Friday, December 6, 2013

“መምህር ሆይ! አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነኽ” /ዮሐ.፩፡፶/

በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፥ ኅዳር ፳፯ ቀን፥ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የምታውቅ ነፍስ ሐሴት ታደርጋለች፡፡ ክርስቶስን፡- “አንተ መምህረ እስራኤል ነኽ፤ አንተ ንጉሠ ሰማይ ወምድር ነኽ” ትሏለች፡፡ ይኸውም እንደ ፊሊጶስ ማለት ነው /ዮሐ.፩፡፶/፡፡ ይኽቺ ነፍስ ሐሴትን የምታደርገው ግን በነቢብ ብቻ አይደለም፤ በገቢርም ጭምር እንጂ፡፡ ተወዳጆች ሆይ! ክርስቶስን ታውቁታላችሁን? እንኪያስ ትእዛዛቱን ጠብቁ፡፡ ክርስቶስን የሚያሳዝን ገቢር እየፈጸምን እንደምን ደስ የሚያሰኘውን ነገር ማድረግ ይቻለናል?


 አንድ እንግዳ ወደ ቤታችን ሲመጣ ቤታችንን እንደምን እንደምናሰናዳው ኹላችንም እናውቀዋለን፡፡ ኹላችንም እንግዳችንን ደስ የሚያሰኘው ነገር ለማድረግ የምንቻኰል አይደለንምን? ለእንግዳችን የኾነ ነገር ባናደርግለት፥ እንግዳችን በመምጣቱ ደስ ተሰኝተን እርሱን ደስ የሚያሰኝ ነገር ባናደርግለት፥ ግን ደግሞ በመምጣቱ ደስ እንደተሰኘን ብንነግረው እንግዳችን በፍጹም አያምነንም፡፡ በእንግዳችን መምጣት ደስ እንደተሰኘን ከቃላት ባለፈ በገቢር መግለጥ አለብንና፡፡ እንኪያስ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሕይወታችን ከመጣ ደስ መሰኘታችንን በገቢር ልንገልጽ ያስፈልጋል፡፡ እንግዳችን ክርስቶስን የሚያስቈጣ ነገር ልንፈጽም አይገባንም፡፡

  እንግዳ ሲመጣ ቆሻሻ ልብስ አይለበስም፡፡ እንግዳ ሲመጣ የሚያስጸይፍ ነገር አይነገርም፡፡ ክርስቶስ በሕይወታችን ውስጥ እንዲኖር ስንፈልግም ቆሻሻ ልብሳችንን (ማንነታችንን) አውልቀን ልንጥል ያስፈልጋል፤ አስጸያፊ ነገራችንን ልንተው ያስፈልጋል፡፡ እንግዳ ሲመጣ ቤት ያፈራው ኹሉ ይቀርብለታል፡፡ ክርስቶስ ወደ ቤታችን ሲመጣም የሚበላ ነገር ልናቀርብለት ይገባል፡፡ ለመኾኑ የክርስቶስ መብል ምንድነው? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይኽን ጥያቄ ሲመልስልን እንዲኽ ብሏል፡- “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” /ዮሐ.፬፡፴፬/፡፡ እንኪያስ ክርስቶስ የራበው ይኸው ነውና እንመግበው፤ ኢየሱስ የጠማው ይኸው ነውና እናጠጣው፡፡ እርሱም ይቀበለናል፡፡ አንዲት ኩባያ ቀዝቃዛ ውኃ ብንሰጠው እንኳ ይቀበለናል፡፡ ስለብዛቱ ሳይኾን ስለፍቅሩ ብሎ ይቀበለናል፡፡ እኛን ስለመውደዱ ይቀበለናል፡፡ የምንወደው ሰው የሰጠነውን የሚቀበለን ስለ መጠኑ አይደለም፤ ስጦታው የወዳጅ ስለኾነበት እንጂ፡፡ ሰው ወዳጁ ጌታም ኹለት ሳንቲም ብንሰጥ እንኳ ብዙ እንደሰጠን አድርጐ ይቀበለናል፡፡

 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስጦታችንን የሚቀበለው ድኻ ስለኾነ አይደለም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የድኻውም የባለጸጋውም ስጦታ እኩል የሚቀበለው ስለ ልቡናችን ኀልዮት (Intention) እንጂ ስለ ስጦታው ትልቅነት ወይም ዋጋ አይደለም፡፡ ስለዚኽ ክርስቶስን እንደምንወደው ለመግለጽ የግድ ብዙ ወይም በውድ ዋጋ የተገዛን ስጦታ መስጠት አያስፈልገንም፡፡ ስጦታችን እርሱ ወደ እኛ ስለመጣ ደስ የመሰኘታችን መግለጫ ነውና ስለ ስጦታችን መጠን ልንመለከት አይገባም፡፡

 ተወዳጆች ሆይ! ክርስቶስ ስለ እኛ ብሎ እስከምን ድረስ እንደመጣ ለብዉ (አስተውሉ)፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ብሎ አርአያ ገብርን ነሥቶ መጥቷል፤ ስለ እኛ ብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቷል፤ ከዚኽ ኹሉ በኋላ እንኳን ሊቀ ካህናችን ነውና እኛን መንከባከቡ አላቋረጠም፡፡
 
  ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖስ ሲመክር፡- “እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን” ብሏል /፪ኛ ቆሮ.፭፡፳/፡፡ ከእናንተ መካከል፡- “አባታችን! ክርስቶስን የሚጠላ ማን አለ?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ ልጆቼ! እርግጥ ነው በቃል ወይም በኀልዮት ደረጃ ኹላችንም ክርስቶስን እንወደዋለን፡፡ ፍቅር የሚገለጠው ግን በቃል ብቻ አይደለም፤ በገቢርም ጭምር እንጂ፡፡ እልፍ ጊዜ እንደምናፈቅር ብንናገር፥ ግን ደግሞ የማናፈቅር ከኾነ ከማንም ይልቅ ምስኪኖች ነን፡፡ በእግዚአብሔርስ ፊት ይቅርና በሰው ፊትም ሞገስ የለንም፡፡ እግዚአብሔርን እንደምናምን በቃል ብንናገር፤ ነገር ግን በገቢር ብንክደው የማይጠቅም ብቻ አይደለም፤ ጉዳትም አለው፡፡ እንኪያስ ተወዳጆች ሆይ! እግዚአብሔርን ማመናችን በቃልም በገቢርም ይኾን ዘንድ እማልዳችኋለኹ፡፡ ክርስቶስን በዚኽ ሰዓት ካልካድነው እርሱም በመጨረሻይቱ ቀን አይክደንምና፡፡ በዚኹ ሰዓት በቃልም በገቢርም በሰው ፊት ብንመሰክርለት እርሱም በመጨረሻይቱ ቀን በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይመሰክርልናል /ሉቃ.፲፪፡፰-፱/፡፡ ይኽን እንድናደርግ በቸርነቱም ርስቱን መንግሥቱን እንዲያወርሰን ሰውን በመውደዱ ሰው የኾነው ኢየሱስ ክርስቶስ ይርዳን አሜን!!!


© ከ “Homily XX on the Gospel of John, p.129-130” የተተረጐመ፡፡        

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount