በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፫ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም.)፡- ሠለስቱ ደቂቅን ያዳናቸው ማን ነው ለሚለው የተሐድሶዎች ጥያቄ የቀረበ መልስ
ሰሞኑን በተለይ በርከት ባሉት በመጽሐፈ ገጽ ወዳጆቼ በኩል ‹‹ ሠለስቱ ደቂቅን ያዳናቸው ማን ነው? ›› የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ ቀርቦልኛል፡፡ በተሐድሶዎች በተሰራጨ አንድ የቪዲዮ ቁራጭ ላይ በሦስቱ ድርሳናት ማለትም በድርሳነ ገብርኤል ላይ ገብርኤል ፤ በድርሳነ ሚካኤል ላይ ሚካኤል ፤ በድርሳነ ሩፋዔል ላይ ደግሞ ሩፋኤል አዳናቸው ተብሎ ስለተገለጸ ትክክሉ የቱ ነው፤ በርግጥ ያዳናቸውስ ማን ነው የሚል ነው፡፡ በዚያም ጊዜ ሆነ ዛሬ ከአንዳንዶቹ መልእክት እንደተረዳሁት የድንጋጤ ስሜትም የተሰማቸው አሉ፡፡ ይህን ሌሎች ተመሳሳይ ድርጊቶችንም ስመለከት ለጉዳዩ ቢያንስ አንዲት ትንሽ መጣጥፍ እንዳአቅሜ እንኳ ለጊዜው መስጠት እንዳለብኝ ስለተሰማኝ ጥያቄውን ለላካችሁልኝ ሁሉ ይህችን መቆያ እንካችሁ ብያለሁ፡፡ ዋናው ወይን ሁልጊዜም ወደ ኋላ መምጣቱ አይቀርምና እርሱን አብረን ከወይን አዳዩ እንጠብቃለን፡፡