Tuesday, August 6, 2013

የውዳሴ ማርያም ትርጓሜ- መግቢያ

ገ/እግዚአብሔር ኪደ
                                                                                  
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፩ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም.)፡- ውዳሴ፡- “ወደሰ” ከሚል ግስ የወጣ ሲኾን ትርጓሜውም ማወደስ፣ መወደስ፣ አወዳደስ፣ ውደሳ፣ ምስጋና… ማለት ነው፡፡ “ውዳሴ ማርያም”        ሲልም የማርያም ምስጋና ማለት ነው፡፡
  የውዳሴ ማርያም መጽሐፍ ጸሐፊ ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም ሲኾን መጽሐፉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ በጣም የታወቀና የተወደደ የጸሎት መጽሐፍ ነው። ይኸውም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በብዙ ምሳሌ እየመሰለ የሚያወድስ፣ ዘለአለማዊ ድንግልናዋን የሚያስተምር፣  በስነ ጽሑፋዊ ይዘቱም እጅግ ውብ የኾነ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ለማመስገን የተጻፈ ይኹን እንጂ በውስጡ እጅግ ረቂቅ የኾነ የስነ መለኮት ትምህርት (ለምሳሌ ስለ ምሥጢረ ሥላሴና ስለ ምሥጢረ ሥጋዌ ) የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ትምህርት መሠረት የቆሎ ተማሪዎች በቃል ትምህርቱ ዘርፍ ከየዘወትር ጸሎት ቀጥለው በንባብና በዜማ ይህን ውዳሴ ማርያም የተባለውን የትምህርት ክፍል ይማሩታል።
 ለጊዜው ይኸን እናቈየውና ወደ ተነሣንበት ዓላማ እንመለስ፡፡ በቀጥታ ወደ ትርጓሜው ከመግባታችን በፊትም ስለ ጸሐፊው ዜና መዋዕል በትንሹም ቢኾን በዚህ ክፍል ልናስቃኛችሁ ወድደናልና ተከታተሉን፡፡ መልካም ንባብ!

የቅዱስ ኤፍሬም አጭር ዜና መዋዕል
 
 ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም የተወለደው በ፫፻፮ ዓ.ም. ገደማ በሜሶፖታሚያ ውስጥ በምትገኝ “ንጽቢን” በተባለ አከባቢ እንደኾነ ይታመናል፡፡ ንጽቢን  በአሁኑ ሰዓት በደቡባዊ ቱርክ እና በምዕራባዊ ሶርያ መካከል የምትገኝ ቦታ ናት፡፡ ምንም እንኳን አንዳንድ መዛግብት ከቅዱስ ኤፍሬም ሕይወት በመነሣት የቅዱስ ኤፍሬም ወላጆቹ ክርስቲያኖች እንደነበሩ ቢያወሱም ሐምሌ ፲፭ የሚነበበው ስንክሳር እንደሚነግረን ግን አባቱ ካህነ ጣዖት ከመኾኑም በላይ ክርስትናን የሚጠላ እንደነበር ይነግረናል፡፡
 ቅዱስ ኤፍሬም ከወላጆቹ ጋር የቆየው እስከ ፲፭ ዓመቱ ብቻ ሲኾን ትምህርተ ክርስትናንም ተምሮ የተጠመቀው በጊዜው የንጽቢን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ከሠለስቱ ምዕት አንዱ ከሚኾን ከያዕቆብ ዘንጽቢን ዘንድ ነበር፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ ቅዱስ ኤፍሬምን አስተምሮ ካጠመቀው በኋላ ዓቅሙ ሲደረጅ ንጽቢን በሚገኘው መንፈሳዊ ትምህርት ቤት በኃላፊነት ሾሞት ነበር፡፡
 በሮማውያን ግዛት ክርስትና እንዲስፋፋ ዋና አስተዋጽኦ ያደረገው ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በ፫፻፴፯ ዓ.ም. ሲሞት ፋርሳውያን በሮማውያን ላይ ስለዘመቱ ንጽቢን በ፫፻፴፰፣ በ፫፻፵፮ና በ፫፻፶ ዓ.ም. በተደጋጋሚ ወረራ ተካሂዶባት ነበር፡፡ በ፫፻፷፫ ዓ.ም. ግን በንጽቢን ዙርያ የነበሩ ከተሞች በፋርሳውያን ተደመሰሱ፤ ዜጐቻቸውም ግማሾቹ ተገደሉ፤ ግማሾቹ ደግሞ ሀገራቸውን ትተው ተሰደዱ፡፡ በመኾኑም ቅዱስ ኤፍሬም ከተሰደዱት ክርስቲያኖች ጋር በመኾን የሮም ግዛት ወደ ነበረችው ኤዴሳ (ታናሽ እስያ፣ዑር) አብሮ ተሰደደ፡፡ ይህች ቦታ (ኤዴሳ - በአሁኑ ሰዓት ሳን ሊ ኡርፍ ተብላ የምትታወቅ) ቅዱስ ኤፍሬም ከመናፍቃን ጋር የተጋደለባት፣ በቤተክርስቲያን ትምህርት ላይ ያላቸውን አብዛኞቹን የክሕደት ትምህርቶች የሞገተባትና  አብዛኞቹን መጻሕፍቱን ያዘጋጀባት ናት፡፡
 ቅዱስ ኤፍሬም ከመምህሩ ከቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢ ጋር በመኾን በአርዮስ ምክንያት በ፫፻፳፭ ዓ.ም. በተካሄደው ጉባኤ ኒቅያ ላይ ተገኝቶ ስለነበር የአርዮስን ክሕደትና ምክንያተ ውግዘት በሚገባ ያውቃል፡፡
  ከኒቅያ ጉባኤ መልስ መንፈሰ እግዚአብሔር በራዕይ በገለፀለት መሠረት ቅዱስ ኤፍሬም ቁጥሩ ከሠለስቱ ምዕት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከሚኾን ከቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያ ዘንድ ለመገናኘት ወደ ቂሣርያ ሄዷል፡፡ ቅዱስ ባስልዮስም የዲቁና ክህነት ሠጥቶ ከሀገረ ስብከቱ ከፍሎ እንዲያስተምር ወስኖ በእርሱ ዘንድ አኑሮታል፡፡ በዚያም ቦታ ብዙ ተአምራትን አድርጓል፤ መጻሕፍትንም ጽፏል፡፡
  ቅዱስ ኤፍሬም በትውፊት እንደሚታወቀው ምንኩስናን በገቢር ገለጣት እንጂ ሥርዓተ ምንኩስናን መፈጸሙን በግልጽ የሚያመለክት ማስረጃ አልተገኘም፡፡ እንዲያውም በሶርያውያን ክርስቲያኖች የሚዘወተረውን ራስን በአንድ ስፍራ ወስኖ በብሕትውናና በመምህርነት ቤተክርስቲያንን የማገልገል (Proto-monasticism) ሕይወት ይኖር እንደነበር ይታመናል፡፡ በትውፊት ቅዱስ ኤፍሬም ቅዱስ ባስልዮስን ለመጎብኘት ወደ ቀጰዶቅያ እንዲሁም አባ ቢሾይን ለመጎብኘት ወደ ግብጽ እንደተጓዘ የሚነገረውም ከዚህ ጋር በተያያዘ ነው፡፡
  ፍጹም በኾነ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቱ፣ ምሳሌ በሚኾነው የምናንኔ ሕይወቱ የሚታወቀው ቅዱስ ኤፍሬም ሐምሌ ፲፭ ቀን በ፫፻፸ ዓ.ም ዐርፏል፡፡ በዚህ ኹሉ ትጋቱም ሶርያውያን ክርስቲያኖች “ጥዑመ ልሳን”፣ “መምህረ ዓለም”፣ “ዓምደ ቤተ ክርስቲያን” ፤ ከሚያስተምረው የትምህርቱ ጣዕም የተነሣም “የመንፈስ ቅዱስ በገና” በማለት ይጠሩታል፤ ያመሰግኑታልም፡፡

የቅዱስ ኤፍሬም ሥራዎች በአጭሩ
  ቅዱስ ኤፍሬም እንደ ሌሎቹ የ፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እጅግ በጣም በርካታ መጻሕፍትን ጽፏል፡፡ ሐምሌ ፲፭ የሚነበበው ስንክሳርም፡- “እጅግም ብዙ የኾኑ ፲፬ ሺሕ ድርሳናትንና ተግሳጻትን ደረሰ፤ ከእርሳቸውም ውስጥ አምላክን የወለደች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ውዳሴዋን ነው፡፡ ‘አቤቱ የጸጋህን ማዕበል ግታልኝ’ እስከሚል ድረስ ድርሳናትን ደርሶአል” በማለት ይገልጧል፡፡
ቅዱስ ኤፍሬም የደረሳቸው የዜማ ድርሰቶች ከ፬፻ ሚልዮን ቅኔያዊ ግጥሞችን ያዘሉ ሲኾኑ፣ “ሶዞሜን” የተባለ የታሪክ ጸሐፊም በውስጣቸው ከ፫ ሚልዮን በላይ ስንኞችን እንዳካተቱ ተናግሯል፡፡ በአጠቃላይ የቅዱስ ኤፍሬም ጽሑፎች በ፬ ከፍሎ ማየት ይቻላል፡-
፩. ቀጥተኛ ትርጓሜያት፡- ይህ ክፍል ከመጽሐፍ ቅዱስ አንዱን መጽሐፍ በመውሰድ የተጻፉ ትርጓሜያትን የሚያጠቃልል ነው፡፡ ለምሳሌ የኦሪት ዘፍጥረት፣ የኦሪት ዘፀአት፣ የአራቱ ወንጌላት (በሶርያውያን ዘንድ ዲያተሳሮን ተብሎ የሚታወቅና አራቱንም ወንጌላት በአንድ ላይ አካቶ የተሠራ)፣ የግብረ ሐዋርያት እንዲሁም የቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት ትርጓሜያትን መጥቀስ ይቻላል፡፡
፪. ጥበበባዊ (Artistic) ትምህርቶች (ትርጓሜያት)፡- በግጥም ወይም በሌላ ጥበባዊ መልክ የተጻፉ ትርጓሜያትን የሚያካትት ነው፡፡ “በእንተ ክርስቶስ” (በጥያቄና መልስ የቀረበው) ትምህርት ተጠቃሽ ነው፡፡ እንዲሁም “በነገረ ምጽአት” ላይ ለፑከሊየስ የተጻፈው ደብዳቤም መጥቀስ ይቻላል፡፡
፫. በቁጥር የተደረጉ ስብከቶች (Verse homilies)፦ አንድን ርዕስ በማንሣት የተሰጡ ስብከቶችን የምናገኝበት ክፍል ነው፡፡ “በእንተ እምነት” የተሰኘው ስብከቱ ተጠቃሽ ነው፡፡ (በመምህር ሽመልስ መርጊያ የተተረጐመውና “ስብከት ወተግሳጽ ዘቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ” የሚል መጽሐፍ መመልከቱ ይጠቅማል፡፡)
፬. የዜማ ወይም የቅዳሴ ድርሰቶች፡፡
                            
ቅዱስ ኤፍሬምና የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ.

  የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ. ያዘጋጀቻቸውን አብዛኛዎቹ የትርጓሜ መጻሕፍት ያጠኑ ሊቃውንት፣ መጻሕፍቱ የኤዴሳ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት የትርጓሜ ስልትና የምሥጢር፣ የዘይቤ አንድነት እንደሚስተዋልባቸው ያስረዳሉ፡፡ ከዚያ ውጪ በውዳሴ ማርያምና በአንቀፀ ብርሃን መካከል ያለው የአንድነት ጉዳይ ከትርጓሜ መጻሕፍት ወደ ጸሎት መጻሕፍትም ሊራመድ እንደሚችል ያስገነዝባል፡፡

ቅዱስ ኤፍሬም ውዳሴ ማርያም እንዴት ሊጽፈው ቻለ?

 የውዳሴ ማርያም መተርጕማን እንደሚያስተምሩት ቅዱስ ኤፍሬም ቢረሌ፣ርጠብ፣ ብርጭቆ፣ ኩዝ፣ ካቦ እየሠራ የዓመት ልብሱን የዕለት ምግቡን እያስቀረ ይመፀውት ነበር፡፡ ሲመፀውትም በሥላሴ፣ በመላእክት፣ በጻድቃን ወይም በሰማዕታት ስም አይመፀውትም፤ በእመቤታችን ስም ይመጸውት ነበር እንጂ፡፡ ከእናንተ መካከል “ንቋቸው አጥቅቷቸውን ነውን?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ በፍጹም! ንቋቸው፤ አጥቅቷቸውም አይደለም፡፡ የእመቤታችን ፍቅር ባያደርሰው ነው እንጂ፡፡ በመኾኑም እመቤታችንን እጅግ ከመውደዱ የተነሣ ኹል ጊዜ “ምነው የእመቤቴ ምስጋናዋ እንደ ሰማይ ኮከብ፤ እንደ ባሕር አሸዋ በዝቶልኝ፤ እንደ ልብስ ለብሼው፤ እንደ ምግብ ተመግቤው ጠግቤው በበዛልኝ” እያለ ይመኝ ነበር፡፡ ያሹትን መግለጽእግዚአብሔር ልማዱ ነውና ገልጾለት አስቀድመን እንደተናገርነው “አኃዝ እግዚኦ መዋግደ ጸጋከ- አቤቱ የጸጋህን ሞገድ ግታልኝ” እስኪል ድረስ ፲፬ ሺሕ ድርሳናትንና ተግሳጻትን ደርሷል፡፡ የሚጸልየውም ጸሎት ከሉቃስ ወንጌል “በ፮ኛው ወር ገብርኤል መልአክ” ከሚል አንሥቶ ጸሎተ እግዝእትነ ማርያምን አውጥቶ ጊዜ ይጸልይ ነበር /ሉቃ.፩፡፳፮/፡፡ ከዕለታት በአንድ ቀን ግን (ዕለቱ ሰኑይ ጊዜው ነግህ ነው) የነግህ ተግባሩን አድርሶ ከመካነ ግብሩ ተቀምጦ ሳለ እመቤታችን መጣች፡፡ የብርሃን ምንጣፍነጥፏል፡፡ የብርሃን ተዘርግቷል፡፡ ከዚያ ላይ ኹናምሰላም ለከ ፍቁርየ ኤፍሬም” አለችው፡፡ እሱም ታጥቆ እጅ ነሥቶ ቆመ፡፡ወድሰኒ” አለችው፡፡ እዚህ ጋር አንዳንድ ልበ ስሑታን የሚያነሡት ጥያቄ ስላለ መልስ ሰጥተንበት እንለፍ፡፡ እመቤታችን ቅዱስ ኤፍሬምን “አመስግነኝ” ስላለችው ክብር፣ ውዳሴ፣ ልዕልናን የፈለገች መስሏቸው “ማርያም በፍጹም እንዲህ አታደርግም፤ በመጽሐፍ ቅዱስ የምናውቃት ማርያም ትሑት ናት” የሚሉ አሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ስሕተት ነው፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ኤፍሬም “ምነው የእመቤቴ ምስጋናዋ እንደ ሰማይ ኮከብ፤ እንደ ባሕር አሸዋ በዝቶልኝ፤ እንደ ልብስ ለብሼው፤ እንደ ምግብ ተመግቤው ጠግቤው በበዛልኝ” እያለ ይመኝ ስለ ነበር እግዚአብሔር ጸሎቱን ሰምቶለት እንጂ እመቤታችን ልዕልናን ፈልጋ አመስግነኝ ያለችው አይደለም፡፡ እመቤታችንን የሚቀድስ ማንኛውም ሰው በእመቤታችን ላይ የሚጨምረው አንዳች ነገር የለም፡፡ እርሱ ይከብራል፤ የሰሙትም ኹሉ ይከብራሉ እንጂ /ቅዳ.ማር. ቁ.፻፸፪/፡፡
 እመቤታችን “ወድሰኒ” ካለችው በኋላ ሊቁም መልሶ እፎ እክል ወድሶተኪ ዘኢይክሉ ሰማያውያን ወምድራውያን- ምድራውያን ጻድቃን ሰማእታት፣ ሰማያውያን መላእክት አንቺን ለማመስገን የማይቻላቸው ለእኔ እንደምን ይቻለኛል?” አላት፡፡ በተረቱበት መርታት ልማድ ነውና /ሉቃ.፩፡፴፯/ በከመ አለበወከ መንፈስ ቅዱስ ተናገር” አለችው፡፡ ከዚህ በኋላባርክኒ” ብሏት እርሷም “በረከተ ወልድየ ወአብሁመንፈስ ቅዱስ ይኀድር በላእሌከ” ብላ ባርካው ምስጋናዋን ጀምሯል፡፡ ሲያመሰግናትም ደቀ መዝሙር ቅኔ ቆጥሮ እንደሚቀኝ፣ ድርሰትም አስቦ እንደሚጽፍ አይደለም፡፡ ብልህ ደቀ መዝሙር ያጠናውን ቀለም ከመምህሩ ፊት ሰተት አድርጎ እንዲያደርስ እንደዚያ ነው እንጂ፡፡ ስታስደርሰውም ከሰባት ከፍላ አስደርሰዋለች፡፡ለምን?” ቢሉ በሰባቱ ዕለታት መመስገን ፈቃድዋ ስለኾነ /ሉቃ.፩፡፵፰/፤ አንድም ሰባቱ ዕለታት ምሳሌዋ ናቸውና፡፡ ይኸውም፡-
©     በዕለተ እሑድ አሥራወ ፍጥረታት አራቱ በሕርያት (እሳት፣ ውሃ፣ ነፋስና መሬት) ተገኝተዋል /ዘፍ.፩፡፩፣ ኩፋ.፪፡፰/፡፡ ከሷም ለዘኮነ ምክንያተ ፍጥረት በህላዌሁ የሚባለው፣ ይህንን ዓለም ካለመኖር ወደመኖር ያመጣ፣ ያለ እርሱ ቃልነት ያለ እርሱ ሕልውና ምንም ምን የተፈጠረ የሌለ፣ አምጻኤ ዓለማት ፈጣሬ ዓለማት ፤ በአጭር ቃል አሥራወ ፍጥረት ጌታችን በግብረ መንፈስ ቅዱስ ተገኝቷል/ዮሐ.፩፡፫/፡፡
©      በሰኞ ዕለት የብርሃን ማኅደር የኾነው ጠፈር ተገኝቷል /ዘፍ.፩፡፮-፯/፡፡ ከእርሷም ብርሃን ክርስቶስ ተገኝቷል /ዮሐ.፩፡፭-፱/፡፡
©     በዕለተ ሠሉስ ምድር ገበሬ ሳይጥርባት፣ ሳይደክምባት፣ ዘር ሳይወድቅባት በቃሉ ብቻ በእጅ የሚለቀሙ አትክልት፣ በማጭድ የሚታጨዱ አዝርእት፣ በምሳር የሚቆረጡ ዕፅዋት ለሥጋውያን ምግብ የሚኾኑ ተገኝተዋል፡፡ ከእሷም የወንድ ዘር ሳይወድቅባት ዕፀ ሕይወት፣ ፍሬ ሕይወት (የመንፈሳዊያን ምግብ) የሚኾን ጌታ ተገኝቷል፡፡
©     በዕለተ ረቡዕለይቁሙ ብርሃናት በገጸ ሰማይ” ባለ ጊዜ የተሠወረውን የሚገልጡ፣ የጨለመውን የሚያስለቅቁ ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ተገኝተዋል /ዘፍ.፩፡፲፬-፲፱/፡፡ ከእሷም በብርሃኑ ኅልፈት ውላጤ የሌለበት፣ ጠፈር ደፈር የማይከለክለው፣ መዓልትና ሌሊት የማይፈራረቀው፣ የጽድቅ ፀሐይ (ለመንፈሳዊያን ምግብ) የሚኾን ጌታ ተገኝቷል፡፡
©     በዕለተ ሐሙስለታወጽእ ባሕር ዘቦ መንፈሰ ሕይወት” ባለ ጊዜ በልባቸው የሚሳቡ፣ በእግቸው የሚሽከረከሩ፣ በክንፋቸው የሚበሩ፣ በደመ ነፍስ ሕይወት ሕያዋን ኹነው የሚኖሩ ደመ ነፍስ ከሌለባት ከባሕር ተገኝተዋል፡፡ ዘርዐ ብእሲ፣ ሩካቤ ብእሲ ከሌለባት ከእመቤታችንም ለምእመናን ምክንያተ ሕይወት የሚኾን ያውም ከጐኑ በፈሰሰ ውሃ ተጠምቀው ምእመናን ሕያዋን የኾኑለት ኢየሱስ ክርስቶስ ተገኝቷል፡፡
©     በዕለተ ዐርብ በኩረ ፍጥረት አዳም ከድንግል መሬት ተገኝቷል፡፡ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያምም ዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ ተገኝቷልና፡፡  
©     በዕለተ ቀዳሚት ሥጋዊ ዕረፍት ተገኝቷል፡፡ ከእርሷም የመንፈሳውያን ዕረፍት ጌታ ተገኝቷልና ነው /ማቴ.፲፩፡፳፰-፴/፡፡
…ይቆየን…
ዋቢ፡ ውዳሴ ማርያም አንድምታ፣ ስንክሳር፣ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ፣ ስብከት ወተግሳጽ ዘቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ በመ/ር ሽመልስ መርጊያ 

2 comments:

FeedBurner FeedCount