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስም "ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሣር ነው፥ ክብሩም ሁሉ እንደ ምድረ በዳ አበባ ነው። " ሲል የተናገረው መልእክት የተነሳንበትን ፍሬ ሃሳብ የሚያጠናክር ነው (ኢሳ. 40:6)::
በጊዜ እንደመወሰን .... ፈጣሪያችን ቅድመ ዘመናት የነበረና ዓመታቱ ሳያልቅ ድኅረ ዘመናት የሚኖር ነውና ሁሉን በጊዜአቸው ይለውጣቸዋል ያሳልፋቸውማል:: "አቤቱ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው። እነርሱ ይጠፋሉ፥ አንተ ግን ትኖራለህ ሁላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጐናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፥ ይለወጡማል:: አንተ ግን ያው አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም።" (መዝ 101:26) በኢየሩሳሌም የነገሠው ሰባኪው የዳዊትም ልጅ እንዲህ ይላል "ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው።" (መክ. 3:1) አበባ በዘመነ ጽጌ ወቅትን ጠብቆ የሚተርፍ ጊዜው ሲያልፍ የሚያልፍ ዘር ለፍሬ መብቃቱን እንደምልክት የሚያስረዳ ለኑሮውም የወራት እድሜ ብቻ የተቸረው ነው:: "ጽጌ ገዳምኒ በጊዜሁ የኃልፍ ኩሉ በጊዜሁ የሐልፍ ወዘኢየሐልፍ አልቦ
ዘይመጽእ...የምድረበዳ አበባ በጊዜው ያልፋል ሁሉም በጊዜው ያልፋል ላያልፍ የሚመያ የለም"ይለናል ቅዱስ ያሬድ :: እንግዲህ ይህን ወደኛ ሕይወት ስናመጣው ቅዱስ ዳዊት "ዘመናችን ሁሉ አልፎአልና፥ እኛም በመዓትህ አልቀናልና ዘመኖቻችንም እንደ ሸረሪት ድር ይሆናሉ። የዘመኖቻችንም ዕድሜ ሰባ ዓመት፥ ቢበረታም ሰማንያ ዓመት ነው ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው ከእኛ ቶሎ ያልፋልና፥" መልሶም "ሰው ከንቱን ነገር ይመስላል ዘመኑ እንደ ጥላ ያልፋል።" (መዝ.89:10,143:4) ይለናል::
ማጠቃለያ
በሚያልፍ ዘመኑ የማያልፍ ሥራ የሚሰራ በተወሰነለት መዋዕሉ ፈቃደ ሥጋውን ወስኖ ለነፍሱ ሥምረት ያደረ የሰማይ አእዋፋትን ያጠገበ የምድር አበቦችን ያስሸበረቀ ፈጣሪ "እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን?" ሲለን በቅዱስ መጽሐፍ እናነባለን:: "የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፤ የሚለውን የጌታችንን ቃል ይዘን ጊዜው ዘመነ ጽጌ ከምድር አበቦች የምንማርበት ወቅት ነው አበባ ለአንክሮ ለተዘክሮ ተፈጥሯልና (ማቴ.6:28):: ምን አበባ በህጹጽ መገለጫው በጊዜ የሚወሰን እና ፈጥኖ የሚጠወልግ ሆኖ ለደካማው የሰው ልጅ የሥጋ ጠባይ መገለጫ ሆኖ ትምህርት ቢሰጥ ይህን እያየን በነፍስ ደርቀን ወደማንጠወልግበት ተቀብረን ወደማንቀርበት ዘልዓለማዊ ሕይወት ለመሻገር የሚሰራው ሁሉ ለሚከናወንለት ምሳሌ የተገለጸውን ዕለት ዕለት በደጁ እየተጋ ከህይወት ምንጭ ቅዱስ ቃሉ እየጠጣ አበባቱ ሲያልፍ የሃይማኖት ቅጠሉ ሳይረግፍ የምግባር ፍሬ እየሰጠ በዘመናት ሳያፍ ዘመናትን የሚያሳልፍ መልካሙን ዕፅ መስሎ መኖር ይገባል "... ከመ ዕፅ እንተ ትክልት ሀበ ሙኃዘ ማይ እንተ ትሁብ ፍሬሃ በበጊዜሃ ወቆጽላኒ ኢይትነገፍ ወኩሎ ዘገብረ ይፌጽም= ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ ቅጠሏም እንደማይረግፍ በፈሳሽ ውኃ ዳር እንደ ተከለች ዛፍ የሚሰራው ሁሉ ይከናወንለታል" (መዝ 1:3)፡፡
ይቆየን!

5 comments:

  1. እግዚአብሔር አምላክ ቃለ ሕይወት ያሰማልን፣ አሜን፡፡

    ReplyDelete
  2. እግዚአብሔር አምላክ ቃለ ሕይወት ያሰማልን፣ አሜን፡፡

    ReplyDelete
  3. እግዚአብሔር አምላክ ቃለ ሕይወት ያሰማልን የአገልግሎት ዘመንህን ይባርክልን፡፡

    ReplyDelete
  4. amen.......egziabhier abatochin ayasatan.

    ReplyDelete
  5. እግዚአብሔር አምላክ ቃለ ሕይወት ያሰማልን፣ አሜን፡፡

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount