በዳዊት አብርሃም
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐሙስ ታኅሳስ
9 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ
አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የጽሑፉ ምንጭ፡-
ሐመር መጽሔት፥ የግንቦት 2005 ዓ.ም. እትም ነው፡፡
መንፈሳዊ ቤተ ሰብ
ቀሲስ ጥላኹን ታደሰ 110 ያኽል የንስሐ ልጆቻቸውን በጥንቃቄ መዝግበው ይዘዋል፡፡
ይኽም እያንዳንዱ የንስሐ ልጅ ያለበትን ደረጃ ለመከታተል አስችሏዋቸዋል፡፡ ከመዠመሪያው የንስሐ ልጆቻቸውን ለመቀበል መንፈሳዊ መስፈርቶችን
በቅድመ ኹኔታነት ያስቀምጣሉ፡፡ በመዠመሪያ ግን የሚያቀርቡት ጥያቄ “ለምን የንስሐ አባት አስፈለገህ?” የሚል ነው፡፡ ይኽን ጥያቄ
የሚያነሡት እያንዳንዱ የንስሐ ልጅ ትክክለኛውን ዓላማ ይዞ የንስሐ ሕይወቱን እንዲዠምር ለማድረግ ነው፡፡ ቀጥለው መስፈርቶቹን ይነግሩታል፡፡
ተስማምቶ ቢቀጥል እንኳ በየጊዜው ለመፈጸም የተስማማባቸውን መስፈርቶች በትክክል እየፈጸመ መኾኑን ከመመርመር አያቆሙም፡፡
·
ወርሓዊ ጕባኤ፡- ለንስሐ ልጆች ወርሓዊ ጕባኤ ላይ ሳያስታጕሉ መገኘት የመዠመሪያው
መስፈርት ነው፡፡ ይኽ ቀላል ግዴታ ቢኾንም በዛው መጠን ደግሞ ዋና ነው፡፡ በጕባኤው የሕይወት ስብከት በተለያዩ መምህራን ከመሰጠቱም
በላይ መሠረታዊ ትምህርተ ሃይማኖት ደግሞ በራሳቸው በቀሲስ ጥላኹን በተከታታይ ስለሚሰጥ በዚኽ ጕባኤ ላይ መገኘት ለሌሎቹ ግዴታዎች
መነሻ ነው፡፡
·
መሠረታዊ ትምህርተ ሃይማኖት፡- ቀሲስ ጥላኹን በተለይ ስለ ንስሐ አባቶች ተግባር ሲናገሩ
ትምህርተ ሃይማኖት ላይ ጠንከር ይላሉ፡፡ “በርካቶች ምእመናን ሃይማኖታቸውን ያጡት፣ በርካቶችም ለቀበሮ ባሕታውያን፣ ለጠንቋዮችና
ለአሳቾች ሰለባ የኾኑት የጠራውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ከምንጩ ማግኘት ስላልቻሉ ነው፡፡ ስለዚኽ የንስሐ አባቶች ይኽን ክፍተት
በመሙላት ምእመናንን በትክክል በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አንጸው በቤተ ክርስቲያን ማኖር አለባቸው” ይላሉ፡፡
·
የራስ ተነሣሽነት፡- ሌላኛው ቀሲስ ከንስሐ ልጆች የሚጠብቁት ግዴታ እያንዳንዱ የንስሐ ልጅ ቀድሞ
የንስሐ አባት የፈለገው በምክንያት እስከኾነ ድረስ በየጊዜው ቀጠሮ እያስያዘ ከንስሐ አባቱ ጋር ለመመካከር ፍላጎት ማሳየት አለበት፡፡
ለደንቡ ብቻ የንስሐ አባት አለኝ ብሎ ለሚቀመጥ ሰው እርሳቸውም ለደንቡ ያኽል የንስሐ አባት ኾነው መኖርን አይፈልጉም፡፡ የንስሐ
ልጆች የሚሰጣቸውን የመፍትሔ ሐሳብና ተግባራዊ መኾን የሚገባቸውን ምክሮች ከተቀበሉ በኋላ ለመተግበር ወሳኙ ነገር የልጆቹ የግል
ቆራጥነት ነው፡፡ የንስሐ አባት የመያዝ ዓላማ በመንፈሳዊ ሕይወት መሻሻልን ለማምጣት ነው፡፡ ወደ ንስሐ ሕይወት ለመቅረብና በንስሐ
ሕይወት ለመመላለስ መወሰን ከዚያም ወደ ሥጋ ወደሙ መቅረብ ስለሚያስፈልግ ቀሲስ የንስሐ ልጆቻቸውን ቀጠሮ እያስያዙ ለመገናኘት ፍላጐት
እንዲኖራቸው ይጠብቃሉ፡፡
·
የካህኑ ድርሻ፡- በርግጥ ለሥጋ ወደሙ ለመብቃት የካህናትንም ድርሻ አይዘነጉትም፡፡
“የንስሐ አባት ልጆቹ ለሥጋ ወደሙ እንዲበቁ መጐትጐትና መቀስቀስ አለበት፡፡ በኃይል፣ በማጣደፍ ወይም በማስፈራት አይደለም፡፡ ኾኖም
ካህኑ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ወኪል፣ የእግዚአብሔር እንደራሴ ስለኾነ ማትጋት፣ መጐትጐት፣ መቀስቀስ ድርሻው ነው፡፡ ይኽን ግዴታውን
ካወቀ ደግሞ አቀራረቡ አሰልቺ እንዳይኾን፣ ወይም የልጆቹን ችግር የማይቀርፍ ኾኖ እንዳይቀር ራሱን በማሳደግ ለተሻለ አገልግሎት
መትጋት አለበት፡፡ በተለይ በዚኽ ዘመን ዘመናዊነት እያደገ ሲመጣ ችግሮቹም ስለሚወሳሰቡ ራሱን ማብቃት ያልቻለ ካህን ለማንም መትረፍ
አይችልም፡፡ ኾኖም የዘመኑን ችግር ዘመኑ በፈጠረው መፍትሔ ለመቅረፍ ዘመኑ ያስገኛቸውን የቴክኖሎጂም ኾኑ ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም
ካህናት ለመምከር ብቁ ኾነው መገኘት” እንዳለባቸው ቀሲስ ከራሳቸው ልምድ በመነሣት ይመክራሉ፡፡ “ይኽ ነገር በተለይ የንስሐ አባቴ
ችግሬን አይረዱልኝም በሚል የሚያማርሩ ወጣቶች ችግር የሚቀንስ ይመስለኛል” ይላሉ፡፡
·
የምእመኑ ድርሻ፡- የኾነ ኾኖ ግን በንስሐ ሕይወት መኖር የግለሰቡን የግል
ውሳኔ የሚጠይቅ ጕዳይ ስለኾነ ቀሲስ ከንስሐ ልጆቻቸው ተግባራዊ ምላሽን ይጠብቃሉ፡፡ “ከንስሐ ልጆች የሚጠበቁ ተግባራዊ ምላሾች
የሚሏቸው መማር፣ በግልጽ መናዘዝ፣ ምክሮችን መተግበር፣ የተቀበሉትን ቀኖና መፈጸም፣ ዳግም ላለመውደቅ መጠንቀቅ፣ ከንስሐ ሕይወት
አለመውጣትና ይኽን የመሳሰለ ነው፡፡”
·
መንፈሳዊ ቤተሰብ፡- የቀሲስ ጥላኹን ሌላ መልካም አብነት በንስሐ ልጆቻቸው
መካከል መቀራረብ እንዲኖር ማድረጋቸው ነው፡፡ በዚኽ ሥራቸው የንስሐ ልጆች ለብዙ ችግሮች የመፍትሔ አካል ኾነው እንዲያገለግሉ ዕድል
አግኝተዋል፡፡ የተቸገሩትን ከመርዳት ዠምሮ አንዱ ለሌላው አርአያ ኾኖ በተግባር እስከማስተማር ድረስ ይደጋገፋሉ፡፡ በትዳር ሕይወት
ያሉት ላላገቡት አስተማሪዎች ናቸው፡፡ ልጆቻቸውን በመልካም ያሳደጉት ለአዲሶቹ መላጆች መካሪዎች ናቸው፡፡ ከዚኹ ጋር ሕፃናት በመንፈሳዊነት
ታንጸው እንዲያድጉ ለማድረግ በንስሐ አባትነታቸው ለወላጆች የሚሰጡት ምክር አለ፡፡
·
ልጆችን በወላጆች በኵል፡- የመዠመሪያው መንገድ ወላጆች ራሳቸው ትዳራቸውን በማክበር
ለልጆቻቸው አርአያ ኾነው መገኘት ነው፡፡ ቀጥሎም ልጆች የሚሳተፉበት የቤተሰብ ጸሎት መርሐ ግብር እንዲኖር በማድረግ፣ ቤተ ክርስቲያን
በማምጣት ልጆች ሃይማኖታቸውን ጠንቅቀው እንዲያድጉ ለማድረግ ወላጆችን ይመክራሉ፡፡ በወርሓዊ ጕባኤ ላይም ቢኾን ሕፃናት ይገኛሉ፡፡
ወላጆች ጕባኤውን ይረብሻሉ ብለው እንዳይሳቀቁ ለሕፃናቱ “ልዩ የመረበሽ መብት” ተሰጥቷቸዋል፡፡
·
በተለይ ለወጣቶች፡- ለወጣቶችም ቢኾን ታላቅ እገዛ ያደርጋሉ፡፡ ይኸውም ወጣቶች በዚኽ አስቸጋሪ ጊዜያቸው
ተስፋ እንዳይቈርጡ በወጣትነት ጊዜያቸው እግዚአብሔርን ደስ ያሰኙ ቅዱሳንን ታሪክ ከመጽሐፍ ቅዱስ እያወጡ ያሳያሉ፡፡ ወጣትነት ለቅድስና
አይመችም የሚለውን መላምት ትተው መኾን እችላለኹ፤ ዓቅሙ አለኝ ብለው እንዲተማመኑ የሚያደርጉ አነቃቂ ትምህርቶችን ይሰጧቸዋል፡፡
ቀደም ያሉት ለኋለኞች አርአያ እንዲኾኑም ያደርጓቸዋል፡፡ በዚኽ የተነሣ ብዙዎቹ የቀሲስ ጥላኹን ወጣት የንስሐ ልጆች ለሥጋ ወደሙ
በቅተዋል፡፡
ይቀጥላል…
No comments:
Post a Comment