Monday, December 2, 2013

ነገረ ነቢያት

ገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፥ ኅዳር ፳፬ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- ነቢይ ማለት አፈ እግዚአብሔር፣ መምህር፣ ሰባኪ፣ … ማለት ነው፡፡ ስያሜውም መንፈሰ ትንቢት ላደረባቸው፣ ራዕይን የማየት ጸጋ ለተሰጣቸው እውነተኛ ነቢያት ብቻ የሚሰጥ ነው፡፡
  በብዙዎቻችን አእምሮ እንደሚታሰበው “ነቢይ ማለት ስለ መፃእያት ብቻ የሚናገር ነው”፡፡ ኾኖም ነቢይ መፃእያትን ከመናገር በተጨማሪ እግዚአብሔር በየትኛውም ዘመን ለሰው ልጆች ያለውን ሐሳብና ፈቃድ በተለይ ደግሞ ከዘለዓለማዊ ድኅነት ጋር አያይዞ የሚገልጥ ነው፡፡ ለዚኽም ነው የነቢያትን መጻሕፍት ስንመለከት በውስጡ ብዙ የሕግ፣ የታሪክ፣ የጥበብና የቅኔ ይዘት እንዳለው የምናስተውለው፡፡

ቅድመ ታሪክ
  እግዚአብሔር አምላክ ለሰው ልጆች ያለችውን ሐሳቡና ፈቃዱ ምን እንደኾነች ከማስታወቅ ዝም ያለበት ጊዜ የለም፡፡ ከጥንት አንሥቶ በተለያየ መንገድ ይኽን ሐሳቡና ፈቃዱ ሲናገር ኖሯል /ዕብ.፩፡፩/፤ የዓለም ፍቅር ድንዛዜ ይዞን ባናስተውለውም አኹንም እየተናገረ ነው፤ ለወደፊትም ይናገራል፡፡ ለምሳሌ የሰው ልጆች ከማናቸውም ዓይነት ርኵሰት ይለዩ ዘንድ (እግዚአብሔር) ይሻል፡፡ “አሕዛብ የሚያደርጉትን ርኵሰት ታደርግ ዘንድ አትማር” /ዘዳ.፲፰፡፱/፤ “በያዕቆብ ላይ አስማት የለም፤ በእስራኤልም ላይ ሟርት የለም” /ዘኅ.፳፫፡፳፫/ እንዲል የሰው ልጆች ከሟርት፣ ከጥንቆላ፣ ሙታንን ከመሳብ፣ መንፈስን ከመጥራት፣ ደባል አምልኮን ከመፈጸም እንዲከለከሉ ይፈልጋል፡፡ እርሱ የሚጠቀም ኾኖ አይደለም፤ ስለ እኛ ረብሕ እንጂ፡፡ ነቢያትን በየጊዜው የመላኩ ምስጢርም ይኸው ነው፡፡ ነቢያቱ ይኽን የእግዚአብሔር ሐሳብና ፈቃድ ለሕዝቡ ይናገራሉ፡፡
 ከላይ በመግቢያው ለመግለጽ እንደሞከርነው፥ ነቢያት ስለ መፃእያት (ስለ መጪው ጊዜ) ከመናገር በተጨማሪ እግዚአብሔር በየትኛውም ዘመን ለሰው ልጆች ያለውን ሐሳብና ፈቃድ በተለይ ደግሞ ከዘለዓለማዊ ድኅነት አንጻር አሰናስለው የሚናገሩ ናቸው፡፡ በመኾኑም ከኹሉም አስቀድመን የምናገኘው ነቢይ አዳምን ነው፡፡ ምንም እንኳን በቁሙ “ነቢይ” ተብሎ ባይነገርለትም አዳም ከተሰጡት ሀብታት አንዱ ሀብተ ትንቢት ስለነበረ የመዠመሪያው ነቢይ ነው ማለት እንችላለን፡፡ ይኸውም “ይኽች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤” ባለው ቃል ይታወቃል /ዘፍ.፪፡፳፫/፡፡ ይኽ አነጋገር በምሥጢራዊው መልኩ ልክ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “ይኽ ምሥጢር ታላቅ ነው፥ እኔ ግን ይኽን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለኹ” እንዳለ በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን ስላለው አንድነት የሚናገር ነውና /ኤፌ.፭፡፴፪/፡፡ አዳም በእንቅልፍ ሳለ ሔዋን ከጐኑ እንደ ተገኘች ኹሉ፥ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ሲሞትም ቤተ ክርስቲያን ከጐኑ ከፈሰሰው ደምና ማየ ገቦ (ውኃ) ተገኘች፡፡ አዳም ከጐኑ ለተገኘች ሔዋን፡- “ይኽች አጥንት ከአጥንቴ ናት ሥጋም ከሥጋዬ ናት” እንዳለ፥ ክርስቶስም በገዛ ደሙ የዋጃትን ቤተ ክርስቲያን አካሉ ናት /፩ኛ ቆሮ.፮፡፲፭/፡፡ ከአዳም ውጪ ያሉትን ስንመለከትም በዋናነት አቤል፣ ሴት፣ ኄኖክ /ይሁዳ. ቍ. ፲፭/፣ ኖኅ /ዘፍ.፱፡፳፯/፣ ሴምና ሌሎችን እናገኛለን፡፡
 ከአብርሃም እስከ ዳዊት ያሉትን ስንመለከት ደግሞ በዋናነት ሊቀ ነቢያት ሙሴን፣ ዲቦራን፣ ነቢዩ ሳሙኤልን፣ ነቢዩ ዳዊትን፣ ነቢዩ ናታንን፣ ነቢዩ ኤልያስን፣ ነቢዩ ኤልሳዕንና ሌሎችን እናገኛለን፡፡ እነዚኽ ከአዳም አንሥተን ያየናቸው ነቢያት “ቀደምት ነቢያት” ተብለው ይጠራሉ፡፡
 ከነቢዩ ዳዊት ዠምረን እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ድረስ ባለ ጊዜ ውስጥ የምናገኛውና “የኋላ ጊዜ ነቢያት” ተብለው ከሚጠሩት ደግሞ በዋናነት የተናገሩት ትንቢት በጽሑፍ ሰፍሮላቸው የምናገኛቸው ፲፮ቱን ነቢያት እናገኛለን፡፡ እኛም (ለጊዜው) ትኩረት የምናደርገው በእነዚኽ ነቢያት ዙርያ ነው፡፡
  ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን እነዚኽን ቅዱሳን ነቢያት፥ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥” ብሎ እንደተናገረ በዚኹ ባለንበት ወርሐ ፆም (ፆመ ነቢያት) ታስባቸዋለች፡፡ በዚኽም መሠረት፡-
·        ከስብከት እስከ ብርሃን ባለ ጊዜ ውስጥ ከአዳም እስከ አብርሃም፤
·        ከብርሃን እስከ ኖላዊ ባለው ሳምንት ከአብርሃም እስከ ዳዊት፤
·        ከኖላዊ እስከ ልደት ባለው ሳምንት ውስጥ ደግሞ ከዳዊት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉ ነቢያት ይታሰባሉ፡፡
ነቢያት ለምን ይላካሉ?
  የሃገር መሪዎች፣ ካህናት፣ ምእመናን፣ … ከእግዚአብሔር መንገድ ፈቀቅ ሲሉ ነቢያት ይላካሉ፡፡ ሰው በተለያየ መንገድ ከፍኖተ እግዚአብሔር ሊወጣ ይችላል፡፡ ሥልጣንን በመሻት፣ ክብርን በመውደድ፣ የቅንጦት ኑሮን በመፈለግ፣ ወይም ደግሞ በአሳቾች ምክንያት የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ሐሳብ ሊርቅ ይችላል፡፡ ነቢያት እነዚኽ ከላይ የገለጽናቸውን አካላት ከጥፋት ወደ ልማት፣ ከስሕተት ወደ እውነት፣ ከሞት ወደ ሕይወት ለመመለስ ይላካሉ፡፡ በአጠቃላይ፡-
Ø ሰዎች ከአፍአ ሳይኾን ከልባቸው ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ለማድረግ፤
Ø የሃይማኖት አባቶችም ኾኑ የሃገር መሪዎች ሲያጠፉ ስማቸውን ለማጉደፍ ሳይኾን ስለ እውነት ሲሉ ስሕተታቸውን ለማጋለጥና በዚያውም የታመመውን ለማከም
Ø በቅርብ ጊዜ ሊፈጸሙ ያሉትን ኩነቶች ለመተንበይ፤
Ø በሩቅ ጊዜ ሊፈጸሙ ያሉትን ኩነቶች ለመተንበይ (የዚኽ ማዕከልም መሲሑ እንደሚመጣ መናገር ነው)፤
Ø ብቸኛውና ረዳት፣ አማካሪ የሌለው አዳኝ እግዚአብሔር ስለኾነ ሕዝቡ ከየትኛውም ዓይነት ደባል አምልኮ እንዲላቀቅ ነቢያት ይላካሉ፡፡
  በአንድ ሰው የሚደረደር በገና የተለያየ ዓይነት ጣዕመ ዜማ እንደሚያወጣ ኹሉ በአንዱ መንፈስ ቅዱስ መሪነት ትንቢትን የሚናገሩ ነቢያትም ትንቢታቸው በውስጡ እጅግ ብዙ ምሥጢራትን ያዘለ ነው፡፡ “የሕግ፣ የታሪክ፣ የጥበብና የቅኔ፣ … ይዘት አለው” እንዳልነው ማለት ነው፡፡  
የነቢያት አከፋፈል
  ነቢያት ዐበይትና ደቂቅ፣ የቃልና የጽሑፍ፣ እውነተኛና ሐሰተኛ፣ ወንዶችና ሴቶች በማለት መክፈል እንችላለን፡፡
·        ዐበይት ነቢያት፡- የሚባሉት መጻሕፍቶቻቸው በይዘት በዛ ስለሚሉ ነው፡፡ በዚኽም ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤልንና ዳንኤልን እናገኛለን፡፡ ደቂቀ ነቢያት፡- የሚባሉት ደግሞ መጻሕፍቶቻቸው በምስጢር ሳይኾን በይዘት አነሥ ስለሚሉ ነው፡፡ እንደውም ሊቃውንት እነዚኽን መጻሕፍት፡- “ምንም እንኳን በይዘት አነሥ ያሉ ቢኾኑም ታላላቅ ኀይልን የተመሉ ናቸው” ይልዋቸዋል፡፡ ደቂቀ (ታናናሽ) ነቢያት የሚባሉት ፲፪ ሲኾኑ እነርሱም በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ከሆሴዕ እስከ ሚልክያስ ያሉት ናቸው፡፡
·        የቃል ነቢያት፡- ማለት ምንም እንኳን በነቢይነት የተላኩ ቢኾኑም የተናገሩት ትንቢት በጽሑፍ ያልሰፈረላቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ ጋድ፣ ኤልያስ፣ ኤልሳዕንና ናታንን መግለጽ ይችላል፡፡ የጽሑፍ ነቢያት፡- ማለት ደግሞ የተናገሩት ትንቢት በጽሑፍ ሰፍሮ የምናገኝላቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ ከነቢዩ ኢሳይያስ ዠምረን እስከ ነቢዩ ሚልክያስ ያሉትን ፲፮ቱን ነቢያት መጥቀስ እንችላለን፡፡
·        ሴት ነቢያት፡- በጾታቸው ሴቶች ሲኾኑ ራዕይን የማየት ትንቢትንም የመናገር ጸጋ የተሰጣቸው ናቸው፡፡ የሴት ነቢያት ተብለው ከሚታወቁት የሙሴ እኅት ማርያም /ዘጸ.፲፭፡፪/፣ ዲቦራ /መሳፍ.፬፡፲፬/፣ ሕልዳና /፪ኛ ነገ.፳፪፡፲፭/፣ እንዲኹም ሐናን /ሉቃ.፪፡፴፮/ መግለጽ ይቻላል፡፡
·        እውነተኛ ነቢያት፡- ማለት እግዚአብሔር መርጧቸውና ልኳቸው ሕዝቡን ሊመጣ ካለው ቁጣ እንዲጠብቁ፣ እንዲሰብኩና እንዲያስተምሩ የተላኩ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር እውነተኛውን ነገር በራዕይ ገልጦላቸው ለሕዝቡ የሚያደርሱ ናቸው፡፡ ሐሰተኛ ነቢያት፡- ግን ከዚኹ በተቃራኒ እግዚአብሔር ሳይመርጣቸውና ሳይልካቸው ተመርጠናል፣ ተልከናል እያሉ ሕዝቡን የሚያውኩ ናቸው፡፡
 ሐሰተኛ ነቢያት ሐሰተኛ መኾናቸውን እንደሚከተለው ማወቅ እንችላለን፡-
ü የተናገሩት ነገር ሳይፈጸም ሲቀር /ዘዳ.፲፰፡፳/፤
ü ባዕድ አምልኮን ሲከተሉ /ዘዳ.፲፫፡፩-፲፬/፤
ü አካሔዳቸው ክፉ ሲኾን /ኤር.፳፫፡፲፮/፤
ü ኀጢአት ሲበዛ ንስሐን ሳይኾን ሰላምን የሚሰብኩ ከኾኑ /ኤር.፮፡፲፬/፤
ü ወእለ ዘተርፈ…፡፡
  አኹን ለጊዜው ትኩረት ወደምናደርግባቸውና “የኋላ ጊዜ ነቢያት” ብለን ወደጠራናቸው ፲፮ቱ ነቢያት ስንመለስ በ፭፻፹፯ ቅ.ል.ክ. የተደረገውን የይሁዳ ምርኮ ማጣቀሻ በማድረግ በሦስት መክፈል እንችላለን፡፡ ከምርኮ በፊት፣ በምርኮ ጊዜና ከምርኮ በኋላ የነበሩ በማለት፡፡
   አንባብያን የትኛው ነቢይ በየትኛው ክፍለ ጊዜ እንደነበረ፣ በኋላም የእያንዳንዱን ነቢይ ዜና መዋዕል ስናጠና በእያንዳንዱ የነቢዩ ዘመን የነበረው/ሩት የይሁዳ ንጉሥ/ነገሥታት (፪ቱን ነገድ የያዘው ደቡባዊ ክፍል)፣ የእስራኤል ንጉሥ/ነገሥታት (፲ሩን ነገድ የያዘው ሰሜናዊው ክፍል)፣ እንዲኹም ከይሁዳና ከእስራኤል ውጪ ኾነው እግዚአብሔር የበኵር ልጆቹን ለማጥፋት ሳይኾን ለመቈንጠጥ ይጠቀምባቸው የነበሩትን መንግሥታት ማመሳከር እንዲችሉ በሰንጠረዥ መልኩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ ሰንጠረዡ በቀጥታ ከ፲፱፻፺፰ቱ ዕትም “የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት” የተወሰደ ሲኾን በሰንጠረዡ “የይሁዳና የእስራኤል ነገሥታት” ተብለው የተጠቀሱትም ሰሎሞን ከሞተ በኋላ መንግሥቱ የይሁዳና የእስራኤል ተብሎ ለኹለት በመከፈሉ ነው፡፡
የይሁዳ ነገሥታት
ነቢያት
የእስራኤል ነገሥታት
ሌሎች መንግሥታት
ሮብዓም (931-913)
አኪያ (935-915)
ኢዮርብዓም ፩ኛ (931-910)
የሶርያ መንግሥት
አቢያም (913-911)

ናዳብ (910-909)
(በግብጽ ሺሻቅ)
አሳ (911-870)
ኢዩ (900)
ባኦስ (909-886)
ወልደ አዴር ፩ኛ


ኤሳ (886-885)



ዘምሪ (885)



ታምኒ (885-880)



ዘንበሪ (885-874)

ኢዮሳፍጥ (870-848)
ኤልያስ (865-853)
አክዓብ (874-853)
ወልደ አዴር ፪ኛ


አካዝያስ (853-852)

ኢዮራም (848-841)
ኤልሳዕ (852-798)
ኢዮራም (852-841)

ጎቶልያ (841-835)
አብድዩ (840)
ኢዩ (841-814)

ኢዮአስ (835-796)
ኢዩኤል (810)
ኢዮአካዝ (814-798)
አዛሄል
አሜስያስ (796-787)

ዮአስ (798-782)
ወልደ አዴር ፫ኛ
አዛርያስ (ዖዝያን) (787-740)
ዮናስ (770)
ኢዮርብዓም ፪ኛ (782-753)


አሞጽ (760)



ሆሴዕ (750)
ዘካርያ (753-752)


ኢሳይያስ (740-688)
ሰሎም (752


ሚክያስ (735-688)
ምናሄም (752-742)
ረአሶን


ፋቂስያስ (742-740)
የደማስቆ ውድቀት (732)
ኢዮአታም (740-732)

ፋቁሔ (740-732)

አካዝ (732-716)

ሆሴዕ (732-722)
የአሦር መንግሥት
ሕዝቅያስ (716-687)

722 የእስራኤል ምርኮ
ስልምናሶር፣ ሳርጎን፣ ሰናክሬም
ምናሴ (687-642)



አሞን (642-640)


(የኢትዮጵያ ቲርሐቅ)
ኢዮስያስ (640-609)
ኤርምያስ (626-585)

አሶራጾን

ሶፎንያስ (620)



ናሆም (612)

የነነዌ ውድቀት (612)
ኢዮአክስ (609)
ዕንባቆም (600)

(በግብጽ ኒካዑ)
ኢዮአቄም (609-597)


የባቢሎን መንግሥት
ዮአኪን (597)


ናቡከደነፆር
ሴዴቅያስ (597-587)
ሕዝቅኤል (592-570)

ብልጣሶር
587 የይሁዳ ምርኮ
ዳንኤል (556-538)

የባቢሎን ውድቀት
የቂሮስ አዋጅ (538)


የፋርስ መንግሥት
ዘሩባቤል (537-516)
ሐጌ፣ ዘካርያስ (520)

ዳርዮስ፣ ቂሮስ

ሚልክያስ (425)


ከነቢዩ ሚልክያስ በኋለ በእስራኤል ነቢይ ነበረን?
  የኋላ ጊዜ ነቢያትን ዜና መዋዕል በቀጥታ ከማየታችን በፊት፥ አንዳንድ ወገኖች “በእስራኤል ነቢይ ያልነበረበት ጊዜ አለ” የሚሉትን አስተምህሮ እንዴት እንደሚታይ እንመልከት፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስተምሩት፡- “እነዚኽ ወገኖች ይኽን ንግግር የሚናገሩት ከነቢዩ ሚልክያስ በኋላ የተጻፉትና በሰማንያ አሐዱ መጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ የተካተቱት የመቃብያን መጻሕፍት በመንፈሰ እግዚአብሔር አልተጻፉም በማለት ላለመቀበል የሚያደርጉት ሽሽት ነው” ይላሉ፡፡ እንደ ሊቃውንቱ አባባል፡- “ምንም እንኳን በግልጽ የተጻፈልን ነገር ባይኖርም፥ ነቢይ አልነበረም ማለት ግን አንችልም፡፡ ለዚኽም ማስረጃ የሚኾነን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- ‘ነቢያትንና ጥበበኞችን ጻፎችንም ወደ እናንተ እልካለኹ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፥ ከእነርሱም በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤ ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ኹሉ ይደርስባችሁ ዘንድ’ ያለው ቃል ነው /ማቴ.፳፫፡፴፬-፴፭/፡፡ ስለዚኽ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፡- ‘ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ’ እንዳለ የመቃብያን መጻሕፍትም በመንፈሰ እግዚአብሔር የተጻፉ ናቸው፤ ሀብተ ትንቢትም እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ጊዜ አልጠፋም። እንኳንስ በዘመነ ብሉይ በዘመነ ሐዲስም ነቢያት አሉ” በማለት የነቃፍያኑን ትችት በመንፈስ ቅዱስ በተሞረደ አንደበታቸው ይናገራሉ፡፡
ይቆየን!


3 comments:

  1. መምህራችን " በብዙዎቻችን አእምሮ እንደሚታሰበው “ነቢይ ማለት ስለ መፃእያት ብቻ የሚናገር ነው”፡፡ ላይ የተቆረጠ ሀሳብ ያለው ይመስላል ይስተካከል።

    ReplyDelete
  2. ጥሩ ግንዛቤ ይሰጣል ነገር ግን ነቢያቶች ለዚህ ዘመን ያስፈልጉታል ወይ ? ካላስፈለጉትስ ለምን ? የሚለውን ጥያቄ አይመስልም ።

    ReplyDelete
  3. ጎበዞች በርቱ

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount