Thursday, August 8, 2013

ሰኮናቸው ያልተሰነጠቀና የማያመሰኩ እንስሳት (የዘመናችን ተሐድሶዎች)

በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፫ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም.)፡- ሠለስቱ ደቂቅን ያዳናቸው ማን ነው ለሚለው የተሐድሶዎች ጥያቄ የቀረበ መልስ

ሰሞኑን በተለይ በርከት ባሉት በመጽሐፈ ገጽ ወዳጆቼ በኩል  ‹‹ ሠለስቱ ደቂቅን ያዳናቸው ማን ነው? ›› የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ ቀርቦልኛል፡፡ በተሐድሶዎች በተሰራጨ አንድ የቪዲዮ ቁራጭ ላይ በሦስቱ ድርሳናት ማለትም በድርሳነ ገብርኤል ላይ ገብርኤል በድርሳነ ሚካኤል ላይ ሚካኤል በድርሳነ ሩፋዔል ላይ ደግሞ ሩፋኤል አዳናቸው ተብሎ ስለተገለጸ ትክክሉ የቱ ነው፤ በርግጥ ያዳናቸውስ ማን ነው የሚል ነው፡፡ በዚያም ጊዜ ሆነ ዛሬ ከአንዳንዶቹ መልእክት እንደተረዳሁት የድንጋጤ ስሜትም የተሰማቸው አሉ፡፡ ይህን ሌሎች ተመሳሳይ ድርጊቶችንም ስመለከት ለጉዳዩ ቢያንስ አንዲት ትንሽ መጣጥፍ እንዳአቅሜ  እንኳ ለጊዜው መስጠት እንዳለብኝ ስለተሰማኝ ጥያቄውን ለላካችሁልኝ ሁሉ ይህችን መቆያ እንካችሁ ብያለሁ፡፡ ዋናው ወይን ሁልጊዜም ወደ ኋላ መምጣቱ አይቀርምና እርሱን አብረን ከወይን አዳዩ እንጠብቃለን፡፡


ከላይ ያነሣሁትንና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች ብዙ ጊዜ የሚረብሹን ለምንድን ነው ብየ ሳስብ ብዙዎቻችን ወግ ባለውና ለእኛ በሚሆን መንገድ አለመማራችን የመጀመሪያውን ስፍራ ሊይዝ ይችላል፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ  ደግሞ በዚህ ጽሑፍ በዋናነት የምንመለከተውን የመሰሉ ጥያቄዎች እያነሡ ገድላትን፤ ድርሳናትንና ሌሎች አዋልድንም የሚነቅፉና የሚያጸይፉ ሰዎች ቁጥራቸው በርከት እያለ መጥቷል፡፡ ከዚህም የተነሣ በተለያዩ ሚዲያዎች የተለያዩ ጽሑፎችና የምስል ወድምፅ ስብከቶች ይቀርባሉ፡፡ በዚህም ስለቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ ወይም ምሥጢራት ግንዛቤያችን አነስተኛ የሆነብንን ሰዎች በትንሹም ቢሆን ሊረብሸን ይችላል፡፡እኔም ዝም ብየ በአንዲት ብጣሽ ጉዳይ ላይ ብቻ እንዲህ ነው ወይም እንዲያ ነው ከማለቴ በፊት ነገሩን ከመሠረቱ ለመረዳት እንዲያመቸን ቅዱሳት መጻሕፍት ላይ የሚነሡ ጥያቄዎችን ብቻ ሳይሆን የማንጠየቃቸውንም በአግባቡ ተረድተን እንድንጠቀም የሚረዳውን መንገድ ጠቆም ላድርግ፡፡ ስለዚህ አስቀድመን ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዴት ልንረዳ እንደምንችል ላቅርብና በሚቀርበው ጥያቄ ሁሉ ሳንረበሽ መልሱን እንድንጠብቅ ለማመላከት ልሞክር፡፡

በቅዱሳት መጻሕፍት ንባብ ሦስት ዓይነት መልእክቶችን እናገኛለን፡፡ የመጀመሪያው ታሪካዊ መልእክት ነው፡፡ ይህም ማለት ድርጊትን ሲዘግብልን ወይም የተጻፈው ደረቅ ትንቢትና ቀጥታ ትምህርት እንኳ ቢሆን ማን መቼ ለማን በምን ምክንያት አንደተናገረው ስናጠና የምናገኘው ታሪካዊና ተጨባጭ መልእክት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ምግባራዊ መልእክት ሊባል የሚችለውና ምን ማድረግ እንዳለብን ወይም እንደሌለብን፤ እንዴትና መቼ ትእዛዛትን መፈጸም እንዳለብን የሚያስተምረን ቀጥታ ልንተገብረው የሚገባንን የሚያሳውቀን መልእክት ነው፡፡ ሦስተኛውና የመጨረሻው ደግሞ ምስጢራዊ ወይም መንፈሳዊ መልእክት ነው፡፡ የዚህም ዋና ዓላማው ምስጢሩን ከተረዳን በኋላ በገቢር እንድንገልጸው ቢሆንም ዋናው መልእክት ግን የሚገኘው ምሳሌው ወይም ትንቢቱ ወይም ታሪኩ በውስጡ አምቆ የያዘው መለኮታዊ መልእክትን ስናውቅ ነው፡፡ ይህ ምስጢራዊ ወይም መንፈሳዊ መልእክት ግን በግምት ወይም በመላምት የሚሰጥ ሳይሆን በመገለጥ ላይ ተመሥረተው ቅዱሳን አባቶች የተናገሩትንንና ከጥንት ከጌታና ከሐዋርያት ጀምሮ እነዚህን መጻሕፍት ያስተማሩ ቅዱሳን እግዚአብሔር ገልጾላቸው ካስተማሩት የሚገኝ ነው፡፡ ለምሳሌ ጌታ ሉቃስንና ቀልዮጳን ወደ ኤማሁስ ከሚሔዱበት መንገድ የመለሳቸው እነርሱ እንደተናገሩት ‹‹ ቅዱሳት መጻሕፍትን እየተረጎመ›› ሲነግራቸውና በምስጢራቱም ‹‹ ልቡናቸውን ካቃጠለው›› በኋላ ነው / ሉቃ 24 13 - 35/ ፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም መልእክቶቻቸውንና ወንጌሎቻቸውን ብናይ በኦሪት የምናውቃቸውን ታሪኮችና ትእዛዛት መንፈሳዊና ምስጢራዊ መልእክቶቻቸውን በሰፊው አስቀምጠውልናል፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ጳውሎስ እሥራኤል ከግብጽ ሲወጡና ባሕረ ኤርትራን ሲሻገሩ የገጠማቸውን ነገር በሙሉ የጥምቀትና የመንፈሳዊ ወይም የጸጋ እግዚአብሔር ምግብና እንደሆነ ተርጎሞልናል / 1 ቆሮ 10 1 -5/፡፡ አጋርንና ሣራንም የኦሪትና የወንጌል ምሳሌዎች አድርጎ ልጆቻቸው እስማኤልና ይስሐቅም ለምን ዓይነት መንፈሳዊና ታላቅ ምስጢራዊ መልእክት ምሳሌዎች እንደሆኑ ነግሮናል / ገላ 4 22-ፍጻ/ ፡፡ የኋላ ሊቃውንትም በዚሁ በእነርሱ መንገድ ሔደው የቅዱሳት መጻሕፍትን ተዝቆ የማያልቅ መለኮታዊ መልእክት ወይም ምስጢራ መጻሕፍት አስተምረውናል፡፡ በሦስተኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ የሚላኖ ሊቀ ጳጳስ የነበረው ቅዱስ አምብሮዝ አባታችን ያዕቆብ በሎዛ በሌሊት በሕልሙ ከላይ እግዚአብሔር ተቀምጦባት መላእክት ሲወጡባት ሲወርዱባት ያያትን መሰላል ሲተረጉም መላእክት የተባሉት ከሐዋርያት ጀምሮ ያሉ ቅዱሳን ሊቃውንት ናቸው፡፡ የመሰላሉ ቋሚዎች የብሉይና የሐዲስ መጻሕፍት ሲሆኑ በቋሚዎቹ ላይ ያሉ ርብራቦች ከእነርሱ የሚገኙት ምግባራት ጾም ጸሎት ቀዊም ስግደትን የመሰሉት ናቸው፡፡ ሊቃውንት በእነዚህ በኩል ወደ ላይ በብቃት ይወጣሉ፤ እንደ ቅዱስ ጳውሎስም እስከ ሦስተኛው ሰማይ ይነጠቃሉ፤ ምስጢራተ መጻሕፍትንም ይዘውልን ይወርዳሉ ብሏል፡፡ ስለዚህ ምስጢራዊ መልእክት አላቸውም ሲባል አንድ ሰው ከራሱ ዓለማዊ ዕወቀት ወይም ልምድ ብቻ ተነሥቶ ወይም ከአስተሳሰቡ አመንጭቶ የሚነግረን ሳይሆን ቅዱሳን ሊቃውንት ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው ጸጋ መሠረት ከእርሱ ተቀብለው የሚሰጡን ነው፡፡ ምክንያቱም ቅዱሳት መጻሕፍት በሰው ቋንቋ የተጻፉ የእግዚአብሔር መለኮታዊ መልእከቶች ከሆኑ ከቃላቱ መደበኛ ትርጉም ያለፈውን መለኮታዊ ምስጢር ወይም መልእክት ልናገኘውም የምንችለው ከእርሱ በሚሰጥ መገለጥ ብቻ ስለሚሆን ነው፡፡ በትንሹም ቢሆን ስለትትርጓሜያት ይህን ያህል ካየን  አሁን ከላይ  በርእሱ ስለተቀመጠው የኦሪት ጥቅስ ምስጢራዊ መልእክት እንመልከት፡፡

በቅዱሳት መጻሕፍት ስለምንቀበለው ትምህርትና ስለማንቀበለው ትምህርት ከተነገረባቸው መንገዶች አንዱ ምሳሌያዊ ነው፡፡ ይህም ማለት ለጊዜው ቀጥታ ለሚተገበር ምግባራዊ ሕግ የተሰጡ መስለው ምሳሌነታቸውና ምስጢራዊ መልእክታቸው ግን ሃይማኖታዊ ወይም ስለሃይማኖታችን ልንቀበላቸውና ላንቀበላቸው ስለሚገባን ትምህርቶች በምሳሌ የተገለጹ መሆናቸው ነው፡፡ ከእነዚህ መልአክቶች አንዱም ‹‹ የተሰነጠቀ ሰኮና ያለውንና የሚያመሰኳውን እንስሳ ሁሉ ብሉ ፡፡ ነገር ግን ከሚያመሰኩት፥ ሰኮናቸው ስንጥቅ ከሆነው ከእነዚህ አትበሉም ግመል ያመሰኳል፥ ነገር ግን ሰኮናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። ሽኮኮ ያመሰኳል፥ ነገር ግን ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። ጥንቸልም ያመሰኳል፥ ነገር ግን ሰኮናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። እርያም ሰኮናው ተሰንጥቋል፥ ነገር ግን ስለማያመሰኳ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው።  የእነዚህን ሥጋ አትበሉም፥ በድናቸውንም አትነኩም በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ናቸው ›› / ዘሌ 11 3 -8 / ተብሎ በኦሪት የተገለጸው ይገኝበታል፡፡

 በኦሪት እንድነበላቸውና እንዳንበላቸው ለማድረግ እግዚአብሔር ለሙሴ ያዘዘው እያንዳንዳቸውን በሙሉ በመዘርዘር ሳይሆን በቡድን በመመደብና ምሳሌም በመጥቀስ ነው፡፡ እንድንበላቸው የተፈቀዱት እንስሳት ሁለት ነገሮችን ሊያሟሉ ይገባቸዋል፡፡ እንደተጻፈው የሚያመሰኩና ሰኮናቸው የተሰነጠቀ መሆን አለባቸው፡፡ ሁለቱንም ያልሆኑ ብቻ ሳይሆን ከሁለቱ አንዱንም የማያሟሉ ደግሞ አይበሉም፡፡ ይህ ትእዛዝ ቀደም ብለን ባየነው መሠረት ሦስቱን መልእክታት ያስተላልፋል፡፡  ታሪካዊ መልእክቱ ይህ ነገር ሕግ ሆኖ መቼ በማን ለማን እንደተሰጠና የመሳሰሉትን ሲነግረን ምግባራዊ መልእክቱ ደግሞ የፈጠራቸውን የሚያውቅ አምላክ ሳስቶና ተመቅኝቶ ሳይሆን ለሰውነታችን ባላቸው ጉዳትና በመሳሰሉት እንዳይበሉ አዝዟል፤ ዳግመኛም በዘመነ ኦሪት እነዚህን መብላትና አለመብላት የመርከስና የመቀደስ ዋና ምክንያትም ነበረ፡፡ በሐዲስ ግን የማይበሉትን እንኳ የማንበላው እግዚአብሔር ጥንቱንም ባይጠቅሙንም ስለሆነ አትብሉ ያለን ( ምንም ሲበሉ የኖሩትን ክርስቲያን ማድረጉ ወይም ክርስትና የሚቀድሳቸው መሆኑ የታወቀ ቢሆንም የማይበሉ የነበሩት ይብሉ ማለት አይደለምና) አይጠቅሙንምና አሁንም አንበላቸውም፡፡ ሐዋርያትም በዲዲስቅልያ ‹‹ ወቦ እለ ይብሉ ሥጋ አኅርው ንጹሕ ባሕቱ ኢኮነ ንጹሐ አላ ርኩስ፤ መፍትው ለነ ንርኀቅ እምዘ ከመዝ ግብር ወዘሰ ኮነ ንጹሐ በውስተ ሕግ ይብልዑ እምኔሁ ›› ማለትም ‹‹ የእሪያዎች ሥጋ ንጹሕ ነው የሚሉ አሉ፤ ነገር ግን ርኩስ ነው እንጂ ንጹሕ አይደለም፡፡ ከእንደዚህ ያለ ሥራ እንርቅ ዘንድ ይገባናል በመጽሐፍ ንጹሕ የሆነውን ግን ከእርሱ ይብሉ›› / አንቀጽ 32 46 - 47 ትርጉም ሊቃውንት ጉባኤ/ ሲሉ አዝዘውናልና፡፡ ዋናውና ምስጢራዊ መልእክቱ ግን ከዚህ ያለፈና በእጂጉ አስፈላጊ ነው፡፡

 ‹‹የሚያመሰኳና ሰኮናው  የተሰነጠቀ ›› ንጹሐን ናቸው የተባሉት በሃይማኖትና በምግባር የሚኖሩት መምህራንና ምእመናን ናቸው፡፡ የሚያመሰኳ ( በአሁኑ አማርኛ የሚያመነዥክ ሲባል የምንሰማው ነው ) ማለትም የቅዱሳት መጻሕፍትን ምስጢራት በኅሊናው የሚያመላለልስ ማለት ነው፡፡ የሚያመነዥክ ወይም የሚያመሰኳ እንስሳ ሳሩንም ቅጠሉንም ከበላው በኋላ እንደገና ወደላይ ወደ አፉ እያመጣ ደጋግሞ እንደሚያላምጠው ቅዱሳንና አውነተኛ መምህራንም አንዴ በትምህርት የተቀበሉትን ምስጢር ወይም ቃለ መጽሐፍ ከዋጡትና ካሳደሩት በኋላ ምስጢሩን ወደ ኅሊናቸው እያመላለሱ እያወጡና እያወረዱ የበለጠ እያራቀቁ ለራሳቸውም ሌላውም ጤናና ሕይወት ሰጭ ያደርጉታል፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ ብጹዕ ብእሲ ... ወዘሕጎ ያነብብ መዓልተ ወሌሊተ ሕጉን ወይም ቃሉን በሌሊትም በቀንም የሚያስብ ( ምሥጢራቱን የሚረዳ) ምስጉን ንዑድ ክቡር ነው ›› /መዝ 13/ ሲል የገለጸው ነው፡፡ ሰኮናው የተሰነጠቀ ማለት ደግሞ በተራመደ ጊዜ መሬት በደንብ የሚቆነጥጥ የሚጨብጥ ማለት ነው፡፡ ይሕም ማለት የሚናገረውንና የሚያውቀውን በሕይወት በደንብ መሬት አስጨብጦ ወይም ተግባራዊ አድርጎ የሚኖርበት ማለት ነው፡፡ዳዊት ከዚያው አስከትሎ  ‹‹ ይከውን ከመ ዕፅ እንተ ትክልት ሀበ ሙሐዘ ማይ እንት ትሁብ ፍሬሃ በበጊዜሃ ወቆጽላኒ ኢይትነገፍ  እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል / መዝ 1 3 /›› እንዳለው የሆነ ማለት ነው ፡፡

የማያመሰኳ እንስሳ የዋጠውን መልሶ እንደማይደቀው መልሶ መላልሶ እንደማያኝከው ሁሉ መናፍቃንም አንድ ጥቅስን በሆነ መንገድ ጎርሰው ከዋጡት በኋላ ምስጢር አያመላልሱም ደጋግመውም አያኝኩትም ማለትም የሚመላለሱ ምስጢራትን አያገኙም፡፡ ዳግመኛም ሰኮናቸው ስላልተሰነጠቀ መሬት አይቆነጥጡም፤ ሃይማኖቱንም በምግባር አይኖሩትም፤ እንዲሁ ሲያደናግሩ ይኖራሉ እንጂ፡፡ ይህም ማለት እንደ ገመል ገዝፈው ብናያቸውም ለሰኮናቸው የሚስማማ አሽዋ ( ያልረጋ ልቡና ) ፈልገው በዚያ ይኖራሉ እንጂ  እንደ ሌሎቹ ቆንጥጠው ረግጠው ገደልና ተራራ አይሻገሩም፤ ሃይማኖት አቀበትን ሊወጡ ገደላ ገድል ተጋድሎዎችንም አልፈው ለምስጢር ለክብር ሊበቁ አይችሉም፡፡ አሁንም ከላይ የመደንገጥና የመረበሽ ስሜት የታየባቸው አሉ ያልኩት በሃይማኖት ገና ያልረጋና እንደ አሸዋ የሚንሸራተት ልቡና ካለ የመናፍቃን ድፍን ሰኮና ይረግጠዋል የበለጠም ያንሸራትተዋልና  ሁላችንም ብንሆን ልቡናችን ለማጽናት እንድንጥር አብሮ ለመጠቆም ነው፡፡

 ከዚሁ ከሚበላውና ከማይበላው ሳንወጣ በባሕር ውስጥ ስላሉት እንድንበላቸው የታዘዙት ቅርፊትና ክንፍ ያላቸውን ነው፡፡ ይህም ማለት ቅርፊት ለባሕር ፍጥረታት ጋሻ መጠበቂያቸው እንደሆነ ሁሉ የሃይማኖት ጋሻ ወይም ከመናፍቃን የኑፋቄ ጦርና የክህደት መርዝ ለመዳን የሃይማኖትና የምግባር ጋሻ ከሌለና በክንፋችው ወደ ባሕሩ ላይኛው ክፍል ድረስ እንደሚንሳፈፉበትና ወደ ታች ብቻ እንደ ድንጋይ እንዳይዘቅጡ እንደሚጠበቁበት በመንፈሳዊነትና በንጽሕና ክንፍ ወደ ከፍተኛው የእግዚአብሔር ምስጢራትና መረዳት የማይወጡ እንደ ድንጋይ በከበደ በዚህ ዓለም ፍልስፍናና ሥጋዊ ሙግት ወደ መሬት መሬታዊነትና ሥጋዊነት የሚዘቅጡት መናፍቃን ‹‹ ርኩሳን›› ከሚባሉት መመደባቸውን አውቆ መጠበቅ ተገቢ ነው፡፡ እንዳልኩት እነርሱ ከዘመን አመጣሽ ሀሳብና ፍጹም ካልተማሩ ሰዎች ሀሳብና ክህደት የሚጠበቁበት ቅርፊት (ጋሻ) የሌላቸው ናቸውና፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ ሲሉ እንደሚደመጡት‹‹ አስኳሉን እንስጣችሁ ስንላቸው ቅርፊቱን አትንኩብን አሉ›› (በኤግዚቢሽን ማዕከል በተደረገው የተሐድሶዎች ልፈፋ ላይ አንድ አባ ተብየ የተናገረውን ያስታውሱ) እያሉ ቅርፊቱ አስኳሉን የያዘውና የሚጠብቀው መሆኑን እንኳ ማሰብ አቅቷቸው ቅርፊት መጠበቂያ የሌላቸው ብቻ ሳይሆኑ ካላቸውም ላይ መስበር የሚፈልጉ መሆናቸውን ነግረውናል፤ ራሳቸው መሆናቸውንም መንፈስ ቅዱስ አፋቸውን ጸፍቶ አናግሯቸዋል፤ በራሳቸውም ላይ አስመስክሯቸዋል፡፡ ስለዚህ ክርስቲያኖች ነጹሐን የሚበሉ (አምላካቸው የሚቀበላቸው) የሚሆኑት ጥርጥርንና ክህደትን ይህንም የመሰለ የመናፍቃንን የመዘባበትና የክህደት ጦር የሚከላከል በቅርፊት የተመሰለ የሃይማኖት ጋሻ ሲኖራቸው ነው፡፡ ከጋሻዎቻችን ዋናው ደግሞ የሃይማኖታችን ነገር የቅዱሳት መጻሕፍትንም ምስጢር ለብሶ ማለትም አውቆ መገኘት ነውና ጊዜ ወስዶ ቁጭ ብሎ መማር እንኳ ባይቻል በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ልቡናን ከፍቶ በወሬና በአሉባልታ ሳይጠመዱ መማር መጠየቅና እንደተገለጸው እያመላለሱ እያኘኩ እያጠኑ መያዝ ተገቢ ነው፡፡ ከዚህም በላይ በሃይማኖት ልብን ማጽናት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነገር ነው፡፡ ከሆነ ጠይቀን ያልገባንና የማናውቀውን እስከምንረዳ ድረስ ጊዜ እናገኛለን፡፡ ነገር ግን ብዙዎቻችን ትእግስት የለንም፤ ዛሬ ይህን ጽሑፍ ከምናነብበው እንኳ አንዳንዶቻችን ቀጥታ ነገሩን በቅርቡ ማግኘት ባለመቻላችን ልንበሳጭም እንችላለን፡፡  ነገር ግን አሁንም አስቀድመን አንዲት ጥያቄ ብቻ መልሰን እንሒድ፡፡
ከላይ እንድንበላና እንዳንበላ የታዘዙት እንስሳት በተገለጸው መንገድ እኛን የሚወክሉ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት ወይም የሐዋርያዊ ትምህርት ትውፊት አለ ወይ? አዎን በርግጥ አለ፡፡ ሰፊውና ዋናው ምስክር ቅዱስ ጴጥሮስ ያየው ራእይ ነው፡፡  ‹‹ ተርቦም ሊበላ ወደደ፤ ሲያዘጋጁለት ሳሉም ተመስጦ መጣበት፤ ሰማይም ተከፍቶ በአራት ማዕዘን የተያዘ ታላቅ ሸማ የሚመስል ዕቃ ወደ ምድር ሲወርድ አየ፤ በዚያውም አራት እግር ያላቸው ሁሉ አራዊትም በምድርም የሚንቀሳቀሱት የሰማይ ወፎችም ነበሩበት፡፡ ጴጥሮስ ሆይ፥ ተነሣና አርደህ ብላ የሚልም ድምፅ ወደ እርሱ መጣ ፡፡ ጴጥሮስ ግን ጌታ ሆይ፥ አይሆንም፤ አንዳች ርኵስ የሚያስጸይፍም ከቶ በልቼ አላውቅምና አለ ፡፡  ደግሞም ሁለተኛ። እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ፡፡ ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ፥ ወዲያውም ዕቃው ወደ ሰማይ ተወሰደ ›› /ሐዋ 10 10 -16/ ተብሎ እንደተጻፈው ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን ራእይ ደጋግሞ ካየ በኋላ ቀጥታ ምግብ ሳይሆን ምስጢራዊ መልእክት እንደሆነ ተረድቶ ምን ይሆን እያለ እያሰበ ነበር፡፡ በኋላ ግን መንፈስ ቅዱስ ገለጸለት፤  ‹‹  ጴጥሮስም ስለ ራእዩ ሲያወጣ ሲያወርድ ሳለ፥ መንፈስ። እነሆ፥ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤ ተነሥተህ ውረድ፥ እኔም ልኬአቸዋለሁና ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ አለው ›› /19-20/ ሲል ተናገረው፡፡ ሔዶም ከደረሰ በኋላ ‹‹ አይሁዳዊ ሰው ከሌላ ወገን ጋር ይተባበር ወይም ይቃረብ ዘንድ እንዳልተፈቀደ እናንተ ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን እግዚአብሔር ማንንም ሰው ርኵስና የሚያስጸይፍ ነው እንዳልል አሳየኝ ›› /. 27/ በማለት ምስክርነቱን አስቀደመ፡፡ በዚህም ባየው ራእይ ላይ ያያቸው የማይበሉ እንስሳት ምሳሌነታቸው ከእምነት ውጭ ላሉ ሰዎች አንደሆነ አረጋገጠ፡፡ ጌታችን ራሱ በዘመነ ሥጋዌው በሚያስተምርበት ጊዜ ‹‹  ደግሞ መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር የተጣለች ከሁሉም ዓይነት የሰበሰበች መረብን ትመስላለች፤ በሞላችም ጊዜ ወደ ወደቡ አወጡአት፥ ተቀምጠውም መልካሙን ለቅመው በዕቃዎች ውስጥ አከማቹ ክፉውን ግን ወደ ውጭ ጣሉት ›› / ማቴ 13 47- 48 / በማለት መረብ በተባለችው ቤተ ክርሰቲያን ሁሉንም እንደምታጠምድና አሳዎቹ ሐዋርያትንና ትምህርታቸውን ተቀብለው የዳኑትን ክርስቲያኖች ወጥተው የሚወድቁት ደግሞ መናፍቃንና ኃጥአንን እንደሚወክሉ በምሳሌ አስተምሮናል፡፡

ለመሥዋዕት የሚቀርቡት እንስሳትም የሰማዕታትና የቅዱሳን  ምሳሌዎች መሆናቸውን ቅዱስ መጽሐፍ ያስረዳል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹ አቤቱ፥ ስለ ምን ለዘወትር ጣልኸኝ? በማሰማርያህ በጎች ላይስ ቍጣህን ስለ ምን ተቈጣህ? ›› / መዝ 74 1/ እያለ መምለክያነ እግዚአብሔር እሥራኤልን በጎች ይላቸዋል፡፡  ‹‹ እንደ በጎች ሊበሉን ሰጠኸን፥ ወደ አሕዛብም በተንኸን ›› ‹‹ ስለ አንተ ሁልጊዜም ተገድለናል፥ እንደሚታረዱም በጎች ሆነናል ›› / መዝ 44 11 22/ በማለትም ሰማዕትነታቸውና ተጋድሏቸው እንደ መሥዋዕት በጎች እንደሚያስቆጥራቸው ተናግሯል፡፡  ይህ በርግጥ ስለ ሰማዕታ መሆኑንም ቅዱስ ጳውሎስ  ‹‹ ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው ››  /ሮሜ 836 /በማለት የተጻፈው ሰለእነርሱ መሆኑን አረጋግጦልናል፡፡  ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለራሱም  ‹‹ በመሥዋዕት እንደሚደረግ፥ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል ›› / 2 ጢሞ 4 6/ በማለት የሚቀበለውን ሰማዕትነት በመሠዋእት የመሰለው ጥንቱንም እነዚህ የመሥዋዕት እንስሳት የቅዱሳን የንጹሐን አማኞች ርኩሳን የተባሉት የማያምኑትና የመናፍቃን ምሳሌዎች በመሆናቸው ነው፡፡ ጌታም በነቢዩ በሕዝቅኤል ‹‹እናንተም በጎቼ፥ የማሰማርያዬ በጎች፥ ሰዎች ናችሁ እኔም አምላካችሁ ነኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር ››  /3431/ አስብሎ እሥራዔልን በጎቼ ይላቸው ነበር፡፡ ነቢያት ሁሉ ይህን ደጋግመው ተናግረዋል፡፡ ጌታም በዘመነ ሥጋዌው ትምህርቱ በሙሉ ይህን በማጽደቅ ነበር፡፡ በመጨረሻ ዕለትም ‹‹ በዚያን ጊዜ ኢየሱስ፦ በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ እረኛውን እመታለሁ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ የሚል ተጽፎአልና ›› / ማቴ 2631 / ያላቸው ቅዱሳኑ ንጹሐኑ የመሥዋዕቱ እንስሶች የሚያመሰኩትና ቆንጥጦ ለመርገጥ የሚያስችል ስንጥቅ ሰኮና ያላቸው እነርሱ በመሆናቸው ነው፡፡

ስለዚህ በጥንቱ ጊዜ ከሁለቱም ወገን የሚያርዱና የሚበሉ የነበሩ ቢሆንም እንኳ እግዚአብሔርና የእርሱ የሆኑት የሚቀበሉት ከንጹሐን የሆኑትን ብቻ ነበር፡፡ እንግዲህ ምሳሌ ከሆነ ዛሬም ከሁለቱም አለ፤ እግዚአብሔርና የእግዚአብሔር የሆኑት ሊቀበሉት የሚገባቸውም በንጹሐን እንስሳት ከተመሰሉት ከሐዋርያት ከሰማዕታት፣ ከቅዱሳን ሊቃውንትና ከእውነተኞች መምህራን የሚገኘውን ብቻ ነው፡፡ ቀደም ብለን እንደገለጽነው እነዚህ ቅዱሳን በበግና በመሳሰሉት የተመሰሉት በሰኮና መንሰጠቅ በሚመሰለው በትክክል መሬትን ጨብጦ ወይም ቆንጥጦ መርገጥ እንደሚችሉት እንዲሁ ሃይማኖታቸውን በሥራ ገልጠው ከእነርሱ የሚጠበቀውን መሥዋእት መሆን ወይም ሰማእትነትንም በገቢር ገልጸው የሚኖሩ በመሆናቸው ነው፡፡ በባሕር በሚኖረው ቅርፊትና ክንፍ ባለው  አሣ የተመሰሉትም በዚህ እንደባሕር በሚነዋወጥ ዓለም ውስጥ ሆነው ወደ ከፍተኛው ጸጋና ክብር ብቻ ሳይሆን ወደ ላይኛው ምስጢር ብቅ የሚሉበት ከንፈ ጸጋና የዚህን ዓለም አለማመን፣ ክህደትና ኑፋቄ ድል የሚነሡበት በቅርፊት የተመሰለ የእምነት ጋሻና ጦር ያላቸው በመሆኑ ነው፡፡ እኛንም ‹‹ በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ›› / ኤፌ 6 16/ ሲሉ አስተምረውናልና የእምነት ጋሻችንን እናነሳለን፡፡  ደግሞም  ‹‹ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው ›› / 2ቆሮ 10 4/ ተብሎ እንደተጻፈው መሣሪያችንም ሥጋዊ አይደለም፤ ነገር ግን የዲያብሎስን የተንኮልና የክህደት ምሽጎች ለመስበር ብርቱ ነው፡፡ ስለዚህ ከእነዚህ ክንፍና ቅርፊት የሌላቸው ከተባሉት ያለ መከላከያ ሆነው ራሳቸውን አስማርከው እኛንም ወደ እነርሱ ጥርጥርና ክህደት ሊስቡ ወደሚሮጡት ዳግመኛም የእግዚአብሔርን ቃል ምስጢራት ወደማያመላልሱትና ሰኮና ክሳደ ልቡናቸው መሬት ገቢርን ወደማይጨብጡት እንዳንጠጋ እነርሱ ሁልጊዜም በነፍስ ርኩሳን ናቸው ተብሎ ተጽፎልናልና፡፡  ስለዚህ  ጥያቄውንም የምንመልሰው በእነዚህ ያመሰኳሉ የተባሉት ሊቃውንት እየመላለሱ ቃሉን መርምረው ከእግዚአብሔር ተረድተው እንደጻፉልን በማመንና በዚሁ መንፈስ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ታዲያ ሠለስቱ ደቂቅን ያወጣቸው ማን ነው?
በቅርብ ቀን ይጠብቁ፡፡


© ይህ ጽሑፍ በቀጥታ ከዲ/ን ብርሃኑ አድማስ የመጽሐፈ ገጽ አድራሻ የተወሰደ ነው፡፡

1 comment:

FeedBurner FeedCount