በዳዊት አብርሃም
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐሙስ ታኅሳስ
9 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ
አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የጽሑፉ ምንጭ፡-
ሐመር መጽሔት፥ የግንቦት 2005 ዓ.ም. እትም ነው፡፡
መንፈሳዊ ቤተ ሰብ
ቀሲስ ጥላኹን ታደሰ 110 ያኽል የንስሐ ልጆቻቸውን በጥንቃቄ መዝግበው ይዘዋል፡፡
ይኽም እያንዳንዱ የንስሐ ልጅ ያለበትን ደረጃ ለመከታተል አስችሏዋቸዋል፡፡ ከመዠመሪያው የንስሐ ልጆቻቸውን ለመቀበል መንፈሳዊ መስፈርቶችን
በቅድመ ኹኔታነት ያስቀምጣሉ፡፡ በመዠመሪያ ግን የሚያቀርቡት ጥያቄ “ለምን የንስሐ አባት አስፈለገህ?” የሚል ነው፡፡ ይኽን ጥያቄ
የሚያነሡት እያንዳንዱ የንስሐ ልጅ ትክክለኛውን ዓላማ ይዞ የንስሐ ሕይወቱን እንዲዠምር ለማድረግ ነው፡፡ ቀጥለው መስፈርቶቹን ይነግሩታል፡፡
ተስማምቶ ቢቀጥል እንኳ በየጊዜው ለመፈጸም የተስማማባቸውን መስፈርቶች በትክክል እየፈጸመ መኾኑን ከመመርመር አያቆሙም፡፡