Saturday, January 9, 2016

ስግደት (ክፍል 1)


በዲ/ ሕሊና በለጠ ዘኆኅተ ብርሃን


(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ 30 ቀን 2008 ..)- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
 በፍጹም ልብ በፍጹም ነፍስ በፍጹም ኃይል (ዘዳ.65) የሚወደድ የሆነውን አምላካችን እግዚአብሔርን ስናመልከው ሥጋችንንም፣ ነፍሳችንንም፣ መንፈሳችንንም አስተባብረን መሆን አለበት፡፡ መጻሕፍትን በማንበብ፣ ለብዎትን /ማስተዋልን/ በመጠቀም፣ ዕውቀትን ገንዘብ በማድረግ፣ ነቢብን /ንግግርን/ በማስገዛት፣ ሀልዎትን /መኖርን/ በመሠዋትና በመሳሰሉት እግዚአብሔርን ማምለክ ባሕርያተ ነፍስን ለአምልኮተ እግዚአብሔር ማስገዛት ነው፡፡ ጾም/ከሥጋ ፍላጎት መከልከል/ እና ስግደትን የመሳሰሉት ደግሞ በሥጋ እግዚአብሔርን የምናመልክባቸው፣ ሥጋችንን የምናስገዛባቸው መንገዶች ናቸው፡፡ (ይህ ማለት ግን ስግደት ለሥጋውያን ብቻ የተገባ ነው ማለት አይደለም፤መላእክቱ ሁሉ ስገዱለት”/መዝ.977/ እንዳለ መላእክትም የሚሰግዱ ናቸውና፡፡) ፍቅር፣ ቸርነት፣ ምኅረት፣ መመጽወት እና የመሳሰሉት የመንፈስ ሥራዎች ደግሞ ወደ ፍጹምነት የሚወስዱን የሥጋን ድካምና የነፍስን ሐልዮት የምንቀድስባቸው እንዲሁም መንፈሳችንን ለአምልኮተ እግዚአብሔር የምናስገዛባቸው መንገዶች ናቸው፡፡

ስለዚህ ስግደት የሰው ልጅ የተፈጠረበትን ዓላማ (የሰው ልጅ የተፈጠረበት ዓላማ እግዚአብሔርን ማምለክ ነው) ከሚያሳካባቸው መንገዶች አንዱ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የሰው ልጅ ካለስግደት ሥጋውን ፍጹም መኮነን(መግዛት) አይችልምና ሰብእናው ምሉዕ አይሆንም፡፡
ስግደት ስንት ዐይነት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን ከአፈጻጸም ሥርዐት አንፃር ስግደት በሦስት ይከፈላል፡፡ የመጀመሪያው የስግደት አፈጻጸም ሥርዐት መሬት ላይ በመውደቅ ወይም ሙሉ በሙሉ ተደፍተው የሚሰግዱት ስግደት ሲሆን በልዩ ስሙ ወዲቅ በመባል ይታወቃል፡፡የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ሥርዐተ አምልኮትና የውጭ ግንኙነትየሚለው በሊቃውንት የተዘጋጀው የቤተክርስቲያናችን መጽሐፍ ይህንን የስግደት ዐይነት ሰጊድ /Prostration/ ብሎ ገልጾታል፡፡(ገጽ 85) ዮሐንስ ወንጌላዊልሰግድለትም በእግሩ ፊት ተደፋሁ።”/ራእ.1910/ ያለው ወዲቅን እንደተገበረ የሚያሳይ ነው፡፡ መደፋቱ ከድንጋጤ ወይም ከመፍራት ወይም ከመታመም የመጣ እንዳልሆነ ሲነግረንልሰግድለትምአለ፡፡ በእግሩ ፊት የተደፋው ሊሰግድለት መሆኑን አስረዳ፡፡ ከዚህ በተጨማሪፊቱንም ደፍቶ ወደ ምድር ሰገደ” /ዘፍ.191/ “ሰገደም በግንባሩም ተደፋ” /ዘኁ.2231/ “በግንባሩ ተደፍቶ ሰገደ” /ኢያ.513/ “ማቅ ለብሰው በግንባራቸው ተደፉ” /1 ዜና.2116/ “በፊቱ ወደ ምድር ተደፉ” /2 ነገ. 215/ “በእግሩ አጠገብ ወደቀች፤ በምድርም ላይ ተደፋች” /2 ነገ.48/ “ከእግሩ በታች ወደቀና ሰገደለት” /ሐዋ.1025/ የሚሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ወዲቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው የስግደት ዐይነት መሆኑን የሚያስረዱ ናቸው፡፡

ሁለተኛው የስግደት ዐይነት ‪‎አስተብርኮ /Kneeling/ በመባል ይታወቃል፡፡ ይህም ስያሜው እንደሚጠቁመው ጉልበትን ሸብረክ በማድረግ፣ በጉልበት በመቆም ወይም በመንበርከክ የሚፈጸም ነው፡፡ ወዶ ፈቅዶ ራሱን ዝቅ አድርጎ በድኅነት ከፍ ላደረገን ክርስቶስ የአምልኮ ስግደትን መስገድ እንዲገባ ሲያጠይቅበሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድነውበማለት ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ፊሊጲስዩስ በላከው መልእክቱ የአስተብርኮ ስግደትን ለክርስቶስ መስገድ እንደሚገባ አስረድቷል፡፡ /ፊል.210/ ምንም እንኳን እያሾፉ ቢሆንም በማር. 1519 ላይ አይሁድ ለስም አጠራሩ ክብር ይሁንና ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስተንበርክከውም ሰገዱለትይላል፡፡ ምንም እንኳን ስግደታቸው የሹፈት፣ የማላገጥ ቢሆንም ጥቅሱ በመንበርከክ መስገድ እንዳለ የሚጠቁመን ነው፡፡ በዚሁ ምእራፍ በማላገጥ እጅ ነሥተውት ነበርና እጅ መንሣታቸው የሹፈት እንደሆነው ሁሉ ስግደታቸውም የማሾፍ ነበር፡፡ እጅ በመንሣት አሹፈዋልና እጅ አይነሣም እንደማይባለው በመንበርከክ ሰግደዋልና በመንበርከክ መስገድ አይገባም አይባልም፡፡


አንዳንድ ሰዎች ተንበርክኮ መጸለይ፣ ተንበርክኮ መስገድ የእኛ ትውፊት አይደለም፤ የቤተክርስቲያን ሥርዐት አይደለም ብለው እንደሚያስተምሩና ተንበርክከው የሚጸልዩትንም እንደሚገሥጹ ጠቅሰው በዚህም የተነሣ ተንበርክኮ መጸለይንና በመንበርከክ መስገድን እንደሚፈሩ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ተግሣጹ ስሕተት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ሌሎች ያዙትና መጽሐፍ ቅዱስን መያዝ የኛ አይደለም እንደማለት አይነት ከንቱ ጨዋነት ነው፡፡ ሌሎች ደጋግመው ጌታ ጌታ ይላሉና ጌታ ማለት የኛ አይደለም እንደማለት ያለ አላዋቂነት ነው፡፡ (በርግጥ በምዕራባውያን ዘንድ ተንበርክኮአምልኮ መፈጸም የተለመደ ነው፡፡ ሆኖም በምሥራቁ ነገረ ሃይማኖት ተንበርክኮ መስገድም ሆነ መጸለይ የተከለከለበት ቦታ የለም፡፡)
ሦስተኛው የስግደት አፈጻጸም ዐይነት አድንኖ /Bowing/ ይባላል፡፡አድንኖ ራሥን፣ ግንባርን፣ አንገትን ዝቅ በማድረግ የሚሰገድ ነው - “አድንኑ አርእስቲክሙ ቅድመ እግዚአብሔር አምላክነ…” እንዲባል በቅዳሴ፡፡ ይህም እንደቀደሙት ሁለቱ የስግደት አፈጻጸም ዐይነቶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው ነው፡፡ በትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 49 ቁጥር 23 ላይግንባራቸውን ወደ ምድር ዝቅ አድርገው ይሰግዱልሻልይላል፡፡ ካህናትምበንስሐ ውስጥ ያላችሁ ራሣችሁን ዝቅ ዝቅ አድርጉማለታቸው አድንኖን በመፈጸም ስገዱ ሲሉን ነው፡፡
ወዲቅም፣ አስተብርኮም ሆነ አድንኖ የስግደት አፈጻጸም ዐይነቶች ናቸው እንጂ ከስግደቱ ዓላማ ጋር ወይም ከሚሰገድለት አካል አንጻር የሚፈጸሙ አይደለም፡፡ በሌላ አገላለፅ ሦስቱን የስግደት ዐይነቶች ስግደት ለሚገባው ሁሉ እንፈጽማለን - ሦስቱንም ዐይነት ስግደት ለእግዚአብሔርም ለቅዱሳንም እናቀርባለን፡፡ ነገር ግን የመስገዳችን ምሥጢሩ ይለያያል፡፡ ይህንንም እንደሚከተለው እንየው፡፡

ስንዱዋ እመቤት ቅድስት ቤተክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጋ ከዓላማው አንፃር ሁለት ዐይነት ስግደት እንዳለ ታስተምራለች፡፡ በሌላ አገላለጽ ስግደቱ ከሚቀርብለት አካል ማንነት አንጻር ስግደት በሁለት ይከፈላል፡፡
‪          የመጀመሪያው ለእግዚአብሔር የምንሰግደው የስግደት ዐይነት ሲሆን የአምልኮ /የባሕርይ/ ስግደት ይባላል፡፡ /የአምልኮ ስንል በባሕርዩ አምላክ ለሆነው ማለታችን ነው፤ በጸጋ አማልክት የተባሉ እንደ ሙሴ ያሉ ቅዱሳን አሉና - ዘጸ.71/ ይህን ስግደት አንድ አምላክ ከሚሆን ከእግዚአብሔር ውጭ ለማንም መስገድ አይቻልም፡፡በዘወትር ጸሎት ላይእሰግድ ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐተ ስግደተ - ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አንዲት ስግደትን እሰግዳለሁማለቱ ይህንን ምሥጢር የሚገልፅ ነው፡፡አሐተ - አንዲትየሚለው የስግደቱን መጠን ወይም ቁጥርን ለመግለፅ ሳይሆን ስግደቱ በባሕርዩ ለሚመለክ ለአንድ አምላክ የሚሰገድ ለሌላ አካል የማይሰገድ የአምልኮ ስግደት መሆኑን ሲጠቁመን ነው፡፡አንድ ጊዜ ብቻ ስገዱብሎ ቁጥርን ለማመልከት ቢሆን ዝቅ ብሎ “3 ጊዜ በልብሎ አንዲት ስግደት የሚለውን 3 ጊዜ እያልን ሦስት ጊዜ እንድንሰግድ አያዘንም ነበር፡፡አንዲትየሚለውን ቃል እንዲህ መተርጎማችን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረትነትን ይዘን ነው፡፡ ብሥራተ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ሊያበሥር መላኩን ቅዱስ ሉቃስ ሲገልጽወደ አንዲት ድንግል ተላከ” /ሉቃ.127/ ብሏል፡፡አንዲት ድንግልየሚለው ቁጥርን ሳይሆን የድንግሊቱን ልዩ መሆን የሚጠቁም መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ እሷም ድንግልናዋም የተለዩ መሆናቸውን የሚገልፅ ነው፡፡ ቁጥርን የሚገልፅ ነው ከተባለማ በዚያን ጊዜ በምድር ላይ አንዲት ድንግል ብቻ አለች ወይም በዚያን ጊዜ በምድር ላይ ያሉ ድንግሎች ብዛት ሁለት እንኳን አይሞላም ወደ ሚል ስሌት ይመራናል፡፡ ዕለቱን እንኳን የሚወለዱ ሕፃናት ደናግላን አሉ፡፡ በተመሳሳይም በዮሐንስ ራእይአንዲት ሴት ነበረች” /ራእ.121/ ሲል በምድር ያሉት ሴቶች ሁለት እንኳን አይሞሉም ለማለት ሳይሆን የሴቲቱን ፍጹም የተለየች መሆን፣ ወይም በእሷ ደረጃ የሚገኝ ሌላ ሴት/ፍጡር አለመኖሩን ሲገልፅልን ነው፡፡ ብዙ ሴቶች በምድር እንደነበሩማ መጽሐፍ ቅዱሳችን በብዙ ቦታ መስክሯል፡፡በተመሳሳይም ከላይ ጸሎተ ሃይማኖታችንም አንዲት ስግደት ማለቱ ለእግዚአብሔር ብቻ የሚገባ መሆኑን ሲያመለክት ነው፡፡
ሁለተኛው ጸጋ እግዚአብሔርን ላገኙ ቅዱሳን ሁሉ የሚሰገድ የጸጋ ስግደት ነው፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ መስቀል ቅዱሳን መላእክት ሰማዕታት ፃድቃን ቅዱሳን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን ቦታዎች ታቦት ቅዱሳት ንዋያት እዚህ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡ የዘወትር ጸሎትለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አንዲት ስግደትን እሰግዳለሁብሎ አያቆምም፤አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ለድንግል ማርያምም እሰግዳለሁ፤ ዓለምን ሁሉ ለማዳን ሲል ኢየሱስ ክርስቶስ ለተሰቀለበት መስቀልም እሰግዳለሁበማለት የጸጋ ስግደትን ለቅድስት ሥላሴ ከሚሰገደው የባሕርይ ስግደት ለይቶ እግዚአብሔር ለቀደሳቸው ሁሉ እንደሚገባ የሚያስረዳ ነው፡፡ እኛ የዘወትር ጸሎት የሚባል ነገር አናውቅምየመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ አምጡ የሚሉም ካሉ እንደሚከተለው እናስረዳለን፡፡
ለቅዱሳን መስገድን ያስተማረው እግዚአብሔር ነው!
መጽሐፍ ቅዱስ ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ለቅዱሳን መስገድ አንደሚገባ ያስረዳል፡፡ በዘፍ. 2729 “አሕዛብ ይገዙልህ ሕዝብም ይስገዱልህ ለወንድሞችህ ጌታ ሁን፥ የእናትህም ልጆች ይስገዱልህ የሚረግምህ እርሱ ርጉም ይሁን የሚባርክህም ቡሩክ ይሁን።ብሎ ልጁን ያዕቆብን የባረከው ይሥሐቅ ነበር፡፡ ይህን ምርቃት ማግኘት የነበረበት የያዕቆብ ታላቅና በኩር የነበረው ኤሳው ቢሆንም ያዕቆብ በእናቱ ብልኃት ታግዞ ተመረቀ፡፡ ይሥሐቅን እንዲህ ብሎ እንዲመርቅ ያደረገው እግዚአብሔር አምላክም የአብርሃም የይሥሐቅና የኤሳው አምላክ በመባል ፋንታ የአብርሃም የይሥሐቅና የያዕቆብ አምላክ ተባለ፡፡ አምላካችንን ሙሴ ማነህ ብሎ በጠየቀው ጊዜም ራሱን ሲገልፅ እርሱ ራሱን ለአብርሃም ለይሥሐቅና ለያዕቆብ የሚገለጥና ምድረ ርስትንም ሊሰጣቸው ቃል እንደገባ ለሙሴ ገልፆለታል፡፡ ስለዚህ በይሥሐቅ አንደበት አድሮ ያዕቆብን የመረቀው እግዚአብሔር ነው፡፡ ይህንን የሚጠራጠሩ ቢኖሩ እንኳን የይሥሐቅን ምርቃት የፈጸመው /እንዲደርስ ያደረገው/ እግዚአብሔር ነው፡፡ ታዲያ አምላካችን ለቅዱሳን የሚገባን ስግደት የሚቃወም ቢሆን ይሥሐቅንሕዝብም ይስገዱልህብሎ ሲመርቅ አይገሥጸውም ነበርን? ባይገሥጸው እንኳንልጆች ይስገዱልህብሎ የመረቀ ይሥሐቅን ምርቃቱን ባለመፈጸም /እንዲደርስ ባለማድረግ/ ቃሉ ልክ እንዳልሆነ አያሳይም ነበርን? ደግሞስ ለፍጡር በሚገባ መስገድ ስሕተት ቢሆን ከብዙ ዘመን በኋላ ያዕቆብ ከነቤተሰቡ ለኤሳው በመስገድ የአባቱን የይሥሐቅንስሕተትይደግመው ነበርን?
ከዘፍ.37-41 ድረስ የፃድቁን የዮሴፍን ታሪክ እናገኛለን፡፡ በዚህ ክፍል እግዚአብሔር ለዮሴፍ እንደሚሰገድለት የሚተነብይ ሕልም አሳየው፡፡እኔ ያለምሑትን ሕልም ስሙ፡ እነሆ እኛ በእርሻ መካከል ነዶ ስናሥር ነበርና፤ እነሆም የእኔ ነዶም ቀጥ ብላ ቆመች፤ የእናንተም ነዶች በዙሪያ ከበው እነሆ ለኔ ነዶ ሰገዱ” /ዘፍ.377/፡፡ ወንድሞቹ ከሕልሙ የተነሣ እንደሚሰግዱለት ተረድተው ወንድማቸው ዮሴፍን ይበልጥ ጠሉት፡፡ለቅዱሳን አንሰግድም ብለው ቅዱሳንን የማያከብሩ ሰዎች በትዕቢት ራሳቸውን ከቅዱሳን በላይ በማድረግ፣ ወንድማቸውን ዝቅ ያደረጉትን የዮሴፍን ወንድሞች ይመስላሉ፡፡ እግዚአብሔር ግን ይህንን እንዲረዱት ዮሴፍ ነዶ በተባሉት በወንድሞቹ ብቻ ተሰግዶለት የሚቀር ሳይሆን በሌሎች ፍጥረታትም ዘንድ እንደሚከብር ሲገልፅላቸው ዮሴፍን ሌላ ሕልም ዐሳየው፡፡እነሆ ደግሞ ሌላ ሕልምን አለምሁ፣ እነሆ ፀሐይና ጨረቃ አሥራ አንድ ከዋክብትም ሲሰግዱልኝ ዐየሁ” /ዘፍ.379/፡፡ እግዚአብሔር ተናግሮ ነገር አይቀርምና ወንድሞቹ እንዳይሰግዱለት፣ እንዳይገዙለት ሽተው ሊገድሉት ቢሞክሩም፣ ጉድጓድ ውስጥ ቢጥሉትም፣ ለነጋድያን ቢሸጡትም በሀገራቸው ሊፈጽሙት የከበዳቸውን ሐቅ ርሐብና ድርቅ ሲመጣ በባዕድ ምድር በግብፅ ሊያደርጉት ግድ ሆኖ ወንድሞቹ ለዮሴፍ መስገዳቸው አልቀረም፡፡የዮሴፍም ወንድሞች በመጡ ጊዜ በግምባራቸው በምድር ላይ ሰገዱለት” /ዘፍ.426/፡፡ ለቅዱሳን አንሰግድም የሚሉ ሰዎች ምንም እንኳን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሊያጠፉት ሽተው ቢሰርዙና ቢደልዙትም፣ በቀላል አማርኛ በሚል ፈሊጥ ቃሉን ቢዘነጥሉትም፣ ጥቅስን ዘንጥሎ በመጣል ጉድጓድ ውስጥ ቢጥሉትም፣ አውጥተው ለሥጋዊ ስሜትና ለዓለም ክህደት ቢሸጡትም ርሐበ ነፍስ ድርቀተ መንፈስ ሲመጣ በሀገራቸው፣ በሕይወተ ሥጋቸው ያላደረጉትን እውነትን በሲዖል እንኳን ለማድረግ መጓጓታቸው አይቀርም፡፡የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉእንዳለ ኢሳይያስ /ኢሳ.6014/፡፡ በምድር ምጽዋት የነፈገውን አልአዛርን በሲዖል በአብርሃም አማላጅነት እንደለመነው ነዌ፡፡ /ሉቃ.1620-31/፡፡
ጳዎሎስንና ሲላስን ለመሰሉ ቅዱሳን ለእናንተ የሚገባው ስግደት ሳይሆን መታሠር ነው ብለው ደብድበው ካሠሯቸው ሰዎች መኃል አንዱ የሆነው የእሥር ቤቱ ጠባቂ በእሥር ቤቱ ውስጥ በነጳውሎስ ዝማሬ ምክንያት ከደረሰው ታላቅ መናወጽ በኋላ ከሥራቸው ተደፍቶ ሰገደላቸው፡፡ከጳውሎስና ከሲላስ ፊት ተደፋ” /ሐዋ.1629/ እንዲል ግብረ ሐዋርያት፡፡ የቅዱሳኑን ዝማሬ ሰምቶ እሥር ቤቱን አናውጾ ጠባቂውን እንዲሰግድ ያደረገው እግዚአብሔር አይደለምን?
እግዚአብሔር ቃል በቃል ለቅዱሳን ስግደት እንደሚገባ የተናገረበት ቦታን ለሚሻ ደግሞ እነሆ፡-
በራእየ ዮሐንስ ምዕራፍ ሦስት ላይ ሁለት የቤተክርስቲያን ጠባቂዎችን እናገኛለን፡፡ አንደኛው በሰርዴስ የሚገኘው መልአክ /ጠባቂ/ ሲሆን አንደኛው ደግሞ የፊልድልፍያ ቤተክርስቲያን መልአክ /ጠባቂ/ ነው፡፡ የሰርዴሱ ጠባቂ ሥራው በአምላክ ፊት ፍጹም ያልሆነና በቁሙም ሞተሀል የተባለ ሲሆን እንዲነቃና ንስሐ እንዲገባ አግዚአብሔር አዟል፡፡ እንዲህ ካላደረገ ግን እንደሚፈርድበትእመጣብሃለሁሲል ነግሮታል፡፡ የፊልድልፍያው መልአክ /ጠባቂ/ ግን በእግዚአብሔር ፊት የተወደደና ቅዱስ ነበርና እግዚአብሔር እንዲህ አለውሥራህን አውቃለሁ፤ እነሆ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ፤ ማንምም ሊዘጋው አይችልም፤ ኃይልህ ትንሽ ቢሆን ቃሌን ጠብቀሃልና ስሜንም አልካድህምና፡፡ እነሆ አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን ከሚሉ ነገር ግን ከሚዋሹ ከሰይጣን ማኅበር አንዳንዶችን እሰጥሃለሁ እነሆ መጥተው በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ እኔም እንደ ወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ” /ራእ.38-9/፡፡

ለቅዱሳን ስግደት አይገባም የሚሉ ምንኛ ያልታደሉ ናቸው? “የተከፈተ በር ሰጥቼሀለሁ ማንምም ሊዘጋው አይችልምየተባለላቸውን ቅዱሳንን የሚመሰገኑበትን የጸጋ በር ሊዘጉ የሚሮጡ ምንኛ ምስኪኖች ናቸው? “እነሆ አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን ከሚሉ ነገር ግን ከሚዋሹ ከሰይጣን ማኅበርየተባሉ ክርስቲያን ሳይሆኑ ክርስቲያን ነን የሚሉ ነገር ግን የሚዋሹ ምንኛ አሳዛኝ ናቸው? እነሆ ክርስቲያን ሳይሆኑ ክርስቲያን ነኝ በሚል ቅዠት ቅዱሳንን የማይወዱ የሰይጣን ማኅበር አባላት መባላቸው እንዴት የሚደንቅ ነው? እንደ ቅዱሳን ሁሉ እንዲ ሰጣቸው ተፈጥረው እነርሱ ራሳቸው ተላልፈው መሰጠታቸውና ባይወዱም እንኳን በቅዱሳን እግር ፊት መስገዳቸው የማይቀር መሆኑ እንዴት ግሩም ነው? በተዐብዮ ራሳቸውን እኔም እንደ እገሌ ቅዱስ ነኝ የሚሉ ዘባቾች ቅዱሳንን በትሕትናቸውና አንዱ ለአንዱ በመስገዳቸው የሚወድ እግዚአብሔርእንዴት እንደወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁብሎ ለቅዱሳን ቃል መግባቱ እንዴት ያለ ምሥጢር ነው?
(እግዚአብሔር ቢፈቅድ በሁለተኛው ክፍል መቼ መቼ እንደሚሰገድ፤ ለመላእክት፣ ለቅዱሳንና ለቅዱሳን ንዋያት የሚሰገድ ስግደትን መላእኩ ዮሐንስን አትስገድልኝ የማለቱን ምሥጢር እናያለን፡፡ በሦስተኛው ክፍልም ከሰሙነ-ሕማማት ጋር በማያያዝ ስግደትን እናነሣለን፤ በተለይ የግዝት በዓላት በሕማማት ቢውሉ ይሰገዳልን የሚለውን ለመመለስ እንሞክራለን፡፡ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡)

8 comments:

  1. ቃለ ሕይወት ያሰማልን፣ የአገልግሎት ዘመንዎትን ይባርክ፡፡ መጽሐፉ የት እንደሚገኝና ተመርቀ እንዴ??? መሸጥ ተጀመረ ወይ ማለቴ ነው????

    ReplyDelete
  2. ቃለ ሕይወት ያስማልን

    ReplyDelete
  3. እግዚአብሔር አምላክ የአገልግሎት ዘመንዎን ያርዝምልን ይባርክልን እኛም ይህን አውቀን የምንጠቀምበት ያድርገን አሜን

    ReplyDelete
  4. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  5. እግዚአብሔር ይስጥልን

    ReplyDelete
  6. ቃል ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  7. ቃለ ህይወት ያሰማልን!

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount