መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ
ኮሌጅ የሐዲሳት መምህር
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፪ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት እንዳስተማሩትና እንደጻፉት በእናቷ በሐና በኩል ያሉ የእመቤታችን ቅድመ አያቶቿ ጴጥሪቃ ቴክታ ሲባሉ “ወኮኑ ክልኤሆሙ ጻድቃን ወፈራህያነ እግዚአብሔር ወይትአመንዎ ለአምላኮሙ በጥቡዕ ልብ እንበለ ኑፋቄ” ይላል (ኹለቱም ሰዎች ደጋጐችና እግዚአብሔርን የሚፈሩ ያለምንም መጠራጠር በፍጹም ልቡናቸው በአምላካቸው የሚተማመኑ ነበሩ)፤ እነሱም በጊዜው ይኽ ቀራችኊ የማይባሉ ባለጠጎች ነበሩ፤ ከሀብታቸው ብዛት የተነሣ ወርቁን ብሩን እንደ ዋንጫ እያሠሩ ከላሙ ከበሬው ቀንድ ይሰኩት ነበር፤ ይኽን ያኽል አቅርንተ ወርቅ፣ አቅርንተ ብሩር እየተባለ ይቈጠር ነበር የዕንቁ ጽዋ እንኳ ፸፣ ፹ ያኽል ነበራቸው፡፡
ከእለታት ባንዳቸው ጴጥሪቃ ከቤተ መዛግብቱ ገብቶ የሀብቱን ብዛት አይቶ ሚስቱ ቴክታን “ለመኑ ዘዘገብነ መዛግብቲነ አልብነ ውሉድ ዘይወርሰነ አንቲኒ ወአነሂ መካን ንሕነ” (የሰበሰብነው ገንዘብ ስንኳን ለኛ ለልጅ ልጅ ይተርፍ ነበር አንቺም እኔም መካን ነንና የሚወርሰን ልጅ የለንም) በማለት ተናገራት፤ ርሷም እንዲኽ ማለቱ ወላድ የፈለገ መስሏት በሐዘን አምላከ እስራኤል ከኔ ልጅ ባይሰጥኽ ከሌላ ይሰጥኽ ይኾናልና ሌላ አግብተኽ ውለድ አለችው፤ ርሱም “አነሂ ኢይፈቅድ የአምር አምላከ እስራኤል ከመ ኢየሐስቦ ለልብየ” (ይኽንስ እንዳላደርገው በልቤም እንዳላስበው የእስራኤል አምላክ ያውቃል) በማለት ተናገረ፡፡
ርሷም ዐዝና ሳለ ራእይ ታያለች፤ ነጭ እምቦሳ ከማሕፀኗ ስትወጣ እንቦሳዪቱ እንቦሳ እየወለደች እስከ ሰባት ስትደርስ ሰባተኛዋ ጨረቃ፤ ጨረቃ ፀሓይን ስትወልድ አይታ በአድናቆት ለባሏ “ግሩም ግብሩ ለእግዚአብሔር ትማልም ርኢኩ በሕልምየ ጸዐዳ ጣዕዋ ወጽአት እምከርሥየ ይእቲኒ ወለደት ጸዐዳ ጣዕዋ እስከ ሰብዐቲሆን ወሳብእትኒ ወለደት ወርኀ ወወርኅኒ ወለደት ፀሓየ” (የእግዚአብሔር ሥራው ድንቅ ነው፤ ትናንትና ማታ በሕልሜ ነጭ ጥጃ ከማሕፀኔ ስትወጣ ያችም ነጭ ጥጃ ደግሞ ነጭ ጥጃ ስትወልድ እንደዚኽ እየኾነ እስከ ሰባት ትውልድ ሲደርሱ ሰባተኛዪቱ ጨረቃን ስትወልድ ጨረቃዋ ደግሞ ፀሓይን ስትወልድ አየኊ) በማለት አስረዳችው፤ ርሱም በእጅጉ ተደንቆ ሕልም ከሚፈታ ሰው ዘንድ በመኼድ የሚስቱን ራእይ ነገረው፤ ያም ሕልም ተርጓሚ ምስጢር ተገልጾለት ሰባት አንስት ጥጆች መውለዳችኊ ሰባት ሴቶች ልጆች ይወለዳሉ፤ ነጭ መኾናቸው ደጋግ ልጆች መኾናቸው ሲኾን “ወሳብእትኒ ትከብር እመላእክት ወትትሌአል እምኲሉ ሰብእ ወበእንተ ፀሓይኒ ኢያእመርኩ” (ሰባተኛዪቱ ጨረቃን መውለዷ ከሰው የበለጠች ከመላእክት የከበረች ናት፤የፀሓይ ነገር ግን አልተገለጸልኝም) በማለት ተረጐመለት፤ ርሱም ለሚስቱ ነገራት፤ ርሷም የእስራኤል አምላክ የሚያደርገውን ርሱ ያውቃል በማለት ፈጣሪዋን አመሰገነች፡፡
ከዚያም ፀንሳ ሴት ልጅ ወለደች ስሟንም ሔሜን አሏት፤ ሔሜን ዴርዴን ወለደች፤ ዴርዴም ቶናን፤ ቶናም ሲካርን ወለደች፤ ሲካርም ሴትናን፤ ሴትናም ሔርሜላን ወለደች፤ ሔርሜላም የተከበረችና የተመረጠች ዓለሙን ኹሉ ለፈጠረ ጌታ አያት ለመኾን የበቃች ሐናን ወልዳለች፤ የዝማሬና የትንቢት ጸጋ ከእግዚአብሔር የተሰጡት ክቡር ዳዊት ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ክብር በተለይም ስለ ሥርወ ልደቷ፤ አምላክን ስለ መውለዷ፤ አስቀድሞ በመንፈስ ቅዱስ ተገልጾለት በመዝ ፹፮፥፩-፯ ላይ “መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን” (መሠረቶችዋ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው) በማለት የእመቤታችን ሥርወ ልደት ከቤተ መንግሥት ከቤተ ክህነት ከኾኑት ከተቀደሱት ከቅዱሱ ኢያቄምና ከቅድስቲቱ ሐና የመኾኑን ነገር በምሳሌ የገለጸው ሊፈጸም ሐና በመልካም አስተዳደግ አድጋ አካለ መጠን ስታደርስ ከነገደ ይሁዳ ከመንግሥት ወገን ኢያቄም የሚባል ደግና ጻድቅ ሰው ዐጭተው አጋቧት፡፡
ይኽነኑ የሥርወ ልደቷን ነገር በመቅድመ ተአምር ላይ ኢትዮጵያውያን የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት “ወሥርወ ልደታ ለእግዝእትነ ማርያም እምቤተ ዳዊት ንጉሥ መንገለ አቡሃ ወእምቤተ አሮን መንገለ እማ፤ ስመ አቡሃ ኢያቄም ወስመ ወላዲታ ሐና” (የእመቤታችን ማርያም ትውልዷ ባባቷ በኩል ከንጉሡ ከዳዊት ወገን ነው፤ በናቷም በኩል ከካህኑ ከአሮን ወገን ነው፤ የአባቷ ስም ኢያቄም ነው፤ የእናቷም ስመ ሐና ነው) ሲል የዘር ሐረግዋ ከቤተ መንግሥት ከቤተ ክህነት ወገን እንደኾነ አስተምረዋል፡፡
ዳዊት ብቻ ሳይኾን ቊጥሩ ከዐበይት ነቢያት መኻከል የኾነው ነቢዩ ኢሳይያስ ጥበብን በሚገልጽ ትንቢትን በሚያናግር በመንፈስ ቅዱስ እየተመራ፤ ቅድስት ድንግል ማርያም ከነገደ ዕሴይ ወገን የምትወለድ ስለመኾኗና ከርሷም ጽጌ (አበባ) የተባለ አካላዊ ቃል ክርስቶስ እንደሚወለድ ተገልጾለት በምዕ ፲፩፥፩ ላይ "ትወፅእ በትር እምሥርወ ዕሴይ ወየዐርግ ጽጌ እምኔሃ" (ከዕሴይ ሥር በትር ትወጣላች፤ አበባም ከርሷ ይወጣል) በማለት አስደናቂ ትንቢትን ተናግሮ ነበር፡፡
በምስጢር የተራቀቀና ከፍተኛ የነገረ ማርያም ዕውቀት የነበረው አባ ጊዮርጊስ ስለ ትውልዷ ኢሳይያስ የተናገረውን ትንቢት በመጽሐፈ ምስጢር ላይ ሲተረጒም "በከመ ፈቀደ ወአልቦ ዘይከልኦ ገቢረ ዘኀለየ በከመ ጽሑፍ ዘይብል ትወፅእ በትር አምሥርወ ዕሴይ ወየዐርግ ጽጌ እምጒንዱ፤ ምንት ውእቱ ፀአተ በትር እምሥርወ ዕሴይ ወየዐርግ ጽጌ እምጒንዱ፤ ምንት ውእቱ ፀአተ በትር እምሥርው ዘእንበለ ዘርዐ ሙላድ ዘቅድስት ድንግል እንተ ኮነት እምኀበ ኢያቄም ውስተ ማሕፀነ ሐና፤ እስመ ዘርዐ ዕሴይ ውእቱ ኢያቄም አቡሃ ለማርያም ወምንትኑመ ካዕበ ዕርገተ ጽጌ እምጒንድ ዘእንበለ ሥጋዌ መለኮት እምወለቱ"
(ከዕሴይ ሥር በትር ትወጣለች፤ ከግንዱም አበባ ይወጣል የሚል እንደተጻፈ፤ ያሰበውን ለማድረግ የሚከለክለው የለም፤ ከኢያቄም ተከፍላ በሐና ማሕፀን ከተፀነሰች ከቅድስት ድንግል የትውልድ ዘር በቀር የበትር ከሥሩ መውጣት ምንድን ነው? የእመቤታችን የማርያም አባቷ ኢያቄም ከዕሴይ ዘር ነውና፤ ዳግመኛም ከኢያቄም ሴት ልጁ የመለኮት ሰው መኾን በቀር የአበባ ከግንዱ መውጣት ምንድን ነው) በማለት የኢሳይያስን ትንቢት በጥልቀት ገልጾታል፡፡
ሐናና ኢያቄምንም “ወክልኤሆሙ ኄራን ወሥሙራን እሙንቱ ወየሐውሩ በሕገ እግዚአብሔር እስመ እግዚአብሔር ኀረዮሙ ወአፍቀሮሙ ትካት” ይላቸዋል እግዚአብሔርን የሚወዱ በሕጉ የሚኖሩ ደጋግና አምላክም የመረጣቸው ሲኾኑ ሐና መካን በመኾኗ ምክንያት ኹለቱም ወደ ቤተ እግዚአብሔር ዕለት ዕለት በመኼድ ለዐይናቸው ማረፊያ ለልባቸው ተስፋ የሚኾን ልጅ እንዲሰጣቸው ይማጸኑ እንደነበር፤ “Protoevangelium of James” (ፕሮቶቫንጊሊዩም ኦፍ ጀምስ) የሚለው ያዕቆብ የጻፈው ጥንታዊዉ መጽሐፍ በስፋት ይገልጻል፡፡ ከእለታት ባንድ ዕለት ሲያዝኑ ሲጸልዩ ውለው ሲመለሱ “ወርእዩ አርጋበ እንዘ ይትፌሥሑ ምስለ ውሉዶሙ” ይላል ርግቦች ከልጆቻቸው ጋር ደስ ብሏቸው ሲጫወቱ አይተው ሐና አቤቱ ጌታዬ ግዕዛን ለሌላት እንስሳ ልጅ የሰጠኽ አምላክ ምነው ለኔ ልጅ ነሣኸኝ ብላ ምርር ብላ አለቀሰች፤ ወዲያው ሱባኤ ይገባሉ፤ ኢያቄም በረሓ ኼዶ ወድቋል፤ ሐና ደግሞ ከቤቷ ዙሪያ ካለ ከተክል ቦታ ሱባኤ ያዘች፤ ኹለቱም ራእይ አይተው ተነጋግረዋል፡፡ “ይቤላ ኢያቄም ለሐና ብእሲቱ እንዘ ይትረኀዉ ሰብዐቱ ሰማያት ዖፍ ጸዐዳ መጽአ ኀቤየ ወነበረ ዲበ ርእስየ” ይላል ሰባቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ዎፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየኊ ብሎ የተገለጸለትን ለሐና ነግሯታል፤ ይኸውም የራእዩ ምስጢር፡- ዎፍ የተባለው አካላዊ ቃል ክርስቶስ ሲኾን፤ ነጭነቱ ንጽሐ ባሕርዩ ነው፤ ከላይ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየኊ ማለቱ የኢያቄምን ባሕርይ ባሕርይ እንደሚያደርግ ሲያጠይቅ ሲኾን ሰባቱ ሰማያት የተባሉ የጌታችን ምልዐቱ፣ ስፍሐቱ፣ ርቀቱ፣ ልዕልናው፣ ዕበዩ ናቸው፡፡
ሐናም ተገልጾላት “ትቤሎ ሐና ለኢያቄም ብእሴሃ አነኑ ርኢኩ በሕልምየ ርግብ ጸዐዳ መጽአት ኀቤየ ወነበረት ዲበ ርእስየ ወቦአት ውስተ እዝንየ ወኀደረት ውስተ ከርሥየ” ይላል ለባሏ ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ላይ ወርዳ በዦሮዬ ገብቶ በማሕፀኔ ስትተኛ አየኊ ብላዋለች፤ ይኽ የራእይ ምስጢር፡- ርግብ የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስትኾን፤ ነጭነቷ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ዘላለማዊ ድንግልናዋ ነው፤ ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ላይ ወርዳ በዦሮዬ ገብታ በማሕፀኔ ስትተኛ አየኊ ማለቷ ብሥራተ ገብርኤልን በዦሮዋ ሰምታ በግብረ መንፈስ ቅዱስ አምላክን የምትፀንሰውን ንጽሕት ርግብ የተባለችውን እመቤታችንን የምትወልድ መኾኗን ሲያጠይቅ ነው
ከነሱም አስቀድሞ የሳሙኤል እናት ሐና በቤተ መቅደስ ኾና “አቤቱ፥ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ የባሪያኽን መዋረድ ተመልክተኽ ብታስበኝ፥ እኔንም ባትረሳ፥ ለባሪያኽም ወንድ ልጅ ብትሰጥ፥ ዕድሜውን ኹሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለኊ፤ ምላጭም በራሱ ላይ አይደርስም” ብላ ስእለት እንደተሳለች ኹሉ (፩ሳሙ፩፥፲፩)፤ ኢያቄምና ሐናም ይኽነን ራእይ ሐምሌ ፴ ካዩ በኋላ ወንድ ልጅ ብንወልድ ወጥቶ ወርዶ ይርዳን አንልም ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ ይኾናል፤ ሴትም ብንወልድ ለቤተ እግዚአብሔር መጋረጃ ፈትላ ትኑር ብለው ስእለት ከተሳሉ በኋላ ራእይ አየን ብለው ዕለቱን አልተገናኙም፤ አዳምንና ሔዋንን “ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት” ብሎ የተናገረው አምላክ ለእኛም ይግለጽልን ብለው ዕለቱን አልጋ ምንጣፍ ለይተው እስከ ሰባት ቀን ደረስ እየብቻቸው ሰነበቱ፤ ነሐሴ በባተ በሰባተኛው ቀን ከሰው የበለጠች ከመላእክት ኹሉ የከበረች ልጅ ትወልዳላችኊ ብሎ መልአኩ ለሐና ነግሯት በፈቃደ እግዚአብሔር በብሥራተ መልአክ እመቤታችን ነሐሴ ሰባት እሑድ ተፀንሳለች፡፡
ከሊቃውንት መኻከል አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፋቸው ላይ
“ሚ ቡርክት ወቅድስት ይእቲ ሰዓተ ትፍሥሕት ሐና ዘጸገየተኪ ባቲ ወፈረየኪ ለሕይወት ኢያቄም መዋቲ እሴብሕ ተአምረኪ ርግብየ አሐቲ ወድኀኒተ ኲሉ ዓለም እስመ ኮንኪ አንቲ” (ሐና አንቺን የፀነሰችባት የደስታ ቀን ምን ያኽል የተባረከች የተቀደሰች ናት፤ ሟች ኢያቄምም ለሕይወት አንቺን ያፈራባት ቀን ምን ያኽል የተባረከች የተቀደሰች ናት፤ አንዲቱ ርግቤ ማርያም አንቺ የዓለሙ ኹሉ መድኀኒት ኾነሻልና ታምርሽን አመሰግናለኊ) በማለት ዓለምን ኹሉ በደሙ ፈሳሽነት ያዳነ ንጉሣችን፣ ፈጣሪያችን ክርስቶስን በድንቅ ተአምር ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ የወለደችልን ምክንያት ድኂን ርግበ ሰሎሞን የተባለች የቅድስት ድንግልን የመፀነሷን ነገር በአድናቆት ገልጸዋል፡፡
ታላቁ ሊቅ በተለይም ዐምስት የሚኾኑ የነገረ ማርያም መጻሕፍትን የጻፈው አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በአርጋኖን መጽሐፉ ላይ የዜና ጽንሰቷን ነገር ሲገልጽ
“ወይእዜኒ ኦ ውሉደ እግዚአብሔር ወማኅበረ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናስተብፅዖሙ ለሐና ወለኢያቄም ዘወለዱ ለነ ዛተ ቡርክተ ወቅድስተ መርዓተ፤ አይ ይእቲ ዕለት ዕለተ ሩካቤሆሙ ንጽሕት እንተ ባቲ ሐንበበት ፍሬ ቡርክተ ድንግልተ አስራኤል አጽዕልተ፤ አይ ይእቲ ዛቲ ዕለት ቅድስት ዕለተ ድማሬሆሙ ለእሉ በሥምረተ እግዚአብሔር ተገብረ ተፀንሶታ ለርግብ ንጽሕት ዘእምቤተ ይሁዳ፤ አይ ይእቲ ዕለት ዕለተ ፍሥሓ እንተ ባቲ ኮነ ተመሥርቶ ንድቅ ለማኅፈደ ንጉሥ” (አኹንም የእግዚአብሔር የጸጋ ልጆችና የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ማኅበሮች ሆይ ይኽቺን የተባረከችና የተመረጠች ሙሽራ የወለዱልንን ኢያቄምንና ሐናን እናመስግናቸው የማትነቀፍ የእስራኤል ድንግልን የተባረከችዋን ፍሬ ያፈራችበትን ንጽሕት የምትኾን የሩካቤያቸው ዕለት እንደምን ያለች ዕለት ናት? ከይሁዳ ወገን ለኾነችው ንጽሕት ርግብ መፀነስ በእግዚአብሔር ፈቃድ የተደረገ የጾታዊ ተዋሕዷቸው ቀን ይኽቺ እንዴት ያለች የተመረጠች ቀን ናት፤ ለንጉሥ ማደሪያ አዳራሽ መመሥረት የተደረገባት (የኾነባት) የደስታ ቀን እንዴት ያላት ቀን ናት?) በማለት አመስግኗታል፡፡
“ወእምድኅረ ስድስቱ አውራኅ ተዐውቀ ፅንሳ ለሐና” ይላል፤ ከስድስት ወርም በኋላ የሐና ፅንሷ እየታወቀ ሲመጣ ጎረቤቶቿ መፅነሷን ይረዱ ዘንድ በአድናቆት ማሕፀኗን ይዳስሱ ነበር፤ በተለይም ዐይኗ የታወረ የሐና ዘመዷ የአርሳባን ልጅ የምትኾን አንዲት ሴት የሐናን ማሕፀን ዳስሳ ዐይኗን ብትነካው በርቶላት በታላቅ ደስታ ኾና “ብጽአን ለኪ ኦ ሐና እስመ እም ፍጥረተ ዓለም አልቦ ዘከማኪ ዘይፌውስ በከርሡ አዕይንተ ዕውራን” (ሐና ሆይ ብጽአን ይገባሻል ዓለም ከተፈጠረ ዠምሮ እንዳንቺ በማሕፀኑ የዕውራን ዐይን የሚያበራ የለምና) በማለት አመስግናታለች፤ ከዚኽ በኋላ ዝናዋ በሀገሩ ኹሉ ተሰምቶ ሕሙማን ኹሉ ማሕፀኗን እየዳሰሱ ይፈወሱ ነበር፡፡
በመቶ ሃምሳ መዝሙረ ዳዊት ልክ መቶ ሃምሳ ክፍል ያለው የእመቤታችንን ምስጋና የጻፉት አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፋቸው ላይ ይኽነን ሲገልጹ “ጸግይየ ሣዕረ ዘኪሩቤል ልሳነ
ተአምረኪ በነጊር እመ ኢፈጸምኩ አነ ባሕቱ አአኲት ማርያም ዘጾረተኪ ማሕፀነ
እንዘ ሀለወት ፀኒሳ ኪያኪ ርጢነ ለለገሠሥዋ ባቲ ትፌውስ ዱያነ” (ሳር የኾንኊ እኔ የኪሩቤልን አንደበትን ገንዘብ አድርጌ ታምርሽን በመንገር በማስተማር ባልፈጽምም፤ ነገር ግን ማርያም የተሸከመቺሽን ማሕፀን አመሰግናለኊ፤ መድኀኒት አንቺን ፀንሳ ሳለች ርሷን የዳሰሷትን ድዉያንን ኹሉ ትፈውስ ነበር) በማለት እመ መድኅነ ዓለም ገና ሳትወለድ የተሠራውን ድንቅ ተአምር አመስግነዋል፡፡
በእጅጉ የሚደንቀው ደግሞ ሳሚናስ የሚባል የጦሊቅ ልጅ ከኤዶቅ ካጐቱ ቤት ኼዶ ሞተ፤ ሐናም በሀገራቸው ልማድ የአልጋውን ሸንኮር ይዛ እየዞረች ስታለቅስ ጥላዋ ቢያርፍበት መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ፈጥኖ ተነሥቶ “ሰላም ለኪ ኦ ሐና ወእምሔውቱ ለዘገብረ ሰማየ ወምድረ” (ሰማይና ምድርን ለፈጠረው አምላክ አያቱን የተባልሽ ሐና ሰላም ላንቺ ይኹን) አላት፤ ከዚያ የነበሩ አይሁድም በመደናገጥ ሳሚናስ ምን አየኽ? ምን ትላለኽ? አሉት፤ ርሱም ከዚች ከሐና ማሕፀን የምትወለደው ሕፃን ሰማይ ምድርን የፈጠረ አምላክን ትወልዳለች እያሉ መላእክት ኹሉ ሲያመሰግኗት ሰማኋቸው፤ እኔንም ያነሣችኝ ርሷ ናት አላቸው፤ እነርሱም ይኽን በሰሙ ጊዜ እግዚአብሔርን ከማመስገን ይልቅ በቅናትና በክፋት ተመልተው ሐና በማሕፀን ሳለ ካዳነች በኛ ላይ ልትሠለጥን አይደል “ንዑ ንገሮሙ ለሐና ወለኢያቄም” ሳትወልድ አስቀድመን ሐናና ኢያቄምን በድንጋይ ወግረን እንግደላቸው ብለው ተነሣሡባቸው፤ ያን ጊዜ ታላቁ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ለኢያቄም ተገልጾ ሐናን ሊባኖስ ወደሚባል ተራራ እንዲወስዳት ነገረው፤ ጠቢቡ ሰሎሞን በመንፈሰ እግዚአብሔር ተቃኝቶ እመቤታችን በሊባኖስ ተራራ እንደምትወለድ ተገልጾለት “ንዒ እምሊባኖስ መርዓት ንዒ እምሊባኖስ ንዒ ወተወፅኢ እምቅድመ ሃይማኖት እምርእሰ ሳኔር ወኤርሞን አምግበበ አናብስት ወእምአድባረ አናምርት” (ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ ከአማና ራስ ከሳኔር ከኤርሞን ራስ ከአንበሶች መኖሪያ ከነብሮችም ተራራ ተመልከች) በማለት የተናገረው ትንቢት ሊፈጸም ቅድስት ድንግል ማርያም በ፭ ሺሕ ፬፻፹፭ ዓመተ ዓለም በሊባኖስ ተራራ ተወልዳለች (ማሕ ፬፥፲)፡፡ ኢትዮጵያዊ ቄርሎስ የተባለው የነገረ ማርያም ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ እመቤታችን በሊባኖስ እንደምትወለድ አስቀድሞ ሰሎሞን የተናገረው ቃል መፈጸሙን ሲገልጽ “ወካዕበ እሰምየኪ ወለተ አናብስት እስመ ከመ ጣሕረ አንበሳ ወንቃወ አንበሳዊት ይደምፅ ዜና ልደትኪ እስመ ለይሁዳ ይቤሎ አቡሁ ያዕቆብ ዕጓለ አንበሳ (ዘፍ ፵፱፥፱) ፤ ወበእንተዝ ሰመይኩኪ ወለተ አናብስት በከመ ይቤ ሰሎሞን ንዒ እምሊባኖስ መርዓት ንዒ ወትወፅኢ እምግበበ አናብስት (ማሕ ፬፥፲) ጥቀ ግሩም ዜና ልደትኪ እምሕዝብ ዘይትሜካሕ ወእምነገድ ኅሩይ”
(ዳግመኛም የአንበሶች ልጅ ነሽ እልሻለኊ፤ የልደትሽ ዜና እንደ አንበሳ ጩኸት እንደ ሴት አንበሳ ድምፅ ነውና፤ ይሁዳን አባቱ ያዕቆብ የአንበሳ ግልገል ብሎታልና (ዘፍ ፵፱፥፱)፤ ስለዚኽም የአናብስት ልጅ አልኹሽ ሰሎሞን እንዲኽ ሲል እንደተናገረ ሙሽራዪት ሆይ ከሊባኖስ ተራራ ነዪ ከአንበሶች ጒድጓድ ወጥተሽ ነዪ (ማሕ ፬፥፲) ከምርጥ ነገድነት የተነሣ ከሚመካ ወገን የመወለድሽ ዜና እጅግ ግሩም ነው) በማለት አመስጥሮታል፡፡
ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ በማሕሌተ ጽጌ የነገረ ማርያም መጽሐፋቸው ላይ “ለንጉሠ ነገሥት ሰሎሞን ከመ ተፈሥሐ ልቡ በዕለተ ወፃእኪ መርዓት ለአንበሳ ትንቢት እምግቡ ማእከለ ማኅበር ፍሱሓን ተአምረኪ እንዘ እነቡ እዜምር ለኪ ጽጌ ሐና ወፍኖተ ነፈርዐጽ እሌቡ ከመ ጣዕዋ ሐሊበ ዘይጠቡ” (ትንቢት ከተነገረለት ከአንበሳ ጉድጓድ፤ ድንግል ሙሽራ በተገኘሽ ጊዜ የንጉሦች ንጉሥ የሰሎሞን ልቡ እንደተደሰተ፤ ደስ ባላቸው በመላእክት አንድነት ፊት ታምርሽን እየተናገርኊ የሐና አበባ ማርያም እዘምርሻለኊ፤ ወተትን ጠብቶ እንደሚዘል እንቦሳም ዝለል ዝለል ይለኛል) በማለት ሰሎሞን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ልደት የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቶ ታላቅ ደስታን ለኹላችን እንደሰጠን አብራርተው ገልጠዋል፡፡
ይኽ የእመቤታችን ልደት ለሰማያውያን መላእክትና ለደቂቀ አዳም ደስታ ሲኾን አካላዊ ቃል ክርስቶስ ከርሷ ተወልዶ ዲያብሎስ ፭ሺሕ፭፻ ዘመን በሲኦል ያኖራቸውን ነፍሳት ወደ ገነት የሚያስገባቸው ነውና፤ ሰይጣን በተቃራኒው ልደቷ እንዳላስደሰተው ሲገልጹ “ተፈሥሐተ ምድር ወሰማይ አንፈርዐፀ በዕለተ ጸገዩኪ አብላስ ወአውጽኡ ሠርፀ ተአምረ ሕይወት ማርያም ዘአልብኪ ቢጸ እስከ ፈርሀ መልአከ ሞት ወሰይጣን ደንገጸ ዜና ልደትኪ ነጐድጓድ እስከ (ውስተ) ሲኦል ደምፀ” (በለሶች (ኢያቄምና ሐና) ቡቃያ አንቺን ባስገኙሽ ጊዜ ምድር ደስ አላት ሰማይም ደስ አለው፤ ጓደኛ (ምሳሌ) የሌለሽ የድኅነት ምልክት ማርያም፤ መልአከ ሞት እስከ ፈራና ሰይጣንም እስከ ደነገጠ ድረስ የመወለድሽ ዜና እስከ ሲኦል ድረስ (በሲኦል) ተሰማ) በማለት አስተምረዋል፡፡
ጠቢቡ ሰሎሞን አስቀድሞ በመንፈሰ እግዚአብሔር ተቃኝቶ በማሕልዩ ላይ “መኑ ይእቲ ዛቲ እንተ ትሔውጽ ከመ ጎሕ ሠናይት ከመ ወርኅ ወብርህት ከመ ፀሓይ” (ይኽቺ እንደ ማለዳ ብርሃን የምትጐበኝ እንደ ጨረቃ የተዋበች፤ እንደ ፀሓይም የጠራች ዐላማ ይዞ እንደተሰለፈ ሰራዊት የምታስፈራ ማን ናት?) በማለት እንደ ፀሓይ የሞቀ እንደ ጨረቃ የደመቀ ንጽሕናዋና ቅድስናዋ የመልኳ ደም ግባት በነቢያት ትንቢት አስቀድሞ የተጐበኘላት የእውነት ፀሓይ የክርስቶስ እናት የቅድስት ድንግል ማርያምን ክብርና ደም ግባቷን እንደተናገረ በሊባኖስ ተራራ በግንቦት ፩ በተወለደች ጊዜ ፊቷ እንደ ፀሓይ ያበራ ነበር፤ መዐዛዋም ከሽቱ ኹሉ ይበልጥ ነበር፡፡
የመዐዛዋን ድንቅነት ይኸው አባት ሰሎሞን መንፈስ ቅዱስ ገልጾለት ይኽነንም በተለያዩ ድንቅ መዐዛ ባላቸው ሽቱዎች መስሎ ሲናገር (ቡቃያሽ ሮማንና የተመረጠ ፍሬ ቆዕ ከናርዶስ ጋር ያለበት ገነት ነው፤ ናርዶስ ከቀጋ ጋር የሽቱ ሣርና ቀረፋ ከልዩ ልዩ ዕጣን ጋር፤ ከርቤና እሬት ከክቡር ሽቱ ኹሉ ጋር አንቺ የገነት ምንጭ የሕይወት ውሃ ጒድጓድ ከሊባኖስም የሚፈስስ ወንዝ ነሽ) በማለት የሕይወት ውሃ የክርስቶስ እናቱ በሊባኖስ የተወለደቺው የቅድስት ድንግል ማርያምን ልዩና ድንቅ መዐዛ ተናግሯል፡፡
ኢትዮጵያዊዉ ሊቅ ቅዱስ ያሬድም የመዐዛዋን አስደናቂነት በሰሎሞንን ቃል በአንቀጸ ብርሃን መጽሐፉ ላይ ሲገልጸው (አባትሽ ሰሎሞን ያፍንጫሽ መዐዛ እንደ ነጭ ዕጣን መዐዛ ነው ብሎ ትንቢት ተናገረ፤ እቴ ሙሽራዬ ሆይ የታጠርሽ ተክል ነሽ፤ መንገድሽም የታጠረች ተክል የታተመች ጒድጓድ ናት፤ ከሽቱ ቅመም ጋራ ሽቱ አለሽ፤ ቆዕ የሚባል ሽቱ ናርዶስ ከሚባል ሽቱ ጋር አለሽ፤ ናርዶስ የሚባል ሽቱ መጽርይ ከሚባል ሽቱ ጋር አለሽ፤ ቀጺመታት ቀናንሞስ የሚባሉ ሽቶች ከደጋ ሽቶች ጋር አሉሽ፤ ከሽቶች ኹሉ የሚበልጡ ከርቤና ዐልው የሚባሉ ሽቶች ከነዚኽ ኹሉ ሽቶች ጋር አሉሽ፤ የገነት ፈሳሽ ሆይ ከደጋ የሚፈስስ የሕይወት ውሃ ጉድጓድ ነሽ) በማለት የመዐዛዋን ነገር አድንቋል፡፡
የእመቤታችን ጣዕመ ውዳሴዋ በእጅጉ የበዛለት ሊቁ አባ ጊዮርጊስም በአርጋኖን ምስጋናው ከሰሎሞን ቃል በመነሣት የመዐዛዋን ነገር ሲያደንቅ
“ወእወዲ ውስተ አፉየ እምፍሬ ከርሥኪ ጥዑም ለጉርዔየ ደመ አስካልኪ ወመድምም ለአንፍየ መዐዛ ዕፍረትኪ ከመ ዘሰትየ ወይነ ከራሜ ያስተፌሥሖ ለልብየ ስብሐተ ድንግልናኪ ሚመጠን ፍሥሓየ በእንቲኣኪ ወሚመጠን ሐሤትየ በእንተ ክብርኪ አዳም ንባብኪ ወመዓርዒር ቃልኪ ሙሐዘ ፍሥሐ ከናፍርኪ ወሙሒዘ ስብሐት ልሳንኪ ጥቀ ሠነይኪ ወጥቀ አደምኪ አፈቅሮ ለፍግዕኪ ዘቆምኪ ይመስል በቀልተ ወጼና አልባስኪ ከመ ርሔ አፈው ወጼና አንፍኪ ከመ ጼና ወይን (ማሕ ፯፥፯-፰) ወመክሥተ አፉኪ ምዑዝ ከመ ጼና ጽጌ ቀናንሞስ ዘምስለ ኲሉ ዕፀወ ሊባኖስ” (ከማሕፀንሽም ፍሬ ወደ አፌ እጨምራለኊ፤ የፍሬሽ ደምም ለጉሮሮዬ የጣፈጠ ነው፤ የሽቱሽ መዐዛም ለአፍንጫዬ ያማረ ነው፤ የድንግልናሽ ክብርም ልቡናዬን እንደ ከረመ ንጹሕ ወይን ደስ ያሰኘዋል፤ ስለ አንቺ ያለኝ ደስታ ምን ያኽል ነው፤ አነጋገርሽ ያማረ ነው፤ ቃልሽም የጣፈጠ ነው፤ ከንፈሮችሽም የደስታ ምንጭ ናቸው፤ አንደበትሽም የምስጋና መፍለቂያ ነው፤ እጅግ በጣም አማርሽ ቁመትሽ የሰሌን ዛፍ፤ የልብሶችሽ መዐዛም አፈው በመባል እንደሚታወቀው ሽቱ፤ የአፍንጫሽ መዐዛም እንደ ወይን አበባ ሽታ የሚኾንልሽ ድንግል ሆይ ደስታሽን እወደዋለኊ (ማሕ ፯፥፰) የአፍሽም አከፋፈት እንደ ቀናንሞስ አበባ የጣፈጠ ነው፤ ከሊባኖስ ዕንጨቶች ኹሉ ጋር (ማሕ ፬፥፲፬)) በማለት እንደ ሰሎሞን ርሱም የፈጣሪውን እናት አመስግኗል፡፡ሐናና ኢያቄምም በእጅጉ ተደስተው በተወለደች በ፰ ቀኗ ስሟን ማርያም ብለው ሰየሟት፡፡
No comments:
Post a Comment