Wednesday, December 11, 2013

ነገረ ማርያም - ክፍል ፫ (የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ መግባት)



በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲሳት መምህር

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፫ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
 ቅድስት ድንግል ማርያምም እስከ ሦስት ዓመት ድረስ በእናት በአባቷ ቤት ውስጥ ኖራለች፤ ይኽነን በእናት በአባቷ ቤት የነበራትን አስተዳደግ “Protoevangelium of James” (ፕሮቶቫንጊሊዩም ኦፍ ጀምስ) በሚለው ጥንታዊዉ መጽሐፍ ሲገልጽ (ሕፃኗም ከቀን ወደ ቀን በኀይልና በብርታት እያደገች ኼደች፤ የስድስት ወር ልጅ በኾነች ጊዜ እናቷ መቆም ትችል እንደኾነ ለማየት መሬት ላይ አቆመቻት፤ ርሷም ሰባት ርምጃ ተራምዳ ወደእናቷ ዕቅፍ ውስጥ ገባች፤ እናቷም እንዲኽ አለቻትወደ ጌታ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አስክወስድሽ ድረስ በራስች እንዳትራመጂ አለቻትና በመኝታ ቤቷ ውስጥ ውስጥ የቅድስና ስፍራ አበጀችላትአንድ ዓመት በኾናት ጊዜም ኢያቄም ታላቅ ግብዣ አድርጎ ካህናቱን፣ ጸሐፈትን፣ ታላቆችንና ሕዝብን ጠራ፤ ከዚያም ኢያቄም ልጁን ወደ ካህናቱ አቀረባት እነርሱምአባታችን እግዚአብሔር ሆይ ይኽቺን ልጅ ባርካት በትውልድ ኹሉ የሚጠራ ማብቂያ የሌለው ስምን ስጣት እያሉ ባረኳት፤ ሕዝቡም ኹሉይደረግ ይኹን ይጽና አሜንአሉ፤ ከዚያም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዳት ርሱምልዑል እግዚአብሔር ሆይ ይኽቺን ልጅ ተመልከት ለዘላለም በሚኖር በፍጹም በረከትም ባርካትበማለት ባረካት፤ ሐናም ይዛት ወደ ተቀደሰው የማደሪያዋ ክፍል በመውሰድ ጡትን ሰጠቻት…) ይላል፡፡

ከዚኽ በኋላ እናቷ ሐና ልጇ ሦስት ዓመት በኾናት ጊዜ ጠቢቡ ሰሎሞን በመጽሐፈ መክብብ ምዕ ፭፥፬- ላይሰነፎች ደስ አያሰኙትምና ለእግዚአብሔር ስእለት በተሳልኽ ጊዜ ትፈጽመው ዘንድ አትዘግይ የተሳልኸውን ፈጽመው፤ ተስለኽ የማትፈጽም ብትኾን ባትሳል ይሻላልብሎ የተናገረውን በማሰብ ባሏ ኢያቄምን ይኽቺ ብላቴና የብጽአት ገንዘብ እንደኾነች ታውቃለኽ ወስደን ለቤተ እግዚአብሔር እንስጣት አለችው፤ ርሱም ፍቅርሽ ይለቅልሽ ብዬ ነው እንጂ እኔማ ፈቃዴ ነው አለ፤ ኢያቄም ይኽነን ማለቱ ሐና እመቤታችንን በመካንነት ኑራ ያገኘቻት አንድያ ልጇ ናትና ከፍቅሯ ጽናት የተነሣ ተለይታት አታውቅም ነበርና ነው፡፡
ጥበብ ሥጋዊ ጥበብ መንፈሳዊ በእጅጉ የተሰጠው ሰሎሞን አስቀድሞ በመንፈሰ እግዚአብሔር በመቃኘት የሐና አንድያ ልጇ የኾነቺው በየዋህነቷ በርግብ የተመሰለች ቅድስት ድንግል ማርያምን ስፍር ቊጥር ከሌላቸው ከሌሎች ሴቶች ተለይታ ለአምላክ እናትነት ብቸኛ ተመራጭ መኾኗን በማሕ ፮፥፰- ላይ
አዋልድ እለ አልቦን ኊልቊ” (ቊጥር የሌላቸው ቆነዣዥት አሉ) በማለት ስፍር ቊጥር የሌላቸው እጅግ የበዙ ሴቶች መኖራቸው ከተናገረ በኋላአሐቲ ይእቲ እምኔሆን ርግብየ ፍጽምትየ” (ርግቤ መደምደሚያዬ አንዲት ናት) ብሎ ከነዚያ ኹሉ ተለይታ በየዋህነቷ በርግብ የተመሰለችው ቅድስት ድንግል ብቸኛ እናት ትኾነው ዘንድ በአምላክ የመመረጧን ነገር ከተናገረ በኋላአሐቲ ይእቲ ለእማ ወኅሪት ይእቲ ለእንተ ወለደታ” (ለእናቷ አንዲት ናት፤ ለወለደቻትም የተመረጠች ናት) በማለት እናቷ ቅድስት ሐና በመካንነት ከኖረች በኋላ የወለደቻት ምርጥ ልጇ መኾኗ ተገልጾለት ተናግሯል፡፡

ከዚኽ በኋላ ዳዊት በመዝ ፳፮፥፬፤ ፵፩፥፰፤ ፻፲፭፥፲፰-፲፱ ላይእግዚአብሔር በቀን ቸርነቱን ያዝዛል በሌሊትም ዝማሬው በእኔ ዘንድ ይኾናል የእኔ ስእለት ለሕይወቴ አምላክ ነውበሕዝቡ ሁሉ ፊት ስእለቴን ለእግዚአብሔር እፈጽማለሁ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ኢየሩሳሌም ሆይ በመካከልሽም ሃሌሉያእግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት እርስዋንም እሻለሁ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፥ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ፥ መቅደሱንም እመለከት ዘንድ … ” በማለት እንደተናገረ ኢያቄምና ሐና እግዚአብሔርን በማመስገን ካህኑ ዘካርያስንይኽቺ ብላቴና ተስለን አምላካችን በቸርነቱ የሰጠን ናትና ተቀበለንአሉት ርሱም ቢያያት እንደ ፀሓይ የምታበራ እንደ መብረቅ ግርማዋ የሚያስፈራ የምታበራ ዕንቈ ባሕርይ መስላ ታየችው፡፡
ርሱም በአድናቆት ይኽቺን የመሰለች ፍጥረት ምን እናደርጋታለን፣ ምን እናበላታለን፣ ምንስ እናጠጣታለን፣ ምን እናነጥፍላታለን፣ ምን እንጋርድላታለን ብሎ ሕዝቡን ሰብስቦ ሲጨነቁ ለእስራኤል ደመና ጋርዶ መናን አውርዶ የመገበ፤ ለኤልያስም በመልአኩ እጅ በመሶበ ወርቅ ኅብሥት የመገበ፤ ለዕዝራ ሱቱኤልም በመልአኩ በቅዱስ ዑራኤል እጅ መልኩ እሳት የሚመስል ጽዋዐ ልቡና ያጠጣው ልዑል እግዚአብሔር ለእናትነት ወደ መረጣት ወደ እናቱ መልአኩ ፋኑኤልን ላከላት (ዘፀ ፲፮፥፴፩፤ ፩ነገ ፲፱፥፮፤ ዕዝ. ሱቱ. ፲፫፥፴፰-፵፩)::

ይኽም ፋኑኤል የተባለው መልአክ ቊጥሩ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንደኛው ሲኾን ሐዋርያው ይሁዳ ከቊ፲፬-፲፭ ላይ ስለመጽሐፉ የጠቀሰለት የአዳም ሰባተኛ ትውልድ የኾነው ሞትን ሳያይ የተሰወረው ታላቁ አባት ሔኖክ በምዕ ፲፥፲፭ ላይአራተኛው የዘላለም ሕይወት የሚወርሱ ሰዎች ተስፋ ሊኾን ንስሐ በሚገቡ ሰዎች ላይ የተሾመ ፋኑኤል ነውበማለት የመልአኩን ክብር መስክሮለታል፡፡
ወሶቤሃ ወረደ ፋኑኤል ሊቀ መላእክት ወጸለላ በአክናፊሁ ወተለዐለ ላዕለ መጠነ ቆመ ብእሲ ወወሃባ ወመጠዋ ወዐርገ ውስተ ሰማይይላል በዚያን ጊዜ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ፋኑኤል ኅብስት ሰማያዊ በብርሃን ጽዋዕ ስቴ ሕይወት ይዞ ረቦ ወረደ፤ ዘካርያስ ለርሱ የመጣ ሀብት መስሎት ሊቀበል ቢነሣ ወደ ላይ ሰቀቀበት፤ ያን ጊዜ ጥበበ እግዚአብሔር አይመረመርምና ለዚኽች ብላቴና የመጣ ሀብት ይኾናል እስኪ እልፍ አድርጋችኊ አኑሯት አለ፤ እልፍ አድርገው ቢያኖሯት ድንኩል ድንኩል እያለች እናቷን ስትከተል መልአኩ አንድ ክንፉን አንጽፎ አንዱን ክንፉን አጐናጽፎ ከመሬት የሰው ቁመት ያኽል ከፍ ብሎ ኅብስቱን መግቧት ጽዋውን አጠጥቷት ወደ ሰማይ ዐርጓል፡፡

አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ በማሕሌተ ጽጌ የነገረ ማርያም መጽሐፋቸው ላይ በመልአኩ እጅ የመመገቧን ነገር ሲገልጹ የሐዝነኒ ማርያም ዘረከበኪ ድክትምና አመ ቤተ መቅደስ ቦእኪ እንዘ ትጠብዊ ሐሊበ ሐና
ወያሥተፌስሐኒ ካዕበ ትእምርተ ልሕቀትኪ በቅድስና ምስለ አብያጺሁ ከመ አብ እንዘ ይሴስየኪ መና ፋኑኤል ጽጌ ነድ ዘይከይድ ደመና (ማርያም የሐናን ወተት እየጠባሽ ወደ ቤተ መቅደስ በገባሽ ጊዜ ያገኘሽ ብቸኝነት ያሳዝነኛል፤ ዳግመኛም በደመና የሚመላለስ ደመናን የሚረግጥ የእሳት አበባ ፋኑኤል ከጓደኞቹ መላእክት ጋር መናን እየመገበሽ በንጽሕና የማደግሽ ተአምር ደስ ያሰኘኛል) በማለት አመስግነዋል፡፡

ካህናቱም ሕዝቡም የምግቧማ ነገር ከተያዘ ከሰው ጋራ ምን ያጋፋታል ቦታዋ ከቤተ መቅደስ ይኹን እንጂ ብለው ዙፋኑን ዘርግተው፣ ምንጣፉን አንጥፈው፣ ግራና ቀኝ መጋረጃውን ጋርደው ነቢዩ ዳዊትም በመዝ 414 ላይወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ምስጋና መኖሪያ ስፍራ እገባለሁና በዓል የሚያደርጉ ሰዎች የደስታና ምስጋና ቃል አሰሙበማለት እንደተናገረ ስላዩትና ስለተደረገው ነገር ኹሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ አማናዊት የአምላክ መቅደስ የአካላዊ ቃል ታቦት እመቤታችንን ወደ ቤተ መቅደስ በ፭ሺሕ ፬፻፹፰ ዓመተ ዓለም በሦስት ዓመቷ አስገቧት፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከእናቷ ከአባቷ ቤት ተለይታ በእግዚአብሔር ቤት በቤተ መቅደስ እንደምታድግ ነቢዩ ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ ተገልጾለት በመዝ ፵፬፥፱-፲፩ ላይበወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች ልጄ ሆይ፥ ስሚ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ ወገንሽን ያባትሽንም ቤት እርሺ ንጉሥ ውበትሽን ወድዶአልና፥ እርሱ ጌታሽ ነውናበማለት የተናገረው ትንቢት ሊደርስ ሊፈጸም አማናዊት መቅደስ ርሷ ምሳሌዋ ወደሚኾነው ቤተ መቅደስ እንድትገባ ባለቤቱ አድርጓል፡፡
በቤተ መቅደስ ውስጥ በንጽሕናና እግዚአብሔርን እያገለገሉ ስለማደግና ስለመኖር መጽሐፍ ቅዱስ በስፋት ሲገልጽ ከዚኽ ውስጥ በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ከተወለደ በኋላ በስለት ተሰጦ የእግዚአብሔር አገልጋይ ኹኖ በቤተ መቅደስ ያደገው ሳሙኤል ሲጠቀስ በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ደግሞ ከአሴር ወገንም የነበረችው የፋኑኤል ልጅ ነቢይት ሐና ከድንግልናዋ ጀምራ ከባልዋ ጋር ሰባት ዓመት ከኖረች በኋላ ሰማኒያ አራት ዓመት ያህል መበለት ኾና በጣም አርጅታ ሳይቀር በጾምና በጸሎትም ሌሊትና ቀን እያገለገለች ከመቅደስ አትለይም እንደነበር ተጽፎ እናነባለን (፩ሳሙ ፪፥፲፰፤ ሉቃ ፪፥፴፮-፴፯)፡፡

አማናዊት የአምላክ መቅደስ እመቤታችንም ምሳሌዋ በኾነ በቤተ መቅደስ ከገባች ዠምሮ መላእክት እያረጋጓት ካህናት እያመሰገኗት ኅብስት ሰማያዊ እየመገቧት ጽዋዕ ሰማያዊ እያጠጧት ለዐሥራ ኹለት ዓመት ያኽል በቤተ መቅደስ ስለመቀመጧ በ፭፻፭ (505) . የተወለደው ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድም በአንቀጸ ብርሃን የነገረ ማርያም መጽሐፉ ላይ ሲገልጽ፡- “አንቲ ውእቱ ንጽሕት እም ንጹሓን ድንግል ኅሪት ዘነበርኪ ውስተ ቤተ መቅደስ ከመ ታቦት ዘግቡር እምዕፅ ዘኢይነቅዝ ሥርግው በወርቅ ንጡፍ ወልቡጥ በዕንቈ ባሕርይ ዘየሐቱ ዘብዙኅ ሤጡ ከመዝ ነበርኪ ውስተ ቤተ መቅደስ ወመላእክት ያመጽኡ ወትረ ሲሳየኪ ከመዝ ነበርኪ ፲ተ ወ፪ተ ዓመተ እንዘ ትትናዘዚ እምኀበ መላእክት ስቴኪኒ ስቴ ሕይወት…” (ከንጹሓን ይልቅ ንጽሕት የኾንሽ አንቺ ነሽ፤ ከማይነቅዝ ዕንጨት እንደተሠራ በወርቅ እንደተጌጠና ዋጋው ብዙ በኾነ በሚያበራ ዕንቊ እንደተለበጠ ታቦት በቤተ መቅደስ ውስጥ የኖርሽ የተመረጥሽ ድንግል ነሽ፤ እንዲኽ ኾነሽ በቤተ መቅደስ ውስጥ ኖርሽ፤ መላእክት ዘወትር ምግብሽን ያመጡ ነበር፤ መላእክት እየጐበኙሽ እንዲኽ ዐሥራ ኹለት ዓመት ኖርሽ፤መጠጥሽም የሕይወት መጠጥ ነበር፤ ምግብሽም የሰማይ ኅብስት ነበር፤ አባትሽ ዳዊት በመሰንቆ አመሰገነ በትንቢት መንፈስም በመንፈስ ቅዱስ በገና እየደረደረ እንዲኽ ብሎ ዘመረ፤ ልጄ ሆይ ስሚ እዪም ዦሮሽንም አዘንብዪ ሕዝብሽንና የአባትሽን ቤት ርሺ፤ ንጉሥ ደም ግባትሽን ወዷልና፤ ርሱ ጌታሽ ነው፤ ለርሱ ትሰግጃለሽ (መዝ ፵፬)) በማለት በቤተ መቅደስ በነበረችበት ወቅት የተደረገውን ተአምራት አድንቋል፡፡
ሊቁ አባ ሕርያቆስም በተመሳሳይ መልኩ በቅዳሴ ማርያም መጽሐፉ ላይ (ድንግል ሆይ አንገታቸውን እንደሚያገዝፉ እንደ ዕብራውያን ሴቶች ልጆች በዋዛ ያደግሽ አይደለም፤ በንጽሕና በቅድስና በቤተ መቅደስ ኖርሽ እንጂ፤ ድንግል ሆይ ምድራዊ ኅብስትን የተመገብሽ አይደለሽም፤ ከሰማየ ሰማያት የበሰለ ሰማያዊ ኅብስትን ነው እንጂ፤ ድንግል ሆይ ምድራዊ መጠጥን የጠጣሽ አይደለሽም፤ ከሰማየ ሰማያት የተቀዳ ሰማያዊ መጠጥን ነው እንጂ፤ ድንግል ሆይ ከአንቺ አስቀድሞ ከአንቺም በኋላ እንዳሉ ሴቶች ዕድፍን የምታውቂ አይደለሽም፤ በንጽሕና በቅድስና ያጌጥሽ ነሽ እንጂ፤ ድንግል ሆይ የሚያታልሉ ጐልማሶች ያረጋጉሽ አይደለሽም የሰማይ መላእክት ጐበኙሽ እንጂ እንደተነገረ ካህናትና የካህናት አለቆች አመሰገኑሽ እንጂ) በማለት እመቤታችን በቤተ መቅደስ በነበረችበት ዐሥራ ኹለት ዓመታት የተደረገላትን ድንቅ ሥራ ገልጾታል፡፡
እመቤታችን ወደ ቤተ መቅደስ እንዴት እንደገባችና በቤተ መቅደስ ውስጥ የነበራትን ቆይታ ቀደምት የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በጥልቀት ጽፈዋል፤ ከእነዚኽ መኻከል ሊቁ የቆጵሮሱ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ የቤተ መቅደስ ቅድስናዊ አኗኗሯን ሲጽፍ “She was grave and dignifified in all her action…” (እመቤታችን በኹሉም እርምጃዎቿ ጐበዝና የተከበረች ነበረች፤ የምትናገረው በጣም ጥቂት ሲኾን ርሱም ለማድረግ አስፈላጊ በሚኾንበት ብቻ ነበር፤ በጣም ዝግጁ ኾና የምትሰማና በቀላሉ ንግግር ለማድረግ የምትችል ናት፤ ለእያንዳንዱ ሰው አክብሮትና ክብር (ሰላምታ) ትሰጣለች፤ ቁመቷ መኻከለኛ ሲኾን አንዳንዶች ግን ቁመቷ ከፍ ያለ እንደነበር ይናገራሉ፤ ከእያንዳንዱ ሰው ጋር ያለምንም ፍርሃት በግልጽነት ያለምንም ሳቅና መጯጯኽ ትናገራለች፤ በተለይ ፈጽማ ለቁጣ የምትጋበዝ አልነበረችም፤ መልኳ እንደ ደረሰ የስንዴ አዝመራ ያማረ ጸጒሯ ቀይማ ነው፤ ዐይኖቿ ብሩሃትና የዋህ የኾኑ ቀለማቸውም ፈዘዝ ያለ ቡናማ ኾኖ የዐይኖቿ ብሌኖች የዘይት-አረንጓዴ ይመስላል፤ የዐይኖቿ ቅንድብ (ሽፋሽፍት) ከፊል ክብና ደማቅ ጥቁር ናቸው፤ አፍንጯዋም ረዥም፣ ከናፍሮቿ ቀይና ምሉዕ ሲኾኑ በቃላቷ ጣፋጭነት የተጥለቀለቁ ነበሩ፤ ፊቷ ክብ ሳይኾን ግን እንቁላልማ ዐይነት ቅርጽ ነበረው፤ እጆቿ ረዥምና ጣቶቿም በጣም ረዣዥም ነበሩ፤ ከማንኛውም ያልተገባ ኩራት ሙሉ በሙሉ የነጻች ስትኾን ግድ የለሽነት ፈጽሞ ጨርሶ የለባትም ነበር፤ የሚመጡትን ነገራት በፍጹም ትሕትና ትቀበል ነበር፤ ተፈጥሯዊ ቀለማት ያላቸው (ማለትም በቤት ድር የተሠሩ) ልብሶችን ታረግ ነበር፤ ይኽም በእጅጉ አብሯት የሚኼደው አለባበስና ይኽ እውነታ በራሷ ላይ በምታደርገው ቅዱስ ልብስ አኹን ቅሉ ሊረጋገጥ የሚችል እውነታ ነው፤ ለማጠቃለል ያኽል በመንገዶቿ ኹሉ በመለኮታዊ ጸጋ የተመላች ነበረች) በማለት የመልኳን አስደናቂ ደም ግባትና የአኗኗሯን ነገር መንፈስ ቅዱስ በገለጸለት መጠን ጥንታውያን አባቶች እነያዕቆብ የተናገሩትን መነሻ በማድረግ ጽፎታል፡፡
የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳስ ዲሜጥሮስ በክርስቶስ ልደት በታኅሣሥ ፳፱ ዕለት በሚነበበው ድርሳኑ ላይ የእመቤታችንን የቤተ መቅደስ ሕይወት ሲያስተምር “At the moment when her mother Anna set her upon her feet, inside the door of the temple…” (እናቷ ሐና በካህናቷ ፊት በቤተ መቅደሱ በር ላይ ርሷን በእግሯ ባኖረቻት ጊዜ በራሷ ለጌታ መሥዋዕት ወደሚቀርብበት ወደ መሠዊያዉ መጋረጃ ወደ ቤተ መቅደስ እስክትደርስ ድረስ ኼደች፤ ከገባችም በኋላ ለመውጣት አልተመለሰችም በልቡናዋም የቤተሰቦቿ ሐሳብና ምድራዊ ነገራትን ከቶ አላሰበችምእናም ባደገችና ስምንትና ዐሥር ዓመት በመላትም ጊዜ ለካህናቱ ኹሉ አብነት (ምሳሌ) ነበረች ርሷንም ለማየት ይፈሩ ነበር፤ መላ ሰውነቷ ንጹሕ ነበር ልቡናዋም በጌታ የጸና ነው፤በሥጋዋም በነፍሷም ንጽሕት ናት፤ ፊቷንም ከቤተ መቅደሱ በር ውጪ በፍጹም አላዞረችም፤ እንግዳ ሰውንም ከቶ አላየችም የወጣት ሰው ፊትን ለመመልከት ፊቷን ከቶ አላዞረችም፤ በቅድስና እግዚአብሔርን በማገልገል ለቤተ መቅደስ በመላላክ ኖረች እንጂ፤ ልብሷ ያማረ እጥፋቱ በማኅተሟ ላይ ወደ ታች የወረደ ሲኾን የራሷ መሸፈኛም እስከ ዐይኖቿ ይደርሳልበዐይኖቿ ላይ በጭራሽ መዋቢያ ቀለም አልተጠቀመችም፤ በጉንጮቿ ላይ ምንም ዐይነት የማጌጫ አበባ አላኖረችም፤ በእግሮቿ ላይ መጫሚያ ሰንደሎች አላደገረችም፤ በክንዶቿና በእጆቿ ላይ አልቦ ወይም አምባር ወይም ጌጣጌጥ አላደረገችም ነበር፤ ከልክ ያለፈ ምግብ በጭራሽ ፈልጋ አታውቅም፤ በከተማዋ የገበያ ስፍራ ውስጥ በጭራሽ ተጉዛ አታውቅም፤ ለዚኽ ዓለም ሥራዎች በጭራሽ ጉጉት ዐድሮባት አያውቅም፤ ራሷን በጭራሽ ለመራቈት አጋልጣ እንዲኹም የአካላቷን ክፍሎች በጭራሽ በጥንቃቄ በአትኩሮት መርምራ አታውቅም) በማለት በቤተ መቅደስ በፍጹም ንጽሕናና ቅድስና መኖሯን መስክሯል::
እስክንድርያዊዉ ቅዱስ ቄርሎስም ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ከማብሠሩ በፊት የነበራትን የትሕትና ሕይወት ለተሰበሰቡት ሴቶች ሲያስተምር “Come, O all ye women who desire virginity…” (ድንግልናን የምትፈልጉ ሴቶች በሙሉ የጌታችን እናት የኾነችውን የማርያምን ምሳሌ ተከተሉ፤ የርሷንም መንገድ መናኛ ምግብ መብላቷንና መሬት ላይ መተኛቷን አስቡ፤ ለዚኽ ዓለም ነገሮች ምንም ዐይነት ጉጉት የላትምና የርሷ ስምም ኹልጊዜም በካህናት አፍ ውስጥ ነበር፤ ሰውነቷን በጭራሽ በሕዝብ መታጠቢያ ውስጥ ታጥባ አታውቅም፤ ራሷን በፍጹም በመዋቢያ የፊት ቀለም፣ በዐይን ኩልና በቅባት በጭራሽ አስውባ አታውቅም፤ በጣም ያጌጠ ልብስ እንደሚወድዱ ኹሉም በዘመኗ የነበሩ ሴቶች በደማቅ ባለቀለም ልብስ በጭራሽ አስጌጣ አታውቅም፤ በጭራሽ የወይንን ጣዕም ቀምሳ አታውቅም፤ ኹልጊዜም ዓለማትን የፈጠረ ፈጣሪዋን ትጠብቅ ስለነበር ፊቷን ወደ ምሥራቅ አዙራ ትቀመጥ ነበር፤ ከእናቷና ከአባቷ በስተቀር ከማንም ጋር ተገናኝታና አውርታ አታውቅም) በማለት የደናግል መመኪያቸው የኾነች የእመቤታችን የቤተ መቅደስ ሕይወት ለንጹሓን ደናግል አስተማሪ እንደነበር በስፋት ገልጾታል፡፡

የኢየሩሳሌሙ ቅዱስ ቄርሎስ በድርሳኑ ላይ የእመቤታችንን የቤተ መቅደስ ሕይወት ሲያስተምር “They (i.e Joachim and Anna) were in the habit of visiting their daughter once each month,…’’ (እነርሱ (ኢያቄምና ሐና) በወር አንድ ጊዜ ልጃቸውን በወር አንድ ጊዜ የመጐብኘት ልምድ ነበራቸው፤ ለርሷ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ይዘው ይመጡ ነበር፤ እናም ትንሿ ድንግል ልጃቸው ከርሷ በዕድሜ ከፍ ከሚሉ ደናግል ጋር በቤተ መቅደስ ታገለግል ነበር፤ እነርሱም በእጆቿ እንዴት መሥራት እንደምትችል ያስተምሯት ነበር፤ ርሷም ዐዋቂ በኾነች ጊዜ በራሷ ወደ ቤተ መቅደሱ ዐደባባይ ስትኼድ ከካህናትና ከአባቷ በቀር ማንም ወንድ ከቶ አይቷት አያውቅምትንሿ ድንግል ማርያም በቤተ መቅደስ ነበረች፤ የመላእክት አለቃው ገብርኤል በጣፋጭ መዐዛው ወደ ርሷ ቀረባትየርሷ ውበቷ ምንም ወሰን አልነበረውም፤ ቤተ መቅደሱም ከጣፋጭ መዐዛዋ የተነሣ በመላእክት ይመላ ነበር፤ ለንግግሯ ሲሉ ብቻ ይጐበኟት ነበረ) በማለት የቤተ መቅደስ አኗኗሯን በጥልቀት ገልጾታል፡፡
የወርቃማው ዘመን ሊቃውንት ከሚባሉት ውስጥ ተጠቃሹ ቅዱስ አትናቴዎስመልእክት (ደብዳቤ) ለደናግል” (Letter to Virgins) በሚል ሥራው ላይ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የቤተ መቅደስ ሕይወቷ ለደናግል ኹሉ አርአያና ምሳሌ እንደነበር ሲገልጸው “Mary was pure virgin, with a harmonius disposition…” (ማርያም ንጽሕት ድንግል ስትኾን በጣም ጥሩ አቋም የነበራትና መልካም ሥራዎችን የምትወድ ነበረች፤ በወንዶች መታየትን ፈጽማ አትፈልግም ነበር፤ ግን እግዚአብሔርን እንዲመረምራት ጠይቃዋለች፤ ያለማቋረጥ በቤቱ ውስጥ ቆይታለች፤ ከጨዋታ የራቀ ሰውን ኑሮ ትኖር የነበረ ሲኾን ማር ከምትሰጥ ንብ ጋር ትመሳሰላለች፤ በእጆቿ ከሠራቻቸው ሥራዎች የምታገኘውን ገንዘብ ለድኾች ታከፋፍላለች፤ በብቸኝነት ኹለት ነገራትን እንዲያደርግላት ወደ እግዚአብሔር ትጸልያለች፤ ይኸውም መጥፎ ሐሳብ በልቧ ውስጥ እንዳይሠርፅና ልቧ በጭራሽ ከፍቅር አምላካዊ እየቀዘቀዘ እንዳይኼድ ነበረ፤ ንግግሯ የተረጋጋ እና ድምፆቿም ዝግ ያሉ ናቸው፤ በየቀኑም መንፈሳዊ ርምጃ (ብቃታዊ መሻሻል ዕድገት) ማድረግ ትፈልጋለች፤ በየቀኑም ያነን ታደርጋለች፤ በጠዋት ስትነሣም ከዚኽ በፊት አስቀድማ ከሠራቻቸው አስበልጣ ሥራዎቿን ለመሥራት ትፈልጋለች፤ ሞትን ፈጽማ አትፈራም ነበር ይልቁኑ በሐዘን ኹና የመንግሥተ ሰማያት መዠመሪያ (መግቢያ) እንዳላቋረጠች በየቀኑ እያየች በጸሎቷ ታነሣለች) በማለት የደናግል መመኪያነቷን በስፋት ገልጾታል፡፡
ነቢዩ ዳዊት በመዝ ፺፩፥፲፪-፲፫ ላይጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል፥ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ያድጋል በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተተክለዋል፥ በአምላካችንም አደባባይ ውስጥ ይበቅላሉበማለት ቅዱሳን በእግዚአብሔር ቤት እንደሚኖሩ በምስጋናው እንደገለጸ ኹሉ የቅዱሳን ቅድስት እመቤታችንም በቤተ መቅደስ በንጽሕና በቅድስና ኖራለች፡፡

6 comments:

  1. Qale hiwot yasemalin, I really didn't know all these details of her life. Please translate such homilies to Amharic for the future.

    ReplyDelete
  2. እንዲህ ዓይነቱን የአጋንንት ትምሕርት በሰው ልብ ውስጥ የሚዘራ ክፉ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተረገመ ይሁን!! አሜን!!1

    ReplyDelete
    Replies
    1. "tinbitu yifetsem zend yegd new " legna lekrstianoch adis aydelem.!!!

      Delete
  3. “... ጌታ ይገስፅህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም፡፡ እነዚህ ግን የማያውቁትን ሁሉ ይሳደባሉ...” ይላል፤ ስለዚህ እህቴ/ወንድሜ ሆይ ስለምን መሳደብ ይሁዳ1፡9-10

    ReplyDelete
  4. አጋንንት ማለት ተሳዳቤ ፣ በውስጡ ክፋት ያለው ነው ። ምንስ ቤል ምን ይገርማል።

    ReplyDelete
  5. citation required for church fathers

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount