Wednesday, April 16, 2014

"ዘበተከ እምኔነ ኩሎ ማእሰረ ኃጣውዒነ በህማማቲከ ማኅየዊት ወመድኃኒት"


በክፍለ ሥላሴ
 (መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 8 ቀን፣ 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን


የኃይሉ ጥበብና ችሎታው ከፍጡራን ኅሊና በላይ የሆነ የቅዱሳን አምላክ ፈጣሪያችን ሰውን በፈቀደለት መንገድ እንዲመራና መንግስቱን እንዲወርስ የቅዱሳን እጆቹ የግብር ውጤት አድርጎ አበጀው:: ግና ህግን አፍርሶ በፈጣሪው ተከሶ እግዚአብሔር = አባቱን : ልጅነት= ሀብቱን : ገነት= ርስቱን..... ያጣው የሰው ልጅ መርገምን ወርሶ ቁርበት ለብሶ ወደ ምድር ተሰደደ:: በዚህ በሥጋ ከተፈረደበት የመቃብር ግዞቱ ላይ በሲኦል የነፍስ ርደት ስላገኘው የሞት ሞትን ሞተ እንላለን:: ቅዱስ ዳዊትም "ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ።" (መዝ.48:12) ያለው የቀድሞ ክብሩን ከኋላ ግብሩ ጋር እያጻጸረ ሲያመለክተን ነው:: ይህንን የነቢዩን ቃል አብራርቶ የሚያስረዳ መልዕእክት በቅዳሴ አትናቴዎስ ላይ እናገኛለን እንዲህ ይላል ሊቁ "ሰብሰ እንዘ ንጉሥ ውእቱ ኢያእመረ" ዳዊት ክቡር ያለው የክብሩ መገለጫ ንግሥናው ነው ግን ያንን ያላወቀው የሰው ልጅ ምን እንዳገኘው ተመልከቱ "አህሰረ ርእሶ በፈቃዱ ወኮነ ገብረ ወመለክዎ እለ ኢኮኑ አጋእዝተ" አዎ ራሱን በፈቃዱ አሰረ ባርያ ሆነ መግዛት መፍጠርና ማስተዳደር ለባህሪያቸው የማይስማማቸውን የሚያመልክ ሆነ:: ከዚህ ጊዜ አንስቶ ለአምስት ሺህ ከአምስት መቶ ዓመታት የቀድሞ ጠላት ዲያቢሎስ ሰውን አስሮ "በግብርናት" የሚገዛው ሆነ::


በኋላኛው ዘመን ሰው ይሆን ዘንድ የወደደ ወልደ አምላክም ለዚህ በደል ካሳ እንዲሆን በለበሰው ሥጋ (በተዋህዶ) ረቂቅ መለኮት ታሠረ :: የእርሱ መታሠር ስለ ሁለት ነገር ነው

፩•. "ተአስረ በእንቲአነ ከመ ይፍትሐነ እምማእሰረ ኃጢዓት" እንዲል እኛን ከታሰርንበት የኃጢዓት ማሰርያ ይፈታን ዘንድ ስለ እኛ ታሰረ .... ግብሩ ከፍቶ ከቤቱ ጠፍቶ የነበረውን ሰው ወደ ቀደመ ክብሩ ሊመልሰው "የታሰሩትን ይፈታል የወደቁትንያነሳል" የተባለለት እርሱ ስለ እኛ ታሰረ (መዝ 145:7) በሥጋው ወደ ወህኒ የተጨመረ ወንበዴ በርባንን የመሰለውና በከፋው የነፍስ ግዞት ወደ ሲዖል የተጋዘውን የዳምን ልጅ እንዲፈታ ክርስቶስን "አስረው ወሰዱት" (ማቴ 27:2) .....ወመለክዎ እለ ኢኮኑ አጋእዝተ የተባለለትን የሰውን ልጅ "የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ቀንበርህን ከአንገትህ እሰብራለሁ እሥራትህንም እበጥሳለሁ ከእንግዲህ ወዲህ ለሌላ አትገዛም" ብሎ (ኤር.30:8, ናሆ.1:13) እኛም በነግህ የኪዳን ምሥጋናችን እንዲህ እያልን ዕለት ዕለት እንመሰክራልን "ወኩሎሙ ነፍሳተ ጻድቃን ብከ ይጼወኑ ....ወለ እለ በመዋቅሕት ጽኑዓን ዘምስሌሆሙ ትሄሉ ዘእማእሰረ ሞት ፈትሐነ= የጻድቃን ነፍሳት ባንተ ጸንተው ይኖራሉ ... በጽኑ እስራት ካሉት ጋር አብረሀቸው የምትኖር ከሞት ሞት ማሰርያ የፈታኸን " ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስም ይህ ተስፋ መፈጸሙን እንዲህ ሲል አስረዳን " ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፥በእርሱም ደግሞ ሄዶ በወኅኒ ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤" (1ኛ.ጴጥ.3:18) ቀድሞ "አዳም ገብሩ ወሔዋን አመቱ ለዲያቢሎስ" የተባልንበትን የግብርናት ስም ሽሮ ወደራሱ አቀረበን ከዚህ በኋላ "አግብርተ ሥላሴ ወሉደ ማርያም = የቅድስት ሥላሴ አገልጋዮች የድንግል ማርያም ልጆች" ተብለን እንድንጠራ በአርባ በሰማንያ ቀናችን ዳግመኛ ተወለድን:: ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ይህን የዲያቢሎስ አገዛዝ አጥብቆ ሲቃወምና በዘመነ ሐዲስ ስላለው ተስፋ ሲመሰክር "እግዚኦ አነ ገብርከ ገብርከ ወልደ አመትከ...አቤቱ፥ እኔ ባሪያህ ነኝ፥ ባሪያህ ነኝ፥ የሴት ባሪያህም ልጅ ነኝ ሰንሰለቴን ሰበርህ።" (መዝ 115:16) ይህችውም "ሴት ባርያ" የዲያቢሎስ ጽኑ መከራ ያላገኛት ብላቴናይቱ ድንግል ናት "የባርያይቱን ትህትና ተመልክቷልና" ያለች ስለራስዋም ለቅዱስ መልአክ ትውልድ ሁሉ የሚያመሰግኗት ያቺ ባርያ (የሴት አገልጋዩ) እኔ ነኝ ስትል "ነየ አመቱ ለእግዚአ ኩሉ" ብላ የመሰከረች ናትና (ሉቃ 1:38, 1:48) እንግዲህ ለአዲስ ኪዳን ትውልድ ተጠግተው የሚጠለሉባት መርሶ (ወደብ) ከግዞት የሚያመልጡባት አንባ ይህችው ድንግልናት:: ልጆቿም በነጻነት እንዲኖሩ ከግዞት የወጡ እስራታቸውን ከአንገታቸው የፈቱ ይልቁንም በእምነት ማዕተብ ከፍቅር ምሰሶ ላይ ራሳቸውን ያስገዙ ናቸው "የጽዮን ልጅ ሆይ የአንገትሽን እሥራት ፍቺ" እንዲል (ኢሳ.52:2)



፪•"አሰሮ ለሰይጣን አግአዞ ለአዳም" እንዲል መታሰሩ አሳሪውን ሊያስር ነው በወንጌል " ... ሰው አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ እቃውን ሊነጥቀው እንዴት ይችላል? ከዚያም ወዲያ ቤቱን ይበዘብዛል።" እንዳለ (ማቴ.12:29) በነፋስ አውታር በእሳትም ዣንዠር አስሮ ሳቀየው ይሁዳም በመልዕክቱ "በዘለዓለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ ጠብቋቸዋል" እንዲል(ይሁ.ቁ 6) ዛሬም የእውነት ወገኖቹ የምንሆን ክርስቲያኖች ነጠላችንን አጣፍተን በፊቱ ስንመላለስ የምንመሰክረውም ይህንኑ ነው:: የቀኝ እጃችን የነጻነት ምሳሌን እንዲያጠይቅ የተፈታ(የተለቀቀ) ሆኖ ግራው ግን በተጣፋው ነጠላ ውስጥ የአሳች ዲያቢሎስን እሱርነት እንዲያመለክት ሆኖ ይታያል ...."የቀደመውንም እባብ ዘንዶውን እርሱም ዲያብሎስና ሰይጣን የተባለውን ያዘው፥ሺህ ዓመትም አሰረው"(ራእ. 20:3)



ምንም እንንኳ የቀደመው ሰው በደሉን እየተዘከረ በንስሐ የቀረበ ተማጽኖውን አምላክ ተመልክቶ በሞቶ ሞቱን ሊያጠፋ በሥጋ ማርያም ተገልጾ መከራን ተቀበሎ ወደ ቀደሞ ክብሩ ቢመልሰው በምድር ያለውን የሰው ዘር ሁሉ ግን ከሥጋ ድካሙ እንዲያርፍባት ከኃጢዓት ታቅቦ እስራቱን እንዲፈታባት በተስፋ የማያልፈውንርስት የሰማዩን መንግስት እንዲጠባበቅባት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በደሙ መሠረታት:: ይህችውም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምዕመናን ሁሉ በአት የስዱዳን መጠጊያ የነዳያን መጠለያ የችግረኞች መጽናኛ የኃጥዓን መማጠኛ የምሥጢራት ሁሉ መፈጸሚያ የመልካሙ እረኛቸውን ድምጽ ሰምተው ለሚከተሉ የዋኃን በጎች ሁሉ ማረፊያ ናት:: ቅዱሳን ሐዋርያትን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን በጥንቃቄ መንጋውን እንዲመሩ ቤቱን እንዲያስተዳድሩ "አነ እሔሉ ምስሌክሙ እስከ ለዓለም" ብሎ እስከ ዓለም ፍጻሜ ሳይለያቸው ሰጎን እንቁላሏን ነቅታ እንደምትጠብቅ ለቅጽበት ጠብቆቱን ሳያጓድል በነሱ አድሮ ሊኖር ቃሉን አጸና :: በዚህ የኖላዊነት ግብር የተሰጣቸው ሥልጣነ ክኅነቱ ነፍሳትን ሁሉ በራሳቸው መሳት በፈቃዳቸውም ባገኛቸው መተላለፍ የታሰሩ ነፍሳትን ሁሉ ከማእሰረ ኃጢዓት እየፈቱ ለሰማዩ መንግስት እንዲያበቁ የተሰጠ ኃላፊነት ነው: ይህንንም እንዲህ እያሉ ይመሰክራሉ "ዘወሀብከነ ዚአከ ሃይማኖተ ዘኢይትነሰት ወቦቱ ገበርከ ለነ ንማዕ ማዕሰሪሁ ለሞት......ዘወሀብከነ በመንፈስ ንኪድ ኩሎ ኀይሎ ለጸላኢ ከመ ንፍታሕ ዘኢይትፈታሕ" (የሞት ማሰርያ ክህደትን በሃይማኖት ድል እንድንነሳው ያደረግህልን....በመንፈስ የጠላትን ኃይል ሁሉ እንረግጥ ዘንድ የሰጠኸን የማይፈታውን እንፈታ ዘንድ" ይህን ጽኑ ሥልጣን ቀድሞ በምሳሌ ኋላ ደግሞ በግብር ጌታችን ለሐዋርያት ሰጥቷቸዋል:: ይኸውም እርሱ በፍቅሩ የአዳምን ዘር ከውርስ የኃጢዓት ማሰርያ ቢፈታ በዘመነ ሀዲስ በገዛ መተላለፉ በፈቃዱ ራሱን እያሰረ ወደ ኩነኔ የሚጋዘውን ነፍስ ፈተው ነጻ እንዲያወጡ ማርከው ወደ በረቱ እንዲያመጡ አዟቸዋልና
በምሳሌ እንዲሰጣቸው ያለውን ኃላፊነት ሲያመለክት የአራት ቀን ሬሳ አልአዛርን ፈትቼኃለሁ ሳይል "ፍቱትና ይሂድ" አላቸው (ዮሐ. 11:44) ዳግመኛም ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ በደረሰ ጊዜ በክብር ተቀምጦባት ወደ ኢየሩሳሌም ሊገባባት የሻትን(የፈለጋትን) አህያ ከርንጫይቱ ጋር እንዲያመጡ እንዲህ ሲል ነበር ያዘዛቸው "ፍትሕዎሙ ወአምጽእዎሙ ሊተ ወእመቦ ዘይቤለክሙ ምንተ ትገብሩ በሉ እግዚኦሙ ይፈቅዶሙ"(ፍቱና አምጡልኝ ምን ታደርጋላችሁ የሚላችሁ ሰው ቢኖር ጌታቸው ይሻቸዋል በሉ" (ማቴ 21:2, ማር 11:2, ሉቃ 19:30) ይህንንም በፍጻሜው "በምድር የምትፈቱት በሰማይ የተፈታ ይሆናል" ብሎ የከበረውን ስልጣን ከምሳሌ ወደ ግብር አሻግሮታል(ማቴ.18:18)


ካህናት ከምን ይፈቱናል?


እማእሰረ ኃጢዓት ወይም ከኃጢዓት ማሰርያ ይፈቱናል:: ናዝዘውም ሲፈቱን የሚሉት ይኸንኑ ነውና "እማእሰረ ኃጢዓት እግዚአብሔር ይፍታችሁ" ...... ኃጢዓት የሰውን ነፍስ አስሮ ለሥጋ ፈቃድ የሚገብር ከፍኖተ ጽድቅ የሚለይ ገመድ ነው መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞን "ኃጥእን ኃጢዓቱ ታስረዋለች በኃጢዓቱ ገመድ ይታሰራል" እንዲል (ምሳ.5:22) ታዲያ አስተዋይ ከዓለም ማሳት አምልጦ የሥጋውን ፈቃድ ቆርጦ ነፍሱን ሊያስፈታ እግረ ሥጋውን ወደ ካህን (ወደ አበ ንሰሃው) እግረ ልቡናውን ወደ ሰማይ መንግስት እያቻኮለ ከቤተ ክርስቲያን ያርፋል:: በአንጻሩ የንሰሃን ጥሪ ገፍቶ ልቡናው ለሥጋ ፈቃድ ያደላ ደካማ ሰው ግን በኃጢዓቱ ያፌዛል እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ "ሰነፍ በኃጢዓት ያፌዛል"(ምሳ.14:9) እንዲህ ያለው ፌዘኛ ለጊዜው የታየበት እግዚአብሔርን ማጣት በነፍስ መታሰር ይሁን እንጂ በፍጻሜው በጽኑ እስራት ወደ ገሀነም እንዲገባ ለፍርድ የቀረበ ይሆናል "እስራት እንዳይጸናባችሁ አታፊዙ "እንዲል (ኢሳ 28:22):: ለዚህም ነው ቀኖና ተቀብለን ያዘነውን ተነሳህያን ካህኑ በፍትሐት ዘወልድ እንዲህ እያለ የሚናዝዘን(የሚያረጋጋን)"እግዚእ እግዚኦ ኢየሱስ ክርስቶስ ወልድ ዋህድ ቃለ እግዚአብሔር አብ ዘበተከ እምኔነ ኩሎ ማእሰረ ኃጣውዒነ በህማማቲከ ማኅየዊት ወመድኃኒት....አቤቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወልድ ዋህድ የእግዚአብሔር አብ ቃል ማኅየዊት መድኃኒትም በምትሆን ሕማምህ የኃጢዓታችንን ማሰርያ ከእኛ የቆረጥክልን" 



ልብ አድርጉ የጌታ ህማሙ "ራስ ፍልጠት ሆድ ቁርጠት" አይደለም ለእኛ ሕይወትን የሚሰጥ (ማኅየዊ) ነፍስን የሚፈውስ (መድኃኒት) ነው እንጂ እርሱ ሕማማችንን ነስቶ ደዌአችንን ተሸክሞ የሞትን ማሰርያ ከኛ ነፍስ ቆረጣት እርሱ ስለ እኛ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ጦሞ ከገዳም ሲወጣ ተርቦ ያልሳሳባቸው ተፈትኖም ድል ያልተነሳባቸውን አርእስተ ኃጣውእን ያሸነፈው እኛም እንደኒዚህ ባሉ እኩያት ፍትወታት ኃጣውእ ርኩሳት ላይሰልጥነን ለወንጌል መንግስት ባለተስፋዎች እንድንሆን ነው:: ታዲያ እንግዲህጾም-ጸሎታችን : ምጽዋት-ሥግደታችን : በጠቅላልው መልካም ምግባር - በጎ ትሩፋታችን ከኃጢዓት ማሰርያ ነፍሳችንን ካልፈታ ምን እንጠቀም ብለን "በከንቱ" የምንደክም ያለዋጋ የምንጋደል ተመልከቱ በልዑለ ቃል ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ በኩል ፈጣሪያችን ለእኛ ያለውን ተግሳጽ እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፥ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፥ የተገፉትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፥ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን?"(ኢሳ. 58:6)
እንግዲህስ አምላካችን በመረጠልን መንገድ ተመርተን የሥጋችንን ፈቃድ ገዝተን ለነፍሳችን አድልተን ለሰማዩ የነጻነት ዋጋ እንድንበቃ በእደ ገብሩ ካህን ፈጣሪያችን ይባርከን ይፍታንም!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን


No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount