Tuesday, December 17, 2013

ነቢዩ አሞጽ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፱ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
“አሞጽ” ማለት “ሽክም፣ ጭነት” ማለት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ በዚኽ ስም የሚጠሩ ሦስት ሰዎች ያሉ ሲኾን እነርሱም የነቢዩ ኢሳይያስ አባት /ኢሳ.፩፡፩/፣ የምናሴ ልጅ ንጉሥ አሞጽ /፪ኛ ነገ.፳፩፡፲፰/ እንዲኹም ለዛሬ የምናየውና ከደቂቀ ነቢያት አንዱ የኾነው ነቢዩ አሞጽ ናቸው፡፡
 የቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት እንደሚያስረዳው የነቢዩ አሞጽ አባት ቴና ሲባል እናቱ ደግሞ ሜስታ ትባላለች፡፡ ነገዱም ከነገደ ስምዖን ወገን ነው፡፡

 ነቢዩ አሞጽ ከመጠራቱ በፊት የላም ጠባቂና የወርካ ለቃሚ ነበር፡፡ ነቢይ ወይም የነቢይ ልጅም አልነበረም፤ እግዚአብሔር በጐችን ከመከተል ጠራው እንጂ /አሞ.፯፡፲፬-፲፭/፡፡ ምንም እንኳን ከግብርና የመጣ ቢኾንም ንግግር የማይችል፣ ያልተማረ፣ ድፍረት የሌለው ነቢይ አልነበረም፡፡
 ነቢዩ አሞጽ ምንም እንኳን ከደቡባዊው መንግሥት ቢኾንም እንዲያስተምር የተላከው ለሰሜናዊው ክፍልም ጭምር ነበር፡፡
 በራሱ መጽሐፍ እንደነገረን በዘመኑ የነበረው የይሁዳ ንጉሥ ዖዝያን ሲኾን በእስራኤል የነበረው ንጉሥ ደግሞ ዳግማዊ ኢዮርብዓም ይባላል /አሞ.፩፡፩/፡፡ በነቢይነት ያገለገለውም ከ፯፻፹፯-፯፴፭ ቅ.ል.ክ. ላይ ነው፡፡
በነቢዩ አሞጽ ዙርያ የነበረው ነባራዊ ኹኔታ
 ነቢዩ አሞጽ በሚያገለግልበት ወራት የይሁዳና የእስራኤል ኃጢአት ጣራ የነካበት ጊዜ ነበር፡፡ ከእኛ ዘመን ጋርም በእጅጉ ይመሳሰላል፡፡ አንባቢያን ይኽን ቀጥሎ ከተጠቀሰው ጋር ማነጻጸር ይችላሉ፡፡ ምንም እንኳን በአንጻራዊ መልኩ ነቢዩ አሞጽ በነበረበት ወራት ሰላም የነገሠበት ቢኾንም ሕዝቡ ግን የእግዚአብሔር ሕግ ጥሏል፤ ትእዛዙን አይጠብቅም፡፡ ባለጸጐች የሚባሉት በሀብት ላይ ሀብት ጨምረው የሚኖሩ ቢኾኑም ድኾቹ ግን ከዕለት ወደ ዕለት ከድጡ ወደ ማጡ የሚኼዱ ነበሩ፡፡ ጻድቁን ስለ ብር፣ ችግረኛውን ስለ አንድ ጥንድ ጫማ የሸጡበት ጊዜ ነበር፡፡ የድኾችን ራስ በምድር ትቢያ ላይ ይረገጣል፤ የትሑታን መንገድ ይጣመማል፡፡ ቅዱሱን የእግዚአብሔር መንገድ ያረክሳሉ፡፡ አባትና ልጅ ለዝሙት ግብር ወደ አንዲት ሴት ይገባሉ፡፡ ጻድቁ በጽድቅ መንገድ ልኺድ ቢል ከእነርሱ ጋር ስላልተስማማ ያስጨንቁታል፡፡ እውነትን የሚናገር ሰው አምርረው ይጸየፉታል፡፡ እግዚአብሔር  ነቢያቱን እየላከ ሐሳቡና ፈቃዱ ምን እንደኾነ ደጋግሞ ቢነግራቸውም አይመለሱም፡፡ ቅን ነገርን ማድረግ አያውቁም፡፡ ችጋረኛውን ይውጡታል፡፡ የአገሩን ድኻ ያጠፋሉ፡፡ ሚዛኑን አሳንሰው በሐሰት ይሸጣሉ፡፡ ንጹሕ እኽል ሳይኾን ግርዱን ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ ድኻውን ይደበድቡታል፤ ይበድሉታል፤ ፍርድ ያጣምሙበታል፤ ያስጨንቁታል፤ ጉቦ ይቀበሉታል፡፡ በዚያም ላይ ቀረጥን ያበዙበታል፡፡ ለራሳቸው ግን ከተጠረበ ድንጋይ ቤቶችን ይሠራሉ፡፡ ያማሩ የወይን ቦታዎችን ይተክላሉ፡፡ ግፍንና ቅሚያን በአዳራሾቻቸው ያከማቻሉ፡፡ ከዝሆን ጥርስ በተሠራ አልጋ ላይ ይተኛሉ፡፡ በምንጣፋቸው ላይ ተደላድለው ይቀመጣሉ፡፡ አምጡ እንብላ እንጠጣ ይላሉ፡፡ ከበጐች መንጋ ጠቦቱን ከጋጥም ውስጥ ጥጃን ይበላሉ፡፡ በመሰንቆ ድምፅ ይንጫጫሉ (ይዘፍናሉ)፡፡ በዚያ ዘመን የነበሩ ካህናትና ነቢያት ለገንዘብ የሚሠሩ ነበሩ፡፡
 በቅርብ ጊዜ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው በአኹኑ ሰዓት የዓለማችን ሰማንያ ከመቶ ሃብትና ንብረት በሃያ ፐርሰንት ግለሰቦች ብቻ የተያዘ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ በዓለማችን ፍትሐዊ የኾነ የሃብት ክፍፍል የለም ማለት ነው፡፡ በአገራችን ያለውን ነባራዊ ኹኔታ ስናየውም ቢብስ እንጂ ከዚኹ አይሻልም፡፡ ነቢዩ አሞጽ በሚያገለግልበት ወራት የነበረው ኹናቴ ከአኹኑ ኹኔታ ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል ያልነውም ከዚኽ ተነሥተን ነው፡፡
 በሌላ መልኩ በመጽሐፈ ነገሥት ካልዕ ምዕራፍ ፲፬ ከቁጥር ፳፫ እስከ ፍጻሜ ያለውን ኃይለ ቃል ስናነብ ኢዮርብዓም ወደ አምልኮ ጣዖት ማዘንበሉን እናነባለን፡፡
 በሕዝቡ ዘንድ የነበረው የእምነትና የጸሎት ኹኔታ በእጅጉ የወደቀ ነበር፡፡ ምንም እንኳን በዓላትን እንዲያከብሩ፣ የተቀደሰ ጉባዔ እንዲያደርጉ፣ የሚቃጠለውን መሥዋዕት እንዲኹም የእኽል የቊርባን እንዲያቀርቡ፣ በመሰንቆ እንዲያመሰገኑ የነገራቸውና ያዘዛቸው እግዚአብሔር ራሱ ቢኾንም ነቢዩ ሆሴዕ፡- “ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን ከሚቃጠለውም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እወዳለኹ” እንዳለ /ሆሴ.፮፡፮/ ግብራቸው እጅግ የከፋ ስለኾነ ይኽን ቢያቀርቡለትም አልተቀበላቸውም፡፡ “ዓመት በዓላችኹን ጠልቼዋለኹ፤ ተጸይፌውማለኹ፤ የተቀደሰውን ጉባዔአችሁ ደስ አያሰኘኝም፡፡ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችኹ የእኽሉን ቊርባናችሁን ብታቀርቡልኝም እንኳ አልቀበለውም፤ ለምስጋና መሥዋዕት የምታቀርቡልኝን የሰቡትን እንስሶች አልመለከትም፡፡ የዝማሬኽንም ጩኸት ከእኔ ዘንድ አርቅ፤ የመሰንቆኽንም ዜማ አላደምጥም” ያላቸው ስለዚኹ ነው /አሞ.፭፡፳፩-፳፫/፡፡ መፍትሔውም እግዚአብሔርን መፈለግ ብቻ መኾኑን ተናግሯል /አሞ.፭፡፬-፱/፡፡ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ መልካሙን እንዲፈልጉ፣ ይኽን ቢያደርጉም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር እንደሚኾን ተናግሯል /አሞ.፭፡፲፬-፲፭/፡፡ 
ትንቢተ አሞጽ
 ከኋለኛው ዘመን ነቢያት የተናገረውን ትንቢት በመጻፍ የመዠመሪያው ነው፡፡ የአሞጽ ትንቢተ በአብዛኛው በእስራኤልና በአከባቢው ባሉ አገሮች ላይ የሚመጣውን ፍርድ ማስታወቅ ነው፡፡ ፵፩ ጊዜ “እግዚአብሔር እንዲኽ ይላል” እያለ መናገሩም ይኽንኑ ያስረዳል፡፡ የሚዠምረውም በአሕዛብ ላይ ማለትም በቂር፣ በኤዶም፣ በደማስቆ፣ በሶርያ፣ በቴማን፣ በጢሮስ፣ በሞዓብ ሊመጣ ያለውን ፍርድ በማስታወቅ ነው /አሞ.፩ ሙሉውን ያንብቡ/፡፡ ቀጥሎም በይሁዳና በእስራኤል ሊመጣ ያለውን ፍርድ ይናገራል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከላይ ለመግለጥ እንደሞከርነው የሕዝቡ በግዴለሽነት መኖር ያመጣው መዘዝ ነው፡፡
 ነቢዩ አሞጽ ክብር ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለበት ጊዜ ስለሚኾነው ተአምር ናግሯል፡፡ ሕዝብና አሕዛብ በክርስቶስ አንድ እንደሚኾኑ መናገሩም ቅዱሳን ሐዋርያት ጠቅሰዉታል /፱፡፲፩-፲፪፣ ሐዋ.፲፭፡፲፭-፲፰/፡፡ በአጠቃላይ መጽሐፉን እንደሚከተለው መክፈል እንችላለን፡-
1.     ፍርድ በእስራኤል ጐረቤት አገሮች /፩:፩-፪፡፭/፤
2.    ፍርድ በእስራኤልና በይሁዳ ላይ /፪፡፮-፫፡፮/፤
3.    ፍርድ በእስራኤል በደል ምክንያት /፫፡፩-፮፡፲፬/፤
4.    ፍርድ በአምስት ዓይነት መንገድ /፯፡፩-፱፡፲/፤ በዚኽም መካከል የአሜስያስና የአሞጽ ታሪክ /፯፡፲-፲፯/፤
5.    በፍጻሜው ዘመን ስላለው የእስራኤል ተስፋ /፱፡፲፩-ፍጻሜ/፡፡
የነቢዩ አሞጽ የመጨረሻው ዕረፍት
 ስለ ነቢዩ አሞጽ የመጨረሻው ዕረፍት መረጃ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ግንቦት ፳፩ ላይ የሚነበበው ስንክሳርም ነቢዩ በዚያ ዕለት እንደሚታሰብ ከመናገር ውጪ ያለው ነገር የለም፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount