(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፲፯ ቀን፣
፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ
አሐዱ አምላክ አሜን!!!
“ናሆም” ማለት “መጽናናት” ማለት ነው፡፡ ብዙዎቹ ነቢያት የተላኩት መንፈሳዊነት
በቀዘቀዘበት ወራት ነው፡፡ የሕዝቡ ኃጢአት ጽዋው ሞልቶ ነበር፡፡ የነቢያቱ መምጣት ዋና ዓላማም ሕዝቡ ከዚኽ ኃጢአት ለመመለስና
ካልተመለሰ ግን እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ሊያመጣ ያለውን ፍርድ ለማስታወቅ ነው፡፡ ጨምረዉም ግን “አጽናኑ ሕዝቤን አጽናኑ” ተብሎ
እንደተጻፈ /ኢሳ.፵፡፩/ ለሕዝቡ ተስፋ ድኅነትን ይሰጡ ነበር፡፡ ናሆምም ይኽን የነቢያት ተልእኮ የሚያሳይ ስም ነው፡፡ ምክንያቱም
በመጽሐፉ ምንም እንኳን ሕዝቡ ለመጥፋት ሳይኾን ለቁንጥጫ ወደ ምርኮ እንደሚኼዱ ፈቃደ እግዚአብሔር ቢኾንም እግዚአብሔር ራሱ ጠላቶቻቸውን
አጥፍቶ እንደሚያድናቸውም ጨምሮ ተናግሯል፡፡ “ለደም ከተማ ወዮላት!” /፫፡፩/፤ “እነሆ የምስራችን የሚያመጣ ሰላምንም የሚያወራ
ሰው እግር በተራሮች ላይ ነው” በማለት የገለጻቸው ቃላት ይኽን የሚያስረዱ ናቸው፡፡
ከመጽሐፉ
ማንበብ እንደምንችል ናሆም ኤልቆሻዊ ነው /፩፡፩/፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚናገሩት ኤልቆሻ በኋላ ላይ ቅፍርናሆም ተብላለች፡፡
ስለዚኽ ነቢዩ ናሆም የገሊላ ሰው ነው ማለት ነው፡፡ የነበረበት ዘመንም በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት እንደኾነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡
ብዙዎች
ነቢያት አስቀድመው እስራኤላውያን ማለትም ዐሥሩ ነገድ በአሦራውያን፣ ኹለቱ ነገድም በባቢሎናውያን እንደሚማረኩ ተንብየዋል፡፡ ነቢዩ
ናሆም ግን የተነበየው የነነዌ ማለትም የአሦራውያንን ውድቀት ነው፡፡ ይኽ ደግሞ ለዐሥሩ ነገድ ትልቅ መጽናናትን የሚሰጥ ቃል ነው፡፡
ትንቢተ ናሆም
ከ፻፶ ዓመታት
በፊት እግዚአብሔር ነቢዩ ዮናስን ልኮላቸው ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ የነበረው ትውልድም ከጥፋት ድኗል፡፡ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ማቅ ለብሶ
ንስሐ ገብቷል፡፡ እግዚአብሔርም ይቅር ብሏቸው ነበር /ዮና. ፫/፡፡ ትንሽ ቆይተው ግን ሃይማኖታቸውን ትቷል፡፡ ወደ ቀድሞ ግብራቸው
ተመልሰዋል፡፡ እንደዉም ከቀድሞ ይልቅ ብሶባቸዋል፡፡ ከተማቸውም “የደም ከተማ” እስከመባል ደርሳለች /ናሆ.፫፡፩/፡፡
የነነዌ
ሰዎች እንዲኽ ወደ ትፋታቸው ሲመለሱ ግን እግዚአብሔር እንደ ቀድሞ ነቢይ አልላከላቸውም፡፡ ስለ ጥፋታቸው የሚናገር ትንቢት አስነገረባቸው
እንጂ፡፡ ይኸውም በነቢዩ ኤርምያስ አንደበት፡- “ስለ ሕዝብም ስለ መንግሥትም እሠራውና እተክለው ዘንድ በተናገርኹ ጊዜ በፊቴ ክፉን
ነገር ቢያደርግ ቃሌንም ባይሰማ እኔ አደርግለት ዘንድ ስለተናገርኹት መልካም ነገር እጸጸታለኹ” ብሎ እንደተናገረው ነው /ኤር.፲፰፡፱-፲/፡፡
በዚኹ በትንቢተ ናሆም ላይ የነነዌን (የአሦርን) ውድቀት የሚናገረውም ስለዚኹ ነው፡፡ ከዚኽም በተጨማሪ በግብጽ ስለነበረው ትዕቢተኛው
ኖእ አሞን ውድቀት ተናግሯል /፫፡፰/፡፡
በአጠቃላይ የትንቢተ ናሆም ዋና ዓላማ ስለ እስራኤል መጽናናትና ኹሉን
ቻይ ስለኾነው እግዚአብሔር መግለጽ ነው፡፡ መጽሐፉን እንደሚከተለው መክፈል እንችላለን፡-
1.
እግዚአብሔር የፍርድና የበቀል አምላክ እንደኾነ /ምዕ.፩/፤
2.
የነነዌ ጥፋት /ምዕ.፪/፤
3.
ለነነዌ ጥፋት ምክንያቱ ምን እንደኾነ /ምዕ.፫/፡፡ ከመጽሐፉ ማንበብ እንደምንችለው ነነዌ የወደቀችው በደም አፍሳሽነቷ፣ ሐሰትና ቅሚያ ስለሞላባት፣ ንጥቅያ
ከእርሷ ስለማያልቅ፣ ስለ ግልሙትናዋና ስለ መተታምነቷ ነው /፫፡፩-፬/፡፡
ከትንቢተ
ናሆም ምን እንማራለን?
v ነነዌ በነቢዩ ዮናስ ስብከት ንስሐ
ገብታ ነበር፤ እግዚአብሔርም ይቅር ብሏት ነበር፡፡ ነገር ግን ደግማ በደለች፡፡ ዳግመኛ በንስሐ መመለስም አልወደደችም፡፡ በመኾኑም
ጠፋች፡፡ የእግዚአብሔር ምሕረትና ቸርነት ከቋንቋ በላይ ስለኾነ ከኃጢአታችን እንድንመለስ በተለያየ መንገድ ይጠራናል፡፡ በተለያየ
መንገድ ይገሥፀናል፡፡ አልመለስ ካልን ግን ቅዱስ እንደመኾኑ ከኃጢአት ጋር ኅብረት የለውም፤ እኛም የዘራነውን እናጭዳለን፡፡
v የፈለገ ያኽል ሥልጣን ይኑረን፣
የፈለገ ያኽል ብርታት ይኑረን፣ የፈለገ ያኽል ሀብት ይኑረን ከታበይንበት እንደ ነነዌ ነገሥታት መጨረሻችን መዋረድ ብቻ ነው፡፡
ከፈቃደ እግዚአብሔር ውጪ የኾነ ማንኛውም እንቅስቃሴአችን አንድ ቀን ጠላልፎ ይጥለናል፡፡
v አሦራውያን በእስራኤል ላይ እንዲሠለጥኑ
የኾነው ሕዝቡን እንዲገርፉና እንዲያሰቃዩ አልነበረም፡፡ እነርሱ ግን በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ግፍን ፈጸሙ፡፡ በእስራኤል ላይ የሠለጠኑት
እግዚአብሔር ፈቅዶላቸው ሳይኾን በራሳቸው ብርታት ይኽን እንዳደረጉ አሰቡ፡፡ በመኾኑም የሚመኩበት መንግሥታቸው እንዳልኾነ ኾኖ ወድቆ
ቀረ፡፡ ምእመናንን ማሳደድና በእነርሱ ላይ ግፍን መፈጸምም ክርስቶስን ማሳደድ ነው፤ በክርስቶስ ላይ ግፍ እንደ መፈጸም ነው፡፡
ክርስቶስን ማሳደድና በክርስቶስ ላይ ግፍ መፈጸም ማለት ደግሞ ሕይወትን ማሳደድ ነው፤ ደስታን ማራቅ ነው፤ ክብርን ማዋረድ ነው፤
ራስን በራስ እንደ መግደል ነው፡፡ የአሦር መንግሥት ውድቀት ይኽን ያስረዳል፡፡
v በበደልን ጊዜ እግዚአብሔር እኛን
የሚገሥፅበት መንገድ ያውቅበታል፡፡ እነ አሦር በእኛ ላይ እንዲሠለጥኑ ያደርጋል፡፡ በንስሐ ስንመለስና ቁንጥጫችንን ስንጨርስ ግን
ከአሦራውያን እጅ በአስደናቂ ማዳን ያድነናል፡፡ እግዚአብሔር እኛን ለማዳን እጁን ሲዘረጋም “ክንድኽን እጠፍ” ሊለው የሚችል ጦር
የለም፡፡
…ተመስጦ…
ቸር ወዳጅ ሆይ! ፍቅርኽ ከመነገር በላይ ነው፡፡ ቸርነትኽ ከቃላት በላይ ነው፡፡
ኃጢአት ከቅድስናኽ ጋር ስለማይስማማ ትቈጥጠናለኽ፡፡ ቁንጥጫኽ ደግሞ ግሩም ነው፡፡ መግደያ ሳይኾን መድኃኒት ነውና፡፡ አባት ሆይ!
ስለዚኸ እናመሰግንኻለን፡፡ ባትቈነጥጠን ልጆች ሳንኾን ዲቃሎች ነንና ስለዚኽ እናመሰግንኻለን፡፡ ቅዱስ እግዚአብሔር ሆይ! የነነዌን
መንግሥት ከማንነታችን ጣልልን፡፡ ደም አፍሳሽነትንና ንጥቅያን፣፣ ሐሰትንና ቅሚያን፣ ግልሙትናንና መተታምነትን፣ እንዲኹም ትዕቢትን
ከልቡናችን ንቀልልን፡፡ እንደ እኛ በደል ሳይኾን እንደ ቸርነትኽ መጠን ይኽን ኹሉ ከእኛ አርቀኽም የቅድስና መንግሥትኽን በኹለንተናችን
ላይ አንግሥልን፡፡ አሜን!!!
No comments:
Post a Comment