Sunday, December 22, 2013

ነቢዩ ኢዩኤል

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፲፬ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
“ኢዩኤል” ማለት “እግዚአብሔር አምላክ ነው” ማለት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱሳችን እንደምንመለከተውም “ኢዩኤል” የሚለው ስም በዕብራውያን የተለመደ መኾኑ ነው /፩ኛ ሳሙ.፰፡፪፣ ፩ኛ ዜና ፬፡፴፭፣ ፪ኛ ዜና ፳፱፡፲፪፣ ዕዝራ ፲፡፵፫/፡፡
 አባቱ ባቱአል እናቱም መርሱላ ይባላሉ፡፡ የመጽሐፉ የአንድምታ ትርጓሜ መቅድም እንደሚናገረው ነገዱ ከነገደ ሮቤል ወገን ነው፡፡ ሌሎች ሊቃውንት ግን ኢዩኤል ከነገደ ይሁዳ ወገን እንደኾነ ይናገራሉ፡፡ ለዚኽ አባባላቸው እንደ ማስረጃ የሚያስቀምጡትም አንደኛ ኢዩኤል ይኖር የነበረው በኢየሩሳሌም መኾኑ፤ ኹለተኛ በመጽሐፉ ስለ ካህናት ማንሣቱ /፩፡፲፫/፤ ሦስተኛ ስለ ቤተ መቅደስ መናገሩ /፩፡፱/፣ እና ሌላም ሌላም በማለት ነው፡፡

 በብዙ ሊቃውንት ዘንድ ነቢዩ ኢዩኤል የነበረበት ዘመን ላይ ልዩነት አለ፡፡ አንዳንዶቹ ከምርኮ በፊት ነበረ ሲሉ ሌሎች ደግሞ “አይደለም ከምርኮ በኋላ የነበረ ነው” ይላሉ፡፡ ኹለቱንም ወገኖች የሚያቀርቡትን ማስረጃ እንስቀምጥና አንባብያን የየትኞቹ አሳማኝ እንደኾነ ማየት ይችላሉ፡፡ አስቀድመንም “ከምርኮ በኋላ ነበረ” የሚሉትን እንመልከት፡፡ እነዚኽ ሊቃውንት ነቢዩ ኢዩኤል ከምርኮ በኋላ ነበረ ለማለት ያነሣሣቸው፡-
1.     ነቢዩ ኢዩኤል በዘመኑ ስለ ነበረው ንጉሥ ሳይናገር ይልቁንም ስለ ካህናትና ስለ ሽማግሌዎች መናገሩ በእስራኤልና በይሁዳ ከምርኮ ከተመለሱ በኋላ ንጉሥ ስላልነበራቸው ነው፡፡
2.    ነቢዩ ኢዩኤል ስለ ሰሜናዊው ግዛት ማለትም ስለ እስራኤል አለመናገሩና ስለ ይሁዳ ብቻ መናገሩ ዘመኑ ከምርኮ በኋላ መኾኑ ያመለክታል፡፡
3.    ነቢዩ ኢዩኤል ከኢየሩሳሌም ውጪ በሰማርያ ስለ ነበሩ የአምልኮ ዐፀዶች ምንም አላለም፡፡ ስለ አምልኮተ ጣዖትና ስለ በኣልም ምንም አላለም፡፡ እነዚኽ ደግሞ ገንነው ይታዩ የነበረው ከምርኮ በፊትና በምርኮው ጊዜ እንጂ ከምርኮ በኋላ አይደለም፡፡
4.    ነቢዩ ካህናቱን፡- “የእግዚአብሔር አገልጋዮች” ብሎ ጠርቷቸዋል /፩፡፲፫/፡፡ ይኽ ዓይነቱ አጠራር ደግሞ ከምርኮ በኋላ ባለው ጊዜ በጣም በተደጋጋሚ ይዘወተር የነበረ አባባል ነው፡፡

  አኹን ደግሞ “ከምርኮ በፊት የነበረ ነው” የሚሉ ሊቃውንት ለትምህርታቸው እንደ ማስረጃ የሚያቀርቡትን እንመልከት፡-
1.     ነቢዩ በጊዜው የነበረውን ንጉሥ ማን እንደኾነ አለመጥቀሱ ንጉሡ ገና ሕፃን ስለ ነበረ ሊኾን ይችላል፡፡ ይኸውም ኢዮአስ መንገሥ የዠመረው በሰባት ዓመቱ እንደነበረ ማለት ነው /፪ኛ ዜና.፳፬፡፩/፡፡ ሕፃን ከኾነ ደግሞ የሚነገረው ነገር ማመዛዘን ስለማይችል፡- “እገሌ ንጉሥ ሳለ እንዲኽ ያለ ትንቢት ተናገርኩ” ቢል ተቀባይነት የለውም፡፡ ወይም ደግሞ ነቢዩ የሚፈልገው የሕዝቡን የንስሐ ሕይወት እንጂ የፖለቲካ ጉዳይ ስላልኾነ ነው፡፡
2.    ነቢዩ ስለ አምልኮተ ጣዖት፣ ወይም ስለ በዓል አለመናገሩ የትንቢት መጽሐፉን ከምርኮ በኋላ መጻፉን አያመለክትም፡፡ ይልቁንም የስብከቱ መንገድ አንዱን አቅጣጫ ማለትም ስለ በዓልና ስለ አምልኮተ ጣዖት ሳይናገር እግዚአብሔርን በንጹሕ ልቡና ማምለክ እንዳለባቸው መንገርን ስለ መረጠ ነው፡፡
3.    ብዙ ነቢያት ለምሳሌ እነ ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤል እና አሞጽ ከትንቢተ ኢዩኤል መጽሐፍ ጠቅሰው ተናግረዋል፡፡ ስለዚኽ ነቢዩ ከእነዚኽ በፊት ነበረ ማለት ነው፡፡
4.    ነቢዩ ኢዩኤል ምርኮ እንደሚኾን ተናገረ እንጂ እንደኾነ አልተናገረም /ኢዩ.፫፡፪-፫/፡፡ ይኽም ከምርኮ በፊት እንደ ነበረ ያስረዳል፡፡
5.    ነቢዩ ግብጽ የይሁዳ ባላንጣ እንደኾነች ተናግሯል /፫፡፲፱/፡፡ ይኽም ከምርኮ በፊት እንጂ ከምርኮ በኋላ ሊኾን አይችልም፡፡ ከዚኽም በተጨማሪ ከምርኮ በፊት ስለነበሩ የይሁዳ ጠላቶች ማለትም ስለ ጢሮስ፣ ስለ ሲዶና፣ ስለ ፍልስጥኤማውያን /፫፡፬/፣ ስለ ኤዶምያስ /፫፡፲፱/ መናገሩ ነቢዩ ከምርኮ በፊት እንደነበረ ያሳያል፡፡
6.    ነቢዩ ስለ ሰሜናዊው መንግሥት ማለትም ስለ እስራኤል አለመናገሩና ጠቅለል አድርጐ ስለ እስራኤል መናገሩ አንደኛ ኹለቱም ሕዝቦች አንድ በመኾናቸው /፪፡፳፯፣ ፫፡፲፮/፤ ኹለተኛው የነቢዩ አገልግሎት በይሁዳ ስለነበር፤ ሦስተኛውና ዋናው ደግሞ ነቢዩ በትንቢት መነጽር በአዲሲቱ እስራኤል (በቤተ ክርስቲያን) መለያየት እንደሌለና ኹሉም አንድ እንደሚኾኑ ሲናገር ነው፡፡
ትንቢተ ኢዩኤል
 ምንም እንኳን ነቢዩ ኢዩኤል የይሁዳን ከተማ የሚወርራት አስፈሪውን የአንበጣ መንጋ ድምፅ ቢሰማም፤ ምንም እንኳን የአንበጦቹ መንጋ ሰማዩን ሲከድነው፣ ፀሐይቱ ስትጨልም፣ ኹሉም ጭጋጋም ኾኖ ቢመለከትም፤ ምንም እንኳን ዛፉ ኹሉ ደርቆ ምድሪቱ ምድረ በዳ ስትኾን ቢያይም ከዚያ ጀርባ የነበረችይቱን የእግዚአብሔር ጣትም ያይ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር እጅ ይኽን ኹሉ እንዳደረገችና ሕዝቡን ለመቈንጠጥ ጥበብ ሰማያዊ መኾኑን ያስተውል ነበር፡፡
 ነቢዩ ኢዩኤል፥ ሕዝቡ የአንበጦቹን ቋንቋ አላደምጥ ሲል የድርቁን ተግሳጽ አልሰማ ሲል በምርኮ እንደሚኼድ ቢመለከትም ይኽም የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደነበረ በትንቢት አጉሊ መነጽር አይቷል፡፡ ደጋግሞ “የጨለማና የጭጋግ ቀን፣ የእግዚአብሔር ቀን” እያለ የጠራትም ይኽቺው የሕዝቡ የምርኮ ቀን ናት /፪፡፩-፫/፡፡
 ምንም እንዲኽ ቢኾንም ግን እግዚአብሔር ሕዝቡን ያለ አንዳች ተስፋ እንዳልተዋቸውም ጨምሮ ተናግሯል፤ መንፈሱን በሥጋ ለባሽ ኹሉ ላይ እንደሚያፈስና የሰው ልጆችን በሙሉ ለታላቂቱ የጌታ ቀን እንደሚያዘጋጃቸው አብሮ ተናገረ እንጂ፡፡ በዚኽም እግዚአብሔር ራሱ ረዳት እንደሚኾናቸውና ለክፉዎቹ የጨለማ ቀን እንደሚኾንባቸው ለመልካሞቹ ግን የብርሃን ቀን እንደሚኾንላቸው ተናገረ፡፡
 መጽሐፉ በአጠቃላይ እግዚአብሔር በሰው ልጆች ላይ ያለውን ዕቅድ የሚያስረዳ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን በተለያየ ቋንቋ (በአንበጦቹ፣ በድርቁ፣ በምርኮው …) ሲያናግራቸው አንዳች ነገር ከእነርሱ አልሰወረባቸውም፤ የክብሩ ተካፋይ ይኾኑ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ስንኳ ከመስጠት አልከለከላቸውም፡፡
 ይኽ መጽሐፍ መንፈስ ቅዱስ በሥጋ ለባሽ ኹሉ ላይ እንደሚፈስ የሚያስረዳ መጽሐፍ ነው፡፡ ሌሎች ነቢያት ክብር ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድንግና ተፀንሶ በድንግልና ተወልዶ የዓለምን ኃጢአት እንደሚያስወግድ ሲናገሩ ትንቢተ ኢዩኤል ግን ስለ ዓለም ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ስለሚወቅስ ስለ መንፈስ ቅዱስ አብዝቶ የሚናገር መጽሐፍ ነው /ዮሐ.፲፮፡፰/፡፡ ነቢዩ ኢዩኤል አብዝቶ የሚናገረው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ የዋጃትን ቤተ ክርስቲያን በጽድቅና በቅድስና እንድትቀጥል ስለሚያድገው አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ አብዝቶ የሚናገረው በረኻ የኾነውን የሰውን ልቡና ምድረ ገነት ወደመኾን ስለሚለውጠው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡
 ነቢዩ የአንበጣ መንጋ ዘሩን፣ ዛፉን፣ ቅጠሉን ጨርሶት እርሻውም ኹሉ ደርቆ ምድረበዳ እንደኾነ መናገሩ ኃጢአት የተባለ አንበጣ “የእግዚአብሔር እርሻ፣ ወይን፣ በለስ፣ ሮማን፣ ተምር፣ እንኮይ፣ የምድር ዛፍ” የተባለውን የሰውን ልጅ ክብሩን እንዳሳጣው ሲናገር ነው /፩፡፲፪/፡፡ የኃጢአት እሳት፥ እርሻ የተባለውን ሰው እንደበላ (እንዳቃጠለ) አስቀድሞ መናገሩ ይኽን እርሻ ዳግም ወደ ገነት የሚመልስ ሌላ እሳት (ይኸውም መንፈስ ቅዱስ ነው) እንደሚያስፈልግ ይናገር ነበር፡፡
 ሊቃውንት እንደሚናገሩት፡- “ምንም እንኳን ነቢዩ ኢዩኤል ደጋግሞ የጌታ ቀን፣ የእግዚአብሔር ቀን እያለ ቢናገርም ይኽን መቼ እንደተናገረው፣ በእርሱ ዘመን የነበሩ ነገሥታትም እነማን እንደኾኑ አለመጥቀሱ መጽሐፉ ለትውልድ ኹሉ መጻፉን የሚያመለክት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ የጌታ ቀን ብለን የምናውቃት የምጽአት ቀን መቼ እንደኾነች የሰው ልጅ በሙሉ እንዳያውቃትና ይልቁንም ዘወትር ዝግጁ ኾኖ እንዲኖር ከመሻት አንጻር ነው” ይላሉ፡፡
 ምንም እንኳን እያንዳንዱ የእግዚአብሔር ነቢይ ሕዝቡ ከኃጢአት እንዲመለስ ለማድረግ እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ሊያመጣ ያሰበውን ቁጣ ቢናገሩም በአጠቃላይ ግን የመሲሑን የማዳን ሥራ፣ የዳዊት ልጅ፣ መንፈሳዊው ንጉሥ፣ አገራትን ኹሉ ወደ አባቱ ዕቅፍ የሚያመጣውን መሲሕ በተዋሕዶ ከብሮ እንደሚመጣ በመናገር ነው፡፡ ሕዝቡ ከሚደርስባቸው ጊዜአዊ ችግር ተሸግረው ይኽን የመሲሑ ዘመን እንመለከቱ ያደረጉበት መንገድ ግን የተለያየ ነው፡፡ ኢሳይያስ፣ አሞጽና ሚክያስ ንስሐ ላይ ትኩረት ያደርጋሉ፤ ዕዝራና ነህምያ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የኢየሩሳሌምን አጥር በማነፅ እንዲመለሱ ያደርጋሉ፤ ሕዝቅኤልና ኤርምያስ ደግሞ አፍአዊ በኾነ መንገድ ሳይኾን ልቡናቸውን ለውጠው ወደ እግዚአብሔር መምጣት እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡ ነቢዩ ኢዩኤል ግን አፍአዊውን የኢየሩሳሌም ቅጥር፣ የቤተ መቅደሱን መታነፅ፣ የካህናቱን አኳኃን ቢመለከትም ስለ ውሳጣዊቷ ኢየሩሳሌም፣ ስለ ምስጢራዊው ቤተ መቅደስ፣ ስለ ልቡናም ጨምሮ ይናገራል፡፡ ነቢዩ፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ ግላዊ በኾነ እይታ እንዲመለከት አይጋብዝም፤ የቤተ ክርስቲያን ሕዋስ እንደመኾኑ “እኛ” በሚል መንፈስ ይናገራል እንጂ፡፡ በደሉን የሠሩት በአንድ ላይ እንደመኾናቸው መመለስም ያለባቸው በአንድ ላይ መኾን እንዳለባቸው ይናገራል፡፡ አንዱ አንዱን እንዲረዳ ያበረታታል፡፡
 ነቢዩ ኢዩኤል “የኦሪት ነቢይ” እየተባለ ይጠራል፤ ይኸውም ከአምስቱ የሙሴ መጻሕፍት ፳፭ ጊዜ ጠቅሶ ስለሚናገር ነው፡፡ ዳግመኛም ስለ መንፈስ ቅዱስ አብዝቶ ስለሚናገር“የጰንጤ ቆስጤ ነቢይ” ይባላል፡፡
 መጽሐፉን እንደሚከተለው መክፈል እንችላለን፡-
1.     የአንበጣ መንጋ አገሩን እንደወረረ /ምዕ. ፩/፤
2.    ጠላት መጥቶ እንደሚወራቸው /ምዕ. ፪፡፩-፳፯/፤
3.    ርደተ መንፈስ ቅዱስ /ምዕ. ፪፡፳፰-፴፪/፤
4.    ታላቂቱ የእግዚአብሔር ቀን /ምዕ. ፫/፡፡
…ተመስጦ…
  ቸርና ቅዱስ እግዚአብሔር ሆይ! ነቢዩ ኢዩኤል እንደተናገረ ኃጢአት እንደ አንበጣ መንጋ ኹለንተናችን ወረረው፡፡ የመንፈስ ፍሬ እንዳናፈራ የኃጢአት ኩብኩባ ልቡናችንን በላው፡፡ ገነት ልቡናችንንም ምድረበዳ አደረገው፡፡ የኃጢአት መንጋ መቅደስኽ ልቡናችንን አቆሸሸው፡፡ ደስታ ከእኛ ዘንድ ራቀ፡፡ የንጉሥ ልጆች ብንኾንም በገዛ ፈቃዳችን “ገብሩ ለዲያብሎስ፣ አመቱ ለዲያብሎስ” ተብለን ወደ ባርነት ኼድን፡፡ መዓዛ መለኮትኽ ከእኛ ዘንድ ራቀ፡፡ በረከትኽን አርቀን ፍርድን በላያችን ላይ ጨመርን፡፡ አንተም ከገነት እንድንወጣ አደረግከን፡፡
 ቅዱስና ርኅሩኅ አባት ሆይ! ከገነት እንድንወጣ ማድረግኽ ግን የፍቅርኽ መገለጫ ነበር፡፡ ከገነት ስታወጣን ዕድፈታችንን አስወግደኽ ዳግም ወደ ጥንተ ተፈጥሮአችን ለመመለስ ነበርና ከፍቅርኽ የተነሣ ወጣን፡፡ ወዮ! ከቁንጥቻኽ ጋር አብሮ የሚታየው ፍቅርኽ እንደምን ይረቃል? እንደምን ይመጥቃል? ከቁንጥጫኽ ጀርባ ያለው የፍቅር እጅኽን ያየ ሰውም ንዑድ ክቡር ነው፡፡
አባት ሆይ! ስንወጣም እንደወጡ ይቅሩ አላልከንም፡፡ እንደቃልኽ ፈለግከን እንጂ፡፡ እንደ ፍቅርኽ በትከሻኽ ተሸከምከን እንጂ፡፡ ፍርዳችንን ተሸክመኽ ዳግም ልጆችኽ አደረግከን እንጂ፡፡ በቈሰለው ማንነታችን፣ በመረቀዘው ልቡናችን ላይ ዘይትን አፈሰስክልን፡፡ ቅድስናችን አንተው ራስኽ ኾንከን፡፡ ይኽም ሳይበቃ ቅድስናችንን እንዳናቆሽሽ መጽንዒ መንፈስ ቅዱስን ላክልን፡፡ በረኻው ልቡናችንንም ገነት ወደ መኾን መለስክልን፡፡
እኛ ግን የተደረገልንን ረስተን የኃጢአት አንበጣ የኃጢአት ኩብኩባና ደጎብያ እየጠራን እንገኛለን፡፡ አባት ሆይ! አንተ ግን አትተወን፡፡ ቅዱስ መንፈስኽን አትውሰድብን፡፡ ከምርኮ መልሰን፡፡ ደካሞች ነንና እርዳን፡፡ መሻት እንጂ ብርታቱ የለንምና ደግፈን፡፡ ለታላቂቱ ቀን የተዘጋጀን አድርገን፡፡ አሜን!!!
ዋቢ ድርሳናት፡-
·        የትንቢተ ኢዩኤል አንድምታ፤
·        የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፤

·        A Patristic Commentary on The Book of Joel By Fr. Tadros Malaty

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount