Wednesday, April 30, 2014

መንፈሳዊ ሕይወት ከትንሣኤ እስከ ጰራቅሊጦስ - ክፍል ፪



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ ፳፪ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
 ውድ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች! በክፍል ፩ ትምህርታችን ከትንሣኤ እስከ ጰራቅሊጦስ ባለው እሑድ ለምን ሱባኤ እንደማይገባ፣ ሰይጣን ይኽን ዓላማ እንዴት እንድንስተው እንዳደረገን፣ በመጨረሻም ይኽን የዲያብሎስን ደባ እንደምን ከንቱ ማድረግ ይቻለናል የሚል ጥያቄ አንሥተን ነበር ያቆምነው፡፡ እስኪ ካቆምንበት እንቀጥልና ለዚኽ ይረዳን ዘንድ አንድ ኃይለ ቃልን መነሻ በማድረግ ለመማማር እንሞክር፡፡ እግዚአብሔር ዓይነ ልቡናችንን ያብራልን፡፡ አሜን!!!

 ቃሉ እንዲኽ ይላል፡- “እንግዲኽ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችኁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ፡፡ በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም፡፡ ሞታችኋልና፥ ሕይወታችኁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሯልና፡፡ ሕይወታችኁ የኾነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችኁ” /ቈላ.፫፡፩-፬/፡፡ ከዚኽ ኃይለ ቃል እጅግ በጣም ብዙ ቁም ነገሮችን መረዳት እንችላለን፡፡ ለጊዜው ግን ከርእሳችን ጋር የሚኼዱትን ነጥቦች ብቻ ለማየት እንሞክር፡፡    
1. ሞተናል
  ሐዋርያው ሲናገር “ሞታችኋልና” ይላል፡፡ ክርስቲያን ሕይወቱን የሚዠምረው በሞት ነው፡፡ በጥምቀት ውኃ ሞቶ ሲቀበር ሕይወቱን ይዠምራል፡፡ ኹላችንም በ፵ና በ፹ ቀናችን ዳግም ከውኃና ከመንፈስ ስንወለድ ብጹዕ የሚኾን ጳውሎስ በሮሜ ክታቡ፡- “ወተቀበርነ ምስሌኁ ውስተ ጥምቀት በሞቱ - ከሞቱ ጋር አንድ እንኾን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን” እንዳለ ከክርስቶስ ሞት ተካፋዮች ኾነናል /ሮሜ.፮፡፬/፡፡ ሞቱን በሚመስል ሞት ሞተናል፡፡ ይኽን ሞት ሞተን ስንቀበር አሮጌው ሰውነታችን ላይነሣ ተቀብሯል፤ በምድር ሳይኾን በውኃ ውስጥ፡፡ አሮጌው ሰውነታችን በተፈጥሮ ሕግ ሳይኾን ከተፈጥሮ ሕግ በላይ በኾነው በግብረ መንፈስ ቅዱስ ሞቶ ግብዓተ ምድሩ ተፈጽሟል፡፡ ሞታችን በተፈጥሮ ሕግ ሞቶ ቢኾን ኖሮ ተመልሶ ሊመጣ ይችል ነበር፤ ነገር ግን የሞተው በግብረ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ይኸውም ልክ የአጋንንት ምሳሌ የኾኑት ግብጻውያን በባሕረ ኤርትራ ሰጥመው እንደሞቱት ነው፡፡
  ከዚኽ መቀበር በላይ ደስ የሚያሰኝ ምንም የለም፡፡ በዚኽ መቀበር ፍጥረት ኹሉ በሐሴት ተመልቷል፡፡ መላእክት ሐሴት አድርገዋል፡፡ ደቂቀ አዳም ሐሴት አድርገዋል፡፡ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ደስ ተሰኝቷል፡፡
  ሰው እንዲኽ ሲቀበር የመግነዝ ጨርቅ አያስፈልገውም፤ የሬሳ ሳጥንም አያስፈልገውም፤ እንዲኽ ያለ ሌላ ነገር ምንም አይፈልግም፡፡ የሚያስፈልገው አሚን ብቻ ነው፡፡
  እሳት ሰምን ያቀልጧል፤ ብረትን ግን ያጠነክሯል፡፡ እኛ ስንጠመቅ የኾነውም እንደዚኹ ነው፡፡ አሮጌው ሰውነታችን እንደ ሰም ቀለጠ፤ አዲሱ ሰውነታችን ግን እንደ ብረት ጠነከረ፡፡ አሮጌው ሰውነታችን ከመወገዱ በፊት ከመሬት መሬታውያን ነበርን፤ አዲሱን ሰው ከለበስነው በኋላ ግን ሰማያውያን ኾነናል /፩ኛ ቆሮ.፲፭፡፵፯/፡፡ አስቀድመን እንደ ሰም ነበርን፤ ከመሬት (ከአዳም) መሬታውያንም (አዳማውያን)  ነበርን፡፡ አሮጌው ሰውነታችንን ሳንጥል፥ እሳት ሰምን ከሚያቀልጠው በላይ የኃጢአት እሳት የሚያቃጥለን ነበርን፡፡ ድንጋይ አንድን ሸክላ ከሚያደቅቀው በላይ የኃጢአት ዓይነት ያደቀቀን ነበርን፡፡ አኹን ግን ሐዋርያው እንዳለው “ሞተናል”፡፡ ይኽን በፍጹም መርሳት የለብንም፤ በተለይ በዚኽ ወራት፡፡ ይኽን የምንረሳ ከኾነ መንገዳችንን ስተናል፡፡
  እስኪ አንድ ጥያቄ እናንሣ፡፡ የሞተ ሰው ብዙ ቪላ ቤቶችን ስለመሥራት፣ በብዙ ጌጣ ጌጦች ስለማጌጥ፣ ስለሚለብሰውና ስለሚበላው፣ አብዝቶ ስለ መብላትና ስለመጠጣት፣ ጊዜአዊ ደስታን ስለማግኘት ሊጨነቅ ይችላል ወይ? በፍጹም! እንግዲኽ ሐዋርያው እያለን ያለው፡- “እኛም እንደዚኽ መኾን አለብን፡፡ ከሞትን (ከከበርን) በኋላ ዳግም ለሐሳር (ለኃጢአት) አንነሣ፤ ኃጢአትን ለመሥራት ስንነሣሣ የሞተውና አሮጌው ሰውነታችን ዳግም ሕይወት እንዲዘራ እናደርጓለን፡፡ አንድ ጊዜ ሞተናልና እንደሞትን እስከመጨረሻ መጽናት አለብን” ነው፡፡
ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount