Tuesday, April 8, 2014

ሆሳዕና ዘሰንበተ ክርስቲያን



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 4 ቀን 2006 ዓ.ም)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

 በዋዜማው ማለትም ቅዳሜ ማታ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ለማኅሌት ደውል ከተደወለ በኋላ ይገባሉ:: ከቅዱስ ያሬድ መጽሐፍትና ከሌሎችም በመላእክት ዜማ ዕለቱን የሚያነሳ ቀለም (ትምህርት) እያነሱ ያድራሉ:: ከዚህ በኋላ ጠዋት ለቅዳሴ ሰዓቱ ሲደርስ ሊቃውንቱተበሀሉ ሕዝብ በበይናቲሆሙ እንዘ ይብሉ ዓይ ውእቱ ዝንቱ ንጉሠ ስብሐት እስመ ውእቱ እግዚአ ለሰንበት ቦአ ሃገረ ኢየሩሳሌም በፍስሐ ወበሰላም- ሕዝቡም እርስ በእርሳቸው ተባባሉ እንዲህ እያሉ ይህ የምሥጋና ንጉሥ ማነው? እርሱ የሰንበት ጌታ ነውና፤ በደስታና በሰላም ወደ ኢየሩሳሌም ሃገር ገባ::” የሚለውን የዕለቱን የጾመ ድጓ ክፍል ይቃኛሉ::


 ከዚህ በኋላ አንድ የሚመራ መሪጌታ፡-ቦአ ኢየሱስ ኢየሩሳሌም በስብሐት በዕለተ ሰንበት ወበልዋ ለወለተ ጽዮን ነዋ ንጉሥ በጽሐ ዘእሴቱ ምሥሌሁ ወምግባሩ ቅድመ ገፁ ዘየሃፅብ በወይን ልብሶ የዓሥር ዲበ ዘይት ዕዋለ አድጉ- በሰንበት ዕለት ኢየሱስ በምሥጋና ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፤ ለጽዮን በሏት ሥራውና ዋጋው በፊቱ የሆነ እነሆ ንጉሥሽ መጣ (ደረሰ) በወይን ልብሱን የሚያጥብ የአህያውን ውርንጭላ በወይራ ዛፍ ላይ ያስራል::” የሚለውን ቀለም ቤተ መቅደስ በር ላይ ሆኖ ይመራል:: ሊቃውንቱም ይቀበሉታልወበልዋብለው እስከመጨረሻው ይዘልቁታል:: የሌሊቱ መዝሙር በመሪጌቶች በሊቃውንት ይደርሳል::

 ከዚህ በኋላ ዘንባባ ተዘጋጅቶ በንጹሕ ጨርቅ በመልካም ልብስ ተሸፍኖ ቅዳሴ ይደርስበታል:: ይህንንም በታቦት ፊት ጸሎት የተደረገበትን ዘንባባ ከአባቶች ከቅዳሴ በኋላ ለበረከት እና ያቺን ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም የገባባትን ቀን ለማሰብ ተቀብለን እንወስዳለን:: የቅዳሴው ሥርዓት ከተለመደው የቅዳሴ ሥርዓት አገባቡ ላይ ለየት ይላል:: ካሕናት እንደ ወትሮው ከቤተልሔም ወጥተው ወደ ቤተመቅደስ ወደ ሰሜን በር ሳይሆን ወደ ምዕራብ በር ያመራሉ፤ ከዚያም ዲያቆኑአርኅዉ ኆኃተ መኳንንት-መኳንንት ደጆችን ክፈቱ::” እያለ ከቤተመቅደሱ ውጪ ያዜማል:: ቄሱም ከውስጥ ሆኖ ይመልሳል፤ “መኑ ውእቱ ዝንቱ ንጉሠ ስብሐት- የምሥጋና ጌታ እርሱ ማነው?” ይህንን ሁለቴ ከተመላለሱ በኋላ ዲያቆኑ ለካሕኑ በዜማ በመቀጠል መልስ ይሰጣል፡-እግዚአብሔር አምላከ ኃያላን ውእቱ ዝንቱ ንጉሠ ስብሐትይህ የምሥጋና ንጉሥ የኃያላን አምላክ እግዚአብሔር ነው::” ካሕኑም መልካም በሆነ ዜማ፡-ይባእ ንጉሠ ስብሐት ይባእ አምላከ ምሕረት- የምሥጋና ንጉሥ ይግባ የምሕረት ንጉሥ ይግባ::” ብሎ ሲጨርስ ዲያቆናቱ ወደ ውስጥ ዘልቀው ቅዳሴ ሥርዓቱ ይቀጥላል::

 ሥርዓተ ቅዳሴው ከተጠናቀቀ በኋላ የሚቀጥለው ሥርዓት ዑደት ነው:: ንፍቅ (ረዳት) ዲያቆን ጥላ ይዞ ንፍቅ ቄስ ደግሞ ዘንባባ፡ ሰራዒ (ቀዳሽ) ቄስ መስቀልና ማዕጠንት ሰራዒ ዲያቆን ወንጌል ይዞ ወደ ቅድስት ይወጣሉ፤ በዚያም ሆነው (መዝ፡ 1176) “ቡሩክ ዘይመጽዕ በስመ እግዚአብሔር ባረክናክሙ እም ቤተእግዚአብሔር እግዚአብሔር እግዚእ አስተርዓየ ለነ- በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ በእግዚአብሔር ቤት መረቅናችሁ፤ እግዚአብሔር ጌታ ለእኛ ገለጠልን (አሳየን)::” የሚለውን ምስባክ ዲያቆኑ ይሰብካል፤ ቄሱ በማስከተል ማቴ፡ 2029-. እንዲሁም ሦስቱ ወንጌላት ከራሳቸው ምስባክ ጋር ይሰበካሉ፤ ይነበባሉ::

 ከዚህ በኋላ የቅዱስ ያሬድ የሆሳዕና ጾመ ድጓ ክፍል፡-አርእዩነ ፍኖቶ ወንኁር ቤቶ እስመ እም ጽዮን ይወጽእ ሕግ ወቃለ እግዚአብሔር እም ኢየሩሳሌም ንሳለማ ለመድኃኒትነ በትፍስሕት ተቀበልዋ ለታቦት እስመ ዋካ ይእቲ ወብርሃን- መንገዱን አሳዩን፤ ወደ ቤቱ እንሂድ:: ከጽዮን ሕግ ከኢየሩሳሌምም ቃለ እግዚአብሔር (ወልድ) ይወጣልና፡፡ መድኃኒታችንን እንሳለማት፤ እርሷ ብርሃን ናትና ታቦትን በደስታ ተቀበሏት::” የሚለውን በመመራት ካሉት በኋላ ተቀብለው ሊቃውንቱ ያዜሙታል::

 በዚህ ጊዜ በስልጣን ከፍ የሚል ጳጳስ፣ ኤጲስ ቆጶስ ወይም ቄስ ዘንባባውን ባርኮእንበለ ደዌ ወሕማም” እያለ እንደየአቅማቸው ለሚያገለግሉ ካሕናት ያድላል:: ሕዝቡምእስመ ዋካ ይእቲ ወብርሃን ዋካ ይእቲ ወብርሃንይህች ብርሃን ናትና ይህች ብርሃን ናት::” እያሉ ከቤተመቅደስ ወጥተው ቤተክርስቲያኗን መዞር ይጀምራሉ:: ይህንንም እያዜሙ ወደ ምዕራብ በመሄድ ይቆማሉ፤ በዚያም ዲያቆኑ(መዝ፡ 803) “ንፍሑ ቀርነ በዕለተ ሠርቅ በእምርት ዕለት በዓልነ እስመ ሥርዓቱ ለእስራኤል ውእቱ- በመባቻ ቀን በከፍተኛው በዓላችን ቀን መለከት ንፉ፤ ለእስራኤል ሥርዓቱ ነውና፡፡ብሎ ይሰብካል፤ ቄሱም ማቴ፡ 211 ያነባል፡፡  በመቀጠል መሪው፡-ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሃሌ ሉያ ሰመያ አብርሃም ወይቤላ ዛቲ ዕለት በዓለ እግዚአብሔር ንፍሑ ቀርነ በዕለተ ሠርቅ በእምርት ዕለት በዓልነ ሶበ ተዘከርናሃ ለጽዮን - ሃሌ ሉያ አብርሃም ይህችን ዕለት የእግዚአብሔር በዓል ቀን ብሎ ሰየማት፡፡ ጽዮንን ባሰብናት ጊዜ በከፍተኛው በዓላችን ቀን መለከትን ንፉ፡፡ሕዝቡምሶበ ተዘከርናሃ ለጽዮን…. ጽዮንን ባሰብናት ጊዜ ጽዮንን ባሰብናት ጊዜእያሉ እያዜሙ ዑደቱ (ዙረቱ) ወደ ደቡብ በር ወይም ሴቶች በር ይሆናል፡፡

 እዚያ ከደረሱ በኋላ ዲያቆኑ መዝ 82 “እምአፈ ደቂቅ ወሕፃናት አስተዳሎከ ስብሐተ በእንተ ጸላዒ ከመ ትንሥቶ ለጸላዒ ወለገፋዒ,,,, ከሕፃናትና ከሚጠቡ አንደበት ምሥጋናን አዘጋጀህ ስለ ጠላትህ፡ ጠላትንና ቂመኛን ታጠፋ ዘንድብሎ ይሰብካል፡፡ ቄሱም ቀጥሎ ማር 111 ያነባል፡፡ ከጾመ ድጓወትቤ ጽዮን አርኅዉ ሊተ አናቅጸ ይባኡ ሕዝብ ብዙሐን ወያእትቱ እብነ እምፍኖት ለንጉሥ ለወልደ ዳዊት ንጉሦሙ ለእስራኤል ውእቱ ይብሉ ሆሳዕና በአርያም---- ጽዮንም አለች ሆሳዕና በአርያም እያሉ ብዙ ሕዝብ ይገቡ ዘንድ በሮችን ክፈቱ፤ ለዳዊት ልጅ ለንጉሥ ድንጋዮችን ከመንገድ ያስወግዱ፤ የእስራኤል ንጉሣቸው ነው፡፡ሕዝቡም ወደ ምስራቅ ካሕናት በር እየሄዱይብሉ ሆሳዕና በአርያምሆሳዕና በአርያም ይበሉእያሉ ያዜማሉ፡፡

 በምስራቅ በርም (መዝ፡ 491) “እምስራቀ ፀሐይ እስከነ ዐረብ ወእምጽዮን ስነ ስብሐቲሁ እግዚአብሔርሰ ገሃደ ይመጽዕ,,,, ከፀሐይ መውጪያ እስከ መግቢያው ድረስ የእግዚአብሔር ስም ይመስገን፤ ከጽዮን ከምሥጋናው ውበት እግዚአብሔርስ በገሃድ ይመጣል፡፡ብሎ ከሰበከ በኋላ ቄሱ ሉቃ፡ 1928 ያነባል፡፡ ከጾመ ድጓባረኮ ያዕቆብ ለይሁዳ ወልዱ ወይቤሎ ሃሎ ንጉሥ ዘይወጽእ እምኔከ ዘየሐጽብ በወይን ልብሶ ወበደመ አስካል ሰንዱኖ ንጉሦሙ ለእስራኤል ውእቱ ይብሉ ሆሳዕና በአርያም- ያዕቆብ ልጁ ይሁዳን እንዲህ ሲል መረቀው ንጉሥ ከአንተ ዘንድ የሚወጣ አለ፡፡ በወይን ልብሱን የሚያጥብ፤ ቀሚሱን በወይን ፍሬ ደም የእስራኤል ንጉሣቸው ነው፤ ሆሳዕና በአርያም ይበሉ፡፡ከተባለ በኋላ ሕዝቡ እንደ ቀድሞው እያሉ ወደ ሰሜን በር ይሄዳሉ፡፡

 በዚያም መዝ፡ 1471 “ትሴብሖ ኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ወሰብሒዮ ለአምላክኪ ጽዮን እስመ አጽንዓ መናስግተ ኆኀትኪ- ኢየሩሳሌም እግዚአብሔርን ታመሰግናለች ጽዮን ለአምላክሽ አመስግኚ የበሮችሽን መዝጊያ አጽንቷልና፡፡የሚለውን ቃል ዲያቆኑ ከሰበከ በኋላ ቄሱ ዮሐ፡ 1212 ያነባል፡፡ ጾመ ድጓሃሌ ሉያባኡ ውስተ ሃገር ወበዊአክሙ ትረክቡ ዕዋለ አድግ እሱረ ፍትሕዎ ወአምጽእዎ ሊተ- ወደ ሃገር ሂዱ (ግቡ)፤ በዚያም በገባችሁ ጊዜ የአህያ ውርንጭላ ታስሮ ታገኛላችሁ ፈታችሁ አምጡልኝእያሉ ሊቃውንቱ ያዜማሉ፡፡

 ከዚያም ወደ ምዕራብ ተመልሰው፡-ሃሌታአልጺቆ ኢየሱስ ኢየሩሳሌም ርእያ ለሃገር ወይቤላ ሶበ ተአምሪ ጽዮን ነዋ ንጉሥኪ በጽሐ ብርሃንኪ ዮም ሰላምኪ ተፈስሒ በሕዝብኪ ዮም ሰላምኪ ይተኃፈሩ ጸላእትኪ ዮም ሰላምኪ ሰላምኪ ሰላምኪ ዮም ሰላምኪ- ኢየሩሳሌም ደርሶ ሃገሯን ተመለከታት፤ እንዲህም አላት፡- ብታውቂ ጽዮን ሆይ ንጉሥሽ መጥቷል፤ ሰላምሽ ዛሬ ነው፤ በሕዝብሽ ደስ ይበልሽ ሰላምሽ ዛሬ ነው፤ ጠላቶችሽ ይፈሩ ሰላምሽ ዛሬ ነው፤ ሰላምሽ ሰላምሽ ዛሬ ነው፡፡

 እንግዲህ ይህ ዑደተ ቤተክርስቲያን ጌታችን 2000 አመታት በፊት ያደረገው ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱንም ቤተመቅደስንም መዞሩን ከታላቅ ምሥጋና ጋር የሚያስታውሰን ታላቅ የቤተክርስቲያን ሥርዓት ነው፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድም ከሰማያዊ ዜማ ጋር ይህንን ሥርዓት ከሞላ ጎደል መዝግቦልናል፤ ስለዚህ የደስታችንን ቀን እያሰብን ይህንን ሥርዓት በልበ ሙሉነት ልንሳተፍ ይገባል፡፡ ከዚህ በኋላ መጪው ሰሙነ ሕማማት ነው፤ ስለሆነም ዑደቱ ካለቀ በኋላ ዘንባባ ታድሎ ፍትሐት ይደረግና ሕዝቡ ይሰናበታል፡፡ ሰላሙን ይስጠን፡፡

1 comment:

  1. እጅግ ደስ ያሰኛል ስርዓቱ ሁሉ። አምላክ ይቀበለን

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount