Thursday, April 3, 2014

ገብር ኄር ዘሐሙስ



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 25 ቀን 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

 በማይለወጥ ሦስት፣ በማየረክስ ንጹሕ፣ በማያንቀላፋ ትጉህ፣ በማይደክም ብርቱ በሆነ በእግዚአብሔር ስም የመላክ ፍለጋ በሌለበት የነፋስን ፍጥነት በሚለካው በፍጥነቱም እንደጢስ ትንታ ጉምን በሚበትነው ለሥጋ ለባሽ ሁሉ ነፍስ ላላቸውም ሁሉ አምላክ በሆነ በአንድ እግዚአብሔር ስም ሰላም ለእናንተ ይሁን:: (መጽሐፈ ምሥጢር)


  ሰክየት ምድር ወትቤ ፈጣሪሃ እንዘ ትብልምድር ወደ ፈጣሪዋ እንዲህ ስትል ከሰሰች፡- አሕዛብ ቅዱስ ስምህን አረከሱ፤ ወደ አባቱ ማደሪያ ልጅ ይወጣል፡፡ ጌታም እንዲህ ሲል መለሰላት: ዐይኔ ያያቸዋል ጆሮዬም ይሰማቸዋል፤ ቢመለሱ ንስሐም ቢገቡ ይድናሉ፤ ባይሆን ግን ይሞታሉ፤ ወደ እኔ ይመጣሉ እኔም እፈርድባቸዋለሁ፤ ምድር እንዲህ ብላ ከሰሰች፡ ለስሙ ዘምሩ አመስግኑም::” የኃጢአታችንን ልሕቀት እንድንመለከት በጠዋት ስንነሳም የደከመውን ሥጋችንን ተሸክመን እንዳንደክም እንጠነቀቅ ዘንድ ቅዱስ ያሬድ የምድርን ክስ ያሰማናል:: ጌታም ተመለሱ እንዳትሞቱ ንስሐን አፍቅሩ ይለናል:: ከዚህ በኋላ የልመና የስግደት የኃጢአት ስርየት የሆነችውን የምታበራውን ነፃ የምታወጣውን ቅድስት ጽዮን ቤተክርስቲያንን እዩአት፤ አመስግኗት፤ ተሳለሟት፤ ወደ እርሷ የመጣ ሁሉ በነፍስ ብርታትን ያገኛል አይደክምም ይለናል:: ምክንያቱም በሰው ሃሳብ አልተሰራችም፤ ልዑል አንተ ልታድርባት መሠረትካት እንጂ ይለናል:: ፀሐይሽ አይጠልቅም፤ ጨረቃሽም አይጨልምም፤ የሚመጣውን ደስታሽን በእኔ ተመልከቺ ይላታል የእስራኤል ቅዱስ:: ጌታዋ በመስቀል የዋለላትን አትረሳም::

 ምርጉዞሙ ለሐንካሳን ልብሰ ለዕሩቃንመስቀል ለአንካሶች ምርኩዝ ለተራቆቱት ልብስ ነው፤ ያዘኑትን ያፅናናል:: በእኔ የሚያምነውን ሁሉ ኃጢአቱን ይቅር እለዋለሁ ይላል፡፡ በንጹሕ ልብ ጹሙ፤ ጸልዩም፤ ቤተክርስቲያንንም ተመርኮዟት::” እርሱ ብቻውን ጨልሞ እንዳይቀር ብርሃንን በጊዜው የሚያወጣ ነው:: በብርሃኑ እንመላለስ፤ ብርሃኑንም በጠዋት ስናይ ወደ ቤተክርስቲያን እንገስግስ፤ ነቢዩ እንዳለው በንጋት ጸሎቴ ወደ አንተ ትድረስ እንበል::

 ውስተ ሃገሩ ለንጉሥ ናፅንዕ ገይሠ ኀቤሃ ዘጌሠ ፈድፋደ ይረክብ ሞገሠየንጉሥ ሃገር ውስጥ መሄድን እናጽና፤ ወደ እርሷ የሄደ አብዝቶ መፈራትን ያገኛልና::” በውጪም መስቀል ይላል ዜመኛው፤ በውጪም መስቀል በውስጥም መስቀል በበረሃም መስቀል በሁሉም ቦታ መስቀል ጨለማን ያበራል::

 ኢይተዓፀው አናቅጽኪ ክቡራትመልካምና ሠላማዊት የከበሩ ደጆችሽ አይዘጉ፡፡ በእውነት የምንወዳት ነን፤ የአፏም መዓዛ እንደ እንኮይ ነው::”

 ከዚህ በኋላ ወደ ምክር ቃል ይመጣል ያዜምልናል፤ ነፍሳችንን ከፍ ከፍ አድርገን እንስማው:: “አኃውየ ምንተ ይበቊዓነ ፀሊዖቱ ለሰብእወንድሞቼ ሰውን መጥላት ምን ይጠቅመናል? ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ወንድሙን የሚወድ እርሱ በሕይወት ይኖራል፤ ሞትንም አያያትም::” አርአያ ይሆነን ዘንድ ስለፍቅር ጾመ፤ አርአያውን ይዘን በፍቅር እንጹም እንፋቀር::

 በጾም ወበጸሎት ፍትወተ ሥጋ አጽምሙ ሰብአ ቤቱ ለክርስቶስ አንትሙየክርስቶስ ቤተሠቦች እናንተ በጾምና በጸሎት የሥጋ ምኞት ጸጥ አለች::”

 አኃውየ ተፋቀሩ በምልዓ ልብክሙወንድሞቼ በምሉዕ ልባችሁ ተፋቀሩ፤ መፋቀር ሁሉን ይሸፍናልና በሃይማኖት የጸናችሁ ሁኑ፤ እንደ ሰላም ወንዝ ጾምና ጸሎት ታላቅ ጥቅም አላቸው::” ስለዚህ በጾማችሁ ሁሉ ፍቅር ከእናንተ አይለይ፤ ዘምሩ፤ ስለፍቅር ዘምሩ፤ ስለ ጸሎት ዘምሩ፤ ስለ ጾም ከሁሉ በላይ ግን አዎን ፍቅርን ካባ አድርጉ::

 ዘኢትፈቅድ ለኃጥእ ሞተ ለንስሐ ጽንሕኒ ንስቲተየኃጥኡን ሞት የማትወድ ለንስሐ ጥቂት ጊዜን ጠብቀኝ::” ጾመኛ ሰው ልምድ ሳይሆን ልብ ያሻዋል፤ ከእርሱ ጋር ደግሞ ፍቅርን በቀን፣ ጠዋትና ማታ ሳይሆን በየሰዓቱ ይውሰድ ይላል ዜመኛው::

 በመጨረሻምይጹም ዐይን ይጹም ልሣንዐይን ይጹም፤ አንደበትም ይጹም፡፡ ዝምታ ሃይማኖትን ትጠብቃለች:: በዚህ አስተራራቂ (የሰላም ሰዎች) ትሆናላችሁ::” ሰላሙን ይስጠን::

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount