በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ
ኮሌጅ የሐዲሳት መምህር
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፫ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ቅድስት ድንግል ማርያምም እስከ ሦስት ዓመት ድረስ በእናት በአባቷ ቤት ውስጥ ኖራለች፤ ይኽነን በእናት በአባቷ ቤት የነበራትን አስተዳደግ “Protoevangelium of James” (ፕሮቶቫንጊሊዩም ኦፍ ጀምስ) በሚለው ጥንታዊዉ መጽሐፍ ሲገልጽ (ሕፃኗም ከቀን ወደ ቀን በኀይልና በብርታት እያደገች ኼደች፤ የስድስት ወር ልጅ በኾነች ጊዜ እናቷ መቆም ትችል እንደኾነ ለማየት መሬት ላይ አቆመቻት፤ ርሷም ሰባት ርምጃ ተራምዳ ወደእናቷ ዕቅፍ ውስጥ ገባች፤ እናቷም እንዲኽ አለቻት “ወደ ጌታ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አስክወስድሽ ድረስ በራስች እንዳትራመጂ አለቻትና በመኝታ ቤቷ ውስጥ ውስጥ የቅድስና ስፍራ አበጀችላት… አንድ ዓመት በኾናት ጊዜም ኢያቄም ታላቅ ግብዣ አድርጎ ካህናቱን፣ ጸሐፈትን፣ ታላቆችንና ሕዝብን ጠራ፤ ከዚያም ኢያቄም ልጁን ወደ ካህናቱ አቀረባት እነርሱም “አባታችን እግዚአብሔር ሆይ ይኽቺን ልጅ ባርካት በትውልድ ኹሉ የሚጠራ ማብቂያ የሌለው ስምን ስጣት እያሉ ባረኳት፤ ሕዝቡም ኹሉ “ይደረግ ይኹን ይጽና አሜን” አሉ፤ ከዚያም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዳት ርሱም “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ ይኽቺን ልጅ ተመልከት ለዘላለም በሚኖር በፍጹም በረከትም ባርካት” በማለት ባረካት፤ ሐናም ይዛት ወደ ተቀደሰው የማደሪያዋ ክፍል በመውሰድ ጡትን ሰጠቻት…) ይላል፡፡